በወይፈኑ መልስ! (በላይነህ አባተ)

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

ዘመን ተቀይሯል! አገርና ሕዝብን የጎመደው ለገሰ ገዥ የሆነ እለት ስምንተኛው ሺ ደርሷል፡፡ እነ እንድርያስ እሸቴ ምሁር፤  እነ ሽመልስ ከማል አቃቤ-ሕግ፤ የድንጋይ ማምረቻ ምሩቅ ካድሬዎች ዳኞች የተባሉ እለት ዘመን ግልብጥብጡ ወጥቷል፡፡ ቤተክስያን መነኩሴ ያስገደለው ገረመድን በፓትርያሪክ ነት እንዲቀጥል የተፈቀደለት ጊዜ ዘመን ተገለባብጧል፡፡ ኤፍሬም ይስሃቅ “ብሔራዊ ሽማግሌ” የተባለ እለት ዘመን ባፈጢሙ ተደፍቷል፡፡ የዋልድባ መነኩሴዎች አማራ ስለሆኑ ከርቸሌ እየተገረፉ እነ “አባ” መላኩ ሆዳቸውን ስላመለኩ ዋሽንግተን ዲሲ እንደ ኮርማ እየደለቡ እንዲኖሩ በተፈቀደ ጊዜ ዘመን  በአፍንጫው ክንችር ብሏል፡፡ እንኳን ሰው ቅጠል ከማይቀጠፍባት ቤተክስትያን እነ ዮሴፍ እሸቱ በጥምቀት ሲቀጠፉ በእነ ዮሴፍ እናት አሥራት ጉማሬ የመሰሉት ጳጳሳት ከገዳዮች በተሽኮረመሙበት ወቅት ዘመን ቅይርይር ብሏል፡፡

አዎን! ዘመን ተቀይሯል፡፡ ዘመን ሲቀየር ብሂልም ይቀየራል፡፡ በዚህም መሰረት “በበሬው መልስ!” የሚለው ያያቶች ብሂል “በወይፈኑ መልስ!” በሚለው ተተክቷል፡፡ በሬ ሙያውን ረስቷል፡፡ በሬ እርሻ ማረሱን ረስቷል፤ ሙጃ እያዬ ገደል መግባቱን ግን ቀጥሏል፡፡ በሬ ሙያ ስለረሳ ቀንበር ከወይፈን ጫንቃ አርፏል፡፡ በሬ ማነቂያ ውስጥ እርስ በርሱ እየተጋፋ ጉልበቱን ሲያቀጥን ግማሽ ክፍለ-ዘመን አሳልፏል፡፡ በሬ እርስ በርሱ ተዋግቶ ተላልቋል፡፡ በሬ አዝምሮ ጪድ ስላልሰበሰበ ወይፈን በርሃብ አድጓል፡፡ በሬ በረቱን መጠበቅ አቅቶት ጅብ ወስዶታል፡፡ በሬ ጠላቱን ለመዋጋት ስለሰነፈ ወይፈን በአህያ ሳይቀር ተደፈሯል፡፡ በሬ ሐላፊነቱን ረስቶ ኖሯል፡፡ ሐላፊነቱን የረሳው ሐፍረተ-ቢሱ በሬ ግን ወይፈንን ሲተችና ሊመክር ሲዳዳ ይስተዋላል፡፡

ከአባቱ ከበሬ ሳይሆን ከመከራው የተማረው ወይፈን ግን “ማንን ማን ይመከራል” በሚል አሻፈረኝ ብሏል፡፡ ማን በወይፈን ይፈርዳል? ሐላፊነቱን ያልተወጣው በሬ እንዴት ወይፈንን ሊመክር ይችላል? ወልዶ ያላሳደገውን ወይፈን የመተቸት መብት በሬ ከየት ያመጣል? በረቱን በጅብ አስነጥቆ ወይፈንን ከርታታ ያደረገው በሬ በምን ህሊና ወይፈንን ሊወቅስ ይችላል? ለሆዳም ቅርጫና ለአህያ እርግጫ አሳልፎ የሰጠውን ወይፈን በሬ እንዴት መምከር ይችላል? ጫጩቶቿን ከጭልፊት ከምትከላከለው ዶሮ አንሶ ጥጆቹንና ወይፈኖቹን በከተማ፣ በገጠር፣ በቤተክርስትያንና በመስጊድ ሲያሳርድ የኖረ በሬ በየትኛው የመንፈስ ልዕልናው ወይፈንን ሊያዝዝ ይችላል? በሬ ጥጃውን አንገት አስደፍቷል! በሬ ጊደርን አስደፍሯል! በሬ ወይፈንን አሸማቋል!

የተሸማቀቀው ወይፈን አባቱን ትቶ በአያቶቹ መጠራቱን ጀምሯል፡፡ ወይፈን የአያቶቹን የእነ ሞግራውን* የጀግንነት ታሪክ መርምሯል፡፡ ወይፈን እንኳን መታረድ ባፉ ማፈኛ እንዳይዞር፤ በጫንቃው ቀንበር እንዳይወድቅ እንደ ሞግራው እምቢኝ ብሏል፡፡ ወይፈን የደፈረውን ሊደፍቅ እንደ ጠላ ጎሽቷል፡፡ ወይፈን የገፋውን ሊያሽቀነጥር እንደ አንበሳ አግስቷል፡፡ ወይፈን አዳኙን ሊያደበይ እንደ አቦ ሰማኔ በተጠንቀቅ ቆሟል፡፡ ወይፈን አፋኙን ሊፋለም እንደ ነብር ደሙ ሞቋል፡፡ ወይፈን አራጁን ሊበቀል እንደ እናት አልቢን ቀንዶቹን ቀስሯል፡፡ ወይፈን ራሱን ሊከላከል እንደ ጥሪኝ** አኮብኩቧል፡፡ ወይፈን ጠላቱን ድባቅ ሊመታ እንደ በላይ ዘለቀ ሸፍቷል!

ሽፍታው ወይፈን ያያቶቹ ባህል ጀግና ፈጣሪ እሴት መሆኑ ገብቶታል፡፡ በዚህም ምክንያት ወይፈን ባህሉን በማደስ ላይ ይገኛል፡፡ ወይፈን ዋሽንት ማንቆርቆሩን ተያይዞታል፡፡ ወይፈን ቀረርቶና ፉከራን ጸሎት አድርጎታል፡፡ ወይፈን “ቡ ..እምቢ ቡቡቡቡቡቡቡ…ብሎ” ሻኛውን እየቦጀረና ቀንዱን እያወናጨፈ ይፎክራል፡፡ ወይፈን በአያቶቹ ወኔ ተጠምቋል! ወይፈን መደፈሩ ቆጪቶታል! ወይፈን ዓይኑን አንጎልጉሏል፡፡ ወይፈን አፍሯል!

ላይመለስ ያፈረው ወይፈን ዘመን መቀየሩን ተረድቷል፡፡ በሬው አባቱ ሳሩን ብቻ በማየቱ እርሱ መጠመዱ፣ መገረፉ፣ መታፈኑ፣ መታረዱ፣ መንከራተቱና መሰደዱ ገብቶታል፡፡ ወይፈን በሬው አባቱ ጀግንነት እንዳላሳየውና እንዳዋረደው ተገንዝቧል፡፡ ይህንን የተገነዘው ወይፈን በጥረቱ ከአያቶቹ ጀግንነት ተምሯል፡፡ ወይፈን እንደ አያቶቹ አርበኛ ሆኗል፡፡ ወይፈን ካህን፣ ሼህ፣ ሽማግሌ፣ ዳኛና ምሁር ሆኗል፡፡ ወይፈን ለግማሽ ክፍለ-ዘመን እየተጋፉና እርስ በርስ እየተዋጉ በሆዳሞች ሲያሳርዱትና በአህያዎች ሲያስረግጡት የኖሩትን በሬዎች “ወግዱ!” ብሏል፡፡ ዛሬ ባለሙያው በሬ ሳይሆን ወይፈን ሆኗል፡፡ ስለዚህ ብሂሉ በበሬው ሳይሆን “በወይፈኑ መልስ!” ሆኗል፡፡ በወይፈኑ መልስ!

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.