“በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ!” ይላል  እግዚአብሔር ( የቅዱስ ሲኖዶስ ሚዲያ ቲም)

የሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ የህዝብ የወቅታዊውን የሀገራችን ጉዳይ ያወጣውን አስመልክቶ ያውጣው መልእክት ከዚህ ኢሜይል ጋር ተያይዟል። የነጻነት ቀን ቀርቧል ትግላችሁ ፍሬ አፍርቷል፤ በርቱ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

“አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ፥ ቁጣው የዘገየ፥ ምሕረቱም የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ።” ኢዩ 2፡12-13

ይድረስ በሃገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ውጭ ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በሙሉ!

ከሁሉ አስቀድሞ  እግዚአብሔር አምላካቸን  በያላችሁበት  ሰላሙን  ፍቅሩንና መረጋጋቱን እንዲያድላችሁ የቤተ ክርስቲያን የዘወትር ጽሎት መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።

የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን

ዛሬ ይልቁንም በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ ሃገራችና በህዝባችን ላይ የሚካሄደው ታሪካዊ የለውጥ ሂደትና የሚታዩት ጉዳዮች በሰዎች አእምሮና ክህሎት የተከሰተ ክስተት የሚመስለው ካለ  የእግዚእብሔርን ተአምራዊ አሰራር ያልተረዳ ወይም ያላስተዋለ ይሆናል ብለን እናስባለን። ምክንያቱም የሰዉ አዋቂዎችና ብልሃተኛ ነን ባዮች  የአንድን ታላቅና ታሪካዊ ሃገር ህዝብ ለሃያ ሰባት ዓመታት በዘርና በጎሳ በመለያየት፣ በማጣላትና፣ በማገዳደል ይልቁንም አንዱን ጎጥ ከፍተኛ ሌላውን ዝቅተኛ በማድረግ የገዥነት ኃይላቸውን በህዝብ መለያየት ላይ መስርተው ሊገዙና በልጅ ልጆቻቸው ሊያስገዙ አቅደውና አምነው ዘመናቸውን ሁሉ ሲደክሙና ሲባዝኑ ነበርና ነው።

ነገር ግን  ሃያላን ነን ባዮቹ ያላወቁት ወይም ሊያውቁ ያልወደዱት እውነት ቢኖር በሰማያዊ የክብር ዙፋኑ ሆኖ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ትላንትም፣ ዛሬና ወደፊትም የሚጠብቃቸው ሃያሉ እግዚእብሔር መሆኑን ነው! ስለሆነም እግዚእብሔር አምላካችን አገር እንመራለንና ብርቱዎች ነን ከሚሉት የዘመኑ ሰዎች ላይ ማስተዋል በጠፋበት በዚህ ዘመን፣  ከልደታቸው ጀምሮ በጎሳ የመለያየትን ክፉ ዘር በተዘራባቸውና አንድነትን ሳይሆን ልዩነትን እንደ ትልቅ ቁምነገር ተደርጎ ሲማሩ ያደጉ ልጆችን አነሳስቶ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የህዝቧ አንድነት ከተቀበረበት በክብር እንዲነሳና ትቢያውን አራግፎ  ዳግም ለዓለም እንዲያበራ የሚያስችል የተስፋ ብርሃን እያሳየን እንደሆነ እናምናለን። ለዚህም ተአምራዊ መነሳት እግዚብሔርን እናመሰግናለን፣ በወጣቶቻችን ላይ አድሮ የተሰራውንም የእግዚአብሔርን ድንቅ ስራ እናደንቃለን።

 

ውድ ወገኖቻችን ኢትዮጵያውያን ሆይ

ዛሬ በጠባቡ እሥር ቤት የሚማቅቁትን ወገኖች በመፍታት የተጀመረ በጎ እርምጃና ተስፋ ሰጭ የድህነት መንገድ መላ ኢትዮጵያን ወደ እሥር ቤት የቀየረውን የጎሳ ፖለቲካንና ጭቆናን መሠረት ያደረገ የአስተዳደር ስልት አስወግዶ በምትኩም ሰብአዊ ነጻነትን መሠረት ባደረገ የሕዝባዊ መንግሥት ሥርዓት መቀየር የሚኖርበት ሲሆን፣ በዚህም አግባብ ይህን ታሪካዊ ሂደት ወደላቀ ደረጃ ከፍ ማድረግ ይገባል የሚል እምነት አለን። ይልቁንም ሀገራችን ኢትዮጵያ የታሠሩት የተፈቱባት ብቻ ሳትሆን ማንም ከእንግዲህ ያለ ህግና ፍትሕ የማይታሠርባት ልትሆን ይገባል።

ይህ ቅዱስ ሃሳብና ተግባር  ያለ  እግዚአብሔር አጋዥነት በሰዎች ዘንድ የማይቻል መሆኑን በተግባር አስተምሮናል። ስለዚህ ነብዩ ኢዩኤል በትንቢቱ አንዳመለከተን ሁሉ በዚህ በታላቁ የአብይ ፆማችን ወቅት እግዚአብሔር አምላካችን ቸርና መሐሪ፥ ቁጣው የዘገየ፥ ምሕረቱም የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ መሆኑን አምነን ለሃገራችንና ለህዝባችን መልካሙን ሁሉ እንዲያደርግልን በፍጹም ልባችን፥ በጾም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እርሱ እንመለስ።

ውድ ወገኖቻችን

ዛሬ “ማዕከላዊ” እየተባለ የሚጠራውን የሰዎች የማሰቃያ ስፍራ ሙዚየም ከማድረግ ባለፈ ዜጎች በሃገራቸው በየትኛው ክፍለ ሃገር  ላይ ቤተሰብ መሥርተውና ሀብት አፍርተው በነጻነትና በሰላም የመኖር ሰብአዊ መብታቸው ዋስትና የሚያገኝበት ህዝባዊ ሥርዓት ለመመሥረት ቅንነትና ቆራጥነት ያሻል። አለበለዚያ ዛሬ የታሠሩትን መፍታቱ ብቻውን ነገ ላለመታሠራቸው ዋስትና አይሆንም፤ ስለዚህ በገዥው ቡድን ለህዝብ የተገባው ቃልና በአደባባይ የታወጀው አዋጅ  ያለምንም ቅደመ ሁኔታ  መተግበር እንዳለበት አናምናለን። ይህንንም በጎ ተግባር ለማድረግ እግዚአብሔር እንዲረዳቸው እንጸልያለን። ገዥው ቡድን ያወጀው  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጀመረው በጎ እርምጃ አፍራሽ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም።

በአጠቃላይ የተጀመረው የአንድነትና የለውጥ ጅምር ሰላማዊና ፍፃሜውም በሁሉ ዘንድ የተወደደ እንዲሆን ሁሉም ህዝባችንው በፍጹም ልብ ወደ እግዚአብሔር ምህረት እጆቹን እንዲያነሳና አንድ ሆነን በጾም፣ በለቅሶና፣ በዋይታ ወደ እርሱ እንድንመለስ በቤተ ክርስቲያን ስም  ጥሪያችንን እናቀርባለን።

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይጠብቅ! አሜን!

አባ ጴጥሮስ የአስውትራልያ ሊቀ ጳጳስ

በሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ሃላፊ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.