“የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ” ወይስ “በችኮላ የወጣ ዓዋጅ”? (ባይሳ ዋቅ-ወያ)

Ethiopia’s Defense Minister Siraj Fegessa.

 ከሁለት ቀናት በፊት “መንግሥታችን” የተለመደውን “የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ” ማወጁን በመከላከያ ሚንስትሩ በኩል አሳወቀን። የለምደነውና የጠበቅነው በመሆኑ በዓዋጁ መውጣት ብዙም ባንደነግጥም፣ ዓዋጁን ለምን ባሁኑ ሰዓት ማወጅ እንዳስፈለገና፣ በተለይም ጠ/ሚኒስትሩ “በሰላማዊ መንገድ ሥልጣንን ማስረከብ እንደሚቻል ሊያስተምረን” ከማሰብ፣ ሥልጣን ለቅቄያለሁ ባለ ማግስት የዓዋጁ መውጣትና፣ ብሎም በመከላከያ ሚኒስትሩ በኩል እንዲለፈፍ መደረጉ ትንሽ አጠያያቂ ሆኖአል። ከሁሉም በላይ ግን፣ ለብዙ ዓመታት አንድም የፖሊቲካ እስረኛ በአገሪቱ እንደሌለ በዓለም ዓቀፉ መድረክ ሲምልና ሲገዝት ያልነበረውን ያህል “የፖሊቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የፖሊቲካ እስረኞችን በሙሉ እፈታቸዋለሁ” ብሎ በተናገረና ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ እፍኝ የማይሞሉትን እስረኞች ከፈታ በኋላ፣ “መንግሥታችን” ይህን የአስቸኳይ ጊዜ ማወጁ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው።

 

የዚህ ጽሁፌ ዓላማ ባገሪቷ እየተከሰተ ያለውን የፖሊቲካ ቀውስ ለመገምገምና “መሆን የለበትን” ለመጠቆም ሳይሆን፣ ዓዋጁ የተደነገገው ህገ መንግሥቱን ተከትሎ አለመሆኑን ለመጠቆምና፣ በዚህም ምክንያት ተፈጻሚነት እንዳይኖረው በተቻለን መጠን ለሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብና ለዓለሙ ማህበረሰብ ለማሳወቅና ብሎም ህጋዊ በሆነ መንገድ ታግለነው በዓዋጁ ምክንያት የዜጎች ህጋዊና የሰው ልጆች መብት እንዳይጣሱ ያለመታከት ድምጻችንን እንድናሰማ ለማለት ነው።

 

አንድ መንግሥት፣ “የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል  ሁኔታ  ሲከሰትና በተለመደው  የህግ  ማስከበር  ሥርዓት  ለመቋቋም  የማይቻል  ሲሆን”  የአስቸኳይ  ጊዜ  አዋጅ  ሊያውጅ  ይችላል።  በህገ መንግሥታችን ውስጥ በአንቀጽ 51/16 እና በአንቀጽ 55/8 የተካተተውም ይህንኑ ያረጋግጣል። “መንግሥታችንም” ያወጀው ”የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ” በመሰረቱ ማንም መንግሥት ሊያደርገው የሚገባው “ግዴታ” ስለሆነ አሳሳቢ ባልሆነ ነበር፣ ግን ዓዋጁ የታወጀበት ሁኔታ አሳሳቢ አርጎታል። እስቲ እንዳስሰው።

 

በመጀመርያ ደረጃ፣ መንግሥት በገባው ቃል መሰረት የፖሊቲካ እሥረኞችን መፍታት ጀምሯል። ገና በጣም ብዙ የሚፈቱም እንዳሉ አሳውቆ ሂደቱ ተስፋን ጭምር በማካተቱ፣ በየቦታው ይከሰቱ የነበሩ ህዝባዊ ዓመጾች ጋብ ማለት ጀምረው ነበር። በመሆኑም እየደፈረሰ የነበረው ሰላም ከሞላ ጎደል የመጥራት ምልክት ማሳየት በጀመረበትና ህዝቡ ገና ለዓመታት ያላያቸውን ብርቅዬ የፖሊቲካ መሪዎቹን በባህሉ መሰረት ጨፍሮ ቀረርቶ አሰምቶ አወድሶ ሳይጠግብ “በቡድን መሰብሰብን” የሚከለክል ዓዋጅ ማውጣት ሆን ተብሎ እነዚህ ተፈቺዎች ከደጋፊዎቻቸው ጋር እንዳይገናኙ የተወጠነ ሴራ ይመስላል።

 

በሁለተኛ ደረጃ፣ አዋጁ የወጣው የህገ መንግሥቱን ቀለምና መንፈስ በመጣስ እንደሆን የሚያመለክቱ ብዙ ክፍሎች አሉት። መሆን የነበረበትና ህገ መንግሥታዊው መንገድ እንደሚከተለው ነው። ያገሪቷ ከፍተኛው  የህግ አስፈጻሚ አካል  ማለትም በጠቅላይ ሚኒስቴር የሚመራው የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የዓዋጁን ያዘጋጅና፣ ላገሪቷ ከፍተኛ የሥልጣን አካል ለሆነው የፌዴራሉ መንግሥት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን “ከዛሬ ጀምሮ ሥልጣን ለቅቄያለሁ” ስላለንና እሱን የሚተካ ደግሞ ማን እንደሆነ ስላልተነገረን፣ ዓዋጁም ራሱ ለህዝብ የቀረበው በመከላከያ ሚኒስትሩ በመሆኑ፣ ብዙ ሰዎች “ይቺ ነገር መፈንቅለ መንግሥት ትመስላለች” ማለታቸው ከእውነት የራቀ አይመስለኝም።

 

ሶሶ፣ በህገ መንግሥቱ መሰረት፣ የሚኒስትሮቹ ምክር ቤት የዓዋጁን ረቂቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም  የህግ አስፈጻሚው  (የሚኒስትሮች ምክር ቤት)  ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ተወያይቶበትና የምክር ቤቱን ሁለተ ሶስተኛ አባላት ድምጽ ድጋፍ ካገኘ በኋላ ይወስናል። እዚህ ላይ ሁለት ግራ የሚያጋቡና ምናልባትም ህገ መንግሥቱን የጣሱ የሚመስሉኝ ሁኔታዎች ይስተዋላሉ። መከላከያ ሚኒስትሩ፣ ዓዋጁ ገና ለወሳኙ አካል ማለትም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሳይላክ “ዓዋጁ ከዛሬ ጀምሮ ሥራ ላይ ይውላል” ማለቱ ህገ መንግሥታዊ አይደለም። ከዚያም በላይ፣ በህጉ መሰረት፣የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የቀረበለትን ዓዋጅ ተወያይቶበት በ48 ሰዓት ውስጥ፣ ሥራ ላይ በሌለበት ጊዜ ደግሞ  በ15  ቀናትውስጥ መወሰን እንዳለበት እየታወቀ፣ ይህን ዓዋጅ ዛሬ የተወካዮቹ ምክር ቤት በሥራ ላይ አለመኖሩ እየታወቀ፣ ለምን ማወጅ አስፈለገ? ይቺ “ከዛሬ ጀምሮ ሥራ ላይ ይውላል” የምትለዋ የአቶ ሲራጅ ንግግርና፣ የተወካዮች ምክር ቤት ሥራ ላይ አለመገኘቱ እየታወቀ ሆን ተብሎ ይህን ዓዋጅ ዛሬ ማወጅ፣ ዓላማው እውነትም አጠጠያያቂ ነው።

 

ለዚህም ነው ከህገ መንግሥቱ ቀለምና መንፈስ አንፃር ከተመለከትነው፣ ይህ ዓዋጅ፣ ያገሪቷን ህልውና የተፈታተነ አደጋን ለማስወገድ የታለመ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” ሳይሆን፣ አንድ የተደበቀና የሆነ ቡድንን የፖሊቲካ ዓላማ ለማራመድ ወይም ለመጥቀም ታስቦ በህዝባችን ላይ የተጫነና በአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ስም የዜጎችን ህጋዊና ሰብዓዊ መብቶችን ለመጣስ የተቀነባበረ “የችኮላ ዓዋጅ” ነው ለማለት የደፈርኩት። ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት፣ ረጋ ብለን ሰላማዊ ትግላችንን እንግፋበት።

*****

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.