የጥቁር ለባሿ ልዩ ጀግና! የዘመን የኔታዊት ገናና! (ሥርጉተ ሥላሴ የሳተናው አምደኛ)

ከሥርጉተ ሥላሴ፤ 18.02.2018 (ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።)

„እግዚአብሄር ኢዮብን ልቡ ከኃጢያት እንደ ነፃች ባዬው ጊዜ፤ በብዙ ክብር ተቀበለው።“

(መጸሐፈ መቃብያን ምዕራፍ ፰ ቁጥር ፪)

 • እፍታ።

እንደም ነሽ ውርሰ ጽናት እማዋይ? ደህና ነሽ ወይ? እህት ዓለም እንኳን ለዚህ አበቃሽ። ግን እንዴት ነሽ የጥቁር ለባሿ ብርቱ ጀግና ብቋዊት?! የኛዊት! እንደተፈታሽ ገጽሽን ሳዬው ውስጤን በጠበጠው። ተረባበሽኩኝ። ለረዥም ጊዜ በጸጥታ ውስጥ ነበርኩኝ። እኔ ጫካ በገባሁበት ጊዜ ተገናኝተን ቢሆን ኖሮ፤ የወላጆቼን የምህረት ጥያቄ አቅርቦት አልቀበልም ነበር። ስቃዩን እንጋራው ነበር በዱር ቤቴነት። አንድ አጋር አንስት በማጣቴ ምክንያት ነበር የተመለስኩት። በምህረት ከገባሁ በኋዋላም ቀዮዋን በር አይቻታለሁ። ስፈታም በቁም እስር በ50 ሺህ ብር ዋስ ነበር። 50 ሺህ ብር ያን ጊዜ ብዙ ነበር፤ የዛሬ ሚሊዮን እንደማለት ነበር። ሌላው ነገር ከእኛ በኋዋላ በአዲሱ ትውልድ የጣይቱ፤ የተዋቡ፤ የምንቴ፤ የሰብለወንጌል የፖለቲካ አስተሳሰብ፤ ብልህነትና ጽናት እንዲሁም የብቃት ንጥረ መንፈስ አልነበረም። ጎልተው የሚወጡ ተተኪ ወጣት ትንታግ አንስት ህልሜ ነበር፤ ልክ እንደ እኛ ዘመን በሃሳብ መዋጮ ትጉሃንን አብዝቼ አልም ነበር። የእኛ ዘመን የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ የጉድ ነበር። እኩል በኩል ነበርን ማለት ይቻላል። አያያዙም መልካም ነበር። የማህበራት መሪዎች ሁሉ ብርቱዎች ነበሩ። በሠራተኛ፤ በሙያ ማህበራት መሪነት ሁሉ አንስቶች በድንቅነት ነበሩ። በአቅም ላይ የተመሠረተ ተመጣጣኝነት ነበር።

 • ክስተት።

ከእኛ በኋዋላ ለአዲሱ ቀጠይ ተከታይ ትውልድ የነገረ ፖለቲከኛ አንስት ቡቃያ ጭራሽ ድርቅ የመታው ያህል ይሰማኝ ነበር። ሃዲድ አልቦሽ ነበር። መንፈስ ማረፊያ አልነበረውም። ልሳን አንደበት የሆነ ለዬትኛውም ጊዜ በአጅጉ በተከታታይነት ያስፈልጋል፤ በሴትነት ማንነትም ላይ ሆነ በሌሎችም ዘርፍ እኩል የተሳትፎ አድማስን የማስፋት ጉዳይ ቸል የተባለም ነው። በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ውስጥን የሚወክል ሁነኛ ያስፈልጋል። ይህ ለነገ የሚቀጠር አልነበረም። በእኛ ዘመን ብዙ ነበርን። በሴቶች ጉዳይ ብቻም ሳይሆን ከዚህም ከፍ ያለ ሃላፊነትን በብቃት የመወጣት የዕውቅና ድርሻ ነበርን። ታስታውሻለሽ አይደል? አንቺ ትሠሪበት በነበረው ወረዳ አስተዳደሪ ሴት የሺዬ ነበረች። ጅምሩ መልካም ነበር። ከእኛ በኋዋላ ግን መጸሐፉም ቄሱም ዝም ሆነ። ሌላው ቀርቶ በገዢው የጎሳ የፖለቲካ ድርጅትም ሚዲያ ላይ የማያቸው አንስቶች ሴት የፖለቲካ ሊሂቃን አብዛኞቹ ራሳቸውን መግለጥ እንኳን የማይችሉ ናቸው። እንኳንስ ክ/ ሀገራት ላይ ለዛውም ዞጋዊ ማጣሪያም አለበት። እርግጥ የ42 ዓመት እሰረኛዋ የመከራዋ ጥቁራት ረቂቅ ነው፤ ከዛ መፈጠር እራሱ የአደጋ ምልክት ነው። የትም ቦታ፤ በማንኛውም ሁኔታ። የሞራሉ መሪ አቦ በቀለ ገርባ እና ግልጡ የፖለቲካ ሊሂቅ አቶ ደረጀ ጣፋ እንዳሉት። ውጪ ሀገርም ተመሳሳይ ነው። ልዩነቱ እዚህ እስር ቤት የለም። ህሊናችን፤ የአቅማችን ኮቴ ግን በድርብ ሰንሰለት የታሰረ ነው። መላወሻ የለም። በማህበረሰቡ ግለት እንዲኖርም ዘመቻው በስውር ታቅዶ ይከወናል። እናቱ ዕውነቱን ነው የምነግርሽ። በፍጥነት ወደ ራስ መመለስ በእጅጉ ያስፈልጋል።

… ወደ ቀደመው …

የተተኪ እጦት ሽታ ሽው ሲለኝ ኖሮ እንዲያው በድንገት ግን አንድ የምሥራች አደረሰኝ የጎንደሩ የአማራ ህልውና ታሪካዊ ተጋድሏዊ አብዮት። በወቅቱም በአደብ ሁኔታውን እከታተል ነበር። አክቲብ ግን አልነበርኩኝም። የአማራ ተጋድሎ ታታሪት የንግሥት ይርጋ መታሰር፤ የክሷ መዝገብ ጭብጥ የተፋለሰ እና በፍጹም ሁኔታ የተሳሳተ ስለነበር እልህ አዋለደ። እርግጥ ሌሎችም እዚህ ውጪ ሐገር ያየኋዋቸው የታቀደ የአግላይነት ዝበቶችም እልህና ቁጭቴን አቀጣጠለው። ደሜ ተቆጣ። አዲሱን የትግል መስክ ልክ እንደ ጾታዊ ማንነቴ ለመቀበል እና እራሴን ለማለማመድ ግን እጅግ በጣም ፈታኝ ነበር። ወያኔም፤ መህአድም፤ ውጪ ሀገርም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሞረሽም „አማራ ነኝ“ አላሰኘኝም ነበር። ግን ይህቺ የዘመኗ ፖለቲካ ያስገደዳት ቀንበጥ „አማራ አሸባሪ አይደለም“ የሚል ቲ ሸርት ስለለበሰች ብቻ ታሠረች። ማንነቴን አትቀሙኝ፤ እንደ ማንነቴ ለመኖር ይፈቀድልኝ፤ መኖሬን አትንጠቁኝ ብላ አደባባይ በመውጣቷ የክርስቶስን ስቃይ ተቀበለች። ሌላዋ ጎንደር ተወልዳ አደገቸው ተወናይት ፍርያት ግን መቀሌ ላይ በማንነቷ ያሻትን ስታደርግ የክብር አቀባባል ነበር የተደረገላት። ዛሬ ብትጠሪያት አትሰማም። ይህቺ የጥቁር ለባሿ ቤተኛ ቀለበት ለቀጣዩ ትውልድ ምልከትነቷ ጉልህ ስለነበር ወሰንኩኝ። የተገባትን ትትርና ዕውቅና ከነፍሴ ሰጠሁት። በሷ ምክንያትነትትም ነው መራሂተ መነግሥት የጀርመኗ ጠ/ ሚስተር ዶር አንጅላ ሜርክል ተቃዋሚወችን ለማነጋጋር የወሰኑት፤ በስብሰባው ላይ የሴት ተወካይ እንዲኖር ያስደረጉት፤ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ጀርመን የተለዬ ትኩረትና ክትትል ታደርጋለች። ከሁሉ ቀድማ ነበር የቆሼን ሃዘን በመጋራት ቀዳሚው ብሄራዊ ሰንደቅዓላማን ዝቅ አድርጎ ነበር ያውለበለበው፤ በቅርቡም ኢትዮጵያዊውን ማንዴላ ዶር. መራራ ጉዲና በክብር ተጠርተው በኢንባሲው ውስጥ ቆይታ አድርገዋል። በጸና መሰረት ላይ የተገነባው እልህ ለውጤት የበቃው በ30 ዓመት ውስጥ የናፈቀችኝ ዕንቡጥ ላይ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በጠራራ ጸሐይ አድሎና ላይ ጥቃት ስለሰነዘረ ነበር። ፍርያትና ንግስት ለወያኔ ሃርነት ትግራይ የክትና የዘወትር ዜጎች ናቸው። ሁለቱም በማንነታቸው ላይ መብታቸውን ለመጠቀም በእኩልነት አልቻሉም። አንዷ የቤተ መንግሥት ደም አላት ከሙሉ ግርማ ሞገስ ጋር፤ ሌላው ደግሞ የዜግነት ስደተኛ ናት።

የምወድሽ እማዋይ የአንችና የእኔ ግዴታችን ነው። ማተባችን አድርገን የቆዬነው፤ የኖርንበት ደማችን ነው – ፖለቲካዊ ትግል። ወጣትነታችን የገበርንበት። ከወጣትነታችን ጋር ፈቅደን የተላለፍንበት። ሌትና ቀን እዛው ቢሮ እያደርን የማሰንበት። በሌሊት የተጓዝነበት፤ ጉድብ ያደርንበት፤ እኛ ድርጅትም ነበረን። የእሷ ግን ባሊህ ባይ በሌለበት፤ አይዞሽ ባይ በፈለሰበት እንዲህ ጎልታ ሳያት ዕውን ይህቺ የእኔ ናትን አስከማለት አድርሶኛል። ድፈረቷ ዕውነት ለመናገር ከእኛ በጥቂቱ ከቀደሙት ዘመን ከነበረው ይበልጣል። ጀግኒትን አዩን ሳልስት ማለት ነው።

… አንድ ነገር ተዚህ ላይ …

ከኢህአፓዋ አርበኛ አዩ ጋር አንድ ቀን ውጪ ሐገር ተገናኘን። በዛ ስበሰባ የክብር እንግዳ ነበረች። እሷ እና እኔ ባመንበት የፖለቲካ መስመር በሃሳብ ብንፋለም ግን የአንገርብና የቀሃ፤ የጓንጉና የጣና፤ የአባይ፤ የጉማራና የተከዜ ወንዝ በኮዳ ስደት ላይ ለዋንጫችን አሰኘን። ጥንካሬዋ የሚገርም ነው። ያን ጊዜ ሳገኛት ያልበረደ የትግል መንፈስ ነበር ያዬሁባት፤ የዛሬን ባለውቅም። ትንሽም ዘለግ አድርገነው ነበር ግንኙነታችን። ባልተጠበቀ ሁኔታ ነገሮች ተለዋወጡና አድራሻችን ተጠፋፋ፤ እናም ተለያዬን።

ሌላው እጅግ ከማደንቃቸው፤ ከማልረሳቸው ሴት የፖለቲካ ሊሂቃን መሃከል ተስፍሽ አንዷ ነበረች። „የተስፍሽን“ ከዚህ ዓለም ሞትም ስሰማ ውስጤ እጅግ ተጎድቶ ነበር። እስር ቤትም አብረን ነበርን። ሰሞኑን በበለሳዋ ወ/ሮ ከቤ ዳዊት „የረሳችሁን ተጋድሎ“ ዙሪያ አንድ ነገር ሳፈላልግ በሚገርም ሁኔታ ኢንተርኔት ላይ ተስፍሽ የሰጠችውን ቃለ ምልልስ አገኘሁት። ፎቶዋንም እንዲሁ። አትሜ ዓርማዬ አደረኩት። እርግጥ ከፖለቲካው ዓለም ወጥታ በዕደ ጥበብ መሪነት ላይ ነበረች። ጎበዝ ሴት ነበረች። የመጀመሪያዋ የሴት የአንደኛ ደረጃ ት/ ቤት ዳያሪክተር፤ የመጀመሪያ የወረዳ ከዛም የአውራጃ ኢሠፓ ኮሜቴ የርዕዮትዓለም ጉዳይ ሃላፊም ነበረች። ብቃቷም ልዩ በሳል ነበር። ቃለ ምልልሱ ላይ „አንደበቱ ርቱ፤ ተደምጣ የማትጠገብ“ ይላል። ጥሩ አድረገው ነበር በፅናት እና በዕውቀት ላይ በተመሰረተ አስተሳሰባዊ ጥረት እን ጓድ ገ/ድህን በርጋ፤ ጓድ ወንደወስን ሃይሉ የቀረጹን። በዬትም ቦታና ሁኔታ አንገትን ቀና የሚያደርግ በተመክሮ በዳበረ አቅም ነበር መንፈሳችን የገነቡት። ጥሩ የስልጡን ህሊና ትጋት ማህንዲሶች ነበሩ። የማይጠገብ የህሊናን የማልማት የግብርና ተግባር ክህሎት ነበራቸው። የተሰጣቸው።

ትናንት በአንቺ መፈታት ደስ ያለው የጋራ ወንድማችን ግርሜው ደውሎ ሲያነጋግረኝ በጠንካራ ሴቶች ጉዳይ ስንወያይ የተስፍሽን ብቃት አነሳን፤ በሥጋ መለየቷንም ነገርኩት፤ የሰማ ስለመሰለኝ። አልቀጠለም። ስልኩን አቋረጠው። ምን አልባት ከሰሞናቱ ከደወለ እስኪ አጽናናዋለሁ። እኔ ስልክ መደወል ስለማልወድ። እሱን መጠበቅ ግድ ይለኛል። ሩህሩህ ነው። የጸጥታ ችግር ሲኖር በእሱ መሪነት በጋራ መጥተው ሌሊት ወደ ቢሮ ይወስዱኝ ነበር። አስከ አሁን ድረስም ያ ቅንነቱ ሴት አንጀትነቱ አብሮት አለ። የእሱ ውጪ ሀገር መኖር በምለሰት ያን የፍቅር ዘመን በሳቅ፤ በትዝታ እንቃኘዋለን። የነበረን ፍቅር፤ መተሳሰብ፤ እናቴ ፓርቲያችን መፍረሱ አለነበረም ያሳዘናት ያ ወልዮሽ መተሳሰብ እንጂ።

 • የአደራዋ ሰንደቅ ድንቅ እመቤት አማዋይ።

ያ የወጣትነት ትንታግነት ዘመንን በጀግንነት አቅልመሽ ምዕራፉን የኮበብ ብርሃናማ ትውፊት አንቺ አደረግሽው። አደራ አወጣሽ።ፈርጥ! የትውልድ ትውፊት ብሩኽ ጎህ ቀዳጅ በመሆንሽ እንኳን ደስ አለሽ ዳግማዊት እቴጌ ጣይቱ! I am proud of You! Ich bin stolze auf dich! እርግጥ ነው የተሻለ የህሊና፤ የተመክሮ፤ የጽናት አቅምሽን እናት ሐገር ኢትዮጵያ ብትጠቀምብሽ መልካም ነበር። ስንት የማይታይ ረቂቅ ክህሎት እንዲህ ባክኖ ቀረ … ራሱን ያለዘር የበተነ ፓርቲ በታሪክ ኢሠፓ ብቻ ነው ማለት ይቻላል። ያ ሁሉ ዕምቅ አቅም ብክንክን ብሎ ቀረ። ሰብሳቢም መሪም አጥቶ። የነፍስ ወከፍ አቅሙን ያደመጠ እንኳን አልተገኘም። ግን ወርቅ ነበር። ተመስጥሮ የተቀመጠ ቅምጥ ሃብት።

 • ዕምቅ አቅም።

እናቱ ከወጣሁ ጀምሮ በቅርበት የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ የተስፋ ጉዞ ሳላገልል እንደ ራሴ የቤት ሥራ እከታተላለሁ። ሦስት ዓመት ብቻ የሱባኤ ጊዜ ነበረኝ። በዛን ጊዜ ቅዱሳን መጻህፍትን አንደ መደበኛ የትምህርት ክፈለ ጊዜ ያጠናሁበት ጊዜ ነበር። በልጅነቴ በቂ እርሾ ስለነበረኝ ከዘመኑ ጋር ለማዋህድ ብዙም አልቸገረኝም። በዛ ላይ አሜሪካን ሀገር የሚኖረው ዲያቆናዊ ህይወት ያለው ታናሽ ወንድሜ በትርጉም አፈታት ብዙ አግዞኛል። ውጭ ሀገር በሚኖሮው ቅዱስ ሲኖዶስ የጎላ ድርሻ ያለው፤ የዳጎሰ የተግባር ተሳትፎ ያለውም ነው። ሊቃውነተ ቤተክርስትያን አባቶቻችንም በተመስጦ ይወዱታል ብቻ ሳይሆን ይሳሱለታል፤ ራስ እግሩ ፍሬ ነው። ትዳር የመሰረተውም አባቶቻችን ለማስደስትም ጭምር ነው። በቅኔ ሾጥ ያደርጉት ስለነበር። ልታይ ልታይ የለም፤ በጽሞና እና በተደሞ ድብቅ ብሎ ነው የሚኖረው። በሚኖርበት ስቲት ባለው ማህበረሰብ በውስጥነት ቅቡል የሆነ ነው። በዚህም ዘርፍ ወጣትነቴን የገበርኩበትን ተልዕኮ አሳክቻለሁ ማለት እችላለሁ። ታላቅ እህት እናትም ነውና።

ወደ ቀደመው ነገር ስመለስ ያ የነጓድ ገ/ መድህን በርጋ ብቃት የፈጠረው ሰብዕና እዚህ ውጭ ሀገር የተነጠለ መሆን ግድ ይለው ነበር። በምን መስመር እንግባባ? የሚገርምሽ በህሊና የተደራጀ ሃሳብ የማስቀመጥ አቅም ጥሞና በሌለበት እንዴት ነፃነትን ያህል ነገር መምራት እና ለድል ማብቃት እንደሚቻል ግራ ይገባኝ ነበር። ቋሚ ጽፈት ቤት ያላቸው ድርጅቶች/ ተቋማት አላዬሁም። የአመራር አካላቱ መደበኛ ስበሰባዎች እና የሃላፊነት ተዋረድ አፈጻጸም የሚመራ የህሊና ሰነድም የለም። መርሃ ግብር የሚባል አዳምጬ አላውቅም። የአፈጻጻም ሂደቶችን በተደሞ ሊመራ የሚችል ሰነዳዊ ዕሳቤ ከቶም የለም። የአጭር ጊዜ የረጅም ጊዜና ሁለቱን ሊያይዝ የሚችል ሊንክ የመካከለኛ ጊዜ ንድፍም የለም። ሁሉ ነገር አዬር ላይ በስልክ ይጠናቀቃል። የዬወቅቱን የፖለቲካ ትኩሳት አውሎ ብቻ ይመራዋል። ለዚህም ነው ፈታኝ ወቅቶችን አስቀድሞ ማለፊያ ርብርብ ስለማይሰናዳላቸው የሚሾልኩት ወይንም ጥለውን ሽው የሚሉት። የወቅቱን ብሄራዊ ጥሪ የሚመጥን አሸናፊ ሃሳብ እንኳን ማሰላት ጋዳ ነው። ቃለ ምልልስ ላይ ትደነግጫለሽ። የሃሳብ ጥሪትን ለማሳደግ አይሰራበትም።

ተልዕኮን መሬት ለማስያዝ ባዕድ ነው የተግባር ማሳው። የመንፈስ ሃዲዱ መግባባት አይቻልም። እኛ እኮ በመተያዬት ብቻ እንግባባ ነበር። ስበሰባ ላይ በአይን ቅኝት ብቻ ብዙ ነገሮች ስምምነት ላይ ተደርሰው ወጥ ውሳኔ ላይ ያደርስ ነበር። ለአንዲት ትንሽ ስበሰባ የነበረውን የመንፈስ የቀደመ፤ የታቀደ መሰናዶ፤ የሂደት ተከታታይነት የነበረው የእርማት ነፍስ ደግሞ ደጋግሞ የመከለስ ሂደት በምልሰት ስታስቤው ሌላ ድንቅ ትይንት ነው። ቢሮ ውስጥ አኮ „ኡሁ“ የግድፈት ማረሚያ ነጭ ፈሳሽ ለታይፒስቶች አይገዛም ነበር። ባጀቱ ታጥፎ ነበር። ተጥንቅቀው መሥራት አለባቸው ይሉ ስለነበር ነፍሳቸውን ይማረው እኔያ ደግ፤ ሰው አክባሪ መሪ ጓድ ገዛህኝ ወርቄ።

ከህዝብ ጋር መሬት ላይ በሥርዓት ለመስራት፤ አገልጋይ የመሆን ስሜቱ እራሱ ዛሬ ላይ ስታስቢው ማሰልጠኛ ተቋም ነበር።  የአስተሳሰብ ፈጣን እድገት እኮ ከታምር በላይ ነበር። በዕውቀት በስልጠና በተደገፈ ድርጅታዊ ህይወት ተግባርን መምራት እዚህ ህልም ነው። ልጀምረውም ብትይ አዬር ላይ ነው የሚቃጠለው። አይፈረድባቸውም ከአቅማቸው በላይ ነው፤ ህይወቱን አልኖሩትም። ገንዘብ ማዋጣት አንቱ የሚሰኝ ትልቁ የዜግነት፤ የፖለቲካ ሊሂቅነትም መለኪያ ነው። በቃ። የመንፈስ ብቃት ተቋማት ተከታታይ የስልጠና ሃዲድ የለም። አይቼም አላውቅም። ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የሰከነ አስተሳብ፤ በሰከነ መንፈስ ድርጁ የህሊና ብቃት ነው። ይህን የሚያደርግ ተቋም የለም። ቃሉ ራሱ ዓመት ይዞ እስከ ዓመት አይቀዬርም እንኳንስ ህሊና። ለዚህ ነው ወጀብ በመጣ ቁጥር አዳዲስ ስብስብ ይፈጠራል፤ ሥሙ ወዘተረፈ ነው ግን የተግባር ተከታታይነት አይታይም። ስለሆነም ነው ስስቡም ሆነ ቃለ ምልልሱ ከልብ ጠብ የሚል የሙግት ክህሎት መሆን የሚያንሰው። ዲሞክራሲም ከቃል ያለፈ ውስጥን የመለወጥ ሚስጢሩ አይታወቅም። በውስጥ አላደረም። እገዳው፤ ክተራው፤ ወሰኑ፤ ድንበሩ ወዘተረፈ ነው … ትምክህትሽን በተመክሮሽ ውስጥ ማድረጉ እንደ መርህ መቀበል ያስፈልጋል። ከእኛ ዘንድ ብዙ ረቂቅ መንገድ መሪ፤ አዳኝም ንጥረ ነገሮች አሉና፤

 • የትርታ የኔታ።

… ይልቅ እመቤቴ አንድ ነገር .. ኦህዲድ በቅርቡ ያሳለፈው ውሳኔ ሰው ሊገባው ያልቻለውም ከላይ በጠቀስኩልሽ ምክንያት ነው። ብዙም አትኩሮት አልተሰጠውም። ስሜት ብቻ የሚመራው ራዕይ ነው ያለን። የሥርዓት ለውጥ የሃሳብ ለውጥ ያስፈልጋል ሲሉ ሊቃናትን እሰማለሁኝ። ያ ውሳኔ የ43 ዓመትን ሰቆቃ በሃሳብ ደረጃ ሊፈታ የተሰናዳ ዕንቁ፤ ትሁት፤ ሁልቀፍ እና ከበሰለ ባለድርብ አንጎል ጭንቅላት ተምጦ የተወለደ ሊቅ ነው። የሥርዓት ለውጥ እኮ የ አስተሳሰብ የለውጥ ንድፈ ሃሳብ ያስፈልገዋል። የሚመራው መንፈስ። ይህ ውሳኔ ብሄራዊ መልክ ቢሰጠው ከሊቅ እሰከ ደቂቅ ደረጃ በደረጃ ችግሮቻችን መልክ በማሳያዝ ጥበበኛው ቴወድሮስ ካሳሁን እንዳለው ከፊት የነበረነው በኋዋላ መቅረታችን አሸንፈን ወደ ፊት የሚያገስግስ የሰማይ ስጦታ ነው። እደግመዋለሁ የኦህዲድ የውሳኔ መግለጫ የኢትዮጵያ እናቶችን ዕንባን ያዳመጠ የመፍትሄ ጣዝማዊ ጭማቂ ነው። በሳልና ደፈር እርምጃም ነው። የሰው ግብር ማስቆም የሚያስችል፤ ከሶሻሊዝም ነፃነት ገዳይ አረንቋ መንጥቆ የሚወጣ የመፍትሄ ዓይን ነው። ትውስት ወይንም ተጠማኝነት ያለሰኘው ኢትዮጵያዊ ማንፌስቶ ነው።

እስኪ እህት ዓለም አትምሽ አጥኚው። የሚገርም ነው። የሞራል ሰብዕና ግንባታው ከመነሻ እሰከ መድረሻው አክብሮቱ፤ ትህትናው ውስጥን ለማዬት ድፈረቱ የፖለቲካ መፍትሄ አሰጣጥ ሚዛናዊነቱ፤ ሃላፊነትን ለማከፋፈል፤ ለመውሰድ ያለው ቁርጠኝነት ከድንቅ በላይ ነው። በዚህ ሞቶ ልብን አጽድቶ፤ ከኢጎ ተፋቶ፤ በቅን ህሊና መንፈስ አህዱ ቢባል ኢትዮጵያ እንደ ቀደመው መሪ መሆን ትችላለች። እነ የሴራው ቦንዳ አቶ በረከት የሚሉት የአፍሪካ ነብርነት የእብለት ፕሮፖጋንዳዊ ጭንብል አዘቅት ቁልቁል ተዘቅዝቆ ይቀበርና፤ ልዕልት ኢትዮጵያ ሐዋርያዊት አፍሪካዊት ሀገርም ትሆናለች። እኛ አለን ከፕ/ ኢሳያስ አፈወርቂ የፖለቲካ ልህቅና ጥገኛ የማያደረግ ራሱን የቻለ ውስጥ የውስጥ አዱኛ። እሰከ መጨረሻው ድሆ እንዳይነሳ ተጠማኝት አፈር ድሜ የሚያስግጥ።

ሐገር ቤት ብርቱ አቅም አለ። ብቁ፤ ትሁት፤ ከትዕቢት ጋር በፍጹም ሁኔታ የተፋታ ልቅና። እርግጥ ነው የለመደብን ነን እኛ በዬጊዜው ደግ መንገዶች በማጣጠል እያሾለክን ሚሊዮን ለእርድ ማቅረብ፤ ውድመትን እንደ ጀግንነት የምንቆጥር ግን ዕውነተኛ ዲሞክራሲያዊ፤ ፍትሃዊ ነፃነት የምንጠብቅ፤ የምንናፈቅ።

የእኔ ጀግና በንጽህና እና በቅድስና ማለቴ በመንፈስ ውስጥነት ብትመረምሪው ናፍቆትሽን፤ ራዕይሽን፤ ግብሽን፤ የተሰዋሽበትን ሚስጢር በዚህ የውስጥነት ወጥ አቋም ማዬት ትችያለሽ። ይህም ስለሆነ ነው አሁን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው። ይህ ውሳኔ ከዬትም ይምጣ ብቻ መንገድ ጠራጊ፤ አብዛኛውን አስማሚ መሆኑ ብቻ መታዬት አለበት። የነጮችን መቅዳትን እንደ መርህ ካልተወሰደ፤ ከራሳችን ሥጋና ደም ተምጦ የተወለደው ውሳኔ ነፍስን ይታደጋል። ዛሬም ሰው ይሞታል፤ ዛሬም ሺዎች ይታሰራሉ፤ በዚህች ደቂቃ በማዕከላዊ፤ በክንፈ ማዕከል ነፍስና ሥጋ በአረመኔዎች ይታረዳሉ። አካል ይንኮላሻል፤ ጥፍር ይወልቃል። ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወገኖቻችን መንገድ ቀን በሃሩር ሌት በቁር ይገረፋሉ። ህመሙ ገና ውስጣችነን አላደማውም።

እኛ ስንትበሰበስ፤ አቅም አዋጥተን በተሻለው አቋራጭ መንገድ መሄድ ሲቻል፤ አሁንም ዝነጣ እና ቅልጣን ነው። የትግራይ ሥርዎ መንግሥት ለአዲስ ግድያና እስራትም ተዘጋጅቷል። ትጥቁን አሟልቶ ባሩንድን ለመልቀቅ በተጠንቀቅ እዬጠበቀ ነው። የታወረ።

የፈለገ የፖለቲካ ሊሂቅ ሺ ሚሊዮን ጊዜ ረቂቅ ያዘጋጅ፤ ይወያይ ከዚህ የኦህዲድ በሳል ሰነድ በላይ መሄድ አይችልም። አይተናዋል እኮ የእሰከ ዛሬውን ፖለቲካዊ የሃሳብ ብቃት። ይህ የውሳኔ ሰነድ የመዳኛ ማንፌስቶ ነው። ለእኛ ብቻ አይደለም ለአፍሪካም ናሙና ነው። ለብ ለብ አይደለም። በስሜት የሚወራጭም አይደለም። አግላይና ጨቋኝም አይደለም። በግብታዊነት ያዙኝ ልቀቁኝ የሚልም አይደለም። የረጅም ጊዜ ፍላጎትን በመኖር ውስጥ ያዬ፤ ያደመጠ የሪሰርች ሰነድ ነው። ጥናታዊ ነው። የፍትሃዊቷ ኢትዮጵያ የፖሊሲ አዲስ ንድፍ ማውጫ ሆኖ ማገልገል የሚችል የድህነት ምንጭ ነው። ለእኔ ትሁት የሆነ የመንፈስ ህገ መንግስት ነው። ዘመኑን ያደመጠ ስልጡንም ነው። እኔ እንዲያውም በረዥም ጊዜ ሂደት በመንፈስ ሲረቀቅ፤ ሲመረመር፤ ሲከለስ የቆዬ ሰነድ መሆኑን ነው እምገነዘበው።

እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው በተመክሯቸው የምመሰጥባቸው የተከበሩ ዶር. ካሳ ከበደ ቢጠዬቁ መሰል አቋም ይኖራቸዋል። ወይንም አገር ቤት ያሉት የቀድሞው የሽዋ ክ/ ሀገር የ ኢሰፓ ተጠሪ ጓድ ደበላ ዴንሳ ቢጠየቁም ይመልሱታል። ጓድ ገ/ድህን በርጋ በህይወት ካላ ቢጠዬቅም ሙሉ ድጋፉን ይሰጠዋል። መንፈሱ በፍጹም ሁኔታ የሰከነ ነው። በግብር ይውጣ የተሠራ፤ በወጀብ የመጣ አይደለም፤ የታሰበበት፤ ቀን ጠብቆ የተገለጠ የኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር የተደሞ ትርጉም ነው። በህሊና ሰሌዳ የቆዬበት ጊዜ ለእኔ የሰሞናት በፍጹም አይደለም። ዓመታትን የስቆጠረ፤ በሙሉ መሰናዶ ፍቅር የመከረበት ሰነድ ነው። ውስጡ ከቆሰለ ኢትዮጵያዊ ማንነት ተነስቶ፤ በተመክሮ ቀልሞ፤ በዕውቀት ተክህኖ፤ በማህሌት ተዘክሮ፤ በልምድ አሽቶ ተምጦ የተወለደ ሰዋዊና ተፈጥሯዊ ሰነድ ነው። እንደማንኛውም ውሳኔ ተነቦ የሚጣል ሳይሆን እንደ ድርሳን ሊጠና የሚገባ፤ በጽሞና ሊመረመር የሚገባ፤ ቁጭ ብሎ ሊመረምሩት የሚጋባ ህይወት ነው። ህሊናን በውል አደራጅቶ ለመምራት የሚያስችል የ43 ዐመታትን የእርስበርስ ጉግስን፤ የደም ፍሰትን ሰቆቃን፤ የሚታደግ የምህረት ዓዋጅ ነው። የጥላቻን ሃውልት ከሥሩ የሚነቅል ፍቅር ነው! ትእግስት ነው! መቻቻል ነው! መከባባር ነው! ይሁንታን ጠያቄ ነው! መርጌታ፤ የኔታም ነው! የተስፋ ሥርዬትም ነው! በታቀደ እና በተደሞ መሬት ላይ አህዱን፤ ክለቱን የጀመረ ተፈጥሯዊ መንፈስ ነው። ይህን በሳል መንፈስ ከሶሻሊዝም የሥልጣን ሹም ሽር ህልም ጋር ተቆራኝቶ ቅዱስ መንፈሱ ሊሰናከል በፍጹም አይገባም። በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ቅንነት ያላቸው ሁሉ በጥሞና የእኔ ብለው አስጠግተው ሊመረምሩት ይገባል። ከመረጋገም የጸዳ ንጹህ የህሊና አብዮት እኮ ነው። በቀል የለሽ፤ ቂም አልቦሽ መከባባር ሰፍኖ መደማመጥን መዋጥን ዝቅ ብሎ በትህትና የጠዬቀ ልባዊ ውሳኔ ነው። መንፈስን ያለ ይሉኝታ የሚያጸዳ ተቋም ነው። አብሮነትን፤ ፍቅርን፤ መደማመጥን ትጉህ ሰባኪ ነው። ማድመጥና ማዬትን ሙያ ማድረግ ያስፈልጋል።

 • ኪዳናዊት።

ውዷ እማዋይ ትውልዳዊ ድርሻሽን በአግባቡ የተወጣሽ ኪዳናችን ነሽ። ጥበባችን ነሽ። ስለእኛ ነፃነት ብለሽ የተማገደሽ ዘመናችን ነሽ። የማይችለውን በማይቻል ሁኔታ ችሎ ራስን ከመስጠት በላይ ሰማዕትነት የለም። መመካትም፤ መኩራራትም ባይኖርም ግን ትውልድን በተግባር በናሙናዊነት በማነጸሽ እጅግ አድርጌ ላመሰግንሽ ክብሬ፤ ጀግናዬ፤ እምቤቴ ልልሽ እፈልጋለሁኝ። የዕውነት ዕውነት ነሽ። ይህን የንጽህና ብርታትሽን፤ ይህን ውርሰ ጽናትሽን፤ ይህን የአይበገሬነት አቅምሽን ለልጆችሽ ማውረስ በመቻልሽም ደግሞ ዕድለኛ ነሽ። ለነገሩ የአማራ ወላጆች ትውልዳዊ ድርሻቸውን ተወጥተዋል ብዬ አስባለሁኝ። የማያቸው ህዝባዊ ተጋድሎች ከአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ህብር ጋር ህብራዊነቱ በህሊና የታተሙ ናቸው። ወጣቶቹ ዞጋዊነት በፖሊሲ ደረጃ በሚተገበርበት ሐገር እያደጉ፤ አማራነት በልዩ ግለት እና ጭቆና ፈተና ውስጥ በከተመበት በዚህ ቀራኒያዊ ድቅድቅ ወቅት የአብሮነት ቀደምት ተምሳሌያዊነቱ የአፍሪካዊነት ዓርማው ኢትዮጵያዊነት ሳይጠፋ አንዲህ ጎምርቶ ማዬት የሰማይ ታምር ነው – ለእኔ።

ሰሞኑን ጥበበኛው ቴወድሮስ ካሳሁን በነበረው የባህርዳር ኮንሰርት ላይ ብሄራዊ ሰንደቅዓላማችን ለታዳጊ ወጣቶች፤ ለወጣቶች ማተባቸው ነበር። የባህርዳሩ ስቴዲዮም እንዴት መንፈስን የሚያረካ፤ የሚክስም የኢትዮጵያዊነት ትዕይንት የታዬበት የመኖር የኔታ ነበር። ግርማ ሞገሱ የከበረ የልብ ነበር። የጸሐይ ቀን ነበር ልበለው። ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማችን ተጎንበሰው ሁሉ ሲሳለሙት ነበር። ሃይማኖታቸው አድርገውታል። በዚህ ሰንደቅ ውስጥ ሁላችንም በክብር አለን።

መቼም የጎጃም ብሄራዊ ተጋድሎ እዬራዊ ነው። ይገርማል። ይህ በእውነቱ ልዩ የዘመን ፍጹማዊ ክስተት ነው። የሚገርመው ወያኔ ሃርነት ትግራይ ስልጣን ከያዘ ከ 10/12 ዓመት በኋዋላ የተወለዱት ልጆች ናቸው የጥቁር አንበሳን አደራ ተረካቢ ለመሆን የፈቀዱት። ለዚህ ነው እኔ ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢርነቱን መርሄ ያደረኩት። በእውነቱ የአማራ ወላጆች ታሪካዊ ሃላፊነታቸሁን በማይናወጽ አዕማዳት ላይ ገንብታችሁታል። ስለሆነም ያውም ካንቺ አንዲህ ዓይነትን የብቃት እትብተ – ውርስ ወልደሽ በማሰደገሽ ብዙም የሚደንቅ ባይሆንም፤ የልጆችሽ አንቺን ለማድመጥ መፍቀድ፤ የአንችን አርማ ለማንሳት መትጋት፤ በተጋድሎው ውስጥ ዘመናቸው የሚፍቅድላቸውን ተጋድሎ ሁሉ ለመፈጸም መታተር መታደል ነው። ልዩ የተልዕኮ ፍሬዘርም ነው። ወጣታ ልጅሽ ትጋቷን አያለሁ፤ እሰማለሁ። ይህ ህያውነት ነው። አሉሽ አሉን ማለት መቻላችን በራሱ አጽናኝ መንፈሳችን ነው። በ አጋጣሚው መከራሽን በቅርበት ለተጋሩ ሁሉ ምስጋናዬ በአክብሮት ይድረሳቸው። ተመስገን!

 • አትኩሮት የተነፈገው ዕምቅ አዱኛ። የተከደነም ሲሳይ።

አትኩሮት የተነፈገው ዕምቅ አዱኛ የሴቶች የማድረግ አቅም ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን ኢትዮጵያ ከዓለም ተለይታ ወንድ ብቻ የሚወለድባት፤ የሚያድግባት፤ የተብዕት ማህበረሰብ ብቻ የሚኖርባት ብቸኛዋ ፕላኔት ናትን ያሰኛል። ኢትዮጵያን ከትውልድ ወደ ትውልድ በማሸጋገርም ረገድ ወንዶች ብቻ የገነቡት የማንነት ታሪክ እንደሆነ ነው ጭብጡ፤ መሬት ላይ ያለው ሃቅ የሚያውጀው። ነገረ እኛ ምድረ በዳ ነው። በፍጹም ሁኔታ በጭቆና ግለት እዬተፈጸመብን ነው። ተፈጥሯዊ ወንጀልም ነው።

ይህ ሲባል ለማሟያ ተዋፆነት ለቁጥር ሳይሆን አቅም ያላቸው ብቁ ሴቶችን በማፍራትም፤ ብቅ የሚሉትን በመቀበልም ደረጃ አንድ ራሱን የቻለ የተደራጀ፤ በአግባቡ የታነጸ የለውጥ እንደገና መወለድን ይጠይቃል። የወንዶች የፖለቲካ ማህበር አጥብቆ ይፈራናል። የሚገርመው እስር ቤት መከራው ረቂቅ ነው። እራስን ማጣት ነው። በተፈጥሮ ውስጥ ተሰርዞ ለዘለዓለም መኖር። ያን ያለፈበት ሁሉ ያውቀዋል። በተለይም ለዬት ላሉት፤ ለዬት ያለ የዕድሜ ልክ ፋስ አለ። ልርሳው ቢባል እኳን ሁልጊዜ እዬገዘገዘ፤ እዬተከታተለ ሰላም የሚነሳ ከትካች አታካችም። የውስጥን ሰላም የሚያውክ። ይህም ሆኖ አሁን ያን ሁሉ መካራ ተሻግረው የማይሽር ረቂቅ ሰቆቃም አዝለው የወጡት የጣይቱ ልጆች ጀግኖቻችን እነ ጫልትሻ፤ ድርቤ፤ እማዋይ ከእስር ሲወጡ አቀባባል በእውነቱ እጅግ ደንዛዛ፤ ቀዝቃዛም ነበር። ዓውዱ ውሃ ውሃ ይሸት ነበር።

ለሴት የፖለቲካ እኩልነት ተጋድሎ ዋጋ ለከፈሉ አንስት ጀግኖች ቢያንስ በተውኔት፤ በሥነ – ጥበብ ቤታዊነት ያሉ ሰውን ማዕከል ያደረጉ አንስቶች ያልጀመሩት ድንቡልቡል ገመና ነው ይህ አመክንዮ። ዕውነት ለመናገር የታመመን መጠዬቅ፤ የታሰረን እግዚአብሄር ያስፈታህ ማለት፤ እንኳንም ተፈታህ ማለት ሰማያዊ ግዴታ ነበር። ግን አንድስም እንኳን አልሆንም። ቀለል ያለች መሰናዶ አዘጋጅቶ ውክል አካልነትን ማሳየት ይቻል ነበር። አለሁሽ እኔም ማለትን ይተረጉም ነበር። የፖለቲካ ሊሂቃን ሴቶች እስር ቤት የደረሰባቸውን ረቂቅ ፈተና አሽንፈው ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ፤ አብሮ ያችን ደቂቃ ለመጋራት አለመፍቀድ እራስን በራስ የመሰረዝ ያክል ነው። መከራን አብሮ መጋራት ባይቻል እንኳን ቢያንስ ደስታን እንዴት አብሮ መጋራት ያቅታል? በቃ! የሰርግ ሚዜነት ብቻ ነውን ተልዕኳችን? በቃ! ቀይ መንጣፍ ላይ መዘናከት ብቻ ላይ ይሆን ፆታዊ ጥሪያችን? ያሳፍራል ይሄ ለአንዲት ዕውቅና ላላት ተዋናይት/ ጋዜጠኛ/ ጸሐፍት/ የሰብዕዊ መብት ተሟጋች/ የፊልም ዳይሪክተር፤ የአንስታዊነት ተፈጥሯዊ ማህበርተኛ።

ቀድሞውንም እንደ ኢትዮጵያ ባለች ወግ አጥባቂ ሀገር ሴት ልጅ አመለካከቷ ልዩ በመሆኑ በህሊናዋ እስረኛ ልትሆን አይገባም ነበር፤ መውጣቷ በራሱ ከድንቅ በላይ ሊከበር ይገባ ነበር። ሴታዊነታችን በራሱ፤ የራሱ ድምጽና ቀለማዊ ቃና አለው። ሴት በመሆናችን ብቻ የምንጋራቸው ወላዊ፤ ተፈጥሯዊ ዕሴቶች አሉን። በዛ ላይ የሴት ተፈጥሮ ሰማያዊ ነው። ርህርህና ከእናትነት ጸጋ ጋር የተሰጠን ባለክብሮች ነን። ይህ የፈጣሪ ጥበብ የአጋርን መከራን ካልተጋራ ሞረድ የሌለው ክህሎት ነው የሚሆነው።

… ስለ ትናንት እምቶች ብቻ ትረካ በቂ አይደለም። ዛሬ ባለው ህይወት ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ለሚተጉት ትዳራቸውን፤ ኑሯቸውን፤ ልጆቻቸውን በትነው፤ ወይንም ወጣትነታቸውን ሁሉ ሳይስቱ ለሰጡ የሙሉ ነፃነት ግንባር ቀደም አርበኛ እህቶች ያልሆነ ታዋቂነት ይበጣጠስ ትላላች ሥርጉተ ሥላሴ ተዚህ ተ-ሲዊዘርላንድ። ይሄ ሴታዊነት የሚባለው ወጣት የሥነ – እኩልነት የተጋድሎ ድርጅት ይህን መከወን ካልቻለ፤ ለዚህ ጥቃት መከታ መሆን ካልቻለ ስለምን ተፈጠረ? ሚዲያም አለ በሥም „የጣይቱ“ የሚነገድበት፤ ታዲያ ለመቼ ሊሆን ነው ይሄ? ዘመኑ እኮ ሰብዕዊነት እና ተፈጥሯዊነት ነው። ስለምን ወጣት ሴቶች እንደ ዘመናችሁ ለመኖር አትፈቅዱም? ለመሆኑ ይህ ሴታዊነት ለዛውም በወርሃ የካቲት የኮፐን ሀገን መለከት በተነፋበት የተስፋ ወር ላይ ክፍተቱን በድፈረትና በሙሉ ልብነት መወጣት ከተሳነው ስለምን ተቋቋመ ዕሴታዊነት? የቄሮ አናብሰት እኮ ማንንም ሳይፈሩ እና ሳይቸሩ እኮ ነው መድፍ እዬረገጡ ፊት ለፊት ወጥተው አደማ ላይ ጀግኖቻቸውን በእልልታ፤ በሆታ፤ የተቀበሉት።

አንስቶች እስከ መቼ ተኝተው በለኝ እንደሚሉ እጅግ የሚገርምም፤ የሚያስጨንቅም ሌላ እጥፍ ድርብ ግማድ ነው – መርግ ያዘለ ዶፍ። መከራውን አብሮ ተኑሮ ፍሰሃውን በግለት ማህጸንን ማዬት ደም ያስለቅሳል። እርር ኩምትርም ያደርጋል። የሚነሽጣት አንስት የመከነባት አገር ኢትዮጵያ መቼ ይሆን የሴቶችን ልቅና በወጉ የምታስተናግደው? ስለመኖራችን ዕውቅናው መቼ ይሆን የሚታወጀው? ስለመከፋታችን አጀንዳ የሚሆነው መቼ ነው? የኔታ ጊዜ እባክህን የምርምር ማዕከል ክፈትበት።

የአሜሪካው ድምጽ ሁለመና ልዕልት ጽዮን ግርማ ወንዶችን ከእስር የተለቀቁትን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፤ የዘመን ፊደል ገባታ የሆነችውን ጀግና እማዋይሽ አለሙን፤ ድንቂት ብርቱዋን ጫልትሻን አልደፈረችም። ለምን? የፋሽት ፈትለወርቅን ገ/ እግዚአብሄር ክብርን ለመጠበቅ ይሆን? በጋራም የታጋሩ ድምጽ ፌስ ቡክ ላይ ውይይት ነበር አንስት አረበኞቻችነን አንስቷ ጋዜጠኛ አልፈቀደቻቸውም? ለምን? የኢትዮጵያ ሴቶች በምን ሁኔታ ተፈጥሯችን እንደተሰረዘ ልብ ልትሉት ይገባል። የሱማሌን ወረራ ለማሸነፍ ቀን እና ሌሊት በሶ፤ ዳቦ ቆሎ በማዘጋጀት እዛው እያደሩ የተጉት እናቶቻችን፤ ባስገኙት ነጻነት የተኮፈሱት ዘመነኞች እንዲህ ረመጥ ለማህጸናችን አዬር ላይ ይልካሉ። ለዛውም የሚሳሳላት ልዕልት ጽዮን ግርማ፤ የእኛ የምትባለው፤ አቅሟን እውደዋለሁ፤ ግን ሚዛናዊነት የመከነበት ነው። ታዳላለች።

… ፍርዱት! ማን ይቅደም? ህሊናን ይቀረድዳል። አጀንዳ አይደለንም። አብይ አይደለንም። አስፈላጊ አይደለንም። ከመንፈስ በዓዋጅ ተሰርዘን ቀዬ አልቦሽ ሆነናል ልክ እንደ አማራ ማህበረሰብ። ሴታዊነት ከምድረ ኢትዮጵያ ተባሯል – በመንፈስ። ከዚህ በላይ ገዳይነት የለም። እነኝህ አንስቶች እኮ ትርጉማችን ናቸው፤ ያን ያህል ሰቆቃ ያስተናገዱ ጀግኖች እንደ አልባሌ ዕቃ ተወርውረዋል። አዬ የፋሽስት ዘመን … የት ትደርስ? የትስ ታደርሰን ይሆን?

 • የመፍትሄ የኔታ!

https://www.youtube.com/watch?v=AHyuaT4mqz4&t=84s

„Ethiopia Dr abiy የሰዉ ልጆች ልዩ ብቃት ክፍል አንድ“

https://www.youtube.com/watch?v=NHhWHrJOuHU&t=88s

Ethiopia Dr abiy የሰዉ ልጆች ልዩ ብቃት ክፍል ሁለት“

አሁን ተመስገን የምለው በፖለቲካ ህይወት በልምድም፤ በተመክሮም ያዘመረች ሊሂቅ፤ በመከራም የተፈተነች ውድ እማዋይ ስላለች መሬት ላይ ተስፋዬ መሬት ይዟል። እዩኝ እዩኝ የለም በሷ ቤት፤ ግን ቁጭ ብሎ አስቦ በመሥራት ተግባር ላይ በመገኘት የሰከነች ናት። ለዛውም ወጣት እያለን ነው እኔ ይሄን የማውቀው። አሁን ደግሞ በቀለም ትምህርት ገፍታ፤ በኑሮ ውስጥ መከራን በተለያዬ ሁኔታ ስታስተናግድ ደግሞ ከሙሉ ዕድሜ ጋር የድርጁ ብቃትና ክህሎት ጥሪት ባለቤት ትሆናለች ብዬ አስባለሁኝ። የመሪነት አቅሟ ሥህን ነው፤ ጽናቷ ተፈታ እንኳን ኪዳን አልጥሰም፤ ጓዶቼን ጥዬ አልወጣም ማለቷ የታሪክ ልዩ ድርሳን ነው። መጸሐፍ። ተጋዳ ነበር ከእስር ቤት የወጣችው። ከሰዋዊነት በላይ ነው ይሄ መልዕክቱ። ቁርባን።

 • የጥበብ ሰዊት ለመከራ ቅርበቷ እስከ ምን?

ለአንዲት የጥበብ እውነተኛ ቤተኛ ማገዶነትን መድፈር ካልቻለች ሰማያዊ መክሊቷን ትተላለፈዋለች። መከራ ይጥማል፤ ወደውና ፈቅደው ሲኖሩበት፤ ምድራዊ ሰምዕትነትም ነው። ቢያንስ ለእነዚህ አንስት ጀግኖች ቆራጣ ጊዜ እንዴት ይጠፋል? ለአፍታ አቀባበል? አንዲት ለምለም ቀንበጥ ቄጠማ ይዞ መጠበቅ እንዴት ያቅታል። ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ፍቅር በአይዞሽ እንዴት ማበልጸግ ይሳናል። አብሶ አሜሪካ ላይ ተሁኖ ማይክን ማጋራት እንዴት በአድሎ ይወራረዳል። ለነገሩ ለበለ አልጋ፤ አልጋ ባልጋ ነው መንገዱ … ማገድም፤ ማግለልም ህሊናን መግደል ስልቱ ታቅዶ እንዲህ ይወራረዳል።

ሥነ – ጥበብ እኮ ጥበብነቱ የማህበረሰቡን መከራን በስልትና በስልጡን መንገድ መሸከም መቻል ነው። ከዚህ ውጪ የሥነ – ጥበብ ህላዊነት የለም። በመከራ ውስጥ ያላለፈ የጥበብ ቤተሰብ ድርቅ ነው። ጥበብ መከራን ከፈራ የተፈጥሮውን ምክንያታዊነት እንጦረጦስ ፈርዶበታል ማለት ነው። የዕምነት ሰዎችም ቢሆኑ፤ የገሃዱ ዓለም ሱባኤ በሰው እጅ የወደቁ ነፍሶችን ቢያንስ አይዟችሁ ማለት እንዴት ያቅታል? መፆም መጸለይም ብቻ በቂ አይደለም።

ጽድቅ ሰማይ ቤት ብቻም አይደለም፤ ምድር ላይ ፈታናን ወደው ፊት ለፊት ሲገሰግሱለት ነው የበለጠው በረከት የሚያስገኘው። ከፆም ጸሎት ይልቅ የውስጥ ተፈጥሯቸው እልቅ ብለው ለሚወጡት ወገኖች ፍቅርን ሳይሰስቱ መመገብ ነበር። እስኪ ጀግኖቻችን ቁመና ቀረብ አድርጋችሁ እዩት፤ ምስላቸው ብቻ እኮ ነው ያለው … የአባ ትርጉም የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ዓይኑ ብቻ ነው የቀረው፤ የድንቁ ጋዜጠኛ ውበሽት ባለቤት አርበኝት ወ/ሮ ብርሃን አንዴት ተጎሳቁለዋል። ይህ አያርመጠምጥም ለሴት ጋዜጠኛ? ባለቤት የለንም እኮ። ለዚህ ነው እማዋይ የታገለችው። በቁሟ በአረመኔዎች የታረደችው። የነፃነት ትግላችን ድል ርቀትም፤ ድርቀትም ይኼው ነው፤ የማይዘለለውን ዘለን ወይንም ስተን ይኼው ዓመት ይዞ አስከ ዓመት መዳከር። የዕእምሮ ቆጣሪያችን በግለት፤ በቂመኝነት የተዘወረ ስለሆነ።

 • ምን መሆን አለበት።

የአማራ ተጋድሎ ሆነ ቄሮ ለተብዕት ጀግኖች የሚሰጠውን ሙሉ ክብርና ሞገስ ለአንስት ጀግኖችም መስጠት ቀዳሚው የተጋድሎ ተግባር ሊሆን ይገባል። ሁሉም ነገር ከመጀመሪያዋ የህይወት ትምህርት ቤት ከሆነችው ከእናት ተፈጥሮ መነሳት ይኖርበታል።  ሌላው ቄሮና የአማራ ተጋድሎ የታሰሩት ይፈቱ ብቻ ሳይሆን፤ መታሰር ይቁም! ግደያ አሁኑኑ ይቁም! የትግል መስመሩ መሆን አለበት። አብሶ ለባለቤት አልቦሾቹ በኢትዮጵያኒዝም ምክንያት ያሉ ዘመን የማይተካው እንደ አርበኛ አንዳርጋቸው ጽጌ፤ እንደ ተዋህዶ አቮ ያሉትን፤ የቀሩት በስቃይ ብዛት አካላቸው የተጎዱት ስለመሆናቸው እየሰማን ነው። ሁሉንም ልክ እንደ እናት የ እኛ ብሎ ተጋድሎ መነሳት አለበት እከሌ ተከሌ ሳይባል። እንኝህን በግንባር ቀደምትነት ምልክት አድርጎ መውጣት የወልዮሽ ግዴታም ነው። ለመከረኛ የምንም ድንበርና ክትር ሊሰራለት አይገባም። ይህ ተጋድሎ „ሰው“ መሆንን ብቻ ነው የሚጠይቀው። ሰው ለመሆን እንፍቀድ ቢያንስ ለጥቁር ልብሱ።

ውድመቱን ግን እኔም አይመቸኝም፤ 43 ዓመት ሙሉ ማፈረስን እንደ ትግል ስልትና ስትራቴጄ ማዬት ቅርስ አልቦሽ ነው የሚያደርገን። ከ100 ዓመት በኋዋላ ልጆቻችን ኢትዮጵያ በምን ደረጃ እንደነበረች መነሻ አልባ እያደረግናቸው ነው። ፍቅር እስከመቃብር ባይኖር „ማር እሰከ ጧፍን“ ፊልም መስራት እና የፊዊዳሊዝምን ከውስጥ ማዬት አንችልም ነበር። በሌላ በኩል ቅርስ እኮ ቱሪዝም ነው። ቅርስ እኮ ት/ቤት ነው። ዕዳ ላይ ሆነን ስንት ሚሊዮን ዕዳ ጫንቃዋ ላይ በተሸከመች አገር፤ የሚሊዮኖች ጉሮሮ ማርጠብ በተሳናት ኢትዮጵያ ቃጠሎ። ትንሽ ተኝተን እንሰበው። ሁልጊዜም እምለው ነገር ኋላቀርነት ማለት የአልተመጣጠነ እድገት ማለት ነው፤ ለምሳሌ ፍላጎትና አቅርቦት፤ እኔ እንደማስበው ኋላቀርነታችን የኢኮኖሜ ብቻ ሳይሆን ኋላቀርነታችን የአሰተሳሰብም አለመመጣጠን አለበን፤ የሃሳብም ግሸፈት Inflation አለብን። ያልተነካው ባጠገቡም ትውር ያላልነበት ችግራችን ይሄ ነው። ሐገር ከፈለግን ሐገርን „ሐገር“ የሚያደርጉ ተቋማት ጥበቃ የህዝብ መሆን አለበት። ወያኔማ የሚፈልገውን ነው እያደረግልነት ያለው። እራሱ እኮ አቅዶ ያቀጥላል። የጎንደር ቅዳሜ ገብያን ያቃጠለው ወንበዴዎችን አደራጅቶ ነው። እኛ ለዚህ ሰይጣናዊ መንፈስ ተባባሪ መሆን የለብንም።

በእያንዳንዱ ነገር ላይ አንጡራ የህዝብ ወዝና ላብ አለበት። ዛሬ የግል ይሆናል፤ ነገ ግን የህዝብ ይሆናል። ተደሞን ለመሪነት ከፈቀድነው። አብክረው ዶር አብይ አህመድ እንደሚሉት ጥበብ ያንሰናል። ይህ በእውነቱ ለማንም የማይገፋ የራሳችን የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል። በእልህ ሀገር አይቆምም። በስክነት እና በእርጋት እንጂ። ይህን በሚመለከት 7ኛ መጸሐፌ ላይ በ2015 ባሳተምኩት መግቢያው ላይ በሚገባ አንስቸዋለሁ ‚የአጋዚ ሠራዊትን‘ ሳይቀር እንዴት ከአውሬነት ወደ ሰውነት በተደራጀ የዕእምሮ እጠባ ፕሮግራም እኛዊነትን ማምጣት የመቻል ግዴታችነን።

የአዲስ ሥርዓት ምኞት ቢሳካ ከእርሾ ወይንስ ከዜሮ ይጀመር? ወያኔ ሃርነት ትግራይ እንደ ሆነ ምሰሶ የሆኑትን ኢትዮጵያዊ ተቋማትን ሲያፈርስ እዬጨፈረ ነው። ተቋማት የቀደምቱ ከስሞ ሥሙ ሁሉ እኮ ሃይሎም፤ ክንፈ ወዘተ ነው። ሳጅን፤ ኢኒስፔክተር፤ ክፍለ ከተማ እኮ ነው፤ ቅርስን ትውፊትን በታቀደ ሁኔታ በስልት ነው የናደው። ወያኔ ሃርነት ትግራይ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት፤ የባህር ሃይል፤ አዬር ሃይል፤ ምድር ጦር ብትንትኑ አውጥቶ በጫካዊ ቡድን ሲተካ ጉዳዮ አልነበረም። ደምና አጥንት የተገበረባቸውን ተፈጣሯዊ ደንበሮች ሲጥስና ሰደረምስ ጉዳዩ አይደለም። „ኢትዮጵያ“ የሚለውን ይባቤ በፖሊሲ ደረጃ ዛሬ ድረስ ሲታገለው፤ ሲፋለመው፤ ጦርነት ሲያውጅበት ጀብዱ ነው። ያ በወልወል፤ ባንባላጌ፤ በባድመ፤ ባፋቤት፤ በሀረር፤ የጥሪው ድል አሰባሳቢ ቀስተዳመናው ብሄራዊ ዓርማውን በህግ ቀፍድዶ የሰይጣን መዋዋያ ሲያደርገው ጉዳዩ አልነበረም። ዛሬን ያቆዩ የጀግንነት አውደ ግንባሮች ሁሉ ማፈሪያችን፤ መሸማቀቂያችን፤ አንገት መድፊያችን፤ ማታኮሻ አውዳችን ሲያደርገው የተነሳበት የፋሺዝም ዓላማ መሆኑን በማስተዋል መቃኘት አልተቻለም። ስለሆነም እኛ መሻላችን ማሳዬት የሚቻለው በመሆን ውስጥ ነው።

ሌላው ልብ ያላልነው አመክንዮ አንዲትም የግንባታ ሂደት ትግራይ ላይ መስተጓጎል ገጥሟት አያውቅም። የሚቃጠል ፋፍሪካ፤ የእርሻ ተቋማት ስሌሉ ለመልሶ ግንባታ የሚወጣ መዋለ ንዋይ አያስፈልጋቸውም፤ ይልቁንም በመጨመር ላይ ይጓዙበታል። አንድ ት/ቤት ስታፈርስ ትምህርት ቤቱን እንደገና ስተሰራው ለዛውም ዕድሉ ከተገኘ፤ 5 ከነበረህ አንተ 5 ላይ ነህ፤ አሁንም። እራሰህ አንድደኸዋልና። ትግራይ ግን 5 ከነበረ፤ አዲስ ሲጨመርበት ስድሰት ይሆናል። መዋለ ንዋዩ በአዲስ ተስፋ ላይ ነው የሚፈሰው፤ ይህ ማለት አዲስ ተጨማሪ አቅምና ሃይል ይፈጣራል። ያም የአንተ ወዝ ነው። ቃሉ ከባድ ቢሆንም፤ የሰው ጭንቅላት ይኖረን። ሚዛን ከማስተዋል ጋር ጭንቅላታችን ውስጥ ይኑር።

 • የተረሱት በአቦይ ክንፈ የፍዳ ማምረቻ ተቋም።

በአቦይ ክንፈ ሚስጢራዊ የደህንነት የሲኦላዊነት የማሰልጠኛ ተቋም የኮተቤ ምሽግም የታሰሩም አንስት እህቶችም ይኖራሉ። ለነገሩ እዛ ያሉ ለሥልጣን ያሰጋሉ ተብለው የታፈኑት ንዑዳን፤ ፃድቃን ምንዱባን በሥምም፤ በጉዳይም፤ በአድራሻም የማይታወቁ ነፍሶች ናቸው። እነኝህ ደምና ሥጋዎቻችንስ መቼ ይሆን ከመቃብር ይፍታህ/ ይፍታሽ የሚባሉት? ማንስ ይሆን ዋቤያቸው? የይስሙላው ፍ/ቤትም አያውቃቸውም እኮ። … አዬ አቦይ ክንፈ ህልፈቱም እንዲህ የኦሾቲዝም ጉድጓድ – መቃብር።

 • ምስጋና!

በተረፈ የእኔ የነባቢቴ አነባቢ ጀግኒት ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ ምስጋናዬ፤ ክብሬ፤ ፍቅሬ፤ አክብሮቴን፤ ናፍቆቴም በትሁት መንፈስ ይድረስሽ ብያለሁ። ብጡላችን ነሽ! ፋናችን ነሽ! መሪያችን ነሽ! እወድሻለሁ የቃልኪዳን አርማዬ! እነ ጫሉቱሻም ብሄራዊ ቀናችን ናችሁ፤ ታኮራላችሁ ትመስጣላችሁ የመሆን እንደራሴዎች። ያ እንዳለፈው ሁሉ ይህም ያልፋል … የዬክልሉ መስተዳድሮች ለሴት  ከእስር ለተፈቱት የተለዬ የሥነ ልቦና ሙያዊ ጥበቃን አጀንዳችሁ ማድረግ ግድ ይላል። ደፍረው የማይንገሩት የሶቆቃ መከራ አለና።

 • ክወና።

የእኛ ጀግኖች አንስት በማሟያነት ሳይሆን፤ በስማ በለውነት ሳይሆን፤ በመናጆነት ሳይሆን ለእውነተኛ የአንደበት ነፃነት፤ የአቅም ሙሉ ፖለቲካዊ የተሳትፎ መድረክ፤ በመወሰን የባልድርሻነት ሚና እኩልነትን በመርህ ደረጃ በትግል ለማምጣት ተኝቶ በለኝን ወስኖ መገነዝ ያስፈልጋል። ዛሬ ዓይን ራሱ ድርቀት ገብቶታል፤ ጆሮም እንዲሁ። ብቁ አንስትን ማዬት አልቻልነም፤ ትጉኽ  የአንስትን ፖለቲካዊ ተሟጋችነት ማድመጥ አልቻልነም። የነፃነት ተጋድሎው በግማሽ ሹሩባ፤ በግንጥል ጌጥ ነው መጪታውን የተያያዘው … ግን እስከመቼ? አይታወቅም። በዚህም ዘርፍ ኦህዲድ በተሻለ ሁኔታ የአንስት ሊሂቃንን ድምጽ እያሰማን ነው። ዓይናችንም እያሳዬን ነው። አንስት ሊሂቃን እንደ ሰማያዊ ጸጋቸው የሞራሉ ሊሂቁ አቦ በቀለ ገርባ አቀባባል ላይ እናታዊነትን በተግባር አስጊጠውታል። ለዚህም ነው ሥርጉተ ሥላሴ ለማውያን የሆነችው። ጠረኑ ጥሟት፤ ወዳውና ፈቅዳው ፊት ለፊት ወጥታ የተሟገተችለት። ተዚህ ላይ ላብቃ …

ሴቶች የነፍስ ልዩ ሥጦታዎች ናቸው።

ሴቶች የፍቅራዊነት ቋሚ አብነቶች ናቸው።

ሴቶች የመሆን ብቁ ጀግኖች ናቸው።

ሴቶችም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነን!

ውዶቼ ለሰጣችሁኝ ስስት ዝር ያላለበት ውድና ተናፋቂ ጊዜ፤ ይሄው እኔ እህታችሁ ኑሩልኝ ሸልምኳችሁ።

መሸቢያ ጊዜ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.