የመገንጠል ጉዳይ ከትላንት እስከ ዛሬ (በይታገሱ ዘውዱ)

 

ጭራቁ አንቀፅ  

“አውራአንባ ታይምስ” የተባለው የማህበራዊ ትስስር ገፅ  ባለቤት የሆነው ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ በቀደመው ሳምንት በዚሁ ገፅ ላይ ያቀረበው ቃለ ምልልስ መነጋገርያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል፡፡  የመቐለ ዩንቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር እንደሆኑ የተነገረላቸው አቶ ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም የተባሉ ግለሰብ በሰጡት አስተያየት የመገንጠል ጥያቄን ዳግም ከህወሓት ጠርሙስ ውስጥ  አውጥተው ዳግም የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ እንዲሆን እድል ሰተውታል፡፡ በስፋት ከተራገበው የመገንጠል ሃሳብ ጋር ተያይዞ አዲሱ የህወሓት ስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ  ጌታቸው ረዳ ጉዳዩ የጥቂት ሰዎች አመለካከት እንደሆነ ብቻ ባጣጣሉበት ምላሻቸው ድርጅታቸውን ከሃሳቡ ነጥለው እንደ ጲላጦስ እጃቸውን ለማጽዳት መሞከራቸው ይህን ጹፍ ለማቅረብ መነሻ ሆኗል። የዚህ ጹፍ ተቀዳሚ አላማ በግለሰቡ የተንፀባረቀውን ሃሳብ መተቸት ብቻ ሳይሆን የመነጠል እምነቱ ባለቤት የሆነውን ህወሓትን የሙጢኝ ያለውን የመገንጠልን ጽኑ ፍላጎት ከየት መጣነት ማጠየቅ ነዉ፡፡

ለሃገሬ ምን ሰርቼላት ከሚለው እምነት የተናጠበ ሃሳብ እንደሚያቀነቅኑ ይፋ ያወጡት እኚሁ “ምሁር”  “ለኢትዮጵያ ሲባል መኖር የለብንም ኢትዮጵያ ነች ለኛ ስትል መኖር ያለባት” ሲሉ ይደመጣል፡፡  ለዚህ ድፍረት የተሞላበት አስተያየት መነሻ የሆናቸው በተለያዩ የተቀዋሞ እንቅስቃሴዎች በተነሳባቸው አካባቢዎች የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ዜጎች በተለያየ መልኩ የጥቃት ሰለባ ሆነዋል የሚል ቅሬታን በማስታከክ ነው፡፡ እርግጥ ነው በማንኛውም መለኪያ ቢሆን ኢትዮጵያውያን ስለ ለብሔርና ቋንቋቸው፣ ስለ ዘውግና ጎሳቸው ሲባል ብቻ የጥቃት ሰለባ  ሊሆኑ አይገባም፡፡ ዘርን እና ቋንቋን ለይቶ ጥቃት ማድረስ፣ በራሱ መወገዝ ያለበትና ፈፅሞ ሊሞከር የማይገባ ድርጊት ሲሆን፣ ፍፃሜውም ለማንም የማይጠቅም፣ ይልቁንስ የሃገር ህልውናን በእጅጉ ፈተና ላይ የሚጥል አደገኛ አካሄድ በመሆኑ በእንጪጩ ሊቀጭ የሚገባው ዕኩይ ምግባር ነው፡፡ ምንም እንኳን ያልተገባ ጥቃት ቋንቋን ለይቶ ደርሷል ቢባልም የዚህን አስተያየት ሰጪ የሃሳብ ጭራ ተከትለው በይሆንታ እንደተቀበሉት ወገኖች እምነት ለተከሰተው ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ምላሽ ይሆናል በማለት የመረጡት መንገድ እጅግ አደገኛ ነው፡፡ እነሱ እንዳሉን መሆን ቢኖርበት ኖሮ ኢትዮጵያ መፍረስ ከነበረባት ትክክለኛ ወቅት እጅግ ዘግይታለች ለማለት ያስደፍራል፡፡

ሰውየው እንዳሉን “እየተጠቃን፣ እየተገደልን ለኢትዮጵያ ስንል እንታገስ መባል የለበትም” ቢሆንማ ኖሮ አማርኛ ተናጋሪው ኢትዮጵያዊ በገዛ ሃገሩ  በበደኖና በአርባ ጉጉ ስለዘር ቋንቋው ብቻ ሲገደልና ሲሳደድ ኢትዮጵያ ትፍረስ ማለት የነበረበት ያኔ ገና ድሮ ነበር እንደማለት ነው። እሺ ያንን ጉዳት አደረሰ ተብሎ እንደሚሳበበው የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ)  ነበር ተብሎ ይታለፍ እንበል ( እንበል ነው ያልነው!) እናም ደግሞ የዚያ ዘመን ጥቃት ሲደርስ እንዲህ እንደዛሬው “የሚያስመካ” የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚል ጉደኛ አንቀፅ ያለበት ህገ-መንግስት  አፀደቀም ተብሎ ይታለፍ።  ነገር ግን እነዚሁ የፈረደባቸው አማሮች ባለፉት ዓስር ዓመታት ውስጥ ስለ ቋንቋቸው እና የዘር ሃረጋቸው ሲባል ብቻ ዳግም ከጉራ ፈርዳ እና ቤንሻንጉል አካባቢዎች ሊያውም የመንግስት መዋቅር እጅ እንዳለበት እየታወቀ ሲገደሉ፣ ንብረታቸውን ሲዘረፉ፣ ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ በገፍና በግፍ ሲሳደዱ  ምነዋ ያንን የፈረደበትን አንቀፅ 39 ጠቅሰው እንገንጠል አለማለታቸው? ከሁሉ በላይ የተገንጣይነትና የጠባብነት ሰሌዳ የተለጠፈበት የኦሮሞ ከምስራቅ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ብቻ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ሲፈናቀል፣ ቁጥሩ የበዛ ሰው ሲሞት ስለምን  ተፈናቃዩ  “ኦሮሞ እየሞተ ኢትዮጵያ አትቀጥልም” ብሎ ሙግት ምነዋ አለመግጠሙ? በዚሁ የምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢ በተነሳ ግጭት ምክንያት ሶማሌ ኢትዮጵያዊ ስለ ዘር ስለ ቋንቋው ተገድሏል እንዲሁም የንብረት ውድመት ደርሶበት ተፈናቅሏል፡፡ ኡጋዴንን ነፃ እናወጣለን ሲሉ የአብዲ ኢሌ ሰዎች ድምፃቸው ያን ያህል ገኖ አልተሰማም፡፡ ነገሩ ከባልሽ ባሌ ይበልጣል ሽሮ አበድሪኝ የሚሉትን አይነት ተረት ያስታውሰናል፣ እኔ ከማንም ዕበልጣለሁ የሚል የበላይነት ትምክህት የተፀናወተው ነው ሰሞንኛው የንገጠል ጉምጉምታ እና ፉከራ።

 

ተናጋሪው ሲቀጥሉ “እኛ ነን ኢትዮጵያ እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ የለችም”  ማለታቸው በተወሰነ መልኩ እውነት ሆኖ በማንነታችን ጥቃት ደርሶብናልና “ሊያጠፉን ጎራዴ ከመዘዙ ጠላቶች ጋር አብረን የመኖር ግዴታም የለብንም” በማለት የተለመደውን የግራ አክራሪዎችን  የጠላትና ወዳጅ ፍረጃ የሆነውን ዝነኛውን  የ“እኛ” እና የ“እነሱን” ተረክን ተከትለው ከባድ የሚመስለው ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ። “አንቀጽ 39 የተቀመጠው ለዚህ ነው። አብሮነት የሚያገዳድለን ከሆነ መለያየት አማራጭ መሆን አለበት። አንዱ ከሌላው በታች ሌላው ከአንዱ በላይ ስለ ኢትዮጵያዊነት ሊጨነቅ አይገባም” በማለት ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።  ይሄ መቼም የሚገርም ሙሁራዊ ምክር ነው። ትግራይ ተገንጥላ ኢትዮጵያ ስትፈርስ የትግራይ ህዝብ መከራ ሊያባራ ነው ማለት ነው? ከቴም ማስተዋል ከቴም አርቆ ማለም እንዲህ ነው¡¡ “እኛ” “እኛ” “እኛ” ………  “እነሱ” “እነሱ” “እነሱ” ብቻ የሚል ዘውገኛ ሌላውን ህዝብ እንደራሱ ወገን መቁጠር የተሳነዉ ምንደኛ አእምሮ ይህን ማለቱ ምን ይደንቅ ማለት ይመጣ ይሆናል።  እውነት ነው ሌላውን ህዝብ ስለቋንቋውና ስለማንነቱ ሲል የሚያጠቃ እብሪተኛም ሆነ እኛ ከተነካን ሃገር ይበተን የሚል የሰንበሌጥ ቤት ገንቢ ሁለቱም አንድ ናቸው። ፍቅርን እና መግባባትን በመትከል አንድነትን ከማፅናት ይልቅ አንዱ አባራሪ ሌላኛው ለምን ተነካው ብሎ ቤት አፍራሽ የሆኑ የጥፋት ልጆች ናቸው።

 

 

ዘውገኝነትና የመገንጠል ጥያቄ

 

የመገንጠል ጥያቄ ሲነሳ በአብዛህኞቻችን አእምሮ ፈጥኖ የሚገለጠው ገፅ ያ ትውልድ የኖረልን፣  ለዚህኛው ትውልድ ያወረሰው ገድል መሆኑ ነው።  ለኢትዮጵያ የአሁን ዘመን የስበት ማዕከሉ የዘውግ ፖለቲካ መሆንም ሆነ ከእናት ሃገር ተገንጥሎ ኩርማን ሃገር የመፍጠርን ግብ የፖለቲካ ርዕዮት አድርጎ በማቆም ውድድር ውስጥ የሃሳቡ ጠንሳሽ ሆኖ የቀደመው ትውልድ ያለምንም ተቀናቃኝ ብኩሩናውንና መኪሊቱን ይወስዳል።

በኢትዮጵያ የተማሪዎች ትግል ታሪክ ውስጥ ምንም እንኳን አስቀድሞ በ1950ዎቹ የኤርትራ ብሔርተኛነት ንቅናቄ መገንጠልን ታሳቢ አድርጎ ቢጀምርም፣ የተቀረው ኢትዮጵያዊ የነፃነት ተሟጋች ዘጠኝ ጥቃቅን “ነፃ ሃገር”  የመመሥረት ግብ ከመነሻው ለትግሉ ማጠንጠኛ አድርጎ አያቀነቅኑም ነበር። የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ሲጀመር ዘርን መሰረት ከማድረግ ይልቅ ሃገራዊ ብሔርተኛነት ላይ ተመስርቶ የእኩልነትና የፍትህ ጥያቄን አንግቦ የመደብ ትግልን ወደፊት ያስቀደመ ነበር በማለት የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ ። ለዚህም ነው በዚያ ትውልድ የትግል ምዕራፍ ውስጥ ቀድሞ በጉልህ ተጽፎ የሚነበበው ማታገያ መሪ ሃሳብ “መሬት ለአራሹ” የሚለው የፖለቲካና የምጣኔ ሃብት  ጥያቄ ሆኖ መገኘቱ።

በ1960ዎቹ መባቻ ላይ ትርክት ቀያሪ ሃሳብ ድንገት በትግል አራማጆቹ ግራ ዘመም ወጣቶች መካከል ፈነዳ። ጥቅምት 1962 ስትራግል (Straggle) በመባል ይታወቅ የነበረው የወቅቱ ዝነኛ  የተማሪዎች መጽሔት/ጋዜጣ የብዙዎችን ሃሳብ ሚዛን ያሳተ ፁሑፍ ይዞ ተከሰተ።  የዋለልኝ መኮንን (“ጥቁሩ ስታሊን”)  ለዘመኑ ወጣት ሊሂቃን የዘረኝነትን ዕፀ-በለስ ቀጥፎ  እነሆ አላቸው። ዘረኝነት የህሊናቸው መብልና መጠጥ ይሆን ዘንድ ኢትዮጵያዊነትን የሚያስጠላ ዕፅ-መሰውር ሰጣቸው።  “አሁን አየ አይኔ”  ያሉቱ የዚያን ጊዜ ፋኖዎች  ድንገት ከሰውነት ማዕረጋቸው አንሰው ማንነትን በዘውጌና በቋንቋቸው ብቻ በመለካት ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ዘውጌያዊነት የተሻለ ማንነት ሆነና ከፊት ረድፍ ተሰለፈ። ዋለልኝም አለ “ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛነት የለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የአማራ ገዢ መደብ የተጫናቸው በደርዘን የሚቆጠሩ ብሔረሰቦች ብቻ ናቸው። እነኚህ ብሔረሰቦች የሶሻሊዝምን ርዕዮት ከተቀበሉ የመገንጠል መብታቸው ሊከበርላቸውና ሊደገፉ የሚገባ ነው።” ያኔም ሃገር ማፍረስና መገንጠል የሚለው መርህ እንደ አላማ በታጋዮች  ልብ ውስጥ ተተከለ ስሩንም አፀና፡፡

ከዛ ጊዜ ወዲህ የነፃነት ትግሉ በሁለት የተከፈለ ሆነ፡፡ ለኢትዮጵያ ብሔርተኛነት ለመታገል በቆረጡና ኩርማን ሃገር ለመስራት በሚታትሩ ዘውግን የማታግያ ማዕከላቸው ባደረጉ ጠባብ ብሔርተኞች፡፡ ኢትዮጵያዊነት እየደበዘዘ ዘውገኝት እንዲጎላ ዋለልኝ በተከለው መርዘኛ አመለካከት የተነሳ የወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት ከተገንጣዮቹ የኤርትራ ቡድኖች ጋር  ሲያደርግ  በነበረው ሃገርን የማዳን ትግል ከኢትዮጵያ አብራክ በወጡ ልጆች ሳይቀር ተቃውሞ እንዲገጥመው ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሮ  ነበር፡፡ በዘመኑ የተደራጁ አብዮታዊና ግራ ዘመም (በራሳቸው አጠራር ተራማጅ ሃሎች) የፖለቲካ ስብስቦች በአንድም በሌላም መልኩ የኤርትራ ብሔርተኛነት እና የዋለልኝ ስታሊናዊነት ጥላ ያጠላባቸው በመሆናቸው ለአብዮታዊነታቸው ማረጋገጫ ይሆናቸው ዘንድ ቢያንስ ቢያንስ የኤርትራን ቅኝ ተገዢነት አምነው የመገንጠል ጥያቄን መቀበል ሚጠበቅባቸው አብይ ጉዳይ ነበር። የዋለልኝ ውርስ የኢትዮጵያ ተራማጅ ሃይሎች ትግል ከመደብ ጥያቄ ወደ ዘውግ ትግል እንዲንሸራተት በማድረግ የራሱን አፍራሽ ሚናም ተጫውቷል፡፡

የኤርትራ ብሔርተኞች እና ዋለልኝ በጠነሰሱት የዘውጌ ብሔርተኝት (ethno-nationalism) አስተሳሰብ የተነቃቃው የትግራይ ብሔርተኛነት አስቀድሞ በተማሪው ማህበረሰብ ወስጥ  ጥያቄ ያነሳው በሁለት ጉዳዮች ላይ በማተኮር ነበር፡፡ ተቀዳሚው ጥያቄ የትግርኛ ቋንቋ ከብሔራዊ ቋንቋነት ተገፍቷል የሚለውን ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያን እና የኤርትራን ያስተሳሰረው የፌዴሬሽን ውል ፈርሶ ኤርትራ  በአህዳዊ አስተዳደር ስር መተዳደር በጀመረች ጊዜ ትግርኛ የአስመራ የስራ ቋንቋ መሆን ማብቃቱ ትግርኛን ይጎደዋል የሚል አመክንዮ ተሰቶታል፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርት አጠናቆ ወደ ኮሌጅ ለመግባት ማለፊያ ነጥብ ከሌሎች አካባቢዮች ይልቅ ለትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ከፍ ብሏል ተብሎ  የተነሳው ጥያቄ ነው፡፡ በመሰረቱ ከፍተኛ ነጥብ በማስመዝገብ ወደ ዩንቨርስቲ ይገቡ የነበሩት ከሰሜኑ ኢትዮጵያ አከባቢ የነበረ ሲሆን በወቅቱ የነበሩ አህዛዊ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት በሃገሪቱ በነበሩ ዩኒቨርስቲዎች በአማካይ ከ20 እስከ 25  በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች ትግርኛ ተናጋሪዎች ነበሩ፡፡

በወቅቱ የዘውጌ ብሔርተኛነት ንቃተ ህሊና ነበራቸው የተባሉ ተማሪዎች ዛሬ በሃገሪቱ ላይ በውል ለሚታየው የዘውግ ዋልተኛነት (Ethnic Polarization) መፋፋት የመሰረት ድንጋዩን “በክብር” አስቀምጣል፡፡  በዘውግ ዋልተኛነት ላይ ለረጅም ዓመታት ጥልቅ ምርምር በማድረግ የሚታወቁት ዮሃን ኤስቴባን እና ዴብሪይ ሬይ የተባሉ ምሁራን እንዳስቀመጡት የዘውግ ዋልተኛነት ዕሳቤን  የሚፈጠረው በግለሰቦች መካከል በሚኖር ቅራኔ ድምር  (the sum of interpersonal antagonisms) ነው፡፡ ለቅራኔ መነሻ የሚሆነው ግለሰቦች እራሳቸውን በዘውግ በማንነት ለይተው  ሲያደራጁ (group identification) እና በተፃራሪው ደግሞ ሌሎችን ስለዘውግ ማንነታቸው ሲነጥሉ (alienation with respect to other groups) የሚመጣ ነው፡፡ የሃገራችን ዘውጌ ብሔርተኞች ንቃታቸውን ካሳዩባቸው አንዱ ስም የመቀየር ( የአማርኛ መጠርያ ስም የነበራቸው ግለሰቦች በመጡበት አከባቢ ቋንቋ ስማቸውን ማስለወጥ ) ሂደት ሲሆን በዋንኛነት ግን እነኚሁ “ንቁሃን” እራሳቸውን በቋንቋና በዘር በማቧደን  በተማሪዎች ማደርያ ዶርም ጭምር እየተሰባሰቡ  ሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎችን በማግለል እራሳቸውን በዘውግ እያደራጁና ከተቀሩት ተማሪዎች ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ መዘፈቃቸው ነበር፡፡ “የአጵሎስ እና የጳውሎስ”  (identity/alienation framework ) የሚለው ማዕቀፍ የሰመረላቸው ዘውገኞች ከሃሳብና ከቃላት ሙግት አልፈው ወደለየለትን መናረት ገብተው ነበር፡፡  በዚህ ረገድ የትግራይ ብሔርተኞች በቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ ( አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ) የትምህርት ፋካልቲ ከአማርኛ ተናጋሪ ተማሪዎች ጋር የነበራቸው ፀብ የሚታወስ ነው፡፡ ይህ የዘውግ ብሔርተኛነት አደረጃጀት ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሳይቀር ወርዶ ጀነራል ዊንጌት የተባለው አዳሪ ትምህርት ቤት የፀብ ማደራጃ ማዕከል ሆኖ እንደነበር ይነገራል፡፡  ለምሳሌ ጆን ያንግ የተባለው ካናዳዊ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የገበሬዎች አብዮት በኢትዮጵያ (Peasant revolution in Ethiopia) በተባለው መጸሐፉ እንደጠቀሰው መሰረት በ1960ዎቹ ወንጌት ትምህርት ቤት የቅርጫት ኳስ ሜዳ ላይ በተነሳ ግጭት የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስቴር መለስ ዜናዊ  (የያኔው ለገሰ ዜናዊ) ይመራ የነበረው የትግራይ ብሔርተኛ ቡድን ከኦሮሞ ብሔርተኛ ቡድን ጋር ከፍተኛ ግጭት ውስጥ ገብተው እስከ መናረት መድርሳቸውን   ያስነብበናል፡፡

 

የአማራ ጠሉ ብሔርተኝነት

 

ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ለዘመናት የኖረው የሁሉም የዘውጌ ብሔርተኞች ቋሚ ትርክት “ጨቋኝ የአማራ ገዢ  መደብ” የሚለው ጭፍን ፍረጃ ነው፡፡  በጣም  አክራሪ የተባሉት ዘውጌኞች የደርግ መንግስትን ጨምረው የአማራ ገዢ መደብ ብለው የዳቦ ስም ሲያወጡለት ጭምር ቅር እንኳን አይላቸውም፡፡  ከዘመናት ሙግትና እሰጣ ገባ በኋላ ከመሰንበቻው “አብዮተኛው” አቶ ለማ መገርሳ ጨቋኝ ገዢ መደብ እንጂ ጨቋኝ ብሔር  የለም የሚል መከራከሪያ  ስልጣን ላይ ካለው መንግስት ወገን ይዘው እስኪመጡ ድረስ ዋንኞቹ የዘውግ ፖለቲከኞችና “ምሁራን” የሚያምኑት አማራ ገዢ መደብ እንደ ነበር ነው፡፡ የአቶ ለማ እምነት ድርጅታዊ ሆኖ ኦሆዴድ በሰሞኑ ድርጅታዊ መግለጫው እንዳፀናው  ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያንስ የኦሮሞ ትግል የነበረው መደባዊ እንደ እና አሁንም ትግሉ መደባዊ ሆኖ መቀጠል እንዳለበት በድርጅት ደረጃ መተማመኛ ሰጥቷል፡፡ ወደ ቆየው ጉዳይ ስንመለስ የዘውግ ብሔርተኛነት በኢትዮጵያ ውስጥ ሲጠነሰስ አማራ ጠል ለምን ያበቃው መነሻው የኤርትራና የትግራይ ብሔርተኛነት አንቂዎች በፈጠሩት ጭራቃዊ ምስል (unfounded allegations)  እንደሆነ ታሪካዊ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 

በ1960ዎቹ በህቡዕ ተደራጅቶ የነበረው የትግራይ ብሔርተኛነት ማህበር በዋንኝነት ያነሳ የነበረው ተቀዳሚ ጥያቄ አማሮች ተቆጣጥረውታል በሚለው መንግስትና ቢሮክራሲ ውስጥ ከስልጣን ተገፍተናል የሚለውን ጥያቄ ነው፡፡ በእርግጥ በዘመኑ በነበሩ የታሪክ ተመራማሪዎች እንደ ተገለፀው በአማራና የትግራይ ሊሂቃን መካከል የነበረው አለመተማመን ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮች ጋር ይኖራል ተብሎ ከሚታሰበው በአንፃራዊነት ጠንከር ያለ እንደ ነበር ኪሊንበርግ እና ዛቫሎኒ የተባሉ  ፀሐፊዎች 1969 (እ.ኤ.አ) Nationalism and Tribalism በተባለው ጥናታቸው ላይ በጉልህ  አመልክተዋል፡፡  ምክኒያቱ ደግሞ  የስልጣን ይገባኛል ትግል ጉዳይ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በስልጣን እና በቢሮክራሲ ትግሉ አማሮችና ኦሮሞዎች የተሻለ ድርሻ ይዘዋል በሚል የትግርኛ ተናጋሪ ሊሂቃን ይሟገቱ ነበር፡፡  በወቅቱ የነበረውን ቅራኔ ለማጦዝ ይመስላል የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ የዩንቨርስቲ ተማሪ በነበሩበት ወቅት “የአደዋን ጦርነት ሚኒሊክ ሳይሆን የትግራይ ገበሬ ነው ተዋግቶ ያሸነፈው” የሚል ድምዳሜ የነበረው አነጋጋሪ የተባለና በወቅቱ ብዙ ጫጫታ የፈጠረ ፅሁፍ እስከ ማቅረብ የደረሱት፡፡

ይህ ማለት ግን በተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ የነበሩ የትግራይ ተወላጅ ታጋዮች ሁሉም  የትግራይ ብሔርተኞች ነበሩ ማለት ፈፅሞ  ስህተት ነው፡፡ ለምሳሌ የተማሪዎች መሪ ከነበሩት ውስጥ ጥላሁን ግዛውና መለስ ተክሌ የትግራይ ተወላጅ ቢሆኑም እንኳን በትግራይ ብሔርተኝነት ስማቸው አይነሳም ነበር፡፡ እርግጥ ነው አብዛኛው የኢህአፓ መስራችና መሪ የነበሩት ጉልቱ ፖለቲከኞች እነ ተስፋዬ ደበሳይ፣ ብረሃነመስቀል ረዳ፣ ዘሩ ክህሸንን የመሳሰሉት መገኛ ዘውጊያቸው ከትግራይ ቢሆንም ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ እንደነበሩ ይታመናል፡፡

እንግዲህ የዚያን ጊዜው የተማሪ ፋኖዎች በዋለልኝ አንቂነት ትግሉን ከመደብ ትግል ወደ ዜውጌ ማንነት ይከበር ብለው ሲያወርዱት እንደ ማርክሳዊና ሌኒንናዊ ተራማጅ ሃይል የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠልን የሚል ፅንፈኛ አቋምን ቢያንስ በመርህ ደረጃ ለማቀንቀን ድፍረት ነበራቸው፡፡ ከመርሁ በስተጀርባ የነበረው ማሳበብያ “እራስን ከአማራ ጨቋኝነት ነፃ ማውጣት ነው” የሚለው ኢትዮጵያን የመጥላትና የማስጠላት ደባ ነበር፡፡

በወቅቱ የነበሩት ኢትዮጵያዊ ግራ ዘመም የፖለቲካ ስብስቦች የራስን እድል በራስ መወሰን የሚለውን ጥያቄ ከፊት ሲያስቀድሙ ማርኪሳዊነታቸው እንዳይረክስ የተጠቀሙበት ማስመስያ አስቀድመን የብሔርን መብት ካስከበረን በኋላ መልሰን ወደ መደብ ትግል እንመለሳን በሚል ብረዛ ነበር፡፡  ይሁንና ትግራዋይ ታጋዮች ከመነሻውም አላቅማሙም። ከጅምሩ የሸዋን/ የአማራን የበላይነትና ፊውዳሊዝምን እንዋጋለን በማለት በረሃ የወረዱት፡፡ የዚያን ጊዜው የትግራይ ብሔራዊ ድርጅት /ትግራይ ናሽናል ኦርጋናዜሽን/ የበኋላው ህወሓት የተመሰረተው ደርግ ስልጣን በያዘ 6 ወራት ውስጥ ሲሆን እንታገለዋለን ያሉት “የአማራ ገዢ መደብም” ሆነ ፊውዳልዚም በአብዮት የተወገዱበት ወቅት ነበር፡፡

 

የህወሓት ማንፌስቶ

የመጀመሪያው የህወሓት ማኒፌስቶ በጉልህ  እንዳስቀመጠው ተቀዳሚው የህወሓት የትግል አላማ ነፃና ዴሞክራትክ ሪፐብሊክ ትግራይን መመሥረት እንደሆነ ያትታል፡፡ ያ ማኒፌስቶ በግልፅ እንደ ሚጠቅሰው ከአፄ ዮሃንስ 4ኛ ሞት በኋላ ትግራይ ሉአላዊነቷንና ነፃነቷን በጨቋኛ አማራ አጥታለች በማለት በይፋ ያስቀምጣል፡፡ በኋላ ላይ በአመራር ውስጥ በነበረ መከፋፈል ማኔፌስቶውን ቢስቡም እስከ መጨረሻው የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚለውን አቋምን አጥብቆ በመያዝ ከአመታት በኋላ እንኳን ከተቀረው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር አብሮ ለመቀጠል ሲወስን ይሄው መርሆ  ሳይቀየር መኖር እንችላለን የሚል የታክቲክ ለውጥ የመጣው፡፡

በወቅቱ የድርጅቱ መሪ የነበሩት አቶ ስብሃት ነጋ ከቀድሞው የድርጅቱ አቋም የለዘበ  በተባለው የ 1972 ንግግራቸው ለህወሓት የብሄር ጥያቄ ቀዳሚው እና ዋንኛው ጉዳዩ  እንደሆነ በማጉላት  “የኢትዮጵያ አንድነት የትኛውም ዋጋ ተከፍሎ  መጠበቅ አለበት በሚለው ሃሳብ አናምንም” በማለት የድርጅቱን የመገንጠል ሃሳብ እንዳልተውት አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ በዚህ መርሆ የተመራው የዘውግ ብሔርተኝነት ትግል ፍሬ አፍርቶ ለአቅመ  ስልጣን ሲበቃ ያንኑ የመገንጠል ጉዳይ አቋምን  የሃገሪቱ የህገ-መንግስት ልዩ መገለጫ አንቀፅ ለማድረግ  በቅተዋል፡፡

ህወሓት መገንጠልን አልሞ ተነስቶ ተከዜን  ምን  አሻገረው?

ከወሓት አቋም አንፃር ብዙዎችን የሚስደንቀው ሲጀመር መገንጠልን አላማ አድርጎ  በረሃ ከወረደ በኋላ ሃገሬ ያላትን ትግራይን ነፃ አውጥቶ ሲያበቃ ምን ወደ መሃል ሃገር እንዲገሰግስ የሚያስችል የአቋም ለውጥን ከየት አገኘው የሚለው ጉዳይ ነው፡፡  አዎን ህወሓት ትግራይን በወቅቱ ከነበረው አገዛዝ ስር  በነሐሴ 1981 ሙሉ በሙሉ ነፃ አውጥቷል፡፡  የወቅቱ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት መንግስቱ ሃይለ ማርያም ለሽንፈታቸው መደበቂያ ሲናገሩ ከሞላ ጎደል “ትግራይ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው አንዳች ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የለም፡፡ ወርቅ አይታፈስበት፣ ዘይት አይመረትበት እንደውም ክፍለ ሃገሩ ከሌላው አከባቢ በሚደረግ ፈሰስ ድጎማ ነው የሚተዳደረው” እስከ ማለት ደርሰው ነበር፡፡  ከሰሞኑም ይሂዱልን የሚለውን አቋም ሲራምዱ የሰነበቱ የሙሉ ሃገርነት ክብርና ዋጋው ያልታያቸው  በሌላኛው ጠርዝ ላይ የቆሙ ዘውጌኞች ይህንኑ ስንኩል አመለካከት ሲያስተጋቡ ተደምጠዋል፡፡ ዋናው ነገር ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመነጠል የተነሳዉ ሃይል አላማው ከተሳካለት በኋላ ምን ሲያሮጥ ሸዋ አዲስ አበባ  አደረሰው የሚለው ጉዳይ ነው፡፡

ህወሓት ከትግራይ ለመሻገር የጥንቱን ኢህዴን የዛሬውን ብአዴንን ጨምሮ የጦር ሜዳ ምርኮኛ  መኮንኖችን  በመሰብሰብ ከትግራይ ነፃ አውጪነት ወደ ኢትዮጵያ ገዢነት የሚያሸጋግረውን ኢህአዴግ የተባለውን ግንባር በመመሥረት ግስጋሴውን ወደ ሚኒሊክ ቤተ መንግስት ሲያደርግ፣ ቆይቶም የዛሬውን አያድርገውና የትላንቱን ኦሆዴድ ጠፍጥፎ  ሰርቶ መንገድ ምራ ሲል ያልተጠበቀ ተቃዋሞ  የገጠመው ከራሱ ታጋዮች ነበር፡፡ የተነሳነው ትግራይን ነፃ ለማውጣት ነው ….. ትግራይ ነፃ ከወጣች ከዚህ በላይ አንቀጥልም ብለው አስር ሺ የሚደርሱ ታጋዮች ከጎንደርና ከወሎ ወደ ትግራይ ተመልሰው ሄደዋል፡፡ የህወሓት አመራር ወደ ነፃይቱ ትግራይ  የሚመለሰውን ተዋጊ አሳምኖ በሙሉ አቅም ወደ ወጊያው ለመመለስ አንድ ዓመት ያህል ፈጅቶበታል፡፡   ታጋዩን ለማሳመን የቀረበው ሁለት ዋንኛ ምክንያቶች ነበሩ፡፡  አንደኛው ማሳመኛ የነበረው ደርግን አሸንፈን ስልጣን ካልያዝን እንደ መጀመሪያው ወያኔ ንቅናቄ በአውሮፕላን ደብድቦ መልሶ ትግራይን ይቀማናል የሚል  ማስፈራሪያ ነበር፡፡  በሁለተኛ ደረጃ የቀረበው ማሳመኛ ካህናትን ተጠቅሞ  ሃይማኖታዊ ስብከት ማቅረብ ነበር፡፡  ምንም እንኳን የህወሓት አመራር እና ካድሬ በዳይሌክቲካል ቁሳካላዊ የተፈጥሮ  ሂደት  የሚያምን እና ለሃይማኖት ግድ የማይሰጥ ቢሆንም አብዛኛው ብረት ተሸካሚ የገበሬ ጦር  በመሆኑ እምነቱን አጥባቂ ነበር፡፡  በመሆኑም ትግራይ ከተገነጠለች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን መነጠል ይሆንብናል እና የግድ ኢትዮጵያን መያዝ አለብን የሚለው ማሳመኛ ነው  ጠመንጃቸውን ወልውለው ታጋዮቹ  ዳግመኛ ቃታ ወደ መሳብ የገቡት፡፡

በወቅቱ የህወሓት መሪዎች እውነተኛ አላማ የኢትዮጵያን መዕከላዊ መንግስት በመቆጣጠር ከስልጣኑ የሚገኘውን ሃይል በመጠቀም ሃገሪቱን ሃብት መዝረፍና ለግል ጥቅም ማዋል እንደ ሆነ በህይወት ከርመው ሸገር የገቡት ታጋዮች የማታ ማታ ሳይገለጽላቸው አልቀረም፡፡ ከምርም የትግራይን ህዝብ ከተቀረው ወንድም እና እህቱ ጋር መነጠል ባያስፈልግ ኖሮ ከጥንት እስከዛሬ የህወሓት ካድሬዎችና ደጋፊዎች የመገንጠል ጥያቄ የተገባ አይደለም የሚል አመክንዮ ሲቀርብ ባላንዘፈዘፋቸው ነበር፡፡ ዋናው ነገር አብዛኛው የትግራይ ህዝብ በኢትዮጲያዊነቱ እንደማይደራደር የሚታመን ቢሆንም ዛሬ ላይ ከውስጡ የበቀሉ ሊሂቃን በመንፈስም በአካልም ከኢትዮጵያ ሊነጥሉት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን አይረዳዉም ተብሎም አይታመንም፡፡

ፍቺ አልባዉ የመገንጠል ጥያቄ   

ህወሓትን እና ደጋፊዎቹን መገንጠል ከሚለው ልክፍታቸው ሊያላቅቃቸው የሚችል ፍቱን መድሃኒት ምን ይሆን? ለትግል ሲወጡ አንስቶ መገንጠልን አላማ ያደረጉ ሃይሎች የሃገሪቱ ፍፁም ስልጣንን በተቆጣጠሩበት ዘመንም መገንጠል የሚለውን ዕሳቤ ከልቦናቸው አልፋቁትም፡፡ እነሆ ዘንድሮ “እስኪ በቃችሁ  ብዙ ገዝታችኋልና ደከማችሁ” ሲባሉ  ደግሞ እንኳን እናቴ ሞታብኝ እንደውም አልቅስ አልቅስ ይለኛል እንዲሉ አበው፣ ስልጣን በቃችሁ ከተባልንማ ሁለተኛ አማራጭ  (plan B) አለን ሲሉ ይደመጣል፡፡ አንዳንድ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን ከመፍታትም በላይ የሚሆኑበት  አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ከነዚህ ጥያቄዎች አንዱ የህወሓት ፖለቲካዊ መስመር ነው፡፡

 

የመገንጠል ጥያቄን ሲያነሳ ህወሓት በአለም ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም አይደለም፡፡ ልዩ  የሚያደርገው መንግስት ሆኖም የመገንጠል ጥያቄ አራማጅ መሆኑ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የዘውግ ብሔርተኛነት በናኘበት የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ ተጨቁነናል የሚሉ ሃይሎች የመገንጠል ጥያቄን በመያዝ በተለያየ መንገድ ሲታገሉ ኖረዋል፡፡ የተሳካላቸው እንዳሉ ሁሉ ያለሆነላቸውም ጥቂት አይደሉም፡፡  የሃገርን ግዛታዊ አንድነትን ከማስጠበቅ አንፃር ከማዕከላዊ መንግስት በዋንኛነት ሁለት የፖሊሲ አቋም ይቀርባል፡፡ አንደኛው ተገንጣዮችን በሃይል የመደምሰስ (repression) አማራጭ ሲሆን ፣ ሁለተኛውና በብዙ የፖለቲካ ሊሂቃን የሚመረጠው አቋም አካታች የፖለቲካ መደላደል  (responsive or representative types of power-sharing)  መፍጠርን ነው፡፡ የመጀመሪያው አማራጭ ከአጭር ጊዜ አንፃር ቢሳካ እንኳን ዘላቂነቱ አስተማማኝ አይሆንም፡፡   ሁለተኛው  መንገድ የበለጠ ተመራጭ እንዲሆን የሚያደርገው መሰረታዊ ጉዳዮችን ለመመለስ የሚያስችል ዘዴ ስለሆነ ነው፡፡  በበርካታ የፖለቲካ ተመራማሪዎች እንደሚመከረው  ለመገንጠል የሚነሱ መከራከሪያዎችን ለማስጣል ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል በክልሎች፣ በሃይማኖት ተከታዮች፣ በዘውጌ ፖለቲከኞች ወይንም በሌላ በየትኛውም የቡድን ስብስቦች የሚነሱ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን ለማስታገስ የሚስችሉ ፖለቲካዊና ተቋማዊ ለውጦችን ማበጀት የተገቢ ይሆናል፡፡ የነዚህ ለውጦች ማስፈፀሚያ መንገዶች መካከል ተበደልን የለሚሉ አካልትን መካሻ የሚሆን ማበረታቻ ዘዴ ማበጀት (affirmativeaction)፣ የባህል ብዝሃነትን ማስጠበቅ (multiculturalliberalism) ፣ ፌደራሊዝም፣ የራስ ገዝ ስረዓተን መፍቀድ፣ እና ስልጣን ማጋራትን ያጠቃልላ፡፡ ህወሓት ለለሚያነሳቸው የመገንጠል ጥያቄ  እነኚህ ምላሾች መፍትሄ መሆን የሚችሉ ቢሆን ኖሮ የመገንጠል ጥያቄ የማዕከላዊ መንግስት ስልጣንን ግንቦት 1983 ሲቆጣጠር ከመነጠል አላማው ጋር ሙሉ በሙሉ በተፋታ ነበር፡፡ ከቀረቡት አማራጮች በላቀ  መልኩ “ከተጨቋኝነት” ወጥቶ ጨቋኝ ቢሆንም መገንጠልን ዋንኛው የፖለቲካ ምህዋሩ አድርጎ መቀጠሉ የድርጅቱን አቋም ከእውናዊ ሳይንስ ውጪ ያደርገዋል፡፡ ሃበሻ ለነገሩ ወለፈንዲ ሲያጣ ልክፍት ነው የሚለው ነገር አለው፡፡  ህወሓትን እና ጭፍን  ደጋፊዎቹን ከመገንጠል ፖለቲካዊ ልክፍታቸው ይፈውሱ ዘንድ መልካም ከመመኘት የተሻለ ምን ደህና ነገር ይገኝ ይሆን?

 

ቸር ያቆየን!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.