ሰማዕታቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ እና ብፁዕ አቡነ ሚካኤል

እንኳንስ ሕዝቡ ምድሪቱም [ኢትዮጵያም] እንዳትገዛላቸው አውግዣለሁ።”                      

የሁለቱም ብፁዓን አባቶች ቃል

መግቢያ

‹‹አርበኞች መሞትን ማን አስተማራቸው

አቡነ ጴጥሮስ ነው ባርኮ የሰጣቸው፤

ሚካኤል ቀድሞ መንገድ ቢመራቸው

በኦሜድላ በኩል ብርሃን ወጣላቸው፡፡››

(ቀኝጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከኢትዮጵያውያን የሃይማኖት አባቶች መካከል እየመረጠች የራሷን ጳጳሣትና ፓትርያርክ መሠየም ከመጀመሯ በፊት፣ ይህንን ሥልጣን ከ1,700 ዓመታት ለማያንስ ጊዜ ተቆጣጥረው የኖሩት በግብፅ የቆጵጥ ቤተክርስቲያን የሚሾሙ መነኮሣት ነበሩ። ሆኖም ከቆጵጦች ቤተ ክርስቲያን ጋር በተደረገው ረዥምና እልህ አስጨራሽ ድርድር በኋላ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በ፲፱፻፳፩ ዓ.ም. አምሥት ኢትዮጵያውያን መነኮሣት እስክንድርያ (ግብፅ) ድረስ ሄደው ጳጳስነት ተቀቡ። እነርሱም፦ አቡነ አብርሃም፦- (የጎንደር እና የጎጃም ጳጳስ) ፣ አቡነ ይስሃቅ (የትግሬ እና የስሜን ጳጳስ) ፤ አቡነ ጴጥሮስ (የወሎ እና የላስታ ጳጳስ) ፣ አቡነ ሚካኤል (የኢሉባቡር እና የምዕራብ ኢትዮጵያ ጳጳስ) እና ጵጵስና ከተቀበሉ በኋላ ብዙም በሕይወት ያልቆዩት አቡነ ሣዊሮስ ነበሩ። ፋሽስት ጣሊያን በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. ኢትዮጵያን ሲወር በተፈጠረው የፖለቲካ ሁኔታ እኒያ ጳጳሶች የተለያዩ አቋሞችን ያዙ። አቡነ ሚካኤል እና አቡነ ጴጥሮስ ለአገራቸውና ለቤተ ክርስቲያናቸው ታማኝ ሆነው ‘መንጋችንን ለነጣቂ ፋሽስት ተኩላ በትነን አንሄድም‘ ብለው በፋሽስቶች እጅ ሰማዕትነትን ሲቀበሉ፣ ግብፃዊው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ ወደ ካይሮ አመሩ፤ በተቃራኒው ደግሞ ትውልዳቸው ከትግራይ የሆኑት አቡነ አብርሃም እና አቡነ ይስሃቅ የወራሪው ጠላት የፋሽስት ጣሊያን አገልጋዮች መሆንን መረጡ። ፋሽስት ጣሊያን ሲባረር ለሰማዕቱ ለአቡነ ጴጥሮስ መታሠቢያ አራዳ ጊዮርጊስ አጠገብ ኃውልት ቆመላቸው፣ ይህንን ኃውልት አሁን ያለው አገዛዝ በ፪ሺህ፮ ዓም አንስቶት እንደነበረ እና በኋላ ወደቦታው እንደመለሰው ይታወቃል። ለአቡነ ሚካኤል ግን እስከ ፪ሺህ፰ ዓ.ም. ድረስ ሐውልት ባይሠራላቸውም መሥዋዕትነት በተቀበሉበት በጎሬ ከተማ (ኢሉባቦር) አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በስማቸው ተሠይሞላቸው ቆይቷል። ሆኖም ቢዘገይም ግንቦት ፲፬ ቀን ፪ሺህ፰ ዓ.ም. በተሰውባት የጎሬ ከተማ ኃውልት ቆሞላቸዋል። ከዚህ ቀጥሎ በ’ሐመር መጽሔት‘ እና በሌሎች ምንጮች በተለያዩ ጊዜያት ለንባብ ከበቁ ጽሑፎች ስለሁለቱ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ሰማዕታትና የሃይማኖት መሪዎች አጭር የሕይወት ታሪክ ተጠናቅሮ ቀርቧል።

ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ[1]

(ከመስከረም ፲፰፻፸፭ ዓ.ም. ሐምሌ ፳፪ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. )

አቡነ ጴጥሮስ በልብሰ-ጵጵስና ……«ሐምሌ 22 ቀን 1928 ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተንጠቀቅ ቆሙ። ወዲያው አዛዡ «ተኩስ» በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቷቸው። ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ። መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ። ከዚያም ሌላ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው። ………  

 

፲፰፻፸፭ ዓ.ም. (እኤአ 1882) በሰሜን ሸዋ አገረ ስብከት ፣ ሰላሌ አውራጃ ፣ በፍቼ ከተማ ተወለዱ። ወላጆቻቸው ዕድሜያቸው ገና በወግ ለትምህርት ሳይደርስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ «ባሕታዊ ተድላ» ለተባሉ መምህር አደራ ሰጧቸው። በዚያው ገዳም የንባብ ቤቱንና የዜማውን የትምህርት ደረጃዎች በሚያስገርም ሁኔታ በአጭር ጊዜ አቀላጥፈው በመጨረስ ገና በልጅነት የዕድሜ ደረጃቸው ሦስተኛውን የቅኔ ትምህርት ጀምረው በአጭር ጊዜ ሙሉ ቤት ተቀኙ። ይህንኑ የቅኔ ትምህርት ለማስፋፋት በምዕራብ ጎጃም አገረ ስብከት ወደሚገኘው የቅኔ ትምህርት ማዕከል ዋሸራ ተሻግረው ለመምህርነት የሚያበቃውን ትምህርት ፈጽመው አስመሰከሩ። ከዚያም ከቅኔው ዐውድማ ጎጃም ወደ ዜማው አዝመራ ጎንደር ተሻገሩ። በዚያም እንደ ቅኔው ሁሉ እስከ ማስመስከር ባይደርሱም የዜማውን ትምህርት በአጥጋቢ ሁኔታ ቀጸሉ። ከጎንደርም በወቅቱ ወሎ አቅንተው፣ ቦሩ ሜዳ ከተባለው ቦታ ላይ ወንበር ዘርግተው የመጻሕፍትን ምሥጢር  በየዓይነቱ ሲመግቡ ወደ ነበሩት ስመ ጥሩው መምህር አካለ ወልድ ዘንድ በመሔድ ዋና ዋናዎቹን የመጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርቶች ማለትም ብሉያትን ፣ ሐዲሳትንና ሊቃውንትን በብቃት አሔዱ።

ከዚህ በኋላ ልክ በ፲፱፻ ዓ.ም. እዚያው ወሎ ፣ አማራ ሣይንት በተባለው ቦታ ወደሚገኘው ምስካበ ቅዱሳን ገዳም በመሔድ ወንበር ዘረጉ። በዚያው ቦታ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ቅኔንና መጻሕፍትን አስተማሩ። በዚህ ዓይነት በመማርና በማስተማር ራሳቸውን በእግዚአብሔር ቃል በሚገባ ከጐሰሙ በኋላ በ፲፱፻፱ ዓ.ም. ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመሔድ ሥርዓተ ምንኩስናን ፈጸሙ። ብዙም ሳይቆዩ ማዕረገ ቅስናን ተቀብለው ከወንበሩ አገልግሎት ጋር የቤተ መቅደሱን ተልእኮም ደርበው ያዙ።

በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. አረመኔው የኢጣልያ ፋሺስት በግፍ አገራችንን ለመውረር «ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት» በማለት ውቅያኖስ አቋርጦ በመምጣት ኢትዮጵያን ሲወርና ሕዝቧን እና ሊቃውንቷን በግፍ ሲጨፈጭፍ ፣ ገዳማቷን እና አድባራቷን ሲያረክስ ያዩት ብፁዕነታቸው ፣ ወራሪውን ኃይል ከኢትዮጵያውያኑ አርበኞች ጋር በመሆን በጸሎት ሊዋጉት ቆረጡ። የወቅቱ የአገሪቱ መሪ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት [ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ] በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከአረመኔው ፋሺስት ጦር ጋር በመፋለም ላይ የነበረውን አርበኛ ለማበረታታት ወደ ማይጨው በሔዱ ጊዜ ብፁዕነታቸውም ተከትለው ሔዱ። ከዚያ እንደ ተመለሱም በታላቁ የደብረ ሊባኖስ ገዳም ተሰባስበው የቤተ ክርስቲያን አምላክ በኢትዮጵያውያን ላይ የመጣውን ችግር እንዲያስታግሥ በጸሎት እየተጉ ወደ ነበሩት አባቶችና አርበኞች በመሔድ ለአገርና ለነጻነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን በመስበክ ሁሉም እንዲጋደሉ ማሳሰብ እና ማትጋት ጀመሩ። ኋላም “የገዳሙ መነኮሳትና የሰላሌ አርበኞች” ይባሉ ከነበሩት አርበኞች ጋር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ፋሽስቶችን ለማባረር በተደረገው ያልተሳካው ጦርነት ተሳታፊ ሆኑ። ከዚያም አርበኞቹ የቻሉትን ሁሉ አድርገው ወደ ሰላሌ ሲመለሱ ብፁዕነታቸው አዲስ አበባ ቀሩ። ብዙም ሳይቆዩ በጠላት እጅ ተያዙ።

ብፁዕነታቸው በተጠቀሰው ቀን በጠላት እጅ ከወደቁበት ቀን ጀምሮ በፋሺስት ኢጣልያ የጥይት እሩምታ በሰማዕትነት እስካለፉበት ጊዜ [ሐምሌ ፳፪ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም.] ድረስ የነበረውን ሒደት የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጋዜጠኞችና የታሪክ ጸሐፍት እንደሚከተለው ዘግበውታል።

«በኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፤ ተከታዮቼን ግን አትንኩ»

የሚለውን ቃለ-ምዕዳን ለገዳዮቻቸው ፋሺስቶች ያስተላለፉት ስለ አገር ነጻነት ፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ክብር ፣ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ሲሉ በሰማዕትነት ያረፉት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ናቸው። ይህንንም የተናገሩት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም ደኅንነት ሕይወቱን ለመስጠት በዚያች በመከራ ሌሊት ሊይዙትና ሊገድሉት ለመጡት ለሮማውያን ጭፍሮች ማንን ትፈልጋላችሁ? እኔ እንደ ሆንኩ አለሁላችሁ። እነሱን ግን ተዉአቸው ይሒዱ” /ዮሐ. ፲፰፥፰/  ሲል በተከታዮቹ ላይ መከራእንዳይፈጽሙባቸው የተናገረውን ቃል ለሕይወታቸው መመሪያ በማድረግ ፣ መስቀሉንም ተሸክመው በኋላ ለመከተልና ፍኖተ-መስቀሉንም ተጉዘው የሰማዕትነት አክሊል ለመቀዳጀት ቆመው ሞትን የሚጠባበቁበት ዕለት ሐምሌ ፳፸ ቀን ፲፱፻፳፰  ዓ.ም.  ( እ.ኤ.አ. July 29, 1936 ) ነበር።

ሰኔ ፰ ቀን ፲፱፳፰ ዓ.ም. ( እ.ኤ.አ. June 15, 1936 ) አዲስ አበባ የገባው ቺሮ ፓጃሊ “ከሪያሬ ዴስራ” የተባለው ጋዜጣ ወኪልና የምሥራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረ ሲሆን ስለ አቡነ ጴጥሮስ የተሰጠውን ፍርድና የተፈጸመውን ግድያ ባየውና በተመለከተው መንገድ እንደሚከተለው ጽፎ ነበር።

«ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም. አቡነ ጴጥሮስ ተይዘው ወደ ግራዝያኒ ቀረቡ። በዚህ ጊዜ አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊው ጳጳስ ቀርበው ለእስክንድርያው መንበረ ፓትርያርክ ምክር ቤት ሳታሰማ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ አንዳች ነገር ማድረግ አይገባህም ሲሉ ለግራዝያኒ ነገሩት። ምክንያቱም ይላሉ አቡነ ቄርሎስ ፤ አቡነ ጴጥሮስ ታላቅ ሰው ናቸው። በመሠረቱ ሊያዙ ባልተገባ ነበር። ከተያዙም ደግሞ ልትገድላቸው ትችላለህ። ነገር ግን በርሳቸው ላይ የምታደርገውን ነገር ሁሉ ለእስክንድርያው መንበረ ፓትርያርክ ምክር ቤት ሳታሰማ ምንም ማድረግ አይገባህም» አሉት። «በኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፤ ተከታዮቼን ግን አትንኩ»

አቡነ ቄርሎስ ይህን ማለታቸው በዲፕሎማቲክ ደረጃ ለዓለም ለማሰማትና የአቡነ ጴጥሮስን ሕይወት ለማትረፍ አስበው እንደ ነበር ግልጥ ነው። ነገር ግን ግራዝያኒ ይህ የአቡነ ጴጥሮስ የሞት ፍርድ እንኳንስ እስከ ግብፅ ከአዲስ አበባ ውጭ እንኳ ከመሰማቱ በፊት በግማሽ ቀን እንዲፈጸም ትእዛዝ አስተላለፈ።

ጸሐፊው ሲገልጥ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረዘም ፣ ፊታቸው ዘለግ ያለ ፣ መልካቸው ጠየም ያለ ፣ ዐዋቂነታቸውና ትሕትናቸው ከገጻቸው የሚነበብ ሲሆን ፣ በዚህ ጊዜ ለብሰውት የነበረው ልብሰ ጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የተበከለ ነበር። በዚህ ሁኔታ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ። ለፍርድም የተሰየሙት ዳኞች ሦስት ሲሆኑ እነዚህም ጣልያኖችና የጦር ሹማምንት ናቸው። የመካከለኛው ዳኛ ኮሎኔል ነበር። የቀረበባቸውም ወንጀል ‘ሕዝብ ቀስቅሰዋል ፣ ራስዎም ዐምፀዋል ፣ ሌሎችንም እንዲያምፁ አድርገዋል’ የሚል ነበር። ዳኛውም «ካህናቱም ሆኑ የቤተ ክህነት ባለሥልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የኢጣልያን መንግሥት ገዥነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን ዐመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ?» ሲል ጠየቃቸው። አቡነ ጴጥሮስም የሚከተለውን መለሱ። «አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም። እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ። ኃላፊነትም ያለብኝ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ። ስለዚህ ስለ አገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ። ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም። ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ። እኔን ለመግደል እንደ ወሰናችሁ ዐውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ። ግን ተከታዮቼን አትንኩ» አሉ።

አስተርጓሚ ዳኞች የሚሉትን ብቻ ከማስተርጐም በቀር ጳጳሱ የሚናገሩትን ሐቀኛ ንግግር አላስተረጐመም። እኔ እንኳን የሰማሁት በአዲስ አበባ ለሠላሳ ዓመት የኖረው የእቴጌ ሆቴል ኃላፊ የነበረው የግሪክ ዜጋ ማንድራኮስ አጠገቤ ተቀምጦ ስለ ነበር የተናገሩትን ሁሉ ስለ ገለጠልኝ ነው። እኔ እንደ ሰማሁት ፍርዱን ለመስማት በብዛት የተሰበሰቡት ጣልያኖችና ታዝዞ የወጣው የአዲስ አበባ ሕዝብ ሐቀኛ የሆነውን ንግግራቸውን ቢሰሙ ኖሮ ልባቸው ይነካ ነበር» ይላል። ሆኖም አስተርጓሚው በጳጳሱ ላይ ተጽዕኖ ስላሳደረባቸው እውነተኛ ንግግራቸው ሳይገለጥ እንደ ቀረ ይጽፋል። ቀጥሎም ብፁዕነታቸው በፍርድ ችሎት ላይ እንዳሉ ሕዝቡ ሁሉ ስለ እርሳቸው እያዘነ ሳለ መስቀላቸውን አውጥተው እየጸለዩ ሕዝቡን ባረኩ። ወዲያው የሞታቸው ሰዓት መድረሱን ዐውቀው ሰዓታቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ተመለከቱ። በዚህ ጊዜ ሁሉ ምንም ፍርሃት አይታይባቸውም ነበር። የሞታቸውን ፍርድ ያነብ የነበረው ኢጣልያዊ ዳኛ ግን ይንቀጠቀጥ ነበር። ታላቅ ፍርሃትም በፊቱ ይታይ ነበር።

«ይሙት በቃ» የተፈረደባቸው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በችሎት ፊት ለብዙ ሰዓታት ቆመው ስለ ዋሉና ደክሟቸው ስለ ነበር ለመቀመጥ ፈልገው ዳኛውን በትሕትናና በፈገግታ ጠየቁት። እንዲቀመጡም ፈቀደላቸው። በመጨረሻም የሞታቸው ፍርድ ከተነበበ በኋላ የፈረዱባቸውን ዳኞች ጸልየው በመስቀላቸው ባረኳቸው። ብፁዕነታቸው እስከ መቃብር አፋፍ ድረስ የፍርሃትና የድንጋጤ ምልክት ያይደለ ከልብ የሆነ ፍጹም የክብር ትሕትና ይታይባቸው ነበር።

የአገራቸው በጠላት መወረር፣ የሕዝባቸው መገደልና መታሰር፣ የቤተ ክርስቲያናቸው መደፈር እስከ ሞት ያደረሳቸው እኒህ እውነተኛ ጳጳስ ለመገደል ሲወሰዱ ጥይት አልፎ ሌላ ሰው እንዳይጐዳ ግንብ ይፈለግ ጀመር። ሩቅ ባለመሔድ ከመካነ ፍትሑ አሥር (10) ሜትር ርቆ ግንብ ያለው መግደያ ቦታ ተገኘና ወደዚያ ተወሰዱ። ከገዳዮቹም አንዱ «ፊትዎን ለመሸፈን ይፈልጋሉን?» ሲል ጠየቃቸው። «ይህ የአንተ ሥራ ነው» ሲሉ ብፁዕነታቸው መለሱ። ከመግደያውም ቦታ እንደ ደረሱ ወንበር ቀረበላቸውና ፊታቸውን ወደ ግንቡ ጀርባቸውን ወደ ሕዝቡ አድርገው እንዲቀመጡ ሆኑ። ከዚያ በኋላ ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተንጠቀቅ ቆሙ (ቆዩ)። ወዲያው አዛዡ «ተኩስ» በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቷቸው። ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ። መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ። ከዚያም ሌላ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው። የብፁዕነታቸው አስከሬን ማንም እንዳይወስደው በአስቸኳይ ከአዲስ አበባ ውጭ ማንም በማያውቀው ቦታ በምሥጢር እንዲቀበር ተደረገ። በዚያች ሌሊት በአዲስ አበባ ውስጥ በየቤቱ ልቅሶና ዋይታ ሆነ» ሲል ጽሑፉን ይደመድማል። ይህም ጠላት የሰጠው ምስክርነት በካቶሊካዊው ፓፓ ቡራኬ አገራችንን የወረረውን የፋሺስት ኢጣልያን ጦር አረመኔነትና በአንጻሩ የታየውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ጀግንነት ሲያረጋግጥ ይኖራል።

በተጨማሪም ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ «አቡነ ጴጥሮስ እንዴት ሞቱ?» ሲል ሙሴ ፓይላክን ጠይቋቸው እርሳቸውም የሚከተለውን ተናግረዋል። «አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉ ዕለት እዚያው ነበርኩ። መጀመሪያ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተሳለሙት። ቀጥለውም የያዙትን መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ። የኪሳቸውንም ሰዓት አውጥተው ካዩ በኋላ መልሰው ከኪሳቸው ከተቱት። ወዲያው ወታደሮች በእሩምታ ተኩሰው ገደሏቸው። ይህ እንደ ሆነ አስገዳዩ ኮሎኔል ተመልካቹን ሕዝብ አጨብጭቡ ብሎ አዘዘና ተጨበጨበ።

ማታ ከአስገዳዩ ኮሎኔል ጋር ተገናኝተን ስንጫወት «በዚህ ቄስ መገደል እኮ ሕዝቡ ተደስቷል» አለኝ። «እንዴት?» ብለው «አላየህም ሲያጨበጭብ?» አለኝ። እኔም «ባታውቀው ነው እንጂ የሕዝቡ ባሕል ሲናደድም ያጨበጭባል» አልኩት። «እንዴት?» ቢለኝ እጄን እያጨበጨብኩ አሳየሁት። እሱም አሳየኝ። «ከዚህ በኋላ የሆነው ቢሆን እኔ ትልቅ ማስታወሻ አግኝቻለሁ» ብሎ አቡነ ጴጥሮስ ሲገደሉ ይዘውት የነበረውን መስቀልና መጽሐፍ ቅዱስ፣ የኪስ ሰዓታቸውን ጭምር አሳየኝ። መጽሐፍ ቅዱሱ መሐል ለመሐል በጥይት ተሰንጥቋል። መስቀሉም ልክ በመሐከሉ ላይ ጥይት በስቶት ወጥቷል። የኪስ ሰዓታቸውንም እንዳየሁት እንደዚሁ ጥይት በስቶታል» ብለው ያዩትን መስክረዋል።» (ትንሣኤ፣ ቁጥር 58፣ 1978 ዓ.ም.)።

የብፁዕነታቸው አኩሪ ታሪክ ትውልድ ሲያዘክርላቸው እንዲኖር መታሰቢያ ይሆናቸው ዘንድ ሐምሌ ፲፮ ቀን ፲፱፻፴፰ ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ እምብርት ኃውልት ቆሞላቸዋል።

የሃይማኖት ተጋዳዩና ሰማዕቱ አባታችን በረከት ይደርብን። አሜን!

 

ማዕቱ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል[2]

ከ፲፰፻፸ ዓ.ም. – ኅዳር ወር ፲፱፻፳፱ ዓ.ም.

የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ታላቅ ተግባርና መስዋዕትነት በተነሣ ቁጥር አብረው በታሪክ የክብር ዘላለማዊ መዝገብ ውስጥ የሚነሡ ታላቅ የአገርና የቤተ ክርስቲያን አባት አሉ ፣ አቡነ ሚካኤል ዘጎሬ። ሁለቱም ብፁአን ፣ አባቶች አቡነ ጴጥሮስ እና አቡነ ሚካኤል ፣ በቤተ ክርስቲያን አባትነት ከነበራቸው አንድነት በተጨማሪ ፣ በተራራቀ ቦታ ሆነው እንኳን ከነበራቸው የመንፈስ ቁርኝት በተጨማሪ፣ በመስዋዕትነታቸው ውኅደት በታሪክ ይታወሳሉ።

ስለ እኚሁ ታላቅ የአገርና የቤተ ክርስቲያን አባት አቡነ ሚካኤል፣ ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ የኢትዮጵያና ሕዝቧ ፅኑ ወዳጅ የነበሩት ስዊድናዊ ኮሎኔል ካውንት ካርል ጉስታፍ በንሮዝን የሰጡት የምስክርነት ቃል እንዲህ ይጠቀሳል።

‹‹ፎከር የምትባለውን አውሮፕላን እያበረርኩ በጎሬ አቅራቢያ አረፍኩ። በምዕራብ ኢትዮጵያ የነበሩትን ስደተኞች አግኝቼ በራስ እምሩ ይመራ ለነበረውም ጦር መገናኛ ከፈትኩ። ጎሬ እንዳረፍኩ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል አስጠሩኝ። “በእርግጥ አንተ ዘመዶችህን ከድተህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማገልገል ወሰነሃልን? ክርስቲያን ነኝ ብለኸኛል፡፡ ለዘመዶችህ ሳታደላ ለዚች ለተጨነቀች አገር ከልብህ ለመሥራት መወሰንህን መስቀሌን በመምታት ማልልኝ” ሲሉኝ የአገር ፍቅር እንዳቃጠላቸው ተሰማኝ። “ጓደኞቼ በዕለት ጥቅም እየተደለሉ ለጠላት ማደራቸውን ስሰማ በጣም አዘንኩ። ሌላው የልብ ጓደኛዬ አቡነ ጴጥሮስ ግን ለጠላት አልገዛም ብለው ለመስዋዕትነት መቃረባቸውን ሰሰማ በጣም ደስ አለኝ። ይህ ነው መሃላን ማክበር። እኔም የምከተለው የጴጥሮስን ፈለግ ነው” ብለው አጫወቱኝ። ቆራጥነታቸውን ሳደንቅ ፋሽስት ንፁሃንን ለምን እንደሚገድል በጣም ተገረምኩ። መስቀላቸውን መትቼ ከጎሬ ተመለስኩ። ወደ ሎንዶን ከሔድኩ በኋላ ጳጳሱ ተገድለው ጎሬም በጠላት መያዟን ሰምቼ በጣም አዘንኩ። አቡነ ሚካኤል ከማልዘነጋቸው ቆራጥ ኢትዮጵያውያን አንዱ ናቸው። በነፃነት ጉዳይ ኢትዮጵያውያን የተለየ አቋም አላቸው። ቋንቋ ፈፅሞ አያግዳቸውም ፣ አይበግራቸውም። ሁሉም በአገራቸው ጉዳይ ቀልድ እንደማያውቁ የጎሬው ጳጳስ አቡነ ሚካኤል ጥንካሬ በሚገባ አስረድቶኛል። የጳጳሱ ድፍረትና የአገር ፍቅር ምን ጊዜም አይረሳኝም›› ይላል።

ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በ፲፰፻፸ ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1878) በጎንደር ክፍለ ሀገር ፣ በደብረ ታቦር አውራጃ ፣ በደራ ወረዳ፣ አፈረዋናት ቀበሌ ፣ ከገበሬ ቤተሰብ ተወለዱ። የቀድሞ መጠሪያቸው ኃይለሚካኤል ነበር። በኋላ መምህር ሐዲስ እየተባሉ ተጠርተዋል። የቤተ ክርስቲያን ትምህርታቸውን የጀመሩት በተወለዱበት ወረዳ በሚገኘው ‘ግንድ አጣም ሚካኤል’ በሚባል ቤተ ክርስቲያን ነው። ቀጥለው ወደ ‘ገላውዴዎስ ደብር’ በመሄድ ጸዋተ-ዜማ አጠናቀቁ። ከዚያም ከፍተኛ ዕውቀት ለመገብየት እና በትምህርታቸው መግፋት ስለ ፈለጉ ወደ ጎንደር አመሩ። በጎንደር ከተማም የብሉያትንና ሐዲሳትን መጻሕፍት ትርጓሜ በሚገባ ተማሩ። ቀጥሎም ወሎ ክፍለ ሀገር በመሄድ ‘ቦሩ ሜዳ’ በሚገኘው የመምህር አካለ ወልድ ጉባኤ ተገኝተው ትርጓሜ መጻሕፍትን አጠናቀው በመምህርነት ተመረቁ። በዚያው የቅኔ መምህርነቱንም አስመስክረዋል። ከዚያ በኋላ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ለጥቂት ጊዜ ቆይተው ወደ አዲስ አበባ በመሄድ አሥራ አራቱን የቅዳሴ ትርጓሜ ተምረዋል።

ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ከረዥሙ የትምህርት ቆይታቸው በኋላ በየአድባራቱና በየገዳማቱ እየተሾሙ የተጣለባቸውን የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት በብቃት ተወጥተዋል። በ፲፱፻፳፩ ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1928) የአገራችን የመጀመሪያዎቹ አምስት አበው ወደ ምድረ-ግብፅ ሄደው የጵጵስና ማዕረግ ሲቀበሉ ፣ አቡነ ሚካኤል ከእነዚያ አንዱ ነበሩ፡፡ ከማዕረገ ጵጵስናቸው በኋላም የደቡብ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ በመሆን ወደ ተመደቡበት ወደ ጎሬ (ኢሉባቦር) ሔደው ከመንፈሳዊ ሥራቸው በተጨማሪ ስለ ሀገር ፍቅርና ስለ ነፃነት ጥቅም ሕዝቡን በሚገባ አስተምረዋል።

በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1935) ፋሽስት ጣሊያን አገራችንን በወረረችበት ጊዜ የኢሉባቦር ሠራዊት ወደ ምሥራቅ ጦር ግንባር ኦጋዴን ሲዘምት ስለ ሀገሩ ነፃነት በርትቶ እንዲከላከል አስተምረው ከመከሩ በኋላ ቡራኬ ሰጥተው አሰናብተዋል። እሳቸውም በጾም ፣ በፀሎት እና በምህላ ወደ እግዚአብሔር እየማለዱ ሕዝቡን በማፅናናት ቆይተዋል። የፋሽስት ጣሊያን ጦር አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ቆራጡ የልብ ጓደኛቸው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ለሃይማኖታቸው እና ለአገራቸው ነፃነት መሥዋዕት ለመሆን መዘጋጀታቸውን እንዲሁም ከነፃነት አርበኞች ጎን በመሰለፍ ሕዝቡ ስለ ሃይማኖቱ እና ስለ ሀገሩ ነፃነት እንዲዋጋ በመቀስቀስ ላይ መሆናቸውን ሲሰሙ በጣም ተደሰቱ። በአንፃሩ ደግሞ በጊዜው ፈጥነው ከጠላት የጣሊያን ጦር ጋር የተስማሙ አባቶች የእሳቸውን (የአቡነ ሚካኤልን) ጠንካራ አቋም ከተረዳው ጠላት ተልከው ወደ እሳቸው ጎሬ ድረስ መጡ። ከጣልያን ጦር ተልከው የመጡት መልዕክተኞች አቡነ ሚካኤል ከጣሊያን ጋር እንዲስማሙ ጠየቋቸው። እሳቸው ግን ‹‹አቅም የለኝም እንጂ ብችል ኖሮ እናንተም ከእኔ ጎን ቆማችሁ ስለ ሃይማኖታችሁና ስለ ሀገራችሁ ነፃነት ብትሞቱ እፈልግ ነበር። ስለዚህ ወደ እኔ አትምጡ። አርበኞች ይጣሏችኋል። እኔ በሞቴ ቆርጫለሁ።›› በማለት እንደ መለሱላቸው ታሪክ ያስረዳል።

አቶ ታደሰ ሜጫ ‹ጥቁር አንበሣ በምዕራብ ኢትዮጵያ› በሚል ርዕስ ስለ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ምሩቃንና ስለ ጥቁር አንበሣ ሠራዊት ተጋድሎ በጻፉት ታሪክ ውስጥ ስለ አቡነ ሚካኤል በሰጡት ምስክርነት ‹‹ጎሬ በገባን ጊዜ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በከተማው እንደሚገኙ ሰማን። መልዕክታችንን ለክቡር ራስ እምሩ አድርሰን ወደ ተሰጠን ሠፈር ከመመለሳችን በፊት የጥቁር አንበሣን ሰላምታ ይዘን ወደ ብፁዕነታቸው መኖሪያ ሄድን። እሳቸውም ከተቀበሉን እና ቃለ ቡራኬ ከሰጡን በኋላ ከዋነኞቹ መልዕክተኞች ጋር ተነጋግረው የማበረታቻ ቃላቸውንም ወደ ጥቁር አንበሳ ጦር እንዲያደርሱላቸው አሳስበው በቡራኬ አሰናበቱን። እኛ ወደ ጥቁር አንበሣ ጦር ከተመለስን በኋላ ራስ እምሩም ጎሬን ለቀው ወደ እኛ በመጡ ጊዜ ብፁዕነታቸው በዚያው ያሉትን ምዕመናን ለነጣቂ ተኩላ ጥዬ አልሄድም በማለት መንፈሳዊ ተግባራቸውን በቆራጥነት ያከናውኑ ነበር።›› በማለት አድንቀዋቸዋል። የጠላት ጦር ወደ ኢሊባቦር እየተቃረበ ሲመጣ የጠቅላይ ግዛቱ አስተዳደር የነበሩት ቢትወደድ ወልደጻድቅ እና ሌሎች የመንግስት ሹማምንት የጎሬን ከተማ ለቀው ወደ ከፋ ሄዱ። ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ግን «በዚያ ያሉትን ምዕመናን ትቼ የትም አልሄድም» በማለት በሕዝቡ ላይ የሚደርሰውን ስቃይና መከራ አብረው ለመካፈል በቁርጠኝነት ቆዩ።

በኮሎኔል ማልታ የሚመራው የፋሺስት ኢጣሊያን ጦር በኅዳር ወር በ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. November 1935) የጎሬን ከተማ ተቆጣጠረ። አቡነ ሚካኤል ደግሞ በጎሬ ከተማ አጠገብ ‘ሳንቤ ቀበሌ’ ሕዝቡ ጠላትን እንዲከላከል በመቀስቀስ ላይ ነበሩ። ይሄንን የሰማው የጠላት ጦር በአፋጣኝ ወታደር ልኮ አስከበባቸው። ከብፁዕነታቸው ጋር የነበሩት አርበኞች ከኢጣሊያን ጦር ጋር ተኩስ ተለዋወጡ። ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ሲያፈገፍጉ አቡነ ሚካኤልም በቅሎዋቸው ላይ ተቀምጠው መንገዱን እንደ ጀመሩ ተያዙ። ኢጣሊያዊው የጦር መኮንን ብፁዕነታቸውን ከበቅሎዋቸው አስወርዶ በእግራቸው እንዲሄዱ በማድረግ እርሱ በቅሎው ላይ ተቀመጠ። አድራጎቱን የተመለከቱት ከጠላት ጋር የነበሩት የሐማሴን ተወላጆች በፈረንጁ ላይ ተቆጡ። “ይማኖት አባታችን የሆኑት አዛውንቱ በቅሎዋቸውን ቀምተህ በእግራቸው እንዲሄዱ ማድረግህ ግፍ ነው፡፡ በቅሎዋን መልስላቸውና አንተ በእግር ሂድ። አለበለዚያ እኛ ከዚህ ስፍራ አንንቀሳቀስም።” በማለት ድርጊቱን ተቃወሙ። ኢጣሊያዊው መኮንን በሁኔታው ደነገጠ። ከበቅሎው ላይ ወረደና ለጳጳሱ መለሰ። አቡነ ሚካኤል በበቅሎው ተቀምጠው ጎሬ እንደደረሱ ለጠላት ሠፈር በተዘጋጀ እሥር ቤት በጥብቅ እንዲታሠሩ ተደረገ።

አቡነ ሚካኤል መንፈሳዊ አባትና ሽማግሌ ስለ ሆኑ ይፈቱልን› በማለት ሕዝቡ ልመና ቢያቀርብም የጠላት ጦር አዛዥ ልመናውን ሳይቀበለው ቀረ። ኮሎኔል ማልታ እሥረኛውን ጳጳስ ከእሥር ቤት አስመጥቶ ሕዝቡ በተሰበሰበበት አደባባይ አቀረባቸው። «ለኃያሉ የኢጣሊያ መንግሥት ለመገዛት ቃል ይግቡና ሕዝቡም እንዲገዛልን ይስበኩልን። ይህንን ካደረጉ እንለቅዎታለን።» በማለት በልዩ ልዩ መደለያ ጭምር አባበሏቸው። ብፁዕነ አቡነ ሚካኤል ከሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጠላት ጋር እንደማይተባበሩ በፅናት ገለፁ። ‹እኔ የማምነው በአንድ እግዚአብሔር ነው። የምቀበለው የነፃነታችን ምልክት የሆነውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ብቻ ነው። ኢጣሊያ የሚባል ገዥ አላውቅም። ለፋሽስት ኢጣሊያ የተገዛ እንደ አርዮስ የተረገመ ይሁን። እንኳንስ ሕዝቡ ምድሪቱም እንዳትገዛላቸው አውግዣለሁ።› በማለት በዚያ ለተሰበሰበው ሰው ሁሉ ውግዘታቸውን አሰሙ። የጠላት ጦር አዛዥ ኮሎኔል ማልታ የብፁዕነታቸው የዓላማ ፅናትና ቆራጥነት ተገነዘበ። እሳቸውን መሸንገል እንደማይቻል ሲያረጋግጥ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ ወሰነ።

ከጎሬ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በታች አሮጌው ቄራ አጠገብ ጉድጓድ ተቆፈረ። በጉድጓዱ ዳር በሁለት ስመጥር አርበኞች (ቀኛዝማች ይነሱ እና ግራዝማች ተክለ ሃይማኖት) መካከል ጳጳሱ እንዲቆሙ ተደረገ። በዚህን ጊዜ አቡነ ሚካኤል ለጥቂት ደቂቃዎች ፀሎት እንዲያደርጉ ጠይቀው ተፈቀደላቸው። ፀሎታቸውን አድርሰው ሲያበቁ መስቀላቸውን በግንባራቸው አድርገው ‹በል እንግዲህ የፈለከውን አድርግ› አሉ። የወታደሮቹ አዛዥ የተኩሱን ትዕዛዝ ሰጠ። ከእነ አቡነ ሚካኤል ፊት ለፊት በተርታ ተሰልፈው (ተደርድረው) በመንፈሳዊ አባት እና በአርበኞች ላይ ጠመንጃቸውን ያነጣጠሩት የጠላት ወታደሮች በእሩምታ ተኮሱ። ብፁዕነታቸውና ሁለቱ አርበኞች በተተኮሰባቸው ጥይት ተመተው ወደቁ። የቀብራቸውም ሥነ ሥርዓት በአግባቡ አልተፈፀመም። አቶ ወልደአብ የተባሉ የአገር ፍቅር የነበረባቸው የአካባቢው ነዋሪ ናቸው በሌሊት የቀበሯቸው።

ከዚህ በኋላ የአካባቢው የጠላት ጦር ዋና አዛዥ የነበረው ኮሎኔል ማልታ በጎሬ ከተማና አካባቢው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሚያገለግሉትን ካህናት በሙሉ ሰብስቦ ገለፃ አደረገላቸው። ‹አቡነ ሚካኤል የተገደሉት ለኃያሉ የኢጣሊያን መንግሥት አልገዛም በማለታቸው ነው። ሕዝቡም እንዳይገዛ በማውገዝ በእምቢተኝነታቸው ፀንተው በፈፀሙት የአመፅ ራ ነው።› አለና ‹‹ስለዚህ አቡኑ መገደላቸው ተገቢ ነው? ወይስ ተገቢ አይደለም?›› ሲል ካህናቱን በአፋጣኝ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ በማዘዝ አፈጠጠባቸው። ካህናቱ ለዚህ አስቸጋሪ ጥያቄ ወዲያውኑ መልስ ለመስጠት ተቸገሩ። ይህም የሆነበት ምክንያት ‹‹አቡኑ መገደላቸው ተገቢ አይደለም።›› ካሉ እነርሱም የሚጠብቃቸው ዕድል ሞት ነው፡፡ ‹‹የአቡኑ መገደል ተገቢ ነው›› እንዳይሉ ደግሞ ለሀገርና ለነፃነት መቆርቆርና መታገል ወንጀል አለመሆኑን እንዲያውም የተቀደሰ ተግባር እንደሆነ ያውቃሉና ካህናቱ በቀረበላቸው ጥያቄ ላይ ተወያዩ። ከመካከላቸውም አነጋገር ይችላሉ ብለው ያመኑባቸውን አለቃ ቢረሳው የተባሉትን አባት መረጡ። ካህናቱን ወክለው መልስ እንዲሰጡ አደረጉ። አለቃ ቢረሳውም ለኮሎኔል ማልታ ‹‹እናንተም ደግ ገደላችሁ፤ እርሳቸውም ደግ ሞቱ›› በማለት መልስ ሰጡ።

ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በካህናቱም ሆነ በሕዝቡ ዘንድ የተወደዱ ደግ ሰው በመሆናቸው መገደላቸው ተገቢ አለመሆኑን አለቃ ቢረሰው ቢናገሩም ምስጢሩ ያልገባው ኮሎኔል ማልታ የእርሱን ሃሣብ የደገፉለት መስሎት ተደሰተ። ‹‹አለቃ ቢረሳውን አቡን አድርጌ ሾሜዋለሁ›› ብለው የሟቹን ጳጳስ መስቀልና መቋሚያ በሽልማት እንዲሰጣቸው አዘዘ። አለቃ ቢረሳው ግን ‹‹መስቀሉ የሚገባው ለቤተ ክርስቲያን ስለ ሆነ ለጎሬ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ይሰጥ።› በማለት አስረከቡ። ካህናቱም በሰላም ወደየቤታቸው ተመለሱ። የብፁዕ አቡነ ሚካኤል አፅም ከነበረበት አልባሌ ሥፍራ ተለቅሞ በሣጥን ተደርጎ፣ በጎሬ ደብረገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በክብር የተቀመጠው ጠላት ከሀገር ተባሮ ነፃነት ከተመለሰ በኋላ በ፲፱፻፴፭ ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. November 1943) ነው። በ፲፱፻፴፬ ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1941) በጎሬ ከተማ ውስጥ የተቋቋው ‹የአቡነ ሚካኤል ትምህርት ቤት› ብቻ በስማቸው ማስታወሻነት ይገኛል። ከ፲፱፻፶፪ ዓ.ም እስከ ፲፱፻፷፯ ዓ.ም ድረስ የኢሊባቡር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የአቡነ ሚካኤልን ፎቶግራፍ ከግብፅ አሌክሳንድርያ አስመጥተው በጎሬ ከተማ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት በሚገኘው አደባባይ ላይ በመስታወት ውስጥ አስቀምጠውት ነበር። በደርግ አስተዳደር ወቅት በዚያ በኩል መንገድ ያልፍበታል ተብሎ ፎቶግራፋቸው እንዲነሣ ተደረገ። በዚያ ላይ ጠላት እንኳን ያልወሰደው የአቡነ ሚካኤል የወርቅ መስቀል ከሃምሣ ዓመታት በላይ በቤተክርስቲያን ውስጥ ተከብሮ ቆይቶ ነበር። በወቅቱ በነበሩት የኢሠፓ ባለስሥልጣናት ትዕዛዝ በኤግዚቭዥን ስም ተወስዶ ሳይመለስ ቀርቷል። ጉዳዩን የሚመለከተው ክፍል ትኩረት ሰጥቶበት በወቅቱ የወሰዱት ግለሰቦች በኃላፊነት ተጠይቀው ወደነበረበት እንዲመለስ ቢደረግ መልካም ነው» ሲል ሐመር የሀገር ወዳዱን አባት ታሪክ ጽፎአል።

ቀደም ብሎ የኢሉባቦር ጠቅላይ ገዥ የነበሩት ደጃዝማች ጣሰው ዋለሉ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በተረሸኑበት ቦታ ላይ ድንጋይ በማስካብ መታሠቢያ እንዲሆናቸው አድርገው ነበር። ይኸው ሐውልት በ፲፱፻፹ ዓ.ም. መጠነኛ እድሳት እንደ ተደረገለት ታውቋል። ሆኖም ቢዘገይም ግንቦት ፲፬ ቀን ፪ሺህ፰ ዓ.ም. በተሰውዉባት የጎሬ ከተማ በጎሬ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ደጀ ሰላም ውስጥ ሐውልት እንደ ቆመላቸው «ሐራ ዘተዋሕዶ» እና «አንድ አድርገን» የተሰኙት ድረ-ገጾች ዘግበዋል[3]

 

እኛም የዘመኑ ኢትዮጵያውያን የእኒህ ብፁዓን አባቶቻችንን የአቡነ ጴጥሮስ እና የአቡነ ሚካኤል የሃይማኖት እና የሀገር ፍቅር ይደርብን።

[1] ሐመር መጽሔት ግንቦት/ሰኔ ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. (ከስንክሳርየዲያቆን መልአኩ እዘዘው ገፅ የተገለበጠ:- http://www.melakuezezew.info/2012/07/blog-post_27.html)

[2] አዲስ Addis 1879, http://www.addis1879.com/index.php?option=com_content&view=article&id=95:2011-12-10-07-21-32&catid=37:ethioia&Itemid=55

[3]https://haratewahido.wordpress.com/2016/05/23/

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.