ከቄሮዎች፣ ከፋኖዎችና ከመላው ሕዝብ ምን ይጠበቃል?

ብሥራት ደረሰ

የሰሞኑ የሀገራችን ሁኔታ ግንቦት 13 /1983 ዓመተ ምሕረትን በመጠኑ ያስታውሰኛል፡፡  ኃይለኛ ወጀብና የለበሱትን ልብስ ሣይቀር ከሰውነት ላይ ገፍፎ እርቃን የሚያስቀር ከባድ ንፋስ ባናወጣት በዚያች የዕለተ ማክሰኞ ግማሽ ቀን ውስጥ አንድ ያልተጠበቀ ተዓምር በኢትዮጵያ ምድር ተከሰተ፡፡ እሱም ይሆናል ያልተባለና “ ‹አንድ ሰውና አንድ ጥይት/ዛፍ?/› እስኪቀር ለሀገሬ እዋጋለሁ” እያለ ሲፎክርና ሲያቅራራ የነበረው የወቅቱ አምባገነን መሪ መንገሥቱ ኃይለ ማርያም ሄሊኮፕተር ጠልፎ ድንበር የተሻገረበት ክስተት ነበር፡፡

ዛሬም ከዚያው ዓይነት አዙሪት አልወጣንም፡፡ ሌላው ዓለም በተወሰነ መልኩ ብዙ ርቀት ወደፊት ሲጓዝ እኛ ግን ወያኔዎችን ምሥጋን ይንሳቸውና ከእንስሳትም እጅግ በወረደ ሁኔታ በዘረኝነትና  በመንደርኝነት የኋሊዮሽ አስተሳሰብ ተጠፍንገን፣ ባለንበት እንኳን መርገጥ አቅቶን እግዜር ይሁነን እንጂ እንደሰውኛ እሳቤ የማይቀርልን ወደማይመስለው እንጦርጦስ ቁልቁል እየጋለብን እንገኛለን፡፡ እንደሚመስለኝ ትልቁ አሣዛኝ ነገር አንድ ሰው ያለውን ይዞታ እንኳን ማቆየት አቅቶት የማጣቱ ልክ ድነበር የለሽ ሲሆንበት ነው፡፡ እኛ አሁን ምን አለን? ምንም! ቀፎ ሆነናል፡፡ ቢከፍቱ ተልባ ዓይነት፡፡

ወያኔዎች እንደቀድሞው እንዳልሆኑ መረዳት ጀምረናል፡፡ ይፈቱልናል ብለን በፍጹም ያልጠበቅናቸው እሥረኞች ተፈትተውልናል፡፡ እሰዬው ነው፡፡ ብልህ ልጅ የሰጡትን እየበላ እንደሚያለቅስ ከነዚህ ዐውሬዎች የምናገኘውን ማናቸውንም መልካም ነገር በአድናቆትና በምስጋና ጭምር መቀበል ይኖርብናል፡፡ “ይህንንስ ማን አይቶበት?” የሚባል ግሩም አባባል አለ፡፡ እናም በየጊዜው የምናገኛቸውን እነዚህን መሰል ጥሩ አጋጣሚዎች ምንም እንኳን የዘመናት የትግል ውጤቶች መሆናቸውን እኛ ቀርተን እነሱ  ራሳቸው ወያኔዎችም ቢረዱትም ሳናጣጥልና ሳናጋንን በአወንታዊነት መያዝ አስተዋይነት ነው፡፡  እዚያና እዚህ የምንለቃቅማቸውን የመራራ ትግል ውጤቶች በስሜታዊነት ተገፋፍተን ለማጣጣል መሞከር ብስለት የሚጎድለው አካሄድ ይመስለኛል፡፡ ከመጨነቅም ይሁን፣ ሕዝብን ለማዘናጋትና ጊዜ ለመግዛትም ይሁን፣ ለተለዬ ሤራ ሊጠቀሙበት አስበውም ይሁን፣… በየትኛውም ሰበብ ይሁን የጀመሩትን እሥረኞችን የመፍታት አወንታዊ ተግባር በፀጋ እንቀበል፡፡ እደግመዋለሁ – “ብልጥ ልጅ የሰጡትን እየበላ ያለቅሳል”፡፡

ይህ ሲሆን ግን ከእባብ ዕንቁላል ዕርግብ እንደማይፈለፈል ሁሉ ወያኔዎች ተለውጠው ደግ ሆኑ ማለት እንደማይቻል መገንዘብ አለብን፡፡ ወያኔዎች የክፋት ተፈጥሯቸውን ከሚለውጡ ይልቅ የክርስቶስን አባባል በመጠኑ ለውጬ ልጠቀምና ግመልና ተራራ በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልኩ ይቀላል፡፡ ወያኔዎች ለውጥ ቢያውቁ ኖሮ ይሄኔ በማኒፌስቷቸው ላይ በማያሻማ ቋንቋ ያሠፈሩትን “አማራንና ኦርቶዶክስን እናጠፋለን” የሚል መመርያ ይቅርታ ጠይቀው ይሠርዙ ነበር፡፡ አንድን ማኅበረሰብና አንድን የሚሊዮኖች ሃይማኖት ለማጥፋት መነሳት ዕብደት ከመሆኑም ባሻገር ከዚህ አጥፊ መንገድ ለመታረም ያለመፈለግ ደግሞ ምንም ዓይነት መድኃኒት የማያሽለው የዕብደት ዕብደት ነው፡፡

ይህን የወያኔዎችን ያለመለወጥ ተፈጥሯዊ ባሕርይ በወቅታዊ ምሣሌ ማስረገጥ ይቻላል፡፡ ወያኔዎች እዚህ እሥረኛ እየፈቱ እዚያ ያስራሉ፤ ይገድላሉም፡፡ እዚህ ተሳስናል እያሉ እዚያ በባሰ የስህተት ጎዳና ይተማሉ፡፡ እዚህ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅን አነሳን እያሉ በዚያው አፍ አፍታም ሳይቆዩ ያንኑ ዐዋጅ አጠናክረው ያውጃሉ፡፡ እዚያ እንደማይዋሹ ሲናገሩ አፍታ ሳይቆዩ እዚህ በውሸታቸው ያደርቁናል፡፡ ወያኔዎችን መግለጽ የየትኛውም ቋንቋ ቃላት አይቻላቸውም፡፡ ፋሽስት ቢባሉ ያንሳቸዋል፤ ናዚዎች ቢባሉ ያንሳቸዋል፤ ጭራቆች ቢባሉ አይመጥናቸውም፤ ጉግማንጉጎች ቢባሉ በቅጡ አይገልጸቸውም፤ በውነቱ ለወያኔዎች የክፋትና የተንኮል ድርጊት የሚመጥን ቃል በዓለም አይገኝም፡፡ ወያኔዎች ባጭር አገላለጽ ዋና የዲያቢሎስ ልዑካን ናቸው፡፡ ንስሃና ፀፀት ሲያልፉ የማይነኳቸው በዐመፅ ተወልደው በዐመፅ አድገው በዐመፅ ያረጁ የእፉኝት ልጆች ናቸው፡፡ የብዙዎቹ ሃይማኖት ሴቴኔዚም ስለመሆኑም የሰሞኑ የየካቲት 11/2010 ዓመታዊ በዓላቸው በግልጽ ያስረዳል፡፡ በዓላቸውን ያደመቁበት ባንዲራ የሕወሓትና የሶዶማውያን እንደነበረ ከመቀሌ አካባቢ ከወጣ ዜና ተከታትለናል – በድፍረት እንደዚያ ያደረጉበትም ምክንያት የላኪዎቻቸውንና የጥልቁን ጨለማ ገዢ ወኪሎች ለማስደሰትና ሁለንተናዊ ድጋፋቸውን ለማግኘት እንደሆነ መገንዘብ አይከብድም፡፡ እነሱ ለነሱ ይተዋወቃሉ፤ የሥራ ክፍፍላቸውንም አይረሱም፡፡ ታስታውሱ እንደሆነ አንድ ጊዜ አንድ ትልቅ ባለሥልጣን ወደ ሀገራችን ሲመጣ የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረው ቴዎድሮስ አድሃኖም የሶዶማውያኑን ዓርማ የያዘ ጃንጥላ አጥልቶ ነበር እንግዶቹን የተቀበለውና በወሮታውም “ዴሞክራሲያዊነታቸውን” ትልቅ በሚመስል ትንሽ ጉባኤ ውስጥ ያስመሰከሩት –  የሰሞኑ ክስተትም የዚያው ማጭበርበር ቅጣይ መሆን አለበት እንጂ በትግራይ ምድር እንዲህ ያለ ቅሌት ታይቶም ሆነ ተሰምቶ አያውቅም፡፡ ሣጥናኤላውያን የሚግባቡባቸው ብዙ ኮዶች አሏቸው፡፡ የሚያደርጉት ሁሉ ትርጉም አለው – ሳይነጋገሩ ይግባባሉ፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያን የዲያብሎስ መናኸሪያ ለማድረግ የተያዘው ዘመቻም ከሞላ ጎደል የተሣካ ይመስላል – ከቤተ መንግሥት እስከ ቤተ አምልኮ፡፡ ብዙ መናገገር አያስፈልግም፤ ጊዜውም አይደለም …  ለማንኛውም እነሱ በግልጽ እንዲህ ነን ሲሉ ያላፈሩ እኛ ስለነሱ ልናፍር አይጠበቅብንም፡፡ በነገራችን ላይ ከሴቴኒዝም ዋና ዋና መገለጫዎች ውስጥ በዊስኪና በጮማና በፎቅ ብዛት መዝናናት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባና በዙሪያዋም እንዲህ እየሆነ ያለው ለዚህ ነው፡፡ የነሱ ምድራዊ ዋጋ ይሄው ነውና፡፡

የሕዝብ ወገኖች የሆንን የድል ሽሚያ ውስጥ መግባት አይገባንም፤ በአእምሮ እንደግ፡፡ “ከብቱ ሳይገዛ ሌባው በረት ሞላ” እየተባለ ባላፊ አግዳሚው አይተረትብን፡፡ “ወጡ ሳይወጠወጥ ወስከምቢያው ቂጢጥ” እያሉ ታዛቢዎች አይዘባበቱብን፡፡ እናም በአካል ብቻ ሣይሆን በመንፈስም እንደግና ይህን መጥፎ ጠባያችንን እናስወግድ፡፡ የሚመዘገቡ ድሎችን እንደሕዝብ ድል ከመቁጠር ባለፈ ለአንድ ቡድን ወይም ለአንድ የኅብረተሰብ ክፍል መስጠቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ስለዚህ በዚህ በኩል ጠንቀቅ ማለቱ አይከፋም፡፡ ገና ብዙ ድሎች ይቀሩናልና እነዚያን አስቀምጠን በብጭቅጫቂ ትሩፋቶች መጨቃጨቅና ዋናውን የሀገር ነፃነት መዘንጋት አይኖርብንም፡፡

እሥረኞች እየተፈቱ ነው፡፡ ወደፊትም የሚፈቱ ይኖራሉ፡፡ አንዳንድ የጠባበቁ ነገሮች ሊፍታቱ ይችሉ ይሆናል፡፡ ጭንቅ ላይ የሚገኙ አምባገነኖች የሚፈጽሟቸው በርካታ መጥፎ ነገሮች የመኖራቸውን ያህል ወደውም ባይሆን ተገደው ከእጃቸው የሚያፈተልኩባቸው አንዳንድ መልካም ነገሮችም ሊኖሩ መቻላቸው የታወቀ ነውና በነዚያ ሳንዘናጋ ለትልቁ ዓላማ መገስገስ ተገቢ ነው፡፡ (አያድርግብን እንጂ እስረኞችን ሁሉ በአንድ ቀን ቢፈጇቸው ማን ይጠይቃቸዋል? በዓለም ህግ አይገዙ፤ በፈጣሪ ትዕዛዛት አይመሩ፤ በሀገራዊ ህግ አይተዳደሩ፤ የጫካን ወሮበላ “እንዲህ አደረግህ” ብሎ ማን ይጠይቀዋል? ከዋናው የዓለማችን ገዢ ከኃይለኛው ጥልሚያኮስ ጋር ደግሞ ንክኪ ስላላቸው የፈለጉትን ቢያደርጉ በርቱ ከማለት በስተቀር የሚገስጻቸው እንኳን የለም፡፡ ያለፉት 30 እና 40 ዓመታት ብዙ አስተምረውናል፡፡ የምንንቃቸው ተራ ሰዎች ልንንቀው ከማይገባን ትልቅ የጨለማ ኃይል ጋር ተሰልፈው በክፋቶች ጥምረት እያጠፉን ናቸው፡፡ ይህን ብዙዎቻችን አላወቅንም፡፡ የሆኖ ሆኖ በኪነ ጥበቡ ውሎ የሚገባ ሕዝብ፣ ከእንስሳትም በታች ተቆጥሮ ማንም እንደፈለገ የሚያላጋው ሕዝብ፣… በዚህ የጨለማ ዘመን ውስጥ አይቀናጣምና ያገኘውን ይዞ የፈጣሪንና የታሪክን ፍርድ መጠበቅ ነው፡፡ ቀኑ ደግሞ ዛሬ ነው፤ በበኩሌ ኮ/ል ደመቀ ተፈታ መባልን ስሰማ በርግጥም እግዜር ለዚህች ሀገር አደግድጎ መቆሙን አመንሁ፡፡ ተመስገን!)

ቄሮዎችና ፋኖዎች የሕዝብንና የሀገርን ሀብትና ንብረት የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው፡፡ የነገው ሥርዓት ባዶ ካዝናና ባዶ መሬት ቢረከብ ሕዝብ ይራባል፤ ይጠማል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘው ማንኛውም ንብረት ሕዝብን ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም፡፡ አንድ የግለሰብም ይሁን የመንግሥት ፋብሪካ ቢቃጠል ተጎጂው ግለሰቡ ወይም መንግሥት ብቻ አይደለም፡፡ በዚያ ፋብሪካ ውስጥ የሚሠሩ ዜጎችና ቤተሰቦቻቸው ለከፋ ችግር ይዳረጋሉ፡፡ “እንዲህ ልጠግብ በሬየን አረድኩ” ያለችውን ሴት እናስታውስ፡፡ ስለሆነም ንብረትን ለማውደም በሕዝባዊ የእምቢተኝነት ዐመፆች በኩል ሠርገው የሚገቡ የወያኔ ሰዎችንና ባልተገባ የጦዘ ስሜት ተነሳስተው ወደዚያ ተግባር የሚሠማሩ የገዛ ወገኖቻችንን ማስተማርና ማንቃት ይገባናል፡፡ አንድ መኪና ወደ ሀገር ሲገባ ብዙ የውጭ ምንዛሬ ፈስሶበት ነው፡፡ ያ መኪና የማንም ይሁን የማን ከማቃጠል ወይ ከማውደም ይልቅ ተረክቦ ቢገለገሉበት ወይም ቁልፉን ቀምቶ በጥንቃቄ በማስቀመጥ ለነገ አገልግሎት እንዲውል ቢደረግ የተሻለ ነው፤ ሥልጡንነትም ነው፡፡ እንኳንስ አቃጥለን ተንከባክበን ይዘንም የሚበቃን ሀብትና ንብረት የለንም፡፡ አንድ ዐይና ደግሞ በአፈር ሊጫወት አይገባም፡፡ ሀብት ንብረታችን በወያኔዎችና በተባባሪዎቻቸው ተመዝብሮ ባዶኣችንን ቀርተናልና ያለንን ጥቂት ጥሪት እንደዐይናችን ብሌን መንከባከብ አለብን፡፡

ስለሆነም በየአካባቢው የምትገኙ ፋኖዎችና ቄሮዎች ይህን ንብረትን የመንከባከብ ጥቆማየን ልብ እንድትሉልኝ እንደ አንድ በሀገሩ ጉዳይ የሚያገባው ዜጋ ማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡

በነገራችን ላይ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በሚቻል ሁኔታ ተቋርጧል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ ዳፍንት ወርሶናል፡፡ ከዓለም የምንገናኝበት መንገድ የለም፡፡ ሁሉንም የመንግሥት ተቋማት ወያኔ ስለተቆጣጠረው ዐይናቸውን እንዳልከፈቱ ቡችሎች አሳውረው ጨለማ ውስጥ ከተውናል፡፡ ስለዚህ ለዚህ ችግር አንዳች መፍትሔ እንዲገኝ የሚመለከታቸው ወገኖች ጥረት ቢያደርጉ መልካም ነው፡፡ መልእክት መለዋወጥ የሚቻልበት ዘዴ ካልተፈጠረ በአንዱ አካባቢ ሊደረግ የታሰበው ነገር በሌላው አይታወቅምና መናበብ አይኖርም፡፡ በተናጠል የሚደረገው ትግል ደግሞ መቼም ቢሆን አይሰምርም፡፡ ይህን ችግር ልብ ብላችሁ አጢኑትና መፍትሔ ይፈለግለት፡፡ አሳሳቢ ችግር ነው፡፡

ንብረትን ማስቀደሜን ከይቅርታ ጋር ላስታውስና ዜጎችንም ማክበርና ከሞትና ከስቃይ መታደግ የቄሮዎችና የፋኖዎች ተግባር መሆኑን እንገንዘብ፡፡ ቄሮና ፋኖ ለኔ የሚገባኝ በበቀልና በቁጭት ተመርዞ የጠላውን የሚያወድምና የሚዘርፍ፣ የወደደውን ደግሞ አለምክንያት የሚሾምና ወደ ሀብት ጫፍ የሚያወጣ ኃይል አይደለም፡፡ ፍትህ የጠማው፣ ስለፍትህ ራሱን ለመሰዋት የተዘጋጀ፣ በፍትህ የሚያምንና በህጋዊ ሥርዓት አጥፊን ወደ ፍርድ የሚያመጣ መሆን አለበት፡፡ እነኚህን ኃይላት ተንተርሶ ሥርዓት አልበኝነትን ለማንገሥና ወደሌላ የጥፋት አዙሪት ሊከተን የሚፈልግ ወገን እንዳይኖር ቄሮዎችና ፋኖወች ሊጠነቀቁ ይገባል፡፡ ስሜትን መቆጣጠርና ምክንያታዊነትን ማዳበር ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል፡፡  አሮጌው ወይን በአዲስ አቅማዳ ከገባ ወይኑም የለም፤ አቅማዳውም አይኖርም፡፡ ተደምሮ ተቀንሶ የሚኖረን ብቸኛ “ትርፍ” ሲበቃቀሉ የመኖር የለመድነው አዙሪት ነው፡፡ መደማመጥ፣ መግባባት፣ ያንዱን ቁስል ሌላው እንደራሱ ማየት … ለውጤት ያበቃል፡፡ በዘርና በጎሣ፣ በሃይማኖትና በወንዝ ልጅነት መቧደን አድሮ ቃሪያ መሆን ነው፡፡ ወያኔን ማሸነፍ የሚቻለው ወያኔ በተጓጓበት መንገድ ሄዶ ሣይሆን በተቃራኒው አቅጣጫ ተጉዞ ነው፡፡ እነሱ በተለሙት መንገድ መጓዝ የዞረ ድምሩ እነሱ በቆፈሩልን ጉድጓድ መግባት ነው፡፡ ይህን ለመረዳት ሌላ የ30 ዓመታት የስቃይና የመከራ ዘመን ማሳለፍ የለብንም፡፡

ወደየኅሊናችን እንመለስ፡፡ አንድን ዘር ማዕከላዊ ጠላት አድርገን መውሰድ እንደሌለብን እንረዳ፡፡ አንድ ሕዝብ የአንድ ሕዝብ ጠላት ሊሆን አይችልም፤ ሆኖም አያውቅም፡፡ ከአንድ ሕዝብ የሚወጡ ጥቂት ባለጌዎች ግን የተወሰነውን የዚያን ማኅበረሰብ አባላት በጥቅምና በቅስቀሳ በማነሁለል ጥፋት ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡ ያን ዓይነቱን ክሰተት በሀገራችን በሚገባ ታዝበናል፡፡ የሆነው ቢሆን ግን መላው ሕዝብ በነዚህ ጥቂት ወሮበሎችና የታሪካዊ ጠላት ተላላኪዎች ጥፋት ሰበብ መወቀስ ወይም በነሱ ዳፋ በእሳት መለብለብ የለበትም፡፡

ከላይ ያልታዘዘ ድል ከታች ብቻ የተወሰነ ውጤት ስለታዬ ብቻ መጨረሻው ጥሩ ይሆናል ብሎ መገመት ያስቸግራል፡፡ በመሠረቱ ለውጥ ለሀገራችን መሬት ብርቅ አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ ለውጥ አለ፤ እኔ እንኳን በዕድሜዬ ወደ ሦስት አካባቢ ለውጦችን አይቻለሁ – የጄኔራል ተስፋዬ ገ/ኪዳን የሣምንት ዕድሜ ሥልጣንና የቀፎው ኃ/ማርያም የአሻንጉሊትነት ዘመን  ሳይቆጠሩ፡፡ እኔን የናፈቀኝ ታዲያ እውነተኛ ለውጥ ነው፡፡ አውነተኛ ለውጥ ስል የሕዝብን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ለሕዝብ የሚጠቅም ለውጥ ለማለት ነው፡፡

ኃ/ማርያም በሞተ ሰዓትም ቢሆን “ሌላ አሻጉሊት ፈልጉ፤ እኔን ደክሞኛል” ማለቱን በዚያን ሰሞን ሰምተናል – “ማለቱን” ነው ያልኩት፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ካልደፈረሰ አይጠራምና በርሱ ውስጥ ተደብቀው በስልክና በደብዳቤ ናላውን ሲያዞሩት የነበሩት ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ወያኔዎች አሁን ራቁታቸውን ይወጣሉ፤ ከዚያም በእኔ እብስ እኔ እብስ ርስ በራሳቸው ሲፋተጉና ሲናጡ አንዳች ሀገራዊ ጠቃሚ ቅቤ ሊወጣ ይችላል፡፡ ከእንግዲህ ያለው ጊዜ የሩጫ ይመስለኛል፡፡ ብዙም ጊዜ ያላቸው አይመስልም፡፡ የተጠናወታቸው የዘረኝነት ልክፍት መጨረሻቸውን እያመጣባቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡ አምባገነኖች በተፈጥሯቸው ዕብሪተኞች በመሆናቸው ትምህርት የሚባል መቅሰም አይወዱም እንጂ ከሰሞኑ ሁኔታ አንዳች ነገር ተምረው የነሱንም የኛንም የሀገራችንንም መፃዒ ዕድል ወደተሻለ ደረጃ ሊለውጡ የሚያስችላቸው ጭላንጭል ዕድል ነበር፡፡ እነሱ ግን ይህን ዓይነቱን የጤነኛ ሰው አስተሳሰብ ደመኛቸው የሆነ ያህል ይጠሉታል፡፡

እናም መጠንቀቅ ያለብን እኛው ነን፡፡ እስካሁን  “ለምጣዱ ስንል ብዙ ዐይጦች እየተንጋጉ እንዲያልፉ” ሳንወድ በግዳችን ፈቅደን ነበር፡፡ አሁን ግን አርቲስት መስፍን ጌታቸው ሰሞኑን በዘሀበሻ ድረገፅ ባስነበበን አጭር ግሩም መጣጥፍ ላይ እንዳነበብኩት የአንድ ጭቁን ድመት ታሪክ ሕዝቡ በደረሰበት ተነግሮ የማያልቅ ግፍና በደል ምክንያት ከዳር እዳር ተቆጥቷል፤ አንዳች ነገር ጣልቃ ካልገባም መጪዎቹ ጥቂት ወራት ታሪክ ሊመዘግበው የሚዘገንነው ክስተት ማየታችን የማይቀር ነው፡፡ የሮማንያው ኒኮላይ ቻውቼስኮ፣ የሊቢያው ጋዳፊና ሌሎች እነዚህን መሰል ድፍን ቅል አምባገነኖች ሕዝብን ሲንቁ ሲንቁ ቆይተው በመጨረሻው በሕዝባዊ ማዕበል ተጠራርገዋል፡፡ እኛ ሀገር ውስጥ ብልኃት የሚያስፈልገን ታዲያ አሁን ነው፡፡ ከነሦርያና ከነሶማሊያ የተለዬን ችግር ፈቺ ሕዝብ መሆናችንን ለዓለም የምናስመሰክርበት አጋጣሚ በየበራችን እያኳኳ ነው፡፡ ይህች ዕድል ካመለጠችን ትርፋችን ፀፀት ብቻ ይሆናል፡፡… እርግጥ ነው የብዙዎቻችን እምነት በአንድዬ በመሆኑ ጥሎ አይጥለንም፡፡ ሰውዬው “እንደእናቴ ሳይሆን እንደሚስቴ አውለኝ” ብሏል አሉ፡፡ ጥሩ መመኘት ጥሩ ነው – ለሆነለት፡፡ “ግን”ን መርሳት ግን አይኖርብንም፡፡ ሰውዬው “ብመጣም ባልመጣም በሩን ዝጊው በጣም” ብሏል አሉ፡፡

ወያኔዎችን ለማንበርከክ ከእምቢተኝነት ሰላማዊ ትግላችን ጎን ለጎን የኢኮኖሚ አቅማቸውን የሚያዳክሙ እርምጃዎችን መውሰድ አማራጭ የማይገኝለት የትግል ሥልት ነው፡፡ ይህም ሲባል በማውደምና በማቃጠል ሳይሆን ሠርተው ትርፍ እንዳያግበሰብሱና መሞቻችንን የጦር መሣሪያ እንዳይገዙበት ማድረግ ነው፡፡ ፈርዶብን “እኛ”ና “እነሱ” በሚል ከተፈራረጅን አይቀር እኛ የነሱን ሸቀጥና አገልግሎት በገንዘባችን እየገዛን እነሱን ማክበር የለብንም፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት የተቀናጡብን፣ ያዋረዱን፣ ያደኸዩንና የገደሉን ይበቃል፡፡ ከአሁን በኋላ እኛም ነፍስ አውቀን ከነሱ ጋር ምንም ዓይነት ግብይት መፈጸም የለብንም፡፡ በአውቶቡሶቻቸው አለመሣፈር፣ በሱቆቻቸው አለመገበያየት፣ በአገልግሎቶቻቸው አለመጠቀም፣ በትምህርት ተቋሞቻቸው ራሳችንንም ልጆቻችንንም አለማስመዝገብ፣ በመዝናኛና በምግብ ቤቶቻቸው ዝር አለማለት፣ ወዘተ. ይገባናል፤ የሚነድፈንን እባብ እኛው ራሳችን መርዝ ማቀበል የለብንም፡፡ የሚወጋንን ኮርማ እኛው ራሳችን ማወፈር የለብንም፡፡ እኛን ያደኸዩን በቁጥጥራቸው ካዋሉት የመንግሥት ሥራና የንግድ እንቅስቀሴ በልዩ ሥልትና በሸር በማስወጣት እንደሆነ መርሳት አይገባንም፡፡ ሁልጊዜ ሞኝነትና ጅልነት ለባሰ መከራና ስቃይ እየዳረገን ከአንዱ ጨለማ ወደ ባሰበት ሌላ ጨለማ ስንዘፈቅ ኖረናልና ከአሁን በኋላ ለራሳችን እንወቅበት፡፡ … የኢኮኖሚውን ዱላችንን ስንሰነዝር ታዲያ በዘሩ ብቻ ተመሥርተን ንጹሑን ሰው እንዳንጎዳ መጠንቀቅ አለብን፡፡ ቁጥራቸው ሚዛን የሚደፋ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም በወያኔ ስም ከምናማቸው ወገኖቻችን ውስጥ ከምር የሚያዝኑልንና የሚቆጩልን ዜጎች አይጠፉምና በፈረንጆቹ ፈሊጥ “ሕጻንን ከነታጠበበት ውኃ ለመድፋት” የምንጥር ሰዎች ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡ ሁሉም ያልፋል – እስኪያልፍ ቢያለፋም፡፡ ሲያልፍ እንዳንተዛዘብ አሁን ጠንቀቅ ማለት አለብን፡፡

ጎንደርና ጎጃም ልውሰዳችሁና ትንሽ ላቆያችሁ፡፡ አንድ አላዋቂ ወይም ትዕቢተኛ የወያኔ አንፋሽ አጎንባሽ የዳሸን ቢራ ሲጠጣ ቢታይ አንድ እዚህ ግባ የማትሉት ተራ “ጨርቅ ለባሽ” ጠጋ ብሎ “ወንድማለም፣ የወንድሞችህን ደም እንዴት ትጠጣለህ!” ይለዋል፡፡ ሌሎቹም በዐይናቸው ሲገርፉት የሚገባበትን ያጣል፡፡ ያኔ ጠጪው በሀፍረት ይሸማቀቅና ያስከፈተውንም ቢራ ሳይጠጣ ከዚያ ቤት ውልቅ ይላል ወይም መጠጥ ይቀይራል፡፡ በዚህ መልክ ተቃውሞን በመግለጽ ጠላትን በኢኮኖሚ ማድቀቅ ይቻላል፡፡ ይህ ትግል ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የሰላማዊ ትግል አካል ነው፡፡ እነማህተመ ጋንዲን የመሳሰሉ የነፃነት አርበኞች ለሕዝባቸው ያስተማሩትና ሕዝባቸውን ለድል ያበቁበት ሁነኛ የነፃነት መንገድ ነው፡፡

ጨረስኩ፡፡ ስለኃ/ማርያም ግን ጥቂት ልበል እባካች – ሆድ ሆዴን እየበላኝ ከሚቀር፡፡ ይህ ዜና፣ ዜና አይደለም በመሠረቱ፡፡ የወያኔው  የሚዲያ አውታሮች የዚህን ነፈዝ ሰው “ሥልጣን መልቀቅ” ልክ አንድ የአውሮፓ መንግሥት ጠ/ሚኒስትር የለቀቀ ያህል ነፋፍተው ነው ያቀረቡት፡፡ ወግ ነው አሉ ሲዳሩ ማልቀስ – ሠላሣና ዐርባ ዓመት በሴተኛ አዳሪነት “ሥራ” ትተዳደር የነበረች መበለት ዛሬ ብታገባ ከቤት ስትወጣ ወግ ነውና ታለቅሳለች – እንደኃይለ ማርያም፡፡ እሱም – ኃይለ ማርያምም – እውነት መስሎት “የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር” መባል እንደሚያምረው ሲናገር ሰማሁ፤ በጣም ፍርፍር ብዬ ሳቅሁ፡፡ ማፈሪያዎች ናቸው፡፡ ይህን ኢቢሲ የሚባል ቲቪ እንዴት እንደሚጫወቱበት ስታዘብ አዘንኩለት፡፡ እንዴትስ ቢንቁን ነው እንደዚያ የሚጃጃሉብን ብዬም ገረመኝ፡፡ አሁን ማን ይሙት ኃ/ማርያም ባለሥልጣን ሆኖ ሞቶ እንደዚያ ያለ ዜና ይሠራል? ቤተ መንግሥት መጠበቅ ሥልጣን ነው? ለወያኔ የቤተ መንግሥት ወጥ ቤትና ዘበኛ ሲያጎበድድ ከርሞ፣ አንድን ሀገራዊ መረጃ ሕዝብ በሚዲያ ካወቀው በኋላ – ቋንጣ ከሆነ በኋላ – የሚሰማ ይህ ማፈሪያ “ ለሰላማዊ ሽግግር ስል ሥልጣኔን ለቀቅሁ” ይበለን? ለመሆኑ ከየትኛው ሥልጣኑ ነው የለቀቀው? እሱም ጌቶቹም ትንሽ አያፍሩም? ትንሹ የልጄ ልጅ ዜናውን ሲሰማ – እውነቴን የምላችሁ – “እንዴ፣ ዱሮውንስ ሥልጣን ነበረው እንዴ” ነው ያለው፡፡ ማፈሪያነታቸው እስከዚህን ድረስ ነው፡፡ ሰላም፡፡

ለበጎ አስተያየት ma74085@gmail.com

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.