ዲሞክራሲ ወይስ ተራ? (በሙሉቀን ተስፋው)

ትናንትና የኦሮሚያ ክልሉን ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳን የሚመለከት ጽሑፍ ፖስት ካደረግሁ በኋላ በርከት ያሉ አስተያየቶች በውስጥ መስመር ደርሰውኛል፡፡ ስለሆነም ሐሳቤን ይበልጥ ዘርዘር አድርጌ ነጥብ በነጥብ ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡

ሀ) የሚያስፈልገን የስርዓት ለውጥ ነው ብየ አምናለሁ፡፡
***

ሙሉቀን ተስፋው
ሙሉቀን ተስፋው

የወያኔ አገዛዝ ሊታረምና ሊሻሻል ከማይችልበት ደረጃ ላይ የደረሰ የግፈኞች አገዛዝ ነው፡፡ ሁላችንም አሳምረን እንደምናውቀው ይህን ስርዓት በግንባር ቀደምነት የሚዘውሩት የትግራይ ተወላጆች ቢሆኑም በሌሎች ብሔረሰቦች ስም የተቋቋሙት የወያኔ ቅምጥ ድርጅቶችም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ስለሆነም ዓላማችን ይህን ግፈኛ ስርዓት ከነግሳንግሱ ነቅለን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ሃቀኛ በሆነ መልኩ በሚያካትት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መተካት ከሆነ (መሆንም ይገባዋል) “ለማ መገርሳ ጠቅላይ ሚኒስትር ካልሆነ ሞተን እንገኛለን፤ አብይ ምንትሴ እንዲያ ካልሆነ እንታነቃለን” የሚለውን እጅግ አደገኛ ሐሳብ/አቋም ልንታገለው ይገባል፡፡

ይህ ሐሳብ አደገኛ ነው የምንልበት ምክንያትም የሐሳቡ አራማጆች ተቀዳሚ ዓላማ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን መመሥረት ሳይሆን “የእኛ ተራ ነው” የሚል እጅግ ኋላቀር አቋም ስለሆነ ነው፡፡ በትናንትናው ጽሑፌ እንደገለጽኩት ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ እንደአገር እንድትቀጥል ካስፈለገ መድኅኗ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ብቻ ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ ደግሞ ሁሉንም ሕዝቦቿን የሚያሳትፈው “አካታች የሆነና የጋራ አመራር የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት” (consociational democracy) እንጂ የአብላጫ ድምጽ ስርዓት አይደለም ተመራጭነት ያለው፡፡ ሁሉም ሕዝብ የሚወከልበት፤ አንድ ሕዝብ ወይም አንድ መሪ የበላይ፣ ሌላው የበታች ሊሆን የማይችልበት የፖለቲካ ስርዓት ብቻ ነው አገሪቷን ሊያድናት የሚችለው፡፡

ሆኖም ይህ አገሪቱንና ሕዝቦቿን ሊታደግ የሚችል መሠረታዊ ዓላማ ተዘንግቶ የዲሞክራሲ ሳይሆን የተራ ጥያቄ እየተራመደ ነው፡፡ “አያ በሬ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” እንደሚባለው የእኛው ወገኖችም በዚህ እጅግ አደገኛ ወጥመድ ውስጥ ሰተት ብለው ገብተው ሲፈተፍቱ እየታዘብን ነው፡፡ ያሳፍራል፤ ያሳዝንማል!! የዐማራ ልጆች ይህን አደገኛ አካሄድ አምርረን ልንታገለው ይገባል፡፡ በቅንነትና ባለማወቅ የጠፉ ወገኖቻችንንም ወጥመዱን እንዲረዱ መርዳት ይገባናል፡፡

ሁ) “መጀመሪያ ወያኔ ይውደቅ…”
***
ብዙ ወገኖች ወያኔ ይውደቅ ወይም ስልጣኑ ከወያኔ እጅ ይውጣ እንጂ ሌላው ሁሉ አሳሳቢ አይደለም ሲሉ ይሰማል፡፡ ይህ እጅግ የተሳሳተና ውድ ዋጋ የሚያስከፍለን አስተያየት ነው ብየ አምናለሁ፡፡ ስለሆነም አጥብቄ እቃወመዋለሁ፤ ሌሎች የዐማራ ልጆችም ይህን አደገኛ ሐሳብ እንዲቃወሙት በምችለው መንገድ ሁሉ እቀሰቅሳለሁ፡፡ ለምን?

ያለነው አፍሪካ ውስጥ ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ ደግሞ በአጋጣሚ ስልጣን የያዘ ኃይል ሌላውን ኃይል እንኳን ሊያሳትፍና ሊያካትት በተቃዋሚነት እንኳን እንዲኖር አይፈቀድለትም፡፡ በአገራችን ያየነውና የምናየው ይህንን ሃቅ ነው፡፡ ደርግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ሁሉንም አብረውት ሲሠሩ የነበሩ የፖለቲካ ኀይሎችን ሁሉ ነው ድምጥማጣቸውን ያጠፋው፡፡ ወያኔም በሽግግር መንግስት ዘመን አብረውት የነበሩትን እነኦነግን ሳይቀር አጥረግርጎና ሌሎችን ድርጅቶች አፈር-ድሜ አብልቶ ነው ስልጣኑን በብቸኝነት የተቆጣጠረው፡፡

ለዚህ ነው፤ ከወያኔ ውድቀት በኋላ የሚመሰረተው ጊዜያዊም ይባል የሽግግር መንግስት የግድ ከወዲሁ ሁሉን ያካተተ እንዲሆን ትግል ማድረግ የሚያስፈልገው፡፡ በሽግግሩ ወቅት አንድ ቡድን ወይም አንድ ግለሰብ ሁሉንም ነገር እንዲቆጣጠረው መፍቀድ ራስን እንደማጥፋት ይቆጠራል፡፡ ሁሉም ነገር ከተበላ በኋላ ‹ወይኔ!› ቢሉት የሚሆን አይደለም!!!

አዎ ወያኔ መወገድ አለበት፡፡ አዎ ወያኔ እንዲወድቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ መታገል አለበት፡፡ ሆኖም ከወያኔ በኋላ የሚመሆነውም ከአገዛዙ ውድቀት በፊት መልክ መያዝ ይኖርበታል፡፡ ዳግም እንዳንበላ በእጅጉ መጠንቀቅ አለብን!!!

ሂ) የዐማራና የኦሮሞ ግንኙነት
***
ዐማራና ኦሮሞ በከፍተኛ ደረጃ የተሳሰሩ ህዝቦች ናቸው፡፡ የእነዚህ ሁለት ህዝቦች ግንኙነትም የአገሪቱን ህልውና የሚወስን ጭምር ነው፡፡ ሆኖም የሁለቱን ህዝቦች አብሮነት ሊወስኑ የሚችሉ ተግባራት ባለፉት 27 ዓመታት ተፈፀመዋል፤ እየተፈፀሙም ነው፡፡ በርካታ ያልተፈቱ አጀንዳዎች ከፊታችን ላይ ተደቅነዋል፡፡ እነዚያን የቤት ሥራዎች ከስር ከስራቸው እየፈታን መሄድ ከሁለቱ ሕዝቦች ኤሊቶች የሚጠበቅ ታላቅ ተግባር ነው፡፡

ለዚህ ነው፤ “የእኛ ተራ ነው” የሚለው አካሄድ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ያሉብንን የቤት ስራዎች እንዳንፈታ የሚያደናቅፍ ደንቀራ ስለሆነ ሊታረም የሚገባው፡፡

መወያየት መልካም ነው፤ እስቲ እንወያይ!

#ድል_ለዴሞክራሲ!
#የዐማራ_ተጋድሎ ይቀጥላል!!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.