የአሜሪካ መንግሥት፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላይ ጫና ማሳደር ለምን አስፈለገው?

 ፋኑኤል ክንፉ/ሰንደቅ

የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት በአንቀጽ 93 ቁጥር 1(ሀ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምን አስቻይ ሁኔታዎች ሊታወጅ እንደሚችል አስቀምጧል። ይኸውም “የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፣ ማናቸውንም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝቡን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፤ የፌደራሉ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ስልጣን አለው።” እንዲሁም (ለ)፣ “የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት” የክልል መስተዳድሮች በክልላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጁ ይችላሉ።

አዋጁ የሚጸድቀው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት በሥራ ላይ ባለ ጊዜ የታወጀ ከሆነ በታወጀ በ48 ሰዓታት ውስጥ ለምክር ቤቱ መቅረብና መጽደቅ አለበት፡፤ አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት ሁለት ሶስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ካገኘ ይጸድቃል። በሁለት ሶስተኛ ድምጽ ካልተደገፈ ውደቅ ይሆኗል። ይሻራል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባልሆነበት ወቅት የሚታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ ያለበት አዋጅ በታወጀ በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ ነው። በተጨማሪም፣ በሚኒስትሮች ምከር ቤት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምከር ቤቱ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ሊቆይ የሚችለው እስከ ስድስት ወራት ነው። የህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምፅ አንድን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በየአራት ወሩ በተደጋጋሚ እንዲታደስ ሊያደርግ ይችላል።

ከላይ የሰፈረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ የሚደረገው በኢትዮጵያ ግዛት እና በኢትዮጵያ ዜጎች ላይ ብቻ ነው።

 

የአሜሪካ መንግስት አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲ በኩል በኢትዮጵያ መንግስት የተጣለውን የአስቸኳይ አዋጅ አልስማማም ሲል መግለጫ አውጥቷል። የአሜሪካ መንግስት ዕምቅ ፍላጎት ምን እንደሆነ ከመገመት በፊት፤ በኢትዮጵያ ባለው ተጨባጭ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ በሕገ መንግስት የሰፈሩ የዜጎች መብቶች አልተደፈሩም የሚል መከራከሪያ አሜሪካኖች ቢያቀርቡ ክርክሩን ያፋፋው ነበር። ሆኖም ቢያንስ የሚከተሉት በሕገ መንግስት የሰፈሩ የዜጎች መብቶች በአደባባይ የተጨፈለቁ መሆናቸውን ያሳያሉ በሚል አቅርበናቸዋል።

አንቀጽ 16፤ ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት አለው።

አንቀጽ 14፤ የሕይወት መብት፤ ማንኛውም ሰው በሕይውት የመኖር መብት አለው። ማንኛውም ሰው በሕግ የተደነገገ ከባድ ወንጀል ቅጣት በስተቀር ሕይወቱን አያጣም።

አንቀጽ 26 የግል ሕይወት የመከበር የመጠበቅ መብት፤ (1) ማንኛውም ሰው የግል ሕይወቱ፣ ግላዊነቱ፣ የመከበር መብት አለው። ይህ መብት መኖሪያ ቤቱ፣ ሰውነቱና ንብረት ከመመርመር እንዲሁም በግል ይዞታው ያለ ንብረት ከመያዝ የመጠበቅ መብትን ያካትታል።

አንቀጽ 32 የመዘዋወር ነፃነት፤ ማንኛውም የኢትዮጵያ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሀገሪቷ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት፣ እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነፃነት አለው። እንዲሁም፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወደ ሀገሩ የመመለስ መብት አለው።

አንቀጽ 40 የንብረት መብት፤ ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ የንብረት ባለቤት መሆኑ/መሆኗ ይከበርለታል/ ይከበርላታል። ይህ መብት የህዝብን ጥቅም ለመጠበቅ በሌላ ሁኔታ በሕግ እስካልተወሰነ ድረስ ንብረት የመያዝና በንብረት የመጠቀም ወይም የሌሎችን ዜጎች መብቶች እስካልተቃረነ ድረስ ንብረት የመሸጥ፣ የማውረስ ወይም በሌላ መንገድ የማስተላለፍ መብቶች ያካትታል።

ከላይ ያሰፈርናቸው በሕገ መንግስት ጥበቃ የተደረገላቸው የዜጎች መብቶች በሀገሪቷ ውስጥ በተከሰቱ የፖለቲካ ቀውሶች መነሻ ኃላፊነት በማይሰማቸው አካሎች ተጥሰዋል። ማሳያዎችን በተወሰነ መልኩ እንመልከታቸው።

በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልል ድንበር ዙሪያ በተነሳ ግጭት በኦሮሚያ ልጆች ላይ የተፈጸመው ድርጊት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዳር እስከ ዳር ያሸማቀቀ፣ አንገት ያስደፋ ነው። በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፣ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ኢሰብአዊ ድርጊቶች ተፈጽሞባቸዋል። በሌላውም የሶማሌ ተወላጆች ላይ መፈናቀልና ዘግናኝ ግድያዎች ደርሶባቸዋል። በሁለቱ ሕዝቦች ላይ የተፈጸመ ድርጊት የሕዝብ ፀብ አለመሆኑን፤ ከሁለቱ ሕዝቦች አዳምጠናል። በተግባሩ ላይ የተሰለፉ ኃይሎች እስካሁን ድረስ ተበዳዮችን በሚያረካ እና የህግ የበላይነትን ባጎናጸፈ መልኩ የተወሰደ እርምጃ የለም። ዜጎች አሁንም ከቤታቸው ውጪ ናቸው። በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ሕዝባዊ እርቅ ለማምጣት የተደረገ ኮንፈረንስ የለም። ሁለቱ ሕዝቦች እንደተኮራረፉ ይገኛሉ።

በአማራ እና በትግራይ ክልል የቅርብ ጊዜውን ብናነሳ፤ በተለይ በወሎ አካባቢ እና በራያና አዘቦ አካባቢ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አደጋ ውስጥ ወድቋል። የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጧል። ሕዝብ ለሕዝብ ሊያቀራርቡ የሚችሉ ሕዝባዊ ኮንፈረንሶች በማዘጋጀት ልዩነቶች እንዲጠቡ የተደረገበት አግባብ የለም። የዜጐች ንብረት እና ሕይወት ጠፍቷል።

እንዲሁም በርካታ አካባቢዎች ላይ የዜጎች ንብረት በአደባባይ በጠራራ ፀሐይ ተቃጥሎ ወድሟል። በሀገራቸው ሃብት የማፍራት መብታቸውን የሚያስጠብቅ መደበኛ የህግ አግባብ ጠፍቷል። ዜጎች በአንድም በሌላ መልኩ የመኖር ሕገመንግስታዊ መብቶቻቸው ተገፎ፤ ተገድለዋል። አሁንም እንደማይገደሉ ዋስትና መስጠት የቻለ አካል የለም።

ሌላው ጠርዝ በያዘ የዘረኝነት አስተሳሰብ ዜጎች ተዘዋውረው መስራት አልቻሉም። በሕይወት መኖርን አማራጭ አድርገው፣ ከሥራ ታቅበው በቤቶቻቸው ውስጥ ይገኛሉ። ነገሮች ባስ ሲሉ ደግሞ፣ አካባቢውን እንዲለቁ ጫና ይደረግባቸዋል።
በደቡብ ሕዝቦች መጤ ነጋዴዎች በሚል የበርካታ ዜጎች ንብረት በቃጠሎ ወድሟል።

በተጨማሪም በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያላቸው ሀገር አቋራጭ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ እና አውቶብሶች በእሳት እየነደዱ ከሥራ ውጪ ሆነዋል። በተለይ የግለሰብ ንብረት በቃጠሎ ሲወድም፣ ተያይዞ የሚመጣው ችግር በመኪና ቃጠሎ ላይ ብቻ የሚቀር አይደለም። በጣም አሳዛኙ ጉዳይ ደግሞ በረብሻ እና በፖለቲካ ቀወስ ጋር ተያይዞ ለሚጠፋ ንብረት ኢንሹራንስ የለውም። በዚህ መልኩ ንብረታቸውን የሚያጡ ዜጎች፣ በዚህች ሀገር ላይ ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ወድቀዋል። ከሀገሪቷ ኢኮኖሚ ርቀዋል።

በተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ለአደጋ ተጋልጠዋል። በስራ ላይ የሚገኙ ባለሃብቶች ንብረቶቻቸው አደጋ ውስጥ ነው የሚገኘው። ለአውሮፓ ገበያ የተዘጋጀው የአበባ ምርት በተከሰተው አለመረጋጋት በወቅቱ ሳይላክ ቀርቷል። ይህ ለውጭ ባለሃብቶች የሚሰጠው ትርጉም ከፍተኛ ነው። በዓመት 55 በመቶ የአበባ ምርት ወደ ውጪ የሚላከው በፈረንጆች የፍቅር ቀን ሳምንታት ውስጥ ብቻ በመሆኑ ሳይላኩ በቀሩ የአበባ ምርቶች ለኪሳራ መጋለጣቸውን እየተናገሩ ነው።

በአጠቃላይ ሲታይ ሀገራችን ሕገ-መንግስታዊ ቁመና በተላበሰ መልኩ ሕግ እየተከበረ ያለባት ሀገር አይደለችም። በመደበኛ ሕግ ችግሮችን ለመፍታት የሚታሰብ አይደለም። በተለይ ዜጎች ያላቸውን በሕይወት የመኖር መብት ለመጠበቅ መደበኛው የሕግ አሰራር አስተማማኝ አለመሆኑን ሁላችንም ያየነው የአደባባይ ጉድ ነው።

ለዚህም ነው፤ የአሜሪካ መንግስት ከምን መነሻ “አልስማማም” የሚለው? የአሜሪካ መንግስት በእኛ ነፃ ሀገር ውሳኔ ላይ የመስማማት አለመስማማት መብትን ከወዴት ነው ያመጣው? የአሜሪካን መንግስት የአንድ ሀገር ልዋዕላዊ ውሳኔን የመፃረር መብት አለው ወይ?

የአሜሪካ መንግስት እንደወዳጅ ሀገር ምክር ቢለግስ፣ ሁላችንም እናዳምጠዋለን። ምክንያቱም ከአሜሪካ መንግስት ጋር ያለን የረጀም ዘመን ወዳጅነት አንዱ ሌላውን ሊመክር የሚያስችለው የሞራል ደረጃ በመኖሩ ነው። ከዚህም በላይ የአሜሪካን ግብር ከፋይ ሕዝብ፤ በተቸገርን ጊዜ ከጎናችን የሚቆም ነው። በተለይ በኤች አይ ቪ ኤድስ ሀገር አቀፍ ዘመቻ የማንረሳው የአሜሪካ ሕዝብ ውለታ አለብን። ወባን ለመከላከል ከፍተኛ ድጋፍ ከአሜሪካን ሕዝብ አግኝተናል፣ እያገኘንም እንገኛለን።

በሌላ መልኩ ከተመለከትነው ግን፣ የአሜሪካ መንግስት ፖለቲከኞች ስለዴሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብቶች የመነጋገር የሞራል ደረጃቸው እንዴት ነው የሚታየው? ይህም ሲባል፣ ሳዑዲ ዓረቢያ በየመን ሕፃናት ላይ እየረገፈችው ያለውን ቦምብ ማን ነው ያስታጠቃት? በተሳሳተ መረጃ አለም አቀፉን ሕብረተሰብ በማታለል ኢራቅን ያፈረሰው ማን ነው? የሶሪያን ምድር በአሸባሪዎች ያጥለቀለቀ ከግማሽ ሚሊዮን ዜጎች በላይ ሕይወት የቀጠፈውን ጦርነት ከጀርባ የመራው ማን ነው? እና ሌሎችንም ማንሳት እንችላለን።

ዛሬ ላይ ኢራቅ መልሳ ለመገንባት ከ100 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ያስፈልጋታል፤ ሶሪያ እንደሀገር ለመቆም ከ300 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ያስፈልጋታል። በእነዚህ ሀገሮች ውስጥ ለደረሰው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት የአሜሪካ ፖለቲከኞች ድርሻ ምን ያህል ነው?

ለዚህም ነው ከላይ ከሰፈሩት በሀገራችን ውስጥ ካሉት ጥሬ ሐቆች መነሻ ሁላችንም መመለስም መጠየቅም ያለብን፤ የአሜሪካ መንግስት በአንድ ነፃ ሀገር የአስቸኳይ አዋጅ ውሳኔ ላይ ጣልቃ በመግባት “አልስማማም” የሚል አቋም ማራመድ ለምን አስፈለገው? የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባልሆነበት ወቅት የሚታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ ያለበት አዋጅ በታወጀ በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ ነው፤ ይላል። ከዚህ ቀደም ብሎ የአሜሪካ መንግስት “አልስማማም” የሚል አቋም በማንጸባረቅ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ላይ ጫና ለማሳደር የሄደበት ርቀት በጣም አስገራሚ ነው።

ሌላው ለአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ መንግስት ውስጥ በአምስተኛ ረድፍ ከተሰለፉ ባለስልጣናት ድጋፍና መረጃ ውጪ ይህንን አቋም የአሜሪካ መንግስት ሊይዝ ይችላል ተብሎ መውሰድ በጣም ከባድ ነው። ሁላችንም እንደምናውቀው፤ የአሜሪካ መንግስት ፖለቲከኞች ገዢው ፓርቲ እንደመንግስት እና እንደ ፓርቲ ከቻይና መንግስትና ፓርቲ ጋር ያለው የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ግንኙነት በጤናማ መንገድ እንደማይመለከቱት ይታወቃል። ስለዚህም ገዥው ፓርቲን ጫና ውስጥ በመክተት ለማንበርከክ እየሰሩ ስለመሆኑ የሮኬት ሳይንስ ማጥናት አያስፈልግም። ለነገሩ “ሞኝ የቄስ ልጅ መድሐኒዓልም አጎቱ ይመስለዋል” እንደሚባለው ነው።

በዚህ ጸሃፊ እምነት ግን፣ የአስቸኳይ አዋጁ የዘገየ ግን ጠቃሚ እርምጃ ነው። ይህ ማለት አስቸኳይ አዋጁ ሁሉንም ችግሮች ይፈታል ማለት አይደለም። ሀገራችን የደረሰችበት ፖለቲካዊ ቀውስ የሚፈታው በተረጋጋ ሁኔታ ሁሉም ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ፤ በሕግ የበላይነት ሥር በሚደረግ ውይይት ብቻ ነው። የአሜሪካና የገዥው ፓርቲ ግንኙነት ከኢትዮጵያና ከዜጐች ሕልውና በተች ነው። የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤትም ከዜጎቹ እንጂ ከአሜሪካ መንግስት ፖለቲከኞች ጋር ውግንና እንደሌለው ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.