ጥሪ ለደኢህዴን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሙሉ (ዋካ ከስዊድን)

“” ጮሻይ ዪን አቻይ አሼና ” ከውስጥ ገፍቶ የመጣን ትውኪያ ጥርስ አያቆመውም

                                                           ዋካ ከስዊድን

በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ውስጥ ከሚገኙት የምርጫ ወረዳዎች የተውጣጣችሁ የፌዴራል ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሆናችሁ ወንድምና እህቶች በያላችሁበት የከበረ ሰላምታዬ ይድረሳችሁ!

ይህንን መልዕክት የማስተላልፍላችሁ አንድ የክልሉ ተወላጅ የሆንኩ ኢትዮጵያዊ ወንድም ነኝ፡፡ መልዕክቴ በሌሎች ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ያልተላለፈና የማታውቁት ያልሰማችሁት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ እንደ በጎች በቀኝ እንደ ፍየሎች ደግሞ ከግራ የምንቆምበት ትክክለኛው የሰማያዊው የፍርድ ቀን እንደሚጠብቀን አብዛኛዎቻችን እንደምናምን ሁሉ አሁን በምንሰራውና በምንወስነው የምድራዊው ሥራ ሕዝብ የሚፈርድበት እያንዳንዳችን እንደየሥራችን የምንጠየቅበት እንደበጎነታችን የምንመሰገንበት እንደወንጀላችን ደግሞ ለፍርድ የምንቆምበት አንድ የፍርድ ቀን በቅርብ እፊታችን እንደሚኖር አምናለሁና የሰማችሁትም ስሙት ባትሰሙትም ስሙት ብዬ የጉዳዩን እጅግ አንገብጋቢነት አበክሬ በመግለጽ ከሕዝብና ከእውነት ጎን እንዳትለዩ ለማሳሰብ ነው፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን እንደምትገነዘቡ እሙን ነው፡፡ ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራት / TPLF / የ”ኢሕአዴግ” አባል የሆኑትን አራቱን ብሔራዊ ድርጅቶችን   /ህወሃትን ጨምሮ / አጋር ፓርቲዎች እያለ የሚያንቆለጳጵሳቸውንም የብሔር ድርጅቶችን ጠቅልሎ የሚመራው የሚቆጣጠረው አመራሮችን  የሚሾመው የሚሽረው የሚቆርጠውም ሆነ የሚፈልጠው ህወሃት መሆኑን እናንተን ለማስረዳት መሞከር ድፍረት ነው፡፡

እንደምታውቁት የደቡብ ክልል አወቃቀር በራሱ የህውሃት የእጅ ሥራ ውጤት ነው፡፡ አንዳች ታሪካዊ መሠረት የሌለው በጉልበትና በማን አለብኝነት የተመሰረተ አስተዳደር ነው፡፡ ከትግራይ ክልል ጋር እንኳን ብናነጻጽር ቢያንስ አራት ክልል ሊሆን የሚችል ሰፊ የህዝብ ቁጥርና የቆዳ ስፋት ያለው በጫና ያለ ሕዝቡ መልካም ፈቃደኝነት የተዋቀረ ክልል ነው፡፡

ከወያኔ ቀደም ሲል በነበረው የሀገር አስተዳደር መዋቅር የትግራይ ክፍለ ሀገር 7 አውራጃ የነበረው አንድ ክልል እንዲሆን ሲከለል ጋሞ ጎፋ ከፋ ከፊል ሸዋና ሲዳሞ አራት  ክፍለ ሀገሮች በአንድ ደቡብ ክልል  እንዲዋቀሩ የተደረገበትን ግፍ በግልጽ ታውቁታላችሁ፡፡ ሁሉም የተከናወነው በህወሃት ውሳኔ ነበር፡፡ አራትና አምስት የተለያዩ ቋንቋዎችን ቀይጦ ሌላ አዲስ ቋንቋ ለመፍጠር ቤተ ሙከራ የነበረውም  የዚህ ሕዝብ ክልል ነበር፡፡ ይህ ድርጊት ትክክል አይደለም በሚል እንዲስተካከል  በተለያየ ወቅት ጥያቄ ያነሱና ይህ እንዲስተካከል ጥረት ያደረጉ የክልሉ ምሁራን በሹመት ከተሰጣቸው ቦታ ብቻ ሳይሆን  በሜሪታቸው  ከሚሰሩት የሙያ ሥራቸው ተወግደዋል፡፡

የደቡብ ክልልን ህወሃት ያዋቀረው የክልሉን ጥሬ ሀብትና ማዕድናትን በመመዝበር  የአገዛዝ ዘመኑን ለማርዘምና ለኢኮኖሚ ግብዓት እንዲያመቸው ነው፡፡ የክልሉ አወቃቀርና ያለው ነባራዊ ሁኔታ ለአስተዳደር ለልማትና ዕድገት በፍጹም እንደማይመች ግልጽ ነበር፡፡ ለምሳሌ አንድ አርሶ አደር ለአቤቱታ ከማሻ ተነስቶ እስከ አዋሳ ከ3-4 ቀን ፈጅቶበት ተጉዞ የትራንስፖርት ወጪውን ችሎ ፍትህ ሊያገኝ እንደማይችል እንዲሁም ለልማት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ከክልል ዋና ከተማ ወደ ተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ማድረስ ከፍተኛ ወጪ የሚያስከትል መሆኑ ይፋ ነበር፡፡ አሁንም በተጨባጭ ሕዝቡን የልማት ተቋዳሽ ለማድረግ በፍጹም አልተቻለም፡፡ እጅግ ብዙ ማሳያዎች እንዳሉ ታውቃላችሁ፡፡

ሕዝቡ ልማትን ይሻል፡፡ ሌሎችንም ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ያነሳል፡፡ የሚሰጠው ምላሽ  ግን ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ እልዲሉ ነው፡፡  የፖሊሲ ችግር አይደለም የመልካም አስተዳደር ነው እንጂ የሚል ቅጥፈት፤ ማንኛውንም ጥያቄ ጠይቁ ነገር ግን  ሕገመንግሥት ይከበር የሚል ማወናበጃ፤ አባይን እየገደብን ነው ህዳሴያችንን እናስቀጥላለን የሚል አሰልቺ ወሬ ወዘተ እየፈበረከ የሕዝቡን ሰላማዊ  የፍትህና የልማት ጥያቄ አቅጣጫ በማሳትና በማቆልመም  ህወሃት የራሱን የሥልጣን ጊዜ ለማራዘም የሚጠቀምበት እንክብል መሆኑን  እያያችሁት ነው፡፡ አሁን ይባስ ብሎ ወደ ለየለት ጣሊያናዊ አገዛዝ ተሸጋግሯል፡፡ ወታደራዊ መንግሥት ሊገዛን ጀምሯል፡፡  ታዲያ ሊፈቀድለት ይገባል?  ይኼ ማብቂያው መቼ ነው?

ገዢው ህወሃት ሀገሪቱን ለመቆጣጠርና ሕዝቧን ለመግዛት እየተጠቀመ ያለው ዘዴ ግልጽ ነው፡፡ ሕብረተሰቡን በዘር በቋንቋ በመንደር በማደራጀትና እርስ በርስ አንዱ ብሔር በሌላው ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበትና መግባባት እንዳይኖር አቅዶ በመሥራት ነው፡፡

ጠቅለል አድርገን ስናየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ አጭርና ግልጽ ነው፡፡ በሀገሬ የመጻፍ የመናገር የመደራጀት ነጻነት ይኑረኝ ነው፡፡ እኩልነት ፍትህና ዴሞክራሲ ይገባኛል ነው፡፡ ከአያት ቅድመ አያቶቼ በወረስኩት መሬት ላይ ልኑርበት አፈናቅላችሁ ሜዳ ላይ ለአውሬ አትስጡኝ ነው፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ተዘዋውሮ ባሻው ቦታ የመኖር ንብረት የማፍራት መብቱ ይከበር ነው፡፡ ያለ አግባብ ሰውን የማሰር የማሰቃየት በሐሰት የመወንጀልና የመፍረድ እንዲሁም የመግደል ሂደት ይገታ ነው፡፡ ዘርን መንደርን ቤተሰብን መሠረት ያደረገ የመጥቀምና የመበደል አካሄድ አይመቸኝም ነው፡፡ ለጉልበተኛ የመገዛትና የባርነት ታሪክ የለኝምና ባሪያ ሆኜ ለማንም አልገዛም ነው፡፡ በሀገሪቱ ሥልጣን የሚያዘው በጉልበት ሳይሆን በሕዝብ ፈቃደኝነትና በእውነተኛ የሕዝብ ምርጫ ይሁን ነው፡፡ የጌታና የሎሌ ሥርዓት ይብቃ ነው፡፡ የሀብት ፍትሐዊ ሥርጭት ይኑረን ነው፡፡ በአጭሩ የጋራችን የሆነች ህዝቧ በእኩልነት የሚኖርባት ኢትዮጵያ የምትባል የጋራ ሀገር ትኑረን ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ሕዝቡ ሆ ብሎ ሥርዓቱን በቃኸን ብሎ በእንቢተኝነት ትግሉ ጠንክሮ እየታገለ እየታሰረ እየተደበደበ እየሞተ ይገኛል፡፡

በግፍ የታሰሩት የተደበደቡት የተገደሉት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ናቸው፡፡ በደላቸው ሊሰማን ሊያመን ይገባል፡፡ የጉራጌ ዞን በደቡብ ክልል ከሚገኙት ዞኖች አንዱ ነው፡፡ በጉራጌ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ወልቂጤ በውጭ ድጋፍ የሚሰራ ሆስፒታል የመሰረት ድንጋዩ ተተክሎ ግንባታው ሲጠበቅ በጀቱን ወያኔ ውሃ አጠጣው፡፡ በዚህ የተነሳ ሕዝቡ ሆስፒታላችን ይሰራልን የሚል ጥያቄ አቅርበ፡፡ የተሰጠው ምላሽ ግን  እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ ለምን ትጠይቀናለህ በሚል ድብደባ እስራትና ግድያ ሆነ፡፡

ወያኔ የአገዛዝ ሥርዓቴ ወደዳችሁም ጠላችሁ ይቀጥላል ብሏል፡፡ በተግባርም በእንቢተኝነት ለሰልፍ የወጣን ሕዝብ በመደብደብ በማሰር በመግደል ሕዝባዊውን እንቅስቃሴ ለማቆም እየሰራ ይገኛል፡፡ በቀጣይ ምንም ዓይነት ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በመላው ሀገሪቱ እንዳይከናወን ለማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል፡፡ በዚህ አዋጅ አንድ ዜጋ እንዲጠቀም የተተወለት ነገር ቢኖር የምንተነፍሰው አየር ብቻ ነው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዓላማ ሕዝቡን በማፈንና ሰቆቃውን በማብዛት ሀገሪቱን ለመዝረፍ እንዲሁም በሕዝብ እንቢተኝነትና አልገዛም ባይነት እየመጣ ያለን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማቆም ያስችለው ዘንድ ነው፡፡ ይህ አዋጅ የሚጸድቀው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2/3ኛ አባላት በድምጽ ስትደግፉት ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ  ከጥቂት ሳምንታት በፊት የአዲስ አበባን ልዩ ጥቅም ለማስከበር ይጠቅማል የሚል ሕግ ለማስጸደቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበውን አጀንዳ አስተውሉት፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም ማስከበሪያ አዋጅ በሚል ወያኔ ያቀረበውን አጀንዳ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሆኑት የኦሮሚያ ክልል ጓደኞቻችሁ ወቅታዊ አይደለም የኦሮሞ ሕዝብ ያልመከረበት ነው ከአምስት መቶ ሺህ በላይ ቁጥር ያለው ኦሮሞ የሆነ ሕዝብ በዘሩ ምክንያት ብቻ ከሶማሌ ክልል ከቤትና  ከንብረቱ ተፋናቅሎ በድንኳን ውስጥ የተጠለለበትና የእኛን ድጋፍ በሚሻበት ሁኔታ ላይ ነንና ይህን አጀንዳ ልንወያይበት ልናጸድቀውም አይገባም ብለው ውድቅ  አድርገውታል፡፡

እነዚህ የኦሮሞ ህዝብን ወክለው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚገኙት አባላት ለሕዝባቸው ለክልላቸው  ልማትና ጥቅም መቆማቸውን በተግባር አሳይተዋል፡፡ ወያኔ እንዳሻው ሕዝብን ከሕዝብ ብሄርን ከብሄር ለማጋጨት የሳበውን ጥቁር ካርድ አስጥለውታል፡፡ በዚህ ተግባራቸው ታሪክ ሰርተዋልና ሲዘከሩ ይኖራሉ፡፡

አሁን ተራው የፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሙሉ ሆኗል፡፡ እናንተን የሚመለከት ነገር በግልጽ መጥቶባችኋል፡፡ ልትሸሹት አትችሉም፡፡ ነገ አልሰማሁም የምትሉት አይደለም፡፡ ከሌሎች የኦሮሞና የአማራ እንዲሁም የጉራጌ ወንድሞቻችሁ ጎን በመሰለፍ ሕዝብንና ሀገርን የምትታደጉበት ከባድ ኢትዮጵያዊና ሕሊናዊ  ውሳኔ እንድታስተላልፉ የሚሻ ጥያቄ ከፊታችሁ ይጠብቃችኋል፡፡

ይኸውም ወያኔን ወግኖ ሕዝብንና ሀገርን አደጋ ውስጥ የመጣል የክህደት ውሳኔ ማስተላለፍ ወይም ሕዝብንና ሀገርን በመታደግ ታሪክ ሰርቶ ኢትዮጵያችን ይህን የተጋረጠባትን የመፈረካከስና ልጆችዋ እርስ በርስ እንዲተላለቁ የተወጠነን ጸያፍ የሆነን የወያኔን እኩይ መንገድ ዘግቶ ወደ ዴሞክራሲ ፍትህና እኩልነት ማሻገር መቻል፡፡ የሚጠብቃችሁ ምርጫ ይህ ነው ፡፡ አንዱን መንገድ መምረጥ የግድ ነው፡፡

አሁን ሀገራችን ያለችበትን ተጨባጭ እውነታ አስሉ፡፡ የወያኔ ግዢዎች የጥፋት ተልዕኮአቸውን ጊዜ ለማርዘም የቻሉትን ከመጣር ባሻገር ሀገርን መቦጥቦጥና መዝረፍ ሕዝብን በአፈሙዝ ረግጦና አፍኖ መግዛት ከማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸውን አውቀውታል፡፡ ድጋፍ የሚያደርጉለት ምዕራባውያን ሀገሮች ጀርባ እንደሰጡት ሰሞኑን በአገዛዙ ላይ የሚያሰሙትን ግልጽ ተቃውሞ እያየን ነው፡፡

የፖለቲካ ተቃዋሚም ሆነ ጋዜጠኛ ማንም ግለሰብ በፖለቲካ አመለካከቱ የተነሳ የታሰረ የለም ወንጀለኛና አሸባሪ እንጂ እያለ የሚያላግጠው ቡድን ሳይወድ በግድ በግፍ ያሰራቸውን እንዲፈታ የሚያስገድድ ሀገር አቀፍ የእንቢተኝነት ተቃውሞ ሀሪቱን እየናጣት ይገኛል፡፡ በተግባርም ይማላገጡ ሂደት በቅቶ እስረኞችን መፍታት ጀምረዋል፡፡

በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በሀገሪቱ የለውጥ መምጣት የግድ አስፈላጊና ወሳኝ እንደሆነ እያስገነዘቡ ያለበት ጊዜ ነው፡፡ የነጻነት ታጋች ከሕዝቡ ጎን በመሰለፍ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንና ይህንንም እየተገበሩ እንዳለ እያየን ነው፡፡ የሽግግር መንግሥት በመመስረት ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማምጣት ከፍተኛ ጥረትና ትግል እየተካሄደ ነው፡፡

ከላይ እንዳልኳችሁ ወክለነዋል ብላችሁ ለምታስቡት ሕዝብ የነጻነት የዴምክራሲና የእኩልነት ባለቤትነን የሚያጎናጽፈውን ታላቅ ወሳኝና ታሪካዊ ውሳኔ የምታስተላልፉበት ጊዜ ላይ ደርሳችኋል፡፡ እውነቱን እውነት ነው ብላችሁ ልትወስኑ አሊያም ፈርታችሁ ወይም ሆዳችሁ በልጦባችሁ እድሜ ልካችሁን የምትጸጸቱበት ከለይ ከፈጣሪም የሚያስጠይቃችሁ እንዳይሆን  እንድታስተውሉ አሳስባችኋለሁ፡፡ በምድር ወክለነዋል  መርጦናል ከምትሉትም ሕዝብ ፊት ቀርባችሁ በሥራችሁ  በፀረ ሕዝብ ውሳኔያችሁ ወደ ፍትህ የምትቀርቡበት ቀን ይኖራልና ለውሳኔ ድምጽ እጅ ስታወጡ አስተውሉ፡፡

በታሪክም ፊት የምታፍሩበትን ሁኔታ የሚፈጥር ታላቅና ወሳኝ መድረክ ነውና እውቁ፡፡ ስም ከመቃብር በላይ ይኖራልና ከሕዝባችሁ ጎን በመቆም የትክክለኛ ሕዝባዊ ውሳኔ አካል እንድትሆኑ አሳስባችኋለሁ፡፡ ይህ አጋጣሚ ቀደም ሲል በሰራችሁት የበደል  ሥራ ወይም  በውሳኔያችሁ ቅር የተሰኘን ዜጋን ክሳችሁ ይቅርታ የምትቀዳጁበት ዳግም ላታገኙት የምትችሉት ትልቅ አጋጣሚም ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡

ለማጠቃለል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዳያልፍ በማድረግ እንዲሁም ለሀገራዊ መግባባት ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽግግር ሂደት እንዲፈጠር የድርሻችሁን ተወጡ፡፡ ” ጮሻይ ዪን አቻይ አሼና ”  ከውስጥ ገፍቶ የመጣን ትውኪያ ጥርስ አያቆመውም እንዲሉ የዳውሮ አባቶች የህዝቡ የእንቢተኝነት ትግል ከግቡ ሳይደርስ አይቆምምና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ቁሙ፡፡ አበቃሁ፡፡

 

 

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.