አዲሱ የዶ/ር አቢይ መንገድ (ወንድወሰን ተክሉ)

**መነሻ ጭብጥ-

የኦህዴድ ስራ አስፈጻሚ አመራር ድንገት ዶ/ር አቢይን በአቶ ለማ መገርሳ  ቦታ  የድርጅቱ ሊቀመንበር  አድርጎ  መሾም  በአንድ  ድንጋይ  ሁለት  ወፍ እንዲሉ የህወሃት ተመራጭና እጩ የተደረጉትን ዶ/ር ወርቅነህ ገበያሁን የጠቅላይ ምኒስትርነት ህልም በአጭሩ ሲቀጭ በሌላ በኩል ደግሞ ድርጅቱ ይዟቸው ለተነሱት የለውጥ አጀንዳዎቹ ተፈጻሚነት የሚያግዘውን የራሱን ተመራጭ እጩ ማቅረብ አስችሎታል፡፡

የኦህዴድ ሊ/ር እና  የኦሮሚያ  ፕሬዚዳንት  በሆኑት  አቶ  ለማ  መገርሳና ዶ/ር አቢይ አህመድ መካከክ የተካሄደው የስልጣን ሽግሽግ ድርጅቱ የኢህአዴግን ሊ/ነትን ስልጣን እንደተለመደው ለህወሃት በጎፈቃጅነት ለመተው እንዳልፈለገ ከበቂ በላይ ማስረጃ ሲሆን በዚህ ባለተጠበቀ እርምጃውም ህወሃትን አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተተ መረዳት ይቻላል፡፡

እንደ የሀገሪቱ ህገ መንግስት ደንብ የፌዴራሉ ጠ/ሚ የሚሆነው የኢህአዴግ ሊ/ር የሆነ ሲሆን ለኢህአዴግ ሊ/ነት የሚወዳደረው ደግሞ የኢህአዴግ አባል የሆኑት አራት ድርጅቶች ሊቀመንበር የሆነ በመሆኑ አቶ ለማ መገርሳ ይዘውት የነበረውን የኦህዴድ ሊ/ነቱን ለዶ/ር አቢይ አህመድ በመስጣት እሳቸው ደግሞ በዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ተይዞ የነበረውን የምክትል ሊ/ነትን በመያዝ የህወሃቱን ተመራጭ እጩ ከመጫወቻው ሜዳ ውጪ በማሽቀንጠር ህወሃትን ኩምና ክምሽሽ አድርገው ተገኝተዋል፡፡

ብአዴን በእነ አቶ በረከት ስምኦን እና በእነ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ቡድን መካከል እያካሄደ ያለውን ውስጠ ድርጅታዊ እሰጠ አገባ  በአንደኛው  ወገን አሸናፊነት ገና ስላላገባደደ ሂደቱ በኦህዴዶችና በህወሃቶች እኩል የሚጠበቅ ወሳኝ ቢሆንም በኦህዴዶች በኩል ግን  ቀጣዩ የኢህአዴግና የፌዴራሉ ወሳኝ መሪ  ከዶ/ር  አቢይ  በስተቀር  ማንም  ሊሆን  አይገባውም በሚል የጸና አቋም ድርጅታዊ የስልጣን ሽግሽግ በማድረግ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸው ታውቋል፡፡

የዶ/ር አቢይን ለጠ/ር ምኒስትርነት መብቃት (ያው ከዚህ በሃላ የሚቀራቸው      አንድ ደረጃ ሲሆን ያም የኢህአዴግ ሊ/ነቱን እንደተቆናጠጡ የሀገሪቱ ጠ/ይ ምኒስትር ከመሆን የሚያግዳቸው ስለሌለ ማለት ነው) ዜናን በመልካምነት ያዩ  ወገኖች  እንዳሉ  ሁሉ  መከላከያው፣ፓሊስ፣ደህንነቱን  እና ኢኮኖሚውን  በህወሃት እጅ ሆኖ ለዶ/ር አቢይ ጠ/ሚ መሆን እንደ ሃይለማሪያም ደሳለኝ የህወሃት አገልጋይ ከመሆን የዘለለ ምን አዲስ ነገር ይሰራል በማለት ቅዋሜያቸውን ሲያስደምጡ ተደምጠዋል፡፡

ቁጥርቻው አነስ ያለና ለየት ያለ አስተያየት ሲያንሸራሽሩ የተደመጡ ሌሎች ወገኖች ደግሞ ዶ/ር አቢይ በህወሃት ተመልምለውና በህወሃት ተነግሮአቸው ህወሃትን ለመታደግ ወደ ስልጣን እያወጡ ያሉ የህወሃት አገልጋይ እንጂ ለኦሮሞ ህዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያመጡት አንዳችም  መልካም ነገር የለም በማለት ዶ/ር አቢይ ህዝባዊውን ትግል እንደካዱ የሚናገሩም ተደምጠዋል፡፡

ኦህዴድ በወሰነው ድርጅታዊ ውሳኔው መሰረት ዶ/ር አቢይ የኢህአዴግ ሊ/ር እና የፌዴራሉ መንግስት ጠ/ይ  ሚ/ር  ቢሆኑ  ምን  ሊፈጠር  ይችላል? በእርግጥ ዶ/ሩ በህወሃት በጎፈቃድና ይሁንታ ነው ወደ ጠ/ይ ምኒስትርነቱ እያዘገሙ  ያሉት?  ዶ/ሩ  ያለ  ህወሃት  ፍቃድና  እንዲያውም  ተቃውሞ ጠ/ይ  ሚ/ር መሆን አይቻላቸውም ለሚሉ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ቀጣዩን የኢትዮጵያ

ፖለቲካዊ ሂደት ምን ሊመስል እንደሚችል ለማመላከት ቀጥሎ የቀረበውን መጣጥፌን አቅርቤያለሁ፡፡

****

**የኦህዴድ ግሥጋሴ ከየት ወዴየት?

ሰላም ጤና ይስጥልኝ ውድ እድምተኞቼ- እንደምን ሰነበታችሁ? የሀገራችን ፖለቲካዊ ክስተት በየእለቱ ፍጥነቱን እና ይዘቱን እየቀያየረ የእኛን የባለጉዳዮቹን ቀልብና አእምሮ በእንጥልጥል ወጥሮ ይዟል፡፡

ሀገራችን በየእለቱ ያለተጠበቁና ያልተገመቱ ክስተቶች የሚስተናገዱባት ከሆነች  ሰንበትበት ብላለች፡፡ ህዝባዊው ትግልና አመጽ የህወሃትን መሰረት መልሶ በማይተከል ሁኔታ ከስሩ ፈንቅሎ መጣሉን የሚመሰክሩ ገሀዳዊ ተግባራት በየእለቱ የሚስተናገዱባት ሆናለች ሀገራችን፡፡ ከምትገምቱት በላይ የለውጥ አየር ሀገሪቷን ከምስራቅ እስከምእራብ ከደቡብ እስከ ሰሜን ሲነፍስባት ይታያል፡፡

ኦህዴድ  ድንበር  ጥሶ  ለመጋዝ  ማኮብኮቡን  እያበሰረ  ወይም  እያወጀ  መሆኑን ብንፈቅድ ባንፈቅድ እያየንና እየሰማን ነው፡፡

ኦህዴድ ታላቂቷ የኦሮሚያ ምድር ጠባኛለች በማለት አይኑን ከኦሮሚያ ድንበር  ባሻገር  ባለው የኢትዮጵያ  ግዛት  ላይ  ጥሎ  ለመዝመት  አኮብኩቧል፡፡  ከእንግዲህ ለእኔ ኦሮሚያ  አትበቃኝም በማለት  በቀደምት  ስድስት የኦሮሚያ  ፕሬዚዳንቶች   ታልሞና   ታስቦ   ያልታወቀን   ህልምና   ምኞት ሰንቆ ብድግ ብሏል፡፡

ማነው የኦህዴድን ግስጋሴ እሚገታው? ማነውስ የኦህዴድን ኢትዮጵያዊ ራእይ ለመቅጨት  አቅሙና  ወኔው  የሚፈቅድለት?  በእርግጥ  አልጋ   በአልጋ አይደለም የኦህዴድ ራእይና ምኞት፡፡ ክፉኛ ባላንጣ እና ተግደርዳሪ ሃይል እንዳለው እሱም ሆነ አባልና ደጋፊዎቹ አሳምረው ቢያውቁም  ኦህዴድ በኦሮሚያ ግዛት ያሰረውን  ገመድ  በጣጥሶ  በኢትዮጵያ  ግዛት  ሊጋልብ ፈርሱን ጭኗል፡ ጋላቢውንም  የ41  ዓመቱን  ጎልማሳ  ዶ/ር  አቢይ  አህመድ መርጦ የሚያስጀምረውን ፊሽካ ተጠባባቂ ሆኗል፡፡

የህወሃትን ህልምና ምኞት ክፍኛ በመዘረር ኦህዴድ በህወሃት እግር ሰተት  ብሎለመግባት መሰናዶውን ጨርሷል፡፡ ብዙዎች ህልሙንና አካሄዱን ወደውለታል፡፡  ጥቂቶች  እጅግ ተንገሽግሸው  ጠልተውለታል፡፡  ሌሎች በግራ መጋባት ስሜት ይህ ጉዳይ ወዴት  እያመራ  ነው ሲሉ  በጥያቄ አስተውሎት ይከታተላሉ፡፡ የቲም ለማ ቡድን ወደ  ኦህዴድ  ከመጣ  ግዜ  ጀምሮ  ኦሮሚያ  ብቻ  ሳትሆን  የኦሮሚያ  ወላጅ   እናት   የሆነችው ኢትዮጵያም እጅግ ብዙ በርካታ  አዳዲስ ነገሮች  ሲፈጸሙ  በአግራሞት እያየች ነው፡፡

ተሰናባቹን ወይም የተባረሩትን የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆኑትን አቶ ሃይለማርያም ደስላኝን የሚተካው የእኔው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆነው ብልሁና አንደበተ ርትኡ የሆነው ዶ/ር አቢይ አህመድ ነው  በማለት  ኦህዴድ  የወሰነ  መስሏል፡፡  ግን  ይፋ  አላደረጉም፡

፡           ድርጅቱ በይፋ ባይገልጸውም የድርጅቱ ቅርብ ምንጮች  እንደሚናገሩት  ከሆነ የአቶ ለማ መገርሳ የድርጅቱን ሊቀመንበርነት ለቆ ለዶ/ር አቢይ በመስጠት የምክትልነቱን ስፍራ እንዲይዙ ያስገደዳቸው የኦህዴድ ከኦሮሚያ ባሻገር ባለችው  ኢትዮጵያ  ላይ  ያለው  ምኞትና  ዓላማ  እንጂ  ሌላ  ምን   አስገድዷቸው ነው ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

ህወሃት ድምጻን አጥፍታ ቅርቃር ገብታለች፡፡ ብአዴን እና ደቡብ ህዝቦች ማለቂያ በሌለው ውስጣዊ ስብሰባ ተጠምደዋል፡፡ ስብሰባውን እንዳጠናቀቁ አራቱ ኢህአዴጋዊያን  ህወሃት፤ብአዴን፣  ኦህዴድና  ደህዴህ  የጥምር ድርጅታቸውን ሊቀመንበር ለመምረጥ እያንዳንዳቸው 45 አባላትን

 

በመወከል 180 ያህሉ ይሰየማሉ፡፡ እነዚህ ሰዎችም ናቸው የድርጅታቸውና የሀገሪቱ መሪ የሚሆነውን የሚመርጡት፡፡

አራቱም ድርጅቶች ያሻቸውን እጩ የማቅረብ መብት አላቸው፡፡ ብአዴኖቹ      የአጋራቸውን ኦህዴድ እጩ ለማሳለፍ የራሳቸውን እጩ እንደማያቀርቡ ይጠበቃል፤ ወይም ለይስሙላ ያቀርቡና ድምጻቸውን ግን ለዶ/ር አቢይ ይሰጠሉ፡፡ ደህዴህ ጥላ ቢሱን አቶ ሲራጅ ፉርጌሳን ለሊቀመንበርነት ማጨቱን አስታውቋል፡፡ ዘግይቶም ምርጫው የእኔ አይደለም ሲልም አስተባብሏል፡፡ የህወሃትን እጩ እየተጠባበቀ ባለበት ሰዓት የህወሃቱ እጩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በእነ ለማ የቆረጣ ስልት (ይህንን ቆረጣ ከሀወሃት እንደተማሩና በህወሃት ላይ እንደተገበሩት ይታወቃል) በመጠቀም ከጫወታው ውጪ ተደርገዋል፡፡

ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በሃይለ ማሪያም ወንበር መቀመጣቸውን ሳያረጋግጡ እኔ የሚቀጠለው ጠ/ሚ ነኝ እያሉ እራሳቸውን  ለዲፕሎማቶችና  ለውጭ  ሀገር መሪዎች ማስተዋወቃቸው አሳፍሮዋቸዋል፡፡ የተማመንኩት  ህወሃት  እራሱ ጉድ ሆኖ እኔንም እንዲህ ጉድ ይስራኝ በማለት  ተስፋ  ያደረጉት ድርጅት ተስፋ እንዳልሆናቸው አማረዋል፡፡

የህወሃት ድንግጤ ከፍተኛ ሆኗል፡፡ መጠባበቂያችንን ሰራዊት ባናዘጋጅ ኖሮ ጅብ በልቶን ነበር በማለት ከሰራዊቱ ጋር ተጣብቀዋል፡፡ ነጋ ጠባም ከሰራዊቱ ጋር ሆነው መዶለት ቢያበዙም አሁን ግን  ይባስ  ብለው ኑሮዋቸውንም በወታደሩ ካምፕ እንዳደረጉ መረጃዎች ይናገራሉ፡፡

ምርጥ እጩ ብለው ያዘጋጁት ወርቅነህ በእነ አቶ ለማ አፈር ድሜ በልቶ አይደለም የኦህዴድ ሊቀመንበር ሊሆን  ይቅርና  ከምክትልነቱም  ተሸቀንጥሮ ተቧራል፡፡ ህወሃት ይህን ሲቪል አስተዳደራዊ ተቋማትን እርምጃ ጥይት አልባው መፈንቅለ መንግስት ብሎቷል፡፡  ጥርሱንም  ነክሶ በፍጹም አያገኟታም ሲል ከራሱ ጋር ሲዝትና ሲፎክር ተሰምታል፡፡  ግን  የዶ/ር አቢይን ግስጋሴ፤ የኦህዴድን ውሳኔ ማስቆም የሚችልበት አቅምና መንገድ ይኖረው ይሆን?

**በአስቸካይ ግዜ አዋጅ ስር በወታደራዊ አገዛዝ እየተገዛች ባለችዋ ኢትዮጵያ የዶ/ር አቢይ ወደ ስልጣን መምጣት ምን የሚፈይደው ነገር አለ?

ህወሃት በኢትዮጵያ ላይ የገነባችው ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ የበላይነትን በሁለት ችካል ላይ የተመሰረተ  ሲሆን  አንደኛው  ችኳል  የሲቪል አስተዳደራዊ ተቋም ሲሆን እሱም እንክትክቱ ከወጣበት ስነባብቷል፡፡

ሁለተኛው  የህወሃት  ችካልም  የወታደራዊው  መወቅር  ሲሆን  ዛሬ  ይህ   የህልውና ችካል ብቻ ድርጅታዊ ህልውናውን ያንጠለጠለበት ሃይል ሆኗል፡፡

በህወሃታዊያን መንደር ይህን ሰላማዊ መሳይ ሲቪል አስተዳደራዊ መዋቅር ተጠቅመው የሚካሄደውን  መፈንቅለ  መንግስት  ሙሉ  በሙሉ  መቀበል  እንደሌለባቸው ከወሰኑ ሰነባብተዋል፡፡ ይህንን እርምጃቸውንም የሚደግፉበትን መከላከያውን ስልጣን ማስያዛቸውም ይታወቃል፡፡ እድሜ ለአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ይሁንና፡፡

በተቻላቸው መጠን ግን እርምጃውን የማክሸፉን ሁኔታ ህጋዊነትን የተላበሰ እንዲሆን ይጥራሉ፡፡

ሆኖም ሁለቱ ሰዎች የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ለህዝባችን ቃል የገባነውን በኦሮሚያ ደረጃ ብቻ ብንተገብረው ለውጡ አይታይም በሚል  እምነት  እና  አቋም አንተ ወደ ፌዴራል ሄደህ ስትፈጽም እኔ እዚህ ሆኜ አስፈጽማለሁ ተባብለውና ስራ ተከፋፍለው እንደተነሱ ታውቋል፡፡

መንቲዮቹ የሚል ቅጽል የተሰጣቸው አቶ ለማ መገርሳና ዶ/ር አቢይ አህመድ የሰነቅነውን ሀገራዊ ስንቅ ኦሮሚያ ላይ ሆነን ለመላው ኢትዮያ ማዳረስ አይቻለንምና በትረ ስልጣኑን መያዝ አለብን ተባብለው እንደሰኑ ይነገራል፡፡

የኦህዴድ መራሹ ጠቅላይ ምኒስትርነት ገና ለስልጣኑም ሳይበቃ የተቃወማቸውና አካሄዳቸውን በጥርጣሬ የሚያይ ወገንንም አይተናል፡፡ ስጋታቸም የዶ/ሩ ጠቅላይ ምኒስትርነት የህወሃትን ስልጣን በመታደግና ህዝባዊውን ትግል በማዳከም ይጎዳል የሚል ነው፡፡

ሆኖም ኦህዲዶች ሰውዬአቸውን ዶ/ር አቢይን ለጠቅላይ ምኒስትርነት ያቀረቡት  ሀገር  ለመታደግ እንጂ  ህወሃትን  ለመታደግ  ሲሉ  አልተደመጡም፡፡

ደጋግመው እየገለጹ  ያሉት  የተጀመረውን  ለውጥ  ምሉእ  በማድረግ  ሀገርን  ለመታደግ ሃላፊነትና ግዴታችንን ለመወጣት ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

ዶ/ር አቢይ የአቶ ሃይለማሪያም ተምሳሌት የህወሃት አገልጋይ ይሆናሉ ማሰቡ    ይከብዳል፡፡

ሁለቱን በወፍ በረር ንጽጽር ብናወዳድራቸው አቶ ሃይለማርያም በታዥነትና በአገልጋይነት መስፈርት ከበስተጀርባቸው ሊኮርፉም ሆነ  ስልጣኔን ልጠቀም  ቢሉ  የሚደግፋቸው  ሃይልና  ወገን የሌላቸው  በጠቅላይ ምኒስትርነቱ ላይ ለመቆየት ብቸኛው ስራቸው ታማኝነት ሲሆን  ዶ/ር  አቢይ ግን የህወሃትን ምርቃትና ድጋፍ ሳይሹ ግላዊ እውቀትና ችሎታ ያላቸው እንዲሁም ከበስተጀርባቸውም ታላቅ ሃይል ያሰለፉ በመሆናቸው ለህወሃት ታማኝ ሆነው ለመስራት ካልፈለጉ በስተቀር የሚያስገድዳቸው ሁኔታ የሌለባቸው መሆኑም ከግንዛቤ መያዝ ይኖርበታል፡፡

**የዶ/ር አቢይ ጠቅላይ ምኒስትርነት እውን ይሆናል? ምንስ ይጠበቃል?

የመከላከያው፣ደህንነቱ፤ፖሊስና ኢኮኖሚው በህወሃት እጅ እንዳለ መሆን እንደ ዋነኛ ችግር አልቆጥረውም፡፡ እነዚህ ተቋማት በህወሃት የበላይነት ስር የወደቁት የህወሃት አመራር ጠ/ሚ በነበረበት ሁኔታ እንደሆነ ሁሉ ዛሬም ስልጣን የሚይዘው ዶ/ር አቢይ ይህንን የበላይነትን በማፈራረስ ፍትሃዊ የስልጣንና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲፈጠር ማድረግ ይቻላቸዋል፡፡

ከሁሉ በላይ የኦህዴዱ ምኞት ተሳክቶላቸው ዶ/ር አቢይ ወደ ጠ/ሚ ስልጣን ቢመጣ  ከሁሉ  ቀድሞ የህወሃትን  የበላይነት  በከፊል  ማፈራረስ  መቻሉን  የሚያበስርበት ሁኔታ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡

የዶ/ር  አቢይ  ለጠ/ሚነት  መብቃት  ህዝባዊውን  ዓመጽ  አዳክሞ  ከመጉዳት  ይልቅ

ህዝባዊውን           ትግል   የሚደግፍበትን   በርካታ   ግብዓቶችን   መስራትም እንደሚችሉ ሊጤን ይገባል፡፡ ቀዳሚውም የህወሃትን  የበላይነት  ማፍረስ መቻሉ  ለትግሉ  ጎራ  አጋዥ  እንደሚሆን  እንጂ  ጎጂ እንደማይፈጥርበት ሊጤን ይገባል፡፡

የዶ/ር አቢይ የጠ/ይ ምኒስትርነት ስልጣን በእጅጉ በእሳት ወንበር ላይ የመቀመጥ  ያህል እንደሚቆጠር  ይታመናል፡፡ ስልጣኑ  በአሁኑ  ሰዓት  ሁለንተናዊ  ለውጥን ከሚፈልገው የኢትዮጵያና የኦሮሞ ህዝብ በአንድ በኩል ስልጣን በመነጠቁ ምክንያት ጥቅሞቼን ማስጠበቅ አለብኝ የሚለውና መከላከያውን በሚያዘው ህወሃት በሌላ በኩል በሚከፈትበት ተጽእኖ የሚለበለብ እንደሚሆን  ይገመታል፡፡

የዶ/አቢይ ህገ መንግስታዊ የስልጣን ገደቡን መሰረት አድርጎ ለመንቀሳቀስ    መሞከር በህወሃት በኩል ወታደራዊ ሃይሉን  ተጠቅሞ  ተጽእኖ  የመፍጠር እርምጃዎችን እንደሚያደርግ የሚያስገምት ሲሆን ሁኔታው በዶ/ር አቢይ በኩል ወይም በህወሃት በኩል በሚወሰድ እርምጃ የመንግስቱን ማፍረስ ተግባርም የምናይበት እድል ሰፊ እንደሆነ ከወዲሁ መግለጽ ይቻላል፡፡

በህገ መንግስቱ አንቀጽ 74 ላይ ከተራ ቁጥር 1 እስከ 11 ድረስ የተዘረዘረውን የጠቅላይ ምኒስትሩን ስልጣን ዶ/ር አቢይ አህመድ ተገበረ ማለት ያለምንም ማብራሪያ ውጤቱም የህወሃት ኢኮኖሚያዊ፤ፓለቲካዊና ማህበራዊ የበላይነት  ሙሉ በሙሉ ተንኮታኮቱ ህወሃት ፈረሰች እንደማለት ነው፡፡ በእርግጥ ይህ እውነታ  ለህወሃት  የተዘጋጀችና  ህወሃት  ሳትወድ  በግድ የምትጨልጣት  እውነታ  ቢሆንም  አሁን  ባለችበት  ደረጃ  መካላከያውን  በእጇ  ይዛ  ሳለ  በጸጋና በዝምታ የምትቀበለው ሳይሆን በሃይል ለማገድ እርምጃ እንደምትወስድ ይጠበቃል፡፡

ምክንያቱም ዶ/ር አቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆነው ታማኝ የህወሃት አገልጋይ  ለመሆን  ሳይሆን ድርጅቱ  ለህዝብ  ቃል  የገባቸውን  የለውጥ  ውጥኖችን  በሀገር አቀፍ ደረጃ እውን ለማድረግና ሀገር ለመታደግ እንደሆነ ተነግሮናል፡፡

የለውጥ ተግባሮችና ሀገር የመታደግ ተግባራት ትርጉማቸው የጸረ ህወሃት ጥቅምና  የበላይነት እርምጃ  መሆናቸውን  መቼም  ልገልጽላችሁ  አይገባኝም፡፡  ምክንያቱም ህወሃት የገነባችው የቢዝነስ ኢምፓየር፤የመሰረተችውና የዘረጋችው የስልጣን ሰንሰለትና ደረጃ ሁሉ ህገ መንገስቱን መሰረት ያደረገ ህጋዊ ሳይሆን ሀግን የተላለፈ ህገ ወጥ በመሆኑ ማንኛውም የማስተካከያ እርምጃዎች የህወሃትን ህልውና እና ጥቅም የሚያፈራርሱ ጸረ ህወሃት እርምጃዎች እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡

ከዚህ ሁሉ ውዝግብና ግብግብ ይልቅ ህወሃት የዶ/ር አቢይን ወደ ጠ/ሚንስትርነት  ጉዞ የከፈለችውን  ከፍላ  ለማስቀረት  እንደምትጥርም  ይታመናል፡፡

ቢሳካላትም ባይሳካላትም፤ ሲሻት ምርጫውን በማራዘምና በወታደራዊ አገዛዝ በመግዛት የዶ/ሩን ወደ ስልጣን መምጣት  ልታግድ  እንደምትችል በተጨባጭ መገመት ይቻላል፡፡

ከተቻላትም ከህወሃት ወይም ከደህዴህ ያሻትን ምርጥ አሻንጉሊት በመምረጥ ልትሟሟትበት የምትችል ሲሆን ከሁሉ በላይ የብአዴን የበረከት ስምኦን ወገኖች አሸናፊ ሆነው ከወጡ የዶ/ር አቢይን እጩነት በቀላሉ ውድቅ በማድረግ ማሸነፍ እንደሚቻላት መታወቅ አለበት፡፡

እርምጃውን  የህወሃት  መንደር  ሲቪል  አስተዳደራዊ  የስልጣን  ነጠቃ  ብሎ  ፈርጆታል፡፡ ክክስተቱ በፊትም ህወሃት ቀደም ብላ የራሳን ስሌት በማስላት ወታደሩን በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ስም ስልጣን በማስረከብ ፈላጭና ቆራጩን ወታደሩ አደርገዋለች፡፡

የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለስሙ ለስድስት ወር ተባለ እንጂ ዝግጅቱና ውሳኔው    እስከመጨረሻ እንደሆነ መረጃው ቀደም ብሎ ደርሶናል (የመጨረሻው  ካርድ  ወታደራዊ አገዛዝ ?በሚል አርእስት ስር አስፍሬዋለሁ) ሆኖም ይህ ወታደራዊ አዋጅ ጭንብሉን ተገፍፎ ይፋ የሚሆንበት ክስተት አንድ እርምጃ ይጠብቀዋል፡፡

በተወካዮች ምክር ቤት ኦህዴድና ብአዴን አዋጁ እንዳይጸድቅ ውድቅ ሊያደርጉት  ተዘጋጅተዋል፡

ሀሳባቸው እውን ከሆነ ህወሃት በይፋ ፓርላማውን ያፈርስና ወታደራዊ አገዛዙን ላልተወሰነ ግዜ ያውጃል፡፡

በምንም አይነት ተአምር ዓይኑ እያየ ወታደሩን ወደ ምሽጉ መልሶ የዶ/ር  አቢይን  ጠ/ይ ምኒስትርነት  በጸጋ  አጨብጭቦ  የሚቀበል  አይሆንም፡፡

ዶ/ር አቢይ በኦህዴዶች ተመረጡ እንጂ በኢህአዴግ ገና እንዳልተመረጡ ይታወቃል፡፡  ህወሃት የእሳቸውን  ወደ  ስልጣን  መጋዝ  ለማደናቀፍ  ያገኘችውን  አጋጣሚ ሁሉ እንደምትወስድ ሲታሰብ ውድድሩ እንዳላለቀ ያሳያናል፡፡ ሆኖም ዶ/ር አቢይን በባሌም ሆነ በቦሌ ማገድ እንኳን ቢቻላትም ህወሃት ይበልጥ ተሸናፊና ተጎጂ ሆና የምትወጣበትን እስትራቴጂ ኦህዴዶች በእርግጥ ይዘውባታል፡፡

ሲያልቅ አያምር ይሉ ነበር ኩሩው አያቴ፡፡ የህወሃት ዘመን ከፍጻሜ ዋዜማ  ላይ  ያለ  መሆኑን አመላካች  ነጥቦች  በርካታዎቹን  መጥቀስ  ብችልም  ለናሙና ያህል ጥቂቱን ብጠቅስ-

1ኛ- በመጨረሻህ ዘመን አንተም በወዳጅህ ላይ ትነሳለህ ወዳጅህም በአንተ ላይ ይነሳል፡፡ የአሜሪካና የአውሮፓ ህብረት በታወጀው  የአስቸኳይ  ግዜ አዋጁ ላይ ተንተርሰው የያዙት አቋም የስርዓቱን እግር ብርክ ያደረጉ ጠንካራ ሲሆን ህወሃትም በአጸፋ በተለይም  ቀለብ  በሚሰፍሩላት አሜሪካኖች ላይ ያሳየችው አቋም የዲፕሎማሲ ፈሩን የለቀቀና ልክ ለቅንጅትና ለአግ7 የምትመልስ ነው ያስመሰላት፡፡

የኤች  አር  128   ጉዳይ  ሌላው  ከአሜሪካ  መንግስት  የተዘጋጀ  ህወሃትን  እረፍት ነሺእርምጃ ስርዓቱ በወዳጆቹ እንኳን ሳይቀር  የትእግስት  በር  የተዘጋበት መሆኑን ያሳያል፡፡

2ኛ-በእያንዳንዱ ስርዓት መሃጸን ውስጥ ስር ዓቱን ጥሎ የሚተካ የለውጥ ጽንስ ተጸንሶ ነው ያለው ሌኒናዊው ቲዮሪም የሚያሳየን ዛሬ ህወሃትን ስልጣን ለመንጠቅ እየተግደረደረ ያለው ኦህዴድ የተፈጠረው በህወሃት  ከርሰ ማህጻን ውስጥ ሲሆን ይህ የለውጥ ጽንስ ደግሞ ተወልዶ ለማደግ ማድረግ ያለበትን ተፈጥሮአዊ እርምጃ ሲወስድ እያየን ነው፡፡

3ኛ-ፈርኦን ይጠፋ ዘንድ ከስህተቱ እንዳይማር ልቦናው የተደፈነ ሆነ፡፡ ህወሃት  ከስህተቱ  መማር ካቃተው  ስንት  ዘመናት  አለፉ?  በስህተት  ላይ  ስህተትን እየደራረበ የብዙዎችን ህይወት እየቀጠፈ ግን ሳይጸጸት ይበልጥ እየተኩራራ በግፍ ስራው ተመጻድቆና ተኩራርቶ መቀጠሉ የስልጣን ዘመኑ ማብቂያ ላይ መሆኑን ከሚያውጁ  አዋጆች  ውስጥ  የተጠቀሱት  ጥቂቶቹ  ናቸው፡፡

የህወሃት አርማጌዶን ከተጀመረ ዓመት አልፎታል፡እስቲ አርማጌዶውን እንዴት  እንደሚመክት እናያለን፡፡

ቸር እንሰንብት፡

———————

አስተያየታችሁን እና ጥያቄያችሁን teklu7@gmail.com ብላችሁ ብትጽፉልኝ በአክብሮት እመልሳለሁ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.