ጉልቻ መቀየር ወጥ አያጣፍጥም! (በላይነህ አባተ)

በላይነህ አባተ  (abatebelai@yahoo.com)

ትናንት ዓለም በጉልበተኛ መገዛቷ ጥቅስ እማያስፈለግው ጠቅላላ እውቀት ነው፡፡ ዛሬም ዓለም በጉልበተኞች እንደምትገዛ እያየን ነው፡፡ ነገም በጉልበተኞች እንደምትገዛ ለመተንበይ ነቢዩ ኢስያስን መሆን የማያስፈልገው ትንቢት ነው፡፡

ትናንት ጉልቤ ምዕራባውያን በቀጥታ ወረራ ደካማ አገሮችን ገዝተዋል፡፡ ዛሬም ጉልቤ ምዕራባውያን ደካማ ሕዝቦችን በተዘዋዋሪ በካሮትም በብትርም መግዛቱን ቀጥለዋል፡፡ እስከ ሰላሳ ዓመታት በፊት ድረስ ቀጥተኛውንም ሆነ ተዘዋዋሪውን ተገዥነት መክተው ከኖሩት ጥቂት አገሮች ጦቢያ አንዷ እንደነበረች ይታወቃል፡፡ ከሰላሳ ዓመታት ወዲህ ግን ጦቢያ በምዕራባውያንና በአረቦች የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ባህሯን አጥታለች፡፡ በሱዳን የእጅ አዙር ቅኝ ገዥነትም መሬቷን ተነጥቃለች፡፡ ኩሩዋ እቴጌ ጦቢያ ቀን ጥሏት ልጆቻን በዶላር እየቸበቸበች ምዕራባውያን ልጆቻቸውን መላክ ካልፈለጉበት የሶማሊያና ሱዳን እሳት እየጨመረች እንደ ጥንቷ ሕንድ የቅኝ ገዥዎቿን ፍላጎት መጠበቁን ቀጥላለች፡፡

ምዕራባውያን ጦቢያን በእጅ አዙር የገዟት ለሽንፈታቸው ማርከሻ የቀመሙትን መርዝ የሚቀቅሉበት ብረት ድስት ደደቢት በርሃ ስለሰሩ ነው፡፡ ይኸንን የደደቢት ድስት የመርዛቸው መቀቀያ ለማድረግ አቶ ገብረመድህን አርአያ በፎቶግራፍ እንዳሳዩን ስንዴ ነሰነሱ፣ ዶላራቸውን መዘዙ፡፡ እነዚህ ምዕራባውያን የደደቢቱ ድስት በጦቢያ ልጆች መዶሻ እንዳይሰብር የጦቢያን መከላከያ ህዋስ በስለላቸው አዳከሙ፡፡ የመከላከያው ህዋስ ተዳክሞ ሲበተን በለንደኑ ኮንፈረንስ የመበታተን አላማ ያላቸውን ብረት ድስቶች ብቻ አሳትፈው የደደቢቱን ድስት አዲስ አበባ ጥደው መርዛቸውን መቀቀሉን ቀጠሉ፡፡

ለዚህ መርዝ ቅቀላ ጉልቻ የመምረጡን እድል በፈለጉት መልክ ለጠፈጠፉት የደደቢቱ ብረት ድስት አስረከቡ፡፡ ይህ ድስትም ታምራት እሚባል ስኳር ላሽ ጉልቻ ቀጠረ፡፡ ስኳር ላሹ ጉልቻ በተቀቀለው መርዝ ሕዝብ ሲያስፈጅ ባጅቶ በላሰው ስኳር ስለወፈረና ድስትን በመጎራበጥ ስለተጠረጠረ በፈጠመው ትልቅ ወንጀል ሳይሆን በትንሹ ወንጀል ተገለለ፡፡ ስኳር ላሹ ጉልቻ ሲገለል ነጋሶ እሚባለው የሕገ-መንግስት ጉልቻ መጎለቱን ቀጠለ፡፡ የሕገ-መንግስቱ ጉልቻ ነጋሶ ወገቡን እንደ ወጥ ሰሪ አደግድጎ “እስከ መገንጠል!” እሚለውን መርዝ እንደ ጓያ ወጥ አንተከተከ፡፡ ያንተከተከውን ሕግ መንግስትም ድፍን ዜጋ ቅመም ያዋጣለት አስመስሎ ሕዝብን ሙልጭ አርጎ ዋሸ፡፡ ቆይቶ ግን የሕገ-መንግስቱ ጉልቻ ከስኳር ላሹ ጉልቻ የተሻለ መሆኑ ታዬ፡፡ ስኳር ላሹ ጉልቻ የናዝሬቱ ወንጂ ስኳር ሲነፈገው የኮሎራዶን የሃይማኖት ስፕሊንዳ ስኳር መላሱን ቀጠለ፡፡ የሕገ-መንግስቱ ጉልቻ ግን ተፀፀተና ውሸታም የሕገ-መንግስት ጉልቻ እንደነበር አምኖ ይቅርታ ጠየቀ፡፡

በውሸት ሕገ-መንግስት ጉልቻነት መጎለት የሰለቸው የሕገ-መንግስቱ ጉልቻ ነጋሶ “ከደደቢት ብረት ድስት ስር ተጎልቼ ስቃጠል ከምኖር ችጋር ይቀፍድደኝ” ብሎ መጎለቱን ሲተው ግርማ የተባለ ኬሻ የኬክ ጉልቻ ብቅ አለ፡፡ በቴክኒክ ችግር መቆም የማይችለው ይህ የኬክ ጉልቻ እንደ ዱባ ተዘርፍጦ መርዝ ሲንተከተክበት ኖረና ከኬክ ክምር ሥር ጡረታ ወጣ፡፡ የኬኩ ጉልቻ ጡረታ ሲወጣ ሙላቱ እሚባል ድንጋይ ጉልቻ መጣ፡፡ ድንጋዩ ጉልቻ እንደ በቀለ ገርባ ያሉ የሰፈሩን ልጆች እያስቀፈደደና ሕክምና እያስከለከለ ወጥ በማመላለስና “የተከበራችሁ የጎዳና ተዳዳሪዎችን” በማለቱ ከሚታወቀው ጉልቻው ሐይሌ ጋር መርዝ ማንተክተኩን ቀጠለ፡፡ ሁለቱ ጉልቻዎች የድስትን መርዝ ሲያንተከትኩ ደም በመላ አገሪቱ እንደ ጅረት ፈሰሰ፡፡ ወጣት፣ ጎልማሳው፣ ባልቴቱና አዛውንቱ በወህኒ እንዲደማ ተደረገ፡፡ በዚህ የደም ጎርፍ የመርዙ ድስት ሳይሆን ወጥ አመላላሹ ጉልቻ ተጠረገ፡፡

ለጥቅሙ ከጉልቻ የሰቀለው ድስት እንዲፈነገል የማይፈልገው መርዝ ቀማሚው ባዕድ እንደልማዱ ወጥ አመላላሹን ጉልቻ “ሕዝብ በመጠኑም ቢሆን በሚቀበለው ጉልቻ” እንዲተካ የደደቢቱን ድስት መከረ፡፡ የደደቢቱ ድስትም ከተጠባባቂ ጉልቻዎቹ አንዱን ሊተካ ቅስቀሳውን ቀጠለ፡፡ በቅስቀሳውም አሰፍሳፊ እጩ ጉልቻዎችን አገኘ፡፡ የደደቢቱ ብረት ድስት ቅስቀሳ የእጩ ጉልቻዎችን ብቻ ሳይሆን የብዙ ሞኝ ሕዝብ ልቦችንም አማለለ፡፡ በሚያሳፍር ሁኔታ ብዙ ሞኝ ሕዝብ ድስት ለዕጩነት ባቀረባቸው ጉልቻዎች ምርጫ መሳተፍ ጀመረ፡፡ ለጉልቻነት የቀረቡትን እጩዎች ድስት አላቁጦና እስተንፋስ እፍ ብሎ የፈጠራቸው መሆኑን እንዴት ሕዝብ ረሳ? እነዚህ ዕጩ ጉልቻዎች ሲፈጽሙት የኖሩትን ዘግናኝ ግፍና ወንጀልስ በየትኛው ንስሀቸው ሰረዘ? እነዚህ እጩ ጉልቻዎች ሲመግባቸው የኖረውን ድስት በምን ተዓምር ገልብጠው ይደፋሉ ብሎ አሰበ? መቼ መንፈስ ቅዱስ አድሮባቸው ወይም የዘር ለውጥ (gene mutation) አድርገው ሕዝብን መርዝ ሳይሆን ወጥ ይመግባሉ ብሎ ደመደመ? መንፈስ-ቅዱስ እንደ ይሁዳ ባሉ ጉልቻዎች መቼ አድሮ አወቀ? የዘር ለውጥስ በዘመናት በሚቆጠር ጊዜ እንጅ በወራት ወስጥ መቼ ተከሰተ?

ችግሮችን ለማስወገድ የችግሮችን መንስኤ መቅረፍ ያስፈልጋል! ከብዙ ችግሮቻችን ዋና ዋናዎቹ የባዕድ መርዝ፣ ባዕድ የሰራው የመርዝ መቀቀያ ብረት ድስትና ብረት ድስቱን የሚሸከሙት ጉልቻዎች ናቸው፡፡ ባዕድ መርዙን የሚቀቅልበት ብረት ድስትና ጉልቻ በጦቢያ ምድር ካልጠፈጠፈ ጥቅሙን ለማሳደድ የሚረጨው መርዝ ባገራችን መሰራጨት አይችልም፡፡ መርዙን የሚቀምሙትን ባዕዳን እንደ ቅድመ-አያቶቻችን ሲመጡብን የመመከት እንጅ የመርዝ ቅመማቸውን የማስቆም እድላችን ውስን ነው። ብረት ድስትና ጉልቻ ግን ከመዳፍ ሥር ስለሆኑ ትኩረት ማረፍ ያለበት ከድስትና ጉልቻዎች ነው፡፡ ጉልቻዎች ተቀያይረው የመርዝን ድስት አሽቀንጥረው የወጥ ድስት ሊሸከሙ እንዳልቻሉ አይተናል፡፡ ስለዚህ ትኩረት ድስት ከሚጎልታቸው ጉልቻዎች ሳይሆን ፈረንጅ ከጠፈጠፈው ብረት ድስት ማረፍ ይኖርበታል፡፡ የፈረንጅ ብረት ድስት በጦቢያ የሸክላ ድስት፤ የባዕድ መርዝም በራሳችን ቅመማቅመም መተካት ይኖርበታል፡፡ የጦቢያ ሸክላ ድስት ወጥን ያሳምራል፡። ስለዚህ  እንደ ቅደመ-አያቶቻችን ጣት እሚያስቆረጥም ወጥ ማድ እያቀረብን በክብር ለመኖር ፈረንጅ የሰራውን ቃጭላም ብረት ድስት በጦቢያ ሸክላ ድስት መቀየር ይኖርብናል፡፡ ባለሙያዎችን ጠይቁ! ድስትን እንጅ ጉልቻን መቀየር መቼ ወጥ አጣፍጦ ያውቃል?

 

የካቲት ሁለት ሺ አሥር ዓ.ም.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.