ብአዴን ከአማራው ክልል ውጭ ላሉ አማርኛ ተናጋሪዎች እቆማለህ አለ  (ግርማ ካሳ)

ብአዴን ከረጅም ጊዜ ስብሰባው በኋላ ረጅም መግለጫ አውጥቷል። መግለጫው ከብዙ ወገኖች ዉግዘትን አስከትሎበታል። እኔ የተለየ አመለካከት ነው ያለኝ። በብአዴን መግለጫ ቅር የተሰኙ ወገኖች ለምን ቅር እንደተሰኙ በሚገባ ይገባኛል። እኔም መግለጫው ላይ መካከት የነበረባቸው ሁለት አበይት ጉዳዮች ባለመጠቀሳቸው አዝኛለሁ።

በአማራ ክልል የክልሉ መንግስት ሳይፈቅድና ሳያዝ አጋዚ የብዙ ወገኖችን ሕይወት ቀጥፏል። የብአዴን መግለጫ በክልሉ በደረሰው የንብረት ውድመት ምክንያት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም እንደሚሰራ፣ የንብረት ዉድመት አደረሱ በተባሉት ላይም የእርምታ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጾ፣ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ስላደረሱ አረመኔዎች ግን ምንም ያለው ነገር የለም። አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥይት ተኩሰው የገደሉ፣ ምርመር ተደረጎ ለፍርድ እንደሚቀርቡ ነበር የተናገሩት። ሆኖም ብአዴን እንደ ድርጅት በግፍ የተገደሉ ዜጎች ፍትህ በማግኘታቸው ዙሪያ ዝምታን መምረጡ በግሌ አሳዝኖኛል።

 

ሌላው ወንድም አቻሜለህ ታምሩ በጥሩ ሁኔታ ገልጾታል። “እንደሚታወቀው የአማራ ተጋድሎ የተጀመረው ከወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ነው። የሕወሓቱ ነውረኛ ድርጅት ብአዴን ግን ያ ሁሉ የአማራ ደም የፈሰሰበትን፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ልጆች በግፍ የታሰሩበትን፣ እልፎ የአካልና የአዕምሮ ጉዳተኛ የሆኑበትን የአማራ ሕዝብ አጀንዳ የሆነውን የወልቃይት ጉዳይ አንዳች ነገር እንኳ ሳይተነፍስ የአስራ ሁለት ገጽ መግለጫ አወጣ።” ያላል አቻሜለህ። ብአዴን በስበባው በወልቃይት ጉዳይ ላይ እንደተጋገረ ውስጥ አዋቂዎች ዘግበዋል። ሆኖም የወልቃይት ጉዳይ የህዝብ ትልቁ ጉዳይ ሆኖ ብአዴን አሁን የጠራ አቋም መያዝ አለመቻሉ ሌላው በጣም ያዘንኩበት ጉዳይ ነው።

የብአዴን መግለጫ አማራ የሚባለውና አማርኛ ተናጋሪው ሕብረ ብሄረሰባዊ ማህበረስብን እንደ ሁለተኛ ዜጋ ያደረገ፣ ወልቃይት ጠገዴና ከጎንደር፣ ቤኔሻጉልን ከጎጃም፣ አላማጣ፣ ኮረምና ራያ አዘቦ የመሳሰሉትን ከወሎ የቆረሰ፣ አማርኛ ተናጋሪዎች በብዛት የሚኖሩበት ሸዋ ፣ ጂማ በመሳሰሉ አካባቢዎች የኦሮሞ ብቻ በሆነ ክልል የጠቀለለ፣ ሕወሃት እና ኦነግ በሕዝቡ ላይ በሃይል የጫኑትን የጎሳ የፌዴራል ስርአት እየደጋገመ “የፌዴራል ስርዓታችን” እያለ መጥቀሱ አልተመቸኝም።

ሆኖም ግን ሁኔታዎችን ከተለየ ማእዘን መመልከት ያለብን መሰለኝ። በዚህ ስብሰባ ሲጀመር ሕወሃትና የህወሃት አሸከሮች አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን በማንሳት ብአዴንን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረትና ፍልሚያ ያደረጉበት ስብሰባ ነው። በዚህ ስብሰባ አቶ ገዱ ተወግዶ ቢሆን ኖሮ ሕወሃት አፈር ልሳ ተነሳች ማለት ነበር። በነገታውም ኦህዴድን ሳይቀር የመጨለቅ አቅም ታገኝ ነበር።በአንድ በኩል በነበረከት ስምኦን አለመነህ መኮንን እና በሌላ በኩል በነገዱ መካከል የነበረው ስድብ ቀረሽ ክርክር እንደነበረ ሁላችንም ሰምተናል። በዚያ ሁሉ ውስጥ የነገዱ ቡድን አሸናፊ ሆኖ መውጣቱ በራሱ ትልቅ ድል ነው። የሚቀጥለው ሳምንትም የሚደረገው ከኢሕአዴግ ስብሰባ የተሻለ ጥሩ ነገር ይገኝ ዘንድ ሁኔታዎችን ያመቻቸ ነው። በዚያ ስብሰባ ኦህዴድና ብአዴን ከበፊቱ ስብሰባ ጠንካራ ሆነው ነው ሚቀመጡት።

 

በመግለጫው ብአዴን በግልጽ ያስቀመጣቸው ችግሮች አሉ፡

– የህዝቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ መሆን በሚገባው ደረጃ አላደገም

– ልዩ ልዩ የተሳሳቱ ዝንባሌዎችን ስርነቀል በሆነ መንገድ ለማስተካከል አልተቻለም

– ብአዴን በሃሳብ ብልጫ መምራት አልቻለም

– በሃሳቦች ነጻ ዝውውር ላይ ገደብ የሚያደርጉ ዝንባሌዎች ታይተዋል

– ለዉጥም ማምጣት የሚችል፣ ህዝብን የሚያረካ አመራር የመስጠት ጉድለትም አለ

– የአገልግሎት አሰጣት ሕዝብን አማሯል

– የሠብአዊ መብት አያያዝ ላይ ጉድለት አለ

– የኑሮ ውድነት ፣ የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት ችግር ፣ ህገ ወጥ ንግድ እና ኮንተሮባንድ ፣ህገ ወጥ የመሬት ወረራ፣ የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ መሆን በሚችለው ደረጃ እንዲሆን አልተደረገም

– በክልላችን ሙስና እና ብልሹ አሠራር ሰፍኗል

– የመንግስትን አገልግሎት በእጅ መንሻ ማግኘት ያልተቀረፈ ችግር በመሆኑ ህብረተሰቡን አማሯል

– ቁጥሩ ቀላል ያለሆነ ህዝብ በድህነት ውስጥ ይኖሯል

ሲል ነው ያሉ ችግሮችን የዘረዘረው። ችግሮችን መዘርዘር ያው የተለመደ ነው።ምንም አዲስ ነገር የለውም። ሆኖም ችግሮች በመፍታት ረገድ ተግባራዊ እርምጃዎች ከተወሰዱ ጥሩ ሁኒታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ።

ለምሳሌ የአማራ ቴሌቪዥኝ ሙሉ ነጻነት ከተሰጠው፣ እነ ኮሎኔል ደመቀና የወልቃይት ኮሚቴ አባላት፣ እንደ ሰማያዊ፣ መኢአድ ያሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ብአዴን ከፈቀደ በራሱ ትልቅ ነገር ነው። በዚህ አጋጣሚ አገር ቤት ያሉ ድርጅቶች ብአዴንን ይፈትኑት ዘንድ አበረታታለሁ። የወልቃይትን ሆነ ማናቸውን የሕዝብ ጥያቄ ብአዴን ራሱ ማንሳት ባይፈልግም፣ ሌሎች እንዲያነሱ ከፈቀደ በራሱ ትልቅ እርምጃ ነው

በረጅሙና በተንዛዛው መገልጫ ውስጥ ስለተቀበሩ ሌሎች ሁለት ጠቃሚና ደስ ያሰኙኝ ቁልፍ ነጥቦችን አንስቼ አበቃለሁ

” የፌደራል ተቋማት የሰው ሃይል አደረጃጀት ብቃትንና ብሄራዊ ተዋጽኦን ማእከል በማድረግ እንዲደራጅ እና የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም ተቋማቱን ሪፎርም የማድረግ ስራ እንዲሰራም የበኩሉን ሚና መጫወት እንደሚገባው ስምምነት ላይ ተደርሷል ” ይላል መግለጫው። ይሄ አለት ባዴን ለመjእመoርያ ጊዜ የሕወሃት የበላየነt እንዳለ በይፋ መግለጹን የሚያመላከት ነው። በደህንነት መሶርያ ቤቶች፣ በመከላከያ ከፍተኛ ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ አብዛኞቹ ሕወሃቶች ናቸው። ብአዴን ያ መቀየር አለበት የሚል አቋም ነው የይዘው።ይሄንን አቋሙን በፌዴራል ደረጃ ማንጸባረቅ ከቻለ በአገር ደረጃ መሰረታዊ ለዉጥ የማምጣት አቅሙ ቀላል አይደለም የሚሆነው።

 

ሌላው ብአዴን ለመጀመሪያ ጊዜ ከአማራ ክልል ዉጭ ስለሚኖሩ አማራዎችና አማርኛ ተናጋሪዎች መብት የሚታገል መሆኑ ገልጿል። እንደሚታወቀው ላለፉት 27 አመታት ከአማራው ክልል፣ ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ከተማ ውጭ የሚኖሩ፣ ራሳቸውን አማራ የሚሉና እንደ እኔ ያሉ ሕብረብሄራዊ የሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን አገር አልባ ሆነው፣ እንደ መጤ እየተቆጠሩ፣ አገራችሁ አይደለም ተብለው እየተገደሉ፣ እየተፈናቀሉ፣እ ስከ አሁን ድረስ አንገታቸው ደፍተው ነው የሚኖሩት። ሆኖም ብአዴን ከአማራ ክልል ውጭ ላሉ አማርኛ ተናጋሪዎች እንደሚቆም መገልጹ በግሌ አስደስቶኛል።

 

ወገኖች፣ የብአዴን መግለጫ የግንቦት ሰባት ወይም የኢሕአፓ መግለጫ እንዲሆን መጠበቅ የለብንም። ሙሉ ለሙሉ ወደ ምንፈልገው ደረጃ አለመድረሳቸው ቢያሳዝነንም፣ ወደምንፈልገው ደረጃ እንዲደርሱ ማገዝና ማበረታታ ያስፈለጋል። አንድ ነገር አንርሳ ብአዴን እነ ኮሎነል ደመቀ፤ እነ ጀነራል አሳምነው ጽጌ ሁሉ እንዲፈቱ ትልቅ ሚና የተጫወተ ነው። ፈረንጆች “let not the perfect be the enemy of the good” ይላሉ። መቶ በመቶ ባናገኝም አምሳት በመቶ ካገኘን፣ ያንን ይዘን ወደ ላይ ወደ መቶ መሄድ እንጂ፣ ያለውን አፈራረሰን ወደ ዜሮ መዉረድ የለብንም።

 

“ከህዝባችን ጋር ሆነን የማነፈታው ችግር የለም !!!!!” ይላሉ ብአድኖች በመግለጫቸው መጨረሻ። ምንም ጥርጣሬ የለዉም። ህዝብን ካከበሩ፣ ህዝቡ ለማገልገል ከቆረጡ፣ ሕዝብን ካስቀደሙ ሕዝቡም ከነርሱ ጎን ይቆማል። ምንም ስጋት የለኝም እነ አቶ ገዱ ከሕዝብ ጎን እንደሚቆሙ። ጥይቄ ያለኝ ግን ከሕዝብ ጎን የመቆም ፍጥነታቸውና የድፍረታቸው መጠን ላይ ነው። በተለይም ለስራ እንቅፋት የሆኑ ተምቾች፣ የሕወሃት አገልጋዮች አዝለው በተጋኡዙ ቁጥር ወደ ሚፈለጉበት ደረጃ በቶሎ መድረሳቸው አጠያያያቂ ነው። ያስቡበት እላለሁ።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.