ከእስር የተፈቱ የኦፌኮ አመራሮች በኦሮሚያ ከተሞች አቀባበል ይደረግላቸዋል ተባለ

“የሰዎችን እንግልት ለማስቀረት አመራሮቹ ወደ ህዝቡ ቢሄዱ ይቀላል”
በቅርቡ ከእስር የተፈቱት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮች በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ከዛሬ ጀምሮ  እስከ የካቲት 22 ቀን 2010 ዓ.ም በህዝቡ ጋባዥነት የአቀባበል ስነ ስርአትና ጉብኝት እንደተዘጋጀላቸው ፓርቲው ገለጸ፡፡
ሕዝቡ ባዘጋጀው የአቀባበል ስነ ስርዓት ላይ የሚሳተፉት የኦፌኮ ሊቀ መንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ተ/ም/ሊቀ መንበሩ አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች አቶ አዲሱ ቡላላ፣ ጉርሜሳ አያኖ፣ አልባና ሌሊሳና ሌሎች ከእስር የተፈቱ አመራሮች መሆናቸውን የፓርቲው ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡ ህዝባዊ የአቀባበል ስነ ስርዓቱ በነቀምት፣ ጊምቢ፣ ደምቢዶሎ፣ ሆሮና ሌሎች ከተሞች እንደሚደረግላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ የካቲት 13 በምዕራብ ሸዋ ጀልዱ ወረዳ፣ ዶ/ር መረራ ጉዲናን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች አቀባበል እንዳደረጉላቸው ታውቋል። በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ሰዎች የሚሳተፉበት የአቀባበል ስነስርአት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር አይጋጭም ወይ የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ “የሚካሄዱት የአቀባበል ስነ ስርአቶች ህዝቡ ብቻ ሳይሆን የየወረዳዎቹና ከተማዎቹ አስተዳደሮች የሚሳተፉባቸው ናቸው፤ ኮማንድ ፖስቱም፣ የፀጥታ ሃይሉም ያውቃቸዋል” ሲሉ መልሰዋል፡፡
እስካሁን የተደረጉት የአቀባበል ስነስርዓቶች ያለ ምንም የፀጥታ ችግር መጠናቀቃቸውን የጠቆሙት ም/ሊቀ መንበሩ፤ ”የፀጥታ ሃይሎችና የአስተዳደር አካላት ትብብር አልተለያቸውም፣ አሁንም የአስተዳደር አካላቱ ራሳቸው የሚሳተፉበት የአቀባበል ስነ ስርዓት ነው” ብለዋል፡፡
ከየአካባቢው የአመራሮቹን መፈታት እየሰሙ ለመጠየቅ የሚመጡ ሰዎች በርካታ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ይህን እንግልት ከማስቀረት አንጻር አመራሮቹ ወደ ህዝቡ ቢሄዱ ይቀላል” ብለዋል፡፡

ምንጭ – አዲስ አድማስ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.