ዶ/ር አብይ፤ የአገሪቱ ጠ/ሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገምቷል

በዚህ ወር መጨረሻ ቀጣዩ ጠ/ሚኒስትር ይታወቃል

ሶስቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ኦህዴድ፣ ብአዴን እና ደኢህዴን ግምገማ ላይ የሰነበቱ ሲሆን ኦህዴድ የ42 ዓመቱን ዶ/ር አብይ አህመድ ሊቀ መንበር አድርጎ መርጧል፡፡ ብአዴን በበኩሉ፤ ነባሮቹ አመራሮች አቶ ደመቀ መኮንን እና  አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዲቀጥሉ ወስኗል፡፡ ደኢህዴን ደግሞ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን የሚተካ ሊቀመንበር እንደሚመርጥ እየተጠበቀ ነው፡፡
ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከመንግስት ሥልጣናቸው የመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ የስልጣን ክፍተት መፈጠሩን ለ“ብሉምበርግ” የጠቆሙት የቀድሞው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ኢህአዴግ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ በሚያደርገው ስብሰባ ቀጣዩን ጠ/ሚኒስትር እንደሚመርጥ አስታውቀዋል፡፡
ኦህዴድ ዶ/ር አብይ አህመድን በሊቀመንበርነት መምረጡን ተከትሎ ለኢህአዴግ ሊቀመንበርነት እጩ ተወዳዳሪ ሆነው እንደሚቀርቡ በስፋት እየተነገረ ሲሆን የአገሪቱ ቀጣይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆኑ እንደሚችሉም ከወዲሁ ሰፊ ግምት ተሰጥቷቸዋል።
ኦህዴድ ባደረገው የአመራር ሹም ሽረት ጉዳይ ላይ የድርጅቱ ሊቀመንበሩ የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ በሰጡት ማብራሪያ፤ ድርጅቱ ይህን የወሰነው ያሉበትን ድርብርብ ኃላፊነቶች በአግባቡ ለመወጣት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ኦህዴድ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው የጠቆሙት አቶ ለማ፤ “ከኦህዴድ የሀገሪቱን ከፍተኛ ስልጣን የሚይዘው ሰው ሰርቆ ኦሮሞን ሀብታም ለማድረግ አይደለም። ለፍትህ፣ ለነፃነት እንዲሁም ሁሉንም ህዝብ እኩል አገልግሎ፣ ህዝባችንን እንዲያስከብር ነው የምንፈልገው” ብለዋል፡፡ የክልሉን ህዝብ ወክሎ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ደረጃ ሀገሪቱን የሚመራ ሰው ሀገሪቱንና ህዝቡን ማገልግል ያለበት በዚህ ደረጃ ነው፤ ሁሉንም በእኩል አይን የሚያይ መሆን አለበት ብለዋል – አቶ ለማ መገርሳ፡፡
የኦህዴድ የሊቀመንበርነት ቦታን ለዶ/ር አብይ በሙሉ ፍቃደኝነት መስጠታቸውን የገለፁት አቶ ለማ፤ ይህን ያደረጉትም አሁን ሀገሪቱ የገባችበት ቀውስ ከስልጣናቸው የማይበልጥ በመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “እኔ በኦሮሚያ የጀመርኳቸው ስራዎች አሉ፡፡
የተሻለ ስልጣን ስለተገኘ ብቻ ከክልሉ ህዝብ ጋር የጀመርኩትን ከግብ ሳላደርስ የምሄድ ከሆነ መልካም አይደለም” ያሉት ፕሬዚዳንት ለማ፤ “ህዝቤ በጀመርኩት ነገር ተደስቶ፤ ለማንም ያልሰጠውን ፍቅር ሰጥቶኛል፡፡ ይህንን ሀሳቤን ብቻ አይቶ ፍቅር የሰጠኝን ህዝብ፣ ሃሳቡን ወደ ተግባር ቀይሬ መካስ እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡
በክልሉ የጀመሩት ስራ የሚሳካላቸው ከሆነም አንድ ቀን አገሪቱን በመሪነት የማገልገል እድል ሊያገኙ እንደሚችሉም አቶ ለማ ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው፤ “ኦህዴድ ከዚህ የስልጣን ሹም ሽረት ውሳኔ ላይ የደረሰው፣ የክልሉና የሀገሪቱ ህዝብ ሲያካሂደው የነበረውን ትግል ከጫፍ ለማድረስ ነው” ሲሉ ፅፈዋል – በማህበራዊ ድረ-ገፃቸው፡፡
ዶ/ር አብይ አህመድ በጠ/ሚኒስትርነት ሊመረጡ እንደሚችሉ ታዋቂ ፖለቲከኞችና የድረ-ገፅ ፀሐፊዎች ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ፤ የኦህዴድን ውሳኔ አስመልክቶ በፌስ ቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት አስተያየት፤ በሁለት ዓመታቱ የህዝብ ተቃውሞ መሃል፣ ኦህዴድ ጥርስ ማብቀል መቻሉን በመጥቀስ፣ የእነ አቶ ለማ ቡድን የኢትዮጵያን ፖለቲካ በአዲስ መልክ መውሰድ እችላለሁ ብሎ፣ በአቶ መለስ ራዕይ ላይ ማመፁን ይገልፃሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ኦህዴድ ካገኘው ድጋፍ አንፃር የጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቦታ ለሱ የማይሰጥበት ምክንያት እንደሌለ የፃፉት አቶ ዳንኤል፤ ይሄን ተከትሎም በሀገሪቱ ፖለቲካዊ መሻሻሎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ተስፋቸውን ገልፀዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለኦህዴድ ድጋፍ የሚያደርጉ ፅሁፎችን በድረ ገፃቸው ላይ በመፃፍ የሚታወቁት ዶ/ር ደረጀ ገረፋ በበኩላቸው፤ “አቶ ለማ የሊቀመንበርነት ቦታቸውን በፓርላማው መቀመጫ ላላቸውና የአገሪቱ የጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ሰፊ እድል ለተሰጣቸው ዶ/ር አብይ አህመድ መልቀቃቸው፣ በሳል መሪነታቸውን ያስመሰክራል” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቦታም ከእንግዲህ የኦህዴድ የማይሆንበት ምክንያት የለም የሚሉት ዶ/ር ደረጀ፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም የኢትዮጵያን ህዝብ ከዳር እስከ ዳር አንድ የሚያደርግ፣ ሁሉንም በእኩልነት የሚያይ ሊሆን ይገባል” ሲሉ ፅፈዋል፡፡
የ“ሆርን አፌይርስ” ድረ-ገፅ ባለቤትና አዘጋጅ ዳንኤል ብርሃነ ደግሞ፤ አዲሱ የኦህዴድ ሊቀ መንበር ብሄር ለይቶ የሚደርስን ጥቃት የመኮነን ዝንባሌ አላቸው፣ ኃላፊነት የሚሰማው መሪ ባህሪይ ለማሳየትም ጥቃቶችን ለማውገዝ ሙከራ አድርገዋል፤ ይህ ባህሪያቸው ወደፊት ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦችን ሁኔታ ለማሻሻል ያግዛል ብሏል፡፡
የህውሓት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፤ አቶ ለማ መገርሳ በቀዳሚነት፣ ዶ/ር አብይ አህመድ በሁለተኝነት የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ሆነው የመሾም ዕድል እንዳላቸው ግምታቸውን ለብሉምበርግ ገልፀዋል፡፡
የኦህዴድ ሊቀ መንበር የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ፤ አሁን ም/ሊቀ መንበር ሆነው በክልሉ ፕሬዚዳንትነታቸው ይቀጥላሉ ተብሏል፡፡
ከአራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች አንዱ የሆነው ህውሓት በቅርቡ  ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤልን በሊቀመንበርነት መምረጡ የሚታወስ ሲሆን ብአዴን በበኩሉ፤ ነባሮቹ አመራሮች አቶ ደመቀ መኮንን እና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዲቀጥሉ ወስኗል፡፡
በሌላ በኩል ደህኢዴን አዲስ ሊቀ መንበርና ምክትል ሊቀ መንበር እንደሚመርጥ ይጠበቃል፡፡
ዶ/ር አብይ አህመድ ማን ናቸው?
ኦህዴድ ሰሞኑን ሊቀ መንበር አድርጎ የሾማቸው ዶ/ር አብይ አህመድ፤ ደርሰዋል፡፡ በጅማ አጋሮ የተወለዱ ሲሆን በወጣትነታቸው የመከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል እስከ ሌተናል ኮሎኔልነት ማዕረግ ደርሰዋል፡፡
የ3 ሴት ልጆች አባት የሆኑት ዶ/ር አብይ፤ የመጀመሪያ ድግሪያቸው በኮምፒውተር ኢንጅነሪንግ ያገኙ ሲሆን በትራንስፎርሜሽናል ሊደርሺፕና የለውጥ አመራር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ ተቀብለዋል፡፡ የዶክትሬት ዲግሪያቸውንም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና የደህንነት ጥናት ተቋም አግኝተዋል፡፡
በወታደራዊ አገልግሎታቸውም በሩዋንዳ ሰላም ማስከበርና በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የተሳተፉ ሲሆን በከፍተኛ የወታደራዊ ደህንነት ሥራ እንዲሁም የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነትን በመመስረትና በመምራት ጉልህ ሚና መጫወታቸውን የህይወት ታሪካቸው ያመለክታል።
ከዚያም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ዶ/ር አብይ፤ ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ኦሮሚያ ክልል በመዛወር የኦሮሚያ ከተማና ቤቶች ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ሲሆኑ ሰሞኑን የኦህዴድ ሊቀ መንበር ከመሆናቸው በፊትም የድርጅቱ ጽ/ቤት ኃላፊ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡

ምንጭ – አዲስ አድማስ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.