የበረከት ስምኦን  ለቅሶና ተቃውሞ  በዶ/ር አብይ አህመድ  እና በኦብኤን ቲቪ ላይ

 
ሰላም የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች።
ልባዊ ሰላምታዬን ባላችሁበት አቀርባለሁ።
 
የውስጥ ድክመቶቻችን ያስከተሉት የህዝብ ቅሬታና ክፍተት እንዲሁም አጋጣሚውን የተጠቀሙበት ሀይሎች አፍራሽ ሚና ተዳምሮ አሳሳቢ ሁኔታዎችን በመፍጠሩ ድርጅታችን ጥልቅ ተከታታይና ዙሪያ መለስ የተሀድሶ ስራዎችን እያካሄደ እንደሆነ ይታወቃል። የዚህ አካል የሆነው የብአዴን ጥልቅ ግምገማ መጠናቀቁንና የአቋም መግለጫውን ከሚዲያ ሰምታችኋል።
 
የተሀድሶ ሂደታችንን በሰፊው ህዝብ ዘንድ ለማስረጽ በተለይም ለስልጣን ያለ የተዛባ አተያይን እና የህዝበኝነት ዝንባሌዎችን የሚተነትኑ ጽሑፎች በአዲስ ራዕይ መጽሔት በኩል በማውጣት ህዝቡ እንዲወያይበት አድርገናል።
 
በነዚህ ሁለት ቁልፍ ችግሮች ዙሪያ በቀጣይም በሚመለከታቸው የኢህአዴግ መዋቅሮች አማካኝነት ሰፋፊና ጥልቅ ውይይቶችን የሚደረጉ ይሆናል።
 
ይሁን እንጂ የድርጅታችን ሊቀመንበር የስራ መልቀቂያ ማስገባት እና የአመራሮች በተለያዩ ስራዎች መጠመድን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለስልጣን ባለ የተዛባ አተያይ የተመሰረተ አደገኛና ትርምስ የሚጋብዝ ህዝበኛ አካሄድ እየታየ በመሆኑ የተወሰኑ ነጥቦችን ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ታይቶኛል።
 
በድርጅታችን ባህል ስልጣን ህዝብን ማገልገያ እና የማህበረሰብ ለውጥ ማምጫ የልማት መሳሪያ እንጂ የግለሰብ ዝና (personality cult የሚባለው) የሚገነባበት አይደለም። ከሊቀመንበር ጀምሮ በየትኛውም ቦታ ላይ የሚደረግ ምደባ የግለሰቡን ጽናት ልምድ የግምገማ ውጤት የመሳሰሉትን ነገሮች መሰረት ያደረገ ብቻና ብቻ ነው። እነዚህን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሟላው እጩ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ጓድ ደመቀ መኮንን ቢሆንም ሌሎች የተሻሉ ካሉ በአመራር ስብሰባ ላይ ቀርቦ የምንነጋገርበት እንጂ እንደኒዎ ሊበራል ድርጅቶች በየሶሻል ሚዲያው ቅስቀሳ የሚደረግበት አሰራር የለም።
 
በክልል ቴሌቪዥን የአንድን እህት ድርጅት የአመራር አባል ማስታወቂያ የሚሰራበት እና ህዝቡ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ የሚደረግበት አካሄድም ከድርጅታችን ባህል ያፈነገጠ ነው። በተለይ ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ አንዱ ምክንያት የሆነው ዛሬ በኦሮሚያ ቴሌቪዥን በአማርኛ የቀረበው ዶኩመንታሪ ከአብዮታዊ ባህል ያፈነገጠ የድርጅትን ስልጣን በህዝበኝነት ለመቆጣጠር የተደረገ እና ህዝቡን ለተሳሳተ ግንዛቤ ብሎም ግርግር ሊሚመራ የሚችል ነው።
 
ዶኩመንታሪውን አስደንጋጭ የሚያደርገው ከድርጅታችን ባህል ማፈንገጡ ብቻ ሳይሆን ከእውነት የራቁ መረጃዎችን የያዘ መሆኑን ነው።
 
የደርግ ስርአትን በሚገረሰስበት ወቅት በየቦታው የኦህዴድን መዋቅር ስናደራጅ ጓድ አብይ አህመድ ድርጅቱን እንዲቀላቀል እንዳደረግን እና በክፍለ ህዝብ ክንፍ ተመድቦ የሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የቅስቀሳና ማደራጀት ስራዎችን እንዲያግዝ ማድረጋችን ትዝ ይለኛል። በ1987 የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ጸድቆ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሲደራጅ የሰራዊቱን ተዋጽኦ ለማመጣጠን ወደ ሰራዊቱ እንዲገቡ ከተደረጉ የድርጅት አባላት አንዱ ነበር። ሻዕቢያ በወረረን ወቅት በሀምሳ አለቃ ማዕረግ በራዲዮ ኦፕሬተርነት ይሰራ እንደነበር የሰራዊቱን ዝግጅት ለመጎብኘት በሄድኩበት ወቅት ተረድቻለሁ።
 
በ1997ቱ ምርጫ ማግስት ከሰራዊቱ ጋር በነበሩ ስራዎች አጋጣሚ አግኝቸው መቶ አለቃ ደርሶ እንደነበር አስታውሳለሁ። ከዛ በኋላ ሰራዊቱ ውስጥ በቆየባቸው ጥቂት አመታት ከመቶ አለቃ ወደ ሌተናል ኮሎኔል ማዕረግ መድረሱ ያጠራጥረኛል። የሌተናል ኮሎኔል ማእረግ ከተሰጠውም ሊሆን የሚችለው የብሄር ተዋጽኦ ማመጣጠን በሚባለው አካሄድ ነው። የብሄር ተዋጽኦ የማመጣጠን አሰራራችን ህገመንግስታዊና ትክክለኛ ቢሆንም በዚህ አካሄድ ፈጣን እድገት ያገኙ አባላት አላማውን በመገንዘብ ሰራዊቱ ውስጥ እስካሉ ድረስ ይገለገሉበታል እንጂ ከሰራዊቱ ከወጡ በኋላ ለማስታወቂያ ፍጆታ አያውሉትም።
 
ለስልጣን ያለንን የተዛባ አተያይ የሚያመለክቱ በርካታ ግነቶች በዶክመንታሪው ላይ መታየታቸው የድርጅታችንን ጤንነት ቆም ብለን መመርመር ማየት እንዳለብን የሚጠቁም ነው። የኢንሳ መስራች ነው ተብሎ የቀረበው ግራ የሚያጋባ ነው። ይህን ዘመናዊ ሀሳብ ያፈለቀው ጓድ መለስ ዜናዊ ነው። ሲከተል ደግሞ ኢንሳ መስራች አለው ከተባለ መስራቹ መንግስት ነው። በመሰረቱ ኢንሳ ቀድሞ ሲግናል ሬጅመንት ሲባል ከነበረው አሀድ ያደገ ተቋም ነው። እዚያ የነበሩ ዋነኛ ሞተሮች ደግሞ የብአዴን ፍሬዎች የሆኑት እነ አህመድ ሀምዛ እነ ተመስገን ጥሩነህ ናቸው። ለጓድ አብይ የኢንሳ ዳይሬክተር ሆኖ የተሾመበት አጋጣሚ የነበረ አይመስለኝም። የመስሪያ ቤቱ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደመሆኑ ጓድ መለስ የዳይሬክተር ለውጥ ሹመት ሰጥተው ቢሆን ያሳውቁን ነበር።
 
ከግል ህይወት ታሪክ ወይም ሲቪ ጋር በተያያዘ ጓድ ሃይለማሪያም በሰጡት መመሪያ መሰረት የአመራሮችን የትምህርት ማስረጃዎች ማሰባሰብና ማደራጀት ሲካሄድ ጓድ አብይ በውጭ ሀገር የማስተር ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን አግኝቻለሁ በሚለው መረጃው ምክንያት ከጓድ ሙክታር ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተው እንደነበር አስታውሳለሁ። የሰነድ አደራጅ ኮሚቴ የተጠቀሰውን ዩኒቨርሲቲ ሆነ የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥ አለመቻሉን ለማዕከል ሪፖርት ሲያደርግ ጓድ ሙክታር ስልጣኑን ተጠቅሞ ባለማስቆሙ ከጓድ አብይ ከፍተኛ ቅሬታ እንደቀረበ ይታወሳል። ይህም ለስልጣን ያለ የተዛባ አተያይን የሚያመለክት መሆኑ ተግልጾለት ሂሱን የዋጠ ሲሆን አጠቃላይ ጉዳዩ በእናት ድርጅት ተገምግሞ እንዲቀርብ አቅጣጫ ተሰጥቶ ነበር። ዛሬ ዶኩመንታሪው ላይ ተደግሞ ሳየው የስንት አመታት ግምገማና ውይይት ምን ወንዝ ወሰደው የሚያስብል ነበር።
 
የግለሰቦች ጉዳይ በተገቢው የድርጅት መድረክ ይታያል። እነዚህን መረጃዎች እዚህ ለማቅረብ ያስገደደው ምክንያት ህዝብ የተሳሳተ ግንዛቤ ተፈጥሮበት ወደውዥንብርና ግርግር እንዳይገባ ከወዲሁ እርማት መስጠት ግዜ የማይሰጥ ድርጅትንና ሀገርን የማዳን ተግባር በመሆኑ ነው። አመራሮች በተለያዩ ስራዎች በመያዛቸው የተለመደውን መዋቅር ሳልጠብቅ የድርጅታችንን አባላትና ደጋፊዎች በቀጥታ እና በፍጥነት ማስገንዘብ አስፈላጊ በመሆኑ ነው።
 
መላው የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች በየአቅጣጫው በሚታዩ ነገሮች ሳይደናገሩ የኢህአዴግና የብአዴን አመራሮች ስልጣንን የለውጥ መሳሪያ እንጂ የግል ጥቅም ማራመጃ አድርገው እንደማያዩት እምነት ሊያሳድሩ ይገባል። አንዳንድ በየቦታው የሚታዩ ጤናማ ያልሆኑ ዝንባሌዎችም በዙሪያ መለስ ግምገማ የሚስተካከሉ ናቸው። በአመራር ረገድ የሚፈጠር ክፍተት አይኖርም። ጓድ ኃይለማርያም በስራ ላይ ናቸው። እሳቸው ፈጥነው መልቀቅ ቢያስፈልጋቸው እንኳን የኢህአዴግ ምክር ቤት ምርጫ እስከሚያደርግ ድረስ በህገ-መንግስቱ መሰረት ምክትላቸው ስራውን እየሸፈኑ ይቆያሉ።
 
ከህዝባችን ጋር ሆነን የማንፈታው ችግር የለም!
የህዳሴ ጉዟችን ይሳካል!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.