እውን አጼ ቴወድሮስ “ኪነት ያገነነው” ንጉሠ ነገሥት ናቸውን? (ከ ሙሉጌታ ገዛኸኝ)

በቅድሚያ ለዚህ መጣጥፍ መነሻ የሆነኝ የዓብዱልጄሊል ዓሊ ድርሰት የሆነውና ሰሞኑን ለገበያ የበቃው «ኪነት ያገነነው አጼ» የሚለው መጽሐፍ መሆኑን ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡

መጽሐፉ እንዲያው በጥቅሉ የአጼ ቴወድሮስን አነሳስና አወዳደቅ ሚዛናዊ ባልሆነ አተያይና ትርክት ላይ ተመርኩዞ የሚተች እንደመሆኑ መጠን ተቀባይነቱ ከንቱ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ምክንያቱም አጉል ጥላቻን በልፍስፍስ የመታገያ ስልትነት በመጠቀም ሌላውን ለመጉዳት በሚገለጽፅ አጻጻፍ ብቻ እርካታን ለመቀዳጀት ደራሲው ሞክሯል፡፡ አጼ ቴወድሮስን አረመኔያዊ አድርጎት አግዝፎ ለአገር ፍፁም በጎ አስተሳሰብ የሌላቸው አስመስሎ አዲሱ ትውልድ ቂምና በቀል አዘል የማጠልሸት ታሪክን እንዲወርስ ጫና መፍጠር ተገቢ አይደለም፡፡ አንድነትና ዘመናይነትን ዕውን ለማድረግ ሲሉ ለከፈሉት መስዋእትነት ውለታ ቢስነት ያስመስላል፡፡ ሌላው ቢቀር ጋፋት ላይ ያሰሩት የሴቫስቶፖል መድፍ አንድምታ ለአሁኑ የመከላከያ ኢንዱስትሪ መዘመን ፈር ቀዳጅ ነው፡፡

የታሪክ ምርምርና ጥናት በተሻለ ማስረጃና አጠናን ዘዴ በየጊዜው እየዳበረ መሄዱ አስፈላጊነቱ ቅቡል ነው ሲባል በፈጠራ ድርሰት የግል ስሜት ማንፀባረቂያ ማድረግ ፈፅሞ ሙያዊ ሃላፊነት የጎደለው ነው፡፡ በየትምህርት ቤቱ እና ዩኒቨርሲቲው ስለ አገር ፍቅርና አርበኝነት አርኣያነት ለማስተማር ምንጊዜም አጼ ቴወድሮስን የመሳሰሉ መሪዎች መጠቀሳቸው እየታወቀ በተቃራኒው ትውልዱን በፈጠራ ድርሰት ለማወናበድ እንደ አብዱልጄሊል ያሉት ይራወጣሉ፡፡ የታሪክ ትምህርት ይዘትን አስመልከቶ በአገር አቀፍ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርት ሲቀረፅ ወደድንም ጠላንም ዘመናዊ ኢትዮጵያ እና የአጼ ቴወድሮስ ጉልህ አስተዋፅዖ ይካተታል፡፡ ታዲያ የትምህርት ሚኒስቴር ትውልድ እንዲታነፅበት ባወጣው የታሪክ ማስተማሪያ እውነታ ላይ የአብዱልጄሊል ዔሊ ዓይነት የሚፋለስ ታሪክ መጽሐፍ እያሳተሙ ኪስ ማደለቢያ ሲሆን ዝም ብሎ ማለፍ ያስተዛዝባል፡፡ የሚመለከታቸው ምሁራንና አስተማሪዎች ምልከታ በማድረግ አስፈላጊውን ሙያዊ ትችት መሰንዘር ይኖርባቸዋል ለማለት ወደድኩ፡፡

አጼ ቴወድሮስ ከጻፏቸው ደብዳቤዎች እንደምንገነዘበው ከትቢያ ተነስቶ ንጉስ ለመሆን ያበቃቸው የተለመደው የዘር ሐረግ ውርስ ሳይሆን በአገር ፍቅር ነዲድ መሆኑን ነው፡፡ ይኸውም አራሽ ገበሬ ተገፋ፤ ድሀ ተበደለ፤ በስግብግብ መሣፍንቶች አገር ቆረቆዘ፤ ስልጣኔ ወደመ፤ ሥርዓት አልበኝነት መገለጫ ሆነ፤ ዘመናዊ አስተዳደር ጠፍቶ ማዕከላዊነት ተዳከመ፤ የተባበረ ክንድ ስላልፈጠርን የወጭ ኀይላት ሉዓላዊነታችን ተደፈረ ወዘተርፈ ቁጭት የፈጠረበት ፋና ወጊ ንጉስ መሆኑን የውጭም ሆኑ የአገር ውስጥ ተመራማሪዎችና ጸሓፍት አበክረው ፅፈዋል፡፡ ዋናው ቁም ነገሩ የቴወድሮስ ራዕይና ዓላማ ከምን እንደመነጨ የመገንዘቡ ጉዳይ ሲሆን በተደጋጋሚ እንደተጠቀሰው ዘመናዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት ብሎም አንድነቷና ኅብረቷ ከብረት የጠነከረች የማትደፈር አገር በዓለም እንድትታወቅ አስችሏል፡፡ በእኛ አገር እንዳለመታደል እርግማን ሆኖ እንጅ ጀርመኖች፣ ኢጣልኖች እና ሌሎችም አውሮጳውን አገር የገነቡ መሪዎቻቸውን ተምሳሌት የማድረግ ቅቡል ነው፡፡ ምዕራባውያን እንደሚሉት ከዜሮ ወደ ዋና ባለታሪክ(from zero to hero) መሆንም እኮ ይቻላል፡፡

ደራሲው ዓብዱልጄሊል አጼ ቴወድሮስን የታሪክ ተወዳሽ ሳይሆን ተወቃሽ መሆን አለበት ሲል ይሞግታል፡፡ በአገሪቱ ልዩ ልዩ ሕዝቦች በተለይም በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ ያደረሰው በደል ከባድ መሆኑን በተገቢው ሙያዊ የታሪክ ማስረጃና ትንታኔ ሳይሆን በተጋነነ መልክ አቅርቧል፡፡ እዚህ ላይ በሀቅ ላይ ተመስርቶ መጻፍ ካለበት እኮ ከአጼ ቴወድሮስ መምጣት በፊት ግራኝ በወረራው ወቅት ያደረሰውን ውድመትና ጥፋት መጥቀስ ነበረበት፡፡ እንደ ጻድቅ የተቆጠረው ኢማም አህመድ ያካሄደው ጦርነትም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንጅ አገሪቱን ለማዘመን ያላንዳች ግድያና ፍጅት በቅዱስ ጦርነት ሰተት ብሎ አልነበረም ከጠረፍ እስከ መሀል አገር የዘለቀው፡፡ መጽሐፉ ከታሪክ ግኝት ጠቀሜታው ይልቅ ለአንድ ወገን የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ በማዋል በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ከሚንፀባረቁ ሕዝባዊ ቅሬታዎች አዳብሎ ቤንዚን ማርከፍከፍን ያለመ እንደሆነ የግድ ምሁር መሆን አያሻም ለማንም ሰው ግልፅ ነው፡፡

የመጻፍ ሕገ መንግስታዊ ነጻነት መብቶች ሰበባ ሰበብ እየሆኑ ማንም የፈለገውን ማሳተም አይቀርምና የአካዳሚክ ነጻነትን መርህ መከተል ደግሞ ከዚህ በእጅጉ ይለያል፤ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ የጥናትና ምርምር ማካሄድ የሚያስገኘውን ጠቃሚ ውጤት ፋይዳ ባለው ሁናቴ ስራ ላይ ማዋል ነው፡፡ በተለይም በማኅበራዊ ሣይንስ ዘርፍ የሚደረጉ ጥናቶችና ምርምሮች ሕብረተሰባዊ ሃላፊነትና ጥንቃቄን ይሻሉ ምክንያቱም በተለያየ ሁናቴ የእኩይ ጭላቻ ሰለባ የሆኑ ጥቂት ግለሰቦች በሚረጩት መርዛማ እሳቤ ነባራዊ የአገር ህልውናን ሊናጋ እንደሚችሉ ታሳቢ መደረግ አለበት፡፡ የታሪክ ጥናት ግኝቶች በመጽሐፍ መልክ ከመታተማቸው በፊት እንደአስፈላጊነቱ እውቅና ባለው የትምህርት ሚኒስቴር አካል ያለበለዚያም በገለልተኛ የባለሙያዎች ቦርድ ተገምግሞ የሚታተምበት አግባብ ቢመቻች ወጣቱን ትውልድ መታደግ ይቻላል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ድብቅ ፍላጎት ባላቸው ዘውግና ሀይማኖትን በሚያስታክኩ ጸሐፊዎች ምክንያት የትውልዱ ስሜት መጎዳት የለበትም፡፡ እንዲያው ለመሆኑ በቻይናውን ዘንድ የአዲሲቷ ቻይና መስራች አባት በመሆን ሊቀመንበር ማኦ ዜዱንግ እዚህ ደረጃ ላይ ለማድረስ የተጓዙበት ረጅም መንገድ አንዳች እንከን ሳይኖረው ቀርቶ አልነበረም፡፡ የታይዋን አበሳን፣ የታይናሚን አደባባይ እልቂትን ወዘተርፈ ከብዙ በጥቂቱ በማኦ የተፈፀሙ እንደነበሩ መጠቃቀስ በቂ ነው፡፡ በአገር ምስረታ ሂደት ላይ ማኦ ቻይናን ለመገንባ የተከተለውን ዓይነት ተሞክሮ የጭካኔ ባህሪን አሁን ላይ ያሉ የአፍሪካ መሪዎች ይከተሉ ማለት አንቀጥቅጦና አርዶ ሕዝባቸውን ለመግዛትና ስልጣናቸውን ለማራዘም ካልሆነ በቀር በአሁኑ ዘመን ተመራጭ አስተዳደራዊ ዘዴ ፈፅሞ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን ከዚህ በተለየ መልክ በዘመነ መሳፍንት ኢትዮጵያ ከገባችበት መቀመቅ እንድትወጣ አጼ ቴወድሮስ የታሪክ ክስተት ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ንጉሠ ነገሥት ቴወድሮስ በአዝማሪ ቀረርቶና ፉከራ መወደስ በጥንቱ ዘመን ተያይዞ የመጣ ባህል እንጅ በተለየ መልክ ሊታይ አይችልም፡፡ በአገራችን መሪዎችንና ጀግኖችን በዘፈን ማንቆለጳጰስ አብሮ የኖረ ልማድ እንጅ አዲስ ነገርም አይደለም፡፡ ዛሬም ላይ አድርባይ ልማታዊ አርቲስቶቻችን በየመድረኩና ዝግጅቱ ባለስልጣናትን ማወዳደስ ላይ ያተኮሩ ክሊፖች እስከሚሰለቸን ድረስ እያየን ነው፡፡
የዘመናዊ ኢትዮጵያ አመሰራረት ሲጠቀስ ቆፍጣናው የቋራው ካሳ ጉልህ ሚና አለው፡፡ የያኔዋን የተበታተነች አገር ለማጠናከር ከፍተኛ ጥረት አድርጓልና፡፡ በእንዲህ ያለ ሁናቴ በትንቅንቅና ትግል ከዘመነ መሳፍንት ድንቁርናና መንጋጋ ለማላቀቅ ባካሄደው የያኔው ትግል ስለየትኛው ዲሞክራሲ አባ ታጠቅ ካሳን እንውቀሰው? በ21ኛው ክፍለ ዘመን የተሞላቀቀ አስተሳሰብ ይዣለሁ ለማለት የ19ኛው ክፍለ ዘመን አድራጎትን ኮንኖ ማላዘን አሳፋሪ ይሆናል፡፡

ዛሬም ወደፊትም አጼ ቴዎድሮስ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለአገራቸው ክብር መስዋዕትነት የከፈሉ የጀግንነት ተምሳሌትና የምዕተ ዓመቱ ፋና ወጊ መሪ ሆነው መታወሳቸውን ታሪካዊ ቲያትር(ኪነት) ብቻም ሳይሆን ታሪክ ራሱ ደጋግሞ ይመሰክራል፡፡ ንጉሠ ነገሥት ቴወድሮስ መቅደላ ላይ ከእንግሊዝ ጦር መሪ ከጄኔራል ናፒዬር ጋር ተፋልመው እጃቸውን እንኳ ሳያስማርኩ በጀግንነት መውደቃቸውን ከማንም አስቀድሞ ሀቁን በዐይናቸው ተመልክተው ለንግስት ቪክቶሪያ ያወጁት ራሳቸው እንግሊዞቹ እንጅ የእኛ የኢትዮጵያውን ፈጠራ ጽሑፍ አይደለም፡፡ በሌሎች ዘንድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፍርሀት ቆፈን ተጨማደው በየቱቦ ስር ተወትፈውና ሀፍረትን ተላብሰው ለምርኮ የበቁትን የቀድሞው የኢራቅ አምባገነን ፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴን እና የሊቢያውን መሪ ሙአመር ጋዳፊን ህልፈተ ህይወት ልብ ይሏል፡፡ ቸር ይግጠመን!!!

1 COMMENT

 1. ኪነት ያገነነው አጼ(መጽሐፍ)፦
  ጸሃፊው ለማስረዳት የፈለገው አንኳር ጭብጥ አለ፥ይሀውም ቴዎድሮስ በእውነተኛው ታሪክና ቴዎድሮስ በኪነጥበቡ አለም።
  እንግዲህ ይህን ለመተቸትና እውነትን ከሃሰት ለመለየት ተጨባጭ ማስረጃ በማቅረብ የሞገተ እውነትም ሃቅን ፈላጊ ተብሎ ሊመደብ ይችላል፥ብጭፍን ደጋፊና
  ቲፎዞው ደግሞ ቀድሞ ጠላት በጨለማ ተዘርቶት የነበረውና አሁን ለአጨዳ የደረሰው እንክርዳዱ ወገን ተብሎ ሊፈረጅ ይችላል።
  የአድርባይ ኪነጥበቡንና የአዝማሪውን እሽኮለሌ ትተን ከታሪክ ትክክለኛ አረዳድ ተነስተን የታሪክ ማስረጃዎችን ለመተንተን ከሞከርን ግን ህልቆ መሳፍርት የሌለው ማስረጃ ማቅረብ እንችላለን።
  ክሳይንሳዊ የታሪክ አተያይ ስንነሳ የአንድ ታሪክ ጥናት ትክክለኛ አውድ በወቅቱ የነበረው ማህበረሰብ የሰጠው ግብረመልስ(ከስነቃል እስከ ተግባራዊ እምቢተኝነት፡አሁን በወያኔ ላይ እንደሚታየው)፥በወቅቱ የነበሩ እማኞችና ጸሃፊዎች—ወዘተ ናቸው።
  ከዚህ ስንነሳ ቴዎድሮስ ተነግሮ የማያልቅ ግፍ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ፈጽመዋል፡ለምሳሌ፦
  1-ራሳቸው በአንደበታቸው፡ፈጣሪ የላከኝ የኢትዮጵያን ሀዝብ ልቀጣ ነው በልው ተናግረዋል
  2-ጎጃምን አይሰሩ ስራ ሰርተውታል፥ህዝቡን ጭፍጭፈዋል ከብቱን ነድተውታል
  3-አንድም ቀን ፋሲል ቤተ መንግስት ገብተው አያውቁም
  4-ቀንደኛ ተቃዋሚያቸው አለቃ ገብረሃና ነበሩ(ከሌሎች ነገስታት ጋር ግን ሰላም ነበሩ አለቃ)
  5-ጎንደር ከተማ ሴቶችን ሰብስበው በእሳት አቃጥለዋል
  6-መቅደላ ላይ ለመመሸግ ሲሄዱ ደብረታቦር ከተማን ከነ ቤተክርስቲያኗ አቃጥለው ነው
  7-በኢትዮጵያ ታሪክ ቤተክርስቲያን ያላሰሩ ብቸኛው አጼ ናቸው
  8-በተደጋጋሚ ጊዜ አልጋውን ለወደዳችሁት ስጡት፡እኔ እንደሁ እንደ ጋላ እየዘረፍኩ መብላት አያቅተኝም በማለት ይዝቱ ነበር
  9-በተደጋጋሚ በሚሰሩት ግፍ እየተጸጸቱ ያለቅሱ ነበር
  10-እንግሊዛዊው ጀነራል(የእንግሊዝ ጀነራል አይደለም) ሊቀጣቸው ሲመጣ አንድም ወዶ ከጎናቸው የነበረ ግለሰብ አልነበረም(ሰራዊቱም ከድቷል)።ልጆቻቸውንና ሚስታቸውን የሚያስጠጋ ግለሰብ ስላልነበር መቅኖ አጥተው ቀርተዋል
  11-ከ26 በላይ ውሽሞችና ብዙ ዲቃላዎች ነበሯቸው
  12-በኢትዮጵያ ታሪክ ተቆጥሮ የማያልቅ እንቁ የብራና ጽሁፍና ቅርስ እንዲዘረፍ ያደረጉ
  12-መልካቸው ከሌላው ኢትዮጵያዊ በተለየ ሁኔታ ጥቁርና አይናቸው ገባ ገባ ያለ ነበር(ይህን ከልጃቸው አለማየሁ መልክ ጋርና አሁነ የልጅ ልጆቻቸው ነን ከሚሉት ዲቃላዎቻቸው ጋር ማስተያየት በቂ ነው)

  አድርባይ ኪነጥበቡና አዝማሪው የሚስለው የጠራ ስእል ደግሞ፥-
  1-መልካቸውን ከለር ፎቶ በአለም ላይ ባልታሰበበት ዘመን ከኢየሱስ ክርስቶስ ትንሽ ሻል አድርጎና አሸናፊዎቻቸውን ፈረንጆችን በሚያስቀና መልክ(በኮምፒውተር ጸጉር በማብቀል)፥አለፍ ሲልም ፍናፍንት(የወንድ ሴት) በማስመሰል መሳል
  2-እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንከን የለሽ ፍጡርና ሁሉን ቻይ
  3-በሰሩት የዲፕሎማሲ ስህተት አንድ ተራ ጄነራል እየተዝናና ሊቀጣቸው የመጣውን፥የእንግሊዝና የኢትዮጵያ የሁለት አገር ፍልሚያ እንደተካሄደና ለአገራቸው ክብር ሲሉ እራሳቸውን እንዳጠፉ ለማስመሰል መሞከር(በነገራችን ላይ ራሳቸውን በሽጉጥ ያጠፉ ብዙ ለክብራቸው የተሰዉ ኢትዮጵያውያኖች አሉ)
  ይህን ስንታዘብ፦ እውነት እንዳትታወቅና እውነተኛው ታሪክ እንዳይወጣ ወጥሮ የሚሰራና በጭፍን የሚፏልል ማህበረሰብ መኖሩን እንረዳለን።ይህም የታሪክና የስብእና ሽንቁራቸውን ለመድፈን የሚፍጨረጨሩ ልበስውሮች ስራ እንጂ የአገር ወዳድና እውነተኛ ታሪክ ያለው ዜጋ ተግባር እንዳልሆነ ያስታውቃል።
  ከዚህ ሃቅ ስንነሳ በጉልህ የሚታየው የጸሃፊው ስህተት ሳይሆን አዝማሪ ያሳደገው ግልብ ቲፎዞ ችግር የማንነት እጦቱን ለማወራረድ እውነትን እያጣመመና ስሜቱን እያራገፈ ያለ መሆኑን ነው።
  ቴዎድሮስ ትክክል ከነበሩ፥
  መንግስቱና መለስ የሰሩት ግፍ ለአገራቸው ሲሉ ነውና አርአያነታቸውና ትሩፋታቸው ይድረሰን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.