“ሰኞ የወጣ ስም ማክሰኞ አይመለስም” – (አብመድ)

ባህር ዳር፡የካቲት 19/2010 ዓ/ም

የዛሬ ቅኝቴ የአማራ ክልል ርዕሰ መዲና በሆነችው ባህርዳር ከተማ የሚገኘው ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል ነው::

ሆስፒታሉን የሚያውቀውም የማያውቀውም የትኛውም ሰው ቢሆን በጥሩ የሚያወሳው የለም:: ማለትም “ሆስፒታል ዘመድ ከሌለህ ዋጋ የለህም:: በሰው፣ በዘመድ አዝማድ ነው የሚሰሩት፤ ጥሩ ህክምናና ክትትልም የምታገኙት እዚያው የሚሰራ ሰው ሲኖራችሁ ነው” ነበር የሚባለው::

አስታውሳለሁ እኔ የመጀመሪያ ልጄን ለመውለድ ቀናት ሲቀሩኝ በእጅጉ ያሳስበኝ የነበረው ሆስፒታል ውስጥ የሚሰራ ሰው ለማወቅ ነበር፤ ነገር ግን ሊሳካልኝ አልቻለም:: ከዚህም ባሻገር የህክምና ባለሙያዎቹ፣ “ታካሚዎችንና አስታማሚውን የሚያመናጭቁበት ስነ ምግባር የጐደላቸው፣ የሆስፒታሉ የጽዳት ሁኔታ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የገባበት፣…” እየተባሉ ለብዙ ዓመታት ሲብጠለጠሉም እሰማ ነበር:: ነገር ግን “ማየት ማመን ነው” እንደሚባለው ሰሞኑን ዘመድ ታሞብኝ በሆስፒታሉ ተገልጋይ ሆኘ ስገኝ ነገሮች ሁሉ ተለዋውጠው ጠበቁኝ::

ሆስፒታሉን ገና ከበር ስገባ ስመለከት በወቀሳ ስናብጠለጥለው የነበረውን የህክምና ተቋም ዛሬ ላይ ተሻሽሎ በማየቴ ያለኝን አድናቆትና ምስጋና ለመግለጽ ወደድኩ:: ምክንያቱም ይህ ተቋም ሲያጠፋ እንደተወቀሰው ሁሉ ተሻሽሎና ተለውጦ ሲታይ ለሰራው ሥራ ዕውቅናና አድናቆት መስጠት ግድ ይለናል::

በመጀመሪያ እና በዋናነት መግለጽ የምፈልገው ሆስፒታሉ ከግቢው አንስቶ ውስጥ ካሉ የህክምና አልጋዎች፣ የህክምና ክፍሎች፣ የመፀዳጃ ቤቶች፣… ሁሉም ፅድት ብለዋል:: በፊት አፍንጫችንን ይዘን ለህክምና ሄደን በሽታ ይዘን እንወጣ ነበር::

ፅዳቱን ከጠበቀው የሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ታካሚውን ለመርዳት ወዲያ ወዲህ ተፍ ተፍ ወደሚሉት የህክምና ባለሙያዎች ልውሰዳችሁ::

እኔ የቆየሁበት ድንገተኛ ክፍልና ማገገሚያ የታካሚውን ብዛት ልነግራችሁ አልችልም:: ሁሉም ታካሚ እዚህ ነው ያለ ለማለት ያስገድዳል::

በዚህ ላይ ግን በጣም ሊመሰገኑና ሊደነቁ የሚገባቸውና ትክክለኛ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ የጤና ባለሞያዎች አሉንና እነዚህን ብርቅዬ ልጆች ከወገቤ ጐንበስ በማለት ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ::

አስተውላችሁ ከሆነ ከዚህ በፊት በህክመና ሙያ ላይ በስፔሻሊስት፣ በዶክተር ደረጃ የነበሩት የሴቶች ቁጥር አናሳ ነበር:: ነገር ግን አሁን ላይ ያየኋቸው ድንገተኛ ክፍል የሚሰሩ የሴት ዶክተሮች ቁጥር መጨመር፣ የሥራ ብቃታቸውና ስነምግባራቸው ታካሚንና አስታማሚን ለመንከባከብ ያላቸውን ፈገግታ የምገልጽበት ቃላት ያጥሩኛል:: እዚህ ላይ ጥሩ ሰብዕና ያላቸውን ወንድ ዶክተሮችንና ነርሶችንም ሳንዘነጋ::

ብዙዎቻችን አንድ ሰው ድንገተኛ አደጋ ሲያጋጥመው መሄድ የምንፈልገው ወደ ግል የህክምና ተቋም ነው:: ነገር ግን በድሮ በሬ አይታረስም እና የሆስፒታሉን የቆየ መጥፎ ስሙን አሁን ድረስ ሰው እየተጠቀመበት ይገኛል::

እኔ ያየሁትን ልንገራችሁ፤ አንድ ሰው ድንገተኛ አደጋ ይደርስበት እና ጓደኞቹ “የግል ይሻላል፤ ከግል እንውሰደው” በማለት ወደ ግል ህክምና ተቋም ወሰዱት:: “ይተኛ” ተብሎ አንድ ቀን ውሎ አድሮ ከፍተኛ ገንዘብ ከከፈሉ በኋላ ብዙም እርዳታ ሳይደረግለት፣ “የለም ወደ ሆስፒታል ውሰዱት” ተባሉ። ቤተሰቦቹም መሄዱ ቁርጥ መሆኑን ሲያውቁ ፊታቸው በሀዘን ተዋጠ::

ነገር ግን ከቦታው ሲደርሱና የተደረገለትን ርብርብ ሲያዩ በጣም ተደነቁ:: እኔም የእነሱን ሁኔታ ስመለከት፣ “ሰኞ የወጣ ስም ማክሰኞ አይመለስም” የሚለውን አባባል አስታወስኩ::

ስለሆስፒታሉ ይህን ያህል አድናቆት ካቀረብኩ በኋላ መቼም የሚሰራ ሰው ይሳሳታልና እኔም በዚህ ተቋም ያየኋቸውን አንዳንድ ህፀፆች ልጠቁም::

በፍጥነት መስተካከል አለበት የምለው ዋናውና ትልቁ ጉዳይ እርስ በርስ ያለመናበብ ችግር ነው:: ያየሁትን ልንገራችሁ:: አንድ ባለሙያ መጥቶ ጉልኮስ ይተክላል፣ ሌላኛው ሲመጣ ደግሞ የለም ይነቀል ይላል:: በዚህ ጊዜ የነቃ አስታማሚ የሌለው ታካሚ ባለሙያዎቹ በተፈራረቁ ቁጥር ችግር ሊደርስበት እንደሚችል ታዝቤያለሁ::

ከዚህ በፊት በታካሚ አልጋዎች ላይ የህክምና ባለሙያው የታካሚውን ታሪክ፣ የመድኃኒት አሰጣጥ አስተያየት የሚሰፍርበት በክላሴር ከአልጋው ጫፍ ላይ ይንጠለጠል ነበር:: ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት አልጋዎች ላይ ተንጠልጥሎ ቢታይም ምንም ዓይነት ጽሁፍ ግን አይሰፍርበትም:: በአብዛኛው ደግሞ ምንም ያልተንጠለጠለባቸው አልጋዎች ነው የነበሩት::

ይህ አለመኖሩ ደግሞ ባለሙያዎቹ እንዳይናበቡ አድርጓቸዋል:: በህክምና እየተናበቡ የማይሰሩ ከሆነ ትንሿ ስህተት ለከፋ ችግር ትዳርጋለችና ለዚህ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው:: የህክምና ስህተትንም ሊያመጣ እንደሚችል አስባለሁ። በእኔ አስተሳሰብ ይህ የህክምና ታሪክ ማስፈሪያ ታካሚው በዕለቱ ምን ዓይነት መድኃኒት እንደተሰጠው በየትኛው ሰዓት … የሚለውን የሚይዝ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

በየቀኑ ዶክተሮች ተሰባስበው ታካሚዎችን ይጐበኛሉ:: አንድ ቀን እኔ ከማስታምምበት ክፍል የነበረ ታካሚን የጐበኙት ዶክተሮች መድኃኒት አዘዙለትና አስታማሚዎቹ በፍጥነት ገዝተው አመጡ:: እነሱ እንደወጡ በግምት 30 ደቂቃ እንኳን ባልሞላ ጊዜ በመደበኛነት የምትከታተለው ሐኪም መጣችና፣ “ዛሬ ትወጣለህ” አለችው:: በዚህ ጊዜ እኔ በጣም ደነገጥኩ፤ ከ30 ደቂቃ በፊት የብዙ ብር መድኃኒት ገዝቶ እንደሚውል እንደሚያድር ከተነገረው በኋላ እንደገና ዛሬ ትወጣለህ ሲባል አስታማሚዎችም እኔም ግራ ተጋባን:: አስታማሚዎችም አዲስ የገዙትን መድኃኒት እና ሌሎች ያልተጠቀሙባቸውን መድኃኒቶች በሙሉ ሰብስበው ወጡ:: አንባቢያን እናንተ ብትሆኑ የየትኛውን ትዕዛዝ ነው የምትፈጽሙት?

በዚህ ጊዜ አንድ ሀሳብ ብልጭ አለብኝና ይህን ሁሉ መድኃኒት ምን ታደርጉታላችሁ? ብዬ ስጠይቃቸው፣ “ታዲያ ገንዘባችን ወጥቶበት ትተነውማ አንሄድም!” አሉኝ::

ከሁለት ወር በፊት አደጋ ደርሶበት ህክምና አድርጐ ህመሙ ስላገረሸበት ቀዶ ህክምና ተሰርቶለት በወጣው ታካሚ አልጋ የተተካው አስታማሚ ደግሞ ጉሉኮስ፣ ማስታገሻ እና ሌሎች የተለያዩ መድኃኒቶች ሲታዘዙለት፣ “አይ ወይኔ የባለፈው አንድ ካርቱን መድኃኒት እኮ እቤት ነው ያለው” በማለት ስትቆጭ ሰማኋት።

“ብዙ መድኃኒት ነው ያለው? እንዴት ሊተርፍ ቻለ?” አልኳት::

“ኧረዲያ! መድኃኒት በላይ በላይ ነው የሚያዙት፤ የሚጠቀምበትን ተጠቀመ የተረፈውን ደግሞ ወደ ቤቴ ይዠው ሄድኩና አስቀመጥኩት” አለችኝ::

“ግን ከዚህ እንዴት ማውጣት ቻልሽ? ጥበቃ ላይ አልጠየቁሽም?”

“ከእቃዎቼ ጋር አብሬ ስለያዝኩት አልጠየቁኝም” በማለት መለሰችልኝ::

አስቡት እስኪ ምን ያህል መድኃኒት ያለአግባብ ጥቅም ላይ እንደሚውልና ብክነት እንደሚፈጠር:: እነዚህን እንደምሳሌ ያቀረብኩላችሁ ሁለት ሰዎች መድኃኒቱን ወደ ቤታቸው ወስደው ያስቀምጡታል:: ምክንያቱም ከቤት ያለን መድኃኒት ማንም ስለማይገዛው:: በውድ የዶላር ምንዛሬ የሚገቡ መድኃኒቶች እንደዚህ በየሥርቻውና በየቤቱ ጥቅም ላይ ሳይውሉ ሲቀሩ በጣሙን አመመኝ::

እነዚያ መድኃኒቶች በአግባቡ ብንጠቀማቸው ኖሮ የስንቱን ህይወት በታደግንበት ነበር:: ከማስታምምበት ክፍል ወጣ ብዬ ሌሎች ታካሚዎችን ስቃኝ በአጋጣሚ አንድ የማውቃት ታካሚ አልጋ ላይ ሳያት ከአጠገቧ ወንበር ስቤ ተቀመጥኩ እና መጫወት ጀመርን:: በዚህ ጊዜ ከእሷ ጐን የተኛው ታካሚ ህክምናውን ጨርሶ ሊወጣ ነበርና የተረፈውን መድኃኒት ለአንች ይጠቅም ይሆናል በማለት ብዙ መድኃኒቶች ሰጣት::

መድኃኒት ከግቢው ካልወጣ ለተገቢው ዓላማ መዋሉ አይቀርም እና ጥሩ መረዳዳት ነው በማለት ገለፅሁላቸው።

“እሱማ ጥሩ ነበር:: ነገር ግን መድኃኒት ሲተርፍሽ የህክምና ባለሙያዎቹ ካዩ እነሱ ይወስዱታል:: አሁንም ቢሆን ቶሎ ብዬ ስለተቀበልኩት ነው እንጂ መጥተው መጠየቃቸው አይቀርም:: ከዚህ በፊት እዚህ የነበረ ታካሚ ሲወጣ በሙሉ ሰጥቶኝ ስለነበር የህክምና ባለሙያው ሲጠይቀኝ ለእኔ ሰጥቶኛልና እኔ ነኝ የምጠቀምበት ብዬ አስቀረሁት::”

“ለመሆኑ እነሱ ወስደው ምንድን ነው የሚያደርጉት?” ጠየቅኋት።

ፈራ ተባ እያለች፣ “ታዲያ ጥቅም ካላገኙበት ለምን አምጭ አታምጭ ይታገሉኛል” በማለት መለሰችልኝ:: በዚህ ጊዜ የተወሰነ ደስታ ተሰማኝ:: ምክንያቱም ሌላው ቢቀር መድኃኒቱ ለተፈለገለት ዓላማ ውሏልና::

ይህን ሁሉ ስህተት እንዲሁ ማለፍ ስለማልፈልግ ችግሩን መጥቀስ ብቻ ሳይሆን መፍትሔውንም ማስቀመጥ እንዳለብኝ አምናለሁ። መድኃኒቶች እንዳይተርፉ በአግባቡ ማዘዝ፣ ካልሆነ ደግሞ መድኃኒቶች ሲተርፉ ወደ መድኃኒት ቤት እንዲመለሱና ለታካሚው ደግሞ ገንዘቡ የሚመለስበት የአሰራር ስልት ቢዘረጋ ታካሚውንም ሆነ በውድ ምንዛሬ የምናስገባቸውን መድኃኒቶቻችንንም መታደግ ይሆናልና ፈጣን የሆነ ምላሽ ቢሰጥ እላለሁ::

ሌላው በጣም ያስደነቀኝን ጉዳይ ላቅርብ:: ከዚህ በፊት የማህበረሠብ አቀፍ ጤና መድን ሲባል ምንም ጥቅም ያለው አይመስለኝም ነበር:: ነገር ግን ሁሉም ነገር ወደ ተግባር ሲመጣ ነውና ግልፅ የሚሆነው አንዱ አርሶ አደር ለቀዶ ጥገና የሚያገለግል ብዙ መድኃኒት ተሸክሞ ሲመጣ ሲያየው አንድ ተገልጋይ ለጓደኛው ጠጋ ብሎ፣ “ይህን ሁሉ መድኃኒት በነፃ እኮ ነው” አለው። በዚህ ጊዜ ጓደኛው ስላልገባው፣ “እንዴት?”

“እንዴት ማለት ጥሩ! እኔ ወደ አንድ ሺህ ብር የሚጠጋ ስከፍል እሱ ግን የጤና መድን አባል ስለሆነ በነፃ ተሸክሞት መጣ::”

እኔም ወሬያቸው ሳበኝና ተቀላቀልኳቸው:: በዚህ ጊዜ አንዱ አርሶ አደር “ለካ እንደዚህ ይጠቅማል? በአሁኑ ሰዓት እንደአንተ በመቶዎች የሚቆጠር ገንዘብ ቢጠየቅ ምን ይውጠው ነበር?” በማለት የራሱን ስሜት ገለፀ:: በዚህ ጊዜ አንደኛውን አርሶ አደር “አንተስ የጤና መድን ተጠቃሚ ነህ?” ብዬ ጠየቅሁት::

“አዎ! በእኛ አካባቢ እኮ አባል አለመሆን አትችይም፤ በአንድ ወቅት አንከፍልም ያሉት ግለሰቦች ታስረው ነበር:: ያኔ እኔ ለምን እንደዚህ ያደርጋሉ ብዬ እነሱን ወቅሻቸው ነበር:: እንደተመለስኩ ግን ይቅርታ ነው የምጠይቃቸው:: ምክንያቱም ሁሉም ነገር ለእኛ ጥቅም ነበርና::” ከዚያም ሲያዳምጠን የነበረው አንድ አስታማሚ “እኔም ይህን በማየቴ የጤና መድን አባል መሆንን ተመኘሁ” ብሎ የተሰማውን ገለፀልን::

አንዱን የጤና መድን ተጠቃሚ መስተንግዶው እንዴት እንደሆነ ስጠይቀው፣ “አንዳንዶቹ ከእኔ አይደለም፤ እዚያኛው ነው በማለት ያዋክቡናል እንጂ ጥሩ ነው” በማለት መለሰልኝ::

አሁን ደግሞ ወደ አስተዳደር ሠራተኞች ልውሰዳችሁ። ሥራቸው የቱንም ያህል ከባድና አስቸጋሪ ቢሆንም ሠራተኞቹ ግን ጥራትና ትህትና በተሞላበት ሁኔታ ሥራቸውን እያከናወኑ የሚገኙትን የተቋሙን የጽዳት ሠራተኞች ቆሜ ላጨበጭብላቸው እወዳለሁ::

የጥበቃ ሠራተኞችም ቢሆኑ መመስገን አለባቸው:: ምክንያቱም የተለያየ ባህሪና መልክ ካለው ሰው ጋር ነው ግንኙነታቸው::

በጥበቃዎች ላይ አንድ ያየሁትን ስተት ግን ልንገራችሁ:: ማታ ከሁለት ሰዓት በኋላ ጥበቃዎቹ ከአስታማሚ ውጭ ያሉትን በሙሉ አስወጥተው የግቢውን በር ይዘጋሉ:: በዚህ ጊዜ በሩ ላይ መኪና እየጠበቅሁ ነበርና የጥበቃዎችን ሁኔታ እመለከት ጀመር:: ሁለት ሴቶች፣ “አዳሪ ነን እንግባ” ሲሉት “የለም አትገቡም” አላቸው። “እባክህን ከውስጥ ያሉት አስታማሚዎች ሙሉን ቀን የዋሉ ስለሆነ እኛ መተካታችን ግድ ነው” በማለት ቆሙ::

በዚህ ጊዜ አንድ ሰው ከኋላችን መጥቶ ብዙም ሳይጠይቁት ገባ:: በቀጠልም እኛ እንደቆምን ሌሎች ሁለት ሰዎች ገቡ:: በዚህ ጊዜ መግባት የተከለከሉት ሰዎች፣ “ለምንድን ነው እኛን ከልክለህ ሌሎችን የምታስገባ? እኛም መግባት አለብን” ብለው በቁጣ ጠየቁ።

ከጥበቃዎች መካከል አንደኛው ጠጋ ብሎ፣ “እስኪ እባካችሁ ምንድን ነው ችግራችሁ?” ጠየቃቸው። ነገር ግን መፍትሔ ይሰጣቸዋል ብዬ ስጠባበቅ አትገቡም! አትገቡም! ብሏቸው አረፈው::

እናም ይህ በዘመድ አዝማድ ከምትሰሩትና በማን አለብኝነት ከምትፈጽሙት ተግባር ልትታረሙ ይገባል እላለሁ::

አንድ ፈገግ ያደረገኝን ነገር ልንገራችሁ:: ጥበቃዎች ከሁለት ሰዓት በኋላ ከአስታማሚ ውጭ ሌላ ሰው ስለማይፈቀድ እየዞሩ ከምኝታ ክፍል ያስወጣሉ። እንዲሁም ሌሊት ላይ በሚዞሩበት ጊዜ ሁለቱም ሰዎች ከታካሚ አልጋ ላይ ተኝተዋል:: በዚህ ጊዜ የጥበቃ ሠራተኛው ግራ ይጋባና ሁለቱንም በእጁ እየነካ፣ “የትኛው ነው ታካሚ ወይም አስታማሚ?” ሲል እኔንም ሌሎችንም ፈገግ አሰኘን:: አስታማሚውም ታካሚውነ ከማስታመም ይልቅ እንቅልፉን ለሽ ብሏል:: ይህ ድርጊት ታካሚውንም የሚረብሽ ነውና ከዚህ ድርጊታችን እንቆጠብ እላለሁ::

እመቤት አህመድ

በኩር ጋዜጣ የካቲት 19/2010 ዓ/ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.