አዲሱ የወያኔ ዘመቻ! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

በመጽሐፈ ገጽ (በፌስ ቡክ) ጓደኝነት ጥቂት የማልላቸው የኢትዮጵያዊነትን የሀገር የወገን የማንነት የቅርስ ተቆርቋሪነትን ስሜት የተላበሱ የሚያስቀናና የሚንቀለቀል ወኔ የተሞሉ እኅቶች ወንድሞች የመጽሐፈ ገጽ ጓደኝነት እየጠየቁኝ እየተቀበልኳቸው በተቻለኝ መጠንም እያበረታታሁ በጉድኝነታችንን እስከአሁን ቀጥለን ነበር፡፡ ለካ እነኝህ ኢትዮጵያዊነትን የተላበሱና ወኔ የተሞሉ ቁጭት የሚበላቸው እያልኩ የማወድሳቸውና የተቻለኝን ያህልም ሳበረታታቸው የነበሩ ወንድሞችና እኅቶች ወያኔዎች ያሁሉ ስሜትና ተቆርቋሪነታቸውም ጭንብል ወይም ሽፋን ኖሯል ለካ ሰሞኑን እነኝህ ሰዎች በዘመቻ በየአቅጣጫው “ከአሁን በኋላ አማራ ስለ ራሱ ብቻ ማሰብ ይኖርበታል፣ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያለ ስለራሱ ማሰብ ትቶ ለ80 ምናምን ብሔረሰብ ሁሉ ማሰብ ለድንበር መበላሸት አለመበላሸት ማሰብ የለበትም፣ አሁን 30 ምናምን ሚሊዬን አማራ ሕዝብ እስከ መኖሩም ለተዘነጋው በችግር በዘረኝነት በረሀብ በሥደት አለንጋ ለሚገረፈው የራሡ ቤተሰብ ብቻ ማሰብ መቻል አለበት፣ ሀገር ማንነት ምናምን እያለ የራሱን ህልውና አደጋ ላይ መጣል የለበትም” ከማለትም አልፈው ካርታ ሠርተው ጎንደር ጎጃም ወሎንና ሸዋን አካለው “መገንጠል ይኖርብናል” በማለት መገኝጠልን በማቀንቀን የምትገነጠለዋንም ሀገር “አማራ፣ ቤተ አማራ፣ አቢሲኒያ፣ ኢትዮጵያ፣ ግዮን” የሚሉ ስሞችን  ለምርጫ አቅርበዋል፡፡ ስለ ወደብ አገልግሎት ጥያቄ ሲመልሱም “እኛ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሀገር ድንበር ማንነት ምንትስ የሚለውን ትተን እራሳችንን ብቻ ካሰብን በራሳችን ጉዳይ ላይ ብቻ ካተኮርን ከሌሎች ጋር ሰላም ስለምንሆን የወደብ አገልግሎትን በጎንደር በኩል ከኤርትራ ማግኘት እንችላለን” ይላሉ፡፡ አንዳንድ ወገኖችንም ይሄ ሴራ የወያኔ መሆኑን ካለማወቅና የጨነቃቸው ወገኖች ያቀረቡት ሐሳብ መስሏቸው ለመደገፍ የዳዳቸው ሁሉ ነበሩ፡፡ ለአንደኛው ምን አልኩት፡-

ወንድሜ ምን ነካህ? ምን ሆንክ? ይሄ እኮ ተሸናፊነት ነው እጅ መስጠት እኮ ነው፡፡ እስኪ አሁን አንተን ከወያኔ ምን እንደሚለይህ ንገረኝ? ኢትዮጵያን ስለተውክ እንዴት ነው እራስህን ልታድን የምትችለው? ውጊያው እኮ አማራ ኢትዮጵያን እስኪተው እስኪጥል ማንነቱን ማለትም አማራነቱን እስኪክድ ድረስ ብቻ ሳይሆን ጨርሶ ዘሩ እስኪጠፋ ድረስ እኮ ነው፡፡ ምን ነው ሲበዛ የዋህ ሆንክብኝ? የትኛውንስ ክፍል ነው የምትገነጥለው? ወያኔ ከጎንደር ከጎጃም ከወሎ ውስጥ አገዎችን ቅማንቶችንና ሌሎች ወገኖችን እያነሣሣ ምን እንዲሉ እያደረገ እንደሆነ አታውቅም? ይሄ አስተሳሰብ የመጨረሻዎቹ የደናቁርቱ የድንቁርና የድንቁርና ብቻም ሳይሆን የጠላትነት አስተሳሰብ ነው የኢትዮጵያ ጠላት አስተሳሰብ፡፡ አንድነት ወይም የኢትዮጵያ ህልውና በምንም ተአምር ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለሱም እንደ እናት አባቶቻችን ሁሉ የማንከፍለው የመሥዋዕተነት ዓይነት ሊኖር አይገባም፡፡ የኢትዮጵያ ነፍስ ያለው በአንድነቷ ውስጥ ነው አንድነቷ ከፈረሰ በድን ትሆናለች ትሞታለች፡፡ ኢትዮጵያ ከሞተች በኋላ ደናቁርቱና የጠላት ቅጥረኞች ይመስላቸዋል እንጅ በየትኛውም የፈራረሰ አካሏ ላይ ሰው መኖር የሚችልበት ዕድልና ሁኔታ አይኖርም፡፡ ለኢትዮጵያ መፈራረስ ተባባሪ የሆነ ሰው የሚጠየቀው በታሪክ ፊት ብቻ ሳይሆን በቅዱስ ቃሉ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያለ ከ70 ጊዜያት በላይ በክብር በፍቅር በሞገስ በሚጠራት በእግዚአብሔር ፊትም ነው፡፡ ለኢትዮጵያ (ለእግዚአብሔር ሀገር) ጠላት መሆን ያስኮንናልና ተጠንቀቅ፡፡  አልኩት፡፡

ብቻ ምን አለፋቹህ በመጽሐፈ ገጽ ሰሞኑን እያያቹህት እንዳላቹህት ይህ ዘመቻ እንደኛ ናቸው ብለን እናስባቸው በነበሩ አሁን ግን ባልጠበቅነው መንገድ በራሳቸው ጊዜ ማንነታቸውን በገለጡት በወያኔ ካድሬዎች በሰፊው የተያዘ ዘመቻ ሆኗልና እንዳትሳሳቱ እንዳትሰናከሉ ማስጠንቀቅ እወዳለሁ፡፡ ይህ ዘዴ ወያኔ እስከዛሬ የያዘው የአማራን ብሔራዊና የባለአደራነት ስሜት ለማጥፋት የደከመው ድካም በፈለገው ፍጥነትና መጠን ውጤት እንዳላመጣለትና ብዙም ውጤታማ እንደማያደርገው ካወቀ በኋላ አዲስ የቀየሰው ስልት ነው፡፡ ነገር ግን በእኔ እምነት ይሄ የወያኔ አዲሱ የኢትዮጵያዊነትንና የባለአደራነትን ስሜት ከአማራ የማጥፋትና ሀገሪቱን ባለቤት ባለአደራ ተቆርቋሪ የማሳጣት እኩይና ሰይጣናዊ ዘመቻ እንደቀደመውና ሲሠራበት እንደቆየው ዘመቻው ሁሉ ይከሽፋል እንጅ ይሠራለታል ብየ አላስብም፡፡ ወያኔ የኢትዮጵያዊነትን ስሜት ከሌሎቹ ብሔረሰቦች በተሳካ መልኩ አጥፍቻለሁ ብሎ ያስባል የቀረኝና ያቃተኝ አማራ ብቻ ነው ብሎ ያስባል፡፡ መስሎት እንጅ የኢትዮጵያዊነትን ስሜት ከኢትዮጵያዊያን አጠፋለሁ ማለት ቅዠት ነው፡፡ ከደሙ ጋር ተቀላቅሎ ያለ ነውና፡፡

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.