ራሱን ኮማንድ ፖስት ብሎ የሚጠራው ክፍል በኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት ላይ የሚወስደውን እርምጃ ቀጥሎበታል

(ኢሳት ዜና የካቲት 22 ቀን 2010 ዓ/ም)የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን በማድረግ ኮማንድ ፖስት የተባለው ቡድን ተቃውሞ በነበረባቸው የኦሮምያ ክልል አካባቢዎች የሚወስደውን እርምጃ ቀጥሎበታል።
ትናንት የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ በኮማንድ ፖስት አባላት ከታሰሩ በሁዋላ ዛሬ ደግሞ ምክትል ከንቲባው ተይዘው መታሰራቸው ታውቋል። ሁለቱም ባለስልጣናት ቄሮ እየተባለ ከሚጠራው የወጣቶች ስብስብ ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል መያዛቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የፓርላማ አባላት በነገው እለት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዙሪያ ውሳኔ ያሳልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። አዋጁ ተግባራዊ ከሆነ ሁለተኛ ሳምንቱን የያዘ ሲሆን፣ ፓርላማው ከዕረፍት ተጠርቶ ድምጽ እንዲሰጥበት ይደረጋል።
የፓርላማ አባላቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንያዳያጸድቁ ግፊት እየተደረገባቸው ነው በማለት ራሱን የኮማንድ ፖስት ሰክሬታሪያት ብሎ የሚጠራው ቡድን ማስጠንቀቂያ አስተላልፎ ነበር። በሌላ በኩል ግን የኮማንድ ፖስት አባላትና የደህንነት ሰዎች ለፓርላማ አባላቱ ስልክ እየደወሉ አዋጁን እንዲያጸድቁት እያስጠነቀቁ ነው።
በኢህአዴግ ድርጅቶች አኳያ እስካሁን ያለው አቋም በግልጽ አልታወቀም። አዋጁ በብዛት የኦሮምያና አማራ ክልሎችን ኢላማ አድርጎ የወጣ እንደሆነ እየተነገረ ነው።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከጸደቀ በኦሮምያ ያለውን ተቃውሞ ያባብሰዋል ተብሎ ተፈርቷል።
በአዋጁ መሰረት ጸጥታን አስመልክቶ የክልል ባለስልጣናት መግለጫ መስጠት አይችሉም። ይሁን እንጅ የኦሮምያ ክልል የህዝብ ግንኙት ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በነቀምቴ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ በመጻፍ መረጃ በመስጠት የመጀመሪው ባለስልጣን ሆነዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.