ወጣት ሆይ! እደግ! ተመንደግ! ማራ እንደ ድኩላ የታደነባቸው (በላይነህ አባተ)

በላይነህ አባተ  (abatebelai@yahoo.com)

መልካም ነገር ካየንና ስለ መልካም ነገር ከጻፍን ሩብ ክፍለ ዘመን አልፎናል፡፡ ዛሬ ግን ለጅብ የሰጠነው ይህ ትውልድ በጥረቱ ጭንቅላቱን አስልቶ፣ አንገቱን አቅንቶና ክንዱን አፈርጥሞ ታሪኩንና ባህሉን ከሚደርስበት ጥፋት ተከላክሎ ወደነበረበት ለመመለስ እሚያደርገው ጥረት በሐዘን መሐል ደስታ ያጽፋል፡፡

በበደኖው የዘር ማጥራት ዘመቻ ባለቤታቸው ገደል ተወርውረው፤ አስራ ሶስት ልጆቻቸው ተበትነው ከአምሳ በላይ “ወታደሮች” በየተራ ደፍረዋቸው ከማህጸናቸው መግል ሲፈሳቸው ያየኋቸው የአምሳ አመት እድሜ እናት እስከ ህይወቴ ፍፃሜ እንዳሳዘኑኝ ይኖራሉ፡፡ አማራ እንደ ድኩላ የታደነባቸው ወልቃይትና ራያ፣ በሬሳ የተሸፈነው ጋንቤላ፣ የወንድሙን አስከሬን እንዲጎትት የተገደደበት ኦጋዴን፣ እናት ከገደሉት ልጇ ሬሳ እንድትቀመጥ የታዘዘችበት ወለጋ፣ ኦሮሞና አማራ በጅምላ የተጨፈጨፉባቸው ከተሞች፣ አማሮች የአርበኛ አያቶቻቸው አጥንት በተከሰከሰበት ስደተኛ የሆኑበት ጉራፈርዳና መተከል እንደዚሁም ዜጎች የታረዱባቸው ሌሎች አካባቢዎች በሐዘን ነክረውኝ ይኖራሉ፡፡ በሌላ በኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጣቶች በእቅድ እንዲሞቱ የተደረጉትን የቅደመ አያቶቻቸውን ታሪክና ባህል ለማዳን የሚያድርጓቸው እንቅስቃሴዎች የደስታን ጮራ በልቤ ይፈነጥቃሉ፡፡

ከባህሉ የወጣ ሕዝብ ከባህር የወጣ ዓሳ ነው፡፡ ከባህሉ የወጣ ሕዝብ ከባህር የወጣ አሳ መሆኑን የረሳው እስከ እኔ ድረስ ያለው አብዛኛው ተማርኩ ባይ ትውልድ ከባህሉ መውጣት ከጀመረ ከአርባ አመታት በላይ ሆኖታል፡፡ የጀግኖች መፍለቂያ የጎበዝ አለቃ ባህላችንን በመጤ የጥበቃ ጓድ ተክቷል፡፡ መለኮታዊ ሽምግልናችንን በኤፍሬም ይሳቃዊ መጤ ንፍጣም ድርድር አጨማልቋል፡፡ በእግዚአብሔር ሚዛን የሚፈርዱ ካህኖቻችንን በወሮበላ ደፍተሮች ተክቷል፡፡ የእውነተኝነትና የታማኝነት ባህላችን በቅጥፈትና በክደት ባህል ተክቷል፡፡ በፍቅር የተሞላ ጉርብትናችንን በጥላቻ ድንበር አጥሯል፡፡ ስንት ጀግና ያፈለቀውን የዘፈን፣ የሽለላና የፉከራ ባህላችንን በፈረንጅ ሙዚቃና ዳንኪራ አድቅቋል፡፡

ይህ እድሜውን እየጠገበ ያለ ትውልድ እስክስታ መውረድ፣ ማቅራራት፣ መፎግላትና መፎከር የኋላቀርነት ምልክት ስለመሰለው ራሱን ለምዕራባውያን የባህል አስገዝቶ በተውሶ ዘፈንና ዳንኪራ ሲወላገድ ኖሯል፡፡ መሰልጠን በህሊና መገዛት መሆኑን ስቶ መሰልጠንን እንደ ፈረንጅ መልበስ፣ እንደ ፈርንጅ መናገር፣ እንደ ፈረንጅ መዝፈን፣ እንደ ፈረንጅ መደነስና እንደ ፈረንጅ ማምለክ አድርጎ ወስዶታል፡፡ ምዕራባውያን በአሕዛብነት እንደ አውሬ በሚኖሩበት ዘመን ኢትዮጵያ በህሊናው የተገዛ ስልጡን ሕዝብ አገር እንደነበረች ዘንግቶ እንደ ምዕራባውያን “ለመሰልጠን” ከኮሚኒዝምና ከካፒታልዚም ጋር ባህላቸውን እንደ መርዝ ሳያጣጥምም ሰርብቋል፡፡

ይህ የምዕራባውያንን መርዝ ሳያጣጥም የመሰርበቅ ባህሪውም አባቶቹ ከቆሙበት ክብር ሥሩ እንደተመነገለ ዛፍ ገንድሶ ጥሎታል፡፡ አባቶቹ ከቆሙበት ክብር ተገንድሶ ሲወድቅም ምዕራባውያን ለክብር፣ ለህሊናና ለይሉኝታ ባዕድ የሆነውን የትግሬ ነፃ አውጪ እንደ ምሳር በእጅ አንስተው ከትክተውታል፡፡ የራሱን ባህል ብልኮ አውልቆ የሌላውን የባህል ጀርሲ የለበሰ እጣፋንታው እንደ በሰበሰ ዛፍ መከትከት መሆኑን ከዚህ በላይ ምን ያሳያል?

በምዕራባውያን ርዕዮተ ዓለምና ባህል መርዝ አባቶቻችን ከቆሙበት ክብር ሥሩ እንደተመነገለ ዛፍ በተገነደስነው በእኛ አፍሮ ለግላጋው ትውልድ በቅድመ አያቶቹ እየተጠራ ይገኛል፡፡ እኛ ከወደቅንበት ትቢያ ተነስቶ ከቅደመ አያቶቹ ማማ ለመውጣት መፍትሔው የቅደመ አያቶቹን ፈለግ መከተል እንደሆነ ተገንዝቧል፡፡ ይህንን መፍትሔ ስላወቀም የቅደመ አያቶቹን ታሪክ እንደ ቅርስ ተመራማሪ በመቆፈር ላይ ይገኛል፡፡ ቅደመ አያቶቹን በጀግንነት መንፈስ ያጠመቃቸው ባህላቸው መሆኑን ተረድቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ይህ ለግላጋ ትውልድ እኛ ማፈሪያዎች እንደ ዛር የጣልነውን የጀግና ምንጭ ባህል እንደ ታቦት በክብር አንስቶ ከራሱ ለመስቀል ሲፋትር ይታያል፡፡

ይህ ቅደመ አያቶቹን አክባሪ ትውልድ የማህበረሰብ መሪውን እንደ ቅድመ አያቶቹ የጎበዝ አለቃ ማለት ጀምሯል፡፡ ይህ ለግላጋ ትውልድ እንደ እኛ ትውልድ በማያውቀውና በማይችልበት የማይክል ጃክሰን ዳንስ በሃያ አምስት ዚፖች በተጣበቀ ጃኬት ወይም እንደ አቦይ ገረመድን ወዳጅ ቦይንሲ እርቃኑን መወላገዱን ትቶ እንደ ቅድመ አያቶቹ በሸማና በጃኖ ተውቦ በአገሩ ዘፈንና ጭፈራ ያገሩን ውበት፣ ታሪኩንና ጀግኖቹን መዘከሩን ተያይዞታል፡፡ ይህ ትውልድ ቀረረቶና ፉከራን የትግሬ ነፃ አውጪ ከቀበርበት መቃብር አውጥቶ እንኳንስ በገጠር በከተማ ነፍስ ዘርቶበታል፡፡ ይህን ባህል መልሶም ከአያቶቹ ማማ ያደርሰዋል የሚል ተስፋ አሳድሯል፡

ከባህሩ የወጣ አሳ ወዲያው ወደ ባህር ሲገባ ነፍስ እንደሚቀጥለው ከቅደመ አያቶቹ ባህል ያወጣነው ይህ ትውልድም ባህላችን ጨርሶ ሳይጠፋ ወደ ቅደመ አያቶቹ ባህል ስለገባ እንደ ቅድመ አያቶቹ ተጀንኖ ከተራራ የመታየት እድል ይኖረዋል፡፡ ከባህላችን ወጥተን ለቅኝ አገዛዝ የዳረግነው ይህ ወጣት በባህሉ መዋኘት ሲቀጥል በዘፈኑ፣ በቀረርቶውና በፉከራው አንስቶ እማይጠግባቸውን ቅድመ አያቶቹን የመሳሰሉ ጀግኖች የመፍጠር ብቃት ያዳብራል፡፡

ታሪክን መርምሩ! የዚህ ትውልድ ቅድመ አያቶች ባህል ጀግና እንደ ፊደል ይዘራል፣እንደ እሸት ያፈራል፡፡ የዚህ ትውልድ ቅደመ አያቶች ባህል እንደ አቡነ ጴጥሮስ፣ አቡነ ሚካኤል፣ አባ ገብረየሱስ፣ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ፣ መላከ ሰላም አለማየሁ ሻሾ የመሳሰሉ ብቁ የሃይማኖት አባቶች ያወጣል፡፡ የዚህ ትውልድ ቅድመ አያቶች ባህል የመለኮትን ፍርድ የሚፈርዱ ሀዲስ አለማየሁን የመሳሰሉ ሽማግሌዎች ይፈጥራል፡፡

ይህ ትውልድ የቅድመ አያቶቹን ጀግና አፍላቂ ባህል ተጎናፅፎ እንደ ቅድመ አያቶቹ ተጀንኖና በዓለምም እሚገባውን ሥፍራ ይዞ የመኖር እድል ይኖረዋል፡፡ ይህ ትውልድ የባህሉ ስሌት የገባው ይመስለኛል፡፡ ስሌቱም ስለገባው በወኔ እየዘለለ ከባህሉ ባህር በመግባት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ትውልድ የቅድመ አያቶቹን ፈለግ ተከትሎ በባህሉ እየጎለበተ እንደ ቅድመ አያቶቹ አገሩን የአገር አውራ አድርጎ በዓለም ተከብሮ ይኖራል፡፡

የምስራች! ይህ ትውልድ እኛ “ለመሰልጠን” የወረወርነውን ጃኖ አንስቶ ለብሷል፡፡ ይህ ትውልድ እኛ “ለመሰልጠን” ያቀነቀነውን የፈረንጅ ዜማ እንደ አተላ ደፍቶ ያገሩን ጣዕመ ዜማ አንቆርቁራል፡፡ ይህ ወጣት እኛ “ለመሰልጠን” በኋላቀርነት የተሳለቅንበትን ቀረርቶና ፉከራ እርሱ ኮርቶበት አራዳ ጊዮርጊስ ሳይቀር ተፎግሎበታል፡፡ ይህ ወጣት እኛ “ለመሰልጠን” የተደፈቅንበትን የፈረንጅ ባህል ተጠይፎ በቅደመ አያቶቹ ባህል እንደ አሳ መዋኘት ጀምሯል፡፡

ይህ ወጣት ያስደስታል፤ እደግ ተመንደግም ያሰኛል፡፡ ወጣት ሆይ! እደግ! ተመንደግ!

የካቲት ሁለት ሺ አሥር ዓ.ም.

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.