በመንሰራፋት ላይ የሚገኘው የዘር መድልዎ በኢትዮጵያ፡- የውስጥ ቅኝ አገዛዝና በክልል ደረጃ ያለው የተዛቡ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ  ተጽእኖዎቹ 

ግርማ ብርሃኑ. Girma Berhanu
በትምህርት መምሪያ የልዩ ትምህርት ክፍል (ፕሮፌሰር)
Department of Education and Special Education (Professor)
ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ. University of Gothenburg
መ.ሣ.ቁ. Box 300
ጎተበርግ ስዊድን. Göteborg, Sweden
E-mail: Girma.Berhanu@ped.gu.se

(1)          መግቢያ

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች ቢባል ማጋነን አይሆን። ሃገሪቷ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በተከታታይ ሁኔታ በተቃውሞዎችና ግጭቶች እየታመሰች ነው። ።አጠቃላይ የህብረተሰቡ መነሳሳትና ብሶት የሚያመለክተን ኢትዮጵያን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ጨቋኝ ጥምር መንግስት ማለትም ከአነስተኛው የትግራይ ክልል በመጣው ህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ(ህወሃት) የበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኢሀአዴግ)[1] ባለፉት ዓመታት ብሄሮችን በማግለሉ የተፈጠረ የተስፋ ማጣት ድምር ውጤት ነው። አጠቃላዩ ህዝብ በተለይም አማራዎችና ኦሮሞዎች ከሃገሪቷ የፖለቲካ ሂደትና ኢኮኖሚ ልማት በወሳኝ ሁኔታ እንዲገለሉ ተደርጓል። በአሁኑ ጊዜ የሚታየው ግጭትና በስፋት እየተካሄዱ ያሉት ሰላማዊ ሰልፎች የብዙ ሰው ህይወት የተቀጠፈባቸው፣ በመላ ሃገሪቷ የሸቀጣሸቀጦችና አገልግሎቶች እንቅስቃሴዎች የተገቱበት፣ በዚህም በክልሎች አንገብጋቢ የሆኑት መዋቅራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ኢፍትሃዊነት የተጋለጠበት ሁኔታ ነው። በ1991 ኤ.አ በመሣሪያ ሃይል መንግሥት ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ በህወሃት ቁጥጥር ስር የወደቀው ሥርዓት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የሥልጣን ሞኖፖሊዎችን በማደራጀት በሌሎች ብሔሮች ላይ ጫናውን አሳርፏል። በህወሃት በኩል የፖለቲካ ሥልጣንና ሃብትን ለማጋራት ያለው እምቢተኝነት በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ቁጣን የፈጠሩ የተቃውሞ ሰልፎች እያስነሳ ነው።(Ethiopia at an Ominous Crossroads, Jan. 02, 2018)[2]  በአብዛናዎቹ የ2017 ወራቶች ባለማቋረጥ የተካሄዱት የፖለቲካ ተቃውሞዎችና ግጭቶች መላ ኢትዮጵያን በማጥለቅለቅ በመንግስት አገዛዝ አቋም ላይ የተፈጠረውን ከፍተኛ ሥጋት እየጨመረ ነው። በገዢው ፓርቲ ውሰጥም ያለው የሥልጣን ትግልም ተጧጥፏል። ሁለቱ ፣ ማለትም በገዢው ፓርቲ ውስጥ እንዲሁም በገዢው ፓርቲ አባል ድርጅቶች መካከል የተጠናከረና ጭንቀት የተጠናወተው የሥልጣን ትግልና ሃገሪቷን ያዳረሱ ተቃውሞዎች በሥርዓቱ ህልውና ላይ ሥጋት ፈጥረዋል። መንግሥት በተለይ በአማራና ኦሮሞዎች ተቃውሞዎች ጥምረት ምክንያት የአስተዳደር ቁጥጥር በማጣቱ ከፍተኛ ሥጋት አድሮበታል። በተጨማሪም አለመረጋጋቱና ተቃውሞዎቹ ብዙሃኑን መሠረት ያደረጉ፣ ሥር የሰደዱና ከዚህም ሌላ የፖለቲካ አድማሱም በፍጥነት አየተስፋፋ መምጣቱ በሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ሥጋትን አሳድረዋል። እንደምዕራባውያን ታዛቢዎች ሁኔታው ትኩረት ካላገኘ ካለፈው በፍጥነት እየተባባሰ የሚቀጥል ነው። ይህም በሰሞኖቹ ተከታታይ ክስተቶች እንደታየው መንግሥት ተቃውሞዎቹን ለማንኮታኮት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎችን ማሰሩን ከማመኑም በተጨማሪ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ለመፍታትና የእስረኞች ማሰቃያና በአስከፊነቱ የታወቀውን እስርቤት ለመዝጋት ዕቅድ እንዳለው ገልጾአል። በዚህም፤ “ብሔራዊ ዕርቅን በማራመድ ዴሞክራሲያዊ መድረኩን ለማስፋት” ጥረት አደርጋለሁ ብሏል። ይህ እንግዲህ ገና የሚታይ ነው የሚሆነው። እነማን እንደሚፈቱ ወይም መቼ እንደሚከናወን አስከ አሁን ግልጽ የሆነ ነገር የለም[3]።  ይህ ጽሁፍ በተዘጋጀበት ጊዜ ( Jan. 8/2018) የፖለቲካ እስረኞች የሚባሉት የትኞቹ እንደሆኑም ብዥታ አለ። የመንግሥት አካሄድ እርስ በርሱ የሚጣረስ፣ አዳፋ ማደናገሪያዎችና ተንኮል አዘል ድርጊቶችና በተጭበረበሩ የፖለቲካና የመንግስት ጉዳዮች የተሞላ ነው። መረጃው ያላቸው በርካታ ታዛቢዎች የመንግሥትን አድራጎትና እርምጃ አዝማሚያ  አደገኛና አሳሳቢ በማለት ይፈርጇቸዋል።

ይህን የአማርኛ ትርጉም ለመጨረስ በምዘጋጅበት ወቅት [March 12/2018]  የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች እነ ዶ/ር መረራና ሌሎችንም መፈታታቸውን አንባቢያን እንዲያስተዉልልኝ አስገነዝባለሁ።

የሥርዓቱ ባህሪ መገለጫ በውስጥ ቅኝ አገዛዝ[4] የሚፈረጅ የዘር መድልዎ አገዛዝ  ሊሆን ይችላል። የውስጥ ቅኝ አገዛዝ[5] ንድፈ ሃሳብ  በአንድ ማህበረሰብ ሁሉም የኑሮ ዘርፎች ውስጥ የውጪ ገዢ ሃይል ሳይኖር ያልተቋረጠና የተንሰራፋ አድልዎና ጫና እንዴት እንደሚዘረጋ ያስረዳል። በዚህ ጉዳይ የውስጥ ቅኝ ግዛቱ ትግራይን ሳይጨምር የተቀረው ኢትዮጵያ ሆኖ ከአገዛዙ ጋር ቅርብ ትስስር ላላቸው አካባቢዎች፣ ደጋፊዎችና ገዢዎቹ እንወክላቸዋለን ለሚሏቸው የዘር/ብሄር/ብሔረሰብ/ጎሳ ምርጫ ክልሎች ጠቀሜታ ያለው ሃብት ያቀርባል። ይህ እንግዲህ በሃገር ውስጥ የበቀለ የቅኝ አገዛዝ ዓይነት መሆኑ ነው። የውስጥ ቅኝ አገዛዝ ንድፈ ሃሳብ በራሳችን ዘር/ጎሳ በማህበረሰብ ውስጥ እንዴት ጫና እንደሚፈጥር የሚያመለክት ነው። በመሆኑም “የውስጥ ቅኝ ግዛቶች  ̋ ማለትም በሃገር ውስጥ ያሉ ክልሎች በራሳቸው የአስተዳደር አመራሮች ወይም ዋና ገዢዎች  ተላልፈው በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ይደረጋል። የተለያዩ የዘርና ጎሳ ወገኖች በህብረተሰቡ ውስጥ የበላይነት ባለው ክፍል ማለትም በህወሃት ተገደው  ለተለያዩ ጭቆናዎች ተጋልጠዋል። (Howe, 2002[6]; Wolpe, 1975[7]). በሌላ አነጋገር የዘር ማበላለጥን/ማዳላትን እንደ ግለሰብ ድርጊት ወይም ኩነት አድርጎ ከመውሰድ ይልቅ ጠለቅ ብሎ በህብረተሰቡ ውስጥ ሥር እንዲሰድ የተደረገና በሃገር ውስጥ የበቀለ የዘር መድልዎ መሆኑን መገንዘብ ያሻል። ከውጪ የመጣ ሂደት አይደለም። ፓርታ ቻተርጂ  (Partha Chatterjee) እንደሚለው ቅኝ ግዛቶቹ በ  ̋ልዩነት አገዛዝ  ̋[8] የሚተዳደሩ ናቸው። አንዳንድ የንደፈ ሃሳቡ ሰዎች እንደሚገልጹት ይህ ልዩነት ከብቸኛ የኢኮኖሚ ብዝበዛም የላቀ ነው። ይልቁኑም ቅኝ ግዛቶቹ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ባህል፣ ጾታና ሃይማኖትን ጨምሮ[9] የብዙ ርስቶች ፈርጀ ብዙ ብዝበዛዊ መዋቅር መገኛ/ቦታ ናቸው። በአሁኗ ኢትዮጵያ ይህንን ገለጻ የሚያረጋግጡ ከፍተኛ መጠን ያላቸው መረጃዎች ይገኛሉ። በዚህ ጽሁፍ እኔ በጽንሰ ሃሳቦች ንድፈ ሃሳባዊነት ላይ በምርምር ጠለቅ ብዬ አልገባም፤ ሰፋ ያለ የምርምር ጽሁፍ በቅርቡ ዝግጁ ይሆናል። እዚህ ላይ የኔ ፍላጎት ተለቅ ባለ ህትመት የተካተቱ ሃሳቦቼን ለማጋራት ነው።

ይህ ልዩ ህትመት ያነጣጠረው ወይም መንስዔ የሆነው ጉዳይ የኢንፎርሜሽን መረብ የመረጃ  ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) [10] ዳይሬክተር የሆነዉ ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ  በቅርቡ ዕብሪት በተመላበት ሁኔታ የትግራይ ብሔርን  ̋ ተፈጥሯዊ ችሎታ ” አስመልክቶ በተናገረው ላይ ነው።  የሱ ቃለ ምልልስ አፋጣኝ ትንተና ንባብ የሚሳየን ግልጽ የዘር የበላይነትን ጥረቃን (ትረካን) ነው።  በሱ ዕምነት

ትግራዮች ጠንካራ ሠራተኞች ናቸው፤ ሥነምግባር አላቸው፤ ጥሩ ጠባይ አላቸው፤ ስሜታቸውን በመቆጣጠር የታደሉ ናቸው፤ የአስተዳደር ብቃቱ አላቸው፤ የመሪነት ክህሎት አላቸው፤ ችግሮችን ተቋቁመው ተግቶ የመስራትና ፅናት አላቸው፤ የትግራይ ህዝብ ለሰው ክብርና ተገቢ ቦታ የላቀ የግብረገብነት እሴት አለው፤ እርምጃዎቻቸውና ድርጊታቸው በዕውቀት፣ በሃቅና በሳይንስ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፤ እንደ ሰው ሃይል በነሱ ላይ ለሚፈስ መዋዕለንዋይ የበለጠ ተጠቃሚነት የሚያስገኝ ተወዳዳሪ ናቸው፤ ትግራዮች እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል በተፈጥሮ ሃብት የታደሉ ስላልሆነ ልጆቻቸውን በቴክኖሎጂና በሌሎችም ተመራጭ ዘርፎች ማስተማር ይፈልጋሉ። የትግራይ ክልል የታሪክ ቅርስና ሥልጣኔ ምንጭ ነዉ። [11]

 

ጀነራሉ በመቀጠልም  ከላይ ባነሳው ሃሳብና ርዕዮት ላይ ብዙ የሚዘገንኑ ነጥቦችን አስቀምጧል። ቃለምልልሱ የዘር/ጎጥ ከፋፋይነት፣ ይህም እንዴት ሊሆን እንደቻለና ሃገሪቷን በዘር የሥልጣን ተዋረድ የማስቀመጥ እንድምታ ያለው ነው። ዘርን ያማከለ ወይም በማንኛውም መልክ የጎሳና የተፈጥሮ ተቃርኖዎች ሃሳብ ስናቀርብ የታሪክ እርግጠኝነት ያሻል።

ዘር ወይም ጎሳ[12]  ከሥነ-ህይወታዊው ውጪ ታሪካዊና ማህበራዊ አወራረድ ባለው መሰረተ ሃሳብ የሚታይ ሆኖ ሳለ ፤ ጀነራሉ ግን ማህበራዊ ውጤትን ከተፈጥሮ መሠረት ልዩነቶች ጋር አያይዞ ለማብራራት የሚሞክር ያልበሰለ ወይም በቁንጽል ግንዛቤ የተመሰረተ፣ ግርድፍ አገላለጹም ለማለት የሚዳዳው ሰዎች ለምን በተለያየ መንገድ እንደሚንቀሳቀሱ፣ ቀልጣፋ/አዝጋሚ፣ ስኬታማ/የማይሳካላቸው የሚሆኑት በተፈጥሮ ባላቸዉ የአእምሮ ብቃት ነዉ የሚል «ውሸ,ት« ነዉ።  ሆኖም ሰዎች «ውሸቱን» ስለሚያምኑት  በገሃዳዊው ዓለም በህጋዊ፣ በባህላዊ፣ በፖሊቲካዊና ማህበራዊ የዘውትር አካሄድ ማዕቀፍ ይህ አስተሳሰብ መዋቅራዊ እንዲሆን ተደርጓል።

መሆኑም ከደቡብ እስከ ሰሜን ጫፍ ልዩነት የለውም፤ ሆነም ግን አንድ የጸጥታ መኮንን የኦሮሞ ወይም የአማራ ወይም የጋምቤላ ሰውን የሚመለከትበት መንገድ የተለያየ ሲሆን  ዘር ወይም ጎሳ የሚታይበት ፍርደገምድል አካሄድ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ገሃድ የወጣ ሃቅ መሆኑን የምንታዘበው ነው[13]። የጀነራሉ ጽሁፍ አዲስ አይደለም። አስፈላጊነቱ በሙሉ ወይም መሠረታዊ ምክንያቱ ሥልጣን ነው፤ በጦር መሣሪያ፣ በሚገኘዉ ስልጣን ወታደራዊ ሃይል፣ ሃብት ወይም በኢኮኖሚያዊ ሃብትና በተጨማሪም ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተቋማትን ሙሉ ሙሉ መቆጣጠር ነው[14]። ይህም ዘርን አንድ ከማድረግ ይልቅ የመከፋፈሉን ሁኔታ መጠቀሚያ የማድረግ ዓይነተኛ ማሳያ ነው[15]። ይህ የመጠቀሚያ ባህል ” የትግራዩን ልዩ ጥቅም ” የፈጠረና ” የነጭ ልዩ ጥቅም ” ከሚለው ጋር የሚመጣጠን ማለትም ” የነጮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ደረጃ ከፍ በማድረግ የዘር መድሎውን ለማጨንበል ” እንደተደረገዉ ነው (Delgado & Stefancic, 2001)[16]። እኔ ” የትግራይ ልዩ ተጠቃሚነት ” የሚለውን የምተረጉመው በተቋማዊ ቅንብር ትግራዮች ለፍተው ያላገኙትን ወይም የሌላቸውን ሃብት እንደ መስጠት ነው። ይህም የበላይነት ያለው ዘር አባል በመሆን ብቻ በገፍ የሚቀርቡ ማህበራዊ ብልጫዎችን፣ ጥቅሞችንና ክብሮችን የሚመለከት ነው። ህወሃትና ጋሻጃግሬዎቹ በያዙት የገዘፈ ሥልጣን በማህበረ ሰቡ ውስጥ አናሳ/ሆን ተብሎ የተዳከመ ሃይል ያላቸውን ክፍሎች  በመጫን አድሏዊ ሥርዓት መስርተዋል። ከጀነራሉ አገላለጽ[17] መረዳት እንደሚቻለው ይህ የአድሏዊነት ሥርዓት በማህበራዊ ሃይሎችና ፕሮፖጋንዳ/ውሸት አማካይነት መቆየትና መቀጠል ችሏል።  ኢትዮጵያ ውስጥም በስልጣን ኮሪደሮች/በይፋ ያልወጡ የውስጥ ሃይሎች ተመሳሳይ አስተያየቶች እየተደመጡ ከመሆኑም ሌላ በተጨባጭም የዕለት ተዕለት ጉዳይ መሆኑ ተስተውሏል። ይህም ማለት የተለያዩ የዘር ክፍሎች በሥልጣን፣ በሃብት፣ በክብርና በሚገባቸው ቦታ እኩል አይደሉም። በመሆኑም የዚህ ጽሁፍ አላማ በከፊል የዘር/ብሔር ተዋረድን አፈታሪክ እውነቱን ማውጣት ነው። ይህንን የዘር የበላይነትንና የባህል የበላይነት ዕምነት ውጤቱን ርዕዮተዓለማዊ/የአስተሳሰብ አፈታሪክ በተቆርቋሪነት በታትኖ ማየት አስፈላጊ ነው። በዘረኛ ርዕዮተዓለሞች አዝማችነት የሁቱና ቱትሲ መከፋፈልና የተጨናበረው የሩዋንዳ ታሪክ፣ አውሮፓውያን ሆን ብለው የፈጠሩት የዘር ክፍፍልና መጨረሻውም ሩዋንዳውን ወደ ዘር ማጥፋት የመራውን አስከፊ ሂደት ሁላችንም የምናውቀው ነው። የጀነራሉ ባህላዊ መልዕክት ግልጽና ሆን ተብሎ ትግራይ ያልሆነውን የኢትዮጵያ ተስፋ ወጣት ለመጉዳት የተቀነባበረ ነው (Crane, 1994)[18]። ክሬን /Crane/ አድናቆትን በተቸረው ጽሁፉ ባበረከተው ዝርዝርና አሳማኝ መከራከሪያ እንዳጠቃለለው  ̋….በዘሮች መካከል በአዕምራዊ ችሎታ/ሥነ-ባሕሪ/ ልዩነት አለመኖሩን አስመልክቶ ፍንጭ ወይም መርትኦ አለመገኘቱ ሊደንቀን አይገባም። ዘር (ስንል) በመሠረቱ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ትርጉም ያለው ጽንሰ ሃሳብ ነው። አንድ የተወሰነ ዘር ከሌሎቹ ዘሮች በሥነ-ህይወታዊው( biological) አመዳደብ ለማስቀመጥ በሥነ-ባህሪ በበቂ ሁኔታ አንድ ዓይነት እና በሥነ-ባህሪ በበቂ ሁኔታ የተለያየ ስለመሆኑ በማናቸውም መንገድ ግልጽ አይደለም  ̋ Gould (1996, p. 399)[19]። በተመሳሳይ ሁኔታ ጉልድ/Gould/  በትክክል እንዳስቀመጠው ስለሰው ልጅ ተፈጥሮና ብዛሃነት/diversity/ ትርጉም/ምንነት ንድፈ ሃሳባዊ/theoretical/ ፣ ጽንሰ ሃሳባዊና/conceptual/ ልዩ መገለጫዎችን በተመለከተ የሚመነዠኩ አስገራሚ አመለካከቶችን አጥብቆ ለማሰብ ብዙ ዓመታት ያስፈልጉናል። ያለመታደል ሆኖ ጀነራሉና የገዢው ሥርዓት ቁንጮዎች ይህንን ሣይንስ የመሰከረላቸውን ሃቆች ዘንግተዋል/አላወቋቸውም፤ በጥበብ/ማህበራዊ ሣይንስ ዓለም የተቃኙ አይደሉምና።

 

(2) ርዕሰ-ምሉዕ ትንቢት (ሲነገር ባይመስልም በራሱ ጊዜ ስለሚፈጸም ትንቢት) ና የማቴዎስ ትንቢት ውጤት (A Self-Fulfilling Prophesy and the So-Called Matthew Effect

 

ያላቸው/የታደሉት በብዙ መንገዶችና መሥኮች የተሻለ ለመስራትና የበለጠ ለማደግ ዕድል እንዳላቸው ግልጽ ነው።  የማቲዎስ ውጤት እየተባለ የሚጠራው እዚህ ላይ አስፈላጊ ነው። ግላድዌል (Gladwell, 2008)[20] በቅርብ ባወጣው መጽሃፍ ሰዎች እንደው ዝም ብሎ ሊሳካላቸው አይችልም በሚል ያስረዳል። እስከ ሚጠበቀው ደረጃ የሚያደርሱ የእገዛ መሥመሮች ማህበራዊ ውርሶች፣ ቤተሰባዊ ትስስርና ሌሎች በርካታ ዳራዊ (background) ጭብጦችን ጨምሮ ወሳኝ ሚናዎችን ይጫወታሉ። መረጣ፣ በፈርጅ ፈርጁ ማስቀመጥና የተለዩ ልምዶች በተጨማሪ አስፈላጊ ናቸው። ለዚህም ምርጥ ምሳሌ  መሆን የሚችሉት የካናዳ የገና ተጫዋቾች ልምድ ነው።

 

የህብረተሰብ ጥናት ምሁሩ ሮበርት ሜርተን (Robert Merton) በአድናቆት ለሚጠራው ርዕሰ-ምሉዕ ትንቢት ካናዳውያን የገና ቡድን ተጫዋቾችን የሚመለምሉበት አሰራር በምርጥ ምሳሌነቱ ተጠቃሽ ነው፤ ይህም ማለት  ከጅምሩ ለራስ ግምት የሚሰጥበት ሁኔታ አዲስ አካሄድ በማስከተል አስቀድሞ ከነበረ የተሳሳተ ግንዛቤ ይልቅ እውነትነቱን ያወጣል። ካናዳውያን ምልመላ ሲጀምሩ የ9 እና የ10 ዓመት የገና ተጫዋቾች ምርጥ መሆናቸውን ባለመገመት በየዓመቱ የሚመርጡት አንጋፋዎቹን ተጫዋቾችን ነው። ነገርግን ሁሉንም ኮከብ ተጫዋቾች የሚያስተናግዱበት ሁኔታ ከጅምሩ የነበራቸውን የተሳሳተ ውሳኔ ትክክለኛ ያስመስለዋል። ሜርተን እንዳስቀመጠው “ይህ ዕውነት መሳይ የርዕሰ-ምሉእ ትንቢት ማረጋገጫ ስህተትን በማስከተል ተንባዩ ከጅምሩ አንስቶ ትክክለኛ መሆኑን ለመግለጽ ከመነሻው የነበሩ ሁኔታዎችን በማመሳከሪያነት ያጣቅሳል”። (Gladwell, 2008, p. 33).

 

ይህ በቡድን (ለምሳሌ የዘርና ጾታ ቡድኖች) እና በሀገር ደረጃዎችም ዕውትነት አለው ። የሥነ-ልቦና አዋቂዎች “በድግግሞሽ ማስፈራራት”(stereo type threat) ብለው የሚጠሩት ክስተት ለዚህ  ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። የተወሰነ ቡድን የተገለሉ አባላት ድግግሞሾቹ በውስጣቸው በመኖሩ ምክንያት በከፊል ከሌሎች ወደ ኋላ ይቀራሉ። አንድ አንድ በቁጥር አናሳ ወገኖች በትምህርትና በሌሎች ዝግጅቶች ጥሩ አይደለንም ብለው ስለሚያስቡ ብቻ ለጥሩ ውጤት አይሰሩም። አሉታዊ ግምታቸው ጭንቀት በመፍጠር የማወቅ ችሎታቸው ውስጥ ጣልቃ ይገባል። በምዕራብ ሃገሮች ጥቁሮች ብቻ አይደሉም ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች እንዲሁም አረጋውያን የበታችነት ስሜትን አምነዉ በመቀበል የራሳቸው ዝቅተኛ ግምት ሰለባ ይሆናሉ (Time, 2009, June 1)[21]። ያለመታደል ሆኖ  የዚህ በጎ ያልሆኑ ሁኔታዎችና ምስቅልቅል ምልክቶችም በኢትዮጵያ ውስጥ ተስተውለዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በ2015 ባደረግኩዋቸው የተወሰኑ ጉብኝቶች እነዚህን ጥያቄዎች ከተራው ህዝብ ጋር በማንሳትና እኔም እንደታዘብኩት አብዛኛዎቹ በኑሯቸው እርካታ እንደማይሰማቸው ወይም ደስተኞች አለመሆናቸውን፣ የዚህን ጠለቅ ያለና የከፋ ችግር ክብደትና ሥርዓት-ወለድ ባህሪ ባለመረዳታቸው ያሉበትን ሁኔታ መቀየር አለመቻላቸው ይሰማቸዋል። ይህ በመንግስት ሆን ተብሎ የተቀነባበረ የጭንቅላት (intellectual) ጅምላ ጭፍጨፋ ነው። እነዚህ ረቀቅ ያሉ አካሄዶች  ሰዎች ለራሳቸው ዝቅተኛ ግምት እንዲሰጡ የሚያደርጉ አጥፊ ዘዴዎች ናቸው።

 

ለሁለት አሰርት ዓመታት ያህል ወይም ከዚያ በላይ በልዩ ትምህርት መሥኮች የፍትሃዊነት ጉዳዮችን አስመልክቶ የሃሳብ ልውውጦችን አድርጊያለሁ። አጠቃላይ የምርምር ትኩረቶቼ የሚያዘነብሉት በዘር፣ በጎሳ እና በልዩ ትምህርት ዙሪያ ነው። በዚህ ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃና ድህረ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት  “ቡድንን መሠረት ያደረጉ አድሏዊነቶች” በትምህርት ስኬታማነት ዙሪያና የአናሳ ወገን ተማሪዎች የመማርና የዕድገት ዕድል የሚለው ልዩ ትኩረቴ ነው። ሰዎች እንደ አሳታፊ-አግላይ እና የተለመደ-አፈንጋጭ የመሳሰሉ ክስተቶችን በልዩ ትምህርት ምርምር መሥክ እንዴት ይመለከቷቸዋል የሚለው በኔ በኩል ከፍተኛ ፍላጎት የሚያሳድርብኝና በቀላሉ ከኔ የምርምር መስክ ጋር የሚዋሃድ ነው። በሚገርም ሁኔታ ባለፉት 26 ዓመታት በገዛ ሀገሬ “የብሄር ደረጃ ተዋረድን(hierarchy)”[22] በተመለከት ምን እየተፈጸመ አንዳለ ዘንግቻለሁ፣ አልተጠራጠርኩም ወይም አልገባኝም ነበር።

 

ይህንን ለማለት የቻልኩበት ምክንያት የምዕራብያውያን ምሁራን ዘረኛ ዕምነቶችን ወይም መሠረተ መርህ (tenets)[23] እርቃን በማስቀረቱ ጉዳይ ላይ ተጠምጄ በነበረበት ጊዜ እናት ሃገሬ በከፋፍለህ ግዛ አባዜ አንዱ ዘር እንደ “ወርቅ” የ  ̋ተመረጠ” ትክክለኛ የሃገሪቷ የበላይ ሌላው ደግሞ መናኛ (inferior)የሆነበት ጉዳይ ላይ ተዋክባ ነበር። ይህ ዕርባና-ቢስ(nonsense) ፖለቲካ ያስታወሰኝ ነገር ቢኖር የትምህርት ሊቃውንት የፒግማሊየን  (Pygmalion) ወይም የሮዜንታል (Rosenthal)[24] ውጤት ብለው የሚጠሩት ነው። የፒግማሊየን ወይም የሮሴንታል ውጤት የሚነግረን ከፍተኛ ነገር ቢኖር መጠበቅ (expectation) ውጤታማነትን የሚጨምርበትን ክስተት ያስከትላል። በግሪክ አፈታሪክ የሚተረክለትና ከቀረጸው ሃውልት ጋር ፍቅር ከያዘው ከሃውልት ቀራጺው ፒግማሊየን በኋላ የሚታወቀው ይህ ውጤት ከሮዜንታል-ጃኮብሰን ጥናት በኋላም ባማራጭነት ይጠቀሳል (Rosenthal & Jacobson, 1992)[25]። የፒግማሊየን ውጤት ነፀብራቅ በሆነውና የጎለም ውጤት(Golem effect) በምንለው ደግሞ ዝቅተኛ ውጤት መጠበቅ ዝቅተኛ አፈጻጸምን/ስራን ያስከትላል። እነዚህ ሁለቱ የርዕሰ-ምሉእ ትንቢት የውጤት ዓይነቶች ናቸው። በፒግማሊየን ውጤት ጥሩ ደረጃዎቻቸውን የራስ ወይም ውስጣዊ የሚያደርጉ በጥሩ ደረጃ ይሳካላቸዋል። ከፒግማሊየን ውጤት ሃሳብ በስተጀርባም ከተከታዮቻቸው ከፍተኛ ሥራ አፈጻጸም የሚጠብቁ መሪዎች በተከታዮቻቸው መልካም ሥራ አፈጻጸም ውጤት ይገለጻል። በህብረተሰብ ጥናትም ውጤት ከትምህርትና ህብረተሰብ ክፍል አኳያ ይታያል[26]። በኢትዮጵያ ሁኔታ ከተመለከትነው ይህንን ጉዳይ በፖለቲካው ቁንጮዎች(elites)፣ አስተዳዳሪዎች፣ አዳዲሶቹ ባለጸጋዎች ወይም በትግራዮች ዝቅተኛ ግምት ከተሰጣቸው ግለሰቦች ወይም ተራ ዜጎች ወይም ”ያልተፈለጉ/የተገለሉ ብሔሮች ̋ ሥነ-ልቦናዊ ክስተት ጋር የሚያያዝ ነው። ይህንን  በትምህርትና ተቋማዊ አካባቢዎቹ በሰፊው የታየና የተጠና ውጤት በቀጣዩ ሥራዬ በአጽንኦት የማካትተው ጉዳይ ይሆናል። በዚህ ረገድ የኔ ሥጋት የሚሆነው አሁን ገዢዎቹ  ያለአግባብ በገፍ የተቆጣጠሩትን ቁሳዊ ሃብት በትምህርት ስኬታማነት ላይ በሂደት ወገንን መሠረት ላደረገ አድሏዊነት ይጠቀሙበታል የሚለው ነው። ዲሜጥሮስ ብሩክ (August 26, 2016)[27] ግልጽ እንዳደረገው ትግራዮች ሳይዘገይ በፊት ፈጥነው ይህንን ችግር መገንዘብ አለባቸው።  በዚህ ሁሉ ጉዳይ ውስጥ አስጊው ሁኔታ ህወሃት ይሁን ወይም በትግራይ መሠረቱ  የሆነዉ ህዝብ ሊያውቁት የሚገባ ነገር ቢኖር ኢትዮጵያውያኖች ከዚህ በኋላ በቀሪው የሃገሪቷ ክፍል ኪሳራ የሚካሄድ  የትግራይ ልዩ ተጠቃሚነትና ትምክህተኝነት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ነው። የኢትዮጵያ ህዝብን ከህወሃት የጭቆና አገዛዝ የመላቀቅ ጥያቄን በተመለከተ ትግራዮች ጥላቻን መቀልበስና ራሳቸውን በማዳን ረገድ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጎን የመቆም ወይም ገዢዎቹን የመደገፍ ምርጫ መሥመር ላይ መገኘታቸውን ሊያውቁት ይገባል። ይህንን ጉዳይ ከራሳቸው የረጂም ጊዜ ወይም ዘላቂ ጠቀሜታ አኳያ በትክክል መመዘን ይኖርባቸዋልም[28]።. For antithesis, see Hanesey Kedusey (Tigrai Online, June 1, 2015)[29]: Tigreans are not “Silent”, but chauvinists chose not to hear them.

 

(3) የብሔር ማንነትና ብሔርን ስለመቆጣጠር:- የጋራ ጥፋትና የግል ተጠያቂነት ተቃርኖ(ለየቅል መሆን)

 

ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ቁሳዊ ሃብቶችን ብክነት፣ ኢኮኖሚያዊ አድሏዊነትን፣ ሙስናን፣ ወታደራዊ፣ ፖለቲካውና ተቋማዊ ግትርነትንና(intransigencies) ብልሹ አሰራሮችን በተመለከተ ጠለቅ ብዬ በዝርዝር መግባት አልፈልግም። ለየት አድርጌ የምገባበት ጉዳይ ቢኖር በህወሃት ግምባር ቀደምትነት በሃገሪቷ ላይ ስለተንሰራፋው  “አደናጋሪ(ያልተነቃበት) ቅኝ አገዛዝ ” (perplexing colonialism)አጠቃላይ ሁኔታ ነው። “ በተለመደው መመዘኛ ” ገዢዎቹና ተባባሪዎቻቸው ኢትዮጵያውያን የሚባሉ ናቸው። ሆኖም ግን የሚወስዷቸው አብዛኛዎቹ እርምጃዎቻቸው እንደ ዕውነቱ ከሆነ በኢትዮጵያዊነት የሚያስፈርጇቸው አይደሉም። በኔ በኩል ይህን ሁኔታ የማስቀምጠው የመጨረሻው ግብ “የነበረችዋን ትግራይ” በራሷ ለማቆም “ታላቋን ትግራይ ”  ያለማቋረጥ የመገንባትና ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ደግሞ የሃገሪቷ የተፈጥሮ ድንበሮች እንደገና ሲሰመሩ በግርታ የሚመለከትበት ሁኔታ መኖሩን ነው። ይህንን ጽሁፍ በማዘጋጅበት ወቅት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ሰፋ ያለ መብት እንዲሰጠው ግፊት እያደረገ መሆኑን ከውስጥ ያፈተለከ የህግ ሰነድ ያመለክታል። በአዲሳ አበባ ውስጥ የኦሮሚያን ልዩ ፍላጎት የሚወስነው አዋጅ ረቂቅ በአስሮች የሚቆጠሩ እርምጃዎችን አካቷል።  ከሚጠቀሱትም መካከል የከተማዋ ስም ፊንፊኔ እንደሚባል፣ አፋን ኦሮሞ ከአማርኛ ቋንቋ ጋር መሳ ለመሳ/ along with/ የከተማዋ “የሥራና ይፋ/አፊሺያል ቋንቋ” እንደሚሆን፣ የከተማዋ ኦሮሞ ነዋሪዎች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እንደሚኖራቸው፣ የኦሮሚያ መንግስትና ኦሮሞ ነዋሪዎች የህዝብ አደባባዮች፣ ማዕከሎች፣ አዳራሾች፣ እና ስታዲዮሞች የመሳሰሉ የጋራ ቦታዎች ላይ የአጠቃቀም ቅድሚያ መብት እንደሚያገኙ፣ የከተማዋ ድንበር በከተማዋ አስተዳደርና በኦሮሚያ ክልል መንግስት የጋራ ስምምነት የወሰናል የሚሉት ይገኙበታል። እዚህ ላይ የሚገርመው ነገር ለምን አሁን?  አጠቃላይ አንድምታው ሲጤንም ከመለያየት ይልቅ የሁሉንም ብሔሮች ፍላጎት የሚጠቅሙ ፖሊሲዎችና የሚጠበቁ ጉዳዮች ላይ ለምን ትኩረት አልተደረገም? የሚሉት አነጋጋሪ ናቸው። ጋርድነር በኳርዝ አፍሪካ እንዳስቀመጠው “የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ግንባር(ኢህአዴግ) ህዝባዊውን አመጽ ለመጨፍለቅ ለዘጠኝ ወራት የጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የፖለቲካዊ መፍትሔ አስፈላጊነትን ግልጽ ያወጣ ነበር። ሆኖም ግን ለፓርላማው የቀረበው  በሁከት የታጀበው ረቂቅ ሰነድ በአፍሪካ በህዝብ ብዛት ሁለተኛ የሆነችው ሃገር ውስጥ ውጥረት እንደነገሰና እንደቀጠለ የሚያመለክት ነው። አሁን ሙዳዩ ውስጥ ያለው፣ በከፍተኛ ደረጃ የገነነውና መልስ የሚሻ ጥያቄ ቢኖር አዲስ አበባ የማን ናት?” የሚለው ነው። በእርግጥ ይህ የህግ ሰነድ ዝርዝር ትንታኔ ይፈልጋል። በሙያው ያልሰለጠነ ወይም በጉዳዩ ዙሪያ የተለየ ዕውቀት የሌለው ሰው የሥርአቱን ሃሳብ ሊያንጸባርቅ ወይም ልብ ትርታ ሊያዳምጥ ቢዳዳውም መብትን በማስመለስ ስም የተቀነባበረው ይህ ረቂቅ ሰነድ ግን ያለምንም ጥርጥር በባህል ጅምላ ጭፍጨፋ ላይ ያነጣጠረ የከፋፍለህ ግዛ ስልቶችና የበላይነት አካሄድ እንደመሆኑ መጠን በቅርቡ ወይም በቀጣዩ የሚያስከትለው ውጤት አደገኛ ይሆናል።. ኦፊሲየል ባልሆነ መንገድ ቃለመጠይቅ ያደረግኩላቸው የተወሰኑ ኢትዮጵያውያን ምሁራን እንደነገሩኝ ከመንግስት ጋር ቁርኝት ያላቸው ማህበራዊ ሜድያዎችና የመንግስት ታማኝ ደጋፊዎች አካባቢ ያለው የሃይል ኮሪደር/ power corridor/ አካሄድ ለኦሮሞና አማራ ብሔሮች ዝቅተኛ ግምት የሚሰጥ አኳኋን የተጠናወተው ነው። ከሚጠቀሱት የበታችነት  መግለጫ አስተሳሰቦች መካከል ዘገምተኛ፣ አዕምሮ-ደካማ፣ ፍርሃት ያደረበት፣ መንቀሳቀስ የተሳናቸው (የጀርባ አጥንት አልባነት ማለትም አከርካሪ የሌለው ዓይነት) የሚሉት ይገኙባቸዋል።  እነዚህ ዓይነት ክብረ-ነክና አንኳሳሽ (derogatory and disparaging) ንግግሮች ደግሞም በሚያበሳጩና ንቀት በተሞላ ቃና የሚነገሩ ናቸዉ።(ለበለጠ መረጃና ጭብጥ የፕሮፍሰር አለማየሁ ገብረማርያምን ኢትዮጵያ፡-የ “ዘገምተኛ አማሮች” እና “ወንጀለኛና አሸባሪ” አሮሞዎች መነሳሳት/Rise የሚል ጽሁፍ በ2016 ተመልከት?) በመሠረቱ እነዚህን ነጥቦች ስዊድን ከሚገኙ የህወሃት ቀንደኛ ደጋፊዎች ጋር ባደረግሁት ክርክርም ታዝቢያለሁ። ከዘር ጋር የተያያዙ እነዚህ ንቀት-አዘል ወይም አጣጣይ አገላለጾች ያልተቋረጡ የረጅም ጊዜ ጥላቻ መገለጫዎች ናቸው።

“ከታሪክ የማይማሩ የከፋውን ቀን ይደግሙታል።” የዚህ ጥቅስ መነሻ ጆርጅ ሳንታያና (George Santayana) ሲሆን እንደወረደ ሲነበብ “ያለፈውን ጊዜ የማያስታወሱ እንዲደግሙት ይገደዳሉ” ይላል። ይህ አገላለጽ በራሱ  በትክክል የሚናገር ነው። ይህንን ጉዳይ ተለቅ የሚያደርገው የተለመደ በመሆኑ ምክንያት ብቻ አይደለም ነገር ግን ዕውነትም ጭምር ከሆነ እንዲሁም ታሪክ አዳፋ ከሆነ(ፍንጭ፡-ነውም)/(hint: it is) ይህ አባባል የህዝብ/የመንግስትና የግል ፖሊሲዎቻችን እንዲቃኝ የግድ ይላል። አዚህ ላይ አለመግባባት አስቸጋሪ ነው።  በታሪካችን ውስጥ ጦርነቶች የሚያበቁት አንዱ በሌላው ተሸንፎ ሥልጣኑን በመነጠቅ በመሆኑ ጦርነት ጦርነቶችን ሲወልድ ኖሯል። በሌላ በኩልም ግለሰቦችን ፍጹማዊ አገዛዝ የሚያጎናጽፉ አብዮቶች ደግሞ በጨካኝ አምባገነንነቶች ማብቃታቸው አይቀሬ ነው።  ስለመጨረሻቸው ቢመከሩም እንኳ ከጠባቸው የማይማሩ ባልና ሚስት መጨረሻቸው ፍቺ ነው። ከስህተታቸው የማይማሩ ሰዎችም አይሻሻሉም ወይም በአስተሳሰብ አይበስሉም። ይህ ሁሉ ፕሮፖጋንዳ መንዛትና ሌሎች ብሔሮችን የማጣጣል (የማሳነስ) ባህሪ መንግሥት በራሱ ላይ ቃታ እየሳበ መሆኑን ሊያስገነዘበዉ ይገባል። ከታሪክ መማር ይገባናል! ቅኝ አገዛዝ ወደ ብሔር ማንነት የተለወጠበትን ፖለቲካዊ፣ ሥነ-ህብረተሰባዊና ሥነ-ልቦናዊ ገጽታዎች/perspectives/ ዳስሰናል። የጎሳ ሴራ ከግለሰብና ውስጣዊ አካባቢ ባለፈ መልኩ  ራሱን ገልጧል። ስኮት ስትራውስ (Scott Straus) ከዊሰኮንሲን ዩኒቨርሲቲ እንደገለጸው የብሔር ማንነት ጉዳይ ለሩዋንዳው የዘር ፍጅት በከፊል አስተዋጸኦ አለው። እንደ ኤሮፓ አቆጣጠር አፕሪል 1994 በግዜው የነበሩት የሩዋንዳ ፕሬዚደንት ጁቬኒየል ሃቢያሪማና ግድያን ተከትሎ ሁቱዎች በጎረቤቶቻቸው ቱትሲዎች ላይ በመነሳት ከ500,000 አስከ 800,000 የሚሆነዉን ህዝብ በ100 ቀናት ጊዜ ውስጥ ፈጅተዋቸዋል። ከፖለቲካ አንፃር ለማመን የሚያስቸግር ውስብስብ ሁኔታ ቢሆንም ለብጥብጡ  አስተዋጸኦ ያለው የብሔር ግፊት ሊታለፍ የማይገባው ነው። ከጀርመን የሩዋንዳ  ቅኝ አገዛዝ በፊት የሁቱና ቱትሲ ማንነት ተለይቶ አልተቀመጠም ነበር። ጀርመን በቱትሲ ንጉሣዊ አገዛዝ የበላይነት አማካይነት ሩዋንዳን የገዛች ሲሆን ጀርመንን የተኳት ቤልጂየሞችም(ቤልጂግ) ሩዋንዳን ከተቆጣጠሩ በኋላም ይህንኑ አካሄድ ተከትለዋል። የቤልጅየም አገዛዝ ደግሞ በቱትሲና ሁቱ መካከከል ያለውን ልዩነት አጠናከረ። አናሳዎቹ(በቁጥር) ቱትሲዎች አንደ ትልቅ ተቆጥረው በበየልጂየም እየተደገፉ  ገዢ እንዲሆኑ ሲደረግ ብዙሃኑ ሁቱዎች ግን በረቀቀ መንገድ ተጨቋኝ ሆኑ። የኋላ ኋላ ግን የሁቱ አብዮት በሚባል እንቅስቃሴ ሃገሪቷ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ በወጣችበት ጊዜ የሃገሪቷ ሥልጣን ባለቤትነት በአስገራሚ ሁኔታ ተቀይሮ ሁቱዎች የበላይ የሆኑበት አዲስ መንግሥት ተቋቋመ። የኖረው የብሔር ውጥረት ቤልጂየሞች ሲወጡ አብሯቸው አልወጣም። ይልቁኑ በጎሳዎቹ መካከል ቁርሾ ሆኖ የቆየዉን ውጥረት አዲሱ መንግሥት ክፍፍሉን አጠናከረው።

በግልጽ ሃላፈነቱ ቁንጮው የህብረተሰብ ክፍል (በትምህርትና በሌላም የቀደመው) ላይ የሚወድቅ ነው። ፊረንና ሌይቲን Fearon and Laitin (1999)[30] ስልታዊ የዘር ማንነት አደረጃጀት ጉዳዮች ከብጥብጥ ጋር ስላላችው ተያያዥነት በርካታ ጭብጦች እንዳሉና በጉዳዩ ዙሪያ የሚነሱ ተጠቃሽ ክርክሮችም ሆኑ አስረጂዎች ግን እምብዛም እንዳልሆኑ ይገልጻል። በዚህ ጽሁፍ ላይ በጸሃፊው ትንተና በእጅጉ የተሰመረበት ጉዳይ ቢኖር ምንጊዜም በብሔሮች መካከል የሚነሱ መጠነ ሰፊ ግጭቶች የሚጫሩት በቁንጮዎቹ ሰለመሆኑ ነው።

ኪሳራውን ባለመረዳት፣ በቁንጮዎቹ (በሁቱም ወገኖች ያሉ) ይሁንታ በተሰጠው ውርጅብኝና ወታደራዊ እርምጃ በተፈጠረ መጠን ያለፈ ፍራቻ አንዲሁም በብሔር አመጣሽነታቸው ከቁብ የማይጣፉ የመንደር ቅሬታዎች ምክንያት ተከታዮች ይከተሏቸዋል ወይም ይነዳሉ። ህዝቡን ለአመጽ የሚያመቻቹ እኩይ ዘዴዎችና የተንዛዙ አሰራሮች አንዲሁም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣን አብሮ የኖረውን የጎሳ ድንበር የብጥብጥ ሚና በሚኖረው መልኩ እንደ ፖሊሲ በሥራ ላይ እየዋሉ ነው የሚሉትን ጨምሮ ብዙ ዘዴዎቻቸው ተጠቅሰዋል (ዝኔ ከማሁ/Ibid)።

ኢክማን በእየሩሳሌም፡-  የሰለቸ የእርኩስ(የእኩይ) መንፈስ ሪፖርት (Eichmann in Jerusalem: A Report on the Banality of Evil,) የሚል በምሁሩ ዓለም ውዝግብ ያስነሳ  መጽሃፍ ጸሃፊ ታዋቂዋ ፖሊቲካል ሳይንቲስት ሃና አረንት “በአምባገነን ሥርዓት የግል ሃላፊነት” የሚል መጽሃፍ ጽፋለች። የዚህ ልዩ መጽሃፍና ሌሎችም በኒዮርከር ጋዜጣ የወጡ በርካታ ጽሁፎቿ ርዕሶች በፍልስፍና አንድምታ የሚያነጋግሩ ናቸው። ሃና አረንት በዚህ ማሳያነት በናዚ ጊዜ በግል ንጹሃን ተብለው የሚታሰቡ ዜጎች ከጦርነት በኋላዋ ጀርመን “በጋራ ጥፋተኝነት” ራሳቸውን ሲያጋልጡ ዋና ዋናዎቹ ወንጀለኞች ግን “በሞራል መምታታት ምንም እንዳላደረጉ ዓይነት” የፀፀት ስሜት አልታየባቸውም በማለት ጠቅሳለች (Arendt, 1987)[31] ።  ሚስስ አረንት እንዳለችው የጋራ ጥፋተኝነት ጽንሰ ሃሳብ ከግል ጥፋተኝነት በተቃርኖ ምንም ማለት አይደለም፤ ይልቁኑም ዕውነቱን በመደበቅ ከበስተጀርባ ለጥፋተኛ ግለሰቦች ለብቻ በመሸሸጊያነት የሚያገለግል ነው። እኔም ይህን ነጥብ የማነሳበት ምክንያት ትግራዮችን ጨምሮ በህወሃት ደጋፊዎች ላይ ንቃተ ህሊና(በሃና አረንት የተጠቀሰው) የሚንጸባረቅ በመሆኑ ነው። እርግጠኛ ነኝ ሁሉም ደጋፊ አይደሉም። እነሱም ጭምር በፍርሃትና በቁጥጥር ሥር እንደሚኖሩ ማመን ፈልጋለሁ። እርግጥ ነው ሰፋ ያለ የማሳመን ሥራ ይሰራል። ከተገኘው አዲስ የጠቀሜታ ዕድል ሁሉም ተቋዳሽ እንደማይሆኑም እርግጠኛ ነኝ። ምንም እንኳ አንድ አንድ መልስ የሰጡኝ የተለየ ነገር የነገሩኝ ቢሆንም ማመን የምፈልገው ያንኑ ነው። ሆኖም ግን በኔ አቋም ከአባለቱ መካከል በዘርማጥፋት ወይም በጅምላ ግድያ የተሳተፉ፤ የሌሎቹን ተሳታፊነት በቸልተኝነት የተመለከቱ ወይም ቢኖሩም አንድን ማህበረሰብ በጅምላ መኮነን ትክክል አይደለም። የህግ ተንታኞችና የፍልስፍና ሰዎች በጋራ ጥፋተኝነት ክስተት ላይ አሁንም ይከራከራሉ። የእንግሊዘኛው ዲክሽነሪ  ወይም የጋራ ጥፋተኝነትን ጥፋተኝነት ከሚለው በመነሳት ሲተረጉመው ጥፋተኝነት የአንድ ቡድን አባላት የሚጋሩት አስነዋሪ ሆነው የሚታዩ ድርጊት ወይም ድርጊቶች ናቸው። አልተነገረለትም ነገርግን በድርጊት ይገለጣል። ለምሳሌ የደቡብ አፍሪካ አፍረካነርስ (ነጮች) የዘር መድልዎ አገዛዝን በተመለከተ የጋራ ጥፋተኝነት አለባቸው። ጀርመኖችም በዘር ማጥፋት (Holocaust) እንዲሁ፤ ይህን አስመልክቶ ከትግራዮች “በስሜ ይህ አይደረግም», «Not in my name” የሚሉትን የምንሰማበት ጊዜ መምጣቱ ሩቅ አይደለም ወይም አይቀሬ ነው።

በኢትዮጵያ ሁኔታ የጋራ ተጠያቂነት ወይም የጋራ ጥፋተኝነት የምንለው ክስተት ከፍተኛ አከራካሪ ጉዳይ ነው። እናም ትግራዮች ህወሃት የፈጸማቸውን ጥፋቶች በመታገስ፣ ጉዳዬ ባለማለት፣ ወይም በማስተናገድ ወይም በገቢር በመተባበር  ተጠያቂ ናቸውን? አይሁዶች እየሱስን በመስቀላቸው የሚኮነኑበት ሁኔታ የኖረ የጋራ ተጠያቂነት ምሳሌ ነው። ይህም  በጊዜው ለነበሩት አይሁዶች ብቻ ሳይሆን ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ መኮነናቸው እንደቀጠለ። ይህም የመጣው “ሕዝቡም ሁሉ መልሰው። ‘ደሙ በኛና በልጆቻችንም ላይ ይሁን አሉ!'” ከሚለው ነው። የማቲዎስ ወንጌል ምዕራፍ 27 ከቁጥር 25 – 66። ይህ ‘የጋራ’ የሚለው አስተሳሰብ ሰዎች ባሉበት ስብስብ ወይም ማህበረሰብ ውስጥ ጥፋት ባያደርሱ እንኳን ጥፋቱን ከፈጸሙት ሌሎች አባላት በላይ ወይም ሌሎች ለፈጸሙት ጥፋት ተጠያቂ የሚሆኑበትን ሁኔታ የሚያመለክት መሆኑ  በኔ አመለካከት አስቸጋሪ ነው። በመሆኑም ትግራዮችና ሌሎችም የሲቪል ማህበረሰቦች በስማቸው እየተፈጸመ ያለውን ወንጀል አስመልክቶ ቢያንስ ተጠቃሽ ተቃውሞ ወይም በሞራል ደረጃ የሚጠበቀውን ማሳየት መቻል አለባቸው። ከተጨቆነው ኢትዮጵያዊ ወገናቸው ጎን ካልቆሙ ግን የታሪክ ተወቃሽ ይሆናሉ። የፖለቲካ ፓርቲን ወይም የመንግሥትን አካሄዶች፣ ግቦችና ፖሊሲዎች አስመልክቶ የተወሰኑ አለመግባባቶች ሊጠበቁ ይችላሉ።

 

እነዚህ ጉዳዮች ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖረው ብቻ ሳይሆን ውጭም ላለው ወሳኝና እየገዘፉ የመጡ ኣሳሳቢዎች  እንደመሆናቸው መጠን በመጨረሻው ላይ ይህ የማንቂያ  ጥሪ ደወል ለትግራዮች እየተደወለ ነው።  ሁሉም የትግራይ ተወላጆች ቁንጮዎቻቸው ለሰሩት ወንጀል የጋራ ተጠያቂነት ባይኖርባቸውም ቢያንስ የሞራል(ህሊና) ሃላፊነት/ተጠያቂነት አለባቸው። ዴቪድ ራይዘር (David Risser) በትክክል እንዳስቀመጠው የሞራል ሃላፊነት ዋና ዋና መሠረታዊ ሃሳቦች በማንኛውም ማህበረሰብ ሁለንተና ማህበራዊ ህይወት ውሰጥ በተጨባጭ ወሳኝነት ያላቸውና ሥር የሰደዱ ናቸው ። የሞራል ሃላፊነት የሚሰማው ግንዛቤ ሳይኖር ምንም ያህል አዲስ ሃሳብ አፍላቂ አርቆ ማስተዋል ቢኖርም እንደ ሰው ልጅ  ማህበረሰብ ዕውቅና ያለው ማህበረሰብ አያመጣም። ግለሰቦች ላይ የሚሰራ የሞራል ሃላፊነት መሠረታዊ ሞዴልን አስመልክቶ ሁሌም እጅ አውጥተው ያልተስማሙበት ስምምነት እንደመኖሩ መጠን ይኸው ሃሳብ እንዴት ቡድኖችና አባላቶቻቸው ላይ እንደሚሰራ ደግሞ ሌሎች በርካታ አከራካሪ ነጥቦችም አልታጡም።

[1] TPLF is the main and most powerful party within the Ethiopian People’s Revolutionary Democratic Front
(EPRDF), the so- called ruling political coalition which consists of four political parties. The TPLF-backed
Ethiopian People’s Revolutionary Democratic Front took power after the collapse of the Derg in 1991.

[2] http://www.cohenonafrica.com/homepage/2018/1/2/ethiopia-at-an-ominous-crossroads.

[3] http://www.bbc.com/news/world-africa-42552643. Ethiopia to release political prisoners, says prime minister.
January 3/ 2018.

 

[4] The recent history of the concept of inner or ‘internal’ colonialism began in the 1960s when it was used both to
describe the status of African-Americans in the United States, as well as that of Québécois in Canada. M. Hechter,

Internal Colonialism: The Celtic Fringe in British National Development, 1536–1966 (Berkeley, 1975).

  1. McRoberts, ‘Internal colonialism: the case of Québec’, Ethnic and Racial Studies, II (1979), 293–318.

Robert J. Hind, ‘The internal colonial concept’, Comparative Studies in Society and History, XXVI (1984), 553.

Robert L. Nelson (2010) From Manitoba to the Memel: Max Sering, inner coloni-zation and the German East, Social History,
35:4, 439-457, DOI:10.1080/03071022.2010.513476 p. 450.

[5] Pinderhughes, Charles (June 2011). “Toward a New Theory of Internal Colonialism”. Socialism and Democracy. 25: 244.

[6] Howe, S. (2002). Empire: A Very Short Introduction. New York: Oxford University Press.

[7] Wolpe, Harold (1975). “The Theory of Internal Colonialism: The South African Case”, in I. Oxaal et al., Beyond the Sociology
of Development
. London: Routledge & Kegan Paul.

[8] Chatterjee, Partha (1993): The Nation and its Fragments, (Princeton: Princeton University Press), p.19

[9] Elizabeth B. Jones. (2014). The Rural »Social Ladder«. Geschichte und Gesellschaft 40:4, pages 457-492. Crossref.
And, Robert L. Nelson. (2011) Emptiness in the Colonial Gaze: Labor, Property, and Nature. International Labor
and Working-Class History 79:01, pages 161-174. Crossref.

[10] http://www.tigraionline.com/future-of-tigrai-ethiopia.pdf. “ጥቕምን መፃኢ ዕድልን ህዝቢ ትግራይ ኣብዛ ሕዚ ትፍጠር ዘላ
ኢትዮጵያ እያ ትምስረት”“ኣብዚ ኩነታት ከምድላዩ ክጨማለቕ ዝደሊ ሓይሊ ክስጉም ዝኽእል ኣይኮነን፡፡ ንግዘኡ ግን ቃንዛ ክፈጥር ይኽእል እዩ፡
ሜ/ጀነራል ተኽለብርሃን ወ/ኣረጋይ (ዶ/ር).https://hornaffairs.com/tg/2017/12/07/general-teklebrhan-woldearegay-interview/

[11] https://hornaffairs.com/tg/2017/12/07/general-teklebrhan-woldearegay-interview/

[12] For my purpose, I use ethnicity and race interchangeably. There are of course some conceptual differences.

[13] Berhanu, G. (2017). Ethiopia: Intellectual Genocide in the making? The Strong and Pervasive Evidence of Ethnic
Ine-qualities. Advances in Social Sciences Research Journal, 4(13) 133-165.

[14] Peckham, Robert (2004). “Internal Colonialism: Nation and Region in Nineteenth-Century Greece”, in Maria
Todorova, Balkan Identities: Nation and Memory. New York: New York University Press, pp. 41–59.

[15] Andersen, M.; Taylor, H.; Logio, K. (2014). Sociology: The Essentials (8th ed.). Cengage Learning. p. 424.

[16] Delgado, Richard; Stefancic, Jean (2001). Critical Race Theory: An Introduction. New York and London: New York
University Press. p. 78.

[17] I will get back to this issue in my final report. The late prime minister Melese Zenawi who belongs to the same
ethnic group as the General expressed similar positions and propaganda in public which by many viewed as
“racist” discourse.

[18] Crane, J. (1994). Exploding the myth of scientific support for the theory of black intellectual inferiority. Journal of
Black Psychology, 20, 189-209.

[19] Gould, S. J. (1981/1996). The Mismeasure of man. New York, NY: W.W. Norton.

 

[20] Gladwell, M. (2008). Outliers: The story of success. New York, NY: Little, Brown

[21] Time (2009, June 1). Why your memory may not be so bad after all. New data on how internalizing stereotypes
affects boomers (By John Cloud).

[22] Berhanu, G. (2011Nov.). Academic Racism: Richard Lynn’s and Satoshi Kanazawa’s bogus and sub-standard
theory of racial differences in intelligence: An essay review of Racial Differences in Intelligence: An Evolutionary
Analysis by Richard Lynn (2008) and a review of Temperature and Evolutionary Novelty as Forces Behind the
Evolution of General Intelligence by Satoshi Kanazawa (2008) In Educational review.  Volume 14, number

[23] Berhanu, G. (2007). Black intellectual genocide: An essay review of IQ and the Wealth of Nations. Education
Review, 10(6). Retrieved from http://edrev.asu.edu/essays/v10n6index.html.

[24] McNatt, D. B. (2000). “Ancient Pygmalion joins contemporary management: A meta-analysis of the result”.
Journal of Applied Psychology. 85 (2): 314–322. doi:10.1037/0021-9010.85.2.314. PMID 10783547

[25] Rosenthal, Robert & Jacobson, (1992). Lenore Pygmalion in the classroom. Expanded edition. New York:
Irvington

[26] Oz, S. & Eden, D. (1994). “Restraining the Golem: Boosting performance by changing the interpretation of low
scores”. Journal of Applied Psychology. 79 (5): 744–754. doi:10.1037/0021-9010.79.5.744

[27] TPLF created a Tigrean psychological image – one that paints Tigreans (or tegaru as they call it) as invincible,
hardworking and valorous while the rest of Ethiopians are painted in light of all forms of derogatory attributes –
including coward. The late Meles Zenawi, for example, told a stadium full of crowed in Tigray that Tigryean are
(note the implied us and other here) golden people. And apparently majority of Tigreans seem to have believed the
new TPLF manufactured images of themselves and other Ethiopians. Perhaps it is even possible to find a good
number of Tigreans who tend to think that the world revolves around TPLF, that TPLF is benevolent and that
Ethiopians owe TPLF praise and support. Also, ample circumstantial evidences seem to exist that suggest TPLF
worked hard to make the rest of Ethiopians believe in the narrative but to no avail.

[28] http://www.borkena.com/2016/08/26/ethiopia-the-hate-from-and-to-tigray/

[29] Risser, David T., “Power and Collective Responsibility.” Kinesis, vol. 9, no. 1 (1978) pp. 23-33. Risser, David T., “The Social Dimension of Moral Responsibility: Taking Organizations Seriously.” Journal of Social Phi-losophy,
vol. 27, no. 1 (1996) pp. 189-207. http://www.iep.utm.edu/collecti/. The Internet Encyclopedia of Phi-losophy (IEP).
Collective Moral Responsibility.

[30] Fearon James D. Laitin David D. 1999 Weak States, Rough Terrain, and Large-Scale Ethnic Violence since 1945 Presented at the Annual Meetings of the American Political Science Association, Atlanta, GA

[31] Arendt, Hannah 1987 ‘Collective Responsibility’, in Amor Mundi: Explorations in the Faith and Thought of

Hannah Arendt, Bernauer, James W (ed.), Dordrecht, Martinus Nijhoff, pp. 43-50

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.