ስዩም ተሾመ ታሰረ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 29/2010)በአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህርና በማህበራዊ ድረ ገጽ በለውጥ አራማጅነቱ የሚታወቀው ስዩም ተሾመ በኮማንድ ፖስት ተከቦ መታሰሩ ተነገረ።

ስዩም ተሾመ
ስዩም ተሾመ

በበርካታ ወታደሮች ተከቦ የታሰረው ስዩም ተሾመ ቤቱ ተሰብሮ ብርበራ እንደተደረገበትና ያሉት መረጃዎች በሙሉ እንደተወሰዱበት ተነግሯል።

በአምቦ ዩኒቨርስቲ የወሊሶ ካምፓስ መምህሩ ስዩም ተሾመ በአገዛዙ ላይ የሰላ ትችት በማቅረብ በማህበራዊ ሚዲያ ይታወቃል።

መምህርና የለውጥ አራማጁ ስዩም ተሾመ በመከላከያና በፌደራል ወታደሮች ተከቦ መታሰሩ ቢነገርም ወዴት እንደሄደ ግን የሚታወቅ ነገር የለም።

የስዩም ተሾመ የቅርብ ጓደኞች ለኢሳት እንደተናገሩት የኮማንድ ፖስቱ አባላት በወሊሶ የተካሄደውን አድማ ተከትሎ በርካታ ወጣቶችም እየተሰሩ ይገኛሉ።

የአምቦ ዩኒቨርስቲ ወሊሶ ካምፓስ መምህርና በማህበራዊ ድረ ገጽ የለውጥ አራማጁ ስዩም ተሾመ የታሰረበት መንገድ ግን አስደንጋጭ እንደነበር ነው ለኢሳት የደረሱት መረጃዎች የሚያመለክቱት።

የስዩም የቅርብ ጓደኛ እንደሚሉት የኮማንድ ፖስቱ አባላት በሶስት መኪና ሙሉ ተጭነው በቤቱ አካባቢ ከበባ በማድረግ መምህርና የለውጥ አራማጁን አስረው ወስደውታል።

ስዩም ተሾመ በመኪና ተጭኖ ሲወሰድ ከማየት በስተቀር ወዴት እንደወሰዱት እንደማይታወቅ የስዩም ተሾመ ጓደኛ ይናገራሉ።

እናም አገዛዙ ስዩም ያለንበትን ሁኔታ ሊያሳውቀን ይገባል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል በርካታ እስረኞች ቢለቅም እንደገና አዲስ የእስር ዘመቻና ዙር መጀመሩን የአካባቢው ምንጮች ይናገራሉ።

በተለይም በኦሮሚያ ላለፉት 3 ቀናት የተካሄደውን አድማ መነሻ በማድረግ የኦሕዴድ ባለስልጣናት ሳይቀሩ እየታሰሩ ነው የሚገኙት።

ስዩም ተሾመ በታሰረበት ውሊሶ ከተማ በርካታ ወጣቶች መታሰራቸውንም የስዩም ተሾመ የቅርብ ጓደኛ ለኢሳት ተናግረዋል።

በኦሮሚያ የተካሄደውን አድማ አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በኢትዮጵያ የቀለም አብዮትን በማካሄድ ስልጣን ለመያዝ የሚፈልጉ ሃይሎች አሉ በማለት የእስር ርምጃ እየተወሰደ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.