“የክርስቲያን አገር በሆነችው ሙስሊሞች ሊነግሡባት ነው” ህወሓት ለአሜሪካ እንደራሴዎች

በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

  • የአስራ ሰባት ታዋቂ ኦሮሞ ሙስሊሞችን ስም ለማስረጃነት አቅርቧል

ህወሓት ከፊቱ የተጋረጠበትን የፖለቲካ ቀውስና ቀውሱን ተከትሎ ከጌቶቹ የተነሳበትን ተቃውሞና ግፊት አቅጣጫ ለማስቀየር ሃይማኖትን የተንተራሰ ስልት ተግባራዊ ማድረጉ ተሰማ። የሚካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ አገሪቱን ለእስልምና አክራሪ አሳልፎ ለመስጠት ያለመ እንደሆነ ህወሓት በወኪሉ በኩል ስም ዘርዝሮ አቅርቧል።

የጎልጉል ዲፕሎማት የመረጃ አቀባዮች ከዋሽንግቶን ዲሲ እንዳስታወቁት ህወሓት አሁን የተነሳበትን ዙሪያ ገጠም ተቃውሞ ከእስልምና አክራሪነት ጋር በማቆራኘት የአስራ ሰባት ኦሮሞ ሙስሊም ታዋቂ ፖለቲከኞችን፣ የመብት ተሟጋቾችን፣ ወዘተ ስም ዘርዝሮ ነው ያቀረበው።

ዙሪያው ገደል የሆነበት ህወሓት የስም ዝርዝሩን ባቀረበ ጊዜ ራሱን የክርስቲያን መንግሥት አድርጎ ለማሳየት ሞክሯል። ይህቺ አገር የክርስቲያን ደሴት ነች፤ እስካሁን ኢትዮጵያን ከመሩት ሁሉ ለሃይማኖት ነጻነት የሰጠነው እኛ ነን፤ የክርስትና እምነታችንን በመጠበቅም ከሆነ እንደ እኛ እስካሁን በትጋት የሠራ የለም፤ ሙስሊሞች ይህችን የክርስቲያን አገር ሊቆጣጠሯት ቆርጠው ተነስተዋል፤ ይህ ካልተገታ አገሪቱ ትበታተናለች – ሃይማኖቱም ያከትምለታል የሚሉ አቅጣጫ የማስቀየሪያ ማስፈራሪዎችን የሎቢ (ውስወሳ) ሥራ በሚያከናውንለት ድርጅት አማካኝነት ህወሓት አቅርቧል።

እነዚህን በአገር ውስጥና በውጪ የሚገኙ ታዋቂ ኦሮሞ ሙስሊሞችን ስም በመዘርዘር፤ የማምለጫ ሰነድ በማዘጋጀት፤ በቀጠራቸው ሎቢስቶች አማካይነት የውስወሳ ሥራ የጀመረው ህወሓት ጉዳዩ በጣት በሚቆጠሩ እንደራሴዎች (የኮንግሬስ አባላት) ዘንድ ይሁንታ እንዳገኘለት የመረጃ ምንጮቹ አመልክተዋል። ህወሓት የፕሮፓጋንዳ ዒላማውን ያነጣጠረው ወግአጥባቂ በሆኑ፣ በኢትዮጵያ ለዘመናት ሙስሊምና ክርስቲያን እንዴት በሰላምና ፍቅር እንደኖሩ ጠለቅ ያለ ግንዛቤ በሌላቸው እንደራሴዎች ላይ መሆኑን የጎልጉል መረጃ አቀባዮች አረጋግጠዋል።  በግምባር ቀደምትነትም የህወሓት ወዳጅ የሆኑት ሴናተር ኢንሆፍ ህወሓት/ኢህአዴግን ለመታደግ ኢትዮጵያ ድረስ እስኪሄዱ ያደረሰ የውትወታ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

እነዚሁ ክፍሎች እንዳሉት ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ተስፋ የተጣለባቸውና የክርስትና (የፕሮቴስታንት) እምነት ተከታይ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አቢይ አህመድም (ዶ/ር) በስማቸው ብቻ ሙስሊም ከሆኑ ታዋቂ ኦሮሞዎች ጋር በመቆራኘታቸው ለኃላፊነት እንደማይበቁ ከአስራ ሰባቱ ስም ዝርዝር ጋር ተካትተው ቀርበዋል።

የዋልድባን ገዳም ከማፍረስ ጀምሮ መንኩሴዎችን፣ የጸሎት ሰዎችን፣ የእምነት መሪዎችንና ህዝብ የሚያከብራቸውን የእምነት እሴቶች እያወደመ ያለው ህወሃት፣ አሁን ለክርስትና ተቆርቋሪ ሆኖ መቅረቡ ያስገረማቸው፣ “አሁን የተመዘዘው የነፍስ አድን ካርድ ነገሮችን እጅግ ሊያወሳስብ ይችላል። አርፈው የተቀመጡና በዜግነታቸው ብቻ ለውጥ የሚጠይቁትን የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደማይሆን መንገድ እንዳይገፋቸው እንፈራለን” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከዚህ አኳያ ትግሉን እየመሩ ያሉ ይህንን የህወሓት መሠሪ አስተሳሰብ አስቀድመው ተረድተው አንድነት፣ ኅብረት፣ አብሮነት፣ መደመር ላይ አበክረው እንዲሠሩ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

ከማግኒትስኪ ሕግ ጋር ተጋብቶ የቀረበው HR 128 በሕዝብ ላይ አስከፊ ግፍ ሲፈጽሙ የነበሩትንና በጠራራ ፀሐይ ሕዝብን ሲዘርፉ የኖሩትን የህወሓት ሹሞችና ቤተሰቦች መግቢያ ያሳጣ ሆኗል። ይህ ረቂቅ ሕግና በአዋጅ እንዳይወጣ ሲከላከል የነበረው ህወሓት በቅርቡ በወርቅነህ ገበየሁ ወልደኪዳን “ነገዎ”አማካኝነት አልሸባብን ማስፈራሪ አድርጎ ለአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች ማቅረቡ ይታወሳል። እኛ ሥልጣኑን ካልቀጠልን አልሸባብ መላውን የአፍሪካ ቀንድ ባጭር ጊዜ ውስጥ ይቆጣጠራል በማለት በመለስ ስልት ለመጫወት ያቀደው ሳይሳካለት ወደመጣበት መመለሱ የሚታወስ ነው።

በቅርቡ ለውይይትና ለድምፅ ይቀርባል የተባለውን HR 128 የህግ ረቂቅ ለማምለጥ ሁሉንም ዓይነት ካርድ ሲስብ የኖረው ህወሃት፣ ስልታዊ መፈንቅለ መንግስት ካካሄደ በኋላ በአስቸኳይ አዋጅ ስም ከውስጥ በጥይት፣ አፈናና የጅምላ እስር፤ ከውጭ በፍረጃ ለማምለጥ በወስዋሾቹ አማካይነት ድጋፍ እያሰባብሰበ መሆኑን ጎልጉል ከሌሎች ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ክፍሎች አረጋግጧል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በቡድን ለማ ሥር የአቢይ አህመድ ለጠ/ሚ/ር ሥልጣን ይበቃል የሚለው አስተሳሰብ እያየለ በመምጣቱ በተለይ በአገር ውስጥ በህወሓት በጀት በሚቆረጥላቸው ደጋፊ የማኅበራዊ ገጽ ሚሊሺያዎችና ካድሬዎች የአቢይን ስም የማጥፋት ዘመቻ መክፈታቸው ከሰሞኑ እንቅስቃሴያቸው ለመረዳት ይቻላል።

ህወሓት እገዛዋለሁ የሚለው ሕዝብ ከከዳው በኋላ ባለቀ ሰዓት የከፈተው ይህ አጀንዳ እንደጠበቀው የበርካታ እንደራሴዎችን አመኔታ አላገኘም። በተለይ ከ“ድምጻችን ይሰማ” የሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ጀምሮ የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅርብ የሚከታተሉ ነባር እንደራሴዎች፤ ጥያቄያቸውን በሰለጠነና ሰላማዊ በሆነ መልኩ ሲቀርቡ በነበሩ ሙስሊሞች ላይ የህወሓት ታጣቂዎች የፈጸሙትን ኢሰብዓዊ ግፍ በማስታወስ ይህንን የህወሓት ማምታቻ ከመስማት ባለፈ ለመደገፍ የማይቻልና በቂ ማስረጃ ያልቀረበበት መላምት አድርገው በመውሰድ ይበልጡኑ በHR 128 ላይ እየሠሩ መሆናቸውን ጎልጉል ያገኘው መረጃ ይጠቁማል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.