ኢህአዴግ ምንግዜም ቢሆን ራሱን አጥፍቶ ህዝቡን ነጻ ሊያወጣ አይችልም (እንስማው ሃረጉ)

ህዝባዊ ትግሉ መዳረሻው የት ይሆን? ዉሃ ቅዳ ዉሃ መልስ ሆነብኝ። የለውጥ ፈላጊው ሰፊው ህዝብ ችግር ጠንካራ መሪ ድርጅት አለመኖር ነው። ኢህአዴግ ምንግዜም ቢሆን ራሱን አጥፍቶ ህዝቡን ነጻ ሊያወጣ አይችልም ምክንያቱም ኢህአዴግ የጎሳ ዘረኛ አምባገነን መንግስት እንጂ ሰማእት ስላልሆነ።

እንስማው ሐረጉ
እንስማው ሐረጉ

ባሳለፍናቸው ሶስት ወራት ረዘም ብለን ስናየው ደግሞ ባለፉት ሶስት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የተደርጉ ፖለቲካዊ ክስተቶችን ወደኋላ አይተን ወደፊት ምን ሊፈጠር ይችል እንደሆን ለማወቅ በሃሳባችን እንባዝናለን። በተለይ በቅርቡ በኢህ አዴግ አባል ድርጅቶች አመራር ተደረገ የተባለው ግምገማና ከዚያ በኋል የተደረጉ አንዳንድ ተስፋ ሰጪ ምልክቶችን ስናይ ጥሩ ነገር ሊመጣ እንደሚችል ያሰብን ብዙ ነን። ይህን ስናስብ ከመሬት ተነስተን ሳይሆን በተግባር እንቅስቃሴዎችን ስላየን ነው።

በተለይ በሽብርና በሌላ ሰበብ “ወንጀለኛ” ተብለው እድሜ ልክና ረጅም አመታት የታሰሩ ንጹህ ዜጉች ምንም እንኳን አሁንም ብዙ ያታሰሩ ቢኖሩም እውቅ የሆኑት አመራሮችና ተከታዮቻቸው ተፈትተዋል። የኢሃዴግ አባል ድርጅቶች ስራ አስፈጻሚ አመራሮች ግምገማም ቢሆን ከበፊቱ ለየት ባለ መልኩ ቁርጠኛ መስለው ለለውጥ የተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸው ነበር። የእስረኞችን መፍታትም ለተናገሩት ለውጥ ዝግጅታቸው እውነት ሊሆን እንደሚችል አስበናል። ከዚህ በተጨማሪም ብዛት ያላቸው የድርጅት ከፍተኛ አመራሮች በተለይ ኦህዴድ ወስጥና በጥቂቱም ቢሆን ብአዴን ውስጥ እጅግ ይበል የሚያሰኝ ተራማጅ አስተሳሰቦችን ሲያስተጋቡ አይተናል። በነዚህ ምክንያቶች ተስፋ ማድረጋችን ግድ ነበር።

ይሁን እንጂ ከእስረኞች መፈታት ጥሩ ነገር ባየን ማግስት ተቃራኒ አፍራሽ ነገር እያየን ስለሆነ ነገሩ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ሆኗል።

አመራሩ በመግለጫው ኑዛዜ ሲያሰማ የነበረው እራሱን ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ያደረገ፤ የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ ራሱ ከፍተኛው አመራር እንደነበር ሃ ሁ በሚመስል መልኩ ለህዝባቸው ተናዘዋል። ይህን ባደረጉ በሳምንታት ውስጥ እኒህ አባል ድርጅቶች በየፊናቸው ድርጅታዊ ጉባኤ አደርግን አሉና አመራሩን ጥፋተኛ ነን ሲሉ ቆይተው እዜው በፊት የነበሩትን መልሰው ያለምንም ለውጥ ቀጥለዋል። መቼም ችግሩ ከአመራሩ ነው ይሉን የነበር አሻንጉሊቱ ተጠቅላይ ሚንስትሩ ደሳለኝ ሃይለማርያምን ለማውረድ ታልሞ ይሆን?

በመቀጠልም ራሳቸውን ጥፋተኛ አድርገው ህዝቡን ሲያደነቁሩት ቆይተው ይባስ ብለው ያልተጠበቀ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀው ህዝቡን ቁም ስቅል እያሳዩት ይገኛል። በተለይ በአማራና በኦሮሞ ክልል ህዝቡን ያነጣጠረ ጥቃት በሰፊው እንደተጀመረ እያየን ነው። እንዴውም በዚህ ባገባደድነው ሳምንት አሮሞ ክልል ውስጥ የኦህዴድ አመራሮችን ማሰር ተጀምሯል። አማራ ክልልም ቢሆን በተለይ ወሎ ውስጥ ከፍተኛ እልቂትና ህዝብ ማሰቃየት ተከስቷል።

ብአዴን አማራ ክልል ከጉባኤው መግለጫው እንደተረዳነው የችግሩ ምንጭ ራሱ አመራሩ ቁርጠኛ ውሳኔ አለማሳለፉ እንደሆነ ነበር። ይሁን እንጅ በተቃራኒው ከችግሩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው በሪፖታቸው ላይ እንደችግር ያልተጠቀስ የአርሶ አደሩን ነፍስ ጠባቂ አንጡራ ንብረት የሆነውን ጦር መሳሪያ ገፈፋ በእቅድ በተጠና መልኩ ጀምረዋል።ልብ በሉ አርሶ አደሩ ባለስልጣን አልገደለም፤ አርሶ አደሩ ባንክ አልዘረፈም፤ አርሶ አደሩ በያዘው መሳርያ ማንንም አልነካም።

ችግሩ ከለውጥ ፈላጊው ወገን አመለካከት ወይም አተያይ ይመስለኛል። ለውጥ ፈላጊው የሚመኘው እንዲሆን የሚፈልገውን ማለትም የመንግስት ለውጥ ነው ኢህአዴግ ድግሞ ራሱን አንጾ ቁመናውን አስተካክሎ መቀጠል ይፈልጋል። ብአዴን እና ኦህዴድም ቢሆን ለውጥ ፈላጊው እንደሚመኘው ራሳቸውን እንደ ጨው አሟሙተው ታግለው አታግለው ህዝቡን ከህወሃት አገዛዝ ቀንበር እንዲያወጡት እንመኛለን ነገር ግን እነዚህ ድርጅቶች በምንም መልኩ ለራሳቸው ቀጣይነት ተግተው ይሰራሉ እንጂ ህዝቡን ነጻ የሚያወጣ ተግባር ሊሰሩ በፍጹም አይችሉም። ህወሃትንም ይፈልጉታል ምክንያቱም የህልውናቸው መሰረት ህወሃት ስለሆነች። በብ አዴንና በኦህዴድ ውስጥ ያሉት ህዝባዊ ትግሉን የሚወግኑ ንጹህ ካድሬዎችም ቢሆን ጠንካራ ተቃዋሚ ድርጅት ስለሌለ ምንም ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም፤ ቀጣዩ የስርዐቱ ጡንጫ እኒህ ሃቀኛ ካድሬዎች ላይ እንደሚሆን በኮማንድ ፖስቱ የሰሞኑ ርምጃዎች እያየን ነው።

ባጠቃላይ ኢህአዴግ ራሱን አያጠፋም፤ሰማእት ስላልሆነ። ዴሞክራሲንም አያመጣም ተፈጥሮው ስላልሆነ። እባብ እርግብ ሊሆን አይችልም። ጠንካራ ታጋይ ተቃዋሚ ድርጅት ስለሌ ለውጥ ፈላጊው ሰፊው ህዝብ ብአዴንና ኦህዴድ ነጻ እንዲያወጡት በቀኑ ያልማል እንጂ እውነታው ይህ ነው። የለውጥ ፈላጊው ሰፊው ህዝብ መሰረታዊ ችግር ጠንካራ መሪ ተቃዋሚ ድርጅት አለመኖር ነው። እንደ አሸን የፈሉት አለን አለን የሚሉት አስመሳይና ውዳቂ ድርጅቶችም አንዳች ፋይዳ አላመጡም። ይባስ የህዝቡን ትግል ስሜትና ተስፋ አጨልመውታል። ድርጅት ስለሌለ ህዝባዊ ትግሉ እንደ ውሃ ሙላት ይፈሥና ይጎድላል አሁንም ይመለሳል እንደገና ወደፊትና ወደ ኋል እያለ እነሆ ሶሥት አመታትን አስቆጥሯል። ጠንካራ ድርጅት ቢኖር ኖሮ ህዝባዊ ማእበሉ አብዮት ሆኖ ወጥቶ በሆነ ነበር። ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ይሏል ይህ ነው። ያም ሆኖ ግን መሪ ድርጅት ስለሌለ ይዘገይ ይሆናል እንጅ ለውጡ የማይቀር የተፈጥሮ ሃቅ ነው። ህዝብ ያሸንፋል!

መልካም አርብ ይሁንላችሁ
እንስማው ሃረጉ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.