የኮረሙን ነገር እስኪ እንነጋገር! (በገነት ዓለሙ)

በገነት ዓለሙ

አገራችን ዛሬም አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ናት፡፡ አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ስንገባ በሁለት ዓመት ውስጥ ይህ ሁለተኛው ጊዜ ነው፡፡ መላውን የ2009 የካሌንደር ዓመት ከሁለት ወር ‹‹ፋታ›› በቀር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ነበርን፡፡ ዘንድሮም ዓመቱ አጋማሽ ላይ የተደነገገው ለስድስት ወራት እንዲፀና በተወካዮች ምክር ቤት የታወጀው በኢፌዴሪ ዘመን ሁለተኛው የሆነው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ ከ2010 ዓ.ም. ጋር አብሮ የሚባጅ/የሚከርም ስለመሆኑ የታወቀ ነው፡፡

መላ ኢትዮጵያ አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ናት፡፡ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሥልጣን አግኝቷል ማለት ራሱ ብዙ ነገር ይናገራል፡፡ ችግር መኖሩንና አደጋ ማንዣበቡን ያረዳል፡፡ አገራችን አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ የምትገባው፣ ከዚህም የተነሳ መንግሥት በተለይም የአስፈጻሚው አካል፣ የፀጥታና የደኅንነት ኃይሎች የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሥልጣን የሚያገኙት፣ በሕግ እንደተደነገገው ‹‹በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል›› በአገር ላይ ያንዣበበ አደጋ ሲከሰት ነው፡፡

አገር እንዲህ ያለ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅን መፍትሔ የሚያደርግ አደጋ ውስጥ ገብታለች ወይ? አገር የገባችበት ወይም ያጋጠማት አደጋስ እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ መግባትን የግድ አስፈላጊ የሚያደርግ፣ ለመንግሥትም የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሥልጣን የሚያሰጥ ‹‹መሠረታዊ የፖለቲካና የዴሞክራሲ መብቶችን … እስከማገድ…›› ያደርሳል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ምንጊዜም መነሳታቸው የታወቀ ነው፡፡ የታወቀ በመሆኑም ነው ይህን ጉዳይ በመጀመርያ ደረጃ በአስቸኳይነቱና በአጣዳፊነቱ ምክንያት የአስፈጻሚው አካል፣ ከዚያም ሕግ አውጪው አካል፣ ሲሆን በ48 ሰዓት ውስጥ፣ አለዚያም በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ እንዲቀርብለትና መክሮና ዘክሮ ጥያቄዎችን እንዲመልስ በሕግ የተወሰነው፡፡ የተወሰነውም የሁሉም የበላይ በሆነው በሕገ መንግሥቱ ነው፡፡

የ2009 ዓ.ም. ሆነ የ2010 ዓ.ም. የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታዎች የመጡት ከ2008 ዓ.ም. ወዲህ በተቀጣጠለው ዴሞክራሲያዊ ትግል ውስጥ በመሆኑ ለዴሞክራሲና ለእኩልነት፣ ለሕግ የበላይነትና ለተገደበ የመንግሥት ሥልጣን የሚደረግ ትግል እንዲህ ያለ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታን አምጦ የሚገላገል መሆን አልነበረበትም ማለት የአብዛኛው አቋምና አጀንዳ መሆኑ አልቀረም፡፡ ያንኑ ያህል ባይሆንም የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው መታወጅ ደጋፊም ነበረው፡፡ ድጋፉም በመንግሥት ወገን ላይ ብቻ ያልታጠረ፣ ሕዝብም ውስጥ ተከታይ ያገኘ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ ብዙ ተስፋዎችን ከወዲሁ ባመላከተው የለውጥ ትግሉ ውስጥ የታየው ውድመትና ጎሰኛ ጥቃት የትግሉን መልካም ገጽታዎች መጉዳት ብቻ ሳይሆን፣ የራሱን የትግሉን አስፈላጊነት ጭምር ለጥያቄ ያቀረበ የትግል ሥልት በመከተሉ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በዴሞክራሲና በእኩልነት ውስጥ መኖርን ይፈልጋሉ፡፡ ይህም የሕዝቦችን የተቀናጀ ትግል ይጠይቃል፡፡ ኢሕአዴግን ከ15 ዓመታት ከሞት የከበደ እንቅልፍ በኋላ ለዳግም ተሃድሶ የቀሰቀሰ፣ የእኔ ብቻ ልክና እውነተኛ ነኝ ባይነት ሃይማኖቱን ያናጋ፣ ያልተቀናጀና ድንገት የተዘረገፈ የሕዝብ የለውጥ ትግልና የተቃውሞ ንጠት ግን የጥላቻ ስሜቶችንና አስተሳሰቦችን በሚያራግብ ጎሰኛ ጥቃት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ ጭምር እየጎደፈ ነው፡፡ መንግሥትንም ከ‹‹ፍጥርጥሩ›› እና ከፍላጎቱ ጋር ተጨምሮ ትግሉን በፀረ ሕዝብነትና በፀረ ልማትነት እንዲኮንነውና እንዲቀጣው አባበለ፡፡ የተወሰነ የሕዝብ ድጋፍም አገኘ፡፡

ዕውን የአገራችን ችግር ‹‹በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን መሠረታዊ የፖለቲካና የዴሞክራሲ መብቶችን›› (አንቀጽ 93/4/ለ) በማገድ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ በማወጅ፣ ለመንግሥትም ይህንን ማድረግ የሚያስችል ሥልጣን በመስጠት የሚፈታ ነው? የሚለው ጥያቄ ይበልጥ ጎልቶ የተነሳው ከአንደኛው ይበልጥ ሁለተኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ነው፡፡ እንደ ብራ መብረቅ ድንገት ‹‹የታወጀው››ም ይኼኛው ሁለተኛው አዋጅ ነው፡፡ ‹‹የፖለቲካ እስረኞች›› ባይላቸውም የታሰሩ ፖለቲከኞችን እያንጠባጠበም ቢሆን የፈታ መንግሥት፣ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የሰላምና የዴሞክራሲ ትግል አስተማማኝ ‹‹የመፍትሔ አካል›› ለመሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩን በገዛ ፈቃዱ ከሥልጣን መልቀቅ በኢትዮጵያም በአፍሪካም ታሪክ አስመዘገበ ያለ መንግሥት፣ በማግሥቱ ሌላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስለመደገሱ በጭራሽ ምልክት አልነበረም፡፡

ከኢሕአዴግ የታኅሳስ ወር የአሥራ ሰባት ቀናት ግምገማ፣ ከዚያ መልስ የአራቱ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት ከሰጡት መግለጫ፣ በዚህ ምክንያት በአጭር ጊዜ (በሁለት ወራት ውስጥ) በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ውስጥ ይወሰዳሉ ተብለው የተገለጹት የመፍትሔ ዕርምጃዎች መካከል ገና የሁለት ወራቱ ክስ የማቋረጥና ይቅርታ የማድረግ፣ እስረኞችን የመልቀቅ ቃል ሙሉ በሙሉ ሳይፈጸም (ቢያንስ ቢያንስ እስከ መጋቢት የመጀመርያ ሳምንት የሚዘልቀው የሁለት ወራት ጊዜ ሳያበቃ)፣ በተለይም ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን የሚለቁ መሆናቸውን ባስታወቁ ማግሥት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ‹‹የሚጠበቅ›› እና የሚታለም በጭራሽ አልነበረም፡፡ ግምገማው ውስጥ ተነሳም አልተነሳም፣ ተወሰነም አልተወሰነም ግምገማውን የሚቃረን ነው፡፡ በግምገማው፣ ከግምገማው በኋላ በየጊዜው የተሰጡ የፓርቲና የመንግሥት መግለጫዎች ላይ ተመሥርተን የነበረንን የአገር ፖለቲካ ዕይታና አተረጓጎምም በጣም የሚለውጥ ነው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው አሁን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል፡፡ ይህን አዋጅ ‹‹ልዩ›› የሚያደርገው ደግሞ እስካሁን ተገቢ ነው? ተገቢ አይደለም? ከሚለው ጥያቄና ንግግር በላይ አለመሆኑ ነው፡፡ እነ ሻለቃ አድማሴ ከነበሩበት ፓርላማ ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መቶ በመቶ በኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች አባላት የተሞላው ፓርላማ 88 እንደራሴዎች ተቃውመውታል፡፡ ብዙዎቹም ኢቢሲ በቀጥታ ሳይሆን ቀድቶና እንደ እሱ ምርጫ አስተካክሎ ባስተላለፈልን መረጃ መሠረት፣ መፅደቅ የለበትም ብለው ሲሞግቱት ዓይተናል፡፡ ፓርላማው ውስጥ ብቻ ሳይሆን ቅዳሜ ዕለት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቀረቡ ‹‹አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች›› ሳይቀሩ ሌላ ጊዜ እንድንናገረው ቀርቶ እንድንሰማው የማይፈቀድልንን የተለየ የተቃውሞ ሐሳብ ሲሰጡ አድምጠናል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጁና በእሱ መሠረት ወጡ የተባሉት ደንብና መመርያዎች ከንግግር በላይ አይደሉም ማለት ግን እዚህ ድረስና በዚህ ላይ ብቻ የተወሰነ ነው፡፡ የአዋጁና የመመርያው ይዘት በተብራራ፣ ተብራራ በተባለ ቁጥር እንደ እኔ እንደ እኔ ፍርኃት ይጨምራል፡፡ በእሱ ውስጥ መኖር በተለይ ሐሳብን ከመግለጽና ከሚዲያ ነፃነት አኳያ እልም ባለው ጫካ እልም ባለው ዱር ውስጥ በጭለማ አንድዬን አምኖ ከመንቀሳቀስ የተለየ አይደለም፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ ሕጉ (አናገረም አላናገረም) ከሚያነጋግርባቸው ጉዳዮች መካከል ሌላው የፀደቀበት መንገድና አካሄድ ነው፡፡ የፀደቀበት መንገድና አካሄድ ማለት ከዓርብ የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያውና ብዙም ይፋ ሆኖ ባልወጣ (በተፈራ) አጀንዳ መሠረት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ማለት ምንድነው በሚለው ጥያቄ ላይ የተመሠረተው ነው፡፡ ለዚህ አጀንዳና ጥያቄ መነሻ የሆነው ደግሞ ምክር ቤቱ ገና አሁን በሁለት ሦስተኛ ድምፅ የሚተላለፍ የውሳኔ ዓይነት ስላጋጠመው አይደለም፡፡ ይህ ምክር ቤት አምስተኛው ፓርላማ ነው፡፡ የዚህኛው ምክር ቤት ሦስተኛ የሥራ ዘመን ነው፡፡ ስለዚህም 23ኛ ዓመቱ ላይ ነው፡፡ እንደ ተቋም በ23 ዓመት ውስጥ ያጋጠመ የመጀመርያው ሁለት ሦስተኛ ድምፅ የሚጠይቅ አሠራር አይደለም፡፡ ምክር ቤቱ የተለያዩ ሐሳቦች፣ ዝንባሌዎችና የአሠራር ዓይነቶች የማይብላሉበት፣ በተለይም የአሠራር ዘዴዎችና ልምዶች እየተጠየቁ፣ እየተፈተሹ የሚፈተጉበትና የሚሰለቁበት ዕድል ስለሌለ፣ ፓርላማውን አሁን ችግሩን ላስከተለው ዓይነት የዘፈቀደ አሠራርና የቢሻኝ ውሳኔ ዳርገውታል፡፡፡

የምክር ቤቱ ስብሰባዎች የሚገዙበት ሕግና ሥርዓት መጀመርያ ስብሰባ ለማካሄድ አስፈላጊ ሁኔታዎች መሟላት ያለባቸው መሆኑን ማረጋገጥን ያስገድዳል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንደኛውና ዋነኛው ምልዓተ ጉባዔ መሟላቱን ማረጋገጥ፣ የስብሰባና በተለይም የፓርላሜንታዊ ስብሰባ የጥበብ መጀመርያ ነው፡፡ የምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ (በየዘመኑ የነበሩት በሙሉ) ስብሰባ ለመጀመር አፈ ጉባዔው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58(1) መሠረት ምልዓተ ጉባዔ መሟላቱን ማረጋገጥ እንዳለበት፣ ሥራ የሚጀመረው፣ የተቀረፁትን የዕለቱን አጀንዳዎች አፈ ጉባዔው ለምክር ቤቱ የሚያቀርበው ምልዓተ ጉባዔ መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ይህ ሳይሟላ፣ ስለዚህም ምልዓተ ጉባዔ መኖሩ ሳይረጋገጥ ሥራ አይጀመርም፡፡

ኮረም ካልተሟላ ፓርላማው በሕግ ፊት የሚፀና ሥራ ሊሠራ አይችልም፡፡ በዚህ ሁኔታ መከናወን የሚችሉ ሥራዎች፣ ‹‹ትንሽ እንጠብቅ›› ብሎ ለጊዜው እረፍት ማድረግ፣ የሚቀጥለውን የስብሰባ ቀን መወሰንና ቀጠሮ መያዝ፣ ግፋ ቢል ደግሞ ኮረም ማረጋገጥ የሚያስችል ዕርምጃ መውሰድ ዓይነት ብቻ ናቸው፡፡ ለማንኛውም ውሳኔ ሰጪ የሥልጣን አካል ኮረም አለ የሚባለው ደግሞ በዚያ አካል ማቋቋሚያ ወይም ሌላ ሰነድ የተቆረጠው አነስተኛ የተሰብሳቢው ሰው ቁጥር ሲሞላ ነው፡፡ ከምክር ቤቱ አባላት ከግማሽ በላይ ከተገኙ ምልዕተ ጉባዔ ይኖራል ብሎ ሕገ መንግሥቱ ስለደነገገ የፓርላማው ኮረም 274 ነው፡፡ የውሳኔ ነገር የሚመጣው ጉዳዩን የምንወስነው በአብላጫ ድምፅ ነው? ወይስ በሁለት ሦስተኛው ድምፅ? የሚለው ጥያቄ የሚነሳው ከዚያ በኋላ ነው፡፡ በ274 መነሻ ቁጥርና ስብሰባ ነው፡፡

ምልዓተ ጉባዔ የመሟላቱን ጉዳይ የማረጋገጥ ወይም አረጋገጥኩ ማለት ደግሞ ለፕሮቶኮል ወግ ተብሎ የሚሠራ ሥራ አይደለም፡፡ ስንት አባላት እንደተገኙ ስንት እንዳልተገኙ በአደባባይ ይፋ ወጥቶ መናገር፣ ሲነገርና ሲመዘገብም መታየት እንኳንስ ለተሰብሳቢዎች ስብሰባው በመገናኛ ብዙኃን ለሚቀርብልንም መነገር አለበት፡፡ የመጀመርያው የአሠራሩ አካል ነው፡፡ አሠራሩና ፍጥርጥሩ የሚያስገድደው ነው፡፡ ሕግ የሚያዘው ነው፡፡ ሁለተኛው የሚዲያው ጉዳይ ከሕዝብ የማወቅ መብት አኳያ የተነሳ ነው፡፡ ስንት የሁለት መቶ ሺሕ (በዛሬው የሕዝብ ቁጥር) ወኪል እንደተገኘ፣ ስንቱ እንደቀረ የማወቅ መብታችን አካል ነው፡፡ ይህ ብዙ ጊዜ አይነገርም፡፡

አፈ ጉባዔው ኮረም ወይም ምልዓተ ጉባዔ መኖሩን አረጋገጠ፣ ይህንንም ለተሰብሳቢው አስታወቀ ማለት ብዙ ነገር መተማመኛ አገኘ ማለት ነው፡፡ መተማመኛ ከሚያገኙት ነገሮች መካከል አንዱ ማንኛውንም ዓይነት ውሳኔ ለማስተላለፍ ተፈላጊው የእንደራሴ ብዛት አለኝ ማለት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፓርላማ አባላት ቁጥር ከ550 እንዳይበልጥ በሕግ ተደንግጓል፡፡ ሲጀመር አንስቶ ምርጫ ሲካሄድበትና ሲመረጥ የኖረው የእንደራሴዎች ቁጥር ግን 547 ነው፡፡ የፓርላማው አባላት ይህን ያህል ቢሆኑም፣ እያንዳንዳቸው የሚወክሉት ሕዝብ ቢኖርም፣ ፓርላማው ሥራውን ይሠራ ዘንድ የግድ ሁሉምና እያንዳንዱ መኖር የለባቸውም፡፡ አንድ ሰው ከጎደለ ወይም 20 ሰው ስላልመጣ፣ ወይም መቶ ሰው ስላልተገኘ ፓርላማው ሥራ አይሠራም ቢባል ፓርላማው ውስጥ ተገኝቶ ተከራክሮ በሐሳብ ረትቶ ከማሸነፍ ይልቅ፣ በመቅረት ያልፈለጉትን አጀንዳ ድል ማድረግ ይቀላል ብሎ መበየን ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት (ከሌሎች መካከል) ምልዓተ ጉባዔ የሚባል ሥልትና ዘዴ ተቋቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ይህን የቁጥር መጠን በአንቀጽ 58(1) ወስኖታል፡፡ ከምክር ቤቱ አባላት ከግማሽ በላይ ከተገኙ ምልዓተ ጉባዔ ይኖራል ብሎ ደንግጓል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መጠን 547 ነው፡፡ የዚህ መነሻ ኢትዮጵያ የተከፋፈለችበት የምርጫ ክልሎችና የምርጫ ውጤቶች ናቸው፡፡ በዚህ ሥሌት ለተወካዮች ምክር ቤት ምልዓተ ጉባዔ (ኮረም) ማለት የ547 ግማሽ በላይ ስለዚህም 274 እንደራሴ ማለት ነው፡፡ ሁለት መቶ ሰባ አራት እንደራሴዎች ብቻ የተገኙበት ስብሰባ የተቀሩትን 273 ያልተገኙ ሰዎች ትቶ በፓርላማው ሥልጣን ውስጥ የትኛውንም ውሳኔ መወሰን ይችላል፡፡ ጦርነት ማወጅ፣ በጀት ማፅደቅ፣ ሊዝ ይቅር ለማለት (እንዲያው ለነገሩ ነው)፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠርቶ ምን እየሠራህ ነው ማለትን ጨምሮ በአንቀጽ 55 ሥር የተዘረዘሩትን ሁሉ መወሰን ይችላል፡፡ በአንቀጽ 60 መሠረት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ መሠረት ራሱን መበተን ይችላል፡፡ ከምክር ቤቱ አባላት ውስጥ ከግማሽ በላይ ብቻ የተገኙበት ምልዓተ ጉባዔ፡፡

እዚህ ላይ አሁን የሚነሳው ጥያቄ ሁለት ሦስተኛ ድምፅ የሚባለውስ ምንድነው የሚል ነው፡፡ ይህንን ጥያቄም ሆነ ከየካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ወዲህ የተነሳውን ውዝግብና ውዥንብር ለማጥራት ሁለት ነገሮችን ለይተንና አጥርተን መረዳት አለብን፡፡ አንዱ ምልዓተ ጉባዔ ነው፡፡ ሌላው ውሳኔ መስጫ የድምፅ መጠን ነው፡፡ ሁለቱ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ እዚያው ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሆነን እናስረዳ፡፡

ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 58(1) ከምክር ቤቱ አባላት ከግማሽ በላይ ከተገኙ ኮረም ይሞላል፣ ምልዓተ ጉባዔ ይኖራል ይላል፡፡ ይኸው ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 64(1) የሌላውን ምክር ቤት ኮረም ሲወስን ደግሞ ‹‹የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ምልዓተ ጉባዔ የሚኖረው ከአባላቱ ሁለት ሦስተኛው የተገኙ እንደሆነ ነው፤›› ይላል፡፡ ይህ ኮረምን የሚመለከተው ነው፡፡

ከኮረም (ምልዓተ ጉባዔ) ለየት ያለውን ጉዳይ በሚወስነው ክፍሉ ስለውሳኔ አሰጣጥ ሲደነግግ ደግሞ ማንኛውም ውሳኔ የሚያልፈው ‹‹ስብሰባ ላይ ከተገኙት›› የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ከግማሽ በላይ ድምፅ ሲደገፍ ብቻ ነው ይላል፡፡ (በአንቀጽ 104 እና 105 የሚጠየቀው የሁለት ሦስተኛ ድምፅም ልዩነት አያመጣም)፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ ማስተላለፍ የሚቻለው ደግሞ በአንቀጽ 59(1) እንደተደነገገው በሕገ መንግሥቱ በግልጽ በተለይ ካልተደነገገ በስተቀር፣ ማናቸውም ውሳኔዎች የሚተላለፉት በምክር ቤቱ የአብላጫ ድምፅ ነው፡፡ ብዙዎቹ ‹‹በሕገ መንግሥቱ በግልጽ በተለይ ካልተደነገገ በስተቀር›› የሚለውን ሐረግ ከሁለት ሦስተኛ ድምፅ አስፈላጊነት ጋር አያይዘው ስለዚህ ምልዓተ ጉባዔ አልሞላም ይላሉ፡፡ የመሰንበቻችን ጎልቶ የሚሰማው መከራከሪያም ይኸው ነው፡፡

የተወካዮች ምክር ቤት የዕለቱ የሥራ አካሄድና አመራር የተለመደ ጉድለት፣ ስህተትና ጥፋት የታየበት ነው፡፡ የምልዓተ ጉባዔውን ትክክለኛ ቁጥር ከስብሰባው አጀንዳ መተዋወቅ በፊት ‹‹ሥራዬ›› ብሎና ነባራዊ አስገዳጅነት ያለው ደንብ አድርጎ አለማስመዝገብ አንዱ የተለመደ ጥፋት ነው፡፡ ሁለተኛው የዕለቱ ስህተትና ጥፋት ጠቅላላ የተገኙት የምክር ቤት አባላት 490 ናቸው እየተባለ የድጋፍ የተቃውሞው የድምፅ ተአቅቦው ቁጥር አልገጥም ያለበት ዝርክርክነት ነው፡፡ ከዚህ ዓይነት ችግር ያልወጣነው፣ ከዚህ ዓይነት የመሳሳትና የማጥፋት ልምዶችን መገላገል ያልቻልነው፣ የኤሌክትሮኒክስ የድምፅ አሰጣጥ ስለሌለን አይደለም፡፡ ግድ ስለሌለን፣ መጠየቅም ሆነ መሳጣት የሌለበትና ሪፖርት የማይደረግበት የቢሻኝ ውሳኔ በመሆኑ ነው፡፡

ከሁሉም የበለጠው የአፈ ጉባዔው ስህተትና ጥፋት ደግሞ የተሰጠውን ድምፅ ሁለት ሦስተኛውን ያሰሉበትና ሌሎችም ‹‹ተቃዋሚዎች›› የተጋሩት ዘዴ ነው፡፡ የምክር ቤቱ አባላት 547 ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ስምንቱ በሞት ወይም በሕመም ‹‹የቀሩ›› ናቸው፣ ስለዚህ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ብዛት 539 ነው፡፡ የዚህ ሁለት ሦስተኛ ደግሞ 359 ነው፡፡ የድጋፍ ድምፅ የሰጠው ከዚህ በላይ ነው አሉ፡፡ ሌሎችም ሁለት ሦስተኛውን የሚያሰሉት ከ547 አባላት አንፃር ነው፡፡

አፈ ጉባዔ አባዱላንና ሌሎችን ይህን ሥሌት የሚከተሉትን ሰዎች እስኪ ልጠይቃቸው፡፡ የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. የተሰበሰበው ፓርላማው ላይ የተገኙት የእንደራሴዎች ቁጥር 274 ብቻ ቢሆን ኖሮ 274 የ547 ሁለት ሦስተኛ አይደለም ብሎ ይበተን ነበር?

የተወካዮች ምክር ቤት በዚህ የ274 የተወካዮች ቁጥር ብቻ ከላይ እንደተገለጸው በሁለት ሦስተኛ ድምፅ (183 ድምፅ) ሕገ መንግሥቱን ሳይቀር ለማሻሻል የራሱን ድርሻ መወሰን ይችላል፡፡፡ የራሱን ድርሻ ያልኩት የተወካዮች ምክር ቤት ብቻውን (ያለ ፌዴሬሽን ምክር ቤትና ክልሎች) ሕገ መንግሥት ማሻሻል ስለማይችል ነው፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት 274 ተወካዮች ብቻ በተገኙበት ስብሰባ በ138 ድምፅ ብቻ (በአብላጫ ድምፅ) ጦርነት ሊያውጅ፣ ምክር ቤቱን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ሊበትን ይችላል፡፡

በፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አግባብነት ይዘትና አስፈላጊነት ላይ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ አዋጁ ይፀድቅ ዘንድ መሰብሰብ ያለበት ተወካይ የ547 ሁለት ሦስተኛ ነው፣ ወይም አዋጁ መፅደቅ ያለበት በ547 ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ነው ማለት ግን፣ ከሕገ መንግሥቱ ውጪ መኖር ነው፡፡ ምልዓተ ጉባዔ የሚሠራው ከግማሽ በላይ አባል ሲገኝ ነው፡፡ የተገኘው ተወካይ እንደ ሁኔታው በተራ አብላጫ ድምፅ ወይም በሕገ መንግሥቱ በግልጽ በተለይ በተደነገጉት ጉዳዮች ደግሞ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ የፀና ውሳኔ ማሳለፍ ይቻላል፡፡

ከመሳሳትና ከማጥፋት ልማዳችን የሚገላግለንና አሠራራችንን የሚያሳጣና ተጠያቂ የሚያደርግ ሥርዓት ስላላበጀን፣ ሳይጠየቁ መቅረትን ስለመረቅን የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. የታየውን ዓይነት ‹‹መቅለል›› አስመዝግበናል፡፡ ጋብዘናልም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.