የአንድነት መሪዎች መታሰርን አይፈሩም ()

February 8/2014

አዲሱ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ግዛቸዉ ሽፈራዉ፣ ለገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ የሰላምና የእርቅ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። «ኢሕአዴግ እኛን እንደ ጠላት እና ሽብርተኛ ማየቱን ማቆም አለበት። እኛም ደግሞ ኢሕአዴግን እንደ አዉሬ ማየት ማቆም አለብን። ከጥላቻ ፖለቲካ በመዉጣት ችግሮቻችንን በሰላም መፍታት መማር አለብን» ሲሉ ነበር፣ ለአገር በሚጠቅሙ በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢሕአዴግ ጋር ለመስራት፣ ያሉትን ልዩነቶችን በዉይይት ለመፍታት አንድነት ፍላጎት እንዳለው የገለጹት።

ይህ የአንድነት ዘመናዊ፣ የሰለጠነ፣ የፍቅርና የመግባባት ፖለቲካ፣ በኢህአዴግ ዉስጥ ያሉ ሞደሬቶችን ሳይቀር፣ አብዛኛዉን ኢትዮጵያዊ ያስደሰተ ቢሆንም፣ ስልጣኑን በያዙ በኢሕአዴግ አክራሪዎች ዘንድ ግን የተገኘዉ የአጸፋ ምላሽ የሚያስደስት አይደለም። ገዥዊ ፓርቲ ኢሕአዴግ ፣ አሁንም የአንድነት ፓርቲን እንደ ጠላት በማየት ፣ አንድነትን ለማዳከም አሳዛኝና አሳፋሪ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ነዉ። ወደ መሃል መጥተዉ፣ ለዉይይት ይዘጋጃሉ ብለን ስንጠብቅ፣ ጭራሹኑ እያከረሩ ነዉ። የታሰሩ የሕሊና እስረኞቹን ይፈታሉ ብለን ስንጠብቅ፣ ጭራሽ የጊዜ ገደባቸው የጨረሱ እንደ አቶ በቀለ ገርባ ያሉ እስረኞችን አንፈታም እያሉ ነዉ። ጭራሽ ሌሎች ሰላማዊ የፖለቲካ ታጋዮችን በተለይም ከአንድነት ፓርቲ እያሰሩና ለማሰርም እየተዘጋጁ ነዉ።
ለረዥም ጊዜ የአንድነት ፓርቲ ዋና ጸሃፊ ሆነው ያገለገሉትና፣ አሁን ደግሞ የብሄራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት፣ አቶ አስራት ጣሴ በአሁኑ ጊዜ ታስረዋል። የታሰሩት በአንድ ጋዜጣ ላይ፣ «በፍርድ ቤቶች ፍርድ ማግኘት አይቻልም» በማለታቸው ነዉ። እዉነትን በመናገራቸው።
የአንድነት ልሳን ፍኖት ጋዜጣም፣ በፍትህ ሚኒስቴር ዉስጥ ያሉትን ምንጮች በመጥቀስ፣ በኢሕአዴግ ጽ/ቤት ትእዛዝ፣ አቶ ዳንኤል ተፈራ እንዲሁም ሌሎች የአንድነት አመራር አባላትን ለማሰር የክስ ሰነድ እንደተዘጋጀም ዘግቧል።
ይህ የአንድነት አመራር አባላትን ለማሰርና ለማዋከብ የሚደረገዉ ጥረት፣ ምክንያቱ አንድና አንድ ነዉ። ኢሕአዴግ፣ የአንድነት ፓርቲ አሰላለፍ በጣም ስላሰጋዉ፣ መሪዎችን በማሰርና የፓርቲዉን አባላትና ደጋፊዎች በማስፈራራት፣ ፓርቲዉን ከወዲሁ ለማዳከም ነዉ።
የአንድነት ፓርቲ በአሁኑ ወቅት፡
1) ከሰማያዊና ከኤዴፓ በስተቀር፣ ከበርካታ ደርጅቶች ጋር ለመዋሃድ ትልቅ ሥራ እየሰራ ነዉ። በተለይም ከመኢአድ እና ከአራና ጋር ዉይይቱ ሥር የሰደደ ይመስላል።
2) በአድዋ ከተማና በአዲስ አበባ፣ የአድዋን ድል በአል ለማክበር፣ እንዲሁም፣ በአማራዉ ክልል የሚኖረዉን ሕዝብ የተሳደቡ የብአዴን አመራር አባል ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚጠይቅ፣ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በባህር ዳር ለማድረግ አቅዷል።
3) የሚሊየነም ድምጽ ለነጻነት ክፍል ሁለት ዘመቻ በቅርብ ጊዜ ዉስጥ ይፋ ለማድረግ በዝግጅት እንዳለ ይነገራል።
እነዚህና የመሳሰሉት የአንድነት እንቅስቃሴዎች፣ የፖለቲካዉን አስተላለፍ በእጅጉ የሚቀየሩ እንደመሆናቸው፣ በገዢው ፓርቲ ዉስጥ ያሉ ፖሊሲ አዉጭዎችን ማሳሰቡ አያስገርምም። አንድነት፣ የኢሕአዴግ ስርዓት ለመቀየር ና ለዉጥ ለማምጣት ሰላማዊና ሕግን በተከተለ መንገድ ስራዉን ሲሰራ፣ ኢሕአዴጎችም በስልጣናቸው ለመቆየት የራሳቸዉን ሥራ መስራት የሚጠበቅ ነዉ። የሚያወቁትና የለመደባቸው ደግሞ ዜጎችን ማሰርና ማዋረድ ስለሆነ ይኸዉ እያሰሩ ነዉ።
ይህ በኢሕአዴግ፣ አመራር አባላቱን በማሰር አንድነቶች ለማስፈራራት የሚደረገዉ እንቅስቃሴ የሚሰራ ግን አይመስለኝም። የአንድነት ፓርቲ መሪዎች፣ ትግሉን ሲቀላቀሉ፣ እንደሚታሰሩ፣ ሊገደሉ እንደሚችሉ በማወቅ ነዉ። በብርቱካን ሚደቅሳ፣ በአንዱዋለም፣ በእስክንደር ነጋ …የሆነዉን ያውቃሉ። ነገር ግን ከምቾታቸዉና ከጥቅማቸው ይልቅ አገራቸውን ያስቀደሙ በመሆናቸው ፣ ለእስራቱም ሆነ ሊመጣ ለሚችለው መከራ የተዘጋጁ ይመስላል።
እንግዲህ መልእክቴ ይሄ ነው። ኢሕአዴግ በአንድነት ፓርቲ ላይ በአንድ በኩል የያዘዉን ጠመንጃ ተጠቅሞ ጫና ሲያሳደር፣ አገር ቤት ያሉ ታጋዮች ሕይወታቸውን መስመር ላይ አድርገዉ ዋጋ ለመክፈል ሲዘጋጁ፣ እኛ ደግሞ የአንድነት ፓርቲን ከመቼዉም ጊዜ በበለጠ በመርዳትና በመደገፍ ማጠናከር አለብን። የአራት ኪሎ ባለስልጣናት በያዙት ዱላ ይተማመናሉ። አንድነት፣ በኔ እና በ እናንት፣ በኛ ፣ አገር ቤት ባለነውም ሆነ በዉጭ በምንኖር ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ጉልበት ይተመመናል።
እንግዲህ ጨዋታዉ ተጀምሯል። ፊሽካዉ ተነፍቷል። ተስፋ ቆርጠን፣ «አይቻልም» ብለን ሜዳዉን ለቀን ከወጣን በፎርፌ ዜሮ ገባን ማለት ነዉ። ነገር ግን ዝምታ፣ ተስፋ መቁረጥ አይሁን። ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣ።
ለኢሕአዴጎች ይህንን እላለሁ። «ጸሃይ ሳትጠልቅ ቀናዉን ነገር ማድረግ ተማሩ። ትንሽ እንኳ የሰላም ነገር ልባችሁ ይግባ። ይህ በሌሎች ላይ የመዘዛችሁት ሰይፍ መልሶ እናንተኑ ነዉ ስለሚበላችሁ ሰይፋችሁን ወደ ሰገባው መለሱና ለሰላም እጆቻችሁን ዘርጉ»

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.