„ቃል የዕምነት ዕዳ ነው!“ በልጽጓል! (ሥርጉተ ሥላሴ የሳተናው አምደኛ)

ከሥርጉተ – ሥላሴ 12.03.3018 (ከጭምቷ – ሲዊዘርላንድ።)

„እግዚአብሄር ብርሃኔና መድሃኒቴ ነው? የሚያስፈራኝ ማን ነው? እግዚአብሄር የሕይወቴ መታመኛዋ ነው፤ የሚያስደነግጠኝ ማን ነው? (መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፳፮ ቁጥር ፩)
ይድረስ ለተከበሩ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕ/ ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው።

ባህርዳር።

 • መቅድም።

„ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ እና ሌሎች 10 ፍርደኞች ዛሬ ከእስር ተለቀቁ፡፡ ከአማራ ቴሌቪዥን ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡“

 • እፍታ።

ጤና ይስጥልኝ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዴት ሰነበቱ? ደህና ነዎት ወይ? ዛሬ እንደ ቀደመው የውስጥ ቁስለት ህመምን አይደለም  የኮለምኩት። ንጡር ምስጋና ነው። ምስጋናዬም ከልቤ ከውስጤ – ለብጡልነት ይድረስልኝ ብያለሁኝ። ግልጽና ቀጥተኛ ስብዕናዬ የአቋሜ አቅም መቋሚያ ነው። የግንባር ሥጋነቱን ከነፈተናው ስቀበለው ደስ ብሎኝ አስመችቼው ነው። ከምቾት ድሎት ይልቅ ጨከን ያለውን የትግል መስመር ደፍሬ እምገባበት ምክንያቱ መጠራቅቅ በበዛበት መስክ ሲሆን የሚገኘው የህሊና ትሩፋት ረቂቅ በመሆኑ ነው። ይህ ክትር የለሽ ምርጫ ሌላ የአቅም ልዩ ፕላኔቴ ነው። እኔ ህይወቴ ብዬ የያዝኩት ምርጫ ሌላው በርቀት፤ ወይንም በግምት፤ ወይንም በስማ በለው ሊያው፤ ሊትለመው ወይንም ሊመትረው አይችልም። አፈጣጠሬም ለዚህ ስብዕና መሆኑን እማውቀው እኔው ብቻ ነኝ። በዚህ ሰብዕና ውስጥ ጥራዝን አለፍ ያሉ ዱላዎች ቢኖሩም፤ እነሱም ሊኖሩ እንደሚችሉ ስለማምን እንደ አመጣጣቸው አስመችቼ አስተናግዳቸዋለሁ። ደስ ብሎኝ። ደስታን በመከራ፤ ደስታን – በትችት፤ ደስታን – በድንበር ዘለለ ዘለፋ ማግኘት መቻል ራስን በጽናት፤ ህሊናን በዓላማ ብልህነት ይመግባል። ደስታ በመልካም ነገሮች ብቻ አይፈጠረም ወይንም አይገኝም – ለእኔ። ደስታ በደመና እና በወጀብ መካከልም ይገኛል ባይም ነኝ። በወጀብና በደመና መካከል የሚገኘው ደስታ መኖሩን መቀበል፤ በዛም ለመንፈስ ስንቅነት ጥቅም ላይ ማዋል የባለቤቱ ነው ብዬም አምናለሁኝ።

 • ሰዋዊነት።

የአማራ የማንነት አባት ቀደም ባለው ጊዜ ትውልድ የማይተካቸው ለአማራ ማንነት ፈቅደው ራሳቸውን የገበሩት፤ በኮሯት የሆኑት፤ ሰብዕዊነትን ከራሳቸው ጀምሮ በመተርጎም በሥነ – ልቦናዊ አቅም ወደ ላቅ የደረጃ ድርጊት ያሸጋገሩት፤ ከዚህም ባለፈ የህይወት ዝክረ ቋሚ ትውፊት በህሊና ውስጥ የገነቡት ቅዱሱ ፕ/ አስራት ወልደዬስ ናቸው። ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ዜናውን ሥሰራ በ100 ዓመት የማይገኙ፤ ትውልድ ከቶውንም የማይተካቸው ብዬ ነበር። ለእኔ የሰባዕዊነት ተሟጋችነት ቅድስና የሚጀመረው ሰው ራሱ „ሰው“ ሆኖ ስለመፈጠሩ አምኖ ከራሱ መጀመር ሲችል ብቻ ነው። የሰው ተግባር መነሻው „ከሰው“ መጀመር አለበት። የሰወች ማህበር ነው ዓለምን፣ ሀገርን፣ አህጉርን የሠራው። የሰዎች ማህበር ነው የጸሎት ዓውዶችን ቤተ – አምልኮችን የፈጠረው። የሰዎች ማህበር ነው ፖለቲካን የሰዬመው። የሰዎች ማህበር ነው ሥልጣኔን የተካነበት የሰለጠነበት።

ከሰው ተፈጥሮ የጀመረ መንፈስ ሁልጊዜም፤ ምንግዜም የፈጣሪ ጥበብ የገባው ነው። ወይንም ቅብዕ ያለው ነው። ፈጣሪ ሰውን የፈጠረበትን አምክንዮ የመተርጎም አቅም ያለው ፍጡር የተሰጠው ባለሙሉ መክሊት መስቀል ነው። „መስቀል መዳኛ፤ መስቀል መጽናኛ፤ መስቀል ሃይል“ ሲሆን፤ መስቀል የተፈጠረው ለሰው ልጅ ጥበቃ መሆኑን ልብ ያለ ባለልብ ብቻ ያውቀዋል። እንደ እኔ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ዶግማ „መስቀል“ የሰው ልጅ የምህረት አዋጅ ነው። የሰው ልጅ ጥበቃ ያስፈልገዋል። የመስቀል ክህሎትም ሆነ ሰማያዊ ሚስጢር ይህው ነው። ለሰው ልጅ የመንፈሳዊ ህይወቱን አጋይስት ዓለሙ ሥላሴ ሠራዊተ መለዕክትን አሰለፈው ሲያስጠብቁት፤ በገህዱ ዓለም ደግሞ የምድራዊ ህይወቱን የሚጠብቁ ጠባቂወቹን የሚፈጠሩት፤ የሚባረኩት፤ የሚቀደሱት ፈጣሪ በቀባው ነፍስ ነው። እኔ የቅዱሱን አባት ፕ/ አስራት ወልደዬስን እማዬው ከዚህ አንጻር ነው። ነፍስን ለመታደግ ራስን ከመማግድ በላይ ቅድስና ስሌለ። አማኑኤልም እኮ ለእኛ ሲል ነው የቀራንዮ፤ የጎለጎታን አሳር የተቀበለው።

አንድን ማህበረሰብ ነጥሎ፤ ዘንጥሎ፤ ለይቶ፤ አግልሎ ከተፈጠረበት አካሉ መንቀል ነበር የወያኔ ሃርነት ትግራይ እና የግብረ -ማህበሮቹ ተልዕኮ። ቅዱስ አባት ፕ/ አስራት ወልደዬስ ይህን ሰይጣናዊ መንገድ „አይ“ በማለት አደባባይ ወጥተው የሞገቱት፤ ራሳቸውንም እንደ አብርሃም በግ ግብር የሰጡበት ምክንያት ለሰው ልጅ ስላላቸው ክብር እና ልዕልና ነው። ዛሬ እንደምንሰማው የሰው ልጅ „በአጋጣሚ“ አይፈጠርም። „በአጋጣሚ“ ሊጠፋ ወይንም ሊከስም አይችልም። የሚያጠፋው ወይንም የሚያከሰመው „አይ“ የሚል ባሊህ ሲያጣ ብቻ ነው። ጸረ ሰብዕ የሆነ ዲያቢሎሳዊ መንፈስ የሰው ልጅ፤ ወይንም አንድ ማህበረሰብ ሊከስም የሚችልበትን ስልትና ስትራቴጅ ቀድሞ አወቆ ሲንቀሳቀስ፤ መከላከያ ካለበጁለት አንድ እንስራ ውሃ ቀስ በቀስ ሲጠጣ ሙጥጥ ብሎ ያልቃል። አሁን ያለው የኦሮሞ ማህበረሰብ ዕጣ ፈንታንም እኔ እማዬው ከዚህ አንጻር ነው። በኮንሶ፤ በአማራ ማህበረሰብ ያለው የዘር ጥፋት፤ ከቀዬ የመነቀል መከራ ቀስ እያለ፤ ኮተት እያለ፤ በኦሮሞ ማህበረሰብ ዘመቻውን ባላባራ ሁኔታ በአደባባይ እያዬን ነው። ቀደም ባለው ጊዜ በተነጠለ እየነጠለ ቀስ እያደረገ፤ ሳይስጠጣ በስልታዊ ሁኔታ ነው አሁን እኮ የጅምላ ግድያኑ አና ብሎ ይዞታል፤ በለመደበት አማራን ባረደበት እጁ – ወያኔ ሃርነት ትግራይ። መቼ ስለነገ ህጻናት ስለዘሮቹ ሊያስብ እንደሚችል አይታወቅም። ከበደል ላይ በደል በመጨመር ያከረዋል።

የጨለንቆው፤ የሙያሌ በቀጥታ ከዘር ጥፋት ጋር የተሳሰረ ስለመሆኑ ለዘመኑ መስካሪ አይስፈልገውም። ሰውን ያህል ታላቅ እጹብ ድንቅ ክቡር „በአጋጣሚ፤ በተሳሳተ መረጃ“ በሚል ነው የተጠቃለለው። ይፈጠራል እንዴ ሰው በአጋጣሚ? የሰውን ልጅን የሚፈጥረው አጋጣሚ ነውን? የጋንቤላው የመሬት ወረራ በአጋጣሚ እኛ መሳፍንቶች እንበዛለን ተብሎ በተደመጠበት የትግራይ ሥርዕዎ መንግሥት አሁን ደግሞ በነበረው የግብረ አራዊት፤ የታቀደ የበቀል ማወራረጃ ትልም „በአጋጣሚ፤ በተሳሳተ መረጃ“ ሲባል ምን ያህል አረመኒያዊነት ኢትዮጵያ ላይ እንደ ነገሰ ማዬት ይቻል። ሰው ከዕቃም፤ ከእንሳሳም በታች ህጋዊ ዕውቅና ያጣባት ዘመን። „አጋጣሚ?“ እንዴት? „አጋጣሚ“ ስለምን ሊሆን ይችላል? አጋጣሚ ከሆኖ ከንግሠ – ከተማቸው አንድ ነፍስ በ27 ዓመቱ የአገዛዝ ዘመን ስለምን መሰል ክስተቱ አልተፈጠረም? አጋጣሚ ከሆነ። እዛስ ስለምን የጅምላ ጭፍጨፋ በአጋጣሚ መሬታቸው ላይ መነሻ አይኖርም? አጋጣሚ ነፍስን የመፍጠር አቅም አለውን? አናሳው የትግራይ ቡድን ሰፊውን ማህበረሰብ አማራ እና ኦሮሞን በጠላትነት ፈርጆ ቀስ እያሉ እንዲከስሙ፤ ባይቻልም የሥነ – ልቦና አቅማቸው እንዲሰለሰል፤ እንዲፈልስ፤ እንዲሰበር እያደረገ ነው። ፍርሃት ውስጥን ከተቆጣጠረ ምርኮኛ ዜጋ ያደርጋል። ህሊናም ዕቁር ይሆናል። ሂደቱ ይሄው ነው … የትም ቦታ፤ በዬትም ሁኔታ „አጋጣሚ፤ በተሳሳተ መረጃ“ የሚል ሽፋን „ይቅርታ በሚል የቧልት ቅርፊተ ግዴለሽነት“ ሲቀርብ አንጎል እዳሪ አዳሪ ስለመሆኑ አስተውለንበታል። ይሄ ነው ያያኔ ሃርነት አዲሱ አመራር የሥጦታ ስጦ የሞት ገብያ … አንድ ቀን እንኳን ያለረፍት ሚሊዮን ሲፈናቀል … ሲሞቱ በቀያቸው ሲሳደዱ … እግዚኦ! እማማ ስላንቺ።

ወደ ቀደመው ስመለስ ያ ቅዱስ አስራት የመሰረተው የህሊና ጉልትን ያደመቀው፤ ያበለጸገው፤ ያፋፋው፤ መሰረት ያስያዘው፤ አደራ ተረካቢው ከሚሊዮን ድርጅት በላይ፤ ከሰፋ መዋቅራዊ አደረጃጃት በላይ ኮ/ ደመቀ ዘውዴ የተፈጠሩባት ዕለት ርህታዊ ናት። የአማራ የህልውና ተጋድሎ መሥራቹ የኮ/ ደመቀ ዘውዱ ፍጥረት ለመንፈስ ቅድስና፤ ልዕልና ወደ ራስ ለመመለስ ቅኔ፤ የአቋማም ዝማሜ ነው። አዲስ ኪዳን በጀግንነት በማህሌተ – ተጋድሎ። ኮ/ ደመቀ ዘውዱ ለሰዋዊነት መንፈሱ ናቸው። አማራም ሰው ነውና። በዜግነትም ደረጃ አማራም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነውና።

የማከብረዎት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ይህን የሰው መንፈስ ይዞ የተነሱትን ኮ/ ደመቀ ዘውዴ በደረሰባቸው ግፍ እና መከራ ከጎኑ ስለነበራችሁ እጅግ አድርጌ ላመሰግናችሁ እውዳለሁኝ። በተለይም የእርስዎን አመራር ለሚያከበሩ፤ መንፈሳቸውን ከመንፈሰዎት ጋር አዋህደው ብቻዎትን እንዳይሆኑ በሚተጉት፤ በሚያከብሩዎት የእርስዎ የህሊና ደማዊ ቤተኞች ኮርቻለሁኝ። አቶ አለምነህ መኮነንን ሳይጨምር። የሴራውን ፊሽካ አቶ በረከት ስምዖን ሳያክል፤ ትግራዊነታቸው የሚቆላቸው እና የሚፈጫችውን አቶ አዲሱ ለገሰን አያካትም ምስጋናዬ። እነሱ የተፈጠሩበት ቀን የአማራን መንፈስ በግፍ ለመነቀል በቀዩ የታወጀበት ዕለት ነበር። ስለርግማን ናቸው።

 • አርበኝነትን በእኛ ዘመን።

ይህ አንበሳ የቀደሙትን የአባት እናቶቻችን አርበኝነት በዚህ ዘመን በጸጋው ልክ ለድል ያበቃ ውሳጥችን ነው። እንደ ቴዲ፤ እንደ ገልሞ፤ እንደ ገብርዬ፤ እንደ በላይ፤ እንደ አሞራው ውብነህ፤ እንደ ቢተወደድ አዳነ፤ እንደ ሻ/ አጠናው ዋሴ፤ እንደ ጄኒራል ሃይሌ መለስ፤ እንደ አርበኛ ጎቤ ወዘተ …  ከእናንተ በረጅም ርቀት ማይል ብንገኝም ግን ቀያችን ላይ የሚፈጸመው ማንኛውም ጥቃት እና ወራራ የውስጣችን ነዲድ ነው፤ የህሊናችን ቋያ ነው። መቼውንም ለድርድር ሊቀርብ የማይገባው የወገራ፤ የስሜን፤ አሁን በቅርቡ የምንሰማው የጎንደር ዙሪያ አውራጃ፤ የወሎም የራያ ጉዳይ „የቃል የዕምንት የዕዳ ነው“ የገዘፈ ዕዳ ነው።

ይህን የአዳራ ቃል ሲታሰብ በዚህ ደቂቃ እና ሰከንድ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በወረራ በያዛቸው ቦታዎች ያ ጉልህ የአማራ ማንነት በጠላት እጅ ወድቆ አቧራ ለብሶ፤ ፍዳውን እዬከፈለ መሆኑን ሲታስብ የውስጥ ረመጥ ነው። የአፓርታይድ ታሪክ እንቃኘው ዘንድ ግድ ይለናል። „በሰው ቁስል እንጨት … “ ሆኖበት ይህ ስቃይ ሊሰማቸው የማይችሉ እንዳሉም እናውቃለን። ከ43 ዓመት በላይ በዘለቀው የዘር መተራ ጉዳይ በመቼውም ጊዜ እና ሁኔታ ሊፋቅ የማይችል፤ በመቼውም ጊዜና ሁኔታ ይሁን/ ይቅር የማይባል የህሊና ነበልባል በደማችን ውስጥ አለ። ምህረት ባይፈራም / ቢፈቀደም ቃለ ወንጌል ቢሆንም ግን ምህረት ዕውነትን ሲጎርስ ብቻ ነው የሚንቀለቀለው እልህና ቁጭት ቃጠሎ ሊበርድ የሚችለው። በተንጠራራ ትዕቢታዊ ተራራ ግን ይህ ግፍ እና በደል በቀላሉ፤ በግብር ይውጣ የሚፋቅ አይሆንም። ይህ ታሪካዊ ዘመን እናንተን የገዱን መንፈስ ከጋለ ምጣድ የሚያስቀምጥ ብቻ ሳይሆን ትልቁ የተጋድሎ ግማድ ነው። መቀዳላ ላይ ያለው ጩኸት አሁንም እናንተን በክብር እና በአርምሞ ይጣራል። „በርስት እና በሚስት“ ቀልድ የለም።

ደም የሚደርቀው እንደ አባት አደሩ በፍቅር የበደለ ክሶ፤ የወረረውን አሳምሮ ሲመልስ ብቻ ነው። ያ ካልሆነ ለምንግዜውም ቢሆን ሰላም እና ምህረት ይመጣል ተብሎ የሚታሰብ አይሆንም። ደም ደም ነው። መሬትም መሬት። ማንነት ገብያ ላይ በፍንጃል ተለክቶ የሚቸበቸብ የጉልት ሸቀጥ አይደለም። ማንነት ማንም እንዳሻው ቆርሶ፤ ለክቶ፤ ሸንሽኖ የሚሰጠው የጨርቅ ቦንዳ አይደለም። ማንነት መንፈስ ነው። ማንነት ውስጥ ነው። ማንነት የደም ቋንቋ ነው። አማራነት አይሸመትም፤ አይቃናም! አማራነት የመፈጠሩ ነገር ቅኔያዊነት እና የሰማይ ሚስጢር ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ቀመር ማዘጋጀት፤ ስሌት ማስላት፤ ድንጋጌ ማውጣት አይቻልም። ፈጽሞ! አማራነት ሰዋዊ ውሳኔ ተጠማኝ አይደለም! አማራነት የፖለቲካ ውሳኔ ውራጅ አይደለም! አማራነት የከንቱ ውዳሴ ከንቱ መረማማጃም አይደለም!

በማንነት ላይ የሰጪም የተቀባይም ግጥግጥ የለም። ማንነት ከማንም እና ከምንም የሚገኝ ችሮታ አይደለም። በማንነት ውስጥ ያሉ ነገሮች በዛ ማንነት ውስጥ ያሉ ንዑድ መለያዎች ናቸው። በዛ ማንነት ውስጥ ያሉ የፊደል ገበታዎች ናቸው። በዛ ማንነት ውስጥ ያሉ የህይወት ደማዊ ፍልስፍናዎች ናቸው። በማንነት ውስጥ እኔ እንደ ሌላው „ሰው“ መሆኔ የሚረጋገጠው አጅግ ጥልቅ እና ረቂቅ ፍሬ ነገር አለው። አይታይም፤ አይጨበጥም፤ አይዳሰስም። ያ ፍሬ ነገር በትውስት የሚገኝ ወይንም በትውስት የሚሰጥ አይሆንም። ማንነት የሰው ለስው ሽልማት አይደለም! ማንነት የትውስት ሳይሆን የራስ መሆንነት ውስጥነት ነው። አማራነት በአማራነት ውስጥ የሚገኙ ማናቸውንም ንጥረ ነገሮች ነጥረው፤ በልጽገው በአማራው ደም ብቻ የሚገኝ ነው።

ኢትጵያዊነትም በወሉ ማንነት አንዱ ከሌላው በጋራ የሚገራው የራሱ የሆነ ዕሴታዊ መስተጋብር አለው። „ጀግንነትን“ ብንወስድ በወል ማንነት ውስጥ ያለ የስሜት ወኔያዊ መንፈስ ነው። በዚህ የጀግንነት አፈጻጻም ውስጥ በቃሉ ነባቢት ያሉ የዓለም ዜጎች የሚጋሩት ቢኖርም ኢትዮጵያዊ ጀግንነት ግን በምርኮ የተፈጠረ ባለመሆኑ የነፃነት ሥነ – ልቦናዊ አቅሙ ኢትጵያ ውስጥ ላይታይ ይችላል። ውጪ ሐገር ግን ቁሞ ሲያናግረን፤ በደማችን ርቅቅና ልንጨብጠው – ልንዳስሰው – ልናገኘው መቻላችን አይተነዋል። ወስጣችን ይንቀሳቀሳል። በደማችን ቃል አንብበነዋል። እኔ እና አንዲት ኬኒያዊ አኩል የሥነ – ልቦና አቅም የለንም። እነሱ  „እኔ“ የሚሉት አንዳችም የባህል፤ የወግ፤ የልማድ፤ የስሜት ልዕልና ዘይቤ ስሌላቸው አንገታቸውን የሚደፉባቸው መስኮች ራሱን የቻለ የጥናት እና የምርምር ተግባር ያሰራል፤ በተሳትፎም ቢሆን እውነት ለመናገር ያ የነፃነት ሙቀት አሳድጎ የሰጠን ብዙ እጅግ ብዙ ነገር አለ። የመኖር ቃና፤ የነፍስ ልዩ ዜማ ነው ኢትዮጵያዊነት።

ወደ አማራነት ስመለስም የራሱ የሆኑ ልዩ ጣዕም ያላቸው ምክንያታዊ አቅሞች አሉን። ስለዚህ ይህን የማንነት ተፈጥሯዊ አቅም መዳፈር ልክ ያጣ ትዕቢት ነበር። ቤተሰቦቼን አውቃለሁ። እንኳንስ ትናንት ዛሬ በጉርብትና አቅም እንኳን አንድም የወልቃይት፤ የጠገዴ፤ የአርማጭሆ፤ የድብ ባህር፤ የአዳርቃይ፤ የአዲረመጽ፤ የማይጸምሪ፤ የዛሪማ ሰው ትግራይ ሄዶ ቤት አይሰራም። በፍጹም አይታሰብም። ትግራይ ሄዶ ኑሮውን አይመሰርትም – ጎንደሬ። ሆኖም አያውቅም። ዘረፋው የዚህ ሁሉ ነው። ትውልድን ማቋረጥ መቁረጥም። ከዚህ ታልፎ ክልላዊ መነግሥት እንደ ተራ ወንበዴ በረት ገልብጦ በቀዬ መብት መዳፈር ደግሞ እጅግ የከፋው/ የከረፋም የአባት/ እናት አያቶቻችን ክብርን በፍጹም ሁኔታ የተዳፈረ ነበር። ይህን የዘመናት የታሪክ ውል ነው በጀግንነት የቀለመው። ይሄ የልብ አድርስ ታሪካዊ ተጋድሎ ርቀቱ፤ ጥልቀቱ፤ የመንፈስ ሃብትነቱ ልቅናው የማንነት ዓዕማደ ሚስጢር ነው። በድርጊት በዘመኑ ለተተኪው ትውልድ ያወረሰው ታላቅ ቤተ – ትውፊት ነው። ዕውነት ለመናገር ኮ/ ደመቀ ዘውዱ የትናንት፤ የዛሬ፤ የወደፊትም የአማራ ትውፊት መሃናዲስ ናቸው። ሊንክ። አገናኙት ትውልዱን። የቅድመ – የማዕከለ እና የድህረ ቅርስ ውርርሱን ጸጥ ባለው በተረጋጋ ልቦና ፈጸሙት። „ቃል የዕምነት ዕዳ ነው“

ጀግነንቱ ልለካው ብል የሚሆን አይደለም። ልምትረውም ብል ድፈረት ይሆንብኛል። ለዚህ ትውልድ ታላቅ የሆነ አማራዊ የመንፈስ ተቋም ሆኗል። አማራነት ተጠቅልሎ በብልኮ፤ ተሸፍኖ ባካሊም ብቅ እንዳይል፤ ሥነ – ልቦናው ተቀብሮ አንገቱን ቀርቅሮ ፤ ተኮርኩዶ የተያዘበትን ጉማም ዘመን ጎህ እንዲቀድ ያደረገው „ታምረ – አማራነት፤ ግድለ አማራነት“ ነው ለዚህም ብርሃኑ ኮ/ ደመቀ ዘውዱ ናቸው። እናታችን ክርስቶስ ሰምራ ግድሏ የተጻፈው በዚህ መሰል ትንግርታዊ የመንፈስ ተግባረ – ክህሎተ – ቆመስነት ነው። የዋልድባ አበርንታት ገዳም አባቶቻችን ገድላትን የጻፉት፤ ታቦት የቀረጹት በዚህ መሰል የጽናት መስቀልነት ነው። ለእኛ ይህ አንበሳ መስቀላችን ነው። ለእኛ ይህ የሚሊዮኖች ድምጽ ቅዱስ መንፈሳችን ነው። ሜሮናችን ነው። ለእኛ ይህ ድንቅ ፍቅር የሆነ ወንድም የአማራነት ስብከተ – ወንጌላችን ነው። የአማራ የዬኔታ ጉልላት መርጌታችን ነው። ይህን መንፈስ እንዲገለታ ስላልፈቀዳችሁ፤ በጠላት እጅ ወድቆ መሳቂያ ሳታደርጉን በመቅረታችሁ እናንተም መመኪያችን ኩራታችን ናችሁ። ተባረኩ! Praud! Stolz!

የቃለ ምልሱን ጭብጥ ስሰማው እንዴት የነባቢቴ ሥህነ – ግርማ ሞገስ እንደሆናችሁ። ብሩክ ቀኖች። ጎንደር ለሚገኘው የጥበቃ አካላትም ልዩ ፍቅር እና አክብሮት አለኝ። ይሄ ነው የቀደምቱ አደራ። የህግ አካሉ የከፈለው መስዋዕትነት ጣዕሙ የእዮር ነው። ዝቅ ብዬ ምስጋናዬን አቀርባለሁኝ። ይሄ ነው ለእውነት መቆም ማለት። ይህ ነው ለሚዛናዊ ፍትሃዊ አስተዳደር መትጋት ማለት። ጀግናችሁም አንገታችሁን አላስደፋችሁም። የሆነውን ሆኖ ነው ያዬነው። በዝምታው ውስጥ አክበሯችኋዋል። መንፈሱ አልተክለፈለፈም። ዕውነት እንዲህ ስታበራ በዘመን ታዬች። ገለዕድ ተራራ ላይ የአዳም ሰገድ እያሱ ታቦት የመሸከም ሚስጢር፤ የቅድስት ማራያሚያዊት መንፈስ ዲማ የደካ የተራራው ስብከት ጥሪ እና አጽመ ርስት የደበረ ብርሃን ሥላሴ ብርሃናማነትን አዬሁት። በአማራ ተጋድሎ ነገረ ጎጃም ታሪካዊ መጸሐፍ ነበር። ዓፄ በከፋ በእውነት የተነሱ ያህል ነው የሚመስለኝ። በእያንዳንዷ ቀን ጎጃም መሬት የታዬው አማራዊ ጽናት ቀስተዳመና ነው የእትብቱ ውርርሱ ቅብብሉ። ለዚህ ለጠራ ተጋድሎ መሪው እስኪፈታ ድረስ የሚሆነውን በስክነት እጠብቅ ነበር። በጠቅላላ በነበረው የእስረኞች ከፊል መፈታት ሁኔታ ከኖርንበት ዘመን እጅግ የቀደመ ዘይቤ ማንዘርዘሪያ አይተንበታል። ብክነታችን ቀንሷል። አቅማችን እንዳናባክን ቁሞ ሰብኮናል። ባልተገባ ቦታ ላይ መዋለ ህሊናዊ ሁኔታችን እንዳይደክም፤ አላስፈላጊ የሂደት ፍሰት እንዳይገጥመው ቁሞ አስተምሮናል።

እኔ ነገር ሰቲት ሁመራን ስለማውቀው ያ መንፈስ እንዲቋረጥ የሆነበትን ዘመን ሁሉ በህሊናዬ ማቅ ለብሼ ኑሬበታለሁኝ። ሳድግ አውቀዋለሁኝ። ሥራም ይዤ ከፈረሰ በኋዋላ ለፌዲራሊዝም አፈጻጻም ነበር ወደ እዛ ኢሠፓ ፓርቲዬ ልኮኝ የነበረው። ያን ጊዜ የቤተሰቦቼን መኖሪያ አካባቢ ስጎበኘው የልጅነት ጊዜዬን በምለስት አስቤ ዕንባዬን አፍስሻለሁኝ። አዎን! ሰቲት ሁመራ ማዕዛውን ጠጥቼ አድጌያለሁ። በፍቅሩ ወተት ጎልምሻለሁኝ። ተለክቶ በማይችለው አዱኛ እና ቤተሰባዊ በረከት ተባርኬበታለሁ። በዘመነ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ዘረፋው የመንፈስ ነው። ወረራው የህሊና ነው። ቅሚያው የነባቢት ነው። ስለዚህም ነው የሚያርመጠምጠኝ። ራህብን ለማያወቅ ሰው „ራህብ ምንድን ነው?“ ተብሎ ቢጠዬቅ መልሶ ይጠይቃል። ግራምጣን ብቻ የምታውቅ አንዲት ሴት፤ የዳጉሳ እሸት ቢወሰድላት፤ ወይንም አክርማ ቢሰጣት ግራምጣ ሊመስላት ይችላል። ቋያው ለደረሰበት የሚቻል አይደለም።

 • የመሆን ሰንሰለቱ በባዕቱ።

„ይህን አላስደፈርም! መሬቱን ወረህ፤ ቀምተህ እና ዘርፈህ እኔንማ በቀዬ መጫወቻህ ልታደርገኝ አትችልም፤“ ብሎ በልበ ሙሉነት ለመከተ የዘመናት ጸሐይ ጥግ፤ ከለላ፤ ጋሻ እና መከታ ሆናችሁ በቀዬው፤ በህዝቡ ማህል፤ የህዝቡ ጠረን ሳይለዬው፤ የሚሊዮኖችን ሥነ – ልቦና ሳይጎዳ ጠብቃችዋል። የሚሊዮኖችን ጥቃት መልሳችኋል። የሚሊዮኖች ነፍስ አረጋግታችዋል። የሚሊዮኖች ማረከሻ ሆናችሁዋል። ዛሬ የመንፈስ ፍሬ ነገር ያለው ከዓይናችን ከኮ/ ደመቀ ዘውዱ ላይ ነው። ዓይናችን የጠበቃችሁበት መንገዱም፤ ስልቱም፤ ዘዴውም፤ ብልህነቱም፤ ማስተዋሉም ሚስጢሩ ለእኔ የዓደዋ ድል ያህል ነው። አማራም ኢትጵያዊ ነውና። ለዬትኛውም ኢትዮጵያዊ የድል እርከን ግማዱን የተሸከመው አማራ በደሙ፣ በአጥንቱ የከፈለው መስዋዕትነት እኩል ነው። ይህን የሚዘሉ ብልህነት የጎደላቸው ግለሰቦች እንዳሉ አውቃለሁ። የፖለቲካ አስተሳብ ብቻ ሳይሆን የሥነ – ተፈጥሮን ሚስጢር የዘለሉ ግዴለሾች ናቸው። ለመወደቂያቸው ገደል ስለሚምሱ፤ ቅጣቱን በራሳቸው ያወራርዱታል። ሌላ ሳይደርስባቸውም እርግማን በራሳቸው ላይ ጭነዋል …

እናንተን ድንቅ የሚያደርጋችሁ ይሄው ነው። ዘመን የጣለውን፤ ዘመን ፊቱን ያዞረበተን እንደ ቤተ – እስራኤል በዬሄደበት፤ ተሰደንም በመሳደድ ላይ የምንገኘውን ራሳችሁን የሚገልጸውን ማንነት ከመንደሩ ድረስ ሄዶ የተንጠራራውን የጥጋብ ታንቡር፤ „ዘመን የሰጠው ቅል“  እንዲሉ ሊያፍርበት ሲጋባ ወስዶ እንደ ሰማነው ጉድ፤ ከሰው ባልተፈጠረ የገዛ አራዊቱ፤ ጥፍር ሲያወልቅ፤ እንደ እንሳሳ ሲሸልት፤ ደም ሲያሸና፤ ሲሳደብ፤ አስኪ እዩዋቸው ወጣቱ ፖለቲከኛ አቶ አንዱአለም አራጌ፤  አባ ትርጉም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ የሰላም ጋዜጠኛው ተመስገን ደሳለኝ፤ የጣይቱ ውርሰ  ወ/ሮ እማዋይሽ ዓለሙ ሲፈቱ ከሌላው እስረኛ ጋር እሲከ በማስተዋል ሆናችሁ መዝኑት። በእስር ቤት ውስጥ ያለው የበለሃሰብእነት አያያዝ መመዘን፤ መለካት ይቻላል። ከዚህ ሁሉ የውስጥ ነበልባላዊ ሞገድ ጥቃት ነው ያዳናችሁት – ዘአማራን። አሁንም ቢሆን ለተፈቱት የተሻለ እንክብካቤ፤ ታስረው ላልተፈቱት ስቃያቸውን በቅርበት በመከታተል፤ ሰቆቃቸውንም በመጋራትም፤ ቤተሰቦቻቸውን በቅርብ በትህትና በማጽናናት፤ ጥቃቱን የእኔ በማለት ከስቃያቸው የሚገላገሉበትን ሁኔታ በግንባር ቀደምትንት ማስፈጸም ይጠበቅባችኋዋል። ፈተናችሁን አውቀዋለሁ፤ ዲያቢሎስ አቶ በረከት ስምዖን እንዳለባችሁ፤ በመሰቀል እምኑ። ዲያቢሎስ መስቀል ካዬ የበረዶ ግግር ይሆናል።

 • ክብረቴ።

ኮ/ደመቀ ዘውዱ በፊት ካከበርኳቸው በላይ አሁን አክብሬያቸዋለሁኝ። ከዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ንክኬ የሌላቸው መሆኑ ተጋድሎው በራሱ ማንነት ውስጥ ጻድቅ አድርጎታል። ከተፈቱ በኋላም ሰብሰብ ብለው መቀመጣቸው ይመስጣል። እዩኝ እዩኝ አላሉም። ርጋታቸው መስጦኛል። የማስተዋል ልካቸው አርክቶኛል። ሚዛናዊነታቸው አስተምሮኛል። የሆነውን ትክክለኛ ነገር ስለተናገሩ እኛንም ሚዛናዊ እንድንሆን አድርጎናል። እውነት ጥሩ ነው። ሌላው ግርማቸው አስፈሪነቱ ቅብዕ አለበት። አላሰፈሯችሁም ለተሟገታችሁላቸው በሙሉ። ይሄ በጣም ትልቅ ነገር ነው። ሰላማችሁን የውስጡን ለማወክ የሄዱበት ምንም መንገድ የለም። ከንቶ ውዳሴ አላሰኛቸው። በቀስታ እና በእርጋታ ክብሩን ይዘውታል። በስክነት ተቀባይነቱን አስጊጠውታል። ይሄ ብቻውን ያደረጋችሁትን የተጋድሎ ምዕራፍ ትክክለኛነት አውጆታል። የአሜሪካ ድምጽ ጋዜጠኞች መርማሪ ጋዜጠኞች ናቸው። ፈርፍረው ለበለሃሰብ ብርንዶ ማቅረብ ያሰኛቸዋል። ግን አልተሳካላቸውም። ስለምን ራስን የማዳን ተጋድሎው ታቅዶ የተከወነ፤ በሴራ የተደራጀ፤ ልጣፊ ኢጎ የነበረበት ሳይሆን በራሱ ጊዜ ዕውነትን የገለጠ የዘመን ትንግርት ስለሆነ። ማሰሩ ራሱ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ሊያፍርበት ይገባል። ከዚህ በኋዋላም አንዲት ቅንጣት ጊዜ ሳያጠፋ በዚህ ምክንያት የታሠሩትን በሩን ከፍቶ ካለምንም ምዝገባ እና ሂደት መለቀቅ ነበረበት። ግን ህሊና የለም? አልተፈጠረም። ማስተዋል ሰባራ ገል ነው። ለዚህ ሳይፈልግ ወንጀል ከበሩ ድረስ ሄዶ ሲጋፈጠው፤ ሲፈታታነው ካሳ ያስፈልገዋል። ለአማራ ተጋድሎ የማንነት ጥያቄ ክብር ሊሰጠው ይገባዋል። ንጽህናው ቅድስናው የታሪክ መቅድምነቱ ምጥቅ ነው። በራሱ ጉዳይ ተነሳ መስዋዕትነቱን በሌላ ልጣፊ ክስ ሰቃዩን እንደ ክርስቶስ ተቀበለ።

 • የክስ ጭብጥ የፖለቲካዊ ውሳኔ አስፈላጊነት።

ሌላው እኔ ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው መንፈስ ክልብ ሆኜ የማሳስበው ትልቁ ነገር የአማራ ተጋድሎ የክስ ጭብጥ አሁን በማያቸው ማናቸውም ሁኔታ የተስተካከለ ይመስላል። ነገር ግን ዘላቂ መሰረት ማስያዝ ያስፈልጋል። የአማራ ተጋድሎ ማንፌስቶው አማራነት ብቻ ነው። የአማራ ተጋድሎ የራሱ ማንነት አለው – የእኔ የሚለው። የአማራ ተጋድሎ ታሪኩን የሠራው እሱ ራሱ እንጁ ተጠውሮ በማንም እና በምንም ተፈብርኮ የተፈጠረ አይደለም። የአማራ የህልውና ተጋድሎ ዓላማ እና ግቡም የአማራነትን ህልውና በዝልቅነት ማስጠበቅ ብቻ ነው። አማራነትን ከጽንስ ጀምሮ ከሚደርሰበት ማናቸውም ጥቃት መከላከል ነው።

አማራነት ሰነዱ ያለው ከውስጥ ከሚመነጭ አማራዊ ስሜት፤ ደም፤ መንፈስ እንጂ ሰው በሚያረቀው ሰነድ ወረቀት አይደለም። አንድ አማራ ሲታሰር፤ ሲያዝ የአንድ ድርጅት ደንብ ፕሮግራም ከእጁ ሊኖር ይገባል። እጅ ከፍንጅ። የአንድ የፖለቲካ ድርጅት አባልነት ካለ ፖለቲካ ደንብ እና ፕሮግራም አይፈጠርም። ክሱ የግንቦት 7 አባልነት ነው። ፉርሽ መሆኑ ታይቷል። ይህ ፉሩሽነት ግን በመደዴ ተድበስብሶ መታለፍ አይገባውም። ግልጽ ፖሊሲ እና የፖለቲካ አቋም፤ ጥርት ያለ ውሳኔ የፌድርል መንግስቱ ሊያዝ ይጋባዋል። ይህም ብቻ አይደለም፤ ባልተገኙበት፤ ባልነበሩበት የአማራ ልጅ ብቻ እዬተነጠለ የባረዱ፤ የበቀል፤ ማወራረጃ ስለሆኑ ካሳ ያሰፈልገዋል። በተፈጥሮው ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ናዚያዊ ግፍ ተፈጽሞበታል። ይህን ቢሯችሁ በአጀንዳ ሊወያይበት ሊወስንበት ይገባል። ለዚህ ታላቅ አጀንዳ የማስፈጸም አቅም ከሌላችሁ አማራን ለቀቅ! የራሱን ደሙን መርጦ ይተዳደራል! ኤርትራ በማረተ ካቢኒዋ አማራን ያህል ማህበርሰብ ለመምራት፤ ለማስተዳደር፤ ለማደራጀት፤ ለማስተናበር አቅምም ወርድም የላትም። መጀመሪያ ውቅያኖስ የሚበላውን የራሷን ትውልድ ታድን። አዲስ ሃሳብ የማፍለቅ፤ የመፍጠር ብጣቂ ምናምን ካላት።

በታሪክ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በቴሌፎን ጽ/ቤት አለው ተብሎ ህዝብ እንደ በግ የተሸለተበት፤ ጥፍሩ የወለቀበት፤ አካሉ የጎደለበት፤ ሥነ – ልቦናው የተቀጠቀጠበት የፖለቲካ ሐገር የለም። በቴሌፎን ጽ/ቤት የአማራን ሥነ – ልቦና የማደራጀት፤ የማስተዳደር፤ የመምራት አቅሙም ወርዱም የለውም ማንኛውም ድርጅት። እኔን ከዚህ የትኛው ድርጅት ነው አባል ማድርግ የቻለው። እናንተም ቢሮ ከፍታችሁ አልቻላችሁትም። ተንሳፋችሁ ነው ያላችሁት። እርግጥ ነው በዚህ በስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአፈጻጸም መመሪያ መግለጫ ላይ ታርሞ አዳምጫለሁ። ግን በፖሊሲ ደረጃ የፖለቲካ ወሳኔ ማሰጠትን ግድ ይላል።

ለሌላ መንፈስ ዕውቅና መሰጠት በራስ የፖለቲካ አቅም ላይም ክስረት ነው ለግንባራችሁ። የአስተሳሰብም ድህነትም ነው – የፖለቲካ ግንዛቤ። የሆኑት እኮ አይፈሩም ድምጹ ይሸተኛል፤ ጠረኑ ይጠራኛል ይላሉ አባሎቹ የግንቦት 7። ኢትጵያዊነት እንዲህ ይገለጻል። የሆንኩትን ሆንኩ ለማለት ክትር አያስፈልገውም። ላልተሆነበትም ልጥፍ አያስፈልገውም። ለነገሩ ለነፃነት መታገል ወንጀል አይደለም። „ነን“ የሚሉትም ቢሆን በፋክት ላይ ሙግት ከፍቶ፤ ነፃ መሬት ፈጥሮ ማሸነፍ መንገድ ነው። ፖለቲካ እኮ ካለ ፉክክር ፖለቲካ ሊሆን አይችልም። ድንጋይ ነው። አለት እንደ አቶ በረከት ጸሐይ ሲወቃው፤ ወንዝ ሲሄድበት የከረመ አለት። ሃሳብ አይፈራም። ሊፈራ የሚገባው ትዕቢት ወይንም የአስተሳሰብ ድህነት ብቻ ነው።

የአማራ ተጋድሎ ህልውና፤ ማንፌስቶው፤ ደንብ እና ፕሮግራሙ አማረነት ብቻ ነው። ክሱ፤ ጥቃቱ፤ እስራቱ ከመጣ በነጠረ የክስ መዝገብ በአማራ ተጋድሎ ላይ መሆን አለበት። „አማራ ነኝ ማለት“ ልክ ካልሆነ። የሚያስከስ፤ የሚስቀጣ ብቻ ሳይሆን የህይወት ግብርም ከኖረ በራሱ ውስጥ ከነክብሩ ታሪኩን ይዘከር።  ይህ አምክንዮ የታሪክ የባለቤትንት ኮፒራይት ጉዳይም አለ። በሌላ ድርጅትም የታሰሩት በህግ የፈረሰው የአንድነት እና አቶ የመኢህአድ ብሄራዊ ፓርቲዎችም ለሌላ ፓርቲ ልዕልና የሚተጉበት ምንም ዓይነት ሎጅክ የለም። ድህነቱ የፖለቲካ ትንተናው ከጫካ አለመውጣቱ ከዚህ በላይ ምስክር የለም። ወያኔ ሃርነት ትግራይ  ለኢህአፓ ይታገላልን? ለመኢሶን ዓላማ ይታገላልን? ምኔ ብሎ? ለሰው ታሪክ ሌላው ግብር የሚከፍልበት ምክንያት የለም፤ ኑሮም አያውቅም። አማራ ብቻ እዬተነጠለ ለበለሃሳብ ጉድጓድ የሚጣልበት ሁኔታ መቆም አለበት። ይህን ደግሞ የአማራ ድርጅት ተብዬው ሳይሆን ደሙ ያላችሁ መሪ አካላት በተለይ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና የመንፈስዎት ቤተኞች ብቻ ልዩ ድርሻ አለባችሁ። ጋዜጠኛም ሲታሰር አማራ ከሆነ ይሄው ነው? ሽርክት ግንዛቤ። በዚህ ግርድፍ ዝርክር ሃሳብ ነው ሐገር የምትመራው። ጮርቃ።

 • የታሪክ የባለቤትነት © ጉዳይ።

የትግራይ መስፋፋት ሲንሰራፋ ትጥቅን በሚመከት አንድ ብልህ መረጃ አዳምጫለሁኝ። ብዙ የፖለቲካ ሽንፍንፍኖች እርቃናቸውን ማውጣት ብቻ ሳይሆን ውልቅልቁን ወደ ቀብር ልካችሁታል። ደግሞ የሚነሳም አይመስለኝም። ይህ ድፍረት እራሳችሁን ረመጥ ውስጥ ማግዳችሁ ቢሆንም ድርጅታችሁ፤ ማህበራችሁ ኢህአድግ ከመንቦጅቦጅ ወጥቶ ሊመሰጥበት የሚገባ እንጂ ሊወቅሳችሁ አይገባም። ምክንያቱም ረቂቅ አቅምን ለባለቤቱ የመለሳችሁ ድንቆች ስለሆናችሁ። በፖለቲካ ትንታኔ ነፍሱ ልዩ ጣዕም፤ ብስል ውሳኔም ነው።

 • ለአማራ ተጋድሎ ታታሪዎች።

እንዴት ሰነበታችሁ ትንታጎቹ። የባለቤትነት በሚመለከት የአማራ ተጋድሎ ታታሪዎች የትኩረት አቅጣጫ ሁለገብ መሆን ያለበት ይመስለኛል። ታሪክ መሬት ላይ አይታፈሰም። የተጋድሎው መንፈስ ነው ታሪክ። ታሪክ ለማንም እና ለምንም የሚሸለም አይደለም። ታሪክ የደም፤ የአቅም፤ የመንፈስ መዋለ የፈሰሰበት ስለሆነ ለባለቤቱ መሆኑ ግድ ይላል። እኛ ስናልፍ ሌላ የታሪክ ጉግስ አንዳይፈጠር ከአሁኑ ተከታትሎ በትህትና ሊስተካከሉ የሚገባቸው ጉዳዮች በሙሉ መልክ መያዝ አለባቸው።

በሙዚቃ ቅንብር ሰፊ የሆነ የታሪክ ስርቆት አለ። ይህን ትጉሃኑ መልክ ማሳያዝ ያለባችሁ ይመስለኛ፤ በዚህም ምክንያት ነው አማራ የታረደው። የታሪክ ባሪያ መሆንም ውርዴት ነው። ለማናሙና ወጣት „ያብስራ ሳሙኤል“ የሚባል ቅንበር ያዬሁት እንዲሁም „MELA Productions“ የፈጸሙት ግዙፍ የታሪክ ግድፈት ተጋድሎውን የመግደል ያህል ነው ድምጽ በሌላው መሳሪያ። እከሌ ከከሌ ማለት አይቻልም። የአማራ ታገድሎ ወጣት ትንታግ ሴት አርበኛ አለው ሰውነቷን ጥፍሯ በግጦት የተነቀለ፤ እንደ ናዚ ዘመን መርዝ ተወግታ እራሷን የሳተች የጣይቱ ልጅ ንግሥት ይርጋ። እነ አርበኛ ጎቤ አሉበት የሞቀ ትዳራቸውን ፍርስርሱን አውጥተው ራሳቸውን የገበሩበት፤ ኮ/ ደመቀ ዘውዱ/ እነ አቶ አታላይ ዛፌ አሉበት ስለምን ከእነሱ ጋር አይቀነባብርም አስፈለጊ ከሆነ። ተጋድሎው ባለቤት የሌለው ቤት ነው የሆነው። ንኪኪው ባልተገባ ሁኔታ ነው ነው ተጠርዞ የሚታዬው። ለምሳሌ የሞራል መምህሩ አቦ በቀለ ገርባን በሚመለከት ራሱ ተጋድሎው ፈቅዶና ውዶ መሪዬ ብሏቸዋል። ይሄ ትክክል ነው። ውዴታውን መጠበቅ ግድ ይላል። የተጋደሎውን ጥልቅት፤ ፍስፍናውንም ይሄው ነው። ላልፈቀደላቸው ግን ልጥፍ መለጠፈ የተጋባ አይደለም። ጎንደር ተወላጅ ቢሆንም ባይሆንም። ይህን መተላለፍ ወንጀልም ነው። ዝርፊያ ሙስና ወንጀል ነው። ያልፉበትን፤ በመንፈስ ተጸንሶ የማያወቀውን ሃብት መዝረፍ የተገባ አይደለም። ቀድሞ ነገር ስሜን ኢትጵያ እኮ በትንሳኤው የተሰረዘ ነው። ጎንደሮች እንዲህ ይላሉ „ሲወዱም፤ ሲጠሉም እስከ ንፍጥ ልጋጉ።“ እንደማንወደድ እናውቀዋልንለ። ኑረንበታል።

ስለዚህ ይህን እንዲስተካከል ማድርግ የአማራ የፖለቲካ ሆኑ የሲቢክስ ድርጅቶች፤ ታታሪዎች፤ ሚደያዎች የቅድሚ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል። በችልታ መታለፍ የለበትም። ሌላው „የወጣቶች ድምጽ“ የሚል እንዲሁ የአማራ ተጋድሎ ከኢትዮጵ ወጣቶች ብቻ ጋር እንዲያያዝ ተደርጎ ተሰርቶም አይቻለሁኝ። የዘመነ ማሌ ፍስፍናና የጅልነት ዘመኑን ተሸከሙ ነው። በዚህም በራሱ መንፈሱ አንዲኮደኮ ተደርጓል፤ ይህም የተገባ አይደለም። ዕድሜ፤ ፆታ፤ ሐይማኖት፤ ሙያ፤ እወቀት ክትር የለውም። ተጋድሎው ህጻናት ሳይቀሩ ተሳትፈውበታል ውሃ በማቀረብ ደምም አንባጊዮርጊስ ላይ ገብረዋል። ስለዚህ የአማራ የህልውና ተጋድሎው ከእዳሪ የተገኘ የዱር ቅጠል አይደለም። የሰው ግብር ከፍሏል፤ እዬተከፈለበትም ነው፤ ወደፊትም ቀጣይ ነው። ይህም ግድፈት ከፈጸሙት ግለሰብ ይሁን ድርጅቶች ጋር በመነጋገር እንዲስተካካል መደረግ አለበት። በቄሮ ተጋድሎ ቀልድ የለም። በባለቅኔው አጫሉ ሁንዴም ኪናዊ ተግባር እንዲህ መደፋፈር የለም።

አማራ ተጋድሎ ላይ ግን ጌታው፤ አዛዡ በዛ … ለመሆኑ የግንቦት 7ስ መሪዎች ሆኑ፤ የግንቦት 7ቷ ጋዜጠኛ ርዮት ዓለሙ ስለምን እዚህ ውስጥ እንድትገባ ተፈለገ? ያን በአይኗ ያዬችውን የወ/ሮ እማዋይሽ ዓለሙን ሰቆቃ እንኳን ለመናገር አልደፈረችም። ቀብራው ነው የኖረችው። የጥቁር ልብ ተምሳሌት ናት። ምን አለ የመጀመሪያው የግንቦት 7 ወታደር አርበኛ ዘመነ ካሴ ይንከራተት፤ ለሴቶች ራሱ ምን ሠራች? የወንዶችን ህሊና ላይ ስላወጣች፤ ዕውቅና ስለሰጠች? „የእማዋይሽ ድምጽ“ ነበር መባል የነበረበት እመራዋለሁ የምትለው የምቾት አውዷ ሥያሜ። ሰቃዮዋን የቆረጠው/ ያሳጠረው የሥርጉተ ብዕር ነበር። ይህን የቀድሟዋን ቀዳማይ እመቤት ርጉዋን፤ ጥንቁቋን፤ የሰከነት፤ የፍቅር ናሙና፤ የአድማጭነት ማህባዊ ነፍስን መጠዬቅ ነው።

የሆነ ሆኖ በጣም ተስተካክሎ ዜና ላይም፤ ከመንፈሱ ጀምሮ ቅንብሩ ታሪክን ጠብቆ ያዬሁት „ጤና አዳም እና ቢ.ቢ.ኤን ሚዲያ“ ላይ የተሰራው ሪፖርት „ሰከን በልም“ የተጋድሎው መንፈስም በፍጹም ሥነ – ምግባር በጥንቃቄ ተሰርቷል። ለዚህ ምስጋናዬ የላቀ ነው። ይሄ ለመነሻ ብቻ ነው ግድፉቱን እንድታዩት በዚህ ዙሪያም ክትትል እንድታደርጉበት ነው …

https://www.youtube.com/watch?v=U9eplBlX4ME

„እናታለም ጎንደር ጎንደርነታ ማንነቴ ጎንደርነቴ ኩራቴ“

https://www.youtube.com/watch?v=BcFXNoXUPvw

„Fasil Demoz 25 Amet New Ethiopian Music 2016“

የአማራ ተጋድሎ ትጉሃን ይህ ተስተካክሎ እንዲሠራ መብርታት ያለባችሁ – ይመስለኛል ለዚህ ነው የተፈጠራችሁት። የኔታዎች ያለፈውን የኢትጵያ ታሪክ እናስታካክላለን ብላችሁ ስትተጉ ዛሬ እናንተ ያለችሁበት ታሪክ እብቅ አይለበሰ ነው። እዬሾለካችሁ ነው።ታሪክ ቢያንስ እናንተ ያለችሁበት መዘረፍ የለበትም። ተቁሞ እዬሄደ። ለአማራ ተጋድሎ „አማራ ነኝ“ ብሎ ደፍሮ መውጣትን ከሁሉ ቀድሞ ማለትን ይጠይቃል። ተጋድሎው ባለቤት አለው። መሪ አለው። ሺህ ጀግኖች አሉት። የቴዲ አፍሮ የባህርዳር ገደል የተጋድሎ ነፍስ ነው። ኳስ ሜዳ ላይ የሚታዬው ትንግርት ሁሉ የዚህ መንፈስ የዓውደ የምህርት ቀንዲል ነው። ቀልዱን አስቁሙት።

 • ክወና።

በመጨረሻ ለአቶ ገዱ መንፈስ ላሳስብ የምሻው የአሁኑ የመሳሪያ ትጥቅ ማስፈታት ጉዳይም ባለፈው ዓመት የግንቦት 7 ቃል አቀባይ „እኛ ያደራጀነው ነው ብሎ“ ሳይፈራ ሳይቸር አሜሪካ ድምጽ ላይ ስለፎከረ ከወያኔ ሃርነት ስጋት  ከመጣ ስጋት ነበር ተጀምሮ የነበረው። መቼም ወያኔ ሃርነት ትግራይ ህሊናው ያለው ከቁርጭምጭሚቱ ላይ ስለሆነ፤ ያ እንኩት ሲል አሁን ሻብያ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል አስተጠኩኝ“ እያለ ስለ አቅራራ ነው ይህ አዲስ ዘመቻ የተጀመረው። እንደ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ቦቅቧቃ የለም። በዚህ ሂደት የኢሳያስ ካቢኔ አማራን አስኪበቃው ድረስ አስጨፍጭፏል ባለፈው ዓመት፤ አሁን ደግሞ ጭፍጨፋው ዳግም ልደቱን ለማዬት ሌላ ነጋሪት እዬጎሰመ ነው። ኮ/ ደመቀ ዘውዱ መፈታትም፤ ተፈቶም ንጥር ዕውነቱን በመናገሩ ራሱ የሚገርም መልሳችሁ እሰሩልን የሚል ጹሑፍ አንብቤያለሁኝ። „ታሰረ ተፈታ“ የሚል ማለት ነው። ሻብያ ርቃኑን ቀረ እንደ አቅራራ።  የሰሞኑ ድለቃ ድግሞ ልበ ቢሱ የወያኔ ሃርነት ትግራ ውስጡን አንቦጫቡጮታል። ለዚህ ነው አማራን ትጥቅ አስፈታለሁ ብሎ የሚዳክረው።

መሆን ያለበት በዚህ ጉዳይ ለገዱ መንፈስ ማስገንዘብ የምፈልገው በኤርትራ የሚመጣ ማናቸውም ሃሳብ አማራን የመምራት አቅም የለውም። ከዚህ መሰረታዊ አንኳር አመክንዮ መነሳት ያስፈልጋል።

ወያኔ ሁልጊዜ ራዱ ኪሳራ ሲደምር ነው የሚኖረው። ድውይ! ይሄን ዕውን ለማድረግ ደግሞ አማራው ትጥቁን መስፈታት ሳይሆን አማራን አምኖ ማስታጠቅ ያስፈልጋል። አማራ እና መሳሪያ ማፋታት አይቻልም። የማይሆን ነው። ይናዳል። ቀበቶውን ከፈታ እሱ እኮ የአዳም ልጅ አይደለም። ሚስቱም አቅፋው አትተኛም። ልጆቹም ይሳለቁበታል።

መፍትሄው ጥያቄውን በአግባቡ መፍተታት፤ ቀዩን አለመዳፈር። መንፈሱን ለመርገጥ አለማሰብ። አማራ ሥነ – ልቦናው ራሱ መትረዬስ ነው። ነፍሱ አዬር መቃወሚያ ነው። ትንፋሹ ቦንብ ፈንጅ ነው፤ ያቃጥላል። የአማራ ገዢ መሬቱ አማራዊ ጽኑ መንፈሱ ነው። ችግርን ታግሶ ይህን ያህል ዓመት አሳልፏል። ቁሞ አብልቷል። አሁን ጫፍ ላይ ነው፤ ቋፍ ላይ። ወያኔ ሃርነት ትግራይ አንካካዋለሁ ካለ በራስ ነፍስ መቀለድ ነው። ሐገርን እግዚአብሄር ካልጠበቀ ሰራዊቶች በከንቱ ይደክማሉ“  ይላል ቃለ ወንጌል።ጎንደር በወያኔ ሃርነት ተጠቅጥቋል። ከእንግዲህ የመጣ ቢመጣ መሻገሪያ ድልድይ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም። የጎንደር እናትም „አድጊ“ ነው የወለድሽው እያለ ለሚያባጭልባት የኤርትራ እጭ ገረዱ አይደለችም።

የአማራ የህልውና ተጋድሎ ግልጽ ጥያቄ አለው። ለግልጽ ጥያቄው መሪዎች አሉት። በስማ በለው ነፃነት አይገኝም። መሬቱ ላይ ያሉት አካሎቹ የተገባውን በተገባው ሁኔታ የማስፈጸም ልምዱም፤ ተመክሮውም፤ ተደማጭነቱም፤ ክህሎቱም አላቸው። አሁን መሬት ላይ የአማራ ህልውና መሪ አለው። በሰላም እታገላለሁ ያለ መንፈስ አለ። ያን ከልብ ሆኖ ማደምጥ ያስፈልጋል።

በመጨረሻ የጥበበኛው ቴወድሮስ ካሳሁን ኮንሰርት ከጅምሩ አስከ ፍጻሜው መልካም ነበር። በማናቸው የአማራነት ተጋድሎ የህሊና ልዩ የአቅም መቅኖ የሆነው የጎጃም ህዝብ መሪው የተናሳበትን ድምጽ ስምቶ ቀፎው እንደተነካ ንብ ሆ ብሎ! የእኔ ብሎ የከፈለው ወደር የለሽ መስዋዕትነት ከድንቅ በላይ ነው። እኔ እዲያውም የኮ/ ደመቀ ዘውዱ ከእስር በክብር መለቀቅ አንኳን ደስ አለህ ሊባል የሚገባው ከጎንደር ይልቅ ደሙን ሳይሰስት የገበረው፤ ትዳሩን ሳያቅማማ የበተነው፤ ልጆቹን ፈቅዶ ለመስዋዕትነት የሰጠው የጎጃም ደምመላሽ ንብ ህዝብ፤ ቅኔ ህዝብ ሊመሰገን ይገባል፤ የዐፄ በካፋ፤ የቅድሰት ማርያማዊት፤ የአዳም ሰገድ እያሱ ነባቢት ቅዱስ ቅብዕ ነው። ለእኔ ይሄ ህዝብ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖቴ ነው። የወንጌል መጸሐፌ። „ክብር ለሚገባው ክብር ስጡ“ ይላል የእግዚብሄር ቃል። ክብር እና ልዕልና ለሚናፍቀኝ ሙሉሰው ለጎጃም ህዝብ! ከዚህ በተጨማሪ ከሽዋ ድረስ እዬተጓዙ መሪያቸውን ጎንደር እዬሄዱ ይጠይቁ ለነበሩ ቤተሶቦቻችንም እንዲሁ ምስግና ይገባል። በተረፈ በውጭም በውስጥም መንፈሳቸውን ሳይሰስቱ አቅማቸውን ላፈሰሱ ቅን ኢትጵውያን ሚደያዎች ሁሉ ፍቅር ይሸለማቸው።

 • የልሳነወርቁአማራበቅኔው ፍልስፍና ውስጠት።

ይሄ ነው …. „አማራ ነኝ“  ለስንብት ለገዱ ቅን መንፈሶች ሁሉ ይህን ልጋብዝ። የልብ አድርስ፤ የመንፈስ ምስባክ የንሰሃ መዝሙር ነው። የውዳሴ ማርያም፤ የመዝሙረ ዳዊትን ያህል ነው እኔ አምድግመው። ድርሳኔ ነው። ጎበዞች! ውስጤን አጣጥሜበታለሁኝ፤ አድምጨበታለሁኝ በዚህ ህብራዊ ብሄራዊ ዜማ። አማራም ኢትዮጵያዊ፤ አማራም ሰዋዊ ነውና!

https://www.youtube.com/watch?v=ykEVNJR_tFs

Amhara Nen / New Ethiopia Amharic Music 2018 (Official Video) – አማራ ነን አዲስ 2010 ሙዚቃ

 

አማራነት ይከበር!

„አማራነት ወንጀል አይደለም!“

„እንከባበር!“

አማራ ጥቃት አይወድም!

መሸቢያ ጊዜ። እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.