ሕወሃት ራሱ ያመነው የጥገኛ ገዥ መደብነት አዝማሚያና ህዝቡ እያነሳው ያለው የበላይነት ዝንባሌ የስም እንጅ የባህሪያት ልዩነት አይታይባቸውም

ከፍትህ ይንገስ

ሕወሃት በቅርቡ አደረኩት ባለው 35 ቀናት የወሰደ ግምገማው አሉብኝ ካላቸው ችግሮች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የተገለፁት በሚከተለው መንገድ ነበር።

“አመራሩ የሃሳብና የተግባር አንድነት የጎደለው፣ ፀረ-ዴሞክራቲክ ተግባርና አስተሳሰብ ውስጥ በስፋት የተነከረ፣ በተልእኮ ዙሪያ  በመተጋገልና በመርህ ላይ የተመሰረተ አመራር የማይሰጥ፣ ህዝብንና አላማን ከማስቀደም ይልቅ የራሱን ክብርና ጥቅም የሚያስቀድም መሆኑ ታይቷል። ለህዝብ ያለው ገንተኝነት እየተሸረሸረ ካገልጋይነት ይልቅ ራሱን እንደተገልጋይ እየቆጠረ፣ መዋቅራዊ ለውጥ በሚያመጡ ስኬታማ የህዝብ ዙሪያ መለስ እንቅስቃሴ ከመጠመድ ይልቅ በተደማሪ ለውጦች የሚረካና በውሸት ሪፖርት ራሱን መሸለም የሚቃጣው አመራር እየሆነ ባጠቃላይ ራሱን ወደጥገኛ ገዥ መደብ የማሸጋገር አዝማሚያ የተጠናወተው መሆኑን በትክክል አስቀምጧል” ይላል።

ለመጀመር ያህል ከዚህ በላይ ተለይተው የተገለፁ የህወሃት ችግሮች ወቅታዊና ተገቢም ናቸው፤ ምክንያቱም ህዝቡም ቢሆን  በተለያየ መንገድ እየገለፃቸው ያሉ ናቸውና። በተለይ ደግሞ አመራሩ የጥገኝነት አዝማሚያ የተጠናወተው መሆኑን በግልፅ ማመኑ ሁሉንም የሚያስማማ ትልቅ እርምጃም ነው። እንደሚታወቀው ጥገኛ የሆነ የገዥ መደብ ቡድን የምንጊዜም ህልሙ ራሱንና ደጋፊዎቹን መጥቀም ነው። ይህ መደብ እታገልለታለሁ የሚለውን የህብረተሰብ ክፍል ጥቅም የሚያስከብር ሳይሆን በስሙ እየነገደ የራሱንና የራሱን ጥቅም ብቻ የሚያሳድድ ተለጣፊ መዥገር ነው። ይህንን ፍላጎቱን ለማሳካት ደግሞ የተለያዩ ስልቶችን ይጠቀማል። ያልተሰሩ ስራዎች እንደተሰሩ አድርጎ የሚያሳይ የሃሰት ረፖርት እያቀረበ ህዝቡን ለመሸንገል ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል። ከዚህ አልፎም ህዝቡን ለማፈንና አንገት ለማስደፋት የተለያዩ ፀረ-ደሞክራሲያዊ የሆኑ አካሄዶችን ይጠቀማል፡፡ እንግዲህ የህወሃት አመራር ትግራይ ውስጥ ፈፀምኩት ያለውም ይህንኑ ነው። ለዚህም ነው የህወሃት አመራር ትግራይ ውስጥ በነበረው የስራ አፈፃፀም ሂደት አጉድያቸዋለሁ ብሎ ያስቀመጣቸው በግምገማ የተለዩ ችግሮች አግባብነት አላቸው ብሎ ደፍሮ መናገር የሚቻለው። ለማንኛውም ከዚህ የህወሃት ግምገማ በኋላ የትግራይ ህዝብ የሚጠብቀው ተጨባጭ የሆነ ተግባራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ እንዲደረግለት ነው።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ ጋ ተያይዞ እየተነሳ ያለው ትልቁና አንገብጋቢው ቁምነገር ደግሞ እነዚህ የህወሃት አመራሮች እና በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች የተጠናወታቸው የጥገኛ ገዥ መደብነት ዝንባሌ እየተከሰተ ያለው በትግራይ ክልል ብቻ እንጅ በፌደራል መንግስት ደረጃ ባላቸው ሚና እንዳልሆነ አይናችሁን ጨፍኑና እናሞኛችሁ አይነት የጂል መከራከሪያ እያቀረቡ የሚገኙ መሆኑ ነው። ይሁንና የህወሃት አመራርና ደጋፊዎቹ  ትግራይ ውስጥ የጥገኝነት ዝንባሌ ከተጠናወታቸው በፌደራል መንግስት ደረጃ ብፁዕ የሚያደርጋቸው ሃይል ሊኖር እንደማይችል አይደለም ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ እነሱ ራሳቸውም በሚገባ ይረዱታል፤ የተረዳቸው መሆኑን ለመቀበል አልፈቀዱም እንጂ። ይህን የህወሃት አመራርና ደጋፊዎቹ በፌደራል መንግስት ደረጃ እያሳዩ ያሉትን የጥገኛ ገዥመደብነት ዝንባሌና አዝማሚያ ለማየት ብዙ ድንጋዮችን መፈንቀል አያስፈልግም።

በመጀመሪያ ደረጃ የህወሃት አመራርና ደጋፊዎቹ የተጠናወታቸውን የጥገኛ ገዥ መደብነት ዝንባሌ በፌደራል መንግስት ደረጃ  እውን ለማድረግ የፀጥታ ተቋማቱን በበላይነት እያንቀሳቀሱ መሆኑን አይደለም ለኢትዮያ ህዝብ ለአለም ማህበረሰብም ግልፅ የሆነ ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ የተለያዩ አለማቀፍ መዲያዎችና ታዋቂ ሰዎች የሚዘግቡትንና የሚያነሱትን ማየት በቂ ነው። ወጣም ወረደ እነዚህ የህወሃት ሰዎች እንደማንኛውም ጥገኛ ገዥ መደብ ሁሉ የፀጥታ ሃይሉን ማለትም መከላከያ ሰራዊቱን፣ ደህንነቱንና እና የተለያዩ የፖሊስ ክፍሎችን የማፈኛና የስልጣን ማራዘሚያ መሳሪያዎች አድርገው እየተጠቀሙባቸው እናዳሉ የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ። ለዚህም ይመስላል ባብዛኛው የህወሃት ደጋፊዎች በየሶሻል ሚድያዎቹ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅና ከታወጀም በኋላ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሌት ተቀን እየባዘኑ የሚገኙት።

እነዚህ የጥገኛ ገዥ መደብ ዝንባሌ የተጠናወታቸው የህወሃት አመራርና ደጋፊዎች  በፌደራል መንግስት ደረጃ ያላቸውን የበላይነት ህልም  ለማሳካት እንዲረዳቸው እየተጠቀሙበት ያለው ሁለተኛው ዘዴ ደግሞ ቁልፍ ቁልፍ የሆኑ የኢኮኖሚ ተቋማትን መቆጣጠር ነው። በዚህ ረገድ አየር መንገድና ጉምሩክን ብቻ ማየት በቂ ነው። እነዚህ ተቋማት በህወሃት ሰዎች መረብ የተተበተቡና የሚሽከረከሩ መሆናቸውን ሃገር ያወቀው ፀሃይ የሞቀው ጉዳይ ነው። ከዚሁ የኢኮኖሚ የበላይነት ዝንባሌ የማሳካት ህልም ጋ ተያይዞ የፌደራል ፕሮጀችቶችንም ማየት ይቻላል። በዚህ ዙሪያ ብዙ ነገር ውስጥ መግባት ሳያስፈልግ  የዩኒቨርስቲዎችን ስርጭት እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። በዚህ ረገድ እነዚሁ  የጥገኛ ገዥ መደብነት የተጠናቸው የህወሃት መሪዎችና ደጋፊወቻቸው ምንም እንኳን ድርጊቱን የፈፀሙት የትግራይን ህዝብ  በመደለልና በመሸንገል ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ስላጣናችንን ለማራዘም ይጠቅመናል በሚል ስሌት ቢሆንም ትግራይ ውስጥ ከሌሎች ክልሎች ጋ ባልተመጣጠነ ሁኔታ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (Universities) እንዲቋቋሙ እድርገዋል። ከዚህ አንፃር የሌሎች ክልሎችን የህዝብ ብዛት እና ያላቸውን ዩኒቨርሲቲዎች በማየት ስርጭቱ ፍትሃዊ አለመሆኑን ማየት የሚከብድ ነገር የለውም። ነገርን ነገር ያነሳዋልና ይህን ጉዳይ በተመለከተ በቅርቡ አቶ አባይ ፀሃየ ያቀረቡት መከራከሪያ አንዱ አይናችሁን ጨፍኑና እናሞኛችሁ አይነት የተለመደ የጥገኛ ገዥ መደቦች የጂል ብሂል የሚያስተዛዝብ መሆኑ አልቀረም።  በዚህ ዙሪያ አንዱ ያነሱት ነጥብ አዋጭነትን የተመለከተ ጉዳይ ነው። ይሁንና ትግራይ ውስጥ ከሌሎች ክልሎች በተለየ መንገድና ተመጣጣኝ ባልሆነ ሁኔታ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (Universities) እንዲከፈቱ የተደረገበት የተለየ ያዋጭነት እሳቤ ምን ሊሆን እንደሚችል ያስቀመጡት ዝርዝር ምክንያት አልነበረም። ይህ በሌለበት ሁኔታ ደግሞ የፕሮጀችቶቹን አዋጭ መሆን ሊረዱት የሚችሉት እኝሁ የጥገኛ ገዥ መደብነት የተጠናወታቸው ሰው እና መሰሎቻቸው ካልሆኑ በስተቀር ሚዛናዊና ምክንያታዊ የሆነ አስተሳሰብ ያለው ሰው ሊሆን አይችልም። አቶ አባይ ፀሃየ ቀጠሉና ትግራይ ውስጥ የትምህርት ተቋማቱ ቢከፈቱ የሚማሩበት የትግራይ ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎቹም የኢትዮጵያ ህዝቦች ናቸው አሉ። ምክንያቱ ይሄ ከሆነማ ታዲያ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ማዕከል ሊሆን በሚችል ቦታ በተገነቡ ነበር። ወጣም ወረደ ግን የአቶ አባይ አመክንዮ ውሃ የማይቋጥርና ህዝቡ እያነሳ ያለውን የእኩልነትና የፍትሃዊነት ጥያቄ የሚፃረር መንገድ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ሌላው በፌዴራል መንግስት ደረጃ የህወሃት ሰዎች የጥገኛ ገዥ መደብነት ዝንባሌ የሚንፀባረቅበት አግባብ ከኤፈርት ጋ የተያያዘው ጉዳይ ነው። ይህ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የምርትና የንግድ ተቋማትን አካቶ የያዘው ድርጅት የሚመራውና የሚንቀሳቀሰው በነዚሁ የህወሃት ሰዎች ነው። የህወሃት አመራርና ደጋፊዎቹ ያላቸውን ረጃጅም እጆች በመጠቀም ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ለዚህ ድርጅት ድጋፍና እገዛ ስለሚያደርጉልት ያለምንም ቢሮክራሲያዊ ተፅዕኖ ስለሚንቀሳቀስ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ ሆኗል። ይሄ ደግሞ ሄዶ ሄዶ የጥገኛ ገዥ መድብ አዝማሚያ የተጠናወተውን ህይል ኢኮኖሚያዊ አቅም ማጎልበቱ አይቀርም። ይህ መሆኑ ደግሞ የፌዴራል ስርዓቱን ፍትሃዊነት ሊያዛባ እንደሚችል የሚያጠራጥር አይሆንም።

ባጠቃላይ ሲታይ የህወሃት አመራር ብሎም በዙሪያው ያሉ ደጋፊዎቹ የጥገኛ ገዥ መደብነት ዝንባሌ  የተጠናወታቸው መሆኑን አረጋግጠዋል። ችግሩ ያለው ይህን ዝንባሌ ትግራይ ክልል ውስጥ ብቻ ገድበው ለማስቀረት ጥረት ማድረጋቸው ላይ ነው። ይሁን እንጅ እነዚህ ሃይሎች በትግራይ ውስጥ ያሳዩት የጥገኛ መደብነት ዝንባሌ በፌዴራል መንግስቱ አደርጃጀቶች ላይም እንዳለ መካድ እንደማይቻል ከዚህ ከፍ ብለው የተጠቆሙ ማሳያዎች ማስረዳት  ይችላሉ።

በተመሳሳይ ሁኔታ አራቱም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሊቃነመናብርት በቴለቪዥን  መግለጫ በሰጡበት መድረክ በወቅቱ የኦህዴድ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ የትግራይ የበላይነት መኖር አለመኖሩን  ተጠይቀው  የሰጡትን መልስ ያስታውሷል። አቶ ለማ ሲመልሱም የትግራይ ህዝብ የበላይነት እንደሌለ አስቀምጠዋል። አያይዘውም የየትኛውም ህዝብ የበላይነት እንዳልነበረ ገልፀዋል። ይሁንና በትግራይ ህዝብ ስም የሚነግዱ ገዥዎች የበላይነት ፍላጎት መኖሩን ግን አልሸሸጉም።

ብአዴን በሰጠው መግለጫ ላይም በፌዴራል ስርዓቱ የተለያዩ ዘርፎችና  ተቋማት ላይ የሚታየውን ኢፍትሃዊነትና እሱንም ለማስወገድ የረፎርም ስራ እንዲካሄድ  ትግል እንደሚያደርግ ለማስቀመጥ ሞክሯል። ብአዴን በዚህ የመግለጫው ክፍል ውስጥ የገለፀው የፍትሃዊነት መጓደል ችግር የህወሃትን የገዥ መደብ ቡድን  የሚመለከት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያስቸግርም። ይህን የሚመለከተው የመግለጫው ክፍል ለግዛቤ ያህል እንደሚከተለው ቀርቧል።

“…በፌደራል ስርዓታችን ውስጥ የፍትሃዊነት መጓደል የሚታይባቸውን ማናቸውም ዘርፎች የማስተካከል ስራ እንዲሠራና ለወደፊቱም ጥርጣሬ የሚያነግሱ መሰል ተግባራት እንዲታረሙ ተገቢ ትግል እንዲደረግ ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡ የፌደራል ተቋማት የሰው ሃይል አደረጃጀት ብቃትንና ብሄራዊ ተዋፅኦን ማእከል በማድረግ እንዲደራጅ እና የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም ተቋማቱን ሪፎርም የማድረግ ስራ እንዲሰራም የበኩሉን ሚና መጫወት እንደሚገባው ስምምነት ላይ ተደርሷል…፡፡ ይላል።

እንግዲህ ከላይ የተገለፁት ማሳያዎች በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የህወሃትን አመራርና ደጋፊዎቹን የጥገኛ ገዥ መደብነት አዝማሚያ የሚያሳዩ ከሆነ እዛው ሳሉም የዚህኑ ቡድን የበላይነት ዝንባሌ ቁልጭ አድርገው ማስረዳት ይችላሉ። ምክንያቱም ማንኛውም ገዥ መደብ አገዛዙን ለማስቀጠል እንዲችል በኢኮኖሚውም፣ በፖለቲካውም፣ በወታደራዊዩም እንዲሁም በማህበራዊ ዘርፎች የበላይነት እንዲኖረው የግድ ይላል።  ለዚህም ነው የህወሃት የጥገኛ ገዝ መደብ ቡድን የፀጥታ ሃይሉን፣ ዋና ዋና የኢኮኖሚ አውታሮችንና ሌሎች ልዩ ልዩ የፌደራል ተቋማትን በበላይነት እያሽከረከረ የሚገኘው። በዚሁ አግባብ ሲታይ የቃላት ጨዋታ በመጫወት ህዝብን ለማሞኘት ተፈልጎ ካልሆነ በቀር የጥገኛ ገዥ መደብነትም ይሁን የበላይነት ባህርያት በመሰረታዊነት አንድና አንድ መሆናቸው የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም።

ዮጵየኢትያ ህዝብም ረዘም ላሉ አመታት ድምፁን ከፍ አድርጎ እያነሳ ያለው ቁልፍ ችግር ይሄው የህወሃት ጥገኛ ገዥ መደብነት ወይም የበላይነት ነው። ቁልፍ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው ደግሞ  ይህንኑ ጥገኛ ገዥ መደብነት ወይም የበላይነት ዝንባሌ ማረምና በምትኩም እኩልነት፣ እኩል ተጠቃሚነት፣ ደሞክራሲ እንዲሁም መልካም አስተዳደር የሰፈነባት ኢትዮጵያን መገንባት ነው። በዚህ መንገድ ሁኔታዎችን ማስኬድ መቻል እዛው ሳለም ሌሎች በህዝብ የሚነሱ ቅሬታዎችን ሊቀርፍ ይችላል። ነገር ግን ይህን ቡድን ላለማስከፋት ወይም በሱ ዛቻ፣ ጫናና ተፀዕኖ፤ ከዚህ አልፎም ሲሻኝ ጭስ ወጋኝ አይነት ማስፈራሪያ ምክንያት ያለውን አሰራር ማስቀጠል ከተመረጠ ሃገሪቷንና ህዝቦቿን አላስፈላጊ ዋጋ ሊያስከፍላቸው እንደሚችል መገመት ካባድ አይሆንም።

ይሁንና ኢህአዴግ የትኛውን መንገድ እንደሚከተል ማወቅ የሚቻለው እሁድ መጋቢት 1 ቀን  2010 ዓ.ም አደርገዋለሁ ካለው የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ በኋላ ይሆናል።  ሊሆን የሚችለውን ግምት ግን ማስቀመጥ ይቻላል። የመጀመሪያው ግምት በህወሃት ጫናና ትፀዕኖ ምክኒያት  ልክ ባለፈው በነበረው የኢህ አዴግ ስራ አስፈፃሚ ግምገማ ተስማማን እንዳሉት ሁሉ የማንም ቡድን የበላይነት ዝንባሌ  የለም የሚል ይሆናል። ይህ ከሆነ ደግሞ የነበረው ሁሉ እንደነበረ ይቀጥላል፤ ኢህአዴግም በበለጠ ከህዝብ እየተነጠለ ይሄዳል።

ሁለተኛው ግምት ደግሞ ኦህዴድና ብአዴን በየድርጅት መድረኮቻቸው ለመጠቆም እንደሞከሩት የህወህት ቡድን የበላይ የመሆን ዝንባሌ አለ  በሚል ጠንክረው የሚጋፈጡበት ሁኔታ ሊፈጠር የሚችል መሆኑ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ አንድም የህወሃት ቡድን ተገዶ ያለበትን ችግር ይቀበላል ካልሆነም  ልክ አቶ አባይ ፀሃየ እንዳሉት የተለየ ጥቅሜ የሚነካው በኢህአዴግ መቃብር ላይ ነው በሚል ፈሊጥ ኢህአዴግን የመበተን አቋም ላይ ሊደርስ ይችላል። በዚህ ሁኔታ ላይ ምን አልባት ብአዴንና ደኢህዴን ኢህአዴግ እንዳይበተንና አደጋ ላይ እንዳይወድቁ በመስጋት ከህወሃት ውይም ከኦህዴድ ጋ አንድ ላይ ሊቆሙ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። በዚህ ጊዜ የኦህዴድ የማፈንገጥ  እድል የሰፋ ይሆናል። ይህም ቢሆን ግን ልዩነቶቻቸውን ለየድርጅቶቻቸው እና ለኢህአዴግ ጉባኤዎች አቅርበው ለማስወሰን ስምምነት ላይ ሊደርሱ ይችላሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.