ህወሓት ኢትዮጵያን በዩጎዝላቪያ (Yugoslavia) መንገድ እንድትነጉድ እያደረጋት ይሆን እንዴ? እናስ ምን ይሻላል? (ከፍትህ ይንገስ)

በተለያየ መንገድ እየተገለፁ ካሉ ሁኔታዎች በመነሳት አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በህወሃት ሰዎች የበላይነት ወይም በነሱ አባባል የጥገኛ ገዥመደብነት አዝማሚያ ላይ ቅሬታ የቋጠረ ይመስላል። ይህ ቅሬታ  ደግሞ ከመሬት ተነስቶ የመጣ አይደለም፤ በተግባር የሚታዩ  ድርጊቶች ስላሉ እንጂ። በመጀመሪያ ደረጃ በፀጥታ ሃይሉ ዉስጥ የህወሓት ሰዎች እጆች በጣም ረጃጅሞች ናቸው። እነዚህን ተቋማት የሚያሽከረክሯቸው የህወሓት ሰዎች ረጃጅም እጆች ናቸው። ሁለተኛ ቁልፍ ቁልፍ የሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች የተያዙት በህወሃት ሰዎች ሲሆን በዚህ ረገድ ዋናው ሞተር ኤፈርት (Effort) ነው። ሶስተኛ ፖለቲካዊ ሁኔታውም ሲታይ የህወሃት ሰዎች ከሚፈልጉት አጀንዳ ዉጭ ማስፈጸም የማይቻልበት ደረጃ የደረሰ ይመስላል። ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለው አየር ህወሓት ህወሓት መሽተት ከጀመረ ብዙ አመታት ተቆጥረዋል። ይህ መሆኑን ሌላው ይቅርና በአንድ ወቅት በጣም ከፍተኛ አመራር ከነበሩት የህወሃት ሰዎች አንዱ ሌ/ጀነራል ፃድቃን ው/ትንሳኤ ፊት ለፊትም ባይሆን በግድምድም ማመናችውን የሚያሳዩ ፅሁፎችን አውጥተዋል፤ ንግግሮችንም አድርገዋል።

ይህን ሁኔታ በተጨባጭ ለማሳየት ብዙም ምርምር የማያስፈልገዉን በተወሰኑ የኢትዮጵያ ክልሎች ያሉትን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (Universities) ስርጭት ማየት በቂ ነው። እንደ አዉሮጳዊያን አቆጣጠር በ2007 ዓ.ም ተካሄዶ በነበረው የህዝብ ቆጠራ ዉጤት መሰረት የኢትዮጵያ ሶማሊና የትግራይ ክልል የህዝብ ብዛት ተመጣጣኝ ነው። ምናልባትም የኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል የህዝብ ብዛት ክትግራይ ክልል በተወሰነ ደረጃ ከፍ ሳይል አይቀርም። ይሁንና ትግራይ ክልል ዉስጥ አዲስ ይገነባል የተባለዉን አድዋ ዩኒቨርሲቲን  ጭምሮ አራት የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ሲኖሩ ኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ዉስጥ  ያለው የመንግስት ዩኒቨርሲቲ (University) ግን አንድ ብቻ ነው። ከላይ በተገለፀው ያሀዝብ ቆጠራ ዉጤት መሰረት አሁንም የኦሮሚያ ክልል የህዝብ ብዛት የትግራይን ክልል ህዝብ ብዛት ከስድስት እጥፍ በላይ ሊሆን ይችላል። በዚህ ስሌት ኦሮሚያ ክልል ዉስጥ መኖር የነበረባቸው ዩኒቨርስቲዎች (Universities) ከሃያ አራት በላይ መሆን ይገባቸው ነበር። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ትምህርት ሚንስቴር ድህረ ገጽ እንደሚያሳየው በኦሮሚያ ክልል ዉስጥ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ከአስር አይበልጡም። አማራ ክልል ዉስጥም ያሉት ዩኒቨርሲቲወች (Universities)  እንዲሁ ከአስር አይበልጡም። ነገር ግን ትግራይ ዉስጥ ባሉት ዩኒቨርስቲዎች (Universities)  ብዛት ስሌት ቢሆን ኖሮ  አማራ ክልል ዉስጥ መኖር የነበረባቸው ዩኒቨርስቲወችም (Universities) አስራ ስድስትና ከዚያ በላይ መሆን በተገባቸው ነበር።  ምክኒያቱም በህዝብ ቆጠራ ዉጤቱ መሰረት የአማራ ክልል ህዝብ የትግራይ ክልልን ህዝብ አራት እጥፍ አካባቢ ሊሆን ስለሚችል ነው።

ይህንኑ ያልተመጣጠነ የትምህርት ተቋማት ስርጭት በበለጠ ለመረዳት ተበጀ ሞላ በሚባል ሰው የተጽፈዉን (Higher Education in Ethiopia: Structural Inequalities and Policy Responses) የሚለውን መፅሃፍ ማንበብ የበለጠ ጠቃሚ ይሆናል። በተረፈ ጭብጡን በቀላሉ ለመረዳት ከላይ ከተገለፀው መፅሃፍ ዉስጥ የተወሰደዉን የሚከተለውን ምስል (Screen Shot) ይመልከቱ።

ህወሓት ኢትዮጵያን በዩጎዝላቪያ (Yugoslavia) መንገድ እንድትነጉድ እያደረጋት ይሆን እንዴ? እናስ ምን ይሻላል?  (ከፍትህ ይንገስ) 1

ታዲያ ይህ ሁኔታ እኩል ተጠቃሚነትንና ሚዛናዊነትን ያሳያል? መልሱን ለአንባቢ መተው ይሻላል።

ለማንኛዉም በህወሃት ሰዎች የበላይነት/ጥገኛ ገዥ መደብነት ዙሪያ ብዙ ስለተባለና ባብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብም የተገነዝበው ስለሆነ ጉዳዩን በዚህ ፅሁፍ ላይ በዝርዝር ማንሳቱ አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም። ይልቁንም ባሁኑ ወቅት አንገብጋቢና ቁልፍ የሆነው ጥያቄ የኢትዮጵያና የህዝቦቿ ሁኔታ ወዴት እያመራ ነው?  የሚለው ነው። ይህን ጥያቄ ለመመለስ ባጋጣሚም ይሁን ታሪክ ራሱን እየደገመ አይታወቅም የአሁኗን ኢትዮጵያ ቀድሞ ዩጎዝላቪያ (Yugoslavia) ተብላ ትታወቅ ከነበረችው አገር አንፃር እየቃኙ ትንታኔ መስጠት የችግሩን ክብደት በደንብ ለመገንዘብ ያስችል ይሆናል። ምክኒያቱ ደግሞ የሁለቱም ሃገሮች ሁኔታ መመሳሰል እየጎላ የመጣ ስለሆነ ነው። በዚህም መሰረት ትንታኔዉን በሚቀጥለው መንገድ ማየት ይቻላል።

እንደሚታወቀው የዩጎዝላቪያ (Yugoslavia) ፈዴሬላዊ ስራዓት አወቃቀር ዘርንና ታሪካዊ ትሥርን መሰረት ያደረገ ነበር።  የኢትዮጲያ የፌዴራል ስርዓትም ቢሆን ከዩጎዝላቪያ (Yugoslavia)  ተመሳሳይ ሊባል በሚችል መልኩ ዘርን፣ ቋንቋንና ታሪካዊ ትሥርን መሰረት አድርጎ የተዋቀረ ስራዓት ነው። በሁለተኛ ደረጃ ዩጎዝላቪያ (Yugoslavia)  ትመራ የነበረው የዩጎዝላቪያ ኮምዩኒስት ልግ (League of Communists of Yugoslavia) ተብሎ ይጠራ በነበረ አገር አቀፍ ፓርቲ ነበር።  ይህ ፓርቲም በስድስቱም የዩጎዝላቪያ ክልልሎች ቅርንጫፎች ነበሩት። ኢትዮጵያም በተመሳሳይ ሁኔታ እየተመራች ያለቸው በኢህአዴግ ሲሆን ይህ ፓርቲም በየክልሎቹ አባል ወይም አጋር ፓርቲወች አሉት። በሶስተኛ ደረጃ ሁለቱም ሃገሮች ይመሩ የነበሩት ጠንካራ (strong) ናቸው ተብለው ይታወቁ በነበሩ መሪዎች ነበር። በዚህም መሰረት ዩጎዝላቪያ ትመራ የነበረው ስልጣን ላይ እንዳሉ ህይወታቸው ባለፈው “አምባገነኑ” ግን ደግሞ “ተወዳጁ” ፕረዚደንት ጆሲፕ ብሮዝ ቲቶ (Josip Broz Tito) ነበር። ኢትዮጵያም ቢሆን ትመራ የነበረው ስልጣን ላይ እያሉ ህይወታቸው ባለፈው “ብሩህ” ግን ደግሞ “ብልጣብልጥና” “አምባገነን” ተብለው በብዙ ሰወች ዘንድ በሚታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነበር። እነዚህ የሁለት ሃገር መሪዎች በየሃገሮቻቸው ተነጻጻሪ የሆነ ሰላምና የኢኮኖሚ እድገት በማስፈናቸው ይታወቃሉ።

ከሁለቱም ሃገራት መሪዎች ህልፈተ-ህይወት በኋላ ግን ይህ ሰላምና የኢኮኖሚ እድገት ፈተና ገጥሞታል። በዮጎዝላቪያ ሁኔታ ከፕረዚደንቱ ህልፈት በኋላ (በየክልሎቹ ይነሱ የነበሩ የመገንጠል ጥያቄወችን ጨምሮ) ፖለቲካዊም ይሁን ኢኮኖሚያዊ ጥያቄቀችን መፍታታት አዳጋች እየሆነ ሄደ።  ይህን ሁኔታ ያባባሰው ደግሞ በስሎቮዳን ሚሎሶቪች (Slobodan Milošević) ይመራ የነበረው የሰርቢያ (Serbia) ሃይሎች የበላይነት ዝንባሌና የሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ጥያቄወች የማፈን አቅጣጫ ነበር። እነዚህና ሌሎች መሰል ችግሮች ተደማምረው ሃገር አቀፍ ፓርቲ የነበረውን የዮጎዝላቪያ ኮሙዩኒስት ሊግ (League of Communists of Yugoslavia) እንዲፈርስ አደረጉ። ይህ አገር አቀፍ ፓርቲ ሲፈርስ ደግሞ  ዘርን ማዓዕከል አድርገው የተደራጁት የየክልል ኮሙዩኒስት ድርጅቶች ራስ ራሳቸዉን ችለው ሶሻሊስት ፓርቲ ሆነው  ቀጠሉ። በመጨረሻም ሁኔታው እየተባባሰ ሄዶ ከብዙ ዘርን ማዕከል ያደረገ  የርስ በርስ ግጭት በኋላ ዩጎዝላቪያ ከአለም ካርታ ላይ ጠፋች።

 

እንግዲህ ከዚህ አንጻር ሲታይ ነው የኢትዮጵያ ሁኔታ በምን ይገለጻል የሚለዉን ማየት ጠቃሚ የሚሆነው። የኢትዮጵያ ሁኔታ በሚታይበት ጊዜ እንደ የሰርቢያ (Serbia) ሃይሎች ሁሉ የህወሃት ሰዎችም የበላይ/ጥገኛ ገዥ መደብ የመሆን አዝማሚያ እየታየባቸው ነው በሚል ቅሬታ የሚያቀርቡ የህብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር ቀላል አይደለም። ይህ ቅሬታ በህዝቡ ዉስጥ ባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ሳይሆን በራሱ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ዉስጥም በተለይም በኦህዴድና በብአዴን በዋነኛነት ደግሞ በኦህዴድ በተደጋጋሚ እየተነሳ ያለ ጉዳይ ነው። ይህ ችግር በግልፅና በስፋት መነሳት የጀመረው ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዘናዊ ካለፉ በኋላ ነው። ከርሳቸው ህልፈተ-ህይወት በኋላ ኢህአዴግ ችግሮችን መፍታት ተስኖት ሃገር አደጋ ላይ ወድቃለች።

ይህ ባለበት ሁኔታ የህወሃት ሰዎች በተለይም ደግሞ አቶ አባይ ፀሃየን የመሳሰሉ በበኩላቸው የሚነሱ ቅሬታወች መሰረት የሌላቸውና ሁኔታወች ሊቀየሩ የሚችሉት በኢህአዴግ መቃብር ላይ ብቻ ነው ብለው ሽንጣቸዉን ገትረው እየተሟገቱ ነው። ሁኔታው በዚህ መልኩ ከቀጠለ ልክ እንደ ዩጎዝላቪያው ኮሙኒስት ሊግ ሁሉ ኢህአዴግም የመፈረካከስ አደጋ ሊደርስበት ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያ የማያባራ የእርስ በርስ ጦርነት ልትገባና በመጨረሻም ልክ እንደ ዩጎዝላቪያ ሁሉ ስሟ የአለም ካርታ ላይ ሊጠፋ የሚችልበት አጋጣሚ አይኖርም ብሎ መደምደም አይቻልም።

ይህ እንዳይሆን ከተፈለገ የህወሃት ሰዎች ከሌሎች ጋ አቻ የሚሆኑበት ተጨባጭ የሆነ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሊደረግ ይገባል። ይህ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ደግሞ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም። አሁን ላይ በፍርሃትም ይሁን በእጅ ቁልመማ ብዙ ቁጥር ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ቅሬታ የቋጠረበትን የህወሓት ሰዎች የበላይነት/ጥገና ገዥ መደብነት የለም በሚል አለባብሶ ለማለፍ መሞከር ጊዜው ሲደርስ ፈንድቶ አገር የሚበታትን ቦምብ ቀብሮ እንደማለፍ ይቆጠራል። ይህ እንዳይሆን ደግሞ ራሳቸው የህወሓት ሰዎችም ይሁኑ ሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ቅንነት ላይ የተመሰረተ ትግል ያካሂዱና ችግሮቻቸዉን ይፍቱ። በተለይም ደግሞ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ከችግሮች ሁሉ ቁልፍ የሆነዉን የህወሃት ሰዎች የበላይነት/ጥገኛ ገዥ መደብነት በሚመለከት ቅንና ግልፅ የሆነ ዉይይት በማድረግ መተማመን ላይ ይድረሱ።

ከዚህ ባለፈም ኢህአዴግ ራሱ እንዲፀድቅ ያስደረገዉን ህገመንግስት በማክበር የዴሞክራሲ ምህዳሩን ያስፋና ጊዜው ሲደርስ ነፃ፣ ሚዛናዊ፣ ግልፅና ቀጥተኛ የሆነ ምርጫ እንዲካሄድ የፀና ፍላጎት ያሳድር፤ ለተግባራዊነቱም ይንቀሳቀስ። ህዝቡም በበኩሉ ይመሩኛል የሚላቸውን ወኪሎቹን ያለምንም ፍርሃትና መሸማቀቅ በነፃና በፍላጎት እንዲመርጥ ሁኔታዎች ይመቻቹለት። ይህ ሲሆን ኢትዮጵያ በዩጎዝላቪያ ሳይሆን በሌሎች ደሞክራሲ በሰፈነባቸው ሃገሮች ጎዳና መራመድ ትጀምራለች። ይህ ደግሞ እዛው ሳለ  የህወሃት ሰዎች ኢትዮጵያን በዩጎዝላቪያ መንገድ እንድትነጉድ እያድረጓት ይሆን እንዴ?  የሚለዉን የብዙ ሰው ጥርጣሬ ይቀርፋል።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.