እየሆነ ያለውን አለማስተዋል ወይስ ሴረኝነት? (ሰርፀ ደስታ – የሳተናው አምደኛ)

ሰሞኑን መቼም ሁሉም እየሆነ ያለውን በእርጋታ ከማሰብ ይልቅ ብዙ የተስፋ መቁረጥ የሚመስሉ ወሬዎችን መንዛት ብዝቷል፡፡ ለማ መናገር አይችልም፣ ኦህዴድ አለቀለት፣ ወያኔ ጉልበቱን አጠነከረ ምናምን ከምሁር እሰከ ተራው ይሄንኑ ይነዛል፡፡ ሂደቱ የመጨረሻው ምዕራፍ እንደሆነ እንኳን ለማስተዋል ፍቃደኛ የሆነም ያለ አይመስልም፡፡ በዛው ልክ ግን ብዙዎች በሚሰጡት አስተያየት በራሳቸው እያሳበቁና የተደበቀ ማንነታቸውም እየወጣ ይመስላል፡፡ ለማንና ቡድኑን ወንድ ከሆነ ለምን እንዲህ አያደርግም ለምን ምናምን ብሎ መካሪው በዝቷል፡፡ ለእንደዚህ ያለ አስመሳይ ዝም በል ብንልም አይልም፡፡ ምክነያቱም ዓላማው የራሱን ምኞት እንጂ ሕዝብም አገርም ለእሱ ምንም አደለም፡፡ ለማና ቡድኑ እስካሁንም የመጡበት አሁንም የደረሱበት ስልት ግን ወደ ወያኔ መክተሚያ ምን ያህል እንዳቀረበው ሊቀበሉት አልቻሉም፡፡ ሲጀምር እነለማን ዛሬ ደርሶ እንዲህ ዛሬ መካሪ የመሰሉት መጀመሪያ እኮ ለማ ሕዝቡን ወያኔ ቀለበት ውስጥ እንዲያስገባ የተላከ ነው በሚል ብዙ ሲዘበዝቡ ነበር፡፡  እነዚህ አንዴ መካሪ ሌላ ጊዜ ደግሞ ተቺ የሆኑ ግማሹም የወያኔ ቅጥር ሌላውም ነጋዴ፣ ሌላውም ሌላ ድብቅ ምኞት ያላቸው ሁሉ በብዛት እየሆነ ያለው ጠፍቷቸው ሳይሆን ላለመቀበልና ሕዝቡን ተስፋ ለማስቆረጥ ብዙ እየዳከሩ ነው፡፡ ታዬ ደንደአ ታሰረ ማለት የለማ ቡድን ቀለበት ውስጥ ወደቀ አበቃለት ማለት አድርገው ሊያሳዩን ይፍጨረጨራሉ፡፡ የታዬ መታሰር ግን ሌላ ሺ ታዬ እንደወለደ ማስተዋል አልፈለጉም፡፡ ታዬ ግልጽና እውነት የሆነን የሕዝብና የአገርን ፍትህ ነው በቪኦኤና ዶችቪሌ ጆሮ ላለው ሁሉ የተናገረው፡፡ ከነ ጥዑመ-ቋንቋ አገላለጹ ታዬ እውነታውን እንደወረደ ነበር ለሕዝብ ያደረሰው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያዊ የሆንን ሁሉ ታዬን የሰማንው ለራሳችን እንደሱ ለመሆን ቃል እንድንገባ በሚያስገድደን መልኩ ነው እንጂ ቅጥረኞችና የባዘኑ ጉዱ ፈላ እንዳሉት አደለም፡፡  ተስፋ የቆረጡ ቅጥረኞች ያለ የሌለ አቅማቸውን እያሟጠጡ ይመስላል፡፡ ብዙ ሚዲያዎች ላይ እድል አግኝተው ተናጋሪ የሆኑ ምሁር ነን ባዮች ዛሬ ተራ የፌስቡክ ትችት ላይ ተመስገው እየዋሉ ናቸው፡፡ ማንነታቸውን ከራሳቸው እያነበብንላችም ነን፡፡

ሌላው አሁን እየተካሄደ ያለውን ከወሮበሎች የወያኔ ቡድን ጋር የሕዝብ ልጆች (እነ ለማ) እያደረጉት ያለውን ፍልሚያ እውነታ ውዥንበር ለመፍጠር እነለማ ሂስ ተቀበሉ፣ ኦሮሚያ ውስጥ እኛም ያልቻልነው ችግር ተከስቷል፣ ቄሮን ማስቆም አልቻልንም፣ ምናምን አሉ፡፡ በሚል ወሬ መንዛት እየተጧጧፈ ነው፡፡ አባ ዱላና ቡድኑ ያለውን ቢል አይገርምም፡፡ የእነለማ አቋም ግን እንደማይቀየር ግልጽ ነው፡፡ እነለማ በአቋም እንደጸኑ ተስፋ ስለቆረጡ ዛሬ እነሱ በማይናገሩበት ሁኔታ ሁሉንም ነገር ቆልፈው ሕዝቡን የእነሱን መርዝ ሊግቱት ይችላሉ፡፡ ማስተዋል ከቻልን እነ ለማ እንደልብ እንዳይነገሩና ሁሉንም በራሳቸው ብቻ በኩል ሕዝቡን በወሬና በሽብር ለመፍታት ነው ወሮበላው ቡደን የሽብር-አዋጅ ያወጣው፡፡ እንጂማ ሰላም ለማስፈን ቢሆን እኮ ሕዝቡ እስረኞች በመፈታታቸው እየተረጋጋ የተፈቱትም ሕዝቡን  እያረጋጉትና በሰላማዊ መልኩ ብቻ እንዲንቀሳቀስ እያደረጉት ነበር፡፡ ይህ እልተፈለግም ለወሮበላው ቡደን፡፡ ሰላም የሚባል ነገር ለወሮበላ አደጋ ነው፡፡ ሰላም ከአለማ ወሮበላ እንዴት ቦታ ይኖረዋል፡፡ በሕገወጥነት በሕግ የወደቀን የሽብር አዋጅ አውጆ ጦርነት በሕዝብ ላይ መክፈት ግድ ስለሚለው እኮ ነው፡፡ እርግጥ ነው እቅዱ ሁሉንም ነገር በኖረበት በወንበዴ ወሮበላና አረመኔያዊ መንገድ ሊወጣው አስቦ ነው፡፡ የሚገርመው መቼም ወሮበላ ማሰብ ስለማይችል እንጂ በቆፈሩት ጉድጓድ መቀበር እንደሚመጣ ለማስተዋል ሁኔታዎች ግልጽ ነበሩ፡፡ አሁን ትግሬ ወያኔ መግቢያ መውጫ ወደምታጣበት ቀለበት ውስጥ እየገባች ነው፡፡ ከወያኔ ጋር የወገኑ ሆድ አደሮች ግን አዚም አድርጋባቸው መሆን አለበት፡፡ በአሁን በአለቀ ጊዜ እንኳን ከሕዝብ ጎን በመቆም ያደለቡት ኃጥያታቸው እንዳይወገድላቸው ሕዝብም ምህረት እንዳያደርግላቸው ይበልጠውንም በዚህ ወቅት ከጎኑ ቢቆሙ በክብር እንዳይቀበላቸው ያዳቆነ ሰይጣን እንደሚባለው ከሚያመልኩት ወያኔ መላቀቅን አልወደዱም፡፡ እኛም እሰይ በለናል፡፡ አባዱላ መልቀቂያ አስገባ የተባለ ጊዜ እንደ ጀግና ተቆጥሮ ነበር፡፡ በዛው ትንሽ ቢቀጥል እኮ ሥሙ በወርቅ ቀለም ሊጻፍ ነበር፡፡ ከእግዚአብሔር ግን እይታ ማምለጥ አይቻልም፡፡ ክፉ ስለሆንህ በደንብ ማንነትህ ታውቆ የመጨረሻዋን ጽዋ ከምታመልካቸው ጌቶችህ ጋር ትጎነጫለህ ተብሎ የተፈረደበት ነው የሚመስለው፡፡

በሽብር ሕዝብን ዝም ለማሰኘት ወሮበላው ቡድን እየሞከረው ያለው መፍጨርጨር ተመልሶ እርሱን እየበላው ነው፡፡ ሕዝብ ሰላማዊ በሚል ትግሉን እስካሁን ገፋ፡፡ እየተገደለም ከሰላማዊ አማራጩ ፈቀቅ አላለም፡፡ ወሮበላው በዛው ልክ በሕዝብ ላይ አረመኔነቱን ተያያዘው፡፡ በመቶዎች በግፍ ተገድለው ወደ ሚሊየን የሚጠጋ ሕዝብ ተሰደደ፡፡ እርግጥ ነው አዲስ አደለም፡፡ በበደኖ በአማራው ላይ የጀመረው ቀጥሎም ዋና የወያኔ ቅጥር በሆነው የደቡቡ ሽፈራው ሽጉጤና በሟች አምላኩ (መለስ) ጥምር አረመኔያዊ ትዕዛዝ ከቤንች ማጂ ዞን ከጉራፈርዳ እንደገና ይሄው የፈረደበት አማራ በግፍ እንዲሰደድ ተደረገ፡፡ የጋምቤላ ሕዝብም ሌላው የአረመኔው ቡድን ሰለባ ነው፡፡ እነዚህና የመሳሰሉት አስከፊነታቸው እጅግ ነበር፡፡ ከአለፉት 2-3ዓመት ወዲህ በሚሊየን የሚሆን የኦሮሞው ሕዝብ ይሄው የምናየው ነው፡፡ ይህ ሁሉ ግፍ አሁን ላይ ሞልቶ ፈሰሰ፡፡ ሕዝብም መጀመሪያ ፍትህ ሲል የነበረው አሁን ለካ ፍትህ ከማያውቅ አረመኔ ወንበዴ ቡድን መንግስት ነኝ ብሎ እንደተቀመጠ ተገለጠለት፡፡ ፍትህን ለማምጣጥ ብቸኛው እድል ይሄን አረመኔ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጰያ ምድር ነቅሎ መቅበር እንደሆነ ተረዳ፡፡ ይህም ሆኖ ለዚህ አረመኔ ቡደን እድል ሰጠው፡፡ በሰላም ለቀህ ወደምትሄድበት ሂደ ቢባልም ጭራሽ የተፈራ መሰለው፡፡ እና የሽብር አዋጅ አውጆ ጦርነት ከፈተ፡፡ ውጤቱን በቅርብ እናየዋለን፡፡

ከላይ ከጠቀስኳቸው ግዙፍ የሕዝብ ግፍ ሌላ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወሮበላው ቡድን በከተማና በመኖሪያ መንደሮች በመገኘት ሕዝብን መግደል ሥራዬ ብሎ  ተያያዘው፡፡ ብዙዎች የአሁኑ የሞያሌ ጭፍጨፋ የተለየ መስሏቸዋል፡፡ ከዛ በፊት እኮ በጨለንቆ፣ በሐማሬሳ (ሊያውም ተሰደው በእርዳት በሚኖሩ ላይ)፣ በወልዲያ ሊያውም በጥምቀት በዓል ላይ፣ በነቀምት፣ በቄለም፣ ደምቢዶሎ፣ በብዙ ቦታዎች ተመሳሳይ አረመኔያዊ ድርጊት ሲፈጽም እንቆየ ለብዙዎች ሂደቱ ተነጣጥሎ የሚታይ አስመስሎብናል፡፡ እውነታው ሁሉንም ድርቶች ተመሳሳይና በወጥነት ታቅዶባቸው እየተሰሩ ያሉ የወሮበላው አፈጻጸሞች ናቸው፡፡ በዚህ ሁሉ ሕዝብ ሳይወድ በግዱ ወያኔንና ዘርማንዘሩን ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋጥ እንዲወስን ሆነ፡፡ አሁን ለጦርነት አንድ ሁለት እያለ ነው፡፡ ቦረና ከእንግዲህ ምን ቀረኝ ያለ ይመስላል፡፡ ልጆቹንና ሴቶቹን ኬኒያ አሻግሮ ቤቱ ድረስ መጥቶ ሲገድለው የኖረውን አረመኔ እኔም መግደል አቅበታለሁ ሌለው የወሰነ ይመስላል፡፡ ጎንደር እንደዛው ነው፡፡ መሀል ያለው ሕዝብ ትዕዛዝ እየጠበቀ ነው የሚመስለው፡፡ ከዳር ከተጀመረ ከመሀል በኃይለኛው ፈንድቶ በቀጥታ አራት ኪሎ የመሸገውን አውሬ ገድሎ ሬሳውን ሊያቃጥል ያሰፈሰፈ ነው የሚመስለው፡፡ እየሆነ ያለው እውነት ይህ ነውና የአገሬ ልጅ ተዘጋጅ አላለሁ፡፡ ሳንወድ በግድ ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ የሕዝቡን ትግል ለራሳቸው ርካሽ ንግድ ሊያውሉት እየሞከሩ ያሉ እንዳሉ አንዘንጋ፡፡ ሰሞኑን ግንቦት 7 ነኝ የሚለው በሰፊው ዘመቻ ከፍቶብናል፡፡ ደጋፊዎቹ ነገሮችን በጥሞና የሚከታተሉና ማን ምን እየሰራ እንደሆነ የሚመረምሩ ኢትዮጵያውያን ሊኖሩ እንደሚችሉም የሚያስቡ አይመስለም፡፡ በዚህ ሳምንት ምስራቅ ጎጃም አማኑኤል አካባቢ በአንድ ቦቲ ላይ አደጋ ጣልኩ አለ፡፡ ቀጥሎ ከሽሬ ወደ ደባርቅ ሲጓዝ የነበረ ኮርኔል ገደልኩ አለ፡፡ አዛዡ ሲሞት አጃቢው ግን ምንም አልደረሰበትም በግንቦት7 ደጋፊዎች ፕሮፓንጋ፡፡ ይህ ግ7 የተባለ ቡድን በኢትዮጵያ ሕዝብ የሚነግድ መሆኑ የሚገባን መቼ እንደሆነ አላውቅም፡፡ ዛሬም ግ7 ለኢትዮጵያውያን የሚታገል ነው ብሎ የሚያስብ ቁጥሩ ቀላል አደለም፡፡ ከአርባምንጩ 6 ሰው ገደልኩ ከአለና ለወያኔ ሆን ብሎ ፕሮፓጋንዳ መስሪያ ከሆነበት ቀን ጀምሮ ይህ ቡደን አደገኛ እንደነበር ለማስተዋል ምርምር የሚፈልግ አልነበረም፡፡ ከዛም በከፋ በሻቢያ በኩል፣ ወያኔ አንድ ነገር ቢሆን ወያኔን ለመታደግ ታጥቆ ከተዘጋጀው ደሚሂት ጋር በተቃዋሚነት ቁማር ድራማ የሚሰራ እንደሆነ አላዋቂ ደጋፊዎች ቢያውቁ፡፡ በአለፈው ሥንት ሕዝብ ሲያልቅ አንዳች ያላለው ትግሬ እንዴት ተነካ በሚል ጭራሽ መግለጫ አወጣብን፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ግ7 ያልገባው ለመኖሩ አሁን እየተጠራጠርኩ ስለሆነ የደጋፊዎቹን ማንነት መከታተሉ ወሳኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በአጭሩ ግ7 የተባለ ቡድን ቢያንስ አማራ ክልል ቦታ የለውም፡፡ ግ7 ወያኔ ሰበብ እየፈጠረች አማራን እንድትጨርስ የሚሰራ ቡድን ነው በአጭሩ፡፡ ኦነግ ለኦሮሞ ሕዝብን ለመጨፍጨፍ ለዘመናት ጥቅም ላይ እንደዋለ፡፡ የአሁኑም የሞያሌው ጭፍጨፋ የሄው ሰበብ ተደርጎ ነው፡፡ በቦታው ግን እኮ ምንም እንደሌለ ወሮበሎቹ አሳምረው ያውቁታል፡፡ ከእንደነዚህ ያሉ የአገርና ሕዝብ ጠንቅ ከሆኑ ቡድኖች እንጠንቀቅ አላለሁ፡፡

አሁን ያየሁት ደግሞ በቀለ ገርባ በቤቱ የኦሮሚያን ካርታ ከፎቶው ጎን አስቀምጦ በኢትዮጵያ ሥም ይነግዳል የሚል ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ይገርማል፡፡ በቀለ የፈለገውን ፊትለፊት ለማድረግ ወደኋላ የሚል ሰው አደለም፡፡ የአላመነበትንም ነገር አያደርግም፡፡ ይህም አቋሙ እስር ቤት ዳርጎት ሲሰቃይ ከርሞ ነው የወጣው፡፡ እናውቃለን የኦፌኮ የአሁኑ ቡድን ለወያኔ የእግር አሳት ነው የሆነባት፡፡ አሁን ላይ ሚስጢሩን መናገር ባያስፈልግም እውነታው ግን ኢትዮጵያን ሊታደጉ የተነሱት የለማም በሉት የመረራ ቡድን አንድ የሚጋሩት ጽኑ እውነት አለ፡፡ በቀለ ከሌላው በላይ የኢትዮጵያዊነት መብት አለው፡፡ ለማም እንደዛው፡፡ እውነትንም ፊትለፊት እንዲሰለፉላት ያስገደዳቸው ይህ የተደበቀ ማንነት ነው፡፡ እንጂማ ወያኔ እኮ ኦሮሞን ሁሉ ከኢትዮጰያዊነት አምክና ለራሷ መፈንጫ አድርጋው ነበር፡፡ ዛሬ በቀለ የኦሮሚያን ካርታ ቤቱ ሰቅሎ የሚለው ቁማር በቀለን ሌላው እንዲጠራጠረው ታስቦ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ሲጀምር በፎቶም ለማውጣት የተሞከረው ቅብ እንደሆነ ራሱ ያሳብቃል፡፡ ደግሞ የኦሮሚያን ካርታ ቢኖረውስ ለምን ከኢትዮጵያዊነት ጋር ተቃረነ፡፡ ይህ ሰው እኮ የኦሮሞን ሕዝብ ትግል እየመራ ነው ስለዚህ ትግሉን የአቀደባቸውን የአገሪቱን ክልሎች ያካተተ ካርታ ይኖረዋል፡፡ ኦፌኮ ራሱ የሚንቀሳቀስባቸው ክልሎች ካርታ ይኖረዋል፡፡ እውነታው የእነዚህ (ለማና ቡድኑ እንዲሁም የኦፌኮ ቡድን በአጠቃላይ) በኢትዮጵያዊነት ላይ አቋም ወስዶ ወያኔን እየቀበራት መሆኑ ለወያኔ ግልጽ ነው፡፡

በመጨረሻም ሁላችንም እንንቃ፣ ለሕዝብ ትግል አጋር እንሁን፣ ውዥንብር ፈጣሪዎችን እናጋልጥ፡፡ ሕዝብ እያደረግ ያለውንና ሂደቱን ሕዝቡ ስለሆኔታዎች በደንብ እንዲገነዘብና በውዥንበር ወሬዎች እንዳይምታታ መረጃ መስጠት የምትችሉ አካላት መረጃውን ስጡ፡፡ ለወሮበላ ቡድኖች በጓደኝነት ይሁን በሌላ በአለ ቅርበት አድሮ የሕዝብን ትግል የሚጎዱ ውዥንብሮችን ከሴረኞች ጋር ማጫፈር ከሁሉም የከፋ ክህደት ነው፡፡ ከአገርና ሕዝብ የሚቀድም የለም፡፡ አሁን ያለንው የመጨረሻው ሂደት ላይ ነው፡፡ ሁላችንም በምንችለው ሁሉ የሕዝባችን ትግል ብዙ ተጨማሪ ግፍ ሳይፈጸም ወደምንፈልገው ግብ እንዲደርስ እንትጋ፡፡ እግዚአብሔርም ይረዳናል!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ! አሜን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.