መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ከገበያ ላይ መጥፋታቸው ተነገረ

ቢቢኤን

በኢትዮጵያ መሰረታዊ የሆኑ የፍጆታ ሸቀጦች ከገበያ ላይ እየጠፉ እንደሚገኝ ተነገረ፡፡ ህብረተሰቡ ለዕለታዊ ኑሮው የሚያስፈልጉት መሰረታዊ ሸቀጦች እና ሌሎች ተዛማጅ ነገሮች ከገበያ ላይ መጥፋት ከጀመሩ ቆየት ቢሉም፤ ሰሞኑን የተፈጠረው ክስተት ግን ከነዋሪው የመቻል አቅም በላይ እንደሆነ የቢቢኤን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከሀገር ቤት ያገኘናቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ እንደ ዘይት፣ ስኳር፣ የቡታጋዝ ጋዝ ያሉ መሰረታዊ ነገሮችን በቀላሉ ገበያ ላይ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ዘይት እና ስኳር በቀበሌ መሰጠት ተጀምሮ እንደነበር የገለጹት የአዲስ አበባ ምንጮቻችን፤ በመከራ ይገኝ የነበረው የቀበሌ ዘይት እና ስኳር አሁን ላይ ግን እሱም መጥፋቱን ገልጸውልናል፡፡

እንደ መረጃዎች አስረጂነት፣ የቡታጋዝ ጋዝ እጥረት የተከሰተው በመካሄድ ላይ በሚገኘው የነዳጅ ምርቶች ተዓቅቦ የተነሳ ሲሆን፤ ስኳር እና ዘይት ከገበያ ላይ ሲጠፋ ግን ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ነገር ግን ሁኔታው አሁን ላይ መቻል ከሚቻለው በላይ መሆኑ፤ የህብረተሰቡን ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያከበደው መጥቷል ሲሉ በሀገር ቤት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የታዘቡ ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡ የመሰረታዊ ሸቀጦች መጥፋት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች እንደሚስተዋል ቢታወቅም፤ የችግሩ ቀዳሚ ተጠቂ የሆነችው በእርሻ አልያም በጓሮ አትክልት የማትተዳደረው አዲስ አበባ ነች ይላሉ ነዋሪዎቹ፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች ዕለታዊ ኑሯቸው በአብዛኛው የተመሰረተው ከሱቅ በሚገዙ ሸቀጦች ላይ መሆኑን የሚገልጹት ነዋሪዎቹ፤ ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ ወጣ ያለ ከተሜነት የሚያጠቃት አዲስ አበባ፣ በመሰረታዊ ሸቀጦች እጥረት ቁም ስቅሏን እያየች እንደሆነም የነዋሪዎቹ ገለጻ ያስረዳል፡፡ የተጠቀሱት መሰረታዊ ሸቀጦች ለከተማም ሆነ ለገጠር ነዋሪዎች በእኩል ደረጃ አስፈላጊ ቢሆኑም፤ በተለይ የአፍሪካ መዲና እየተባለች የምትጠራው አዲስ አበባ፣ ስሟ ከዘይት እና ስኳር መጥፋት ጋር ተደጋግሞ መነሳቱ አሳፋሪ ነው በታዛቢዎች ገለጻ መሰረት፡፡ እንደ አጀማመሯ እና ዕድሜዋ፣ የትላልቅ ሳይንሳዊ ቴክኖሎጂዎች ባለቤት መሆን የነበረባት አዲስ አበባ፤ በህወሓት አገዛዝ ጭቆና የተነሳ ዛሬም ምግብ ማብሰያ ዘይት ማጣቷ በእጅጉ ያሳዝናል ሲሉም ገልጸዋል-በችግሩ የተማረሩት የከተማዋ ነዋሪዎች፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.