ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ – ስለ 81ኛው የየካቲት 12 ዝክረ-በዓል መግለጫ

የ2010 ዓ/ም 81ኛው የየካቲት 12 የሰማእታት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ በመዘከሩ እጅግ ከባድ ለሆነው ጉዳይ ቅድሚያ በመስጠት አስፈላጊውን ዝግጅት ላከናወኑትና ለተሳተፉትም ሁሉ ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ – የኢትዮጵያ ጉዳይ ከፍ ያለ ምስጋናውን በአክብሮት ይገልጻል።

እስካሁን  በደረሰን መረጃ መሠረት፤ የሰማእታቱ ቀን የተዘከሩባቸው ሐገሮችና ከተሞች፤

በኢትዮጵያ፤ በአዲስ አበባ፤ ጎንደርና በደብረ ሊባኖስ ገዳም፤
በኢጣልያ፤ በሮምና በቤሉኖ፤
በአሜሪካ፤ በአትላንታ፤ በዳላስ፤ በዴንቨር፤ በማያሚ፤ በኒውዮርክ፤ በዋሺንግተን ዲሲ፤ በሳን ሆዜና በታምፓ፤
በእሥራኤል፤ በኢየሩሳሌም፤
በእንግሊዝ ሐገር፤ በኮቬንትሪና በለንደን፤
በካናዳ፤ በቫንኩቨርና በቶሮንቶ፤
በጀርመን ሐገር፤ በሙኒክ፤ በበርሊን፤ በፍራንክፈርትና በኑረምበርግ፤
በደቡብ አፍሪካ፤ በፕሪቶሪያ፤
በዚምባብዌ።

የካቲት 12 የተዘከረበትም በጸሎት፤ በጉባኤ እና እንደ ዋሺንግተን ዲሲና ቫንኩቨር ከተሞች በተከናወነው መሠረት በሰላማዊ ሰልፍ ነበር።

የካቲት 12 የሚዘከረው ፋሺሽት ኢጣልያ፤ በቫቲካን ያልተቆጠበ ድጋፍ፤ ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ፤ በየካቲት 12-14 ቀኖች 1929 ዓ/ም፤ ኢጣልያኖች 30 000 ኢትዮጵያውያንን ጨፍጭፈው ስለ ነበር ነው። በተጨማሪም፤ በኢጣልያ ወረራ ዘመን በጠቅላላው አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ከመጨፍጨፋቸው በላይ፤ 2 000 ቤተ ክርስቲያኖች፤ 525 000 ቤቶች እንዲሁም 14 ሚሊዮን እንስሶች ወድመው እጅግ ብዙ የኢትዮጵያ ንብረትም በኢጣልያኖቹ ተዘርፎ ነበር። ይህ አልበቃ ብሎ፤ በቅርቡ “የኢትዮጵያ ጨፍጫፊ” በመባል ለሚታወቀው ለሮዶልፎ ግራዚያኒ ኢጣልያኖች የጀግና መታሰቢያ አቁመውለታል።

በውድ ሐገራችን በኢትዮጵያ ላይ ለተፈጸመው የኢጣልያ የጦር ወንጀል፤ ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ – የኢትዮጵያ ጉዳይ ተገቢው ፍትሕ እንዲገኝ እየታገለ ነው። ዓላማውም የኢጣልያ መንግሥት ተገቢውን ካሣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በፕሮጀክት መልክ የሚጠቅም እንዲከፍል፤ የተዘረፉትን ንብረቶች እንዲመልስ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለወንጀሉ እውቅናን እንዲሰጥ፤ ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅና የግራዚያኒ ኃውልትም እንዲወገድ ለማድረግ ነው።

በቸሩ አምላካችን እርዳታም፤ በቅርቡ የኢጣልያ ፍርድ ቤት ለፋሺሽቱ ለግራዚያኒ መታሰቢያ ባቋቋሙት ኢጣልያኖች ላይ የእሥርና የገንዘብ ቅጣት በይኖባቸዋል። ከላይ እንደ ተገለጸውም በዚህ ዓመት የካቲት 12 በኢጣልያ ተዘክሯል።

ለተገኘው የሚያበረታታ ውጤት ከፍ ያለ ምስጋና የሚገባቸው፤
በወንጀለኛው በግራዚያኒ መታሰቢያ ተጠያቂዎች ላይ ፍትሐዊ ብያኔ ያስተላለፈው የኢጣልያ ፍርድ ቤት፤
ክቡር ሚር. ኒኮላ ዚንጋሬቲ፤ በኢጣልያ የላዚዮ አውራጃ ገዢና የአውራጃው ምክር ቤት፤
አንፒ (ANPI (The National Association of Italian Partisans);
ፋሪ (FARI (Federazione Assemblee Rastafari in Italy);
የኢትዮጵያውያን ሕብረተሰብ በሮም (The Ethiopian Community in Rome);
ሚር. ካርሜሎ ክሬሸንቲ (Mr. Carmelo Crescenti);
ሚር. ቫሌሪዮ ቺሪያቺ፤ የፊልም አዘጋጅ (Mr. Valerio Ciriaci, producer of the documentary film: “If
Only I Were That Warrior”;
ሚር. ኢያን ካምፕቤል፤ ስለ አዲስ አበባው ጭፍጨፋ ደራሲ (Mr. Ian Campbell, author of “The Addis

Ababa Massacre”.

እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋትን ፍትሕ ያስገኝልን።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.