ፖለቲካችን እንደ Minesweeper ጨዋታ (ያሬድ ኃይለማርያም)

ከያሬድ ኃይለማርያም
ህዳር 22 ቀን 2018 እ.አ.አ

የወያኔ አገዛዝ ሥርዓት ቀና የሆነውን እና የተቀደሰውን መንገድ የአግድሞሽ ትቶ በተንሻፈፈው ሴጣናዊ መንገድ ጉዞውን ካቀና ውሎ አደረ። ቀናው መንገድ ከወራቶች በፊት ከረዥም የግምገማ ሂድት ማግስት በአደባባይ ወጥቶ ለሕዝብና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰጠው ንስሃና ኑዛዜ የተቀላቀለበት መግለጫ ነበር። እስረኞችን እፈታለሁ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን አሰፋለሁ፣ ብሔራዊና ሁሉን አቀፍ የመግባቢያ ጉባዔ አካሂዳለሁ ወዘተ…። ይህን ዜና ብዙዎች ከሥርዓቱ እኩይ ባህርይ በመነሳት በጥርጣሬ ቢያዩትም ወያኔ ማጣፊያ ሲያጥረው ወንጀሉን ተናዞና ንስሃ ገብቶ ከሕዝብ ጋር የሚታረቅበትን መንገድ እያፈላለገ ይሆናል በሚል በግማሽ ልብ ነገሩ ከቁብ የከተቱም በርካቶች ናቸው። ይሁንና ‘ያዲያቆነ ሴጣን ሳያቀስ አይለቅም’ ሆነና የወያኔ ነገር መታደሱን በተናዘዘ ማግስት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም እራሱን ወደ ለየለት ወታደራዊ አገዛዝ በመቀየር አገሪቱን ከሲቪል አስተዳደር ወደ ወታደራዊ ኮማንድ ፖስት አስተዳደር አሸጋግሯታል። ይህ ወታደራዊ ኃይልም ሕዝብን ለማሸማቀቅና የተጀመሩን ሕዝባዊ ንቅናቄዎች ለማዳፈን የጭካኔ በትሩን በድሃው ሕዝብ ላይ እያሳረፈ ይገኛል። ለዚህም በቅርቡ በሞያሌ ከተማ በጠራራ ፀሃይ በንጹሃን ዜጎች ላይ ሆን ተብሎና በተቀነባበረ መልኩ የተፈጸመው ጭፍጨፋም ጥሩ ማሳያ ነው። የዚህ ጽሁፍ አላማ በህውሃትና በአጋር ደርጅቶቹ መካከል ወይም ወያኔ ከቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በገጠመው ግብግብ ዙሪያ ያሉትን የፖለቲካ ተግዳራቶች መቃኘት ሳይሆን ኢትዮጵያ እንደ አገር ዛሬ የምትገኝበትን አሳሳቢ ሁኔታ ማመላከት፣ ፖለቲካችን ምን መልክ እንደያዘ እና ከዚህ አደጋ ውስጥስ ለመውጣት ያሉን ቀሪ እድሎች ምን እንደሆኑ ለመጠቆም ነው።

በመጀመሪያ ከላይ ከርዕሴ ውስጥ ሻጥ ያደረኩትንና አቻ አማሪኛ ቃል ያጣሁለትን በእንግሊዘኛ ቃል  Minesweeper ተብሎ የሚታወቀውን የኮምፒውተር ላይ ጨዋታ ብዙ ሰው ቢያውቀውም ለማያውቁት ላስተዋውቅና ለጽሑፌ አርዕት እንዲሆን የመረጥኩበትን ምክንያትና ከጽሁፌም ጋር ያለውን ዝምድና ባጭሩ ላብራራ።

ከዚህ በትይዩ የምትመለከቱዋቸው ሦስት ምስሎች የጨዋታውን አይነትና ባህሪይ የሚያሳዩ ናቸው። ፊት ለፊት በምትመለከቱት የመጀመሪያው ሳጥን ውስጥ የሚታዩት የተሸፈኑ ባለ አራት ማዕዘን ሳጥኖች በውስጣቸው ሁለት አማራጮችን ይዘዋል። አንዱ፤ ከ1 እስክ 3 ያሉ ቁጥሮችን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሚፈነዱ ፈንጂዎችን ነው። በመጀመሪያው ሳጥን ውስጥ እንደሚታየው የትኛው ክፍልፋይ ቁጥርን ወይም ፈንጂን እንደያዘ ማወቅ አይቻልም። የሚጫወተው ሰው የመጀመሪያውን እድል የሚሞክረው በአቦ ሰጥ ወይም በግምት ብቻ ነው። አንዳንዴ ገና በመጀመሪያው ሙከራ የምንነካው ክፍል ፈንጂ ሊሆን ይችላል። ካልሆነ ግን ከሦስቱ ቁጥሮች አንዱን እናገኛለን። ፈንጂው ከሆን በአንድ ሙከራ ጨዋታው ያከትማል። ምክንያቱም ተቀጣጣይ ፈንጂዎች ስለሆኑ በየ ክፍልፋዩቹ ውስጥ ያሉት ሁሉም በአንዴ ይፈነዱና ጨዋታው ይፈጸማል። በእድል ቁጥር ከወጣ የሚቀጥሉት እርምጃዎቻችን በጥንቃቄና እጅግ ከፍተኛ ማስተዋል የተሞላበት ካልሆነ በማናቸውም ሰአት በሌሎቹ ክፍልፋዮች ውስጥ ከተቀበሩት ፈንጂዎች አንዱን የመንካት እድላችን እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ አሁንም ጨዋታው በተሸናፊነት ይጠናቀቃል። እያንዳንዱ የሚወጣው ቁጥር ቆይታችንን ከማደሱም ባሻገር በአካባቢው የተደበቀውን የቦንብ መጠን አመላካችም ስለሆነ እርምጃችንም በሱ የተወሰነ ይሆናል። መጀመሪያ የወጣልን ቁጥር አንድ ቢሆን ከእሱ ጋር ከተነካኩት ሳጥኖች ውስጥ በአንዱ የተቀበረ ፈንጂ አለ ማለት ነው። ሁለትና ሦስትም ከሆነ የወጡት እንዲሁ ከቁጥሮቹ አጠገብ ባሉ ሳጥኖች መካከል በሁለቱ ወይም በሦስቱ ውስጥ የተቀበረ ፈንጂ ስላለ ተጠንቀቅ ማለት ነው።

በዚህ መመሪያና በእድል እየተመራ ፈንጂ የተቀበረባቸውን ሳጥኖች ሳይነካ አብዛኛውን የሳጥኑን ክፍሎች መክፈት የቻለ ሰው ከታች የምትመለከቱትን ውጤት በማግኘት የጨዋታው አሸናፊ ይሆናል። ሲደናበር አንዱን ፈንጂ የረገጠ ሰው ደግሞ ከመነሻው ወይም በጉዞ ላይ እንዳለ በመሃል የምትመለከቱትን ውጤት ያገኝና ሳጥኑን በበርካታ ፈንጂዎች ሸፍኖ ተሸናፊነቱንም ያረጋግጣል። ከጨዋታውም ይወገዳል። ያንኑ ጨዋታ መልሶ ሊጫወት አይችልም። ሌላ እንዳዲስ ይሞክራል እንጂ። እድሉ አንድ እና አንድ ብቻ ነው። አንዴ ከከሸፈ ከሸፈ ነው።

የአገራችንም ፖለቲካ በዚህ ጨዋታ ውስጥ የሚታየው አይነት አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ይመስለኛል። ትልቁ ሳጥን ኢትዮጵያን ይወክላል። በውስጡ የሚታዮት በርካታ ክፍልፋዮችና ትናንሽ ሳጥኖች ደግሞ አገሪቱ ውስይ ያለውን የቋንቋ፣ የጎሳ፣ የኃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል፣ የኑሮ ደረጃና ሌሎች ስብጥሮችን ይወክላሉ። ተጫዋቹ ህውሃት ይሁን ወይም ኦህዴድ ወይም ብአዴን ይሁን ሌሎች አጋር ድርጅቶች ወይም ኢህአዲግ እንደ ግንባር ወይም ከወያኔ ማዕቀፍ ውጭ ያሉ የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች ወይም ትጥቅ ያነሱ የለውጥ አቀንቃኞች ወይም ኢትዮጵያን ለማዳንም ይሁን ለመበታተን ያደፈጡ የውጪ ኃይሎች የዚህ ጨዋታ ፈተና ከፊታቸው የተደቀነ ይመስለኛል። እድሉም አንድና አንድ ብቻ ይመስላል።

ሲነኩ ሊፈነዱና ከአንድ ጫፍ እስከ ሌላ የአገሪቱ ጫፍ የተጠመዱትን ፈንጂዎች ሊያቀጣጥሉ የሚችሉ በርካታ ነገሮች በአገሪቱ ውስጥ ተከስተዋል። ይሁንና የመጫወቻው ሜዳ ፈንጂ ብቻ እንዳልሆነው ሁሉ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊያንን ከአደጋ ሊታደጉና አገሪቱንም ወደ ተሻለ አቅጣጫ ሊወስዱ የሚችሉ በጨዋታው ላይ እንዳሉት ቁጥሮች እድልና ተስፋን የሚሰጡ፤ ከዛም አልፈው በቀጠናቸው ያሉትን የተጠመዱ ፈንጂዎች መጠን በመጠቆም አደጋዎች መኖራቸውን ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሚሰጡ በርካታ ነገሮችም አሉን። እንግዲህ የጨዋታው መጨረሻ በተጫዋጩ አስተዋይነትና ጠንቃቃነት እንደሚወሰነው ሁሉ በአገራች ፖለቲካ ውስጥ በቀጣይ የሚወሰዱ ማናቸውም እርምጃዎች አንድም መጥፊያችን አልያም ተስፋችንን የሚያለመልምና ወደ ብርሃን የሚወስድ ሊሆን ይችላል። ይህንን መረዳት ግን የእያንዳንዱ የፖለቲካ ኃይል ብቃት፣ አስተዋይነትና ኃላፊነትም ነው።

ስር የሰደደው ድህነት፣ መረን የለቀቀው ሙስና፣ የፍትህ እጦት፣ የኢኮኖሚ ድቀቱ የፈጠረው ስራ አጥነት፣ ያልተመጣጠነ የሃብት ክፍፍልና የማህበራዊ ፍትህ መጓደል፣ የተጠያቂነት መጥፋት፣ የመሰረታዊ አቅርቦቶች በከፋ ሁኔታ መጓደል፣ የመልካም አስተዳደር እጦት ያስከተለው ክፌትና ብሶት፣ በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች የሚታዩት ዘር ተኮር ግጭቶች፣ የአገዛዝ ሥርዓቱ መፍረክረክና በሂደትም እራሱን ወደ ወታደራዊ አስተዳደር እየቀየረ መምጣቱ፣ የተቃዋሚው ጎራ መዳከምና እጅግ የተሰበጣጠረና እርስ በራሱም የማይተማመን፣ የጎሪጥ የሚተያይ መሆኑ፣ ለህሊናቸው ያደሩ የኃይማኖት መሪዎች መታጣትና ሌሎችም ችግሮች ተደማምረው የተቀጣጣይ ፈንጂውን መጠን ያበራከቱት ይመስለኛል።

እንግዲህ የቀሩት ጥቂት ነገሮች ናቸው። አርቆ አስተዋይ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በአገዛዝ ሥርዓቱም ውስጥ ሆነው ለህሊናቸው ያደሩና የእዚችን አገር ክፉ ማየት የማይመኙና ሕዝብንና አገርን የሚያስቀድሙ እንድ እነ አቶ ለማ መገርሳ ያሉ ሰዎች፣ ጥቂትም ቢሆኑ ሆደ ሰፊና አስተዋይ የሆኑ የተቃዋሚ ፖርቲዎች መሪዎችና አባላት፣ ለተሻለ ማህበራዊ ፍትህ የሚታገሉ የሲቪክ ማህበራት አባላት፣ ለህሊናቸውና ለሙያቸው ያደሩ ጋዜጠኞችና የለውጥ አራማጆች እነዚህን የተጠመዱ ፈንጂዎች በማምከንም ሆነ በተቀበሩበት ሳይፈነዱ እንዲቀሩና ኢትዮጵያ ይህን ክፉ ጊዜ በጥንቃቄ እንድትሻገር የማድረግ አቅም ሊፈጥሩ ይችላሉም፤ ይገባልም።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ግልጽና ግልጽ ናቸው።

  • ከወያኔም ሆነ ከመጻዒ ወያኔ ወይም የወያኔን በትረ-ሥልጣን ከሚቋምጡ ወረፋ ጠባቂ አፋኝና አንባገነናዊ ሥርዓቶች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መላቀቅ፣
  • ኢትዮጵያዊያን በፖለቲካ አመለካከታቸው ወይም በጎሣ ማንነታቸው ወይም በኃይማኖታቸውም ሆነ በሌሎች ማንነቶቻቸው ሳቢያ የማይዋከቡባት፣ የማይታሰሩባት፣ የማይገደሉባት፣ የማይሳደዱባትና የማይሸማቀቁባት አገር ባለቤት መሆን፣
  • ሕዝብ የአገሩና የሥልጣን ባለቤት የሆነባት ኢትዮጵያ እንድትኖር እና
  • ሁሉም ዜጋ በእኩልነትና በፍትሀዊነት የሚታይበት፣ የሚዳኝበትና ተጠቃሚ የሚሆንባት አገር ባለቤት መሆን ነው””

እነዚህን የሕዝብ ጥያቄዎች በተሟላ መልኩ ለመመልስ የሚያስችል ተክለ አቋም ያለው የፖለቲካ አደረጃጀትና ስብዕና ያስፈልጋል። የአገዛዝ ሥርዓቱ ይህን ፈተና ከወደቀ ውሎ አድሯል። ዛሬ ላይ ከረፈደ ተነስቶ ያሚያደርገው መላላጥና መጋጋጥ የትም እንደማያደርሰው በግልጽ የሚታይ ነው። በተቃዋሚዎችም ጎራ እነዚህን ጥያቄዎች በራሱ አቅም ብቻ ለመመለስ የሚችል ተክለ አቋም ያለው አንድም ድርጅት አለ ብዮ አላምንም።

 

መፍትሔ

እንደ እኔ እምነት መፍትሄው ብዙዎች ደጋግመው እንደገለጹት አንድና አንድ ብቻ ነው። ይህውም ሁሉም የፖለቲካ ኃይል ያዘጋጁዋቸውን የፓሪቲዎቻቸውን ማኒፌስቶዎች፣ የሚከተሉትን የፖለቲካ ፍልስፍና ወይም የአስተሳሰብ ምሪት፣ የጎሳ አጥርና ሌሎች ልዩነቶቻቸውን ለጊዜው በየኪሳቸው ያቆዩዋቸው። እነዚህ ልዩነቶች ሊቀነቀኑና በተወዳዳሪነት ሊቀርቡ የሚችሉት አገር አማን ሲሆንና ሕዝብ በሰላም ወጥቶ ሲገባ ብቻ ነው። ማኒፌስቷቸውንም አገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለምታደርገው ዲሞክራሲያዊ ምርጭ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ዛሬ ላይ ግን ሕብረ ብሄራዊም ይህን የብሔር ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማህበራት ይሁኑ የለውጥ አራማጆች፤ ሁሉም አንድ የጋራ አጀንዳ አላቸው። ይህውም አገርና ሕዝብን አላስፈላጊ ከሆነ ደም አፋስሽ ግጭትና እልቂት መታደግ ነው። በዚህ አጅንዳ ላይ ብቻ ያተኮረ አንድ ታላቅ ንቅናቄ መፍጠር ካልተቻለ ይህ ድህነት ያቆረቆዘው ህዝብ ብቻውን ሲጮህ ቢውልና ቢያድር ሰሚ አያገኝም። ይልቁንስ የወያኔ ጥይት ሰለባ እየሆነ መምጣቱ ሲበረታ ቁጣውም ሰከን ይላል እንጂ ትግሉን ፈቅ አያደርገውም። ይህ ተሰበጣጥሮና አጥር ሰርቶ የተቀመጠው የፖለቲካ ኃይል ለህዝብ ጥሪ ተግባራው ምላሹን ሳይውል ሳያድር ካልሰጠ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጩኸት ጆሮ ዳባ ልበስ ካለው የአለም አቀፍ ማህበረሰብ በምን ይለያል? በወያኔ ጥላ ስር ማን ይጠቅልለን ከሚለው ጉንጭ አልፋ የመንደር ፖለቲካ ወጥተን ከወያኔ የአገዛዝ ሥርዓት እንዴት እንላቀቅ የሚለው ላይ ማተኮሩ ይበጃል። ምዕራብያዊያኑና ወያኔ እያጋነኑ የሚያያራግቡትና የሚያናፍሱት ሰላማዊ የጠቅላይ ሚኒስትር ሽግግር ‘ዶሮን ሲያታልሏት‘ አይነት ነገር ስለሆነ እሱን ለነሱ ብንተወው።

 

ቸር እንሰንብት

ያሬድ ኃይለማርያም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.