ምን ያደርግ ደብርዬ¡ አብራክ የብረት … (ሥርጉተ ሥላሴ የሳተናው አምደኛ)

ከሥርጉተ – ሥላሴ 22.03.2018 (ከጭምቷ – ሲዊዘርላንድ)
„ኃጢያት የሚሠሩ ይሰወሩበት ዘንድ ጨለማ ወይንም የሞት ጥላ የለም።“ (መጽሐፈ እዮብ ምዕራፍ ፴፬ ቁጥር ፳፩)

ምን ያደርግ ደብርዬ¡ አብራክ የብረት …
የአሳር ምልክት፤ በሚስማር መርጐት።

የጭካኔ አቤታ፤ ገዳይ የአንደበት፤
የመኖር ተቃርኖ፤ የጥፋት ውልደት፤
የሲዖል ምስለኔ ቃል-አቫይ ግብዘት።

ምን ያድርግ ደብርዬ¡ አብራክ የብረት …
የፍዳ ምልክት፤ በሚስማር ገርሞት።

ብትሰሩለት ምንው የብረት ገበርዲን?
ብትሰፉለት ምነው የባሩድ ከረባት?
ብታጫሙት ምነው ጫማ የቀልሃ?
እሱ የሚያሰኛው የመትረዬስ ዘኃ።

ምንያድርግ ደብርዬ¡ አብራክ የብረት …
የራሮት ምልክት፤ በሚስማር መርጐት።

ሳጥናኤል ቢመጣ ማንችሎት እሱን?
ጭራቁም ቢመጣ ማንችሎት እሱን?
ሲዖሉም ቢመጣ ማንችሎት እሱን?
አደላድሎ ይዞት ‘ሚሊዬን ቀብርን።

ምን ያድርግ ደብርዬ¡ አብራክ የብረት …
የጥፋት ምልክት፤ በሚስማር ገርሞት።

ኧረ! እሱ ምን ተዳው? ምኑስ ሲገድበው?
ጫካው ዱር ገደሉ ሰባኪ እያለው።
ዝናር ከወገቡ መች ተገኝቶ ያውቃል?
ሳንጃው ከሽንጡ ላይ መች በመኖርን ያውቃል?
የብረት ፖስተኛው ጭንቅላት ገዳማይ፤
ዓይን ዓዋጅ ሆነበት የሞት ግዳይ ሲሳይ።

ምን ያድርግ ደብርዬ¡ አብራክ የብረት …
የለቅሶ ምልክት፤ በሚስማር መርጐት።

ይሄው ተደመረ // ይሄው ተቀነሰ፣
እንዲህ ነው ባዘቶ // መባጃው መቀሰ፤
የዋይታ // የምሾ በጀት ሲሞገስ፣
ማዕልተ – ተለሌት፤ የዕንባ ጎርፍ ሲቀስ።

ምን ያድርግ ደብርዬ¡ አብራክ የብረት …
የጭንቁን ምልክት፣ በሚስማር ገርሞት።

የደብርዬ¡ እናት የት ይሆን ያለሽው?
የደብርዬ¡ እህት የት ይሆን ያለሽው?
የደብርዬ¡ አክስት የት ይሆን ያለሽው?
የደብርዬ¡ አጋሩ ሁሉዬ የሆንሽው?
እርሻው ደም ጠገበ // አዬሩም ደም ሆነ፣
አስፓልቱ እራሰ ሰውነት መከነ፤
ንፋሱም አነባ ጭጎጎት ከወነ፤
ጭጋጉም ድል ነስቶ ሞት በዓይነት ዘበነ።

ምን ያድርግ ደብርዬ¡ አብራክ የብረት …
የሞቱን ምልክት፤ በሚስማር መርጐት።

የጠማው ስለሱ
የራበውም ስልሱ
ደምቅዳ ደምመልስ ማክተሚያው ነው ምሱ።
ያለደም አይነጋ የደብርዬ¡ ህልሙ፣
ያለጭንቅ አይውልም የደበርዬ¡ ስልሙ፣
ያለስጋት ላይሆን መላጊያው ገርዳሙ፣
አራዊተ – ነፍሱ፤ ፍጥረት ዓለሙ።

ምን ያድርግ ደብርዬ¡ አብራክ የብረት …
የመርዶ ምልክት፤ በሚስማር ገርሞት።
• ለዕንባ ቤተኞች በሙሉ ይሁንልኝ። (22.03.2018)
አማኑኤል አባታችን በቃችሁ ይበለን። አሜን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.