አርቲስት ፈቃዱ ተከለማርያም መግለጫ ሰጠ – “እኔ እንድኖር ካስፈለገ መጀመሪያ እሷን አሳክሙ”

አድማስ ሬዲዮ

አርቲስት ፈቃዱ ተክለማርያም ዛሬ ቅዳሜ አፍሮዳይት በተባለ ሆቴል አዲስ አበባ ውስጥ መግለጫ ሰጥቷል። በዚህ መግለጫውም ከተዋጣለት ገንዘብ ውስጥ ሜላት አሰፋ ለተባለችውና ሁለት ኩላሊቶቿ ለታመሙት የ19 ዓመት ታዳጊ ከተሰጠው ማካፈል እንደሚፈልግ አስታውቋል። የፍቃዱ ተክለማርያም ሙሉ ንግግር የሚከተለው ነው።

“ሰው ፊት መቅረብ ብዙም አልወድም . ፈተና ሲገጥመኝ .. እመብርሃንን ከነልጇ ጠይቄ አሳፍረውኝ አያውቁም፣ ዛሬ የመጣሁት ላመሰግን ነው፣ የሰው ሃብታም ነኝ፣ ግን ሃብታም ልሁን ብዬ አላውቅም፣ የሰው ፍቅር አለኝ፣ እሱን አይቻለሁ፣ ከዚህ በላይ ሃብት የለም፣ የመጣሁት ላመስግን ነው፣ እናትና ልጁን ፣ ሁላችሁንም ፣ ባለቤቴን፣ ቤተሰቤን ላመስግን፣ የሙያ ጓደኞቼን፣ መቅደስ ጸጋዬ፣ ሃይሉ ከበደ፣ መሰረት መብራቴን፣ ቴዎድሮስ ተሾመ እና ሌሎችንም ላመሰግን ነው፣ የሚዲያ ባለሙያዎችን ላመሰግን ነው፣ ከዓለም ዳርቻ ሁሉ የተጨነቀልኝን ሁሉ አመሰግናለሁ፣ …..”

“……. እኔ ሞቼ አንተ ኑር ያለኝን ሁሉ ፣ ቋንቋ እስኪያጥረኝ ድረስ አመሰግናለሁ፣ ዘርና ሃይማኖቴን ሳይጠይቁ የለገሱልኝ ሁሉ አመሰግናለሁ …… ኩላሊት መስጠት ባልችል፣ በሬዬን ሸጬ እሰጥሃለሁ ያሉኝን የሎሜ ወረዳ ምስራቅ ሸዋ ያሉ ገበሬ፣ . እስር ቤት ሆነው የራሳቸው ችግር ሳያንስ እኔ እያለሁ አንተ አትታመምም ብለው ከፍተኛ ገንዘብ የላኩልኝን አቶ ከተማ ከበደ (አንድ ሚሊዮን ብር እንደረዱት ተሰምቷል) ፣ በ97 ዓመታቸው ኩላሊት የሚሰጥ ከሆነ የኔን ስጡልኝ ያሉትን እማ ወርቅዬ ፣ እንዲሁም ሌሎች .. ጳውሎስ ሆስፒታል ላሁኑም ለወደፊቱም ላደረጉልኝ ሁሉ፣ ሙሉ ወጪዬን እሸፍናለሁ ያለውን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከሩቅም ከቅርብም ያላሰብኩትን ፍቅር ላሳየኝ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ። ግማሹ እዚሁ ታከም፣ ሌላው ውጭ አገር ታከም ይለኛል . እሱን ወደፊት የምናየው ይሆናል።…..”

“…….ከሁሉት በፊት ግን የኔ ዕድሜ ስልሳዎቹ ውስጥ ነው፣ ነገር ግን ገና ትንሽ ልጅ ኩላሊቷ ሥራ አቁሞ ተቸግራለች፣ እናም እሷ እያለች እኔ ቀድሜ ልታከም አልችልም፣ የህዝብ ፍቅር ያስተማረኝ ይህንን ነው፣ ስለዚህ እኔ እንድኖር ካስፈለገ መጀመሪያ እሷን አሳክሙ፣ ለኔ ከተዋጣው ውስጥ ለሷ ያስፈልጋታል የሚባለውን ገንዘብ ለመስጠት እፈልጋለሁ፣ ወደፊትም ለኔ የመጣውን በረከት ለሷም የማካፍል መሆኔን አረጋግጣለሁ፣ እንዲህ በማድረጌ እንደማትቀየሙኝ ተስፋ አደርጋለሁ። እንደኔ ታመው አስታዋሽ ያጡትን ሁሉ እመብርሃን ከነልጇ ትርዳቸው። ”

ሲል መግለጫውን አጠቃሏል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.