“ለኛ ያለኛ ማ” (በአርቲስት መሠረት መብራቴ)

ተወዳጁ አርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም መታመሙ በሚዲያ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ በአጭር ቀናት ውስጥ አስገራሚ ምላሾች ከመላው አለም እየጎረፉ ነው:: አቤት ፍቅር! አቤት አክብሮት! ለዘመናት በሙያው ሲያገለግለው የነበረው ህዝብ ምላሹን ከቃላት በላይ በተግባር አሳይቶታል:: ህዝቡ ዜናውን ከሰማበት ጊዜ ጀምሮ ያሳየው እርብርብ እጅግ ልብ የሚነካ ነው! ኩላሊታችን መለገስ እንፈልጋለን ብለው ቃል ከገቡ ወገኖች ጀምሮ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት በተከፈቱ አካውንቶች ለተደረገው ወገናዊ ምላሽ ምስጋናችን ላቅ ያለ ነው::አርቲስቱ ለአምስት ዓመታት በክብር አምባሳደርነት ያገለገለው ጤና ጥበቃ የህክምና ወጪውን ሸፍኖ በሀገር ውስጥ እንዲታከም መወሰኑም ደስ የሚል ዜና ነው::

የህክምና ባለሙያዎች እንደገለፁት የኩላሊት ህክምና በአንድ ጊዜ ብቻ የማይቆም ስለሆነ ንቅለ ተከላው ከተከናወነ በኃላም በድሜ ዘመን የማይቋረጡ ክትትሎች ስለሚኖሩ ሙሉ በሙሉ ገንዘቡ ለአርቲስቱ ርክክብ ተደርጎ በህክምና ሂደቱም ሆነ ከዛ በኃላ ለሚያስፈልጉት ወጪዎች የሚውል ይሆናል::

በቀጣይ የታሰቡ ገቢ የማሰባሰብ ሂደቶችም እንዳሉ ሆነው:: በዛሬው እለት በአፍሮዳይት ሆቴል በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ በራሱ አንደበት ህዝቡ ላደረገለት ወገናዊ ድጋፍ ምስጋናውን አቅርቦ በተመሳሳይ ህመሞ ለምትሰቃይ ለአንዲት ሜላት ለተባለች ታዳጊ ህዝቡ ካደረገለት ድጋፍ 200,000 (ሁለት መቶ ሺ ብር) በመለገስ እጅግ የሚያኮራ ተግባር ፈፅሞአል:: ልብ የሚነካ የፍቅር ምላሽ! ሁልጊዜም ነገሮች የሚከናወኑበት የራሳቸው ምክንያት አለና በጋሽ ፍቃዱ ምክንያት ይህቺ ታማሚ ይህን እድል አግኝታለች:: እግዚአብሔር ይማራት::

ይሄ አጋጣሚም ስለህመሙ ክብደት ግንዛቤን እንድናገኝና በዚህ ህመም ለሚሰቃዩ ወገኖችም ድጋፍ ማድረግ የሁላችንም ሀላፊነት እንደሆነ ትልቅ የቤት ስራ ሰጥቶናል:: አሁንም ነገሮች በአግባቡ እንዲከናወኑ ፀሎታችሁ አይለየው:: በሙሉ ጤንነት ሆኖ በተመሳሳይ መድረክ ፈጣሪውንም ህዝቡንም የሚያመሰግንበት ቀን ቅርብ እንዲሆን ምኞቴ ነው:: እግዚአብሄር አምላክ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.