ኢትዮጵያ በዴር ሱልጣን ገዳም ያላትን ይዞታ ልታጣ ትችላለች ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 17/2018) ኢትዮጵያ በእስራኤል በሚገኘው የዴር ሱልጣን ገዳም ያላት ይዞታን ልታጣ እንደምትችል ተገለጸ።

ሰሞኑን በግብጽ በኩል የመጣውን ጫና ተከትሎ በእስራኤል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው። ከትላንት በስትያ ቅዳሜ ግብጾች በኢትዮጵያ ይዞታ ላይ ወረራ መፈጸማቸው ታውቋል። በየዓመቱ የፋሲካ በዓል ሲደርስ እንዲህ ዓይነት ወረራ የተለመደ ቢሆንም ዘንድሮ የሆነው የኢትዮጵያን ይዞታ አደጋ ውስጥ የሚከት ነው ሲሉ በእስራኤል ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል።

ኤምባሲውም ሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምንም ያደረጉት ነገር የለም የሚሉት ኢትዮጵያውያን ሁኔታዎች በዚሁ ከቀጠሉ የኢትዮጵያ ይዞታ ሙሉ በሙሉ በግብጽ እጅ ላይ መውደቁ አይቀርም ሲሉ ስጋታቸውን  ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በእስራዔል ከ4ኛው ክፍለዘመን አንስቶ ጠንካራ ይዞታ እንደነበራት መረጃዎች ያመለክታሉ። ዴር ሱልጣን በተሰኘው ገዳም አራት አብያተ ክርስቲያናት የነበራት ኢትዮጵያ በየዘመናቱ በነበሩ  ነገስታት  ተገቢው ድጋፍ ባለመደረጉ ቤተክርስቲያናቱን ልታጣቸው እንደቻለችም ይታወቃል። አሁን የቀራት በገዳሙ ጣሪያ የሚገኝ አንድ የጸሎት ቦታ ሲሆን ይህንንም ለመንጠቅ በግብጾች በኩል ከፍተኛ ጫና ሲደረግ ቆይቷል። በተለይም የፋሲካ በዓል ሲደርስ ግብጾች በብዛት ወደ ገዳሙ በመምጣት ወረራ የሚፈጽሙበት የተለመደ ተግባራቸው የኢትዮጵያውያንን በገዳሙ ያላቸውን መብት የሚጋፋ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነሳል። ከ1970 እ ኤ አ ጀምሮ በግብጾች በኩል የሚደረገውን ጫናና ወረራ  በመቋቋም የቀረውን ይዞታዋን አስጠብቃ የቆየችው ኢትዮጵያ ዘንድሮ ጫናው የበረታ ሆኖ መጥቶባታል። ባለፈው ቅዳሜ ግብጾች በኢትዮጵያ ይዞታ ላይ ወረራ በመፈጸም የኢትዮጵያን ባለበትነት አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ ማድረጋቸውን ነው በእስራዔል ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያን የሚገልጹት። በእስራዔል ከ50 ዓመት በላይ የኖሩት አቶ ብርሃኑ ዮሴፍ እንደሚሉት ቅዳሜ ሌሊት ግብጾቹ የኢትዮጵያን ይዞታ ወረዋል። ይዞታው የእኛ ነው – ውጡ ነው የሚሉት ግብጾቹ።

ቆይተው በውዝግቡ ቦታ የደረሱት የእስራዔል ፖሊሶች በገዳሙ የኢትዮጵያውያን መጠቀሚያ የሆኑ ሁለት መጸዳጃ ቤቶች በራቸው እንዲገነጠል ማድረጋቸውን ኢትዮጵያውያን በቁጭት ያነሱታል። ከእኛ ይልቅ የግብጾቹ ድምጽ ይሰማል ነው የሚሉት ኢትዮጵያውያኑ። በዚህ ሳምንት ለትንሳዔ በዓል ከ10ሺህ በላይ ግብጻውያን ወደ ገዳሙ እንደሚመጡ የገለጹት አቶ ብርሃኑ አንድ ነገር ሊያደርጉብን ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

የግብጾቹ ጫና በሂደት ገዳሙን ለቀን እንድወጣና ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ፡ የመንግስታቸው ድጋፍ ስላላቸው፡ እስራዔልም ከእኛ ይልቅ የምታደላው ለእነሱ በመሆኑ፡ እንዲሁም ለኢትዮጵያ የሚከራከር መንግስትም ሆነ ሌላ አካል ባለመኖሩ በዴር ሱልጣን ያለን ይዞታ አደጋ ላይ ወድቋል በማለትም ይገልጻሉ።

በእስራዔል ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገዳሙ ላይ የኢትዮጵያን መብት ለመንጠቅ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በቸልታ እንዳይመለከቱት ያሉት አቶ ብርሃኑ የትንሳዔ በዓል እስኪያልፍ ድረስ ኢትዮጵውያኑ ከገዳሙ አከባቢ እንዳይርቁ ጥሪ አድርገዋል። ለሚመለከተው የእስራዔል መንግስት አካል በሙሉ በተለያዩ መንገዶች እየቀረብን ድምጻችንን ማሰማትም አለብን በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.