አብይ ሆይ ጆሮ ካለህ ስማ!

ግዮን

በትላንትናው እለት የኢህአዴግ ምክር ቤት ዶ/ር አብይን የግንባሩ ሊቀ መንበር አድርጎ መምረጡን አሳውቋል። ዛሬ ደግሞ የኢህዴግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ የግንባሩ ሊቀ መንበር የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ አሳውቀዋል። እኔ የኢህአዴግ ከፋፋይ፣ ጨቋኝና አፋኝ ፖሊሲዎች ቀንደኛ ተቃዋሚ ነኝ። ኢህአዴግም በህዝብ የተመረጠ ድርጅት ነው ብዬ አላምንም። ይልቁን የህዝብን ድምፅ ማጭበርበርንና ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ ማናከስን እንደ እድሜ ማራዘሚያ እየተጠቀመ እስከ ዛሬ የቆየ ወታደራዊ ሃይል ነው ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ በመሰረቱ የኢህአዴግ ሊቀ መንበር ማንም ሆነ ማን ሊሞቀኝም ሆነ ሊበርደኝ አይገባም ነበር። ነገር ግን አገራችን ኢትዮጵያ በወቅቱ ካለችበት መስቀለኛ መንገድ አንፃርና በነአቶ ለማ ቡድን ውስጥ ባለፉት አጭር ግዜያት ውስጥ ከተስተዋሉ ኢ-ኢህአዴጋዊና ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች አንፃር በጉዳዩ ላይ በይፋ አቋም መያዝ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

በአጭሩ የዶክተሩን መመርጥ እደግፋለሁ። የምደግፈውም በሚከተሉት ምክንያቶች ነው።

 1. 1. የእውነት ለውጥ የሚፈልግ ሰው ይመስላል፤ እንደ ቀደመው ጠቅላይ (ድንቄም) ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም የሆነ ሰውን ሌጋሲ ለማስፈጸም ተፍ ተፍ የሚል ጉዳይ አስፈፃሚ ሳይሆን እውነተኛ ለውጥን ለአገሪቱ ለማምጣት ተግቶ የሚሰራ፣ የተሰነጣጠቀውን የአገር አንድነት ለመሰብሰብ የሚተጋ፣ የራሱንና ያመነበትን ነገር ለማድረግ ወደ ኋላ የማይል ልበ ሙሉ ሰው ይመስለኛል።
 2. ከንግግሮቹ እንደተረዳሁት የህዝብን አንድነትና እርቅ የሚፈልግ ሰው ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ዶ/ር አብይ የአንድነትን ጥቅም ማወቅ ብቻ ሳይሆን ከአንድነት ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ደጋግሞ ሲናገር አዳምጫለሁ። (“እንደህዝብ ከመደመር ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም።”) ከመናገርም ባለፈ ባለፉት 27 ዓመታት በጎሪጥ እንዲተያዩ ተፈርዶባቸው የነበሩትን የአማርኛና የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያንን ለማቀራረብ እሱና አቶ ለማ የወሰዱት እርምጃ ምን ያህል ከመናገር ባለፈ ከልብ የመነጨ የአንድነትና የእርቅ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳያል።
 3. በእሱና በለማ የሚመራው የኦህዴድ ቡድን የኢትዮጵያን ታሪካዊና ወቅታዊ ችግሮች በሚገባ ተርድተዋል ብዬ አስባለሁ።ለዚህ ማስረጃ እንዲሆን ኦህዴድ ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ያሳየውን እንቅስቃሴ ማስታወስ፣ መግለጫቸውንም መመልከት በቂ ይመስለኛል። እንደ ምሳሌ ያህል ግን ከኦሮሚያ ክልል የመታወቂያ ካርዶች ላይ ብሄር የሚለውን ማስወጣታቸው፣ ከብአዴን ጋር የጀመሩት አስደናቂ መናበብ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ የመደብ እንጂ የብሄር ጭቆና እንዳልነበረ እንደሚያምኑ የሚፈነጥቅ መግለጫ ማውጣታቸውና ለሎች መሰረታዊ እርምጃዎችን ለአብነት ያህል መጥቀስ ይቻላይ። የዶክተሩን ንግግር ለመጥቀስ ያህል “ታሪክ ለነገ ድልድይ ከሆነ መልካም ነው። ታሪክ ዛሬን የሚያበላሽብን ከሆነ ግን ችግር አለ።”
 4. በአደጋ ግዜና በውጥረት ሰዓት ያሳየውን መረጋጋትና ከስሜታዊነት ውጪ የሆነ አመራር ወድጄዋለሁ። ለአንድ መሪ ከሚያስፈልጉ ብቃቶች አንዱና ዋነኛው ከሁኔታዎችና ከሰዎች ተፅዕኖና ከግፊት ነጻ ሆኖ በእውቀትና በተረጋጋ መንፈስ መወሰን መቻል፣ ውሳኔውንም ደግሞ በልበ ሙሉነት ማስፈፀም ነው። ከዶክተር አብይና በአጠቃለይ ከለማ ቡድን ይሄን አስተውያለሁ።
 5. ሌላው የዶ/ር አብይን መምጣት እንድደግፈው ያነሳሳኝ የመጡበት መንገድ ከዚህ ቀደም ወደግንባሩ ሊቀ መንበር የነበሩት ሁለት ሰዎች (አቶ መለስና አቶ ኃይለማርያም) ከመጡበት መንገድ እጅግ የተለየ ስለሆነ ነው። እንደ አቶ መለስ በሃይል ወይም እንደ አቶ ኃይለማርያም በምደባ ሳይሆን ስር ነቀል የሆነ ህዝባዊ ተቃውሞ ገፍቶ እዚህ

ያደረሰው ሰው ነው። ያለፉት ጥቂት አመታት መላው ኢትዮጵያን ያናወጠው ህዝባዊ ተቃውሞ ባይኖር ኖሮ አቶ አብይንና አቶ ለማን ማሰብ የሚቻል አይመስለኝም።

 1. ላለፉት 100 አመታት ኢትዮጵያን በርዕሰ መንግስትነት ካስተዳደሩ ሰዎች መካከል በትምህርት ደረጃው፣ በንግግር ችሎታውና በአስተሳሰብ ጥልቀቱ የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ።
 2. በዶ/ር አብይና በአቶ ለማ መካከል ያየሁት የመቀባበልና በተቀናጀ ሁኔታ ህዝብን የማገልገል አካሄድ አይቼ በአገራችን ከለመድነው አንፃር እንግዳ ሆኖብኛል። አብረው ለረጅም ዘመን በትግል ያሳለፉ የህውሃት ወታደሮች ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ አሳሪና ታሳሪ፣ አባራሪና ተባራሪ በሆኑባት አገር፣ ተቃዋሚዎች ገና ስልጣን ላይ ሳይወጡ በስልጣንና ክብር ሽሚያ አንገት ለአንገት በሚተናነቁባት አገር፣ በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን በሃይማኖትና በሲቪክ ማህበራት ሳይቀር ሁለት አውራዎች በአንድ ማዕቀፍ ውስጥ አብረው ሲሰሩ ማየት ትንግርት በሆነበት ማህበረሰብ ውስጥ እንዲህ አይነት “አንተ ቅደም፤ አንተ ቅደም” መባባልና መቀናጀት ከመቀመጫ አስነስቶ የሚያስጨበጭብ ገድል ነው። ይህ “መንፈሳዊ” ትህትና ደግሞ የሚያሳየው የሰዎቹን መልካምና ቅን ባህርይ ብቻ ሳይሆን ምን ያህል የሃገርን ጥቅም የሚያስቀድሙ የህዝብ ልጆች መሆናቸውን ጭምር ነው። (ባርኔጣዬን አንስቼ፣ ከወገቤ ጎንበስ ብያለሁ አቶ ለማ! ዶ/ር አብይ።)
 3. ከአራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት ውስጥ የተሻሉና ስራቸውንም በአግባብ ሊወጡ ይችላሉ ብዬ የማስበው አቶ አብይን ስለሆነ፤
 4. አሁንም ላለፉት 100 አመታት ርዕሰ መንግስት ከሆኑ ኢትዮጵያውያን መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ አብሬው ግዜ ባሳልፍ የምወደው አይነት ሰው ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ሌሎቹን ምናልባት መንገድ ላይ ባገኛቸው ዞር ብዬ መመልከቴንም እጠራጠራለሁ። ዶ/ር አብይ ግን እንደውም ከተመቸው ሻይ ቡና ብንልና አብሬው ግዜ ባሳልፍ ደስ የሚለኝ አይነት ሰው ይመስለኛል። በምኖርባት የአሜሪካ ምድር ከመሪዎች ምርጫ በፊት ከሚሰራጩ መጠይቆች መካከል “ከማን ጋር ቢራ ብትጠጣ ትወዳለህ?” ወይም “ከተመራጮቹ መሃል ማንን ወደ ቤትህ ለእራት ብትጋብዝ ትመርጣለህ?” (who would you rather have beer with? And who would you prefer to invite into your home for dinner?) የሚሉ ጥያቄዎች አሉ። መጠይቁን እንደ ሚያዘጋጁት አካላት እምነት ሰዎች የሚመስላቸውን፣ የሚስማማቸውን ሰው በዚህ መልኩ መለየት ይቻለል ብለው ያስባሉ። ነገሩ የቅንጦት ቢመስልም በተደጋጋሚ እውነት ሆኖ ታይቷል። ድሮ ድሮ ይሄ እንደ አንድ መስፈርት መሆኑ ያበሳጨኝ ነበር። አገር መምራት ሌላ አብሮ ቢራ መጠጣት ሌላ ሊባል ይችላል። ጥያቄው እንደኛ ላለ አምባገነኖች እየተፈራረቁ ሲደቁሱት ለኖረ ማህበረሰብ እጅግ ቅንጦት ሊመስል ይችላል። ነውም። ግን ተመሳሳይ ጥያቄ ብጠየቅ እጩ ሆነው ከቀረቡትም ሆነ ባለፉት 100 አመታት ኢትዮጵያን በርዕሰ መንግስትነት ከመሩት ሰዎች መሃል አብሬው ሻይ ብጠጣ የምወድ መሪ ያገኘሁት ዶ/ር አብይን ነው። (ርዕሰ መንግስት ማለቴን ያስተውሏል። እንጂ ከጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሃብተወልድንና ከዶክተር ነጋሶም ጋር ሻይ ቡና ለማለት እድሉን ባገኝ ደስታውን አልችለውም ነበር።)

ዶክተር አብይን በነዚህ ምክንያቶች ተነስቼ ብደግፋቸውም አይኔን ጨፍኜ ግን ልከተላቸው ፈቃደኛ አይደለሁም። ድጋፌም ዛሬ ስለሰውየው ባወቅሁት በመነሳት ወደፊት ይሰሯቸዋል ብዬ ላመንኳቸው ነገሮች እንደ ቀብድ ተደርጎ ይቆጠርልኝ። ስለዚህ እጅግ ብዙ ስራ ይጠበቅባቸዋል። የሌላ ሰው ሌጋሲ ከማስጠበቅና የሌላ ሰው ራዕይ ከማስፈፀም ያለፈ የራሳቸው ራዕይ ያላቸውና የራሳቸውን ሌጋሲ ትተው ማለፍ የሚፈልጉ ከማንም ስውር አካል መመሪያ የማይቀበሉና ልበ ሙሉ መሪ

 

መሆናቸውን በስራ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። ‘ስሙን ይያዙት እንጂ እውነተኛ ስልጣኑና ሃይሉ ይኖራቸዋል ወይ?’ የሚለውን የብዙዎችን ጥርጣሬ ማጥፋት የሚችሉት በመጀመሪያዎቹ የስልጣን ቀናት፣ ሳምንታትና ወራት በሚወስዷቸው እርምጃዎች ነው።

ዶክተር አብይ ይሄንን እውነት ያጡታል የሚል ግምት የለኝም። እንደ አንድ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት ሲከታተል እንደቆየ ግለሰብ ዶ/ር አብይ የሚከተሉትን እርምጃዎች በመጀመሪያዎቹ የስልጣናቸው ወራት መውሰድ አለባቸው ብዬ አምናለሁ።

 1. ከሃገር ውጪና ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎችን ሁሉ ለእርቅና ለሰላማዊ ድርድር መጋበዝ፤ ሃገር አቀፍ የሰላምና የእርቅ ዘመቻ መጀመር፤ ለዚህም ገለልተኛ የሆኑ አቀራራቢ የአገር ሽማግሌዎችን መርጦ ማሰማራት (አደራ ሃይሌ ገብረስላሴና ፓስተር ዳንኤል የተባሉ ነጋዴዎችን ሽማግሌ አድርገው እንገቴን እንዳያስደፉት…)
 2. የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የተባለውን በህዝብ ላይ የተጫነ የሞት አዋጅ በአስቸኳይ መሻር/ማስሻር ይጠበቅባቸዋል። በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ወቅትና ከዚያም በፊት በነበሩ የህዝብ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ላይ በህዝብ ላይ የተፈፀመውን በደል የሚያጣራ ገለልተኛ ቡድን ማቋቋምና የቡድኑን የመጨረሻ ሪፖርት ለህዝብ ይፋ ማድረግ፤ ወንጀለኞቹንም በሂደት ለፍርድ ማቅረብ፤
 3. 3. የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ያረቀቀውን የኃይለማርያም ደሳለኝን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአስቸኳይ በመበተን ከአባል ድርጅቶች ተዋፅዖና ምደባ ነፃ የሆነ፣ የትምህርትና የማስፈፀም አቅምን ብቻ መስፈርት ያደረገ አዲስ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ማዋቀር፤
 4. ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ መፍታት፤ ፍቺውም በፍፁም ምህረት እንጂ በይቅርታ ሊሆን አይገባውም። ትኩረቱም በብዙዎች ዘንድ በሚታወቁና ሰላማዊ ሰልፍ በሚወጣለቸው ሰዎች ዙርያ ብቻ ያተኰረ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉ የፖለቲካ እስረኞችን ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት ሊሆን ይገባል፤ (አደራ አቶ አብይ፦ እንደቀደሙት የኢህአዴግ መሪዎች ‘በአገራችን በፖለቲካ ምክንያት የታሰረ ሰው የለም’ የሚል የጅል ፈሊጥ እንዳይጠቀሙና እንዳንቆራረጥ…)
 5. 5. የነጻው ፕሬስ፣ መንግስታዊ የሆኑ ተቋማትና ተቃዋሚዎች እንዳይንቀሳቀሱ ሰቅዘው የያዙትን የፀረ ሽብር፣ የፕሬስና የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አዋጆችን በፓርላማ እንዲሻሩ አልያም መሰረታዊ ማሻሻል እንዲደረግባቸው ማድረግ፤
 6. መጪው ሃገር አቀፍ ምርጫ ፍትሃዊና ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ይካሄድ ዘንድ ነፃና ፍትሃዊ የምርጫ ቦርድ እንዲቋቋም ማድረግና ተቃዋሚዎችም በነፃነት እንዲደራጁና እንዲቀሰቅሱ የሚፈቅድ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። መቼም ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ በአገር አቀፍ ደረጃ ተደርጎ ድርጅቱ ኦህዴድ/ኢህአዴግም ሆነ እሱ በእውነተኛ የህዝብ ይሁንታና ፍላጎት ካልተመረጡ በቀር የአገሪቱ ትክክለኛና ዲሞክራሲያዊ መሪ ነኝ ብሎ እንደማያስብና እራሱን እንደማያታልል ተስፋ አደርጋለሁ። ስለዚህ እራሱንም ሆነ የሚመሰርተውን መንግስትና የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአደጋ ግዜና የሽግግር ወቅት አስተዳደር አድርጎ በመቁጠር ዘላቂ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ዋነኛ ስራው አድርጎ ሊወስድ ይገባል፤
 7. በኦህዴድ ውስጥ የተጀመረውን ህዝብን ከህዝብ የማቀራረብ እርምጃዎች በፌደራል መንግስት ደረጃና ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ባካተተ ሁኔታ አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅባቸዋል፤
 8. በአገሪቱ ያለው የህውሃት የበላይነትና የወታደራዊ ሃይሉና የደህንነቱ መዋቅር ያሰበውን ሊያሰራው እንደማይችል ከተገነዘበ፣ ወዲያውኑ ስልጣኑን በመልቀቅ ወደ ወጣበት የህዝብ ጉያ ተመልሶ ለመግባትና ህዝባዊ ተቃውሞውን በማፋፋም ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት እራሱን ቢያዘጋጅ መልካም ይመስለኛል።

ከላይ የጠቀስኳቸው እርምጃዎች በአንድ ጀምበር ሊደረጉ እንደማይችሉ አውቃለሁ። ነገር ግን ከዚህ መለስ የሆኑ ማናቸውም አይነት ለውጦች ጥገናዊ ለውጥን እንጂ እውነተኛ መታደስን አያመለክቱም። ስለዚህም ዶ/ር አብይ ያገኘውን አንፃራዊ የህዝብ ተቀባይነት በመጠቀም እነዚህን ለማድረግ እንቅስቃሴ ቢጀምር ለውጥ ናፋቂው ሃይል ሁሉ ከጎኑ ይቆማል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በአንፃሩ ደግሞ አቶ አብይ ከላይ የተጠቀሱትን መሰረታዊ የለውጥ እርምጃዎች ከማድረግ ይልቅ በጥገናዊ ለውጦች ህዝብን ለመደለልል ቢሞክርና እንደ አቶ ኃይለማርያም የሌሎች ጉዳይ አስፈፃሚ ቢሆን ገፍቶ ያመጣው ህዝባዊ ማዕበል አሽቀንጥሮ እንደሚጥለው ምንም ጥርጥር የለኝም።

ለዶ/ር አብይ መልካም የስራ ዘመን እየተመኘሁ እውነተኛ ዲሞክራሲ በአገራችን ሰፍኖ በሚቀጥለው ምርጫ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሌሎች የተሻሉ አማራጮች የሚቀርቡበትና ህዝቡ በታሪኩ ለመጀመሪያ ግዜ በመረጠው ድርጅትና ሰዎች የሚመራበት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።

አመሰግናለሁ!! ግዮን ውብሸት

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.