ማደንዘዣ ወይንስ ዕድሜ መግዣ? (አገሬ አዲስ)

መጋቢት 18 ቀን 2010ዓም (28-03-2018)

በበሽታ ዕድሜ ልኩን የሚሰቃይ ሰው እድልና አቅሙ ፈቅዶለት ለሕክምና ቢሄድ፤የመረመረው ሃኪም ለበሽታው የሚሆን ትክክለኛ መድሃኒት ሳይሰጠው ማስታገሻ ወይም ማደንዘዣ ወይም የተሳሳተ መድሃኒት ቢሰጠው ከሚያሰቃዬው በሽታ ወይንም ህመም ተገላገለ ወይም ተፈወሰ ማለት አይደለም።ማደንዘዣውም ለተራዘመ ጊዜ ሳይሆን ለአጭር ጊዜ የበሽተኛውን ጩኸትና ስቃይ ለማለሳለስ  የሚረዳ በመሆኑ የማደንዘዣው አቅም እየቀነሰ ሲሄድ የሚያሰቃዬው በሽታ ተመልሶ የበለጠ ሃይል ጨምሮ ያገረሽበትና በተዳከ ሰውነቱ ላይ ከማይቋቋምበት ደረጃ ላይ ይደርሳል።በሽተኛውም ሌላ መድሃኒት ፍለጋ ለመሄድ ይገደዳል።ለበሽታው የሚሆን ፈዋሽ መድሃኒት እስኪያገኝ ድረስ ጥረቱ ይቀጥላል። ከበሽታው የሚገላገለው  ሁነኛ መድሃኒት ሲያገኝ አለያም ሲሞት ብቻ ነው።ከጊዜ በዃላ ተሳክቶለት ፈዋሽ መድሃኒት ቢያገኝና ከሞት ቢተርፍ ለዚያ ያበቃውን ሃኪምና መድሃኒት እያወደሰና እያመሰገነ መባከኑን ትቶ ወደ ኑሮው ፊቱን ያዞራል።

በተመሳሳይ ደረጃ ሰላምና እረፍት የሚነሳ በሽታ በሰው ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም ።አገርና ሕዝብም ይታመማል። ኢሰብአዊና ዘረኛ የሆነ ስርዓት ከሰፈነ  አገር ላይ ሰላም አይሰፍንም፤ የሕዝብ ጤነኛ ግንኙነት ይናጋል።የመጨረሻም እጣ ፈንታ ቀውስና የእርስ በርስ መተላለቅና አገር መፈራረስ ይሆናል። ለዚህ ማህበራዊ ቀውስና አገራዊ አደጋ ምንጭና ምክንያት የሚሆነው የሰፈነው ስርዓት ነው።የአንድ አገር ዜጋ ወይም ህብረተሰብ መብቱ ሲደፈርና  ስብዕናው ሲነካ፣የአገር አንድነት አደጋ ውስጥ ሲወድቅ  በሰላም ውሎ ማደር አይቻልም፤ኑሮው ሁሉ የጭንቀትና የስጋት ይሆናል።በዚያ አይነቱ ማጥ ውስጥ የተነከረ ሕዝብ ያንን የሚያሶግድለት መፍትሔ ለመፈለግ ይገደዳል።በመጀመሪያ የሚያተኩረውና መፍትሔ እንዲሰጠው የሚጠይቀው ስርዓቱንና የስርዓቱን ተጠሪዎች ይሆናል።እነሱ የማይረዱት ከሆነ ሌላ አማራጭ ይፈልጋል።

የስርዓቱ ተጠሪ የሆነ ወይም የሆኑ ባለሥልጣኖች በመጀመሪያ የሕዝቡን ጥያቄ በሃይል ለማፈን የጸጥታ ሃይላቸውን ያሰማራሉ።በሽብር ለመቆጣጠር ይሞክራሉ።ይገላሉ፣ያስራሉ፣ያሰድዳሉ።ይህ ሁሉ አልሰራላቸው ሲል የመጨረሻው እርምጃቸው ሕዝቡን መደለል የሚችሉበትን ዘዴ መጠቀም ነው።ደካሞችን የተቃዋሚ መሪዎች በሹመትና በሽልማት ለመደለልና ተቃውሞውን ለማብረድ አንዱ ስልት ሲሆን፤የሕዝቡ ቁጣና ትግል በዚያ መንገድ የማይበርድ ከሆነና ከቀጠለ ወደ ሌላው አማራጭ ያመራሉ።በውስጣቸው ሹም ሽር በማድረግ ያለፈውን እንደተጠያቂና ደካማ አድርጎ በመቅረብ የሕዝቡን ስነ ልቦና የሚያለዝብና የሚያማልል ችሎታ አለው የሚሉትን ወደ ስልጣን በማምጣት ለውጥ የተደረገ አስመስለው ዕድሜያቸውን ለማራዘም የሚረዳ ስልት ይቀይሳሉ።

በኢትዮጵያ እዬሆነ ያለውም ይህ ነው።ለ28 ዓመታት በግፍ ተማሮ ሲታገል የኖረ ሕዝብ ከሁለት ዓመት ወዲህ በያቅጣጫው አልገዛም፣የዘረኞች ስርዓት በቃኝ! ብሎ ሲነሳና ስርዓቱን ሲያርበደብድ  ወያኔ መራሹ ኢሕአዴግ  ድርጅቶችና መሪዎቻቸው የመጨረሻ መፍትሔና ለሕዝቡም ትግል ማቀዝቀዣ ኪኒን አድርገው የገመቱትን የሹም ሽር ስልት ይዘው ብቅ አሉ።ለደረሰው ቀውስና ወንጀል ተጠያቂ ከሆነው ስብስብ መሃል የአንዱን ጎሰኛ አጋር ድርጅት መሪ፣በስርዓቱ ተኮትኩቶ ያደገውን ዶር. አብይ አህመድ የተባለውን  ምላሰ ጠቢብ ይበልጥ ከሞረዱት በዃላ  በካሄዱት የእርስ በርስ ምርጫ አሸነፈ ብለው  የለውጥ ሃዋርያ ካባ አልብሰው የጠ/ሚኒስትሪነቱን ቦታ ከደካማው ሃይለማርያም ነጥቀው  ሰጡት።በዚህ ትያትር ውስጥ የውጭ ሃይሎች ሚና መጫወታቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው።ያለው ስርዓት እንዲቀየርባቸው የሚፈልጉ አይደሉም፤ ስልት ቀይሮ ቢቀጥልላቸው ይመርጣሉ።ለዚያም ባለፉት ወራት የተላላኪዎች ውጣ ውረድና ሽር ጉድ በቦሌ መግቢያና መውጫ አይተናል።አገር ወዳድ የሆነ የፖለቲካ ድርጅት ጥቅማቸውን እንደማያስጠብቅላቸው ያውቁታል።ስለዚህ ተረባርበው የሕዝቡን ትግልና የለውጥ አቅጣጫ ማስቀየር ከተቻለም ላንዴም ለሁሌውም እንዳያንሰራራ ማድረግ ቀዳሚ ምርጫቸው ነው።አሁን እቅድ አንድን ተግባራዊ አድርገዋል።የሚቀጥለው እቅድ ሁለት ደግሞ በአብይ አህመድ በኩል የሕዝቡ ትግል ካልበረደ፣በስም ተቃዋሚ ሆነው የተመዘገቡትን ሕገ ወያኔን የሚቀበሉትን ድርጅቶች ያካተተ ምርጫ እንዲካሄድና የሥልጣን ቅርጫ ተደርጎ ስርዓቱ እንዲቀጥል ማድረግ ይሆናል።አብይ ወጣ ወረደ፣የአስመሳይ ተቃዋሚ ድርጅት በምርጫ ተካፈለ አልተካፈለ የሚገኝ መሰረታዊ ለውጥ አይኖርም።የጥገና ለውጥ ወይም የባለስልጣን መበወዝ ለሕዝቡ ጥያቄ ሙሉ መልስ አይሆንም።ለበሽተኛው እንደሚሰጠው ማደንዘዣ ወይም የተሳሳተ መድሃኒት ስለሆነ የሕዝቡ ትግል መሰረታዊ ስር ነቀልና ከጎሰኞች ነጻ የሆነ ፍጹም አገር ወዳድ ስርዓት እስኪመሰረት ድረስ የሚቀጥል ይሆናል።ከዚህ በፊትም የኦሕዴድ የተባለው ድርጅት አባል መቶ አለቃ ግርማና ዶር. ነጋሶ ጊዳዳ ስልጣን ላይ ነበሩ፤አሁንም የዚሁ ድርጅት

 

አባል ዶር. ሙላቱ የአገሪቱ ፕሬዚደንቶች ተብለው በወያኔ ተመርጠው ቁጭ ብለዋል ። በነሱ የስልጣን መቀባበል ግን የኦሮሞ ጎሳ ተወላጅ  ያገኘው ጥቅም የለም፤ እንደ ተቀረው ኢትዮጵያዊ ሲታሰር፣ ሲገደል፣ ሲሰደድ፣ ኖሯል።አሁንም በነዶር. አብይ ዘመነ ስልጣን እየተገደለ፣እየታሰረ፣ እየተሰደደ ነው።ዴሞክራቲክ ስርዓት እስካልተመሰረተ ድረስ ወደፊትም ይቀጥላል። አንዳንድ ደካሞችና ለውጥን ከጎሳ ተወላጆች ሹም ሽር ጋር የሚያቆራኙት ጎሰኞች የደስታ ዳንኪራ ሊረግጡ ይችላሉ፤እየረገጡም ነው። መታወቅ ያለበት ነገር ግን ስርዓቱ  አልተቀየረም እንዳለ ነው። የተለያዩት የሚንስትር ሹመኞች እንደነበሩ ናቸው፣አይነኩም።ጠ/ሚኒስትር ሆኖ የተመረጠው ዶር አብይ ሚኒስትሮቹን የመምረጥና የመሾም መብትና ስልጣን የለውም።አራቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ተነጋግረው የሚደላደሉት የቅርጫ ድርሻ ነው።ይህ ማለት የስርዓት ለውጥ መጣ ብለው የሚቆጥሩ ቢኖሩ ስህተተኞች እንደሆኑ ያሳያል።ለስር ነቀል ለውጥ የተሰለፈው ግን በዚህ  መርካት፣ መደናገጥና ተስፋ መቁረጥ አይኖርበትም። በጆሮ የሚሰማው ድለላ ትጥቁን ሊያስፈታው አይገባም።በስርዓቱ ዙሪያ የደረሰው ቀውስና ለሹም ሽሩ ያስገደደው የትግሉ ግለት እንደሆነ ተረድቶ ለበለጠ ዘላቂ ድል ይበልጥ አንድነቱን አጠንክሮ፣ ብሔራዊ ዓላማ ነድፎ ከመታገል ሌላ ምርጫ አይኖረውም።

ለዘላቂ ለውጥ አስተማማኙ  የጎሳን ፖለቲካ የሚቃወም፣የክልልን ግምብ አፈራርሶ የአገሪቱን አንድነት ለማስከበር የቆረጠ፣ ለዴሞክራሲ ስርዓት መስፈን፣ለዜጋና ለሰብአዊ መብት መከበር የሚታገለው አገር ወዳድ ሃይል መሰባሰብና ትግሉን ማቀናጀት ሲችል ብቻ ነው።በወያኔ ላይ ድንጋይ የወረወረ ሁሉ አጋር ነው የሚለው የጅሎች ማደናገሪያ ቦታ ሊሰጠው አይገባም።የትግሉ ጎራ መጥራት አለበት።

ዶር. አብይ አህመድ የሥርዓቱ ተጠሪ ነው፤ሕገወያኔን የማክበርና የማስከበር ግዴታ አለበት።ስልጣኑን ሲረከብም ምሎ ቃል የሚገባው ያንኑ ለማድረግ ነው።ያንን የማይፈጽም ቢሆንና ጥርጣሬ  ቢኖር ኖሮ ወደዚህ የሥልጣን እርከን ሊጠጋ ባልቻለ ነበር።እራሱንና ድርጅቱን ላድን ብሎ ሊቆርጥና እምቢ ሊል የሚችለው የሕዝቡ ትግል ከተጠናከረ ብቻ ነው።በዚያ ሁኔታ የወያኔን ዓላማና የኢሕአዴግን መመሪያ አሻፈረኝ ብሎ  የጠ/ሚኒስቴርነቱን ስልጣን ተጠቅሞ አንዳንድ እርምጃዎችን ሊወስድ ይችል ይሆናል።ወይም በገዛ ፈቃዱ ስልጣኑን ሊያስረክብ ይችል ይሆናል።ይህን እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ግን የራሱን ድርጅት ኦሕዴድን ማጠናከር፤ከውጭ ሃይሎችም ጋር ጠንካራ ግንኙነት መመስረት ይኖርበታል።የሱ ዱላ ድርጅቱና የውጭ ሃይሎች ናቸው። ለዚያ ያለው ዕድል የጠበበ ቢሆንም ምናልባት ሊሆን ቢችልስ ከሚል ግምት ተነስቶ ወደፊት የሚያደርገውን እያዩ መናገርና መፍረድ ይቻላል።በዚህም በዚያም ቢሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለውጥ አያመጣም፤ያው በገሌ ነው።ከጎሰኞች ዴሞክራሲ መጠበቅ ማለት ከዶሮ ወተት ይታለባል ብሎ እንደመመኘት ነው።

መጭውን ለማዬት የዕድሜ ደሃ አያርገን! አገሬ አዲስ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.