አሸናፊው„ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ነው። ያሸነፈችውም እናት ሐገር ኢትዮጵያ ናት። በዚህ ሂደት ከሰውኛ ትርጉሙ ይልቅ መንፈሳዊ ገድሉ ነው ጎልቶ እና ጎልብቶ የወጣው – ለእኔ

ከሥርጉተ ሥላሴ 29.03.2018 (ከጭምቷ – ሲዊዘርላንድ።)

„የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል። እግዚአብሄር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።“ (ምሳሌ ፲፮ ቁጥር ፱)

በቅድሚያ አቦ ለማ መግርሳ እንኳን ደስ አለዎት። መንፈሰዎት የሚሊዮኖች ማረፊያ ሆኗልና። ታሪክ ነዎት! ህሊና ነዎት! ተስፋ ነዎት! የዴሞክራሲ አናባቢም ተነባቢም ሰዋሰው ነዎት!

 • አይዋ ደስታ።

ስለምን ደስ አላችሁ ተብሎ ወቀሳ ቀርቧል። ይገርማል! በዬቤታችን እዬመጣችሁ ልዩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንጠልጠል ነው። ፈጣሪ አማላኬ በሰጠኝ ህሊና፤ በሰጠኝ ተፈጥሮ ውስጥ ስሜት አለኝ። በስሜቴ ውስጥ ሀዘን እንዳለ ሁሉ ደስታም አለ። ስሜት ራሱን የቻለ የሁሉም ነገር ሞተር ነው። በስሜቴ ውስጥ ለሚፈጠሩ ክስተቶች ተጠያቂ መሆን ካለበት እኔ ሳልሆን የፈጠረኝ ጌታ ልዑል እግዚአብሄር ነው። አማኑኤልን ጠዩቅት ስለምን ደስታን እንደ ፈጠረልን። አዎን! ደስ ብሎኛል ዶር አብይ አህመድ በመመረጣቸው። „ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው“ አሸናፊ መሆኑ ብሥራትን አውጆልኛል። ቀሬው የፈጣሪ ተግባር ነው። ነገ የእኛ ሳይሆን ብይኑ የፈጣሪው ነው።

አሁን ለእኔ ኢህአዴግ አይደለም ትዝ የሚለኝ። ትዝ የሚለኝ ማተቤ፣ ወስጤ፣ ድምጼ፣ ልዕልናዬ፣ ተስፋዬ፤ ራዕዬ የሆነው „ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው“ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ሰው ሰራሽ ቢሆን በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ለቁጥር የሚያታክቱ አዳዲስ ብሩህ ክስተቶች ባልተፈጠሩ ነበር። ፈቃዱ ባይሆን የደቡብ ህዝቦች ድምጽ ደኢህዴን ተወዳደሪ እያላቸው „ለኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ይሆን ነበርን? ለዛውም መጨረሻ ሰዓት ላይ። ገድል እኮ ነው። በፍጹም ሁኔታ ታሪኩን ራሱ የጻፈው ራሱ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ነው። ስለዚህ ለእኔ በዚህ ውስጥ አሸናፊ ብቻ ነው ያለው። እሱም „ገናናው ኢትዮጵያዊነት“ ነው። ተሸናፊ ሰው ድርጅትም የለም። በዚህ ማዕቀፍ ብቻ ችግሮቻችን ተሻገረን ጥላቻን ረትተን፤ ቂምን አፈር አስግጠን ትውልድን ማትረፍ ይቻላል። በዚህ መስመር ብቻ ነገን ማሰብም መሥራትም ይቻላል። በዚህ ልቅና ብቻ ማግሥትን መተንበይም መግንባትም ይቻላል። ግን እንደ አቦ ለማ መገርሳ ውስጡን ለማኖር ለፈቀደ ብቻ። ፈቀዱ ከሰው በላይ ምን ፍቅር አለ። ሃይማኖቴ እስከ ማለት አደረሰኝ እኔን እራሴን።

ሌሊቱን ሙሉ አልተኛሁም። በኢሜል ከማገኛቸው ቅኖች ጋር ስንወያዬ በማሃልም ደስ ያላቸው ሰዎች ሲደውሉልኝ ቁጭ እንዳልኩ ነበር የነጋው። ሃዘንም ሲሆን የሚሆነው እንዲሁ ነው። በፖለቲካ ህይወቴ በስደት ኑሮ ደስ ያለኝ አብይ ቀን ቢኖር ይህን የሰማሁበት ቅጽበት ነው። ደስታም አይደለም ከደስታም ያለፈ ሐሤት ነው። አሸናፊው ለእኔ ቁጥር አልነበረም፤ ቅዱስ መንፈስ ነበር። ጂኦሜቴሪ ወይንም አልጀብራዊ ሰው ሰራሽ ቀለም አልነበረም ድል ያደረገው። አሸናፊው እዮራዊ ነበር። ሁዳዴ ነው። አብይ ፆም ላይ ነን፤ ለዓለም ክርስቲያኖች በሙሉ የምህላ ወቅት ነው። አሸናፊው ሰብዕዊነት፤ ተፈጥሯዊነት፤ ዜግነት፤ እኛዊነት፤ ፍቅራዊነት፤ ቅናዊነት፤ አብሯዊነት ነው። ሐሤቴ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ በቅብዕው ስለ አሸነፈ ነው። ተሸናፊው ደግሞ የዘረኝነት እና የልዩነት ጥቁር እና ክፉ መንፈስ ነው።

„ደስ አላችሁ“ ብለው የሚወቅሱን ወገኖቼ … የፕ/ ባራክ ኦባማ ምርጫ ያን ያህል የዓለም ፍሰኃ የነበረው በእያንዳንዱ የዓለም ግለሰባዊ ቤት ቀጥተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነ ነገር ይፈጠራል ተብሎም አልነበረም። ለዛውም ገና መሬት ላይ የታዬ ነገር ሳይኖር ነበር ደስታው የሁሉ የነበረው። ነገርን ከጉዳይ የማትጠፈው ብቻ ሳይሆን የማይደንቃት እናት ዓለም // ጭምቷ ሲዊዝዬ አይደለም ያን ጊዜ ዛሬም ምክንያት እዬፈለገች በመልካም ታነሳቸዋለች። እስከ ቀዳማዮዋ // ደርባባዋ ወ/ሮ ሚኬኤል ኦባማን ጨምሮ። መልካም ዜና ጤና ነው። መልካምን ዜና ስለምን መጣ፤ እንደ መርዶ መታዬት አለበት የሚል ለውጥ ፍላጊ ለእኔ ሰዋዊም ተፈጥሯዊም ነው ለማለት ይቸግረኛል።

ሰው የምስራች ሲሰማ ደስ ይለዋል። ፍቅር ራሱ የምሥራች ጥሩ ዜና ነው እና። አስደንጋጭ ዜና ደግሞ ህመም ነው፤ በፍቅር ውስጥ ለሆነ ሰው ሰውኛውን ስብዕና ስለሚገልጸው፤ ተፈጥሯዊው የሆነ ድንገተኛ ነገር ሲሰማ ያዝናል፤ ያለቅሳል፤ ይተክዛል የሰው ልጅ፤ ይህም ፍቅር በውስጡ ሲኖር ብቻ ነው። የሶርያው መሪ ፕ/ ሳዳም ቢወርዱ እኔ ሌሊቱን ሁሉ ሻማ አበራለሁኝ። ዓለምም ደስ ይላታል። ስለምን? ሰቆቃውን እንደ ዓለም ዜግነቴ አብሬ አልቅሸበታለሁ እና። በሌላ በኩልም እኔ የሐገሬን የሬቻን ሰቀቀን ስሰማ ሦስት ቀን ዓይኔ ዕንቅልፍ አልነበረውም። ዓይኔን መክፈት እስኪያቅተኝ ድረስ። መልዕክቴን ለቀድሙት የተባበሩት መንግሥታት ጸሐፊ ከላኩ በኋዋላ ደግሞ ለረዥም ሰዓት በተከታታይ ጥልቅ እንቅልፍ ተኝቻለሁኝ። ያን መሰል እንቅልፍ በህይወቴ የተኛሁባቸው ቀናት ጥቂት ናቸው።

ዛሬ ከዛ ሊያወጣኝ ከቻለ // ባይችልም እንኳን ዕንባዬን ተመጣጣኝ ሊያደርግ የሚችል የሐገሬ ተስፋ መሪ ሲሆን ደስታዬ ወደር አለነበረውም። ችግሩ መቀነሱ // ለመጥበብ ተስፋ መኖሩ በራሱ ለእኔ ግማሽ እረፍት ነው። ይህም ባይሆን ይህን ያህል ወያኔ ሃርነት ትግራይ የዛጉ ምርኩዞቹን አሰባስቦ ባልታገለው ነበር። ቀላል የቤት ሥራ ቢሆን እንደ ተለመደው በአንድ አፍታ ፉት ያደርጋት ነበር እንደ ለመደበት። መዝገይቱ በራሱ ለፖለቲካ አዋቂዎች የሚልከው መልእክትም መክሊትም ነበረው። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መልዕክትም መክሊትም ይዞ ይወለዳል። ተስፋ አሁን ይጠበቃል … ያላለቀ ተስፋ ነው ያለው፤ ነገ ምን ሊሆን እንደሚችል አይታወቅም። ድርጅቱ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ነው … በዛ ላይ የሳጅን በረከት ጋንታም አለ።

የሆነ ሁኖ የፊት የፊቱን ይላል ጓያ ነቃይ … ቢያንስ ለችግር ባለቤት የሚሆን ሰው፤ ቢያንስ ኢትዮጵያ ሐገሬን ወክሎ ሲገኝ አንገቴን የማልደፋበት መሪ ኢትዮጵያ ሲኖራት እንደራሴ ሲኖር ደስ ሊለኝ ይገባል ገና ውጥን ቢሆንም። ይህን ደስታዬን ማንም ሊሰጠኝ ወይንም ሊነሳኝ መብት የለውም። አጉል መንጠራራት ነው። ቃሉ ራሱ ሲጻፍ ቁልጭ ያለ ጭቆና እና የሰባዕዊ መብት ረገጣ ነው። በሌላው ይሄ እንደ ተለመደው በዬፌርማታው ማዕቅብ በመጣል እና በማስጣል እንደተኖርበት … ጉማም ዘመን በዚህም ማዕቀብ መጣል ተፈለገ። በጅምላ መደገፍ በጅምላ መቃወም ቀረ። ለጅምላ ድጋፍም ለጅምላ ተቃውሞ ተፈትሾ ነው። ለመሆኑ አትደሰቺ ብሎ ነገር አለ እንዴ? አልተፈጠርሽም፤ ስሜት የለሽም እኮ ነው፤ ወያኔ ሃርነት ትግራይም እኮ ይሄን ነው የሚያደርገው። ህግ መተላለፉ ቅጥ አጣ። … ነብዬ እግዚአብሄር ዳዊት „ህግ ተላላፊዎችን ጠላሁ“ ያለው እኮ እንዲህ የተፈጥሮን ድንበር ጥሰው ለመገደብ ለሚያምራቸው ሰዎች ነው። „ልክን መዋቅ ከልክ ያደርስል“ ይላሉ ጎንደሮችም ሲተርቱ። አለመደስትም መደሰትም አንጡራ መብት ነው። ደስ የማይለው አይበለው። እኔ ግን አሁንም ደግሜ ዳጋግሜ ደስ ብሎኛል። ደስታዬ ከደስታም በላይም ሐሤት ነው።

 • ምህረት አሸናፋሚ ተሸናፊም የለውም።

በምህረት መንፈስ ውስጥ አሸናፊም ተሸናፊም የለም – ለእኔ። ለእኔ የዶር ደብረጽዮን ገብረሚኬኤል 2 ድምጽ ማግኘት // አለማግኘት አይደለም ቁም ነገሩ። አልነበረም። ትግራይ አቅራቢያ መቀሌ ላይ የታዬው የመሬት መንቀጥቀጥ ደወል አድማጭ ማግኘቱ ነበር ለህሊናዬ እረፍት የሰጠው። ይህን ሰቀቀን ላያስቡት ይችላሉ ተሳታፊዎች፤ ግን ፈጣሪ ራሱ ህሊናቸውን ያዘጋጀው 108 ቅዱሳን ተገኙ በቤቱ። ቅብዕማ ቀደም ብዬም በተደጋጋሚም ጽፌዋለሁ። መንግሥታዊ እና ክህነታዊ ቅብዕ የፈጠሪ ነው። ያልተሰጠው በፈለገው መንገድ ቢማስን፤ ቢወድቅ ቢነሳ፤ 6 ሰባት ፓርቲ ቢገላባበጥ ቅብዕ ከሌለው አይሆንም። ቅብዕ ያለው ግን ወደፊትም ቢሆን ጊዜው ቢረዝምም አይቀሬ ነው። ካልተሰጠ ግን አልተሰጠም …

የሆነ ሆኖ በዚህ የለማ፤ የገዱ መንፈስ መጨረሻ ላይም የደኢህዴን መንፈስም ለእኔ ታላቅ ዋጋ አለው። ታሪኩ ግንጥል ጌጥ ወይንም ግማሽ ሹሩባ እንዳይሆን አግዞታል። በተለዬ ሁኔታ ታሪካዊም ዕሴታዊም ነው። ትውፊታዊም ነው። የ1899ኙን የራስ መንገሻ ዮሖንስን ድምጽ ያደመጠ ልባም ባህረ ውሳኔ ነው። ባጋጣሚው ለ108 ቅን የምህረት ፍቅሮች ድምጽ ሰጪ ወገኖቼ ከመቀመጫዬ ብድግ ብዬ አምስግናቸዋለሁኝ። ለድንቅ ትልዕኮ በተፈለገው ነጥብ ላይ ወስነዋል። ወሸኔ! ማለፊያ! Praud!

እነኝህ የእኛ ብርቅና ድንቅ 108ቶቹ ለሰጡት ድምጽ ለራሳቸው ውሳኔ ልዕልና ማገር፤ ባላ እና ወጋግራ ሆነው መቀጠል ደግሞ ራሳቸውን በቀጣይ ማስከበር ነው። ይህን ማስጠበቅ ሲችሉ ብቻ ነው ደህንነታቸው በዘለቄታ ሊጠበቅ የሚችለው። በስተቀር ተሸናፊው ድምጽ ገና ይህ አሰራር ለዴሞክራሲ ነፃነት „ሀ“ ተብሎ ስለ ተጀመረ እንደ ጠላት ስለሚያቸው፤ ጥቃቱን አንሰራርተው በተለያዬ ሁኔታ ሊተናኮሏቸው ይችላሉ። ስለዚህ „ሀ“ ራስህን አድን ስለሆነ ለራስ ውሳኔ ዘብ መቆም ዋንኛ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል 108ቱ።

በዚህ ከቀጠሉ 108 ድምጽ በራሳቸው ውስጥ ከከተሙ፤ ለወሰኑለት ድምጽ ተገዢ ከሆኑ፤ ለወሰኑት ድምጽ አጥር ቅጥር ለመሆን ከፈቀዱ በኢትዮጵያ አዲስ ሥርዓት የመዘርጋቱ ሂደት ወሳኙ ድምጽ ሆኖ ይወጣል። ጉልበታም ተደማጭ እና የማይበገርም ይሆናል። ይህ ትልቁ ፍሬ ነገር ነው። የተወሰኑ ውሳኔዎችን በተገቢው ሁኔታ መፈጸም ያስችላል። ለራሱ የማይደፈር አቅም ለመሆን ወጡን አቋም ማዝለቅ ይሆናል ቀጣዩ ድርሻው ውሳኔው። በተደጋጋሚ እንደምግለጸው አንድ ጥቁርን አሜሪካዊ ሁለት ጊዜ የነጮች የመሪነት ብቃት ያቀዳጀው ሥርዓቱ ስለተዘረጋ ብቻ ነው። ስለዚህ ሰው አቅሙ ካለው በአቅሙ ውስጥ የአቅሙን ማግኘት ይችል ዘንድ ቀጥ ያለ አቋም እና የማያወላዳ መስመርን መከተል ይኖርበታል። የወሰኑለት ድምጽ ደግሞ ሁኔታው ከተመቻቸ እና ጊዜ ከተሰጠው ካገዙትም ለአፍሪካም የሚመጥን ነው። አያሳፍራቸውም! የሰጡት ድምጽ የሚያስቆጫቸው ከቶውንም አይሆንም። እንዲያውም የታሪኩ ክፍለ አካል በመሆናቸው የውስጥ ደስታን ያበረክትላቸዋል፤ በማለት ሳይሆን ገቢር ላይ ወሳኔያቸው አብቦ እና አፍርቶ ያዩታል። ያጡት ነገር የለም። ይልቁንም ያተረፉት የህሊና ሰብል ግምት ሊወጣለት ከቶውንም አይችልም። ታሪካቸውን ሠርተውታል።

 • ድርሻ።

ሥርዓት ከተዘረጋ ኢትዮጵያዊው ሰው ከተማ ያለው ብቻ አይደለም። የገጠሩም ህዝብም የኢትዮጵያዊው ሰው ቤተኛ ነው። ስለዚህ ቀበቶን ጠበቅ አድርጎ ገጠር ሄዶ፣ አቀበት ቁልቁለቱን ወጥቶ ወርዶ፤ ዳገቱን ዳጡን ሰኔሏንም ተላምዶ፤ አጓዛ ምንጣፋንም ተጋርቶ፤መደብ ላይ ድርቆሸ ጎዝጎዝ አድርጎ መኝታውንም ቀምሶ፤ የተገኘውን፤ ቤት የፈራውን በድልህ ይሁን በጭልቃ፤ በጭልቃ ይሁን በዳቦ፤ በዳቦ ይሁን በአነባባሮ፤ በአነባባሮ ይሁን በጭኮ ይሁን በአሹቅ ወይንም ቆሎ አንጀቱን አስታግሶ፤ ጉሮሮውን በቡብኝ ሆነ በውሃ፤ በአሰር ውሃ ሆነ በኮረፌ፤ በርጎዋ ሆነ በወተት አወራርዶ፤ ሃሳብን አስረድቶ ከሌላ ተፎካካሪ ሃሳብ ጋር ተሟግቶ መሬት ላይ የገበሬውን ኑሮ እዬኖሩ መወዳደር እና ማሸነፍ ይቻላል።

ያ የህሊና አቅም እና ብቃትን ይጠይቃል። መቁረጥን፤ መወሰንን ይጠይቃል። ሳይታክቱ፤ ሳይሰለቹ ቀን ከሌት መድከምን ይጠይቃል። በእግር መጓዝን ይጠይቃል። መንገድ ላይ ማደርን ይጠይቃል። ያ ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ፈቃደ አይጠይቅም። ሥርዓቱ ከተዘረጋ መብቱ እኩል ነው። ሚደያው እኩል ነው። ተፎካካሪውም እኮ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነው። እሱም በሚገብረው በሚከፍለው ቀረጥ ነው መንግሥታዊ መዋቅሩ የሚንቀሳቀሰው። ጋዜጠኛውም ክብሩን የሙያውን አዋርዶ ካድሬ ሳይሆን ለሥነ – ምግባሩ ሁሉንም ተፎካካሪውን የፖለቲካ ድርጅትም እኩል በማስተናገድ፤ እኩል እውቅና በመስጠት ለህዝብ አቅማቸውን አደባባይ ማቅረብ እንዲችሉ ማድረግ ቀዳሚ ተግባሩ ይሆናል። የጸጥታ አስካባሪውም ለሁሉም ተፎካካሪዎች ደህንነታቸው አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ጥበቃውን እኩል ማድረግ ይጠበቅበታል። ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው እና።

ምርጫ አስፈጻሚውም እንደ አሁኑ የካድሬ በረት ሳይሆን የስብዕዊንት ማዕከል ሆኖ ሚዛኑን በተፈጥሮ ችሎት ላይ ማድረግ ይኖርበታል። ሲዛነፍ ጫና ሲኖር ደግሞ ህግ አስፈጻማዊ ህጉ ብቻ ዳኝነት እንዲሰጥ የህሊና መሰናዶ ማድረግ ይኖርበታል። ለዚህ ግን ሥርዓት ሲዘረጋ ብቻ ነው። ለዛ ደግሞ የተጀመሩ መልካም ነገሮችን በማብጠልጠል፤ በማጣጣል፤ በዘመቻ ጥለሸት ለመቀባት እንደ ተያዘው በማቃለል ሳይሆን አክብሮ በመነሳት ይሆናል። እንዲህ የራሱን የደንብ መንፈስ የማያወቅ አባል ይዞ የቤት ሥራ በመደርደር ሳይሆን፤ በመግለጫ በማጣደፍ ሳይሆን፤ አብረን ታግለን እናሸንፋልን ከሆነ መርሁ ቅንነትን ምራኝ ማለት ይገባል። ጭላንጭል ብርሃን ሲታይ በጭላንጭኗ ውስጥ የምትገባውን ብርሃን ተጠቅሜ ምን ላድርግ? እንዴት ልጠቀምባት ብልህነት ነው። ማስተዋል የሚባለው ነገር ትንሹ ነገርን ስትጠቀምበት የትንሹ ነገር ስብስብ ትልቅ ነገር እንደሚያስረክብህ ማወቅን መቅደም ሲቻል ብቻ ነው።

 • አቋራጭነት ለጠቀመው ጠቅሟል በጊዜው፤ ዛሬ ግን ከ27 ዓመት በኋዋላ እእ …

በአቋራጭ እኛ አፈር ድሜ ግጠን አቀበት ቁልቁልት ወርድን እና ወጥተን፤ ወጣትነታችን ገብርን ባደራጀነው ላይ፤ በውስጥ አርበኞች የሻብያ፤ እና የወያኔ ሴራም ታክሎበት ወያኔ ሃርነት ትግራይ ምዕራባውያን ወስደው ቁብ እንዳደረጉት ዛሬ አቋራጭ መንገድን ማስላት ግን ከእንግዲህ የሚሆን አይደለም። በቦሌ ሥልጣን አይታሰብም። ይልቅ መተጋት ያለበት ሁሉም አሳታፊ ሥርዓቱ እንዲዘረጋ ነው። ለዚህ ደግሞ በትልቅ መጸሐፍ ተደጉሶ ሲለፈፍለት የኖረው ቃል አባዩ የሶሻሊዝም ጸረ ስብ ዴሞክራሲ ወናነቱን አቦ ለማ መገርሳ በራሳቸው ላይ በወሰዱት እርምጃ አዲስ የእውነት መጸሐፍ ጽፈው አሳይተውናል። የለማ መንፈስ እራሱ ለፈጠረው፤ ለሆነበትም ኢትዮጵያዊ የዴሞክራሲ መንፈስ ለዚህ መታተሩን ቅኖች ፈጽሞ አንጠራጠረውም። ጥድፊያ ግን አያስፈልገውም። ስለሆነም መካሪም፤ ዘካሪም፤ አስጠንቃቂም እኔ አውቅልሃለሁም ብዙም የሚያስፈልገው አይመስለኝም። ይልቅ ራስን መፈተሹ ይበጃል። ኦህዴድማ አደብን ሰክኖበታል። መግለጫው ራሱ ቁጭ ብሎ የሚማሩት ነው። የሶሻሊዚምን አክርካሪ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ እንዳይንሰራራ አድርጎ ኦህዴድ አድቅቆታል። ለተፈጻሚነቱ ብረት መዝጊያ ያስፈለገው ነበር፤ አሁን 108 ወታደሮች አሉት። ጥበቡ እግዚአብሄርም በቃችሁ ሊለን አስቦ ነው ሂደቱ እንዲህ አጓጕ እና መሳጭ ያደረገው። የኦህዴድ እያንዳንዷ የእርምጃው ቅደም ተከተል ተመስጦ የትውልድ ግንባታ ያህል ነው። በቅን ልቦና የተጠና፤ ምራቁን የዋጠ የአመራር ክህሎቱ የታዬበት ሲሆን ጥልቀቱ አንቱ ነው። ብቃት!

አዲሱ ካቢኔ ደግሞ ይታያል። ለዚህም የሳይስና ቴክኖሎጂ ጉባኤ ትምህርት አቅራቢዎችን ማዬት ብቻ ይበቃል። „አንባሳ ሆነን ድመት፤ ወይንስ ድምት ሆነን አንባሳ፤ ወይንስ ሰው ሆን ሰው ይታዬናል“  የምትል ሊሂቅን ዕውቅና የሰጠ አዕምሮ ነው ዛሬ ቦታው ላይ ያለው። „ዘመን አመጣሹ ስማርት ፎን“ መሠረቱ እኛ ነን የሚል መንፈስን ዕውቅና የሰጠ ነው አሁን ቦታውን የያዘው ንጹህ። ይህ ሲባል ሁሉ ነገር ሙጥጥ ብሎ በአንድ ጀንብር ጊዜ ይጠረጋል ማለት አይደለም። የመቻቻል መርህ ሥራ ላይ በአግባቡ ይውላል። እጅግ በርካት ቁልፍ ቦታዎች በዬትኛውም ደረጃ ርብራቡ፤ ንጣፉ፤ ማገሩ በወያኔ ሃርነት ትግራይ የተዋቀረ ነው። 27 ዓመት አንድ ትውልድ ነው። ተተኪ እስኪፈጠር፤ መለማመድ አስኪቻል ድረስ በነባር ተመክሮ ጊዜ ተገዛ፤ ከዛ ቀስ እያለ በሂደት ተተኪው ተተካ። በሁሉም ዘርፍ። ነገር ግን ዶር አብይ አህመድ በዛ ውስጥ ሆነው ነው በዬተሰማሩበት የሥራ መስክ ሁሉንም እንደ ባህሪው አቻችለው በሥርዓት በመምራት ነበር ለስኬት የበቁት፤ ታሪካቸውን አብረው የሠሩት እንደሚነግሩን። በሥራ ዓለም ጠንካራም ደካማም ሠራተኛ ይኖራል። ጠንካራ መሪ ከኖረ ግን ያሾራል ያጠነክራል። ልፍስፍሱም እዬሸሎከ ይቀራል …

በዛ ላይ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ የተገለለውን፤ ባለቤት ያልነበረውን፤ ባለቤት የነበረውንም ሁሉንም በመቻቻል ስለሚያቀፈው አቅሙ ልክ የሚወጣለት አይሆንም። ግን ችግር እያመረትን ችግር ካቢዎች፤ ችግር ደርዳሪዎች መሆናችን ለህሊናችን ፍርድ ዕድሉን ከሰጠነው ርትህ እንዲሰጥ ህሊናችን ከፈቀድንለት ብቻ ነው። አደብ በእጅጉ ያስፈልገናል። እርጋታ አጣን። ስክነት ተነፈገን። መንፈሳችንን አክለፈለፍነው። ራሱ ብስጩው አዬር ያለበትን ሁኔታ እንኳን ልብ ልንለው አልቻልነም። የላይ ላይ ግልቢያ …

27 ዓመት የተኖረው ለተወሰኑ ጊዜ ትእግስት ከዬት ይሸመት? ዕድሉ ሲገኝ ዕድል የአያያዝም፣ የአጠቃቀም ስልት እዬጠፋ ችግር ፈቺ ሊሆን ይቻላል የተባለው ሊሂቅ ችግር አምራች ይሆናል። ራስን መመርመር፤ በራስ ላይ ርምጃ ለመውሰድ ማሰብ በእጅጉ ያስፍልግ ይመስለኛል። ይሄ ተጨማሪ የቤት ሥራ እዬሰጡ አቅምን ማወክ፤ የውስጥ ሰላምን መበጥበጥ አደብ ቢኖረው መልካም ነው – ቢቻል። ወያኔ ሃርነት እኮ ሚሊዮኖችን ገድሎ እና አፈናቅሎ ፍዳቸውን እያስከፈላቸው ነው። እኛ ደግሞ ጎሽ ወያኔ ሃርነት ትግራይ እንኳን አቅሙን አደቀቅክልን እኛም ተጨማሪ የቤት ሥራ እዬደረብን ፍራሽ እንሆንሃለን ነው ነገሩ። … ያሳዝናል።

መምራት ስልትን እንጂ እልህ አይደለም። መምራት ጥበብ እንጂ ኩርፊያ አይደለም። መምራት ማስታዋል እንጂ ትእግስት ማጣት አይደለም። ትንሿን ዕድል ለመጠቀም አያያዝ ከታጣ ትልቁን ለመጠቀም ወና ነው። የሚታዬው የሚደመጠውም ግን የተገለበጠ ነገር ነው። በታሪክ ቅንጅት ብቻ ነበር እኮ በህዝብ ድምጽ የተመረጠው። አቅም፤ ክህሎት፤ መደማመጥ ጠፋ። ላቅ ብሎ የሚወጣ ተዳማጭ የሆነ ባሊህ ባይ ክህሎትና ጥበብ አጣ። ዕድሉ የንጹሃን ዜጎችን መስዋዕትነቱን ተረክቦ ፈሶ ቀረ። ከዚያ በኋዋላ የባከነው መዋለ ንዋይ፤ መዋለ መንፈስ ቀርቶ የባከነው ሰብዕና ታሪክ ይፈረደው። ለዛውም ለድክምቱ፤ ለጥፋቱ ተጠያቂ እኔ ነኝ የሚል ባለቤት እንኳን የለውም – ለሙሉ ኪሳራው። የተሰዋው ቀርቶ እስር ቤት እስተዛሬ ድረስ የሚማቅቁት ባለቤት የላቸውም። የተጎዳ ተጎዳ፤ የተበተነ ቤት ተበተነ። በብሄራዊ ፓርቲዎች ለተደራጁት አሁንም ባለቤት የላቸውም። ስለምን? ኢትዮጵያዊነት እዳሪ የተጣለ ብቻ ሳይሆን ወንጀለኛ ሆኖ የተከሰሰ፤ የተፈረደበት ስለሆነ። ዛሬም የሚደመጠው ይሄው ነው። ኢትዮጵያዊነትን ያቀነቀነ፤ የዘመረ፤ የአሰበ፤ የተለባሰ አንጡራ ጠላት ነው … የካቴናም ራት ነው። የባሩድም ስንቅ ነው። የሰሞኑ ተጋድሎም ይሄው ነው። ኢትዮጵያዊነት ሚደያ ላይ ቀለብ ሲሆን፤ መሬት ላይ ግን መቀጣጫ እና እንደ ብርት ቀልጦ መቅለጫ ነው። …. ለዚህ ደግሞ ደጀኑ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ሆኖ ሳላ አሳሩን አበዛነው። አብዝተን አወክነው – ራሳችን። የተደከበትን ውጤት ሁሉ መልሶ ጭቃ በማልበስ። በዓምት አንዲት አዲስ ሃሳብ ብቅ በማትልበት ምድረ ባዳ ሁኔታ በዬዕለቱ ሲሆን ቅልጣን አሰኘን።

 • ዛሬን የሚያሻግር ብቻ ሳይሆን ነገንም የሚያቆይ ብሄራዊ ሰንደቅዓላማችን ብቻ ነው።

የለማ መንፈስ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ እኮ ነው የአቅም ምንጭ የሆነው በራሱ ውስጥ ለመኖር በመፍቀዱ ነው። ሌላ ፍልስፋና የለውም። ሌላም ቀመር የለውም። ያገነነው እኮ ሰንደቁ ነው። ይህ ሰንደቅዓላማ የፍቅር ምልክት ነው ሁላችንም ሳንሰስት ፍቅርን የቀለብነው። ያ ፍቅር እኮ ነው ዛሬን ያቆዬልን። በቀልና ጥላቻ፤ ቁርሾ እና ቂም አንድ ቦታ ላይ አዟሪቱ መቆም አለበት ሲባልም ከሰንደቁ ጋር ቁርሾ ያለበት ሁሉ ህሊናውን ራሱ ይጠብ ነው። ለወደፊቱም „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ የመሸከም አቅም አለው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁኝ። አሁንም ወ/ሮ እናት ፋናዬ እንደተለመደው ጨልሞባት ለቅሶ ላይ ናት፤ ዶር. ሰላም ሆነ ጋዜጠኛ ሰርኬ ዕንባ ላይ ናቸው። አሁንም ናፍቆት ት/ቤት መሄድ ቀፎታል። አሁንም ያቺ መከረኛ እናት፤ ሚስት፤ እህት፤ ወንድም ስንቅ ለመቋጠር እዬተጣደፉ ነው። ነገ ደግሞ ተረኛው ይቀጥላል። የቂም፤ የበቀል የጥላቻ ውርርስ ነው ሶሻሊዝም የሚሉት ጠንቅ። ይህን የራታ ነው „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ግን አደብ ያስፈልገዋል። አወክነው።

ዛሬ ላለው ልዕልና የ27 ዓመት የወያኔ ሃርነት ትግራይ እና ቤተሰቦቹ ገዢነት፤ ዝመና፤ መቀናጣት ሐገር በመኖሯ ነው። ለዚህ ያበቃው የዚህ ሰንድቅዓላማ ውለታ ነው። ሌላ ሰብሳቢ ቴሌቪዢን አልነበረም። ፌስ ቡክ አይደለም ኢትዮጵያን ከጠላት ጠብቆ፤ ማንነት ያለን ኩሩ ህዝብ ያደረገን። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሰንድቅዓላማ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ልሙጡ ነው ብሄራዊ ቀናችን ነፃነታችን ያወጀው። ዛሬ ትልቁ ጠላት ይሄ ነው። „ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ“ ሆኖ … አሁን ይህን ብሄራዊ ሰንደቅዓላማን ጠላት አድርጎ የሚያደረገው ወከባ በፍጹም ትውልዱን አያበረክትም። የዘመኑ የሚመስላቸው ሁሉ አዳኛቸው ብሄራዊ ስንደቅዓላማቸው ብቻ ነው። አዳኝን ማሰር ክርስቶስን የማሰር ያህል ነው። ዓደዋ ባዕል የ2010 ሲከበር ብዙ ቦታ ተዋናዮች ብሄራዊ ሰንደቃቸውን ለብሰው ነበር፤ ነገር ግን እነሱ ምንም አልሆኑም። ዛሬ ዓይናቸውን ይዘው የወጡት ከሰውነት ተራ ርግፍ ብለው ከእሥር የተለቀቁት ሌላ ተጨማሪ አባልተኞችን ጨምረው እንደገና ካቴና እዬበላቸው ነው። ስለምን የዓድዋ ባዕል እንደዛ በብሄራዊ ሰንደቅ አሸብርቆ ተከበረ? መልስ አለው የወያኔ ሃርነት ትግራይ? ሱማሌ ኢትዮጵያን ተቆጣጥራ ቢሆን ኖሮ ዛሬ እንዲህ እስከ ዘር ማንዘር መዘመን ይኖር ነበርን? ያ ሰንደቅዓመላማ እኮ ነው ለዚህ ሁሉ ክብር እና ልዕልና ያበቃው። ቀለም እንዴት ይጠላል? ቀለም ብቻ እኮ ነው ያለው። ቀለሙ ደግሞ እንኳንስ ለኢትዮጵያ አፍሪካን የፈጠረ ነው፤ ያዳነም ነው … አለማስተዋል።

 • የተስፋ ስንቅ ቋጠሮ።

ወደ ተነሳሁበት ስመለስ ዶር አብይ አህመድን እንኳን ደስ አላቸው ስል አዲስ ተስፋ በሁሉም ዘርፍ ሰንቄ ነው። ተስፋ ግን በአንድ ጀንበር እንደማይከውን አሳምሬ አውቃለሁኝ። አንድ ጽንስ በአንድ ቀን ሙሉ ሰው ሊሆን እንደማይችል ስለማውቅ። ለዛውም ማህሉም ዳሩም እሳት በሆነበት ሁኔታ ወቅትና ጊዜ የሚጠይቁ አመክንዮች እንዳሉ ከልብ አውቃለሁኝ። ተግባር ካለመርሃ ግብር አይሆንም። መርሃ ግብር ደግሞ የአጭር እና የረጅም ጊዜን ይጠይቃል። የሁለቱ መገናኛው ደግሞ የመካከለኛ ጊዜ ይሆናል። በወቅት የታቀዱት ወቅቱ በፈቀደ ልክ ነው የሚከወኑት። ሐገርን ያህል ነገር በደመንፈስ ምኞች አትመራም። በጊዜ ሰንጠረዥ ግን ዕውን ሊሆን በሚችል የአቅም ምጣኔ ልክ ነው ነገ የሚሰላው።

ከዚህ በተጨማሪም ቅጣ አንባሩ በወጣ የትውስት የሶሻሊዝም ፍልስፍና ሰዋዊነትን እና ተፈጥሯዊነትን አሸንፈው እንዲወጡ ለማድረግ ተጋድሎው መጠነ ሰፊ ነው። ይሄ የኢንትሪጉ እና የኢጎ ትብትብ መረቡ እሾኽ ነው። ይህን መጠነ ሰፊ ተልዕኮ ለመወጣት የህሊና አቅም ሙሉ መሆኑ አንዱ መልካም ነገር ሲሆን ማገዙ፤ መርዳቱ፤ ደጀን መሆኑ ደግሞ ከቅኖች ከእያንዳንዱ በግል ከሁሉም በጋራ የሚጠበቅ ግዴታ ነው። በተለይ 108ቶች የምህረት ቀን ታታሪዎች መንፈሳቸውን ሁሉ ለድምጻቸው ማድረግ ይጠብቃባቸዋል። በሌላ በኩል ችግር ለመሸከም እንጂ ችግርን ለመጠዬፍ አይደለም ተልዕኮው። ተልዕኮው የህዝብ ገረድ ሎሌ ለመሆን ነው። ይህን ደግሞ ዶር አብይ አህመድ አሳምረው ያውቁታል። ሲመሯቸው የነበሩት ሁሉ ያላቸውን የአመራር ችሎታ እና ጥበብ፤ የአዛኝነት እና ድካምን ለመጋራት ያላቸው በጉነት፤ በሰፊው ምስክርነት ሰጥተዋል። ከሁሉ በላይ ጋዜጠኛ ሃኒ ትንቢቷ ሜዳ ላይ አልቀረም። ተስፋን መጠበቁ አይከፋም ብላን ነበር። አሁን የተስፋችን ፍንጩን አይተናል። ነገ ደግሞ ግርማችን እንዲሆን ከእያንዳንዳችን በግል ከሁላችንም በጋራ እገዛና ድጋፍ ያስፈልጋል – ቅኖች።

…. አየር ላይ የኖረ መንፈስ አይደለም ዛሬ ለተስፋችን ሙሴ እንዲሆን ድምጽ የተሰጠው። የህዝብን ችግር አብሮ በመኖር፤ በማጥናት፤ በመራመር፤ ያዬ ያዳመጠ ሁነኛ መፍትሄም ያበጀ፤ የተፈተሸም ነው። ይህን ሥራዬ ላለ ማንኛውም ዜጋ ከእውነቱ የሚያደርሰው የቅንነት ሠረገላው ነው። ሐገር መውደድ ማለት ከሥሩ የመፍትሄ መንገዶችን፤ አውራ ጎዳናዎችን ማሰስ የዕለት ተለት ተግባሩ ሊሆን ይገባል። የእኔ ላሉት ነገር ጊዜ መስጠት የተገባ ነው። ጊዜ ከተሰጠው ደግሞ መረጃ ዛሬ እድሜ ለጉግል ለዩቱብ … በሽ ነው። ስለዚህ በቂ አቅም ኢትዮጵያ አላት። እርግጠኛ የሚያደርግ ከውስጧ የኖረ ልዩ መንፈስ አላት። እሷን አሳምሮ፤ አበጥሮ አንተርትሮ የሚያውቃት ልዩ የአቅም መቅኖ ነው የዶር አብይ አህመድ ክህሎት።

 • ክንፍ ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊህቅ የለም።

ክንፍ ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊህቅ የለም። አላዬንም እስከ ዛሬ። በአንድ ጀንበር ችግሮችን አብንኖ አትንኖ የሚበትን ባለስድስት ክንፍ ቅዱስ ሊሂቅ አላገጠመንም። ያሉን መሪዎች ሰዎች ናቸው። አንዱ ከሌላው በልምድ፤ በተመክሮ፤ በጥበብ፤ በማስተዋል የተሻለ ዕድል በማግኘት፤ የሚሻልበት ወይንም የሚበልጥበት የክህሎት መበላለጥ እንዳለ ሆኖ። የሽግግር መንግስት ይባል የአደራ መንግሥት ክንፍ ላለው መላዕክ አይደለም አደራው የሚሰጠው። የለንም 12 ክንፍ ያወጣ የፖለቲካ ሊሂቅ። ሩህሩህ ለማግኘት እንኳን የሰማይ ደጅ ነው። ሌላው ቀርቶ አሁን ባለው መልካም አጋጣሚ እንኳን ካዳመጥኳቸው የፖለቲካ መሪዎች አንድም ቅን ዕይታ ያለው የለም። አዎንታዊነቱ የተላጠ ወይንም የተላመጠ አገዳ ነው። ሶሻሊዝም እንዲህ ነው፤ የሌለው ያለውን አቅም ሲያንኳስስ፤ ሲያደቅ፤ ሲተች፤ ሲያብጠለጥል … የተለመደ ነው። ምን አለህ ሲባል? ምንም ነው። ወይንም በዓመት ሁለት ፓርቲ በተለያዬ ሥም መፈብረክ። አንጃ ፈጥሮ ሲያውክ – ሲያተራምስ። የሆነ ሆኖ ቅኖች በሳል የፖለቲካ ተንታኞች ባለሙያዎች ደግሞ በበጎነት ማዬት ብቻ ሳይሆን ሂደትን የሚጠይቁ፤ ጊዜ የሚያስፈልጋቸው አምክንዮች እንዳሉም አብክረው ገልጸዋል። እኔም አምጋራው ይሄንኑ ነው።

ሌላው ዶር አብይ አህመድ ከሰማይ የመጡ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ በችግሩ አድገው፤ ኑረው ከህዝብ ጋር ከታችኛው ክፍል ጋር ሰርተው ውጤት ያስመዘገቡ ስለመሆኑ ሊያስቀርቡት አልፈለጉም የተቃዋሚ ሃይሎች ቃለ ምልልስ ግብረ ምላሽ እንደሚነገርኝ። ማደራጀት ለእነሱ የአዬር ላይ ሰብል ነው። የማይክራፎን ገብያ። በቃ። ወይ ጎርፍ የከመረው ምናምንነቴ … በቃ። አንድ ተራ የጽዋ ማህበር ለመምራት እንኳን ክህሎትና ተደማጭነት ያስፈልጋል። ለተደማጭነቱ ደግሞ የተደራጀ መንፈስ ያስፈልጋዋል። ለተደራጀው መንፈስ ደግሞ መሪው ቀድሞ ሊያደምጠው የሚችል የተደራጀ መንፈስ መፍጠር መቅረጽ ግድ ይለዋል። ማደራጀት ገብያ ተሂዶ የሚሸመት ሸቀጥ አይደለም።

 • ስለ ምዕራብውያን በጎ ዝንባሌ።

ከምርጫው በፊት አንድ ቅን ሃሳብ አነበብኩኝ። አዎንታዊ ነው። ግን ትንሽ ነገር ማከል ፈለግሁኝ። የምዕራባውያኑ ዝንባሌ በዶር አብይ አህመድ መመረጥ ላይ ዝንባሌያቸው ከቄሮ ጋር ብቻ ተያይዟል። ይህ ብቻ አይደለም። ዶር አብይ አህመድ የዓለም አቀፉ ማህበረስብ ቤተኛ ናቸው። ለዚህ ለምዕራቡ ዓለም አሰተማሪ ወይንም ነጋሪ አያስፈልገውም። የዓለም ዐቀፉ ማህበረስብ ፈቃድ እና መርህ ፈጻሚ ናቸው። የዲጅታለም ማዕከል የሆነው የሳይስና ቴክኖሎጂ ያህል የሥልጣኔ ማዕከል በሚ/ር ማዕረግ መምራት ብቻ ሳይሆን በአጭር ጊዜ ድንቅ ተግባር ፈጽመዋል። ለዚህ ደግሞ የቅንነት ጋዜጠኞች መስክረውላቸዋል። አዎንታዊነት አራማጅነታቸው ሌላ ጉልህ አቅማቸው ነው። ጥላቻን መጸዬፋቸው የአቅማቸው ጉልላት ነው። ከዚህ በላይ የአቦ ለማ መግርሳ የጠራ ምስክርነት ሙሉና ብቃቱ በሁሉም ዘርፍ የማያሳፍር፤ ብልጹግ፤ ብጡል መሆኑም ጭምር ሌላው የድንቅ ሰብል ነው – ተጽዕኖም ፈጣሪ ነው። በራሳቸው ላይ አቦ ለማ መግርሳ የወሰዱትም እርምጃ የተለዬ መስህብ የነበረው ለአፍሪካዊ ፖለቲካ አዲስ ቀለምም ነው። አዲስ የተስፋ እንኳይ አባባ ነው። የማይታሰብ፤ ከቶውን ተደፍሮ የማያውቅ ርምጃ ነበር የወሰዱት። ይህ ሳቢ ስሜትን ፈጣሯል።

ዶር አብይ አህመድ ብቻቸውን አለመሆናቸውም ምዕራባውያኑ ያውቃሉ። የለማ ገናና መንፈስ ብቻ ሳይሆን የገዱም መንፈስ ተጨማሪ ጉልበቱ ስለመሆኑ፤ ኦህዴድ እንደ ድርጅትም ከብቁ የህሊና ድርጅታዊ አቋም ጋር ስለመገኘቱ መረጃው ይኖራል ብዬ አስባለሁኝ። በሌላ በኩል ቀልዱ ቁሟል። በአንድ እጅ ነበር ጭብጨባው። የቄሮ ተጋድሎ ብቻ። ዛሬ የአውሮፓው ህብረት ማህበር ሳይቀር የአማራ ተጋድሎን እኩል ዕውቅናን ሰጥቶታል። ሐገረ አሜሪካም የሰማነው ነው። አስቀድመው ስልጣኑን ለወያኔ ሃርነት ትግራይ ያስረከቧቸው ሊሂቃን ሳይቀሩ ተናግረውታል። በዚህም በዚያም ቢባል ዕውቅናው ጭንቅላት ብቻ ሳይሆን አዕምሮ የት ላይ እንዳለ ስለተገነዘቡ ይመስለኛል ዝንባሌያቸው ጉልበታም የነበረው።

ቤላ በኩል ፈተናውንም ያጡታል ተብሎ አይታሰብም። መከላከያው፤ ደህነንቱ፤ ልዩ ሃይሉ፤ የኢኮኖሚ መዋቅሩ ወሳኝ ተቋማት አዬር መንገዱ ሆነ ኢትዮ – ቴሌኮሙ፤ ሚዲያው ሁሉም በወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥር በሆነበት የጠ/ ሚር ብቃት ላይ ሊያመጣ የሚችለውን የለውጥ ተስፋ ላይ ተጽዕኖናውና ፈተናም ቸል የሚሉት ጉዳይ አይሆንም ብዬም አስባለሁኝ። ወይኔ ሃርነት ትግራይ እኮ በማሰር በመግደል ትጋት ላይ ብቻ ነው ያለው – ዛሬም።

የቀረው ሙጣጭ ጤነኛ መንፈስ የለውም ይህ ዘመነ ዲጅታል ለሁሉም ያደርሳል – መረጃውን። አይዋ ጉገል እኮ ሥራው ይሄው ነው። ከዚህ በላይ በፍጹም ሁኔታ በወንዶች የፖለቲካ ዓለም ለተገለለው የሴቶች የጨለማ ዘመን ጠበቃ፤ ዋቢ፤ እና ተማራማሪ ለመሆን መፍቀድ ዶር አብይ አህመድ ቢሆኑ ለሚለው ሚዛኑን የደፋ፤ ተጽዕኖም ፈጣሪ ሊሆን የሚችል አንኳር ጉዳይ ነው። በዚህ ድርድር የለም። አይኖርምም። የለማ መንፈስ አቅሙ ከተለመደው የሶሻሊዘም የሴራ ገብታ ወጥቶ የግሎባሉ ዜጋ የፈቀደውን የምዕቱ አውራ አጀንዳን በተፈጥሮ እና በሰዋዊነት ፍልስፍና ማተኮሩ ከሚጠበቀውም፤ ከሚታሰበውም በላይ ሁለገብ ዕምቅ አቅም እንዳለው እያሳዬ ነው። 30 ሺህ እስረኛ ካለምንም ቅደመ ሁኔታ መፍታት ከድንቅ በላይ ነው። አቅሙና ሥልጣኑ በፈቀደው ልክ በክልሉ ሥራ ላይ ያዋላቸው ተግባራት መቁጠር ይቻላል። ለዛውም ሞትን ፈቅዶ። አሁንም እኮ አካሎቹ እዬታሰሩ ነው። ነዋሪዎቹ እየፈለሱ ነው።

ዕድሉን የእኛ አድርጎ በመቀበል ሂደቱን በተሟላ ተስፋ መንገዱን እንዲጠርግ የማድረግ ጥረቱ ደግሞ ለውጥን የሚፈልገው ግን ለውጥን ሲፈራና ሲሸሸው ለኖረው ሁሉ የፊት ለፊቱ የተጋድሎ አድማሱ ነው … „ጨው ለራስህ ብትል“

 • እነ ልግጫ እና ፍጥጫ ….

እነ እትዬ ልግጫ እና እነ ፊ/ ፍጥጫ ሰሞኑን ሞቅ ደመቀ ብላችኋዋል? ወና የነበረው ቤታችሁ ሁሉ ዛሬ ለወግ ለማዕርግ አድርሷችኋዋል የ108ቱ የብሄራዊ ቀን ዓዋጅ ድምጸት። ሙሉ ኢትዮጵያዊው ሁሉ ታደመላችሁ። ይህን መቼም በህልማችሁም በውናችሁም አስባችሁት የማታውቁት የሰማይ መና ነው። ኢቢሲ፤ ፋና፤ ኢኤንኤን ዕድሜያችሁን ተዚህች ቅጽበት ጀምሮ ብትቆጥሩትስ ምን ይመስላችኋዋል? … እነ ልግጫ እና ፍጥጫ እነ ልግሜ … ወግ ደረሳችሁ … አይደል?

https://www.youtube.com/watch?v=AHyuaT4mqz4&t=276s

Ethiopia Dr abiy የሰዉ ልጆች ልዩ ብቃት ክፍል አንድ

https://www.youtube.com/watch?v=NHhWHrJOuHU&t=23s

Ethiopia Dr abiy የሰዉ ልጆች ልዩ ብቃት ክፍል ሁለት

እሺ ልዩ ዝግጅታችሁንም አዬን ሰማን። አባሪ ተባባሪወቻቸሁ የዶር አብይን አህመድን ንግግር እያነሱ ፕሮግራም መስራታቸውን አዳመጠን። መልካም ነው። እንዲያውም አህዱ ክለቱ ድርሳናችን ይሁነን ሲሉም ጥዋት፤ ጥዋት መደመጥ አለበትም እንደ ውዳሴ ማርያም ዓይነትም … ዋው። ተመስገን። ተዚህ ላይ ግን እነ ቅቤ ጠበሾች ምነው ስለሴቶች ዶር አብይ አህመድ የተናገሩት መድፈርን ተሳናችሁ ያሰኛል ከሰራችሁት ላይቅር ቅንብሩን? እስቲ ድፈሩት። ለሴቶች የብቃት ማዕክል ከንጉሦች ንጉሥ ከዐጤ ዳግማዊ ሚኒሊክ ወዲህ የመጀመሪያው ፈላስፋችን፤ ተመራማሪያችን ናቸው ዶር አብይ አህመድ። የፍቅራዊነትም መምህር ናቸው። ለዚህ ለወንዱ ዓለም መቼም መብረቅ እንደመጣበት ክው ሳያደርገው አይቀርም። በሴቶች ላይ ያላቸው የማያዋላዳ አቋም „ወንዶች በደንብ እንድታዳምጡኝ እፈልጋለሁኝ“ ብለው ነው የሚጀምሩት … „ሴቶች ከወንዶች የተሻለ ድንቅ ተፈጥሮም አላቸው ይላሉ። ሴቶች ጥልቅ፤ ተመልካች፤ ተመራማሪ፤ እና ሙሉ አቅም ያላቸው የሆኑትም ይላሉ። ሴቶች በተፈጣሯቸው ጸሐፊ ናቸውም ይላሉ፤ ሴቶች የክርስትናም የእስልምናም የብስራት ነጋሪ ናቸው ይላሉ። ሴት ታጀግናላችም ይላሉ …“  „ጣይቱ“ የሚል ዝግጅት እኮ ለስሙ አላችሁ፤ ወንዶችን በዘረኝነት ስሜት የምታኮላሽ ሴት ሳጅን ባለባት መከረኛ ሐገር። ብዕርን ለሚፈራም ወዬለት ነው። ወይ ይሠራል ወይ ዱላውን ይሸከማታል እይተገላበጠ … መቼስ ፖለቲከኛ የሚፈራው ጠመንጃ አይደለም። የብዕርን ቦንብ አንጂ። … እናንተም እስቲ ከታሠራችሁበት እግር ብርት ያስፈታችሁ ብለናል … ካድሬነት እና ጋዜጠኝነት …. ይጎፈንናል።

 • አማራነት።

43 ዓመት ሙሉ በሶሻሊዝም ገዳይ ርዕዮት በአማራነት ለደረሰው፤ ለሚደረሰው ወደፊትም ታቀዶ ስለሚፈጸመው በደል ከልቡ ገብቶ ዬሚቆረቁረው ከኦህዴድ የተሻለ ንጹህ መንፈስ ያለው ቅርብ የፖለቲካ ድርጅት የለም – ለእኔ። ሰለዚህ ከሰማይ መና ሳይሆን መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ውሳጣችን ጋር መንፈሳችን ማዋህድ የግድ ነው። ፍቅራችንም ለዚህ ድርጅት መለገስ ይኖርብናል። ስስታምም መሆን አይኖርብንም። ሆነው ነው ያሳኙኝ። „ጣና ኬኛ! አማራ ኬኛ!  አማራን እንዳትነኩብን፤ ከነካችሁት ጠቡ ከኛ ጋር ነው! አማራ የእኛ ነው ያሉት። ለእነሱስ ማን አላቸው ነው ያሉት። መመሰጋገኑ ይቅርብን ተግባር ላይ እንገናኝ ነው ያሉት አቶ ለማ መገርሳ ባህርዳር ላይ።“  በልቡ መሽጎ የነበረው ሁሉ ራድ ያስያዘ ጉልተ ርስት ነው ለዛውም የመንፈስ። ለአማራ „የኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ለድል መብቃቱ ትንሳኤው ነው። ብርሃኑ ነው። ቀለሙ ነው። የሳጅን በረከት፤ የኢንስፔክተር አዲሱ ለገሰ፤ የኢንስፔኢክተር አለምነህ መኮነን ብአዴን አማራን ሲያሳድድ፤ ሲያድን፤ ሲያሳርድ፤ ሲሳደብ፤ ሲቀብር የኖረ ነው። ነገም ፈጣሪ ይህን የሰይጣን ሰቤጠራ ሁሉ መልክ ካልስያዘው ቀጣይ ነው። በምንም መስፈርት ከኦህዴድ የተሻለ አማራን ከልቡ እና ከእውነቱ የተቀበለ በመንፈሱ የተሰናዳ፤ ያቀረበን፤ የጣማው ማንም ምንም ድርጅት የለም። እንደ ድርጅት ማለቴ ነው። በግለሰብ ደረጃ ሚሊዮኖች አሉ። ጋብቻውም፤ አብሮ መኖሩም የአማራው ሰው አማኝነቱን፤ ርህርናውን፤ ደግነቱን፤ ገርነቱን ያዩ የመረመሩ የመንፈስ ቅዱስ ባለሟሎች ሊኖሩ ይችላሉ። እንደ ድርጅት ግን ኦህዴድ የስለት ልጅ ነው ለአማራ ማህበረሰብ። ይህ ዕድል ለእኛ ከሰማይ የወረደ መባ ነው። ሰገነት። ስለዚህም የገዱ መንፈስ ሙሉውን ድምጽ ለመንፈሳችን አፍቃሪ ለኦህዴድ አቅም ማበርከቱ የተጋበ የጽድቅ መንገድ ነው። ሊሆንም ሊደረግም የሚገባ የተግባር ኣናት ነበር። ታሪካዊም ነው። ተባረኩ። አቅም መፈሰስ ያለበት ተፈጥሯችን አክብሮ ለሚነሳ ብቻ መሆን አለበት።

 • የፖለቲካ ተፎካካሪዎች።

የፖለቲካ ተፎካካሪዎች ግን ሐገራቸው ኢትዮጵያ እነሱንም ታሳትፍ ዘንድ በመግለጫ ሳይሆን በመንፈስ መጎልበትን መደበኛ ሥራቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል – ይመስለኛል። ዛሬ ኦህዴድን ተፎካክሮ ለማሸነፍ ሌት ተቀን መስራት ብቻ ሳይሆን የማደራጃ ዕውቅት ት/ ቤት መግባትን በውል ይጠይቃል። ህዝብ እንደ ቅርጫ መንፈሱን ልትክፍለው አትችልም። መንፈስን ወደ ራስ ለማምጣት ከህዝብ ማህበራዊ ንቃተ ህሊና በላይ የሄደ የሃሳብ አቅም፤ የሰብዕና አቅም፤ የማድርግ አቅም፤ የመሆን አቅም፤ በቃል የመገኘት አቅም፤ የመፍጠር አቅምን ይጠይቃል። የትናንት ትችቶች „ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥምን“ ዛሬ ረስተናቸዋል … መሰረታዊ ነገር በእጅ ያለ መንፈስ ቢያንስ አብሮ እንዲዘልቅ በማይታይ፤ በማይጨበጥ ህዋዋ ክንፍ አስወጥቶ ማብረር ሳይሆን መሬት የረገጠ የመሆን መሠረትን አህዱ ብሎ መጀመር ነው። ውስጥን መፈተሽ? ምን አለኝ? ማንስ አለኝ? ምንስ ማድረግ ይኖርብኛል? ሞግቶ የሚረታ በእጄ ውስጥ ምን የተግባር ቋት፤ ምን የመንፈስ ገበታ አለኝ? ማን ይተካኛል? ለሚተካውስ ማን ይተካዋል? ፈቅ አድርጎ ማስብ ያስፈልግ – ይመስለኛል። ህብር የሆነ ቀለማም አቅምን ለማምጣት አቻ ሆኑ መውጣት ባይቻል እንኳን ተፎካካሪ ለመሆን ውስጥን ዳሰስ ማድረግ መልካም ይመስለኛል። ባሻጋሪ ሔዶ ሌላው ላይ … ጦር ከመምዘዝ።

እርግጥ ነው ሐገር ቤት ይሄ ሁኔታ የለም፤ ግን ቢያንስ ራስን፤ ውስጥን በማደራጀት ረገድ ትጋት ሊኖር ይገባል፤ የተዘጋው በር ተክፍቶ ተፎካካሪ ዕውነተኛ ፓርቲዎች ቢሯቸውን እስኪንቀሳቀሱ ድረስ ውስጥን ማደራጀት ይገባ ይመስለኛል።  … ዛሬ ኦህዴድ ያለው አቅም የአንድ ድርጅት ብቻ አይደለም ብሄራዊ አቅም አለው … ሙሉዑ ነው። ሙሉዑነቱን ያመጣው የአቦ ለማ መግርሳ መሪ ተግባር፤ መርህ „ማብቃት“ ነው። „ማብቃትን“ በተከታታይነት እንደ ፏፏቴ ልክ እንደ ጀርመን የእግር ኳስ ቡድን አደረጃጀት እና አመራር በፖሊሲች ደረጃ ነድፎ የሚንቀሳቀስ ብቸኛው ብሄራዊ ፓርቲ ነው ኦህዴድ። መንፈሱ አፍሪካንም ያጠቃልላል። አብነት። አርያ የመሆን ህልሙ መጠነ ሰፊ ነው። የለማ መንፈስ የትኛውም አሃይል አቅም አያርደውም። የሚበልጠውን አቅምን ኮትኩቶ ቅደመኝ ብሎ የሚያወጣው እሱ ራሱ ነው። ስለምን ሐገራዊ ራዕይ እንጂ የሥም ራዕይ ስሌለው። …

ይህን አቅም በማብቃት መፍጠር ብቻ ሳይሆን ቦታ ሰጥቶ መፈተሽንም፤ መመዘንም፤ መለካትንም ተክህነውበታል አቦ ለማ መገርሳ። 6ጉዳዮች ላይ በአንድ ወቅት ማብራሪያ ቢያስፈልግ ባለጉዳዩ 6 ሰው ብቻ እንጂ በ6ቦታ አቦ ለማ መገርሳ ወይንም ዶር አብይ አህመድ መግለጫውን ይሁን ቃለ ምልልሱን አይሰጡም። ቃለ ምልልሱ ይሁን መግለጫው ደግሞ የጥንቃቄው፤ የብስለቱ ይዘት ይመስጣል። አንዱ ሲነድል ሌለው አይወትፍም። ስለምን? ወጥ የሆነ የሥነ – ልቦና የአገነባባ ስልትን ጥበቡ ረቂቅ ስለሆነ። የመንፈስ ግንባታ ላይ ያላቸው ልቅና ከሚመሩት ላቅ ያለ መሆኑ ተቀባዩን በፈቃዱ አብቅሎታል። ደረጃውን የጠበቀ አቅም አለው ኦህዴድ። ስለሆነም ታሪካዊ ሃላፊነቱን ስለመወጣቱ እኔ ጥርጥር የለኝም። የ108ቱ ድምጽም ከተገባው ላይ ስለመዋሉ ነገ ምስክር ይሆናል። ቅንነት ከእዮብ ትእግስትንም ከእዮብ መማር ከተፈቀደለት።

አቦ ለማ መግርሳ በፖለቲካዊ ህይወት በማደራጀት ውስጥ ህልው ስለመሆኑ ሊህቁ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ክንውኖችን በመደበኛ ሳጠናቸው ጸጋውም አላቸው። ውስጣቸው የተደረጃ በመሆኑ ለመደራጀት ወይንም ለማደራጀት ክህሎቱ መክሊት አለበት።  ለዚህም ነው ደረጃውን የያዘው ባለ ሙሉ ድርሻ ብቻ ለቦታው ከነተጠያቂነቱ ነው የሰጡት። ኃላፊነቱ ከሙሉ የማድረግ አቅም ጋር ነው የፈቀዱት። ሁሉም በቦታው የአቦ ለማ መግርሳን ፊርማ ሳይጠብቅ ይወስናል። ያደርጋል። ሆኖ አያውቅም በሶሻሊዝም ፍልስፍና። ማዕከላዊነት የሚሉት ጋኔን ስላለ። ለማ አዲስ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ነው። አሁን እራሱ እዛው ከቅርብ መሆን የፈለጉበት ምክንያት የሥልጣኑ መሠረቱ ያለው ከዛ ህዝብ ዘንድ ስለሆነ ነው። በስማ በለው ሳይሆን ከህዝቡ ጋር እዬኖሩ፤ ችግሩን ማድመጥ እና የህዝብን ችግር መጋራት ቀዳሚው ተልዕኮው ነው ለብልሁ አቦ ለማ መግርሳ። የለማ መንፈስ በዕውቀት ላይ የገነባውን መሠረት በተከታታይነት እና በትጋት ማስጠበቅ ታላቁ ተልዕኮው ነው ለለማ መንፈስ። የለማ መንፈስ የበቀለ ትውልድ ነው። እንዲህ ዓይነት ሰዎች በዘመናት አንድ ጊዜ ብቻ ነው የሚገኙት። ለዛውም ሲታደሉት። ኢትዮጵያን ዕንባዋን አዳምጧል አማኑኤል። የለማ መንፈስ መንፈሱ ካለበት ቦታ ሁሉ ፈጥኖ ደራሽ አሰማርቷል፤ አሁንም ቤተ – መንግሥቱ ላይ መንፈሱን ይጠብቃል፤ ይንከባከባል፤ ደጀኑ ይሆናል። ጥበብ ትውልደ ነገረ በሚስጢር። እርግጥ አሁንም ፈቃደ እግዚአብሄርን የሚጠብቁ ነገሮች ይኖራሉ … ሁሉ በእርሱ ነው የሆነውና … አሁን ከኢህአዴግ ስብስብ ውስጥ መንፈስ የሚገዛ፤ አጀንዳ የሚሆን፤ ኢትዮጵያን የሚመራ ይኖራል ተብሎ ህልም አልነበረም። ግን ለእግዚአብሄር የሚሳነው የለም እና ሆኖ ታዬ፤ ለዛውም እንዲህ መቼ አንደበቱን ጣዕም በሰማን የሚባልለት፤ የሚናፈቅና ለዛ እና ክህሎት ያለው። … ኑርልን እባክህን እጬጌው „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ መንፈሳችን መልስህ ለዚህ ያበቃህን እኮ አንተው ነህ። ኑርልን!

የተከበሩ አቦ ለማ መግርሳ እርስዎን የሰጠን አምላክ የተመሰገነ ይሁን። አሜን! ያላዬነው የዴሞክራሲ ህይወት ማርሸት አቀመሱን። ልጆቸዎትን፤ ቤተሰቦወትን „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ መንፈሰዎትን እግዚአብሄር አምላክ ጨምሮ ጨማምሮ፤ ግርማ ሞገሱን ይስጥልን። ትውልዱን አተረፉልን። በዚህ ውስጥ ትግራይም መትረፍ አለባት። እሷም አንደ አቅሟ ለመኖር መፍቀድ እና የወረረቻቸውን አካባቢዎችም ለቀቅ ማድረግ ይጠበቅባታል። ያን የእዮርን የሰንበት ደወል ማዳመጥ ይኖርበታል። መሬት መንቀጥቀጥ አዬር መቃወሚያ የማይጠመድበት ክስተት ነው። እትዬ ትግራይን እስከ ፍሬዎቿ መሪዎቿ ይዛዋት ላጥ ካለ ገደል አፋፋ ላይ አደረሷት። ፈጣሪ ግን ባለቀ ሰዓት ተማለዳት። የቀደሙት ጸሎት እና በረከት። አሁን አንጻራዊ በሆነ ሁኔታ ተመስገን ነው። መሪዎቿ ልብ ሰጥቷቸው „ለኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ እርምጃ እንቅስቃሴ ራሳቸውን ማስገዛት እስከ ፈቀዱ ድረስ ይህ ሽንፈት አይደለም። ብልህነት ነው። መኖር ይትረፍ። ነገ ሌላ ቀን ነው … ለሌላ ቀን በጎ ማሰብ ጤና ነው። ጤና ደግሞ የተስፋዎች ሁሉ ጉልላት ነው። ተስፋን ያዝልቅ ፈጣሪ … አሜን!

 • ስጋት።

ትልቅ ተራራ የሚያክል ስጋት አለብኝ። ኤርትራ ለለማ መንፈስ አትተኛም። ስለምን? ኦህዴድ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅት ነው ከኤርትራ የማረተ ትእዛዝና ውሳኔ፤ የማደረግ አቅም ተጠዋሪ ያልሆነው። ኢትዮጵያ ከኤርትራ ማመስ እና ማተራመስ በታሪክ የወጣችበት ንፁህ አጋጣሚ ቢኖር አሁን ነው። መልካም ስንብት ነው የሆነው። ከተመስገን በላይም ነው። በኦህዴድ ሰርገው ገብተው ሊያምሱና ሊያተራምሱ የሚችሉ አንድም የኤርትራ ነውፀኛ መንፈስ የለም። ቦታ የላቸውም። ብሄራዊ ፓርቲ ቢሆን ተሟምተው አይቀሬ ነበር።

ስለዚህም ኤርትራ ድንኳናን ጥላ ተቀምጣለች። አስተዛዘኞቿም ክብብ አድርገው ቁልምጫ ቢጤ ያደርጋሉ። ያ ገብረ ከይሲም አከርካሪው ነኮተ። ኤርትራ ያሰበችው፤ ያደራጀችው፤ እስከዛሬ ድርስ ብቅ የሚለውን ንጹህ ኢትዮጵያዊ መንፈስ በስውር ሴራዋ እምሽክ ያደረገቸው ነገር ሁሉ ዛሬ እንዳሻዋ መረቧን ዘርግታ ልታሽመደምደው አልቻለችም ባለንባረስ ዛሬን።

ነገር ግን ሰውዬው አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ፕሬዚዳንቷ ናቸው። ቀላል ሰው አይደሉም። እሳቸውን አውቃቸዋለሁ ማለትም አይቻልም። ጥልቅ ናቸው። ጥገቴን አንድ ቀን አጠምዳለሁ የማለት ህልመኛ ነበሩ። ሲንጋፖር አፍሪካዊቷ የህልም መሬት። እንዳሻ የምትታለብ ካለቀረጥ – ኢትዮጵያ ታስባ። በኤርትራ ቅኝ ግዛት በናቅፋ ቅኝ ግዛት የምትወድቅ ኢትዮጵያ ምኞት ተራራ የሚያክል ህልመኛ ነበሩ። ያ ቢቀር የኮሰመነች ልፍስፍ ኢትዮጵያን ማዬት የሌት ተቀን ህልማቸው ነበር። እኩል ደሃ ሐገር። ስለሆነም አሁን ህልሟ ለጊዜው ሳይሳካ ሲቀር በማንኛውም ሁኔታ መወራጨቷ አይቀርም። በመፍንቅለ መንግሥትም ብትችል መሞከሯ አይቀርም። ሌላም የግድያ ሙከራ ነው። በምግብ ብክለት፤ በመኪና አደጋ፤ አውሮፕላን አደጋ ወይንም ጠለፋ፤ በመኖሪያ አካባቢ ጥበቃ ላይ በገንዘብ ሰው በመቀጠር ብቻ አትተኛትም፤ በዛ ላይ የሰይጣን ሰቤጠራ አቶ በረከት ስምዖንም አሉላት እስከ ጋንታቸው አሉላት።

አማራ ሊሂቅ እኮ አልቋል። የክንፈ ማሰልጠኛ እኮ የበላው እኮ ይሄው ነው። ለሥልጣን ያሰጋል የተባለው ሁሉ ተውጧል። … ስለዚህ አቦ ለማ መግርሳ፤ ዶር አብይ አህመድ፤ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና መንፈሳቸው ብርቱ የሆኑት ሁሉ ከወትሮው በተለዬ የተጠናከረ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በዬትኛውም ሁኔታ መዘናጋት የለባቸውም። የገዱ መንፈስ ጥቃትን እንደ አባት አደሩ ያወጣ የጀርባ አጥንት ነው ለኦህዴድ። የኦህዴድን ታሪክ በወርቅ መዝገብ ያጻፈው የገዱ መንፈስ ነው። ይህን በቀላል ሁኔታ የኤርትራ መንግሥት ያየዋል ተብሎ አይታሰብም። አማራ መሬት የሻብያ የመሸጋገሪያ ትልም ነው። ስለዚህ ጠላትን አውቆ ሳይዘናጉ በተጠንቀቅ መጠበቅ ግድ ይላል። በተራዘም ጊዜ ቢሆንም ይህ እቅድ አይቀሬ ነው። አሁን ሽግግር ላይ ነው። ስክነት፤ አደብ፤ እርጋታ፤ ነገሮችን ማድመጥ ያስፈልጋል። ይሄ የጋረ ጉዞ፤ የጋራ ማዕድ፤ የጋራ ፌስታ ላይ መጠንቀቅ በእጅጉ ያስፈልጋል። ጥቃቱ በራስ ወገንም ሊከወን ይችላል። ኤርትራን ያህል ጣውንት ሐገር፤ ወይኔ ሃርነት ትግራይን ያህል ጉድጓድ ድርጅት ይዞ መቀናጣት የተገባ አይደለም። ኢትዮጵያም ሐዘን ላይ ናት። በዚህች ደቂቃ ጩኸታቸው ደማቸው የሚፈሱ ወገኖቻችን በማዕከላዊ አሉን። የሚሰደዱ ወገኖች አሉን። የሚደበደቡ ወገኖች አሉን። የሚገደሉ ወገኖች አሉን። ፈርተው መንቀሳቀስ ያቃታቸው በሥነ ልቦና የተጎዱ ልጆች አሉን … መከራችን ብዙ ነው …

ወደ ቀደመው ስመለስ እኛ ጫን ተደል የቤት ሥራ ለአዲሱ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ለዛውም ነገ ጠ/ ሚር ይሁኑ አይሁኑ ሌላም ነገር ይከሰት አይከሰት ሳናውቅ ሌትና ቀን ሥራ ስንከምር ውለን እናድራለን። የሰው ህሊና ከሚችለው በላይ ውቅያኖስ የቅደመ ሁኔታ የቤት ሥራ ቆልለናል። አቅል ነስቶን፤ አደብ ነስቶን፤ ስንደረድር ሌላ ድራማ እንዳይኖር ስጋት አለብኝ። ፈሪ ነኝ። የኪንግ ማርቲን ሉትር ወይን የፕ/ አብርሃማ ሊንከን ታሪክ እንዳይደግም ሌላ ትራጄዲ እንዳይኖር ስጋቴ እጅግ ሰፊ ነው። ያን የመሰለ ስብዕናው ድርጅት የሆነውን አርበኛ አንዳርጋቸው ጽጌ የገጠመው መጠራቅቅ ይሄ ነበር፤ ኢትዮጵያዊነትን ማጉላት እና ማላቅ ነበር ሃጢያቱ። ሌላማ ምንሠርቶ? ስለዚህ ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ አያከስርም። አቦ ለማ መግርሳ፤ ዶር. አብይ አህመድ፤ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ሌሎችም ተተኪ ስሌለችሁ ራሳችሁን መጠበቅ ግድ ይላል። ከዬትኛውም የዘመነ ወይንም የሚጫናችሁ ከሚደረደርላችሁ የቤት ሥራ በፊት፤ በፊት ልጆቻችሁን፤ ቤተሰቦቻችሁን፤ የቅርብ ሰዎቻችሁን ሁሉ ቢያንስ የግል ጥበቃ እንዲያደርጉ ምክሩ። ቅስም መስበር፤ ሥነ – ልቦናን ማወክ የሶሻሊዝም መስምሩ ነው። ሶሻሊዝም መርዝ ነው። ነገሩ አሁን ላይሆን ይችላል። ተዘናግቶ ግን አይቀሬ ነው። ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ ፈጽሞ አያከስርም።

በታሪኳ ኤርትራ ራድ ሊያስያዝት ከቻሉ ገጠመኞቿ ሁሉ ይሄኛው አንዱ ነው። ተንጠራርታ እኮ እኛ አዝለን እንዳወጣነው ወያኔ ሃረንት ትግራይን እኛው እንጥለዋለን ብላን ነበር። እና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከጎረቤት ሐገሮች በተለዬ ሁኔታ እሷ አራጊ ፈጣሪ ሆና ማቡካት መጋገር እዬመጠመጡ የመኖር ህልሟ ሲተን፤ ራዕዮዋ ቁሞ ቀር ሆኖ ሲቀር አትተኛም። በፍጹም። አደራ የእኛዊነት አርበኞች እራሳችሁን ጠብቁ። ቅጂ የላችሁም። ደግመንም አናገኛችሁም። ስትኖሩ ነው ለተስፋችን ተስፋ የምትሆኑት።

ሌላው ወያኔ ሃርነት የደህንነት መረብም ቀላል አይደለም። ለራሳቸው ደሞችም የውስጥ ሰላም አግኝቶ መኖር ይጨንቃቸዋል ብዬ አላስብም። ያማ ባይሆን ይህን ያህል የግፍ መከራ በራሳቸው በወገናቸው ላይ የውጪ ሀገር ቢገዛን እንኳ ሊሆን የማይችል እጅግ አሰቃቂ፤ ሊሰሙት የሚከብድ የሰው እርድ፤ እንግልት፤ መፈናቀል፤ መንኮላሽት፤ የህጻናት ዋይታን ፈቅደው ባላደረጉት ነበር። አውሬነታቸው ከ – እስከ አይባልም። በፍጹም እኮ ሌላ ትግራይን እኮ ነው በምስላችን የቀረጹት። ሌላ የማናውቃቸው ደሞቻችን ከዬት መጡብን እኮ ነው የሚያስብለው። አንዲት ሰከንድ እረፍት የላቸውም። ደም ብቻ። እንባ ብቻ። መበተን ብቻ። ጥላቻን መርህ ሆኖ እንዲቀጥል ስለምን እንደሚፈልጉ አይታወቅም? ግን ለምን? ልብ ይስጣቸው ፈጣሪ አምላክ። አሜን!

 • ኦህዴድ አንደ ድርጅት።

ኦህዴድ እንደ ድርጅት የማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት እና የበታች አካሉትን ተከታትያቸዋለሁኝ። ትሁት ናቸው። ለተመዱቡበት ቦታ ግልጽና አጭር መልስ የሚሰጡ ሻርፕ ናቸው። በጣም አውንታዊ ናቸው። የድምጻቸው ምት ለስላሳና ፍቅርን ሰባኪ ነው። የድምጻቸው ቃና ምቹ እና አብሮነትን ያዘከረ ነው። ዓላማቸው እና ግባቸውን ብቻ ሳይሆን የተመደቡበትን ቦታም ጠንቅቀው የሚያውቁ ስጦታ ናቸው – ለቅኖች። ወጥ የአቅም ክህሎትም አይባቸዋለሁኝ። አቦ ለማ መግርሳ እና ዶር አብይ አህመድን ይህም ጸጋ አላቸው። የሚናፈቅ የድምጽ ምት እና ቃና አላቸው። ገፃቸው በራሱ ተግባቢ፤ አግባቢ እና አቅራቢ ነው። የሰውነት ስብዕና ቋንቋቸው ትክ ብሎ በአስተውሎት ውስጣቸውን ለመመርምር ለሚተጋ ለአንድ ሐገር ብሄራዊ መሪነት ብቁ ነው። ገጻቸው ገረጭራጫ እና ቁጡ ወይንም ማንአህሎኝነት በፍጹም የለበትም። ራሱን ዝቅ ያደረገ ፈርሃ እግዚአብሄር የከተመበት ነው። ሲዮዋቸው ብቻ ተስፋ የመሆን መልዕክት በገፃቸው ላይ ይነባበል። ፈጣሪ አምላኬ ይጠብቅልኝ። ድንግልዬም አደራሽን የሎሬቱን ታቦታት ጠብቂልኝ። የቅኔው ልዑል ሎሬት ብላቴ ጸጋዬ ገ/መድህን መንፈሱ ምንኛ ደስ ይለው … ኢትዮጵያዊነት እንዲህ ባለቤት ሲያገኝለት። እሱን የያዘ የፍቅር ጥሪት አያጣም …

 • ክወና።

ሌላው ጊዜ ታሪክ ስለሚሰራ አደብ ለሚሰጣቸው ቅኖች አፍ ሞልቶ የሚያናገር ጥበብ ማዬት ይቻላል። ሁሉ እኩል ጸጋ የለውም፤ ግን ያለውን ጸጋ በአግባቡ ሊጠቀምበት የሚችል መሪ ካገኘ ኢትዮጵያ የአፍሪካ መሪ ትሆናለች … በጣም በእርግጥ … ቀድሞም ኢትዮጵያ የስብዕዊነት ተምሳሌት ናት። ይህን የሰብዕ ተምሳሌነቷን የናደው፤ ያቆሸሸው የሶሻሊዝም ስታሌናዊ መንገድ ነው። ኢትዮጵያ ሰብዕዊነቷ ከፈጣሪ የተሰጣት መሆኑ ተደርምሶ ነው የዋይታ እና የጭንቅ ቤት የሆነችው፤ ለራሷም መሆን የተሳናት። ሩህሩህ ተፈጥሮዋን በሶሻሊዘም ተነቀለ። ደግ ተፈጥሯዋ ቅስሙ ተሰበረ። ፍቅራዊ ተፈጠሯዋ ከሰለ። የ አብሮነት ግርማ ሞገስ ተፈጥሯዋ ረከሰ።

ስለዚህ አሁን ያለው የለማ መንፈስ የደፈረሰውን ተፈጥሯዋን በልኳ እና በአቅሟ መልክ ማስያዝ እንዲችል አቅም ማዋጣት ያስፈልጋል – ቅኖች። ኢትዮጵያ ሶሻሊዝም የቀማትን ሰማያዊ መክሊቷን ከተመለሰላት እንኳንስ ለልጆቿ የአፈሪካ እናት እኮ ናት። ለሁሉም ትሆናለች። ግን ይህ በቱማታ፤ ሱሪ ባንገት፤ በአንድ ጀንበር አይደለም። የ43 ዓመት ችግር ብን ትን ሊል እንደ ንፋስ በአፍታ ሊል ከቶውንም አይችልም። ያ ቢሆን እስታሁን ማርስም በደረስን ነበር። እንደ ፖለቲካ ድርጅቱ ብዛት እንደ የሥርነቀሉ አብዮት ምኞትና ተስፋ እንደ ተከፈለው የከፋ የሰው ግብር …

… ምህረትን ምህረት ለማድረግ ለምህረት ህግ ራስን ማስገዛትን ይጠይቃል። ራስን በማድመጥ ብቻ የምህርትን ፍሬ ነገር ማግኘት ይቻላል። ለምህረት ሥነ – ምግባር ማድመጥን ቢፈቀድለት ምህረትን ማስቀደም ለመቻል ቢታተር አዋጪ መንገድ – ይመስለኛል። መልካም የሥራ ጊዜ „ለኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ መልካም የእረፍት ጊዜ ለአቶ ሃይለማርያም ደስአለኝ እና ለመላ ቤተሰቦቻቸው። ከነሙሉ አካል፤ በጤና ከወያኔ ሃርነት ትግራይ ጋር ግልግል ማድረግ በራሱ መልካም ነገር ነው።

ይሄ እንግዲህ የመንፈስ ቴራፒ ያስፈልገናል ላሉት ወያኔ ሃርነት ትግራይ በበላይነት ለሚያስተዳድራቸው ሚዲያዎች ደፈር ካሉ እስኪ ያሰሙን በማለት ነው የተለጠፈው …

https://www.youtube.com/watch?v=Dmyzlr-jpp8

„ሐሳብ አለው ለማ ለለማ መገርሳ አዲስ ሙዚቃ በበርካታ አርቲስቶች – NEW! Music For Lemma Megersa

https://www.youtube.com/watch?v=i7i9hDTCFdo

Abiy Zema – New music Video 2018 – Dedicated to Dr. Abiy Ahmed Ali“

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።

አደብ ይስጠን ፈጣሪያችን! ከትእግስት ጋር እጅግ ተራርቀናል እና።

እግዚአብሄር ይስጥልኝ። መሸቢያ ጊዜ።፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.