ሆሣዕና ለንጉሠ ሰላም – ሆሣዕና በኣርያም – ሆሣዕና በአክሱም

ሐራ ዘተዋሕዶ

  • በዓሉ ከመንፈሳዊ እሴቱ ባሻገር ጥልቅ የኾኑ የቀደምት ትንቢቶች መድረስ፣ የተስፋዎች መፈጸም፣ የምሳሌዎች መተርጎም የታየበት፣ የፖሊቲካና የመንፈሳዊ ትርጓሜ ፍጥጫ፣ የባህሎች ጥምረት ማሳያ ነው፡፡ በዚህ በዓል የተደረጉ ኹነታት የጥንት ምዕራባውያንና የመካከለኛውን ምሥራቅ ባህልና ጥበብ አጣምሮ በተምሳሌትነት የያዘ ነው፡፡
  • በሆሣዕና በዓል፣ ሕፃናት ከዐዋቂዎች፣ ካህናት ከመላው ምእመናን ጋራ በአንድነት ከባለተራው መኖሪያ መንደር ጀምሮ እስከ መቅደሰ ጽዮን ድረስ በዝማሬና በእልልታ ያከብሩታል፡፡ በመንፈሳዊ እምነት መሠረት፣ በዚህች ዕለት በአክሱም ተገኝቶ የሰላም በዓልን በጽዮን አክብሮ፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብሎ ወደ ቤቱ የሚሔድ የቃል ኪዳኑ ባለቤት ስለሚኾን፣ በዓሉ በልዩ ግርማና ድምቀት ይከበራል፡፡
  • ሕፃናት የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው እየደጋገሙ፣ “ኪሮስ-ሜሎስ” እያሉ በመዘመር ይከተላሉ፡፡ ያልተተረጎመ እጅግ ጥንታዊ መሠረት ያለው የግሪክ ቃል ነው፡፡ ምናልባት ከዘመነ አክሱም ጀምሮ የነበረ ሊኾን ይችላል፡፡ “ኪሮስ” ማለት ከግሪኩ “ኩሪዮስ” የተገኘ ቃል ሲኾን፣ “ጌታ” ወይም “ጌታችን” ማለት ነው፡፡ “ሜሎስ” ማለትም እንዲሁ ከግሪክ የተገኘ ሲኾን፣ “ከእኛ ጋራ ኹን”/ከእኛ አንድ አካል መኾን/ ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ትርጉሙ፣ “ጌታችን ሆይ፣ ከእኛ ጋራ ኹን” ማለት ነው፡፡የአንድ ትልቅ ታሪክ ጠቋሚ ምሥጢር ነው፡፡ በሥነ ልሳናት(ቋንቋ) ጥናት ውስጥ እንዲህ ዓይነት ምልክቶች በራሳቸው የሚፈጥሩት የጥናትና ምርምር ጭረት አለ፡፡ ይህም ልብ ላለው የምርምር ጥሪ ነው፡፡

†††

/መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል/

ከትንሣኤ በፊት ባለው እሑድ የሚከበረውና ከታላላቆቹ የክርስትና በዓላት አንዱ የኾነው “በዓለ ሆሣዕና”፥ “የሰኔል በዓል”፣ “የሰላም ንጉሥ በዓል” ነው፡፡ “ሆሣዕና” የሥርወ ቃሉ አመጣጥ “ኾሻና” በአረማይክ ቋንቋ ከባለቤት ጋራ የተጣመረ ቃል ኾኖ በቀጥታ ወደ ዕብራይስጥ የተወሰደ ሲኾን፣ ትርጉሙም “እባክህ እርዳ፤ አኹን አድን” ማለት ነው፡፡ ንጉሥ ዳዊት በመዝሙሩ “አቤቱ እባክ አኹን አድን”/አቤቱ እባክ አኹን አቅና/(መዝ. 118:25) በማለት ዘምሯል፡፡

አለቃ ኪዳነ ወልድ፣ ቃሉን (ሆሻዓህ-ናእ) በማለት ዘርዘር አድርገው በፊደል በመግለጽ አቻ የግእዝ ትርጉሙን “አድኀንኮ”፣ “አድነን-እኮ፣ አድነን እንጅ፣ እባክ አድን” በሚል ተርጉመውታል፡፡ በቅድመ ክርስትና ልማደ አይሁድ ሰባት ቀን በሚከበረው “በዓለ መጸለት”/የታቦተ ጽዮንና የቤተ መቅደስ በዓል በየቀኑ ጠዋት በመጸለይ ሰባተኛውን ቀን ታላቁ ሆሣዕና/ሆሻና-ራባ/ በማለት ያከብሩት ነበር፡፡ በዓሉ፣ የድኅነት ቀንና አዳኝ መሲሕን የሚጠብቁ መኾናቸውን የሚገልጹበት ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ/ፖሊቲካዊ ትርጉም ነበረው፡፡

ከወንጌላዊው ሉቃስ በስተቀር በሦስቱ ወንጌላውያን ማለትም በማቴዎስ 21:9-15፤ በማርቆስ 11:9 እንዲሁም በዮሐንስ 12:13፤ “የሰላም ንጉሥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ላይ ተቀምጦ፣ በልዩ ግርማ፣ ሕፃናት ሆሣዕና በአርያም” እያሉ በመዘመር፣ ሕዝብ ኹሉ ልብሳቸውንና የዘንባባ ቅርንጫፍ እያነጠፉለት ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱን በጻፉት መሠረት ከበዓለ ትንሣኤ አንድ ሳምንት በፊት የሚከበር በዓል ነው፡፡ ጥንት ክርስትና ለመከበሩ በርከት ያሉ የጥበብ ምስክሮች ቢኖሩም በቀኖና ውስጥ በኹለተኛውና በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን “በጋንጋራ ሦስተኛ ጉባኤ” እንደ ጋብቻና ሥጋ መብላት ይከለክሉ የነበሩ ግኖስቲኮችን ለማውገዝ የተሰበሰቡ ኤጲስ ቆጶሳት ከሠሯቸው 20 ቀኖናት አንዱ ነው፡፡

ፍትሕ መንፈሳዊ በአንቀጽ 19/728 የጋንግራን 15ኛ ቀኖና በመጥቀስ “ወያብዕሉ በዓለ ሆሣዕና”/በዓለ ሆሣዕናን ያክብሩ/ በማለት ያዛል፡፡ በዚሁ ተመሳሳይ አንቀጽ(19/724) በዓለ “ሆሣዕና”ን ከክርስቶስ ዓበይት በዓላት ጋራ ቆጥሮታል፡፡ “ሆሣዕና” ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ቦታ የሚገኝ ሲኾን፣ “ሆሣዕና በአርያም” የሚለው ሐረግ ኹለት ጊዜ ተጠቅሷል፡፡ በክርስትናም ይኸው ዕለት ክርስቶስ ጦረኛና ዓለማዊ ንጉሥ ኾኖ ሳይኾን የሰላም እና የፍትሕ ንጉሥ፣ የሕዝቡን ኃጢአት የሚሸከም፣ በሞትና በኃጢአት፣ በጠብና በክፋት ተቃራኒ፣ አዳኝና ድል አድራጊ የሰላም ንጉሥ ኾኖ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱን ከታሪካዊ ክሥተቱ ጀምሮ በመተርጎምና መንፈሳዊ አምልኮ በመፈጸም በደማቅ ሥርዐት ይከበራል፡፡


የበዓለ ሆሣዕና ታሪካዊ መነሻዎችና ክንውኖች

ሃይማኖታዊ በኾነው የሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ “ድኅነት” ትልቁን ቦታ ይይዛል፡፡ ስለ ሰው ልጅ መንፈሳዊ ድኅነት ተስፋ ተሰጥቷል፤ ትንቢት ተነግሯል፤ ምሳሌ ተመስሏል፡፡ ኢየሩሳሌም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ታሪካዊ እና መልክዓ ምድራዊ ሚና አላት፡፡ በንጉሥ ዳዊት የተመሠረተችው ኢየሩሳሌም፣ በምድር የሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን፣ በሰማይ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ናት፡፡ የስሟ ትርጓሜ ኢር-ሳሌም “የሩ-ሻላይ/ሌ/ም” የሰላም ከተማ ማለት ነው፡፡ በርሷ ላይ የሚነግሠው ንጉሥ ደግሞ የሰላም ንጉሥ ይባላል፡፡ ስለዚህ በነቢዩ ዘካርያስ፣ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፣ እጅግ ደስ ይበልሽ፡፡ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፣ እልል በዪ፡፡ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፡፡ ትሑትም ኾኖ በአህያም፣ በአህያዪቱ ግልገል በውርንጫዪቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፤”(ዘካ.9፡9) ተብሎ ተጽፎላታል፡፡

ኢየሩሳሌም፣ ከንጉሥ ዳዊት በፊት በኢያቡሳውያን ስምና ዖፌል በሚባሉ ስሞች ተጠርታለች፤ በኋላም ጽዮን ተብላለች፡፡ ዳዊት ከኢያቡሳውያን ወስዶ ምስጋድና መካነ አምልኮ አደረጋት፡፡ ከዳዊት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ለከተማዋ ቅጽሮች ተሠርተዋል፡፡ ንጉሥ ሰሎሞን፣ ቅጽሮቿን አስፋፍቶና ቤተ መቅደስም ሠርቶ ነበር፡፡ ከባቢሎን ምርኮ ማብቂያ አካባቢ ነህምያ ሕዝቡን በማስተባበር በፋርስና በባቢሎን የፈረሰውን አድሶ፣ ኹለቱን በአንድ አጥር ጠቅልሎ ሠራ፡፡ ከዚያም በሮማውያን ፈርሶ እንደገና በሄሮድስ ኹለተኛውን፣ ሄሮድስ አግሪጳ ሦስተኛውን ቅጥር ገንብተዋል፡፡ በተጨማሪም በእነዚህ ኹሉ የዙሪያ መለስ ቅጽሮች ልዩ ልዩ ትርጉምና ስያሜ ያላቸው በሮች አሉ፡፡

የኢየሩሳሌም በሮች በተለያዩ ጊዜያት በመሠራታቸው፡- የሄሮድስ በር፣ የደማስቆ በር፣ አዲስ በር፣ ጃፋ በር፣ ጽዮን በር፣ ጥንድ በር፣ ምሥራቅ በር፣ አንበሳ በር… እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ ከእነዚህ ኹሉ የምሥራቅ በር የተባለው ደጅ ከሆሣዕና ጋራ ልዩ ቁርኝት አለው፡፡ የምሥራቅ በር የሚገኘው በደብረ ዘይት ተራራ አንጻር ሲኾን፣ በክርስትና የተዘጋው/የማይከፈተው ደጅ፣ ወርቃማው በር፣ የመሲሕ በር በመባልም ይታወቃል፡፡ በአይሁድ ዘንድ የምሕረት በር/ ሻር-ሐራኻሚሚ፤ በአረቦች የዘላለም ሕይወት በር ይባላል፡፡ በአረብ ሙስሊሞች ታሪክ፣ “የዘላለም ሕይወት በር” ወጥና ጥንድ ምሶሶዎች፣ ንግሥተ ሳባ ለንጉሥ ሰሎሞን የሰጠችው እንደኾነ ይነገራል፡፡

ይህ በር በኋላ ዘመን የአል-አቅሳ መስጊድ ወደ ታነፀበት ወደ ሰሎሞን ቤተ መቅደስ የሚያስገባ ሲኾን፣ የምሥራቁን የኢየሩሳሌም ቅጥር ጠርዝ ይዞ ይገኛል፡፡ የዚህ ደጅ ዋናው ሚና በአይሁድ ታሪክ ውስጥ የሰላም ንጉሥና የድኅነት አለቃ የኾነው መሲሕ የሚገባበት በር ተደርጎ መታመኑ ነበር፡፡ በሩ በመሲሑ ሲከፈት የድኅነት ቀን “ዮም-ኪፑር” መድረስ ስለኾነ የተዘጋውን በር “ማንም ሳይከፍትለት ይገባል” ተብሎ የተጻፈለትን መሲሕ አይሁድ በከፍተኛ ጉጉት ይጠብቁት ነበር፡፡

ከዚህ ታሪክ ጋራ በተያያዘ በየዘመኑ ኢየሩሳሌምን የተቆጣጠሩ መሪዎች፣ ለዚህ በር ልዩ ትኩረት ነበራቸው፡፡ ከተሠራበት ጊዜ ጀምሮ በየዘመኑ ሲከፈት ሲዘጋ፣ ሲፈርስና ሲገነባ ኖሯል፡፡ የመጀመሪያው በፋርስና ባቢሎን ፈረሰ፤ በነህምያ ተሠራ፡፡ በሮማውያን ፈረሰ፤ በ520 አካባቢ በጁስቲኒያን ተሠራ፡፡ በ630 ዓ.ም. ሔራቅሊስ(ሕርቃን) የክርስቶስ መስቀል ከተማረከበት ከፋርስ አምጥቶ በጎልጎታ ባስቀመጠ ጊዜ በዚሁ በር ገባ፤ ከዚያ በ810 በአረቦች ተዘጋ፡፡ በ1102 በመስቀል ጦረኞች ተከፈተ፤ ለመጨረሻ ጊዜ በሡልጣን ሱሌማን ዘመን(እአአ 1541) ተዘጋ፡፡ አኹን የሚታየው በር፣ ጌታችን በሆሣዕና ከገባበት በር የተለየ ነው፡፡ ጌታ እንደገባበት የሚነገረው፣ በነህምያ ጊዜ የተሠራው ነው፡፡

ኢየሩሳሌም በተለያዩ ጊዜያት ስትፈርስ ስትሠራ፣ የጥንቷ ኢየሩሳሌም ከአኹኑ መሬት ሥር ተቀብራለች፡፡ እአአ በ1969 ዓ.ም.፣ የዚህን በር ምሥጢራዊ ታሪክ ለማጥናት የተጋው አርኬዎሎጂስት ጀምስ ፍሌሚንግ በሥራ ላይ እያለ የቆመበት መሬት ተደርምሶ ወደ ታች በመውደቁ ጉዳት ባይደርስበትም፣ አንድ አስደናቂ ግኝት አስተዋወቀ፡፡ አኹን ካለው በር ሥር በንጉሥ ሰሎሞን ወይም በነህምያ(ነህ.3:29) ጊዜ የተሠራውን በር ተቀብሮ አገኘው፡፡ በተመሳሳይ ነቢዩ ሕዝቅኤል፣ “ይህ በር አይከፈትም፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ገብቶበታልና” በማለት ትንቢት ተናግሯል፡፡

በክርስትና፣ ይህ በር ከምሳሌነት ያለፈ ትርጉም የለውም፡፡ በነቢዩ ሕዝቅኤል የተነገረው(ሕዝ.43/44) እውነተኛው የሰላም ንጉሥ የተገለጸባት፣ አማናዊት የቤተ መቅደሱ የምሥራቅ አቅጣጫ የተዘጋች በር ድንግል ማርያም ነች፡፡ የተዘጋ የተባለበትም፣ የቅድስት ማርያም ዘላለማዊ ድንግልና ማስረጃ ነው፡፡ ስለ ታሪካዊነቱ ግን በዓለ ሆሣዕና ተከናውኖበታል፡፡

ጌታ ኢየሱስ በምሥራቁ በር ወደ ኢየሩሳሌም በ33 ዓ.ም. ገባ፡፡ ኢየሱስም ከኢያሪኮ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ፣ ከቤተ ፋጌ መንደር ኹለቱን ደቀ መዛሙርት ልኮ አህያዪቱንና ውርንጫዪቱን ከታሰሩበት ፈትተው እንዲያመጡለት አዟል፡፡(ማቴ.21:2) እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፡፡ “ልብሳቸውን በእነርሱ ላይ ጫኑ፤ ከሕዝቡም ብዙ ልብሳቸውን አነጠፉ፤ የዘንባባ ዝንጣፊም እየቆረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር፡፡ የሚከተሉትም፡- ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር፡፡” በበዓሉ የሚፈጸሙት መሠረታውያን ክንውኖች ከዚሁ ታሪካዊና መንፈሳዊ ክሥተት ጋራ የተያያዙ ናቸው፡፡

የአምልኮ ሥርዐቱ ከዋዜማው ጀምሮ የሚደረገው፣ በዕለተ እሑድ በተለይም በሰሙነ ሕማማት መግቢያ እንደመኾኑ፣ የሚፈጸሙት ሥርዐቶች ይህንኑ የወንጌል ንባብ መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ በዓሉ ከመንፈሳዊ እሴቱ ባሻገር ጥልቅ የኾኑ የቀደምት ትንቢቶች መድረስ፣ የተስፋዎች መፈጸም፣ የምሳሌዎች መተርጎም የታየበት፣ የፖሊቲካና የመንፈሳዊ ትርጓሜ ፍጥጫ፣ የባህሎች ጥምረት ማሳያ ነው፡፡ በዚህ በዓል የተደረጉ ኹነታት የጥንት ምዕራባውያንና የመካከለኛውን ምሥራቅ ባህልና ጥበብ አጣምሮ በተምሳሌትነት የያዘ ነው፡፡

mqdefault2

ክርስቶስ በአህያ ተጭኖ የመምጣቱ ምሳሌያዊ ትርጉም፣ በተለይ በዕብራውያን ልምድ፣ አህያ የሰላም ምልክት መኾኗ ነው፡፡ ነቢይ፣ መስፍን ወይም ንጉሥ በአህያ ኾኖ ከመጣ የሰላም ዘመን ነው፡፡ በፈረስ ከመጣ ጠብ ነው፡፡ በምዕራቡ ዓለም፣ አህያ የአገልጋይነት ምሳሌ ናት፡፡ አንድ ዐዋቂ/ፈላስፋ ወይም ገዥ በአህያ ወይም በአህያ ሰረገላ ከተጓዘ፣ የአገልጋይነት ምሳሌ ነው፡፡ የኦሎምፒክ ድል አድራጊ፣ በራሱ ላይ የሚደረግለት የዘንባባ ዝንጣፊ ነው፡፡ በዕብራውያንና በመካከለኛው ምሥራቅ ደግሞ ዘንባባ፡- የደስታ፣ የልዕልና፣ በፈተና ያለመሸነፍ ምሳሌ ነው፡፡

1c4346_palmas.jpgክርስቶስ እንዲመጡለት ያዘዛቸው የኹለቱ አህዮች ምሳሌነት ደግሞ፣ ትልቋ ሸክም የለመደች ኦሪት ያላት የእስራኤል ምሳሌ፤ ትንሿ ደግሞ ሸክም ያለመደች፣ ገና አዲስ ሕግ የሚማሩት የአሕዛብ ምሳሌ ነች፡፡ ክርስቶስ የኹሉ ንጉሥ መኾኑንና፣ ከእስር መፈታታቸውም ክርስቶስ ሕዝቡን ከኃጢአት ማሰሪያ፣ ከበደልና ከግዞት ነፃ የሚያወጣ ንጉሥ መኾኑን ለመግለጽ ነው፡፡ ልብስ ማንጠፍ በምዕራቡ ዓለም የመረታት፣ የመሸነፍና የሚመጣውን የመቀበል ምሳሌ ነው፡፡ በአይሁድ ልማድ ደግሞ የማክበር ምልክት ነው፡፡ አሕዛብ የራሳቸውን ያለማወቅ ልምድ ለመተው፣ ዕብራውያን የጠበቁትን ለመቀበል እሽ ማለታቸውን ለመግለጽ የተደረገ ነው፡፡

ክርስቶስ በዚህ ልዩ ግርማና በድምቀት ሕፃናት እየዘመሩ፣ አይሁድ እየታዘቡ፣ ሮማውያን በጥንቃቄ እየተከታተሉት ወደ ኢየሩሳሌም ገብቷል፡፡ በቤተ መቅደስ፣ ከመንፈሳዊ አገልግሎት ውጭ ቤተ መቅደሱን የንግድ ቤት ያደረጉትን ጠርጎ/ገርፎ አስወጣ፤ ድውያንን ፈወሰ፤ አስተማረ፤ ፍሬ የሌላትን በለስ ረገመ፤ ስለኢየሩሳሌም ጥፋት አዘነ፤ ከተቃዋሚዎቹም ጋራ ተነጋገረ፡፡ በዚኹ ሰሞን የድኅነት ሥራን ፈጸመ፤ የክርስትና ምሥጢራትን መሠረተ፡፡ በአይሁድ ሤራ ተይዞ በጲላጦስ ፍርድ በዐደባባይ ቆመ፤ ተገረፈ፤ መከራን ተቀበለ፤ በአራተኛው ፋሲካ ራሱን ለሰው ልጅ ኹሉ መሥዋዕት አድርጎ በመስቀል ላይ ሞተ፤ በሦስተኛው ቀንም ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፡፡ በተዘጋው የምሥራቅ ደጅ በሰላም ተምሳሌት፣ በአህያ ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው የሰላም ንጉሥ፣ ድል አድራጊነቱን ፈጸመ፡፡

ራሱን የፍቅር መሥዋዕት አድርጎ፣ ስለፍጥረቱ ኹሉ ሞቶ፣ እኛን ከራሱ ጋራ በማስታረቅ ሰላምን ለፍጥረቱ ሰጠ፡፡ ሰላም ያለ እውነተኛ ትሕትና፣ መከበር ያለፍትሕ፣ ፍቅርና ስምምነት ያለዕርቅ እንደማይገኝ በሕማሙና በመስቀሉ አስተማረን፡፡ በአህያ ተጭኖ የአገልጋይነትን አርኣያ ሰጠን፡፡ ከእናንተ መካከል ሊሾም የሚወድ ቢኖር ያገልግል፤ በማለት እውነተኛ የሥልጣን ምንጭ ማገልገል መኾኑን አስተማረ፡፡

በሀገራችን ሙሰኞች፣ “ሢሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” እንደሚሉት፣ በግሪክ ወሮም ዘመን፣ የሥልጣን ትርጉም ለመግዛት፣ ለመመለክ፣ ለማስገበርና የራስን ፍላጎትና ድሎት ብቻ ለመፈጸም መሣሪያ ነበር፡፡ ክርስቶስ በአህያ ላይ ማለትም፣ ለሮማውያን – የአገልጋይ ምሳሌ፤ ለአይሁድ የሰላም ምሳሌ ኾኖ ወደ ኢየሩሳሌም በመግባት በዚሁ ሳምንት ይህን መመሪያ ሻረ፡፡ የአላዋቂዎች መገለጫ የኾነ የትዕቢትንና ትምክህትን አከርካሪ በትሕትና በትር ሰበረ፤ እርሱ መምህር ኾኖ ሳለ ጎንበስ ብሎ የተማሪዎቹን እግር አጠበ፤ ትሕትና የሰላምና የአገልጋይነት መሣሪያ መኾኑን አስተማረ፡፡ “ይኸንንም ኹልጊዜ ካላደረጋችሁ ከእኔ አይደላችሁም” ብሎ ማገልገልን የሥልጣን ምንጭ/መገኛ አድርጎ ሰጣቸው፡፡ “ሊሾም የሚወድ ያገለግል/ የማያገለግል አይሾም” ብሎ አዘዘ፡፡ የጥንቱ የግሪክ ወሮም የሥልጣን መመሪያ ተሸሮ፣ ዛሬ መሪዎች ወደ በትክክለኛ የሕዝብ ምርጫ ወደ ሥልጣን ሲመጡ፣ “ሕዝባችንን እንድናገለግለው ስለ መረጠን እናመሰግናለን” እንዲሉ ያደረጋቸው፡፡

በጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት፣ ይህ ኹሉ ክሥተት፣ ታሪኩንና ምሳሌውን ሳይለቅ፣ ከአማናዊ ትርጉሙ ጋራ በየዓመቱ ይከወናል፡፡ ትንቢቱ ከነፍጻሜው በየተራ ይነበባል፤ ምሳሌው ከነአማናዊ ትርጉሙ በተግባር ይከወናል፡፡ ሜል ጊብሰን፣ በ“The Passion of Christ”(የክርስቶስ ሕማም) በተባለ ሥራው፣ ይህን ሥርዐተ አምልኮ በከፍተኛ ጥንቃቄ አጥንቶ በፊልም ሲተውነው አንድ የሃይማኖት መሪ “It is as it was”(እንደነበረ ተደርጎ የተሠራ ነው) ብለው ነበር፡፡ በቤተ ክርስቲያን ግን በትወና ሳይኾን በልዩ ሥርዐት፣ ከእምነት እና ከመሰጠት ጋራ በልዩ ሥርዐት ይከበራል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በዓሉን በጥንታዊ ሥርዐቱ በማክበር፣ ከጥንታውያን ኦሪየንታል ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ወገን ስትኾን፣ በራሷ ትውፊት ከብሉይ ኪዳን ወይም ከቅድመ ክርስትና ታሪክ ጋራ በማዋሐድ በማክበሯ ደግሞ ከየትኛውም ዓለም ልዩ ያደርጋታል፡፡ በዓሉ ከመንፈሳዊ ዕሴቱ ባሻገር በርካታ ትኩረት ያልተሰጣቸው፣ ነገር ግን በባህላዊ ትስስራችን፣ በባህል ግንባታ፣ በማኅበራዊ ዕድገት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው በዓል ነው፡፡

በዚህ በዓል፣ ሀገራችን የራሷን ትውፊት እንድትይዝ በማድረጉ ሒደት ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ እና ሌሎችም በየዘመናቱ የተነሡ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ደክመውበታል፡፡ በኹሉም የሀገራችን ክፍል በአንድነትና በተመሳሳይ መንፈሳዊ ክዋኔ የሚከበር ቢኾንም፣ በአክሱም ቦታው ካለው ጥንታዊ የእምነት ሽግግር መሠረትነቱ አንጻር ለየት ያለ አከባበር አለው፡፡

ሆሣዕና በርአሰ ገዳማት ወአድባራት አክሱም ጽዮን

በአክሱም፣ ለምእመናን የምትነበብ “ድርሳነ ጽዮን” የምትባል መጽሐፍ አለች፡፡ በመጽሐፏ አንድ ክፍል፣ “ምእመናን ሆሣዕናን በአክሱም እንዲያከብሩ” ጥሪ ታስተላልፋለች፡፡ አክሱም የአፍሪቃ ጥንታዊት ከተማ ናት፡፡ በርካታ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ክንውኖች ስለተፈጸሙባትም፣ በአኹኑ ጊዜ ዓለም አቀፍ የታሪክ እና የመንፈሳዊ በዓላት ማዕከል ነች፡፡ ትውፊትንና ታሪክን መሠረት አድርጎ የአክሱምን አመሠራረትና ታሪካዊ እድገት፣ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ማዕከልነት የሚናገረው ኹለተኛው መጽሐፍ፣ “መጽሐፈ አክሱም” ይባላል፡፡ ስለ አክሱም አመሠራረት፣ ሰፊ ትውፊታዊ ትንታኔ ይሰጣል፡፡ የአኹኖቹ የግሪክ እና የሮም ከተሞች እጅግ ሰፊ የነበረው የግሪክ ወሮም ግዛትና መንግሥት ታሪክ ማሳያዎች እንደመኾናቸው፤ የአኹኗ አክሱምም፣ ምሥራቅ አፍሪቃን ከደቡብ አረብ አጣምራ ትገዛ ለነበረችው የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ(ዘመነ አክሱም) ታሪክ መዘክር ነች፡፡

በጥንታዊቷ ከተማ፣ በዓመት ኹለት ጊዜ፣ የአክሱምን ታሪክ፣ የብሉይ ኪዳንን ትንቢት፣ በአዲስ ኪዳን የተፈጸመውን የድኅነት ምሥጢር አንድ አድርገው የሚዘክሩ፡- የሆሣዕና በዓል እና ኅዳር 21 ቀን የሚከበረው የጽዮን በዓል ይከበራሉ፡፡ በአክሱም የሆሣዕና በዓል አከባበር፣ አስደናቂ ታሪክ ያለውና በሰፊው ሊጠና የሚገባው ነው፡፡

የዚህ ምክንያቱ፣ አንደኛ፡- በዓሉ ከአክሱም ሥልጣኔ አመሠራረትና ዕድገት፣ የመንግሥትና የማኅበራዊ ማዕከልነት ታሪክ ጋራ ተጣምሮ ስለሚከበር፤ ኹለተኛ፣ የቀድሞዎቹ የአክሱም ነገሥታት በዚህች ዕለት ታላላቅ ሀገራዊና መንፈሳዊ በዓላትን ማክበራቸው ስለሚተረክ፤ ሦስተኛ፣ በዓለ ሆሣዕና በብሉይ ኪዳን የታቦተ ጽዮን/ቤተ መቅደስ በዓለ መጸለት እንዲሁም ከጽዮን ንጉሥ ክርስቶስ ጋራ ተያይዞ የተነገሩ ትንቢቶችንና ምሳሌዎችን በመዘከር ብሉይን ከሐዲስ ጋራ አስማምቶ የሚከበር ስለኾነ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በዓለ ልደትን በላሊበላ፣ ትንሣኤን በኢየሩሳሌም ተገኝተው እንደሚያከብሩ ኹሉ ሆሣዕናን በአክሱም ያከብሩ እንደነበር ታሪካዊ መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡

በሆሣዕና በዓል፣ ሕፃናት ከዐዋቂዎች፣ ካህናት ከመላው ምእመናን ጋራ በአንድነት ከባለተራው መኖሪያ መንደር ጀምሮ እስከ መቅደሰ ጽዮን ድረስ በዝማሬና በእልልታ ያከብሩታል፡፡ በመንፈሳዊ እምነት መሠረት፣ በዚህች ዕለት በአክሱም ተገኝቶ የሰላም በዓልን በጽዮን አክብሮ፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብሎ ወደ ቤቱ የሚሔድ የቃል ኪዳኑ ባለቤት ስለሚኾን፣ በዓሉ በልዩ ግርማና ድምቀት ይከበራል፡፡

የበዓሉን ታላቅነት የሚገልጹት ባሕርያቱም፤ አንደኛ፡- ለረጅም ዘመናት በወጥነት ሲከበር የኖረ በመኾኑ፤ ኹለተኛ፡- ለኹለት ቀናት በዐደባባይ የሚከበርና በጣም ብዙ ሕዝብ የሚሳተፍበት መኾኑ፤ ሦስተኛ፡- በዓሉ የሚከበረው በራሱ ታሪካዊ መነሻና ከጥንታዊው የመልክዓ ምድር ስያሜ ጋራ ያልተለያየ መኾኑ፤ አራተኛ፡- አፈ ታሪክ ሳይኾን መሠረታዊ የታሪክ መረጃዎችን ድጋፍ አድርጎ የሚከበር መኾኑ፤ አምስተኛ፡- የዚህ በዓል ቀዳሚ ባለቤቶችና የታሪኩ ወራሾች በዓሉን ለማክበር ያላቸው ተነሣሽነት፤ ስድስተኛ፡- በዓሉ የሚከበረው በታሪካዊቷ፣ በጥንታዊው የሀገራችን የሥነ ጽሑፍ እና የሥነ ጥበብ ታሪክ ጉልሕ ቦታ ባላት አክሱም መኾኑ ናቸው፡፡ በዓሉ ዛሬም፣ በከተማዋና በነዋሪዎቿ የባህል፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ ትስስር ሕይወት፣ የቋንቋ ዕድገትና ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የያዘ ነው፡፡

በአክሱም ትውፊት መሠረት፣ አክሱምን የመሠረቷት ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፡፡ የእነርሱም ትውልድ እስከ አኹን ድረስ በአክሱም ይገኛል፡፡ ወንድማማቾቹ በመላው ሀገሪቱ ተሠራጭተው ታላቅ ሀገር መሥርተዋል፡፡ ይህ ታሪክ ከክርስትና በፊት በየዓመቱ ሲከበር፣ በዘመነ ክርስትና ከሆሣዕና በዓል ጋራ አብሮ መከበሩን እንደቀጠለ አበው ይመሰክራሉ፡፡ የበዓሉ ትውፊታዊና ክርስቲያናዊ አከባበርም በአጭሩ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

በዋዜማው ከኹሉ አስቀድሞ የጽዮን ካህናት የክብር ልብሳቸውን ለብሰውና ንዋየ ቅድሳቱን ይዘው ወሰደ ተረኛው ቤት ይሔዳሉ፡፡ ተረኛውም ከሰባቱ ወንድማማቾች ትውልድ አንዱ ሲኾን፣ በሰባት ዓመት አንድ ጊዜ ይደርሰዋል፡፡ ከዚያም የጽዮን ካህናት፣ የቤቱን ባለቤትና ቤተ ዘመዶቹን ከባረኩ በኋላ ልዩ ልዩ ጸሎቶችንና ሥርዐቶችን እዚያው ያከናውናሉ፡፡ በሥርዐቱ መካከልም በተረኛው ቤትና ቤተ ዘመዶች አዲስ የተዘጋጀውን የአንድነት ማዕድ ይቀምሳሉ፡፡ በዚሁ ቤት ውስጥ ለሆሣዕና በዓል አከባበር የተመረጠችውንና ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ሲሔድ የተቀመጠባት አህያ ምሳሌ የኾነችውን አህያ በልዩ ልዩ አልባሳት በክብር ያስጌጣሉ፡፡ በዋዜማው ኹሉም ካህናት በዚሁ ቤት ይመገባሉ፤ ከዚህ ጊዜ በኋላ በልዩ ልዩ ሥርዐት ውስጥ ስለሚኾኑ እስከ በዓሉ ፍጻሜ ድረስ አይመገቡም፡፡

በቤት ውስጥ የሚካሔደው የጸሎትና የቡራኬ አገልግሎት ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ መቅደሰ ጽዮን ለመጓዝ ዝግጅቱ ይጀመራል፤ ጸሎትም ይደረጋል፡፡ የበዓሉ መሪ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት ካህናቱ በተራ ይቆማሉ፡፡ በየማዕረጋቸውና በያዙት ንዋያት ቅደም ተከተል መሠረት ለዑደቱ ይወጣሉ፡፡ በመሰንቆ እና በበገና ልዩ ልዩ ጣዕመ ዜማዎች ይሰማሉ፡፡ በካህናቱና በዲያቆናቱ ታጅበው መዘምራኑ በሃሌታ፣ ሕዝቡ በእልልታ እየተከተሉ ለክብረ በዓሉ የሚኾነው ኹሉ ተይዞ ከባለተራው ቤት ይወጣሉ፡፡

ሕፃናት የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው እየደጋገሙ፣ “ኪሮስ-ሜሎስ” እያሉ በመዘመር ይከተላሉ፡፡ ያልተተረጎመ እጅግ ጥንታዊ መሠረት ያለው የግሪክ ቃል ነው፡፡ ምናልባት ከዘመነ አክሱም ጀምሮ የነበረ ሊኾን ይችላል፡፡ “ኪሮስ” ማለት ከግሪኩ “ኩሪዮስ” የተገኘ ቃል ሲኾን፣ “ጌታ” ወይም “ጌታችን” ማለት ነው፡፡ “ሜሎስ” ማለትም እንዲሁ ከግሪክ የተገኘ ሲኾን፣ “ከእኛ ጋራ ኹን”/ከእኛ አንድ አካል መኾን/ ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ትርጉሙ፣ “ጌታችን ሆይ፣ ከእኛ ጋራ ኹን” ማለት ነው፡፡የአንድ ትልቅ ታሪክ ጠቋሚ ምሥጢር ነው፡፡ በሥነ ልሳናት(ቋንቋ) ጥናት ውስጥ እንዲህ ዓይነት ምልክቶች በራሳቸው የሚፈጥሩት የጥናትና ምርምር ጭረት አለ፡፡ ይህም ልብ ላለው የምርምር ጥሪ ነው፡፡

ወደ ቤተ ክርስቲያን ከተደረሰ በኋላ ካህናቱ ሕዝቡን ባርከው ያሰናብታሉ፡፡ ኹሉም ሌሊት ለሚደረገው ሥርዐት ዝግጅት ወደየቤቱ ይሔዳል፡፡ በዚሁ ዋዜማ ሌሊቱን በሙሉ ሊቃውንት፣ መዘምራን በያሬዳዊ ዝማሬ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ያድራሉ፡፡ ምእመናንም ቤታቸውን ትተው በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ያድራሉ፡፡ ጌታችን ለእኛ ድኅነት ሲል ወደ ኢየሩሳሌም ገብቶ በምኩራብ ማስተማሩ የሚዘከርበት ስለኾነ ከሩቅም ከቅርብም የተሰበሰቡ ምእመናን፣ በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ በጸሎት እና በምሕላ ያድራሉ፡፡

በውስጥም በውጭም ኹነው በጋራና በተናጠል፣ በጸሎትና በምስጋና ሌሊቱን ያሳልፋሉ፡፡ ንጋት ላይ ደግሞ የዕለቱ ሥርዐተ ቅዳሴ በተገኙት ቅዱስ ፓትርያርክ፣ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ንቡረ እድ እና ቀሳውስት ይከናወናል፡፡ ከሩቅም ከቅርብም የመጡት ምእመናን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ በዚህ ቀን በአክሱም ተገኝቶ ቅዱስ ቁርባን ሳይቀበል የሚቀር የለም፡፡ ይህ እንደ ቃል ኪዳንዋ ለብዙ ዘመን የቆየ ሥርዐት ነው፡፡

 

header_neu_4

ከሥርዐተ ቅዳሴው በኋላ ወደ ዐውደ ምሕረቱ ተወጥቶ በዕለቱ በተገኙት ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃነ ካህናት በአክሱም ንቡረ እድ ጭምር ታጅበው በቤተ ክርስቲያን በአራቱም ማዕዘናት እየተዞረ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ፤ ጸሎትና ዝማሬም ይደረጋል፡፡ ከወንጌላቱ ንባብና ጸሎት በኋላ፣ ሊቃውንቱ የዘንባባ ዝንጣፊ በእጃቸው ይዘው በዐውደ ምሕረቱ ፊት በመቆም፣ “ተፅዒኖ ዲበ ዕዋል” የሚለውንና ጌታችን በአህያ ውርንጭላ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱን የሚያስታውሰውን ዝማሬ ያዜማሉ፡፡ የዘንባባ ዝንጣፊ ለምእመናን ታድሎ፣ የዕለቱ ጸሎት ተደርሶ፣ ቃለ ቡራኬ እና ቃለ ምዕዳን ይሰጣል፡፡ ሆሣዕና በአርያም! ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት! ሆሣዕና ለንጉሠ ሰላም፤ ሰላም በምድራችን ኹሉ ለሰው ልጆች ይኹን! የሰላም ንጉሥ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነትና በረከት ከኹላችን ጋራ ይኹን፡፡ አሜን ተብሎ፣ ለሳምንት የሚኾን ጸሎተ ፍትሐት ተደርሶ የበዓሉ ፍጻሜ ይኾናል፡፡

ከዚህ ቀን ጀምሮ ሳምንቱን በሙሉ ሰው ቢሞት አይፈታም፤ ፍትሐቱ በዚህ ቀን ተደርጓልና፡፡ መስቀል መሳለምና ማማተብም እስከ ዕለተ ዓርብ ድረስ(ለአንድ ሳምንት ያህል) ይቆማሉ፡፡ ከጸሎተ ሐሙስ በቀር ለአንድ ሳምንት ቅዳሴ አይኖርም፡፡ በስግደት፣ በንባብ፣ በጸሎት ተቆይቶ ሐሙስ ጸሎተ ሐሙስ፣ ዓርብ ስቅለት፣ እሑድ ትንሣኤ ይከበራል፡፡

ምእመናን የተሰጣቸውን የዘንባባ ዝንጣፊ በእጃቸው እንደ አንባር፣ በጣታቸው እንደ ቀለበት፣ በግንባራቸው እንደ አክሊል እያሰሩ ወደየቤታቸው ይሔዳሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ በሆሣዕና የሠሩትን የዘንባባ ጌጥ በሰሙነ ሕማማት አድርገውት ይቆያሉ፡፡ ይህም የራሱ ማኅበራዊ ምሳሌ እንዳለው አበው ይናገራሉ፡፡ አጠቃላይ ትርጉሙ ግን ከሰላም ጋራ የተያያዘና ሰላምን የምናነግሥበት ነው፡፡

ሆሣዕና የሰላም በዓል ነው፡፡ ሰላም ሃይማኖት ነው፤ የፈጣሪ መገለጫና የስጦታዎቹ ኹሉ ፍጻሜ ታላቁ ጸጋ ነው፡፡ ሰላም ምትክ የለውም፤ በምንም አይሰፈርም፡፡ የማያልፈውን ሰላም ፍለጋ ሰዎች የሚያልፉ ምድራዊ ነገሮቻቸውን ይተዋሉ፡፡ ዛሬም ሆሣዕናን ስናከበር ከኹሉ በላይ ለሰላም በመጸለይና ኹላችንንም የሰላም መሣሪያዎች እንዲያደርገን በመመኘት ነው፡፡

hqdefault3

አባ ጊዮርጊስ በመጽሐፈ ምሥጢር ስለ ሆሣዕና በጻፈው ምንባብ፣ “ሆሣዕና ከቅድስት ድንግል ማርያም ለተወለደው ለዳዊት ልጅ፣ በእልልታ ቃል በዓል እናድርግ፤ የወይራ ዝንጣፊ-የመስቀል፤ የሰኔል/ዘንባባ ዝንጣፊ-የወንጌል፤ የአይሁድ ቤተ መቅደስ- የቤተ ክርስቲያን፤ የታቦት ምሳሌ ድንግል ማርያም ናቸው፤” በማለት ሆሣዕናን የሰላም በዓል አድርገን እንድናከብር ያስተምራል፡፡ ሆሣዕና ለሰላም ሆሣዕና በአርያም! ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት! ሆሣዕና ለንጉሠ ሰላም፤ ሰላም በምድራችን ይኹን!

ምንጭ፡- ታዛ መጽሔት፤ መጋቢት ፳፻፲ ዓ.ም.

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.