ለዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ግልጽ ደብዳቤ (የዐማራው ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት)

4/2/18

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር፣

ከሁሉ አስቀድመን፣ የታላቁንና የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲል የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ መሪ ለመሆን ላገኙት ዕድል እንኳን ደስ አለዎት እንላለን።

ደስታዎትና ደስታችን ግን፣ ዕውነተኛ ደስታ የሚሆነው፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ መሠረታዊ እና ተፈጥሮአዊ የሆነው ሰዋዊ መብቶቹና ጥቅሞቹ የሆኑት፣ በፈለገው ቦታ የመኖር፣ የመረጠውን ሥራ የመሥራት፣ ሀሳብና ምኞቱን ሳይሸማቀቅ የመግለጽና የመደራጀት፣ ኃላፊነቶች በውድድርና በችሎታ እንዲያዙ ሲደረግ፣ የግለሰብ ነፃነት እና የግል ሀብት ሲረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነት ሲሰፍን እና የዜግነት መብትና ጥቅም ሲከበሩ፣ ኢትዮጵያ ጥንታዊ አገር እንደመሆኗ፣ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ያላት እንጂ፣ የሕዝቦች ስብስብ አለመሆኗ ሲታወቅ እንደሆነ እናምናለን። የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ስንልም፣ አንድ የአገርና የሕዝብነት መለያ የወል ዕሴቶች የገነባ ሕዝብ ማለታችን እንደሆነ ይስቱታል አንልም።

በኃላፊነት ርክክበዎ ሰዓት ያደረጉትን ንግግር በጥሞና አዳምጠነዋል። በንግግረዎ! እናተዎና ባለቤተዎ፣ ለደረሱበት ደረጃ ያበቁዎ መሆኑን ማመስገነዎና  የእግዚአብሔርን ስም መጥራተዎ፣ ከአቶ መለስና ከአቶ ኃይለማርያም የሚለየው ቁም ነገር እንደ ሆነ አጢነናል። ይህ በራሱ መልካም ነገር እንደሆነም እንገነዘባለን። ከዚያ በተረፈ፣ ቸኮላችሁ፣ ካልተባልን በቀር፣ የተናገሩትን ወደ ተግባር የመለወጥ ሙሉ ሥልጣን ከነበራቸው ከአቶ መለስ ዜናዊ ንግግርና በል የተባሉትን ከሚሉት ከአቶ ኃይለማርያም የሚለየዎ፣ ንግግረዎ፣ ስለኢትዮጵያ አንድነትና ይህ አንድነት እንዴት እንደተገነባ የተጠቀሙበት አገላለጽ ነው።

በዚህ ንግግረዎ፣ ስለብሔራዊ መግባባት የተናገሩት ለተለያዩ ትርጉሞች የተጋለጠ ሆኖ አግኝተነዋል። እንደ ዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት አቋም ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት የብሔራዊ መግባባት ዕውን ሊሆን የሚችለው የሚከተሉትን በተግባር ሲገለጹ ነው ብለን እናምናለን። ብሔራዊ መግባባት መፍጠር የሚቻለው፣ የበደለ ሲክስና ተበዳይ ሲካስ ነው። ይህም ካሽና ተካሽ ይቅር ለእግዚአብሔር ተባብለው ማኅበራዊ ሰላም የሚሰፍነው የሚከተሉት ዕውን ሲሆኑ ነው። እነዚህም፦

  • ኢሕአዴግ እመራበታለሁ በማለት የሚመካበትንና እርሰዎም ከአቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ የተቀበሉት ሕገ መንግሥት ከሚፈቅደው ውጭ እና በፓርላማው ሁለት ሦስተኛ ድጋፍ ሳያገኝ ፀደቀ የተባለውን የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ ሲያነሱ፣
  • የፖለቲካ እስረኞችን ካላንዳች ቅደመ ሁኔታ ሲፈቱ፣
  • ከትውልድ ቦታቸው በኃይል የተፈናቀሉ፣ ዐማሮች፣ ኦሮሞዎች፣ አኙዋኮች፣ ወዘተ አስፈላጊው ካሣ ተከፍሏቸው ወደ ነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ ሲያደርጉ፤
  • በግልጽ ፕሮግራም ተነድፎ የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ወንጀል ለተፈጸመባቸው ከ5 ሚሊዮን በላይ ዐማሮች ቤተሰቦች፣ የደም ካሣ እንዲከፈላቸው ሲደረግ እና ድርጊቱን የፈጸሙ ቡድኖችና ግለሰቦች ለፍትሕ የሚቀርቡበት ሁኔታ ሲመቻች፤
  • የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት የማንነት ጥያቄ በአስቸኳይ ተገቢውን መልስ እንዲያገኝ ሲደረግ፤
  • የአገራችን ችግሮች ሁሉ ቋጠሮ የሆነው የጎሣ ፌዴራሊዝም እና የሚመራበት በዘር ላይ የተመሠረተ አመለካከት፣ የሕዝቡ ዕውነተኛ ፍልጎት መገለጫ በሆነ፣ ሕዝቡ በቀጥታ ተሳታፊ የሚሆንበት፣ ማንንም ያላገለለ የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ሂደት ውስጥ ሊያስገባ የሚችል የአሠራር ዘዴ በመቀየስ ወደዚያ ግብ የሚያመራ ሁኔታ ማመቻቸት ሲቻል፤
  • በሙስና የተዘፈቁ ግለሰቦችና ቡድኖችን በአፋጣኝ ለፍትሕ እንዲቀርቡ ሲደረግ፣ ያን ጊዜ ወደ ብሔራዊ መግባባት ወደሚያስችለው ጎዳና ገባን ማለት ይቻላል ብለን እናምናለን።

እነዚህን እርምጃዎች ለመውሰድ እንደሚችሉ በሕገመንግሥቱ የተሰጠዎ ተግባርና ኃላፊነት በግልጽ ያሳይል።  የሚፈልገው የእርሰዎን ቅንና ፍትሓዊ እሳቤ ብቻ ነው። እነዚህን እርማጃዎች ከወሰዱ፣ በእርግጥ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት የቆሙ ሆነው ከመታየተዎትም በላይ፣ በታሪኳ ልዩ ቦታ የሚይዙ ይሆናሉ። ይህን በማድረገዎትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎነዎ ከመቆም አልፎ፣ «መሪአችን» ብሎ ወዶ ያከብረዎታል። ይህን ካላደረጉ፣ ከአቶ መለስና ከአቶ ኃይለማርያም የሚለዩበት ምንም ነገር ስለማይኖር፣ በታሪከዎ ሊጠቀስ የሚችል ቁምነገር ይኖራል ለማለት ያስቸግራል ። የለውጥ ተነሳሺነተዎን ከላይ በጠቀስናቸው አንኳር ጉዳዮች ካልጀመሩ፣ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ ሕዝቡን በማስተባበርና አገር አፍራሽ የሆነውን ሥርዓት ከሥሩ ለመንቀል የተያያዘውን ትግል አጠናክሮ የሚገፋበት መሆኑን ከወዲሁ ለማሳወቅ ይወዳል።

የዐማራው ኅልውና መጠበቅ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነው!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.