‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲ ይገባናል ያስፈልገናል›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

ዮሐንስ አንበርብር

ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን በመተካት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሰየሙት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲና ነፃነት የሚያስፈልግ ብቻ ሳይሆን የሚገባ እንደሆነ ተናገሩ፡፡

‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲ ይገባናል፣ ያስፈልገናል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹ዴሞክራሲ ያለ ነፃነት አይታሰብም፣ ነፃነት ደግሞ ከመንግሥት ለሕዝብ የሚበረከት ስጦታ አይደለም፤›› ሲሉ ለፓርላማ አባላትና በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ለተከታተሉ ኢትዮጵያውያን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶች በተለይም ሐሳብን የመግለጽ፣ የመሰብሰብና የመደራጀት መብቶች በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሊከበሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

‹‹ሕዝብ አገልጋዩን የመተቸት፣ የመምረጥና የመጠየቅ ሙሉ መብት አለው፡፡ መንግሥት የሕዝብ አገልጋይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የአገሪቱ ሕዝብ ፍላጎት ከፍትሕ መፋታት እንዳልሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ለፍትሕ የቆመ የሕግ ሥርዓት እንደሚገነባና ሕግ ሁሉንም በእኩል የሚዳኝ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ ለቆየው አለመግባባት መንግሥታቸው ከልብ እንደሚሠራ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩ የሁለቱ አገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል ልዩነቶቻችንን በውይይት ለመፍታት ያለንን ዝግጁነት እየገለጽኩ፣ የኤርትራ መንግሥት ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን በተናገሩበት ወቅት ከፍተኛ የድጋፍ ጭብጨባ ከምክር ቤቱ አባላት ተሰምቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገሪቱን ሕዝብ ብሶት ካጋጋሉ ምክንያቶች አንዱ ሙስና መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹ኢትዮጵያችን አንዱ ሠርቶ ሌላው ቀምቶ የሚኖርባት አገር እንዳትሆን ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ በትህትና እጠይቃችኋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.