የሚጠበቅና እየሆነ ያለው (ኤርሚያስ ለገሰ)

  1. ክላስተሪንግ በጓሮ በር!”
ኤርሚያስ ለገሰ
ኤርሚያስ ለገሰ

ከውስጥ የሚወጡ መረጃዎች እየሰማን ያለነው ነገር በጣም አስደንጋጭ ነው። አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ከጨዋታ ውጪ የሚያወጣ ኢመደበኛ አደረጃጀቶች የወሳኝ ስራዎች ባለቤት ሆነዋል። መጀመሪያ በ12 የተደራጁ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በኃላ ወደ 7 የወረዱ ግብረ ሃይሎች ( Task Force) ተደራጅተው የጠቅላዩን ወሳኝ ስራዎች ጠቅልለው ወስደዋል። ከሁሉም በላይ ለውጥ ይመጣል በሚል ተስፋ ላደረጉ ኢትዬጲያውያን የሚያሳዝነው ክላስተሩን የሚመሩት ሰዎች እነማን እንደሆኑ መታወቃቸው ነው። ቡድኑ እስከሚቀጥለው የኢህአዴግ ጉባኤ ይቀጥላል መባሉ ሌላ አስደንጋጭ መርዶ ነው።

ቢያንስ አራቱን እንመልከት።

# የመጀመሪያው ግብረ ሀይልዲሞክራታይዜሽን የተባለ ስያሜ የተሰጠው ሲሆን የክላስተሩ አስተባባሪ በረኸት ስምኦን እና ህላዌ ዬሴፍ ናቸው። በረኸት በመላው ኢትዬጲያ ያሉ የህዝብ አደረጃጀቶችን፣ ሲቪክ ማህበራትን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ ወጣቶችና ሴቶችን በሀላፊነት እንዲመራ ተሰጥቶታል። በሌላ አነጋገር የኢህአዴግ ቢሮን፣ የወጣቶች ሚኒስትርን፣ ሴቶች ሚኒስትርን፣ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትርን በክላስተር የሚመራው በሕዝብ እጅግ የሚጠላው በረኸት ስምኦን ሆኗል።

በአገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ቦታዎች የሚካሄዱ የህዝብ ስብሰባዎች ሰነድ የሚዘጋጀው፣ መድረክ መሪ የሚመርጠው፣ በየቀኑ የመወያያ ነጥቦች የሚያሰራጨው እና የሚመራው በረኸት ስምኦን ነው። ከዚህ በተጨማሪም “ ምድር አንቀጥቅጥ” የሚል ስያሜዎች የተሰጣቸውን ስብሰባዎች እየገመገመ በድርጅት እና የመንግስት ሚዲያዎች እንዲተላለፋ፣ ተሳታፊዎችን ወደ ፓርቲ ምልመላ መምጣታቸውን የሚያረጋግጠው ህላዌ ዬሴፍ እንደሆነ ተነግሮኛል። በረኸት፣ ህላዌና ሽፈራው ሽጉጤ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር እሳትና ጭድ መሆናቸው ለሚያውቅ ደግሞ ዶክተር አቢይ የገባበትን አጣብቂኝ በቀላሉ ይገነዘባል።

# ሁለተኛው ክላስተርየኢኮኖሚ ጉዳዬች ግብረ ሀይል የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ኢኮኖሚውን ለመቆጣጠር ክላስተሩን የሚመሩት ህውሓቶቹ አርከበ እቁባይ እና ዶክተር አብርሃም ናቸው።

# ሶስተኛው ክላስተርድርጅት የማጠናከር የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ፓርላማውን፣ የክልል ምክር ቤቶችን፣ የማእከላዊ ኮሚቴ እና እስከ ቀበሌ ያለውን ምክር ቤት የሚመራ ነው። ለዚህ ክላስተር ሃላፊነት የተሰጠው በዋናነት ለአባዱላ ገመዳ እና ሽፈራው ሽጉጤ ነው። ከዚህ በኃላ ከላይ እስከ ቀበሌ ያሉት የምክር ቤት አባላት ወደ ድሮ አድርባይነታቸው እንዲመለሱ ለአባዱላ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል።

# ሌላው አስቂኝ ግብረ ሃይልህገ ወጥነት መከላከል የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን የበላይ አስተባባሪው አባይ ፀሀዬ መሆኑ እየተገለጠ ነው።

# ሌላው ክላስተርየውጭ ግንኙነት የሚባል ሲሆን አስተባባሪው ስዩም መስፍንና ወርቅነህ ገበየሁ ናቸው። ይሄ ቡድን የውጭ አገሮችን ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዬጲያውያንን እና ትውልድ ኢትዬጲያውያንን የማማለል ስራ ይሰራል። በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ አንዳንድ ግለሰቦች በዲያስፓራው ስም እንቅስቃሴ እንዲጀምሩ ከጀርባ ሆኖ የሚመራው ይሄ ቡድን እንደሆነ ይነገራል።

            ማስጠንቀቂያ:-
መልእክቱን ያደረሱን ሰዎች ዶክተር አቢይ በአንድ ሳምንት ውስጥ ይሄንን በግብረ ሃይል ስም በጓሮ በር የገባውን ክላስተር ማፍረስ ካልቻለ በመጀመሪያው ወራት ኃይለማርያም የገባበትን ቅርቃር ሰተት ብሎ ይገባል። እናም ጊዜ ሳያጠፋ በይፋ ለህዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ ክላስተሮቹን ማፍረስ ይኖርበታል። አባይ ፀሀዬን፣ በረከትን፣ ስዩም መስፍንን፣ አርከበ እቁባይን በጡረታ መሸኘት አለበት።
***

  1. የካቢኔ ለውጥ ይኖራል ወይ?

የካቢኔ ለውጥ ይኑር አይኑር የሚለው አጀንዳ አዲስ መጨቃጨቂያ ሆኖ ብቅ ብሏል። ህውሓቶች ባጠቃላይ፣ ብአዴን ውስጥ የበረከት ኔትወርክና የሽፈራው ሽጉጤ ክሊኮች በአንድ መስመር ተሰልፈዋል። እነዚህ ሀይሎች ክፍተት የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ በመሆኑ አዲስ ካቢኔ መኖር የለበትም የሚል አቋም ወስደዋል። ህውሓት በደብረጺዬን ምትክ ከህውሓት ስራ አስፈፃሚ ይመድባል በሚል ግልፅ አድርገዋል።

ከላይ የተጠቀሱት ሕውሓቶችና ተላላኪዎቻቸው የያዙት አቋም “ አዲስ ካቢኔ የሚደራጅ ከሆነ እንኳን ስልጣኑ የብሔራዊ እና አጋር ድርጅቶቹ ነው” የሚል ነው።የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን የሰጠነውን ተቀብሎ ስምሪት መስጠት ብቻ ነው እስከማለት ደርሰዋል። በተለይ በበረኸት የሚመራው ብአዴን ከህውሓት በላይ ህውሓት የሆኑትን ጌታቸው አምባዬ፣ ከበደ ጫኔ፣ አለምነው መኮንን፣ ዶክተር ጥላዬ ጌቱ፣ አቶ አህመድ አብተውን ለሚኒስትርነት በፊት መስመር አሰልፏል። ሽፈራው ሽጉጤም ራሱን ጨምሮ ከዶክተር አቢይ ጋር አይንና ናጫ የሆኑትን ሲራጅ ፈርጌሳ፣ ሞፈሪያት ካሚል፣ ተስፋዬ በጅጋ፣አሰፋ አቢዩና ተክለ ወልድን ማሰለፋ እየተነገረ ነው።

መጨረሻው ምን ይሆናል? ከዶክተር አቢይ አቅም በላይ ነው? በፍፁም! የማያቋርጥ የህዝብ ትግል እስከቀጠለ ድረስ! በተጨማሪም ትልቅ የሚያስብ በመሆኑ።

…//…

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.