የቸርነት አንበል። (ሥርጉተ ሥላሴ …የሳተናው አምደኛ)

ከሥርጉተ ሥላሴ 09.04.2018 (ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።)

„አምላካችን መጠጊያችንና ሃይላችን፤ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው።“ (መዝሙር ፵፭ ቁጥር ፩)

  • መነሻ።

https://www.youtube.com/watch?v=tg9U4fMMNfU

„Ethiopia: ጆሲ በፋሲካ በዓል ከቤታቸው ተፈናቀሉ ዜጎች ያደረገላቸው“

  • የቸርነት አንበሉ ወጣት ድምጽ፤

„ተጣልተን ከኖርንበት ጊዜ በፍቅር የኖርንበት ጊዜ ይበልጣል። ኢትጵያዊነት መልካምነት። እኛ ኢትዮጵውያን ፈጣሪ ሰውን ሲፈጠር አብረን ተፈጥረናል። ለዚህ ምስክሩም ከአንድ አባት እናት ተወልደን እንኳን ቀለማችን ይለያያል። በፍቅር አብረን እንኖራለን!“

  • እንዲህም ሆነ …

ልክ በእኛ በሲዊዝ ሰዓት አቆጣጠር 22.18 ነው። ክምሽቱ 4 ሰዓት ከአስራ ስምንት ደቂቃ። „እጬጌ ሂደትን“ ወግ ቢጤ ጹሑፍ ጨርሼ ለማከብረው ለሳተናው ቀድሜ ከተወሰነ ደቂቃ በፊት ልኬለታለሁኝ። ሰውነቴ ስለዛለ ለቅለቅ አልኩኝ። ሻማዬን አብርቼ የተለመደውን አደረስኩ። አንቅልፌን ለማባባል ጋዳም ብዬ ከመተኛቴ በፊትም እናት ሐገሬ ልዕልት ኢትዮጵያ እንዴት ዋልሽ፤ አመሸሽ ለማለት ቴሌቬዢኔን ከፍቼ ዩቱብ ሳይ መጀመሪያ ጅጅጋ ላይ ለብሄራዊ ሰንደቃችን የተሰጠውን ታላቅ ክብር በኢትጵያ የመወድስ የክብር ሙዚቃ ተቀነባባሮ አዳመጥኩኝ።

„ለቀላሃ የምናውለውን መዋለ ንዋይ ለራሃባችን ማስታገሻ እናውለው“ የሚል የጠ/ ሚር ዶር አብይ አህመድ መሪ ዕድምታ አዳመጥኩኝ። ቸር ወሬ ነው አልኩኝ። ተመስገን ብዬ ያን ጨርሼ ሌሎችን ሳይ ከልቤ የሚገባ አላገኘሁም። የኔ ውድ ቅኖቹ የወንዜ ልጆች እንደነገርኳችሁ አሉታዊ ነገሮችን ማደመጥን አልፈቅድም ዛሬ … ዛሬ። ለምን እምቅ ሃብቴን ላቃጥል ፈቅጄ። ፍለጋዬን ስቀጥል የጆሲን የፋሲካ ውሎ ላይ ዓይኔ አረፈ። መልካምነት የማይበት ወጣት ስለሆነ እስቲ ዛሬስ በዕለ ትንሳኤን ምን ሰንቀሃል አንተ ብሩክ ወጣት፤ ምን ከእጅህ ስል ርህርህናን እናትነትን አገኘሁት።

መተኛት አልቻልኩም። ወስጤ በቃ ሌላ ሆነ። ቢያንስ ይህን ቅን ድምጽ ላመስግነው። ተባረክልኝ ልበለው። ብሩክ ቅዱስ ሁንልኝ ብዬ ውስጤን ልግለጽለት ብዬ ጥፍትፍት ያደረጉትን ኮንፒተሬን እንደገና አስነስቼ ኮለምኩኝ።

ይህ እናት ሆዱ ወጣት እንደሚለው የምርት ሆነ የገበያ ሂደቱ በመቀዛቀዙ የተነሳ ሊያስተባብር የፈለገውን ያህል እንዳለገኝ ነበር የገለጸው። ለእኔ ግን የኔ እናት አይናቸውን ሄደህ ማዬትህ ከሚሊዮን ቁስ በላይ ነው። እቅፍ አድርገህ ስትገናኘቸው፤ አለሁላችሁ ስትላቸው፤ ራሱ ወገን አለን። ዜጋ ነን። ሐገር አለን ይላሉ። የሁላችንም ድርሻ ነው የከወንከው። የአራስ እህቶች እንግልት ነገን ኢትዮጵያን በማንኛውም ሁኔታ የሚረከቧት ህፃናትም ወደዚህች ምድር ሲመጡ በቀያቸው በድህነት ለመኖር እንኳን ሳይፈቀድላቸው ቀርቶ በሐገር ውስጥ ሌላ የስደት ሥጦታ ቀርቦላቸዋል።

የእኔ ብሩክ ወጣት ታናሼ አቶ ዮሴፍ ይህን መከራ መጋራት በራሱ ከበቂ በላይ ነው። ዓይን ለዓይን መተያዬታችሁ። መንፈስ ለመንፈስ መገናኘታችሁ። ውስጥ ለውስጥ መተሳሰራችሁ ከበቂ በላይ ነው። እኛም እኮ ውስጣችን አዬናቸው። በዚህ የመከራ ቀን ተገኝተህ ለዛውም ከጮማ፤ ከውስኪ፤ ከልብስ ምርጫ ከሁሉም ያልታደሉትን ምንዱባን የእኔ ብለህ ትንሳኤን ከእነሱ ጋር ለማሳለፍ መሄድህ በራሱ ታላቅ ጸጋ ነው። ሃሳቡ ራሱ ሰማዕትነት ነው። „ነገር ሁሉ ለበጎ ነው“ የፈጣሪን ቃል በመግለጽ አጽናንተሃቸዋል።አዎን አንተንም ፈጣሪ አምላክ ለኢትዮጵያ ሲሰጥ ለበጎ እና ለመልካም ተልዕኮ ነው። መልካም ስጦታችን ነህ። በቆሼ አደጋ ጊዜም ያደረከውን አዳምጫለሁኝ፤ ከኢትጵያ ወጣት ፖለቲከኛ አምስግኖ ስለጸፋው ብቻ ነው ዝም ያልኩት።

በጭንቅ ጊዜ ከመገኘት በላይ ምን የህሊና ሰላም አለና? ከዚህ በላይስ ምን የጽድቅ መንገድ አለና? መፆምም፤ መስገድም እኮ ከዚህ በላይ የዋጋ ብልጫ የለውም። ለዛውም በቸገረ እና መድረሻ በታጣ ጊዜ አለኋዋችሁ አይዟችሁ ህይወት ነው። አጽናኝ መንፈስህ በስንት ማይል ርቆ እኔም ዳስሶኛል። ድክም ባለኝ ሰዓት ስለሆነ ብዙ ልል በፈቀድኩኝ፤ ባሳድረው ውስጤ የተሰማኝን ልገልጸው የማልችለው፤ ላብራራው የማልችለው፤ ልተረጉመው ያምልችለው ስሜቴ ይደንዝዝብኛል። ይቆረፍዳልም። አንቅልፉም ሰላማዊ አይሆንም። እንዴት ብዬ ልግለጽልህ ሆደ ባሻ ስለሆንኩኝ ተረባበሽኩኝ። ይህን ሁሉ ሰቀቀን ስትመለከት ከእስር የተፈቱትን የነፃነት አረበኞች ወጣትነታቸውን የሚገብሩለት ነፃነት እና የሰውነታቸውን መገርጣት ስትመለከት የእነ አቶ አንዱአለም አራጌ፤ የእነ ጋዜጠኛ አስክንድር ነጋ እንደዛ ብለው አጽማቸው ብቻ ቀርቶ ስታይ ይከብዳል። ተሜ እኮ ሽበት ወሮታል ወጣትነቱን መከራው በላው። ዕውነት ለመናገር እኔ አሁን አሁንስ አቅም እያነሰኝ መጣ። … እምጽናነው እንዲህ ለመልካም ነገር የምትተጉ ወጣቶች በመኖራችሁ ብቻ ነው። አሁን አሁን የነፃነት አርበኞቼን ገጽ ላለማዬት ሽሽት ጀምሬያለሁ። በሐገር ላይ ይህን ያህል ሰቆቃ፤ ይህን ያህል መከራ፤ ይህን ያክል ዕንባ … ዘር አያበርክትም። ነገ ያስፈራኝል ፈሪ ነኝ እና ….

ለዚህች ደሃ ሐገር ያልን ወዘተረፈ ችግር ላይበቃ በራስ የታቀደ ችግር እያመረቱ ሰውን ያህል ታልቅ ፍጡር እንዲህ የስቃይ መጫወቻ ሲሆን ያሳዝናል ብቻ ሳይሆን የደም እንባ ማህጸን ያነባል። የእርግማን ነው። ዲያቢሎሳዊም ነው። በቃችሁ ይበለን ፈጣሪያችን። አሜን። ይህ የመከራችን ሁሉ መጨረሻ፤ የፍዳችን ሁሉ መደመምደሚያ ዘመን ያድርግልን ፈጣሪ አምላክ። አሜን።

ሁሉንም ሂደቱን ቤተ እግዚአብሄር ያለሁ እስኪመስለኝ ድረስ ነበር የተከታተልኩት። የከንከው መንፈሳዊ ተግባር ለእኔ ቃለ ወንጌል ነው። ለእኔ ቃለ ህይወት ነው። ለወጣቶች እኮ ዛሬ ታላቅ ት/ ቤት ከፍተሃል። ቸርነት የሚባል። ደግነት የሚባል። ርህርህና የሚባል። መከራን መጋራት የሚባል። የራስን የፍሰሃ ቀን ለሌለው ደስታ የማወል መክሊት።

እዛው ካሉት ወጣቶች „የልጅና የጢስ መውጫው አይታወቅም“ የሚለው ብሂል ያለምክንያት አበው/ እመው ይሉት አልነበረም። መሪም፤ እጬጌም፤ ሃጅም / ሸህም ሊፈጠር/ ልትፈጠረ ትችላለች – ይችላል። ጊዜ ታሪክን ይሠራል። አጋሮ አንድ ታላቅ አንደበቱ የሚናፈቅ መሪ ይወጣባታል ተብሎ አይታሰብም ነበር። ቀዳማዊ እምቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸውም ትውልድ ሥፍራቸውን ባለውቀውም እንዲሁ የዚህ ዕድል ተቋዳሽ ይሆናሉ ተብሎ አልታቀደም ነበር። እርግጥ ነው ሥማቸው መልዕክትም ጥሪም አለበት። የቤተ መንግሥት ቆይታቸውን የመልካም ነገሮች፤ የመልካም ምግባር ዝና መጠሪያ፤ የርህርህና፤ የቸርነት እና የመሆን ያድርግላቸው ፈጣሪዬ። አሜን! ዕንባው አደከመን ከምል ጨረሰን ብል ይሻለኛል። ደከመኝ። በዛብንም። ሰው ከሚችለው በላይ ጭንቁ ገደለን።

የሆነ ሆኖ ዛሬ አንተ ብሩክ፤ አንተ የደግነት ብርሃን። የሰረሃው መልካም ሥራ ለሐገርም፤ ለትውልድም የመፍትሄ አመንጪ የሚሆን/ የምትሆን ሳይንቲስት/ ፈለሳፋ/ ተመራማሪ ከዚህ መንፈስ ውስጥ ነገ ሊፈጠር ይችላል። ማን አውቃል ማግስት የፈጣሪው ነው። ስለሆነም የእናት ሐገርህን የልዕልት ኢትጵያን የተስፋ ራዕይ አደራ ነው በትክክል የፈጸምከው። ተባረክ። እሾኽ አሜኬላ አይንካህ። ድንግልዬ ትጠበቅህ። ኑርልን የእኛ የደግነት አብነት።

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!

የኔዎቹ – ቅኖቹ አብራችሁኝ ስለነባራችሁ ኑሩልኝን ልሸልም። ከዚህ የቸርነት አንበል መንፈስ ጋርም ለመዝለቅ ትፈቅዳላችሁ ብዬም አስባለሁኝ – ቸርነትን የሰነቀ መኖር ጀምሮታል።

እግዚአብሄር ይስጥልኝ። መሸቢያ ጊዜ።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.