ይህቺ ናት ጫዋታ (ከእውነቱ ፈረደ)

የኢትዮጵያ ህዝብ የጠየቀው የጉልቻ መቀያየር ሳይሆን የወጡን መጣፈጥ ነው።ለመሆኑ ኢህአደግን በኢህአደግ ምን የሚሉት ለውጥ ነው? ኢህአደግ ሰው አይደለም። አንድን የፖለቲካ ስረዐት ያዋቀረና የሚመራ በሰዎች በድርጅቶች የተደራጀ ማዕከል ነው።ይህ ማዕከል የራሱ የሆነ የፖለቲካ ፍልስፍና አለው። ይህም በዘርና በቋንቋ ላይ የተመሰረተ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚሉት ርዕዮተ ዐለም ነው። ይህንን  አመለካከት በኢትዮጵያና በህዝቧ ላይ ተገባራዊ ለማድረግ በማዕከሉ ፍልስፍና የተቀረጸ ህገ መንግሥት አለው። ህገ መነግስቱ ኢትዮጵያ፤ የኢትዮጵያውያን መሆኗን የሚክድና ማንም ሰው በዘር በሀረጉ ካልመጣ በስተቀር አገር አይኖረዉም ብሎ የሚደነግግ ነው።ሉአላዊነትም የሚያርፈዉ በብሄር ብሄረሰብ ላይነዉ። ኢህአደጎች ሲፈልጉ የሚገነጣጥሏት አለያም በእስረኛነት የያዟት ኢትዮጵያን እየገዙ ነው።

ለዚህ ነው የህዝቡም ትግል መሰዋዕትነትም የሚከፈለው ኢትዮጵያንና ህዝቧን ከእሥር ለማስፈታት ነዉ የምንለዉ። ይህ ደገሞ ሊከናውን የሚችለው የችግሮቻችንና የመታሰራችን መንሰዔ የሆነው ኢህአዴግ ሲነሳ፤ ህገመንግስቱ ሲታገድና በህዝባዊ ህገ መንግሥት ሲቀየር እንጂ የሐይለማርያም ወንበር ከአንድኛው ኢሃአዴግ አባል ድርጀት ወድሌላው መቀያየሩ አይደለም።

በሰሞኑ የኢሃዴግ ሊቀመንበር-የጠቅላይ ሚኒስቴር እጩ ምርጫ የታየው ትርኢት እንዳያስተዛዝበን እሰጋለሁ። የተመረጠው የኢሃዴግ ሊቀመንበር ነው እየተባለ ከኢህአዴግ ውጭ አድርጎ ማየት ምን ማለት ነው? እውነትን በውሸት ሣይሸፍኑ ማየት ለምን ይሳናችኋል? ወይስ የደበቃችሁት ጉዳይ ቢኖር ነውን?

ተመራጩን ነጥለን ማየት የምንችለዉ (እንደምትሉት ሊሆን የሚችለዉ)  ኢህአዴግ ግለሰብ እንጂ ድርጅት አይደለም በማለት ማሳመን ከቻላችሁ ብቻ ነዉ። ይህስ ይቻላልን?

አንዳንዶች ደግሞ የተመረጠው የኦሮሚያው አብይ ሣይሆን የኢትዮጵያው አብይ ነው ይሉናል። ሌሎች ደገሞ ጊዜ ልንሰጠው ይገባል ይሉናል። ለመሆኑ ማን ለማን ነው ጊዜ የሚሰጠው? የኢትዮጵያ ህዝብ ከደረሰበት ግፍና በደል አንጻር የቀረው የሚሰጠው ጊዜ አለን? ጊዜያቸውን ያሟጠጡት መንግስት ነኝ ባዩ ኢህአዴግ ሆኖ እያለ እነርሱኑ በቃችሁ አስተዳደሩን ለህዝብ ልቀቁ ማለት ሲገባ ጊዜ እንስጣቸው ማለት ትርጉም አልባ ነው። ኢህአዴግ መልኩን እይቀያየረ ይግዛን የሚለው አዘናጊና ትጥቅ አስፈቺ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባርና የመሰሎቻቸው መፈክር ምን የሚሉት የፖለቲካ ሥልት ነው? ጌቶች ባጠፉ ምስኪኑ ደሀ ይገረፍ የጌታውን እዳ ይክፈል ለምን እንላለን።ይህስ እሳቤ አዋቂነት ወይስ የፖለቲካ ድህነት? እንደ እውነቱ ከሆነ የፖለቲካ ድህነት አለያም መሰሪነት ነው።በሚገባ እንተዋወቃለን እኮ! ኤርትራን ማን አስገነጠለ? አንቀጽ 39ኝን አንግቦ የሚጓዘው ፀረ እትዮጵያን ሕገ መንግሥት ማን አወጣው? ማንስ ተገባራዊ አደረገው? እውነት ተሰውሮ መኖር አይቻልምና እየተስተዋሉ መጛዙ የሚበጅ ይመስለኞል።ታሪኳን ማንነቷን የካድዋት በቀጥታ ቋንቛ ለምን ኢትዮጵያን ይቅርታ መጠየቅ ተሳናቸዉ።መነሻ መግባቢያ ይህ ነዉና።ብሔራዊ መግባባትም ከዚህ እዉነታ ይጀምራል።

አስቲ ክዚህ በታች የተፃፈውን የሁለት ሀሣቦች ውይይት ተመልከቱ። በፈረስ ጋሪ ዘመን ክህብረተሰቡ ለሁለቱ ሓሣቦች የቀረበ፤

ጥያቄ

  • ከፍጥነት አንፃር፣ ብዙ ሰዎችን ባንድ ጊዜ ባንድ ላይ ከመጓጓዝ አንፃር፣ እንዲሁም ከምቾት አንፃር ፣ፈረስና የፈረስ ጋሪ የትራንስፖርት ፍላጎታችንን ሊያሟሉ አልቻሉምና መፈትሄ ትፈልጉልን ዘንድ ማልደን መጥተናል በማለት ጥያቄያቸውን በትህትና አቀረቡ።

መልስ

  • ሀሣብ አንድ ! ጥያቄያችሁ ወይም ችግሮቻችሁ በእውነትም መፍትሔ ሊያገኙ ይገባል። ቀላል ጥያቄ ነው ። መፍትሔው በጉልበታቸው በሰውነታቸው አቋም የተሻሉ ፈረሶችን በመጠቆምና የሚጎትቷቸውን ሠረገላዎች ክብደት በመቀነስ ፈረሶቹ ፍጥነት እንዲጨምሩ ማድረግ ይቻላል።
  • ሀሣብ ሁለት! የወንድሜ የሀሣብ አንድ፣ መፍትሄ በጆሮ ሲደመጥ መፍትሄ ይመስላል። በዕርግጥ የተወሰነ ግን ዘለቄታ የሌለው (ፈረሶች መድከማቸው አይቀርምና) ለውጥ ሊመጣ ይችላል። ይህብረተሰባችን ጥያቄ ግን ፍጥነት ብቻ ሣይሆን ሌሎችንም ያካተተ ባለብዙ ፈርጅ ከመሆኑም በላይ ዘለቄታዊ መፍትሄ የሚሻ በመሆኑ ያንተ መልስ ልክም አጥጋቢም አይደለም ይለውና የራሱን መፍትሄ እንዲህ ሲል ይገልፃል። ፈረስ ከመቀየር ይልቅ ሞተር ብንፈለስፍና የሞተር ጉልበት ለፍጥነት እንዲሁም ተስማሚ አካልና ጋቢና ብንገጥምለት ለምቾቱና ብዙ ተሳፋሪ ለመጫን እንችላለን ሲል ሀሣቡን ደመደመ። (ይህ የክርክር ሀሳብ የሄነሪ ፎርድ ንግግርን መሠረት በማድረግ የተረኩት ነዉ)

እንግዲህ ይህ ሀሣብ ሲተነተን ፤

የመጀመሪያው ሀሣብ ችግርን በራሱ መፍትሄ አድርጎ ተነሣ፤የችግር አካል የሆነውን አነስትኛ መቀባባት ካደረገበት በኋላ ራሱን እንደመፍትሄ አካል ቆጠረው። የይዘት ለውጥ ጥያቄን በቅርጽ ለውጥ ሸፍኖ ተመለከተው።

ሀሣብ ሁለት ግን  መፈትሄ ለማግኘት ክችግሩ ሣጥን ውስጥ ወጣና ፈጠራማ በሆነ አስተሣሰብ ላይ በመመርኮዝ መፍትሄ ማፈላለግ ጀመረ።

ታዲያ! በጎና ትክክል ሆኖ የተገኘው  የቱ ነው? የ21ኛው ዘመንን ሥልጣኔ በመመርመር የሀሣብ ሁለት መፍትሄ ትክክል እንደነበር በአለም ተገለጸ።

ለነገሩ የሀሣብ አንድ አስተሳሰብ  እኮ ውሀ ቢወቅጡት ያው እንቦጭ ነው ከሚለው ይዘል ይሆን?

እስቲ ተጠየቁ!

በንጉሱ ዘመን፤ ለእንዳልካቸው መኮንን ጊዜ እንሰጠው ቢባል እምቢ፡ አይሆንም፤ እኛ የምንታገለው ለመሰረታዊ ለውጥ ነው በሚል አሻፈረኝ አልን።

ሐይለማሪያም ሲመጣ ከህወሀት/ኢህአዴግ የተሠራ ኢህአዴግ ነውና መሠረታዊ ለውጥ ስለማያመጣ አይሆንም አልን።

ታዲያ! እንዴት ሆኖ ነው አብይ ምንም ዐይነት የፖለቲካ ፍልስፍናና የርዮት ዐለም  ይዘት ለውጥ ለማምጣት ሲታገል ያልታየ፤ ከኢሀአዴግነት በስተቀር ሌላነት ያልታየበትን የለውጥ ሐዋሪያ ነው! የለውጥ ግፊት ያመጣው ነው! (የህዝቡ ትግል ሌላ የኢህአዴግ የሥልጣን ግብግብ ሌላ! ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ) እየተባለ ጊዜ እንስጠው፤እንደግፈው የሚለውን ጩኧትን መሰማትና ከበሮ መደለቅ የተጀመረው? እንግዲህ ይህ ዓይነቱ ዳኝነት በምን ይፈረጃል? ከዘር ዘርን ማበላለጥ ወይስ ቤተሰብነት?

ይህን በጥሞና በማሰላሰል ከጠባብነትና ከጎሰኛነት በመውጣት ለማሰብ ከሞከርን ለመልሱ መቃረባችን አይቀረምና ማስተዋል ይስጠን ።

ማጠቃለያ

ኢትዮጵያውያኖች ካገራችን ሕዝብ ውስጥ የፖለቲካ አሳቢና ጀግና መሪ  የሌለ ይመስል፤ ኢህአዴግን ብቻ ለምን እናመልካለን። ይህ መቆም አለበት። ይህ አምልኮ፤ ኢህአዴግ ደግሞ አክቲቪስት ነን፤ የደረጅት መሪዎች ነን አዋቂ ምሁር ነን ከሚሉ አፍ ሲወጣ እጅግ ይዘገንናል።

 

“ጉልቻ ቢለዋዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም የሚለው ምሳሌ እንዳይፈርድባችሁ!”

አደራ! አደራ!አደራ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.