ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠልፈው እንዳይወድቁ ሕገ መንግሥቱን ይታጠቁ! (አስራት አብርሃም)

ዶ/ር ዓቢይ አህመድ ከአሁን በፊት ከነበሩት የኢትዮጵያ መሪዎች የተለየ ስኬት ማስመዝገብ የሚፈልጉ ከሆነ እዚህ አገር ላይ ሕገ መንግስታዊ መሰረት ያለው ተቋማዊ አሰራር ነው መትከል ያለባቸው። እንዲህ ዓይነቱን የአሰራር እንዳይኖር ቀዳሚው እንቅፋት የሚሆነው ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የሚባለው ልማዳዊው የኢህአዴግ አሰራር ነው። ይህ አሰራር ምንም ዓይነት ህገ መንግስታዊ መሰረት የሌለው ከመሆኑም ባሻገር፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር እንዳይሰፍን በማድረግ በኩል አሉታዊ የሆነ አስተዋፅኦ ሲጫወት የነበረ ነው። ስለዚህ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲህ ዓይነቱን የለውጥ ማነቆ ለማለፍ ሕገ መንግስቱን በቀዳሚ ጋሻነት መጠቀም ይኖርባቸዋል። ይህም አንደኛ ህገ መንግስቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰጠውን ስልጣንና ተግባር እስከጥግ ድረስ ወስዶ በአግባቡ ሙሉ ለሙሉ መጠቀም ነው።

በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 70 ስር ከተጠቀሱት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጡት ተግባራት አንዱ በቁጥር 13 ላይ የተቀመጠው ሕገ መንግስቱን ማክበርና ማስከበር ቀዳሚው ነው። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማነኛውም ሁኔታ ፀረ ህገ መንግስታዊ የሆኑ አሰራሮች እንዲያስፈፅሙ አይገደዱም ማለት ነው። ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ደግሞ ፀረ ሕገ መንግስት ነው። ምክንያቱም ሕገ መንግስቱ የመንግስትን አሰራር እንዴት እንደሚካሄድ በግልፅና በዝርዝር ያስቀመጠ በመሆኑ ነው። ለምሳሌ የፓርላማ አባላት ተጠሪነታቸው ለሕገ መንግስቱ፣ ለመረጣቸው ህዝብና ለህሊናቸው እንደሆነ በግልፅ ተደንጓጓል። ስለዚህ በጓሮ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ውሳኔ እንዲያፀድቁ ብቻ የሚደረገው አሰራር ሕገ መንግስታዊ አይደለም ማለት ነው። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህን ፀረ ሕገ መንግስት የሆነን አሰራር የሚያስቀጥሉ ከሆነ በቀላሉ ተጠልፈው የሚወድቁበትና የሚከሽፉበት ሁኔታ ነው የሚፈጠረው። በቀላሉም በነባሮቹ የኢህአዴግ አመራሮች ተፅዕኖ ሥር እንዲወድቁ ይሆናሉ። እኔ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህን አልመኝላቸውም።

እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ቁም ነገር ስልጣን ለማይገባቸው አካላት ማካፈል ኢህገመንግስታዊ መሆኑ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕገ መንግስቱ የሚሰጣቸው ስልጣንና ተግባር ለመፈፀም አስፈላጊ መስሎ ከታያቸው የሌሎችን ሰዎች ወይም አመራሮች ምክር ሊጠይቁ ይችላሉ። በጉዳዩ ላይ ውይይት እንዲደረግበት የኢህአዴግን ስራ አስፈፃሚም ጠርተው ሊያወያዩ ይችላሉ፤ የመጨረሻውን ውሳኔ ማሳለፍ ያለባቸው ግን ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናችው። በተቃራኒው ግን ለትንሹም ለትልቁም ውሳኔ የኢህአዴግን ስራ አስፈፃሚ ለስብሰባ የሚጠሩ ከሆነ የሚፈለገውን ፈጣን ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም ብቻ ሳይሆን፣ ለስራ ይውል የነበረው ውድ ጊዜም ጭምር በስብሰባ እንዲባክን ማድረግ ነው የሚሆነው። በስብሰባ የእኛ አገር ችግሮች የሚፈቱ ቢሆን ኖሮ ባለፉት 27 ዓመታት ያደረግናቸው ስብሰባዎች ከዓለም አንደኛ ስኬታማ ህዝቦች ያደርገን ነበር። እዚህ አገር ኢህአዴግ ስብሰባ ማደንዘዛ አድርጎታል። በሽታ ሆነዋል። የአገር በሽታ ደግሞ በሌላ በሽታ ሊታከም አይችለም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተሰጣቸው የስልጣን ማዕቀፍ ውጭ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ደግሞ በቀጥታ ፓርላማው ላይ በማቅረብ ማወያየትና ውሳኔ ማሰጠት ይችላሉ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስኬት ከሚለካባቸው መንገዶች አንዱ ልማዳዊውን የኢህአዴግ አሰራር በሕገ መንግስታዊ አሰራር የመተካት ብቃታቸው ነው። በሕገ መንግስቱ መሰረት አልሄድም ወይም አልሰራም የሚል ግለሰብ ወይም ቡድን ካለ ደግሞ ጉዳዩ በይፋ ለህዝብ እንዲገለፅ በማድረግ ከመንግስታዊ ሃላፊነቱ ገለል እንዲሉ ማድረግ ነው። ሁለተኛው የነባር አሰራር ተፅዕኖ ማስወገጃ መንገድ ደግሞ ሕገ መንግስቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰጠው የራሱን የሚኒስትሮች ካብኔ የማቋቋም ስልጣን በአግባቡ መጠቀም ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት ከሁለቱም ምክር ቤቶች አባላት ወይም ለስራው ብቃት ካላቸው ሌሎች ግለሰቦች መካከል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በእጩነት አቅርቦ ሹመታቸውን ማፀደቅ እንደሚችሉ ተደንግጓል። ይህ አንቀፅ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከዚህ በፊት የተሾሙትን ሚኒስትሮች በግድ ይዘው ለመሄድ እንዳይገደዱ የሚያደርግ ነው። ስለዚህ ይህ ድንጋጌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአዲሱ ህገ መንግስታዊ አሰራር ጋር አብሮ መሄድ የማይችሉትን ሚኒስትሮች በሌላ ለቦታው ተስማሚ በሆኑ ሚኒስትሮች ለመተካት የሚያስችል ነው። እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚኒስትሮች ውጭ የሆኑ ከፍተኛ የመንግስት ሲቪል ሽሞቶች መስጠት ስለሚችል፣ በዙሪያቸው ሊኖሩ የሚችሉ አማካሪዎችና ሌሎች ወሳኝ የሆኑ የመንግስት ሽሞቶች ለቦታው የሚመጥኑ ብቃት ባላቸው፣ ከለውጡ ጋር ለመጓዝ ወይም ለውጡን ለማፋጠር ፍላጎቱንና ድፍረቱን ባላቸውን ሰዎች በመተካት ለውጡን በአስተማማኝ ሃዲድ ላይ እንዲጓዝ ማድረግ ይቻላል።

ሌላው ደግሞ የህዝቡን ድጋፍ ለማግኘት እንዲቻል የሚሰሩ ሥራዎች ሁሉ በቀጥታ በሚዲያ መገለፅና ወደ ህዝቡ እንዲደርሱ መደረግ መቻል አለባቸው። የሚያጋጥሙ ችግሮችም ካሉ እንደዚሁ አፍኖ ከመያዝ ይልቅ በይፋ ለህዝብ እንዲቀርቡ በማድረግ ህዝባዊ ድጋፉ ማስቀጠልና አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዲኖረው ማድረግ ይቻላል። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝቡ ጋር በቀጥታ የሚገናኙበት የሚዲያ ማዕቀፍ ማበጀት አስፈላጊ ይሆናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በኢህአዴግ ውስጥ ያለው ከህዝብ አገልጋይነት ያፈነገጠ መንፈስ መታገል ያስፈልጋል። የፓርቲ አባልነትን የግል ጥቅም ማግኛ ዘዴ አድርገው የሚያዩ፣ የተጧሪነት መንፈስ ያላቸው የኢህአዴግ አመራሮችና አባላት ከመንግስታዊ ተቋማት ከላይ እስከታች እንዲወገዱ ወይም በተሻለ የሰው ኃይል እንዲተኩ ማድረግ ያስፈልጋል። ነገርዬው ጠቅለል አድርገን ስንረዳው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህ ማነቆዎች ደረጃ በደረጃ መሻገር የሚችሉት ሕገ መንግስታዊ አሰራሩን በቁርጠኝነት ለማስፈን የተነሱ እንደሆነ ነው።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢያንስ ከላይ የተዘረዘሩትን ለውጦች ለመተግበር ቁርጠኝነት የሚያንሳቸው ከሆነ ግን እንደተከበሩ፣ በህዝብ እንደተወደዱ በፍቀዳቸው አልቻልኩም ብለው ቢወርዱ ነው የሚሻላቸው። ምክንያቱም በአገሪቱ ላይ የተከማቹ ችግሮች እጅግ በጣም ብዙ እንደመሆናቸው መጠን፣ እንዚህ ቀላል የሆኑ ለውጦች እንኳ ለማድረግ ቆራጥ እርምጃ ለመውሰድ ያልቻለ መሪ፣ ከዚህ ባሻገር የሆኑ፣ እንዲተገበሩ የሚጠበቁ፣ ለምሳሌ የህገ መንግስት ማሻሽያ፣ የፌዴራል ስርዓቱን የተሻለ እንዲሆን የማድረጉ ነገር፣ የኢኮኖሚ ለውጥና ሽግግር፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትህ የማስፈኑና ሙስናን የመዋጋቱ ነገር የማይታሰብ እንዲሆን ነው የሚያደርገው። ለእነዚህ ነገሮች የመጀመሪያ መሰረት፣ የውሀ ልክ ሆኖ ሊያገለግል የሚችለው ህገ መንግስታዊ አሰራር ማስፈን ነው። ሌሎች ነገሮች በዚሁ፣ በህገ መንግስታዊነት ላይ ነው የሚገነቡ ናቸው።

ስኬትና መልካም የስራ ዘመን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ እመኛለሁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.