ኦሮምኛን በግእዝ መጻፉ ቋንቋውን ያሳድገዋል፣ ላቲን ግን ያቀጭጨዋል  (አብርሃም ቀጄላ)

ይህ ጽሑፍ “ምሁራን/አክቲቪስቶች ኦሮምኛ በአማራ ክልል በግእዝ ፊደል እንደ ትምህርት እንዲሰጥ ጠየቁ።” በሚል ርዕስ –  https://www.satenaw.com/amharic/archives/52224
መቅረቡ ይታወሳል። ዳንኤል አበራ የሚባሉ ኣንባቢ ኦሮምኛን በግዕዝ በዐማራ ክልልግብረመልስ ለምሑራኑ ስብስብ እና ግርማ ካሳ  https://www.satenaw.com/amharic/archives/53342

ኣጓዳኝ ለጠየቁት 6 ጥያቄዎቹ መልሶች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

በአማራ ክልል ኦሮምኛን በግእዝ በማስተማር ዙሪያ፣ አቶ ግርማ ካሳን ጨምሮ የተወሰንን ምሁራንና አክቲቪስቶች ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ደብዳቤ ጽፈናል። ደብዳቤውን በመመርኮዝ የቀድሞ የኢሕአዴሪ ፕሬዘዳንት ግርማ ወልዲጊዮርጊስ ቀድሞውኑ ኦሮምኛ በላቲን መጻፍ አልነበረበት በሚል ለአማራ ክልል የተጻፈውን ደብዳቤ ደግፈዋል። ፕሪዘዳንት ግርማ ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ማእዘናት የሚሰጡ አስተያየቶች አብዛኛው የድጋፍ ናቸው። ሆኖም የተወሰኑ ወገኖች አሉታዊ አስተያየት ሰጥተዋል።ያም የሚጠበቅ ነው። ለምን በአንድ ነገር ላይ ሁሉም ሰው መቶ በመቶ ይስማማል ማለት አስቸጋሪ ስለሆነ።

የአማራ ብሄረተኛ ጋዜጠኛ አያሌው መንበር በጽሁፉ ላቀርባቸው አሥራ ሶስት ነጥቦች «በአማራ ክልል ኦሮሞኛ መሰጠት የለበትም የሚሉ በስሜት ሳይሆን በመረጃ ይከራከሩን» ሲሉ አቶ ግርማ ካሳ ምላሽ ሰጥተዋል። “ኦሮምኛን በግዕዝ በዐማራ ክልል – ግብረ-መልስ ለምሑራኑ ስብስብ እና ግርማ ካሳ” በሚል ርእስ ደግሞ ስድስት ነጥቦችን በማስቀመጥ ሌላ ኢትዮጵያው አስተያየት ሰጥተዋል። አቶ ዳንኢል አበራ ይባላሉ።

አቶ ዳንኤል፣ ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተጻፈውን ጽሁፍ “ለኛ በግልባጭ አራት ጦማሮች በተከታታይ አድርሳችሁናል” ሲሉ ነው ጽሁፋቸው የጀመሩት። ማንኛውም አስተያየት የድጋፍ ሆነ የተቃውሞ የከበረ በመሆኑ፣ የቀረቡ ነጥቦች ዜጎች የበለጠ መረዳት ይኖራቸው ዘንድ የሚከተለውን ምላሽ አቅርቢያለሁ። ይሄን ምላሽ ሳቀርብ ምላሹ የግል አስተያየቴ እንደሆነ አስቀድሜ ለመግለጽ እወዳለሁ።

“ጦር-አውርዱ፣ ኑና እንያችሁ ፉከራው ሲበዛ አጭር መልስ እና ትክክለኛውን መንገድ ለመጠቆም ተከስቻለሁ” ይላሉ አቶ ዳንኤል። ፉከራው፣ ጦሩ ምን ላይ እንደሆነ ባይገባኝም፣ ይመስለኛል ጸሃፊው በኛ የቀረበውን ሐሳብ አንዱን ጠቅሞ ሌላውን ለመጉዳት እንደሆነ አድርገው ያሰቡ መስለኝ። ዜጎች በነጻነት ይጠቅማል የሚሉትን አስተያየት የማቅረብ መብት አላቸው። ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው አስተያየት ሲሰጡ፣ አንድ ዜጋ በሌላ ነገር ከተረጎመው፣ የታዘዘ ከመሰለው፣ የበታችነት ከተሰማው፣ ያ የርሱ ችግር ነው የሚሆነው። እኛ አስተያየት ስናቀርብ ድጋፍ እንዳለው ሁሉ ተቃዉሞ ሊኖር እንደሚችል እናውቃለን። ያንንም እናከብራለን። ተቃውሞው መሰረት ያለው ከሆነ እናስተካከላን፣ ተቃውሞው መሰረት ከሌለው ደግሞ ተቃውሞውን እንደ ተቃውሞ ቆጥረን እናልፈዋለን። አቶ ዳንኤል እኛ የፎከርን ከመሰላቸው ችግሩ ያላቸው እርሳቸው ጋር እንጅ እኛ ጋራ አይመስለኝም።

አቶ ዳንኤል ባቀረቡት ስድስት ነጥቦች ላይ ምላሽ እነሆ፡

  1. አቶ ዳንኤል – ትዛዛዊ ጥያቄአችሁ “ኦሮምኛን በግዕዝ በዐማራ ክልል” ድርብርብ ችግር የነበረው፤ ያለው፤ የሚያስከትል ስለኾነ ፕ/ት ገዱ እና የዐማራ ክልል ከተናጠላዊ እርምጃ እንዲታቀቡ እጠይቃለሁ።

መልስ- በአማራ ክልል ውስጥ ስለሚሆነው ነገር የሚያገባው የክልሉ መንግስትና የክልሉ ሕዝብ ነው። አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በሌላው ክልል “ይሄን ያድርጉ፣ ያንን ያድርጉ ..” የሚል ጥያቄ አይደለም የቀረበው። አቶ ዳንኤል የክልል መንግስትን ነጻነትና መብት መቀበል አለባቸው። በአማራ ክልል ውስጥ ስለሚሆነው ነገር፣ የሶማሌ፣ ወይም፣ የትግራይ ፣ ወይም የኦሮሚያ ክልል ሊወስን አይችልም።

የአማራ ክልል ሕዝብ፣ ከአማርኛና እንግሊዘኛ ቀጥሎ ተጨማሪ ቋንቋ ቢያወቅ ሊጠቅመው ስለሚችል ሶስተኛ ቋንቋ ( አገዉኛ፣ ቅምናትኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግሪኛ ….) እንዲማርና ኦሮምኛ የሚሆን ከሆነ ደግሞ ፊደሉ የአገራችን ቅርስ በሆነው በግእዝ ፊደል እንዲጻፍ ስንጠይቅ፣ እንደ ዜጎች ሐሳባችንን ነው ያቀረብነው። ጥቅሙናን ጉዳቱን አመዛዝኖ የክልል መንግስት ከሕዝብ ጋር በመመካገር የሚወስነው ይሆናል። ያለ ህዝብ ፍላጎት ምንም ነገር መሆን ስለሌለበት፣ ከሆነ ደግሞ የሚከሽፍ በመሆኑ።

አቶ ዳንኤል በአማራ ክልል ኦሮምኛ መስጠቱን አልተቃወሙም። የተቃወሙት በግእዝ መሰጠቱን መሰለኝ። በላቲን እስከሆነ ድረስ በአማራ ክልል ኦሮሞኛ መሰጠቱ ላይ ችግር ያለባቸው አይመስልም። ችግራቸው ግእዙ ላይ ከሆነ፣ ኦሮምኛን በአማራ ክልል በላቲን እንዲማሩ ከፈለጉ፣ እርሳቸው ማሳመን አሰቸጋሪ ነው የሚሆነው። እርሳቸው እንዳሉት ግን ኦሮምኛ በግእዝ ፊደል ማስተማር እንኳን ድርብርብ ችግር ሊፈጥር፣ እንደውም ወደፊት ሊከሰት የሚችልን ችግርን ነው መፍትሔ የሚሰጠው። የላቲን ፊደል የአንድ አገር ዜጎች እንዳይግባቡ ያደረገ ከፋፋይ ፊደል ነው። ይህ ፊደል ላለፊት 27 አመታት በኦሮሚያ ሕዝቡ ሳይወስኑ፣ ያለ ሕዝቡ ፍላጎት፣ በመዘርጋቱ የኦሮሞ ማህበረሰብ በጣም ተጎድቷል። በኦሮሚያ ያሉ ከተሞች በኢኮኖሚ በጣም ወድቀዋል። አፋን ኦሮሞ በግእዝ መጻፉ ግን በሂደት ወደ ኦሮሚያ እንዲቀጥል የሚረዳ ሲሆን፣አገርንና አንድነት የሚያጠናክር አስፈላጊ ጉዳይ ነው።

 

2 አቶ ዳንኤል – በኢትዮጵያ የቅርብ 25 አመት ታሪክ የቋንቋ ጉዳይ ደም አፋሳሽ ንብረት አውዳሚ ነው፤ ለምሳሌ ከደቡብ ወጋጎዳ እንዲሁም የምሁራኑ ደብዳቤ አይግለፀው እንጂ በምሁራኑ የተጠቀሰው የ1990 የዐማራ ክልል ጥናት በጎንደር ደም እንዳፋሰሰ መዘንጋት የለበትም። ስለኾነም ክልሉ ከተናጠላዊ ተግባራዊ እርምጃ እንዲታቀብ እማፀናለኹ።

መልስ- “ፍየል ወዲህ ቅምዝምዝ ወዲያ” እንደሚባለው አቶ ዳንኤል የማይገናኙ ሐሳቦችን ነው ለማገናኘት የሞከሩት። ስለቋንቋ ያወራሉ። ጥያቄው የቋንቋ የኦሮምኛ ጥያቄ አይደለም። ለአቶ ገዱ ባቀረብነው ጽሁፍ ኦሮምኛን በተመለከተ ያነሳናቸው ጉዳዮች የፊደል ጉዳይ ነው። በአማራ ክልል ኦሮሞኛ የሚሰጥ ከሆነ በግእዝ ፊደል እንዲሆን ነው የጠየቅነው። ጸሃፊው በቋንቋ ጥላቻ የታወሩ በመሆናቸው የጽሁፋችንን ርዕሱን እንኳን ማስተዋል የተሳናቸው መስለኝ።

አቶ ዳንኤል ስለወጋጎዳ ጠቅሰዋል። ወጋጎጎ (ወላይትኛ- ጋሞኛ- ጎፋኛ-ዳውሮኛ) አንድ ላይ በማድረግ ሕወሃት በደቡብ ኢትዮጵያ ለመፍጠር የሞከረው አዲስ ቋንቋ ነበር። ያኔ ወያኔ የሞከረው ቋንቋዎችን ለማጥፋት ነበር። አራቱን ቋንቋዎች አጥፍቶ አዲስ ቋንቋ ሊፈጥራላቸው ሲሞክር፣ ሕዝቡ ተቃውሞ አቀረበ። በአማርኛ ነው ልጆቻችን እንዲማሩ የምንፈለገው አለ። ሕዝቡ ሳይፈለግ የሚወሰን ውሳኔ ሁልጊዜ ችግር አለው።

በአሁኑ ወቅት ኦነጋዊያንና የኦሮሞ ብሄረተኞች በፌዴራል ደረጃ አፋን ኦሮሞ የስራ ቋንቋ እንዲህን ግፊት እያደረጉ ነው። በአዲስ አበባ አፋን ኦሮሞ በየትምህርት ቤቱ እንዲሰጥ ቀንና ለሊት እየደከሙ ሲሆን፣ በአማራ ክልል የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኦሮሞኛ ትምህርት ሊሰጥ ነው። በባህር ዳር የኦሮሞ ማእከል ሊገነባ ነው። ያ ሁሉ ሲደረግ ያለ ሕዝብ ፍላጎት በሕዝብ ላይ፣ ልክ ያኔ ወጋጎዳ በሕዝቡ ላይ ለመጫን እንደተሞከረ፣ አሁንም ላቲንን ያለ ሕዝብ ፍላጎት ለመጫን እየተሰራ መሆኑን ለአንድ አፍታ መዘንጋት የለብንም።

የአማራ ክልል ሆነ የአዲስ አበባ ሕዝብ ኦሮምኛን ይፈለጋል። ኦሮምኛ ጋር ምንም ችግር የለውም። ነገር ግን ላቲንን አይፈልግም። ከወጋጎዳ ጋር በተገናኘ የነበረው ችግር እንዳይከሰት ፍራቻ ካላቸው፣ አቶ ዳንኤል ያኔ የተከሰተው ችግር ዋና ምክንያቱ ከሕዝብ ፍቃድ ውጭ በሕዝቡ ላይ የሚወሰን ውሳኔ መሆኑን መረዳት አለባቸው። ላቲን ያለ ሕዝብ ፍላጎት በሕዝብ ላይ የተጫነ ነው። የአማራ ክልል መንግስት ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶበት የብዙሃኑን ፍላጎት እንዲያስተናገድ ነው ፍላጎታችን። በአማራ ክልል ሕዝብም ኦሮሞኛን መማር ከፈለገ በሚፈልገው ፌደል ነው መማር ያለበት። በአማራው ክልል በከሚሴ ኦሮሞኛ በላቲን ይሰጣል። የከሚሴ ሕዝብ ፈልጎ አይደለም። በግድ ነው ላቲን የተጫነበት። በመሆኑን ሕዝቡ ተጠይቆ የሕዝቡ ፍላጎት ከሆነ በግእዝ መማር መጀመሩ ተገቢ ነው።

አቶ ዳንኤል፣ በ1990 በአማራ ክልል ኦሮሞኛ ትምህርት እንዲሰጥ ጥናት ተደርጎ በነበረበት ወቅት በጎንደር ደም መፍሰስ እንደነበረ ገልጸዋል። ይህ ያልተጨበጠ መረጃ የለሽ አስተያየት ነው። በጎንደር ላለፉት 27 በተለያዩ ምክንያቶች ወያኔ የዜጎችን ደም አፍሷል። ሆኖም አንድ ጊዜ የጎንደር ሕዝብ ኦሮሞኛን ወይንም ትግሪኛን፣ ጉራጌኛ ተቃውሞ የወጣበት ጊዜ የለም። “የኦሮሞ ወንድሞቻችን ደም የኛም ደም ነው” ብሎ በአደባባይ የጮኸ ሕዝብ ኦሮሞኛ አልማርም ብሎ ይቃወማል ማለት የጎንደርን ሕዝብ መሳደብ ነው። በአገሩና በቅርሱ የሚኮራው፣ ለነጮች እጄን አሳልፌ አልሰጥም ያለው፣ የኢትዮጵያ አባት የመይሳው ልጆች ግን የሙሶሊኒን ፊደል ይቀበላሉ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው።

  1. አቶ ዳንኤል – በኢትዮጵያ የቋንቋ አጠቃቀም ጉዳይ ውስብስብ ስለኾነ፤ የቋንቋ አጠቃቀም የክልል የውስጥ ጉዳይ ብቻ ስላልኾነ፤ ጦማር የላኩትን ምሑራኑንም ሆነ ፕ/ት ግርማን አመስግነን፤ ኦሮምኛን በዐማራ ክልል ኾነ ሌላው የቋንቋን ጉዳይ፤ ያለንን ቸግር ለመፍታት ኾነ ወደፊት ለሚፈጠሩት በተጠና ሁኔታ መፍትሔ ለመስጠት የምንችለው በሐገራዊ እንቅስቃሴ ብቻ ነው።

መልስ – ፈረንጆች double standards ይሉታል። አንዱን በአንድ መለኪያ ሌላውን ደግሞ በሌላ መለኪያ መለካት ማለት ነው። የኦሮሚያ ክልል እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ አማርኛን አያስተምርም ነበር። አሁንም አማርኛ እንደ ትምህርት የሚሰጠው ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ ነው። በኦሮሚያ ውስጥ በርካታ ዞኖች አሉ አማርኛ ተናጋሪዎች በብዛት የሚኖሩባቸው። ሆኖም ግን የስራ ቋንቋ ኦሮምኛ ብቻ እንዲሆን ነው የተደረገው። የኦሮሚያ ክልል ይሄን ኦሮሞዎችን ብቻ የሚጠቅም አሰራር ሲዘረጋ ፣ የአማራ ክልል በክልሉ ያሉ ተማሪዎችን በምን መልኩ ማስተማር እንዳለበት በፌዴራል ክልል መወሰን አለበት ማለት የክልሉን መንግስት ስልጣን መጋፋት ነው።

ነገሮች በተጠና ሁኔታ መደረጋቸው ተገቢ ነው። ለዚህም ነው ስሜት ላይ ተመርኩዘን ሳይሆን መረጃ ላይ ተመርኩዘን ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረብነው። ኦሮሞኛ በግእዝ መጻፉ ከኢኮኖሚ አንጻር፣ ቋንቋውን ለመማር ካለው አመችነት አንጻር፣ የታሪክን ቅርስ ከማቆየት አንጻር፣ የአገርን አንድነት ከማጠናከር አንጻርና ከቴክኖሊጂና ከሳይንሳ አንጻር መረጃዎችን አስቀምጠናል። “አይ ላቲን ቢሆን ጥሩ ነው” የሚል መረጃዎችን አቅርቦ መከራከር ይቻላል። ማንም ዜጋ ከጥላቻ በጸዳ መልኩ ሀሳቡን ካቀረበ የማንሰማበት ምንም ምክንያት የለም። ሆኖም ግን “ላቲን ካልሆነ” የሚሉ ግልሰቦች ሂደው ሂደው የተቃውሟቸው ምንጭ ለኢትዮጵያ፣ ለግእዝ፣ ለአማርኛ ያላቸው ጥላቻ ነው። “በአማራ ክልል ኦሮሞኛ መሰጠት ከተጀመረ፣ በኦሮሚያም ሕዝቡ ያንን ይጠይቀናል፤ ላቲናችንም ይዳከማል” የሚል ፍርሃት አላቸው። ግን አንድ ያልተገነዘቡት ነገር ቢኖር፣ ላቲን ከቀጠለ ኦሮሞኛ የሚዳከም መሆኑን ነው። አንደኛ ከኦሮሚያ የተወሰኑ አካባቢዎች በስተቀር የመስፋፋት እድሉ በእጅጉ የመነመነ ነው። ሁለተኛ ይኸው ለ27 ላቲን በሃይል ተዘርግቶ እስቲ ምን ያህል ኦሮምኛ በሸገር፣ በአዳማ፣ በጂማ፣ በቢሾፍቱ ..አድጓል? የላቲን መቀጠል ለኦሮሞኛ መስፋፋት ትልቅ እንቅፋት ነው። በአንጻሩ ግን ኦሮሞኛ በግእዝ ከሆነ ኦሮምኛ በቀላሉ ይስፋፋል። ብዙ ሕዝብ ከኦሮሚያ ውጭ የማወቅ እድል ይኖረዋል። በኦሮሚያም ያሉ ሌሎች ማህበረሰባት ደስ ብላቸው ይማሩታል።

  1. አቶ ዳንኤል – ሐገራዊ እንቅስቃሴ ስል የቋንቋ ፖሊሲን የሚያሻሽል፤ የቋንቋ አጠቃቀም ዕቅድን የሚነድፍ፤ የቋንቋ አጠቃቀም ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌን የሚተነተን ነው።

መልስ – አቶ ዳንኤል የአገሪቷ ሕግ መንግስት ይቀየር የሚል ከሆነ አስተያየቱ ያ ሌላ አጀንዳ ነው። አሁን ባለው አሰራር የክልል የትምርህት ሆነ የቋንቋ ፖሊሲ ወሳኙ የክልል መንግስት ነው። በሃረሪ ክልል አደሪኛ ተናጋሪው 8%፣ አማርኛ ተናጋሪው 31%፣ ኦሮሞኛ ተናጋሪው 56% ሆኖ፣ በኦህዴዶችና በሃረሬ ሊግ ውሳኔ፣ የክልሉ መንግስት ነው አደርኛንና ኦሮሞኛን ብቻ የክልሉ የሥራ ቋንቋ አድርጎ፣ አማርኛን ግን የነፍጠኞች ቋንቋ በሚል የሥራ ቋንቋ እንዳይሆን ያደረገው። በትግራይ አማርኛ ትምህርት ሲሰጥ ለብዙ አመታት በኦሮሚያ አማርኛ ያልተሰጠው የክልል መንግስታት በወሰኑት ውሳኔ ነው።

  1. አቶ ዳንኤል – አኹን ባለው ኹኔታ ይህንን በዕውቀት፣ በተማከለ መንገድ አስፈፃሚ አካል የለም።

መልስ- በተለያዩ አገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ ጥናቶች የሚያቀርቡ ተቋማት በስፋት ቢኖሩ ጥሩ ነው። ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትም የሚያቀርቡትን ጥናቶች በመመለከት፣ ለህዝብ ይጠቅማል የሚሏቸው በፖሊሲ ደረጃ ውሳኔዎችን አስወስነው ተግባራዊ ሊያደርጓቸው ይችላሉ። ሃላፊነቱ ያለው እነርሱ ጋር ነው። “በተማከለ” መልኩ የተባለው አሁን የክልል መንግሥታትን ስልጣን የሚዳፈር ነው። የኦሮሚያ ክልል፣ የሃረሬ ክልል በተናጥል ውሳኔ እየወሰኑ የአማራ ክልል መንሥስት በክልሉ መሆን ስላለበት ለመወሰን የማእከላዊ መንግሥትን ውሳኔ መጠበቅ የለበትም። ሁሉም ክልሎች የዘረጉት የትምህርትና የቋንቋ ፖሊሲ በማእከል ይወሰን ከተባለ፣ ያ ሌላ አጀንዳ ነው የሚሆነው። ለአማራ ክልል ብቻ ሲሆን ግን ማእከላዊነትን መናገር ግን አግባብነት ያለው አይመስለኝም።

  1. አቶ ዳንኤል – ሐገሪቷ ክልሎችም ከአላስፈላጊ መጓተት አጓጉል ምክር ከመተግበር፣ ከአጓጉል ጥናት እንዲድኑ አሁን ባለቤት እና አቅም አልባውን የኢትዮጵያ የቋንቋዎች አካዳሚን (የኢትዮጵያ የቋንቋዎች ጥናት ማዕከልን) እንደ አስፈፃሚ አማካሪ አካል በሚኒስተር መስሪያ ቤት ደረጃ በአስቸኳይ አዋቅሮ መንቀሳቀስ ግድ ይላል።

መልስ- የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚ የተባለውም ሆነ ሌሎች በአገሪቱ በቋንቋና በትምህርት ዙሪያ አሉ የተባሉ ተቋማት አሉ ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ ነው። ካሉም ሥራቸውን እየሥሩ አይደለም ወይም ደካሞች ናቸው። እነዚህ ተቋማት ተጠናክረው ቢወጡና ፣ ለሕዝብ አካለው ጠቀሜታ አንጻር፣ የሕዝብን ፍላጎት ባንጸባረቀ መልኩ፣ ጥናቶችን ሪፖርቶቾን በማዘጋጀት ፖሊሲ አውጭዎች ውሳኔዎች በመመሪያ ወይም በፖለቲካ ውሳኔ ሳይሆን በመረጃ እንዲወስኑ ማስደረግ ቢችሉ ጥቅም ይኖረዋል። እኛ የምናቀርባቸው ሐሳቦች ይህን ዓይነት ሥራ የሚሠሩ ተቋማትን የሚያግዝ ነው የሚሆነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.