አፋኞች የሚፈሩት የታፈነ ድምፅ በዓለም አደባባዮች ሲደመጥ

አፈና በማናቸውም መልኩ በሰብዓውያን ላይ ሲፈፀም የፀያፍ ድርጊቶች ጊዜያዊ ማሰንበቻ እኩይ ተግባር ነው። ይህ ደሞ ለራሱ የመንግስትን ገጽታ በሰጠ ቡድን ሲከወን መጠኑ እጅግ ይከፋል፤ ይገዝፋልም

የሚገለፀውም በተለያዩ ዓይነቶች የግፍ መሥፈርቶች ነው። ግፎቹም ባለብዙ ፈርጆች በመሆናቸው የማይነኩት የኀብረተሰብ ክፍል የለም። በሚፈሩትና በፈቃደኝነት እጃቸውን በሰጡትም ላይ እየቆየ ሲሄድ ትንሽ ሲያንገረሰግሩም ሲፈፀም ይስተዋላል።

ይህ ፀያፍ ተግባር እንደቡድን በህወሓት እንደ አገር እና ሕዝብ ደገሞ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያን ላይ እተፈፀመ ነው። ” ፍርድ ቤት አለ! ግን ዳኛ የለም፣
ሕግ አለ ግን ፍትህ የለም፣
አፈና አለ ግን አስተዳደር የለም፣
የሚሉት የሕዝብ ጩኸቶች ብዛት በዓለም አደባባዮች በመላው የኢትዮጵያ ግፉአን ስም ዘረኛውን ህወሓትን እና የኅሊና ስንኩል ደንገጡሮቹን( ልጥፍ የጅ ሥራ ቡድኖችን እና ሆድ አደር ተውሳካትን ጨምሮ) በማውገዙ ላይ አተኩሮ እየተስተጋባ ይገኛል።

ትናንት ማርች 20 ቀን 2015 በስዊዘርላንድ የተባበሩት መንግሥታት ጽ/ ቤት ፊት ለፊት የተደረገው ከባድ የወገናዊነት ቁጣ የተስተጋባበት ፍትህ የሚሻ የኢትዮጵያውን ጩኸት ነበር።
ለድምፅ— የለሾቹ የአገር ቤት ኢትዮጵያውያን ታፋኞች የተሰማ ታላቅ የታማኞች አገራዊ እሪታ። የአገር ቤቱን የነፃነት ትግል ልክ በአሜሪካ በአውሮፖ በእስራኤል በአውስትራሊያ በኒውዚላንድ እንዲሁም በሌሎች አህጉራት የሚደረገውን የነፃነት ትግል የድርሻ ቅብብል ተከታታይነት የነቀሰ የማያቋርጥ ትግል።

ህወሓት የዘራው የወያኔ የትግሬ ብሔረተኝነት ካልቆመ፣ በምትኩም ሁሉም ዜጋ ለኢትዮጵያዊነት ቤቱ የነፃነትና የፍትህ እሪታውን አንድ ላይ ካላሰማ በህወሓት ቅያስ ወደ ጥፋት መንጎዳችን ከሰልፉም በኋላ አስተውሎት በውይይት የተወሰደበትነበር።

ወያኔ መጀመሪያ እያጠፋቸው የመጣው የራሴ ናቸው እያለ የሚሰብክላቸውን ኢትዮጵያዊ የትግራይ ታጋዮችን መሆኑ የሚያሳየው ወያኔ ለጥቅም እና ለጥፋት የቆመ ትግራይን እንደምሽግ መጠቀሚያ ማድረጉን ሰልፉ በስፋት አንስቶ በዚህ ከአፈናና ከግፍ ሥርዓት ለመላቀቅ በሚደረገው ትግል የትግራዊ ልጆች ትግሉን በቁርጥ እንደወጡት እንደነ አብረሃ ደስታ እንዲቀላቀሉ አሳስቧል።

ከሰልፉም በኋላ የትግራይ አካባቢ ልጆች ወያኔ ሲወገዝ ትግሬ ተወገዘ ማለት ትተው ከትግሬ ተወልዶ በገዛ አገሩ ላይ ግፍ የፈፀመ ትግሬን የማይወክል ዘረኛ ቡድን ተወገዘ ብለው አደባባይ በግልፅ እንዲወጡ ከኢትዮጵያዊነት ጋር በግልፅ እንዲወግኑ ጥሪ አሰምቷል። ግፍን ከአማራ የወጣ ቢፈፅም ይወገዛል፤ ከኦሮሞ፣ ከደቡብ፣ ከአፋር የወጣም ቢያደርገው ይወገዛል። በዓለም ላይ የሚፈፀም ግፍ እንደሚወገዝ ሁሉ።

ከትግራይ በመወለድ ምክንያት ብቻ በአንድ ጥቂት ግፈኛ የትግሬ ቡድን የሚፈፀመውን ግፍ አለማውገዝ ቀጥተኛ ትርጉሙ የዘረኛን ወያኔ የእይታው እንሽውርርና የአስተሳሰቡ የዘረኝነት ብክለት ተካፋይነት እንጂ ትግራይን ስላለመወከሉ ተወስቷል።

ዘመቻው በትግሬነት ላይ ሳይሆን በወያኔነት እና አገር በሚያሻሽጡ ኩልኩል የየክልሉ የወያኔ ሎሌዎች ላይ ነው። ይህንን የፍትህ መሻት ትግል በፀረ— ትግሬነት መፈረጅ ህወሓት የሚያነሳው አዋራ ነው በሚሉ ነጥቦች ዙሪያ የሀሳቦች መንሸራሸር መደረጉ የአይቀሬው ነፃነታችን ምልክት ነው።

የሙስሊም እህቶቻችን እና ወንድሞቻችን የአገር ፍቅር ስሜት፣ የተስተዋለው የእምነት ነፃነት ቁጭትና የአብሮነት ስሜት የወያኔን በሃይማኖት ከፋፍሎ መግዛትን ቀፎነት በሠልፉ አስደምሞናል።

ሠልፉ በግፍ በአፈናው አገዛዝ የተሰውና የታሠሩ የፍትህ ልጆች እንዳይዘከሩ በዘረኞች የሚሸረበውን ገመድ በጥሶ በአደባባይ ለሞቱት ሰማዕታት በወህኒ እና በማሰቃያ ጣቢያዎች የሰቆቃው እንግልት ለሆኑት በአንዲት ሙስሊም እህታችን አሳሳቢነት የኅሊና ፀሎት መፈፀሙ ያቆራኘን ኢትዮጵያዊነት በምንም ዓይነት በከፋፋዮች ሴራ አይበጠሴነቱን መስክሮልናል።

በአገራችን ሕዝባችን በእግሩ ቆሞ እንዳይሄድ መደረጉን ሠልፈኛው በሙሉ ተንበርክኮ በመሄድ መኪና መተላለፍያ መንገዶችን በመዝጋት ኃያል ቁጣውን ለዓለም መገናኛ ብዙኃን ማጋለጡ ድንቅ የሚያስብል የአፈናን መግላሊት በዓለም አደባባዮች ላይ ማጋለጥ ለኢትዮጵያዊነት ሲባል አፈናን አሸቀንጥሮ የመጣል ቀጣይ ጉዞ ሆኗል።

መነሳሳቱ በተለይ በወጣቱ በኩል መታየቱ ተስፋችንን ብሩህ እያረገው ነው። ከምንም በላይ የሴቶች ፀንተው ለነፃነቱ ትግል በቁጭትና በጥበብ መነሳታቸው በሁሉም መልክ የጉዞውን ሥልት አመላካች ሆኗል።

የስዊዘርላንዱን በተምሳሌት አነሳሁ እንጂ በየክፍለ ዓለማቱ ጥራትን ዋቢ ባደረገ እንቅስቃሴ የተጨበጠው ተስፋ አቋዳሽ ውጤቶች ሁሉ አካሄዳቸው የዚሁ የአብሮነቱ ጥያቄ ተመጋጋቢ ኩነቶች ሆነዋል።።

በውይይቶቹም ሚዛን የሚያነሳ መልዕክት በትግሉ ተጠናክሮ መቀጠል ዙሪያ የተደመጠው የፍትህ ፍለጋው ጉዞ መንገዱ በአፈና ሥር የማይቀር የነፃነት ማብሰሪያ ቀዳሚ ብሥረት ሆኗል።

አፈና ሲከፋ አፋኙን የሚበላ ክስተት ስለመሆኑ የማይገባቸው ጉዶች የሚማሩበት መንገድ በነፃት ታጋዮች ዕውን በቅርቡ ይሆናል።

UNHCR( የተባበሩት መንግሥታት የየሰበዓዊ መብት ኮሚሽን፣) RCS (የዓለም ቀይ መስቀል ማኅበር) እና HRC( የሰበዓዊ መብት ምክር ቤት) ተወካዮች ለሠልፈኛው ተወካዮች የሰጡት መልስና ያደረጉትም ውይይት የዚሁ አፈናን በሕዝባዊ ትግል ድል የማድረግ የነፃነት ንቅናቄ ሆኗል። እንበርታ፤ በሚያስማማን አገራዊ ጉዳይ አናመንታ፤ ግባችን ነፃነት ጥማታችን ፍትህ ናፍቆታችን ዴሞክራሲ ነው።

ምስጋና ለሕዝባችን፣ ምስጋና ለአሰተባባሪዎቹ፣

አትዮጵያን እግዚአብሔር ይታደጋት!!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.